Tuesday, August 16, 2022

አቶ ገለታው ዘለቀ በኢትዮ 360 ላይ ተጋብዞ ስርዓታዊ ሽብር በሚለው አርዕስት ላይ በኤርምያስ ለገሰ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ለሰጣቸው መልሶች ትችታዊ አስተያየት!
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

ነሐሴ 16፣ 2022

በመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያ ብቻ ነች ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ስትነፃፀር የተጠናቀቀ የመንግስት መኪና አወቃቀር(State Building) የነበራት አገር የሚለው በመሰረቱ አከራካሪ መልስ ነው። እንደሚታወቀው አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች በባሪያ ንግድና በቅኝ-ግዛት አስተዳደር ምክንያት የተነሳ የነበራቸውን የማህበረሰብ አወቃቀር፣ ለምሳሌ የነበራቸው የስራ-ክፍፍል፣ የገበያ ተቋማትና፣ እንዲሁም የህዝቡ የእርስ በርስ ግኑኝነት፣ ህዝቡን ያስተሳስሩ የነበሩ ልዩ ልዩ ባህላዊ ግንኙነቶችና ተቋማት እንዳሉ ሊደመሰሱ ችለዋል። በተለይም በባርያ ንግድ አማካይነት የተነሳ በጊዜው ስሌት ወደ አርባ ሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ወደ አውሮፓና ወደ ላቲን አሜሪካ አገሮች ሲሸጡ፣ በዚያው መጠንም እስከዚያን ጊዜ ድረስ ዳብረው የነበሩ ልዩ ልዩ ማህበራዊ ግኑኝነቶችና የአመራረት ዘዴዎች ሊወድሙ ችለዋል። በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ደግሞ የተለያዩ የአውሮፓ አገሮች አፍሪካን ቅኝ-ግዛት ሲያደርጉ፣ ጥቁር አፍሪካውያን ገበሬዎች እስከዚያን ጊዜ ድረስ የነበራቸውን የአስተራረስ ዘዴ እንዲተው በማስገደድ ለአውሮፓ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ብቻ እንዲያርሱ ተደረጉ።  በሁለቱ ምክንያቶች የተነሳ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች እስከዚያን ጊዜ ድረስ የነበራቸው የመንግስት አወቃቀርና ኢቮሉሺናራዊ ዕድገት ሊጨናገፍ ቻለ።  ከዚህም በላይ በቅኝ ገዢዎች በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ የዕደ ጥበብ ስራዎች፣ ከዲንጋይና ከእንጨት፣ እንዲሁም ከነሃስ የተሰሩ ቅርሳ ቅርሶች እየተዘረፉ ወደ አውሮፓ በመጓዝ አጠቃላዩ የህብረተሰብ አወቃቀር ሊበላሽባቸው ቻለ። እንደሚገመተው ከሆነ በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ከአፍሪካ ተዘርፈው የመጡ ቅርሳ ቅርሶች በአውሮፓና በአሜሪካ ትላልቅ ሙዜየሞች ውስጥ እንደሚገኙ ነው። ከዚህ ስንነሳ አቶ ገለታው ዘለቀ የሌሎች አፍሪካን አገሮች የመንግስትና የአገር ግንባታ ሂደት ዝቅ አድርጎ ማየቱ ትክክል አይደለም። በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የደረሰው በደል በኢትዮጵያ ላይ በፍጹም አልደረሰም ማለት ይቻላል።

ወደ አገራችን ስንመጣ አገራችን ከውጭ የመጣባትን ወራሪ ኃይል  በተደጋጋሚ መክታ ለመመለስ ብትችልም፣ በጊዜው በነበረው ዝቅተኛ የምሁራዊ እንቅስቃሴ ምክንያት የተነሳና፣ ከውጭው ዓለም ጋር የነበረው ግኑኝነትም በጣም የላላ ወይም የተዘጋ ስለነበር ዘመናዊ የሆነና የተስተካከለ ዕድገትን ሊያመጣ የሚችል የመንግስት አወቃቀር ሊመሰረት በፍጹም አልተቻለም። አፄ ኃይለስላሴ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት የነበረውን የመንግስት መኪናን ሁኔታ  ስንመለከት ለአንድ አገር ግንባታ የሚያስፈልጉ ቢሮክራሲያዊና ህዝባዊ ተቋማት ይጎድሉ ነበር። አብዛኛው ህዝብ በገጠር ውስጥ ይኖር ስለነበርና፣  የዕደ-ጥበብ ስራዎችንና የእርሻ ምርት ውጤቶችን ወደ ገበያ እያመጡ የሚሸጡበት ሁኔታ ባለመኖሩ፣ ወይም ደግሞ የገበያ ተቋም ባለመዳበሩ የተነሳ ህዝቡን የሚያስተሳስረው ምንም ዐይነት ማህበራዊ ግኑኝነት አልነበረም። አፄ ኃይለስላሴ ስልጣን ከያዙ በኋላ፣ በተለይም ደግሞ ከስደት ከተመለሱ በኋላ ዘመናዊ ቢሮክራሲ፣ ማለትም የሚሊታሪ፣ የፀጥታ፣ የሲቪልና አንዳንድ ተቋማትን በተለይም በአዲስ አበባ ውስጥ ለማቋቋም ቢችሉም ወደ ሌሎች ክፍለ-ሀገሮችና ወደ ወረዳዎች ዝቅ እያልን ስንሄድ ዘመናዊ ቢሮክራሲ የሚባል ነገር በፍጹም አይታወቅም ነበር። ዘመናዊና የሰለጠነ ቢሮክራሲ በአገር አቀፍ ደረጃ ካልተዋቀረ ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ የጥሬ-ሀብቶችንና የሰው ኃይልን ማንቀሳቀስና ለአገር ግንባታ    ማዋል በፍጹም አይቻልም። በአጠቃላይ ሲታይ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የነበረው የመንግስት መኪና ዘመናዊና ባህላዊ በመባል የሚገለጽ ነበር።

ዘመናዊ የሚባለው የመንግስት መኪናን ስንመለከት ደግሞ አስተሳሰቡ እንዳለ ከውጭ የተቀዳ ወይም የተወሰደ ነው። የሚሊታሪው፣ የፀጥታውና የፖሊሱ ተቋማትና ሰዎች  በውጭ ኃይሎች የሰለጠኑ ሲሆኑ፣ የሲቭል ቢሮክራሲውም ውጭ ሰልጥኖ የመጣ ነው።  ይህም ማለት በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የተመሰረተው የመንግስት መኪና ከውስጥ ኦርጋኒካሊ ከታች ወደ ላይ በዕውቅ በቲዎሪና በሳይንስ እየተመረመረ ከተሟላ ህብረተሰብአዊ ግንባታ ጋር በመያያዝ የተቋቋመ ሳይሆን ከውጭ የተኮረጀና በተለይም በጊዜው የነበረውን የኃይል አሰላለፍ የሚጠብቅና የሚደግፍ ነበር። በሌላ አነጋገር፣ በጊዜው ሰፍኖ የነበረውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግኑኝነት የሚከላከልና የአገዛዙን ጥቅም የሚያስጠብቅ እንጂ ህዝባዊ ባህርይ የነበረው አልነበረም። በአፄ ኃይለስላሴ አገዛዝ ዘመን ተግባራዊ የሆነው  የኢኮኖሚ ፖሊሲንም ስንመለከት እንደዚሁ ከውጭ የመጣ አስተሳሰብ ነው። ስለሆነም ከውጭ የመጣውና በደንብ ሳይመረመር ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ያልተስተካከለ ዕድገት እንዲፈጠር ለማድረግ በቅቷል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ነው በጊዜው የነበረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መፍታት ያልተቻለው። ምክንያቱም የተተከሉት ኢንዱስትሪዎች በሙሉ ከውጭ የመጡና የተቋቋሙ ሲሆን፣ የሚመረቱትም ምርቶች የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል የፍጆታ ፍላጎት ለማርካት የታቀዱ ብቻ ናቸው። ይህም ማለት የሰፊውን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶች ሊያሟሉ የማይችሉና፣ በተለይም ደግሞ ለእርሻው መስክ አስፈላጊውን የማረሻ መሳሪያዎች እያመረቱ ሊያቀርቡ የሚችሉ አልነበሩም። ስለሆነም ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነው ገበሬ የእርሻ ተግባሩን የሚያካሂደውና ሰፊውን ህዝብ የሚመግበው በበሬና በማረሻ ብቻ እየታገዘ ነበር።  በዚህ መልክ የሚካሄደው የእርሻ ምርት ክንውን ምርታማነቱ በጣም ዝቅተኛ ነበር። ለምሳሌ በ1973 ዓ.ም የተከሰተው ረሃብ አፄ ኃይለስላሴና አገዛዛቸው በተለይም በእርሻው ላይ አትኩሮ ባለመስጠታቸውና፣ በቁጥር እየጨመረ የመጣውን ህዝብ ሊያስተናግድ የሚችል የኢኮኖሚ ስርዓት መገንባት ባለመቻላቸው ነው። ስለሆነም ያልተገለጸለትና በራሱ ዓለም የሚኖረው የፊዩዳል አሪስቶክራሲው መደብና ሚኒስተሮችም ጭምር ኢትዮጵያን እንደ አገርና እንደማህበረሰብ ከታች ወደ ላይ በሁሉም አቅጣጫ የመገንባት ኃይል አልነበረቻውም። በመሀከላቸውም ስለወደፊቱ የአገራችንና የህዝባችን ዕድል ውይይትና ክርክር ስለማይካሄድ ተግባራዊ የሚሆኑት ፖሊሲዎች በሙሉ በግብታዊነት ብቻ ነበር። ስርዓቱም እንዳለ ለፖለቲካ ክርክርና ለሳይንሳዊ ምርምር የሚያመች ሳይሆን፣ ይበልጥ ፊዩዳላዊ አስተሳሰብ የሚንጸባረቅበት ወይም ደግሞ እጅ እየነሱና እየሰገዱ የሚኖርበት ነበር ማለት ይቻላል።

