እምቢኝ ለማተቤ - እምቢኝ ላገር ብሎ ፤
ሚስትና ልጆቹን - እርግፍ አርጎ ጥሎ፤
እርሻው አይታረስ! - አረም ይብላው ብሎ፤
አረም እንዳይበቅል - ባድዋ ተራራ፤
በጎራዴው አርሶ - ጥይቱን የዘራ፤
ጭንቅላት የቀላው - በጩቤ በካራ፤
ድሉን ያደመቀው - በጀግና ፉከራ፤
አልነበረም እንዴ - መላው ድፍን ሃገር?
አድዋ ተናገር!!
በማተብህ ጽና_ ለህሊናህ እደር፡፡
ከሰሜን ከደቡብ - ርቀት ሳይገድበው፤
ከምዕራብ ከምስራቅ - ጠሃዩ ሳይገታው፤
ሆ! ብሎ የወጣው - ላንተ የሞተልህ፤
ሞቱን ባንተ ሽሮ - ድል ያጎናፀፈህ፤
አልነበረም እንዴ መላው ድፍን አገር ?!
አድዋ ተናገር!!
ቃልኪዳን አትፋቅ ማ’ተብ አትበጥስ፤
በደም የተጣፈ ታሪክ አትከልስ፡፡
አድዋ ተናገር! - ማነው የሞተልህ?
ማንስ አስደፍሮ - ማንስ ዘብ ቆመልህ?
ስጋውን አጥንቱን - ማን ከሰከሰልህ?
ሞቱን ባንተ ሽሮ ድል አጎናፀፈህ?!
አድዋ ተናገር - ምንድነው ዝምታው?
ድንበር ያስከበረው - ደሙን ያፈሰሰው?
አንድ ጎሣ ነበር - ላንተ ሲል የሞተው?
ወይስ መላው ሃገር?!
ሲዳሞና_ ሐረር፤
ወለጋና_ ጎንደር፤
ሸዋና_ ወሎየው፤
አሩሲው_ ጎጃሜው፤
ኢሉባቦር_ ከፋው፤
ባሌ_ ጋሞጎፋው
ኤርትራና_ ትግሬው፤
አልነበረም እንዴ - ላንተ ሲል የሞተው?!
በዘር ሳይታጠር - ሃይማኖት ሳይፈታው፣
ጥቅም ሳይደልለው- ድህነት ሳይረታው፡፡
አሁን ዘመን ከፍቶ - አገር ተበትኖ፤
በዘር በሃይማኖት - ጎሣ ተሸንሽኖ፤
አገር እበት ወልዳ - ትል ደሟን ሲጠባ፤
በባንዳ ታጅቦ - ጠላት ቤት ሲገባ፤
አድዋ የኛ ነው! - ላንተ ምንህም ነው!
ይሉን ጀምረዋል - ጥንቱን እያወቅነው፤
አድዋ ያለ እናቱ፤
አድዋ ያለ ኢትዮጵያ የሙት ልጅ ባንዳ ነው፡፡
አድዋ ተናገር!!
ቃልኪዳን አትፋቅ - ማ’ተብ አትበጥስ፤
በደም የተጣፈ - ታሪክ አትከልስ፤
ኧረ ለመሆኑ - ማነው የሞተልህ?!!
ማነው የቆሰለው - ማነው የደማልህ?
አጥንቱን ከስክሶ - ድል ያጎናፀፈህ?!
ቼ!! ብሎ በመትመም - ነጋሪት የመታው፤
አንቢልታውን ነፍቶ - ፎክሮ የወጣው፤
ጎራዴውን መዞ - ጦሩን የሰበቀው፤
አንተ እንዳትደፈር - ቃል ኪዳን የገባው፤
ላንተ የሞተልህ - ላንተ የተሰዋው፣
መላው ኢትዮጵያዊ - ድፍን ሃገሩ ነው?
ወይስ አንድ ጎሣ - ብቻውን ትግሬ ነው??
አድዋ ተናገር!!
ቃልኪዳን አትፋቅ - ማ’ተብ አትበጥስ፤
በደም የተጣፈ - ታሪክ አትከልስ፤
ኧረ ለመሆኑ - ማነው የሞተልህ?!!
ማነው የቆሰለው - ማነው የደማልህ?
አጥንቱን ከስክሶ - ድል ያጎናፀፈህ?!
በህይወቴ እያለሁ - ጠላት አይደፍርህም፤
ጣሊያን ባንተ ጉያ - አይውልም አያድርም፤
ፋሺስት ባንተ መንደር - አይምነሸነሽም፤
ብሎ የተመመው - ላንተ ሊሞትልህ፤
ላንተ የቆሰለው - ላንተ የደማልህ፤
አርነት ያወጀው - ድል ያጎናጸፈህ፤
ኧረ ለመሆኑ - አንድ ጎሣ ነበር ?!
ወይንስ ጦብያ መላው ድፍን አገር ::
አድዋ ተናገር!
በቃል ኪዳና ጽና - ለማ’ተብህ እደር፤
በደም የተጣፈ - ታሪክ አትሸርሽር፤
እንዲህ እንደዛሬው !
ጥላቻን አንግቦ - በዘር ሳይታጠር፤
ላንተ የሞተልህ - መላው ጦቢያ ነበር::
አንድ ቀን
https://amharic-zehabesha.com/archives/180083
No comments:
Post a Comment