Tuesday, August 16, 2022

ሸኖ፣ አሌልቱ፣ ቤኪ፣ ሰንዳፋና ለገጣፎ - ከመርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ
ከዚህ በላይ በስም የጠራኋቸው አነስተኛና መካከለኛ ከተሞች የግልም ሆነ የህዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪዎችና ተሽከርካሪዎች ከዎልድያ፣ ከደሴም ሆነ ከሰቆጣ በሸዋ-ሮቢት፣ በደብረ-ሲናና በደብረ-ብርሃን በኩል አድርገው ወደሀገሪቱ ርእሰ-ከተማ፣ አዲስ አበባ መናህሪያዎች ለመግባት በየእለቱ የሚንደረደሩባቸው የኦሮምያ ክልል ከተሞች ናቸው፡፡ሆኖም ይህ የየብስ ትራንስፖርት በለየለት የውንብድና ስራ ላይ በተሰማሩ የኦሮምያ ጸጥታ ሀይሎች ያለአግባብ መስተጓጎልና አልፏልፎም ጭራሹን መቋረጥ ከጀመረ ትንሽ ሰነባብቷል፡፡

ለቁጥር የበዙ የዚያን መስመር መንገደኞች በተለያዩ ጊዜያት ካነጋገሩ የሀገር ውስጥና የውጭ መገናኛ-ብዙኃን በግርድፉም ቢሆን ለመረዳት እንደተቻለው እየሆነ ያለውና የሚሰማው አስነዋሪ ነገር ሁሉ ፍጹም ለጀሮ ይቀፋል፡፡

ህዝባዊ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብለው ከፍተኛ እምነት የተጣለባቸው የጸጥታ ሀይሎች ከፍ ሲል የተጠቀሱትን ከተሞች መነሻ አድርገው በተቋቋሙት የፍተሻ ኬላዎች ተሽከርካሪዎችን በሀይል እያስቆሙ ያሳፈሯቸውን ሠላማዊ ተጓዦች በፍተሻ ስም ያስወርዳሉ፣ የነዋሪነት መታወቂያዎቻቼውን እየጠየቁ ይሰበስባሉ፣ የአማራ ብሔር ተወላጆችን ለይተው ያለሀፍረትና ያለይሉኝታ ወደመጡበት እንዲመለሱ ያስገድዳሉ፣ ይልቁንም አሽከርካሪዎችን ለምን ጫናችኋቸው በማለት ያሸማቅቃሉ፣ ያንገላታሉ የትራፊክ ፖሊስ አባሎቻቸውን በመሳሪያነት እየተጠቀሙ ያለአግባብ በገንዘብ ይቀጣሉ፣ ሲያሻቸውም በአደባባይ ጉቦ እየተቀበሉ አንዳንዶቻቸውን በሙሰኝነት ያሳልፋሉ፡፡

በሂደቱ ተመላላሽ ህሙማን ሀኪም በያዘላቸው ቀጠሮ መሰረት ወደሆስፒታል በወቅቱu እንዳይደርሱ በመከልከላቸው የቁም ሞት ተፈርዶባቸዋል፡፡ የውጭ በረራ የተስተጓጎለባቸው ወገኖችም እንዳሉ ተወስቷል፡፡

ከመካከላቸው ሰብኣዊ ክብርን በሚጋፋ አኳኋን ብሔራዊ ማንነታቸው እየተጠቀሰ ያለአግባብ የሚዘለፉና በድብደባ ምክንያት አካላዊ ጥቃት የሚደርስባቸው እናቶችና ህጻናት እንደሚገኙባቸውም ሮሮዎች በስፋት ተስተጋብተዋል፣ አሁንም ድረስ እየተስተጋቡ ነው፡፡

እዚህ ላይ ታዲያ ይበልጥ የሚገርመው፣ እንደኮሶ የሚያንገሸግሸውና ክፉኛ የሚያመው ይህ ሁሉ በደል ከሳምንታት ለበለጠ ጊዜ በገሃድና በማናለብኝነት በወገኖቻችን ላይ ሲፈጸም የአውራ ጎዳናው ባለቤት ነኝ ከሚለው ከፌደራሉ መንግሥት አንስቶ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ክልሎች በኩል እየተሰጠ ያለው ምላሽ በጣም ቀዝቃዛና ታዲያ ምን ይጠበስ? የሚል አይነት ሆኖ መታዘባችን ነው፡፡

ለምሳሌ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በጉዳዩ የሚያገባው እንደሌለ ሁሉ እንዲህ ያለውን ከረር ያለ ስሞታ ቢያዳምጥም ጀሮ ዳባ ልበስ እንዳለ ነው፡፡

የፌደራሉ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ ነኝ ያሉ አንዲት ሴት ደግሞ ስለጉዳዩ የበኩላቸውን ማብራሪያ እንዲሰጡ ያን ሰሞን በአንድ የውጭ ሚዲያ ተጠይቀው ነበር፡፡ የፈረደባቸው ኦ.ነ.ግ ሸኔና ህ.ወ.ሀ.ት ድህረ-ወረራ ያሰማሯቸው አሸባሪዎች በተጭበረበረ የመታወቂያ ወረቀት ወደመዲናዋ ሰርገው ወይም ተሹለክልከው እንዳይገቡ ለመከላከል በታቀደ እርምጃ ጥብቅ ፍተሻ እየተካሄደ እንደሆነ እናውቃለን ሲሉ ኀላፊነት የጎደለው የግብር ይውጣ ምላሽ በመስጠት አድራጎቱን ከመኮነን ይልቅ ያልተገባ ኦፊሴላዊ ሽፋን ሲያላብሱት ተደምጠዋል፡፡

ከንዲህ አይነቱ መንግሥታዊ ሥልጣን የሚመነጨው ኩርማን እንጀራ ሳይበላ ቢቀር ምን አለበት ጎበዝ?

የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት የሲቪልና የፀጥታ ባለሥልጣናትማ ስለጉዳዩ አንዳች እውቀት እንደሌላቸው ነበር ደጋግመው የነገሩን፡፡

ለነገሩ ውሉ ጨርሶ ከጠፋባቸው ከኒያ ሴቲዮ እነርሱ ሳይሻሉ አልቀሩም፡፡

ተሳፋሪዎቹ የሚነሱበት የአማራ ክልልም ቢሆን አፍጥጦ ለወጣውና አሁንም ድረስ ሃይ ባይ ሳያገኝ ተጠናክሮ ለቀጠለው ለዚህ ችግር መፍትሄውን በዋነኝነት እየጠበቀ ያለው በበደሉ አድራሽነት ከሚወቀሰው ከኦሮምያ ክልል የስራ ኀላፊዎች በመሆኑ ያው እንደተለመደው የምንትስ ባል ከምንትስ አያስጥልም አስብሎታል፡፡

ይህ የዘፈቀደ እርምጃ ከገዢው የብልጽግና ፓርቲ የኦሮምያ ክንፍ አኳያ ሲታይ ወደአዲስ አበባ ድርሽ እንዳትል  ብንለው አማራ ምን ሊያመጣ ይችላል? እየተባለ ያለ ነው የሚመስለው፡፡

በርግጥ ለጊዜው ምንም ያመጣው የለም ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ግን ለወደፊቱ ምንም የሚያስከትለው መዘዝ አይኖርም ማለት እንዳልሆነ ከወዲሁ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ለመሆኑ ግኡዙና ዳፍንታሙ ሕገ-መንግሥታችን እንዲህ ያለውን አፓርታይድ-መራሽ እርምጃ በተመለከተ ምን ይላል?

እንደኔ ባሉት ጦማርያን አማካኝነት ለአካዳሚያዊ ፍጆታ ብቻ የሚያገለግል በሚመስል መልኩ አሸብርቆ በዋቢነት ከመጠቀስ ባለፈ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ገቢራዊ ለመደረግ ያልታደለው የኢ.ፌ.ደ.ሪ ሕገ-መንግሥት በአንቀጽ 32 ንኡስ አንቀጽ (1) ድንጋጌ ስር አይደለም የዜጎችን፣ በሀገሪቱ የግዛት ወሰን በሕጋዊ መንገድ የሚኖሩ ባእዳንን የእንቅስቃሴ መብትና የመኖሪያ ስፍራ ምርጫ ነጻነት ያከብራል፣ ለዚህም በሰነድ የተረጋገጠ ዋስትና ይሰጣል፡፡

ዳሩ ይህ ፍሬቢስና አማላይ ቃለ-ሕገ-መንግሥት ብቻውን ምን ይረባናል?

የተጻፈ ሕግ በስማችን ስለተጻፈ ብቻ ህይወት አይኖረውም፡፡ አበው አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም! የሚሉት ለዚህ ነው፡፡

ውድ ወገኖቼ፣ ቁልፉ የሀገራችን ችግር እኮ ለተራዘመ ጊዜ ተንሰራፍቶ የቆየው የተጠያቂነት አለመኖር ባህል ወይም ክፉ ልማድ እንጂ ነው፡፡

እስካሁን ድረስ እንግዲህ ከነዚህ ቀማኛና ወስላታ የጸጥታ ሀይሎች መካከል አንዳቸውስ እንኳ በሕግ ተይዞ ሥልጣንን አለአግባብ በመገልገል ወንጀል የተጠየቀ ስለመሆኑ ያወቅነው ነገር የለም፡፡

ነገሩ ሚስትህ ወለደች ወይ ቢሉት ማንን ወንድ ብላ እንዳለው አባ-ወራ መሆኑ ነው፡፡

ለመሆኑ መንግሥት ሸኔ እያለ በዳቦ ስም የሚጠራው የዎለጋው አሸባሪ ቡድን ታጣቂዎች በሕግ ማስከበር ጥላ ስር ተከልለው በ1ኛው የአዲስ አበባ መግቢያ በር ላይ ለጥፋት የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ወሮበሎች ከሚፈጽሙት የከፋ ምን በደል አድርሰው ነው የማያቋርጥ የውግዘት ናዳ የሚወርድባቸውና በየደረሱበት የሚሳደዱት?

ለማናቸውም ፈጣሪ በኪነ-ጥበቡ ቶሎ ወደቀልባችን እንድንመለስ ካልረዳን በስተቀር የጀመርነው እርስበርስ የመገፋፋት መጥፎ ልምምድ ፍጹም አደገኛና ዳፋውም ለትውልድ የሚተርፍ በመሆኑ አስተውለን መራመድ ይኖርብናል፡፡ እድሉ ስለተመቻቸልን ብቻ ዛሬ በገፍ የምንወስደው ግዙፍ የመከራ ብድር ለነገ የምንከፍለውን እዳ እንዳያከብደው መጠንቀቅ አለብን፡፡

አስፍተን ካየነው ተረኝነት የኑሮ ሕግ ነው፡፡ የዛሬ አጥቂ የነገ ተጠቂ የመሆን እድል አለው፡፡ ስለሆነም ይህንኑ እውነታ ከወዲሁ ተረድተን በኀላፊነት ከሚያስጠይቁ አስነዋሪ ድርጊቶች ብንታቀብ እላለሁ፡፡
https://amharic-zehabesha.com/archives/176600

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...