የአውሮፓውን ዕድገት ስንመለከት ግን የሄዱበት መንገድ የተለየ ሲሆን፣ የመንግስት መኪናና የህብረተሰብ ግንባታ በቲዎሪና በሳይንስ የተደገፉ ናቸው ማለት ይቻላል። የዕውቀትን አመነጫጨት ተከታትለን ከሆነ በግለሰብ ደረጃ የተፈጠሩና የዳበሩ ሲሆን፣ አብዛኛዎች የምዕራብ አውሮፓ ነገስታት ወደ አንድ መንግስትነትና ወደ አንድ ስርዓት ከመሸጋገራቸው በፊት በየአካባቢዎቻቸው ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎችንና ቤተ-መጻህፍቶችን ያቋቋሙ ነበር። አንደኛው የአውሮፓ አገር ከሌላው ይኮርጅ ስለነበረና፣ በምሁራንም ዘንድ የዕውቀት ሽግግር ስለነበር  ለዕድገት የሚያመች መንግስታዊ መዋቅርንና አገርን ለመገንባት አስቸጋሪ አልነበረም። ይሁንና በአውሮፓ ውስጥ አገሮች እንደ አገር ከመገንባታቸው በፊት በእያንዳንዱ አገር ውስጥም ሆነ በአገሮች መሀከል ከፍተኛ ጦርነት ይካሄድ ነበር። የመቶ ዓመት ጦርነት፣ የስላሳ ዓመት ጦርነት፣ የሰባት ዓመት ጦርነት፣ እንዲሁም የአንደኛውና የሁለተኛው ዓለም ጦርነቶች በአውሮፓ ምድር ውስጥ  የተካሄዱ ሲሆን፣ ቀደም ብሎ በእንግሊዝ አገር በ17ኛው ክፍለ-ዘመን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ዕድገትን በሚፈልጉና የሊበራል አስተሳሰብ ባላቸው በአንድ በኩልና፣ በሌላ ወግን ደግሞ የድሮው ስርዓት እንዳለ እንዲቀጥል በሚፈልጉ ኮንሰርቫቲብ አስተሳሰብ ባላቸው መሀከል 20 ዓመት የፈጀ የእርስ በርስ ጦርነት ተካሂዷል። ከዚያም በኋላ ነው የከበርቴው መደብ በማሸነፍ ቀስ በቀስ ለኢንዱስትሪ አብዮት መሰረት ለመጣል የቻለው። ይሁንና ግን በአውሮፓ ውስጥ አነሰም በዛም የተሟላ ሰላም ሊሰፍን የቻለው ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ነው ማለት ይቻላል። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በመንግስት ጣልቃ-ገብነትና ድጋፍ ነው የምዕራብ አውሮፓ ኢኮኖሚዎች ከደቀቁበት ሊያገግሙ የቻሉትና ካፒታሊዝምም በእርግጠኛ መሰረት ላይ ሊገነባ የቻለው።  ወደዚህ ዐይነቱ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ወደሚገለጽ ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ግንባታ ለመምጣት ደግሞ አብዛኛዎቹ የአውሮፓ አገሮች መንፈስን የሚያድስና አዕምሮን ክፍት የሚያደርግ የባህል አብዮት ለማካሄድ ችለዋል። ከአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ለመንፈስ ተሃድሶ፣ ማለትም ለአርቆ-ማሰብና ለሎጂካዊ አስተሳሰቦች የሚያመቹ የጭንቅላት ስራዎችን ተግባራዊ ማድረግ ባይችሉ ኖሮ ዛሬ በምናየው መልክ ካፒታሊዝም ባላደገና ጠቅላላውን ዓለም የመቆጣጠር ዕድል ባላገኘ ነበር። ሳይንሳዊ ምርምርና በኋላ ላይ ደግሞ የቴክኖሎጂ ዕድገት ጉዳይ የባህል አብዮት ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል። ይህም የሚያረጋግጠው የሰው ልጅ የመንፈስ ነፃነት ሲያገኝና በድሮው መልክ መኖር እንደማይቻል ሲያምን የግዴታ አዳዲስ መሳሪያዎችን እንደሚፈጥርና ተፈጥሮንም የመቆጣጠር ኃይሉ እንደሚጨምርና፣ በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ነገሮችን ለማወቅ ጥረት እንደሚያደርግ ነው። ምክንያቱም ለሰው ልጅ ዕድገት የሚጠቅሙ ነገሮች በሙሉ በተፈጥሮ ውስጥ ብቻ የሚገኙ ስለሆነና በጭንቅላት ምርምር አማካይነት ተግብራዊ ለመሆን ስለሚችሉ ነው። ከአውሮፓው የባህል ታሪክ አንፃር ስንነሳ በቃለ-ምልልሱ ላይ የቀረበው የመንግስት መኪናና የህብረ-ብሄር ግንባታ በተሟላ መልክ የቀረበ አይደለም ብል የምሳሳት አይመስለኝም። በተሟላ መልክ ሊቀርብ ያልቻለው ምናልባትም ጠያቂው አስጨናቂ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ በደንብ ተዘጋጅቶ ባለመምጣቱ ወይም ደግሞ መሰረታዊ ነገሮች ስለሚጎድሉት ሊሆን ይችላል።

ስለ አሜሪካን የመንግስትና የአገር ግንባታ አወቃቀርም እንደዚሁ በደንብ ተብላልቶ የቀረበ አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ ከእንግሊዝ የመጡ ቅኝ-ገዢዎች ወደ 17 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢንዲያኖችን በመግደል ነው አሜሪካንን ሊቆጣጠሩ የቻሉት። እስከዚያ ጊዘ ድረስ የገነቧቸውንና ያካበቱትን ዕውቀትና የስልጣኔ መሰረት፣ እንዲሁም ታሪካቸውን እንዳለ ደምስሰውባቸዋል። በሁለተኛ ደረጃ፣ እንግሊዝ አሜሪካንን በቁጥጥሯ ስር ካደረገች በኋላ አስራሶስት ቅኝ-ግዛቶችን በመመስረት ለኢንዱስትሪ አብዮት የሚያመቻትን የጥሬ-ሀብት በከፊል ታገኝ የነበረው ከዚህ አስራሶት ቅኝ-ግዛቶቿ  ነበር። እነዚህ አስራሶስት የቅኝ-ግዛቶች ለእንግሊዝ ኢንዱስትሪ የጥሬ-ሀብት የሚያመርቱና፣ እንዲሁም ደግሞ እያደገ ለመጣው የከበርቴ መደብ የሻይ ቅጠል በማምረት በቀጥታ ወደ እንግሊዝ የሚልኩ ነበሩ። ይህም ማለት የራሳቸውን ኢኮኖሚ በሚፈልጉት መንገድና ከህዝባቸው ፍላጎት አንፃር ማዋቀርና መገንባት አይችሉም ነበር። የኋላ ኋላ ጭነቱ ሲበዛባቸውና፣ በተለይም ደግሞ እንግሊዝ በቅኝ-ግዛቶቿ ውስጥ ትከተል የነበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለተሟላ ዕድገት የማያመች መሆኑን የተገነዘቡ አንዳንድ የተገለጸላቸው ኃይሎች ጥያቄን በማቅረብ በእንግሊዝ አስተዳደር ላይ ማመጽ ይጀምራሉ። ሌሎች ደግሞ ለእንግሊዝ ያደሉ ስለነበር በቅኝ-ግዛቶች በተለይም በማደግ ላይ በነበረው ኤሊት ውስጥ ጥርጣሬና አለመግባባት ይፈጠራል። በአዲስ አስተሳሰብ መንፈሳቸው የተቀረጸው አንዳንድ ምሁራንና የራስን ነፃ ግዛትና መንግስት የሚፈልጉ ኃይሎች ከእንግሊዝ ቅኝ-ግዛት ከተላቀቁ ብቻ ዕውነተኛ ነፃነታቸውን ለመጎናጸፍ እንደሚችሉ በመረዳታቸው ትግላቸውን ያጧጡፋሉ። ትግላቸውም ደግሞ ሁለመንታዊ ሲሆን፣ በመጀመሪያ ደረጃ ግን በዕውቀት ላይ ያተኮረ ነበር።  የመጨረሻ መጨረሻም ኃይላቸውን በማጣመርና በተቀነባበረ መልክ ከእንግሊዝ ጋር ውጊያ ገጥመው ነፃነታቸውን ከአወጁ በኋላ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ ለተሟላ የአገር ግንባታ የሚያመች የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ያደርጋሉ። ለዚህ ደግሞ እንደነ ሃሚልተን የመሳሰሉ በጊዜው የአሜሪካን የገንዘብ ሚኒስተር የነበረው ልዩ የብድር ስርዓት በማቋቋም  በተለይም የማኑፋክቸሪንግ መስኩ እንዲዳብርና እንዲስፋፋ አመቺ ሁኔታ ይፈጠራል። ቀስ በቀስም የባቡር ሃዲድ ግንባታ ይካሄዳል። በዚህም መልክ የውስጥ ገበያ ሊዳብር የሚችልበትና ህዝቡን የሚያስተሳስረው ተቋማት መስፋፋት ይጀምራሉ። ይሁንና የአሜሪካንን የመንግስት መኪናና የህብረ-ብሄር ግንባታን ስንመለከት አቶ ገለታው ዘለቀ እንደሚለን በስምምነትና በለሰለሰ መልክ ወይም ደግሞ ካለምንም ግጭትና ብዝበዛ የተካሄደ አልነበረም። በመሀክላቸውም ልዩነት እንደነበርና እንደነ አብራሃም ሊንከን የመሳሰሉት የተገለጸላቸው ፕሬዚደንቶች ኋላ-ቀር አስተሳሰብ በነበራቸውና የተሟላ ዕድገትን በሚቀናቀኑ ኃይሎች ሊገደሉ ችለዋል። ከዚህም ባሻገር የአሜሪካን ህገ-መንግስት በጣም ጥሩ የሆነውን ያህል  በሌላ ወገን ግን ደግሞ የጥቁሮች መብት የተከበረ አልነበረም። አብዛኛዎች የመማር ዕድል ስላልነበራቸው የግዴታ በፕላንቴሽን ኢኮኖሚ ውስጥ ተቀጥረው በመስራት በከፍተኛ ደረጃ የሚበዘበዙና ለአሜሪካን ካፒታሊዝም ዕድገት አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ የተገደዱ ነበሩ።

ከዚህ ሀቅ ስንነሳ የአውሮፓውም ሆነ የአሜሪካኑ ካፒታሊዝም ካለብዝበዛና የሌሎች አገሮችን የተሟላ ዕድገት ሳይቀናቀኑና በቀጥታ ጣልቃ ሳይገቡ ለማደግ ወይም ለመበልጸግ አልቻሉም። በሌላ አነጋገር፣ በአውሮፓና በአሜሪካ የካፒታሊዝም ዕድገት በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በአፍሪካና በደቡብ አሜሪካ አገሮች ቀድሞም ሆነ ዛሬ የሚታየው ኋለ-ቀርነትና የመንገስታት ጨቋኝነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ማለት ይቻላል። ባጭሩ አሜሪካና አውሮፓ የካፒታሊዝምን ዕድገት ሊጎናጸፉ የቻሉት የትምህርትቤት ኢኮኖሚክስ እንደሚያስተምረን በነፃ ገበያ አማካይነት ሳይሆን በከፍተኛ ብዝበዛና በመንግስት ጣልቃ-ገብነት(Interventionist Policy) አማካይነት ብቻ ነው። ካፒታሊዝም ባፍላው ወቅት በነበረበት በ18ኛው፣ በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ በምዕራብ አውሮፓም ሆነ በአሜሪካን አገር በተለይም ወዝአደሩ በሳምንት ክ50 ሰዓትና ከዚያ በላይ የሚሰራበት ጊዜም ነበር። ከብዙ ትግል በኋላ ነው በሙያው ማህበርና በኢንዱትሪዎችም ውስጥ መደራጀትና የሚወክሉትን ለመምረጥ የቻለው። የዛሬውንም ሁኔታ ስንመለከት አብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች፣ አሜሪካንንም ጨምሮ በወዝአደሩ የረጅም ጊዜ ትግል የተገኘ የሶሻል ወይም የወልፌር ፖሊሲ ቢኖራቸውም፣ በእነዚህ አገሮች ውስጥ በገንዘብ የሚቆጠርውንና በተጨባጭ የሚለካውን(Finance and Real Capital) ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነውን ሀብት የሚቆጣጠረው ከ5-10% በመቶ የሚሆነው ህዝብ ብቻ ነው። ይህም ማለት አብዛኛው ህዝብ ለራሱ መጦሪያ የሚሆንና አንድ ነገር ሲያጋጥመው ድጋፍ ሊሆነው የሚችል ሀብት መፍጠር እንደማይችል ነው። በተለያዩ ዘዴዎችና ለሰፊው ህዝብ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ በተለይም በቀረጥና በፋይናንስ ፖሊሲ፣ እንዲሁም በብድር አሰጣጥ አብዛኛው ገንዘብ የሚፈሰው ሀብት ላላቸው ነው።

ወደ አገራችን ስንመጣ አቶ ገለታው ዘለቀ ከሰጠው የቃለ-መጠይቅ መልስ የተረዳሁት አስተሳሰቡ ስታቲክ(Static) ወይም ደግሞ አንድ ህብረተሰብ ባለበት ቆሞ እንደሚቀር ወይም ደግሞ እንደማይለወጥ አድርጎ ነው ለመግለጽ የሞከረው። ይህም ማለት አንድ አገር በድሮው ስርዓት እንዳለ ሊቀጥል ይችላል ከሚለው አስተሳሰ የሚነሳ ይመሰለኛል። እንደሚታወቀው ራሱንና አካባቢውን ለመለወጥ የማይችል እንስሳ ወይም ደግሞ ለማሰብ የማይችል ሰው ብቻ ነው። የሰው ልጅ ፍላጎት ስላለውና ህብረተሰብም ከአንድ ስርዓት ወደሌላ ስለሚሸጋገር የግዴታ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ለውጥ ይታያል። እያንዳንዳችን ተጸንሰን፣ ተረግዘን ከተወሰነ ወራት በኋላ እንደምንወለድና ቀስ በቀስም እንደምናድግና በሰውነትም ሆነ በሃሳብ እንደምንጎለምስ ሁሉ፣ ህብረተስብም እንደዚህ ከዝቅተኛ ደረጃ ወደ ተሻለ የመለወጥ ችሎታ አለው። ይሁንና በፖለቲካዊና በባህላዊ ምክንያቶች የተነሳ፣ በተለይም ደግሞ ስልጣንን የጨበጡ ኃይሎች ያልተገለጸላቸው ከሆኑና ሁለ-ገብ ዕውቀት ከሌላቸው አንድ ህብረተሰብ የመለወጥ ዕድሉ በጣም ዝቅተኛ ይሆናል። ይሁንና ግን አንድ ህዝብ ጭቆናና ብዝበዛ ሲበዛበትና ኑሮው የማይለወጥ ከሆነ ከስርዓቱ ውጭ የሆኑ የተገለጸላቸው ኃይሎች ጥያቄ በመጠየቅ ካለው ስርዓት ጋር መጋፈጥ ይችላሉ። ስለሆነም በአገራችን ምድር የአፄው ስርዓት ሊገረሰስ የቻለው  በአንድ በኩል በራሱ ድክመት የተነሳ ሲሆን፣ በሌላው ወገን ደግሞ ጥያቄን መጠየቅ በጀመሩና ለውጥን በሚፈልጉ አዳዲስ ኃይሎች አማካይነት ነው። የአፄው አገዛዝ በጊዜው የነበረውን ኢኮኖሚያዊ፣  ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና የባህል ቀውስ ለመፍታት ባለመቻሉ የግዴታ  ሊወድቅ ችሏል። ስልጣን በደርግ እጅ ሊወድቅ የቻለውም በጊዜው የተደራጀ ኃይል ስላልነበር ነው። አፄ ኃይለስላሴና ሚኒስተሮቻቸው በስልጣናቸው ዘመን የአገራችንና የህዝባችንን ዕድል ከራሳቸው ባሻገር ለማየት የሚችሉ ስላልነበሩ ስልጣንን ሊረከብና አገሪቱን ሊያስተዳደር የሚችል ኃይል እንዲፈጠር አመቺ ሁኔታዎችን አልፈጠሩም። ስለሆነም ደርግ የሚባለው ከሚሊታሪው የተውጣጣ ኃይል በመቋቋም ስልጣንን ሊወስድ ቻለ። ደርግ ደግሞ በአስተሳሰቡ ሶሻሊስታዊ ሳይሆን ከፊዩዳሉ ስርዓትና ከውጭ የመጣው የአሜሪካን ርዕዮተ-ዓለም ውጤት ነው። ይህም ማለት አስተሳሰቡ በዚህ ዐይነቱ አስተሳሰብ የተቀረጸና የኋላ ኋላ በተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎች በመገፋት የሶሻሊስት ርዕዮተ-ዓለምን የተቀበለ ነው። ሲቀበልም ተመራምሮና አጥንቶ ይህ ርዕዮተ-ዓለም ለዕድገት ያመቻል በማለት ሳይሆን የግዜው አስተሳሰብ ስለነበር ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ትቅደም ሲል ኢትዮጵያ ትደግ፣ ህዝባችንም ከድህነት መላቀቅ አለበት ከሚለው አስተሳሰብ በመነሳት እንጂ ከመጀመሪያውኑ ከሶሻሊዝም ጋር የሚያያዝ አልነበረም። በጊዜው ደግሞ እንደዚህ ዐይነቱን ማስተጋባቱ እንደክፋት የሚቆጠር ሊሆን አይገባውም። በእርግጥ ደርግ እንዳለው ኢትዮጵያ ትቅደም ካለምንም ደም መፋሰስ የሚለው ጥሩው አባባል በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ተግባራዊ ሊሆን በፍጹም አልቻለም።

ለማንኛውም የመሬት ለአራሹ መታወጅ፣ የህዝቡ መደራጀት፣ ህዝቡን ማስተማርና ማንቃት በጣም አስፈላጊና የሚደገፉ እርምጃዎች ነበሩ። በእግጥ የመሬት ለአራሹ ሲታወጅ በደንብ በተጠና መልክ አልነበረም የታወጀው። በተለይም የኋላ ኋላ በራሳቸው ጥረት በመስራትና በጊዜው የተከፈተውን ዕድል በመጠቀም ሀብት በማካበት ወደ መሬት ከበርቴነት የተሸጋገሩ ነበሩ።  ካለማወቅ የተነሳና ሰፋና ጠለቅ ያለ ጥናት ባለመደረጉ ወደ ኢንዱስትሪ ከበርቴነት ሊለወጡ የሚችሉና ድጋፍም የሚያስፈልጋቸው እንደተበዝባዥ በመቆጠር ተሳደዋል፣ አንዳንዶችም ተገድለዋል። ቤተሰቦቻቸውም ወደድህነት ዓለም ለመገፍተር በቅተዋል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ከፖለቲካ አንጻር ግጭት እንዳይነሳ ለማድረግ ሲባል የፊዩዳል መደብ ለሚባለው የተወሰነ መሬት በመተው  የተወሰነውን መውረስ ይቻል ነበር። አብዛኛው የፊዩዳል መደብ ደግሞ ሀብቱ በመሬት ላይ የተመሰረተ ስለነበር መሬቱ ሲነጠቅ ለረሃብ ለመጋለጥ በቅቷል። ያም ሆኖ የመሬት ለአዋጁ ለምን ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም በሚለው ላይ ብዙም ጥናት አልተካሄደም። ማለት የሚቻለው ግን በጊዜው በአገራችንም ምድር የፈነዳው አብዮት በውስጥ ተቀናቃኝና በውጭ ደግሞ በኢምፔሪያሊስት ኃይሎች የደርግ አገዛዝ ተወጥሮና ጦርነትም ይካሄድበት ነበር። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረአበሮቹ አብዮቱ ተግባራዊ እንዳሆንና ብሄራዊ ሰሜትም እንዳይዳብር አገራችንን ወደ ጦር አውድማነት መለወጥ ነበረባቸው። በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አብዮትና ሶሻሊዝም በሚለው ላይ ያልተደሰተ ስለነበረና፣ ኢትዮጵያም እንደ ሶቭየት ህብረትና ቻይና የማደግ ዕድል ያጋጥማታል ብሎ ስለፈራ የግዴታ ሂደቱ መጨናገፍ ነበረበት። ስለሆነም የአብዮቱን ወይም የድርግ ጠላቶችን በሙሉ ማስታጠቅ ጀመረ። ከውስጥ ደግሞ በቀይና በነጭ ሽብር ውስጥ በመሳተፍና ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችን በማስታጠቅ ደርግ የባሰውኑ እንዲቆጣ ለማድረግ በቃ። ከዚህም በላይ ሶማሊያን በማስታጠቅ አገራችንን እንድትወር ለማድረግ በቃ። ኢድህ፣ ሻቢያ፣ ወያኔና አንዳንድ የማርክሲስት ድርጅቶች ነን ባዮች በአሜሪካን የሚደገፉና በግድያ ውስጥ የተሳተፉ ነበሩ። እንደዚሁ በሲቪል ቢሮክራሲው ውስጥ፣ በፀጥታውና በሚሊታሪው ውስጥም ለአሜሪካኖች ተመልምሎ ይሰልልና ውዥንብር የሚነዛ ኃይል ከፍተኛ ወንጀል ፈጽሟል፤ ደርግን አስበርግጎታል። በተለይም ደርግ በሰሜን ኮሪያ መንግስት በመደገፍ የጋፋት የጦር ኢንዱስትሪን ለማቋቋም በመዘጋጀት ላይ ስለነበር ይህ ፕሮጀክት የግዴታ መክሸፍ ነበረበት። ይህንን አስመልክቶ ፕሮጀክቱ እንዲከሽፍ ለአሜሪካ ተቀጥረው የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ኃይሎች እንደነበሩ የሚያትት መጽሀፍ በአንድ አገር ወዳድ መኮንን ተጽፎ ለአንባብያን ቀርቧል። በአጭሩ በጊዜው የተፈጠረው ትርምስ፣ የሰው ህይወት መጥፋትና መገዳደል በደርግ ላይ ብቻ የሚሳበብ መሆን የለበትም። በጊዜው የነበረውን ሁኔታ መረዳት የሚቻለው በአብዮቱ ውስጥ የተሳተፉትን ኃይሎች የንቃተ-ህሊና ደረጃና ብስለት፣ ሶሻሊዝምን በመጥላትና በአሜሪካን በመደገፍ ጦርነት ያወጁትን ኢትዮጵያውያን ኃይሎች የምሁርና የፖለቲካ ብስለት ሁኔታ፤ እንዲሁም ደርግን ብቻ በመጥላት አሻፈረኝ ብሎ የተነሳውን በአስተሳሰብ በዝቅተኛ ደረጃ ይገኝ የነበረውን ኃይል ሁሉ ስሌት ውስጥ ለማስገባት የተቻለ እንደሆን ብቻ ነው የተሟላ ስዕል ማግኘት የሚቻለው። ባልሳሳት አቶ ገለታው ዘለቀ ከንጹህ የሶሻሊዝም ጥላቻ በመነሳት ነው በጊዜው የነበረውን ሁኔታ ለመዳሰስ የሞከረው። ይህ ዐይነት ገለጻና አስተሳሰብ ደግሞ በጣም አደገኛና ለምሁራዊ ውይይትና ክርክር፣ እንዲሁም ደግሞ ነገሮችን ከተለያዩ አንፃሮች እንዳንመለከትና እንዳንመረምር ያግዳል። ሌላው በዚህ ገለጻና በአብዛኛዎቹ የኢትዮጵያውያን የሶሻሊዝም ጠላቶች ዘንድ ያለው አስቸጋሪ ጉዳይ ሰለአገራችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ፣ እንዲሁም የባህል ሁኔታ ያላቸው ግንዛቤ የተሳሳተ መሆኑ ነው። በሌላ አነጋር አብዛኛዎቹ ምሁራንና የሶሻሊዝም ጠላቶች ነን ባዮች የአገራችንን ሁኔታ በሳይንስ መነጽር ለመመርምር ዝግጁ አይደሉም።

ስለሆነም ሶሻሊዝም እንደ ርዕየተ-ዓለም ሲታወጅና መመሪያ ሲሆን የአገራችን የማቴሪያልም ሆነ የምሁር ብስለት ደረጃ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተገነዘበ ኃይል የለም።  በማርክስና በኢንግልስ አስተሳሰብ ሶሻሊዝም ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው የምርት ኃይሎች፣ ወይም ደግሞ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባደጉበት አገር ብቻ ሳሆን፣ ይህም ቢሆን በከፍተኛ ንቃት-ህሊናና በዕውቀት የሚደገፍና የተለያዩ ቲዎሪዎችንና የሳይንስ ዘርፎችን መረዳታ ያስፈልጋል። በሌላ አነጋገር፣ ሁኔታዎች ሳይበስሉ እንደዚህ ዐይነቱን ርዕዮተ-ዓለም ተግባራዊ አደርጋለሁ ብሎ መነሳት በተለይም በኢምፔሪያሊዝም ዘመን አስቸጋሪ ነው። ይሁንና ርዕተ-ዓለሙን ተገን በማድረግ ያልተሰበሰበውን ህዝብ ማንቃትና ማደራጀት፣ እንዲሁም ኃይልን በማጣመር አገርን ከታች ወደላይ መገንባት ይቻላል። ስለሆነም ሶቭየት-ህበረትና ቻይና ሰፊውን ህዝብ የማንቀሳቀስና የማደራጀት ሁኔታን በመጠቀም ነው ከነበራቸው ኋላ-ቀር ስርዓት ሊላቀቁና ታላቅ አገር ለመገንባት የቻሉት። በእነዚህ አገሮች ውስጥ ደግሞ ሶሻሊዝም የሚባለው ነገር ከሞላ ጎደል ተግባራዊ ሊሆን የቻለው የተሻለ ንቃተ-ህሊና ስላላቸውና፣ የሚያፈነግጥና ከውስጥ ሆኖ የኢምፔሪያሊስቶችን አጀንዳ የሚያስፈጽም ኋላ-ቀር ኃይል ባለመኖሩ ነው። በሌላ አነጋገር፣ የሶቭየት-ህብረትና የቻይናዎቹ ምሁራን ንቃተ-ህሊናቸው ብቻ ሳይሆን ብሄራዊ ስሜታቸውም በጣም ከፍ ያለ ስለነበር ታላቅ አገር ለመገንባትና ለመከበር ችለዋል።

እንደገና ወደ ሶሻሊስዝም ጽንሰ-ሃሳብ ላይ ስንመጣ አቶ ገለታው ከውጭ የመጣ አስተሳሰብ ነው በማለት ለማጥላላት ይሞክራል። በአፄ ምኒልክም ሆነ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ከውጭ ብዙ አስተሳሰቦች፣ ለባህላችን እንግዳ የሆኑ ነገሮች ገብተዋል። ራሱ የክርስትና ሃይማኖት ከውጭ የመጣ ነው። ኢትዮጵያ ከውጭ ተገልላ ትኑር የማንል ከሆነ በስተቀር ከውጭ ልዩ ልዩ አስተሳሰቦች መምጣታቸው የማይቀር ጉዳይ ነው። ጥያቄው ከውጭ የሚመጣውን ባህልም ሆነ ርዕዮተ-ዓለም እንዴት ማስተናገድ ይቻላል? ጠቃሚውን ከሚጎዳው እንዴት መነጠል ይቻላል? የሚለው ላይ ነው መወያየት የሚያስፈልገው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ ልክ እንደ ነፃ ገበያም የሶሻሊስት ርዕዮተ-ዓለም ወደ አገራችን መግባቱ ልናልፈው የምንችለው ጉዳይ አይደለም። ከ1950ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ አፄ ኃይለስላሴ እስከወደቁበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ሁኔታ ስንመለከት አንዳንድ ጥሩ ነገሮች የገቡትን ያህል የሰውንም ስነ-ልቦና በመጥፎ ነገር የሚቀርጹ ባህል ነክ ነገሮችም ገብተው እንደነበርም የማይታበል ጉዳይ ነው። እንዲያውም ለሶሻሊዝም መክሸፍና እንደዚያ እርስ በርስ ለመጨራረስ ዋናው ምክንያት የሶሻሊዝምን አስተሳሰብ በመከተላችን ሳይሆን ከህብረተሰብ አወቃቀር አንፃር በአፄ ኃይለስላሴ ጊዜ የተፈጠረው የተሙለጨለጨ የህብረተሰብ ኃይል አንደኛው ምክንያት ነው። የፊዩዳሉ ግትርነት ከዚህ ጋር ሲደመር ለአመጽ እንደገፋፋን የማይታበል ሀቅ ነው። ይህም ማለት የሶሻሊዝም አስተሳሰብ በራሱ አመጽ እንዲካሄድ አልገፋፋንም። በማንኛውም የማርክስ ስራዎችም ውስጥ ከትንተና በስተቀር አብዮት መካሄድ ያለበት በመገዳደል ነው የሚል የለም። ማርክስ ስለመደብ ትግል ሲያወራ ከነበረው የሀብት ክፍፍል፣ የከበርቴው መደብ የፖለቲካ የበላይነት፣ በጊዜው በኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን በየኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥሮ ይሰራ የነበረውን ሰራተኛ  መደብ የሚደርስበትን ጫናና ግፍ በማጥናት፣ ከዚህም በላይ በኢንዱስትሪ አብዮት ምክንያት የተነሳ ከገጠሩ እየተፈናቀለ የመጣው ሰራተኛ በለንደን፣ በማንቼስተርና በሌሎች ትላልቅ የእንግሊዝ ከተማዎች የሚኖረውን የሰራተኛን የኑሮ ሁኔታና፣ ከዚህም በላይ ስራ ለማግኘት ባለመቻሉ በከፋ ድህነት ይኖር የነበረውን ተጠባባቂ የሰራተኛ ኃይል(Reserve Army)  በማየቱና በመመርመሩ ብቻ ነው። ስለሆነም ማርክስና ተከታዮቹ ይታገሉ የነበረው በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ይኖር ለነበረው ሰፊው ህዝብና በፋብሪካዎች ውስጥ ተቀጥሮ አሰልቺና አድካሚ ስራዎችን የሚሰራው ሰራተኛ የኑሮው ሁኔታ እንዲሻሻል፣ የስራ ሰዓቱ እንዲቀንስለትና, በሙያ ማህበሩም አማካይነት በመደራጀት ፖለቲካዊ ኃይል ሆኖ እንዲወጣ ለማድረግ ነው። ባጭሩ ስለሶሻሊዝም ስናወራ ጽንሰ-ሃስቡን ማርክስና ኤንግልስ የፈጠሩት ሳይሆን ቀደም ብሎ የነበረ ነው፡፡ ይህንንም ካልን ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስም የመጀመሪያው ሶሻሊስት ሰው ነው ብሎ መጥራት ይቻላል።

ወደ አገራችን ተጨባጩ ሁኔታ ስንምጣ ደርግ የሶሻሊዝምን ርዕዮተ-ዓለም ካወጀ በኋላ፣ በ1976 ዓ.ም መለስተኛ የዲሞክራቲክ አብዮት ፕሮግራም ተጽፎ ቀርቧል። በዚህ ፕሮግራም መሰረት በተቻለ መጠን በጊዜው ተራማጅ የሚባሉ ኃይሎች በሙሉ የሚሳተፉበት ሲሆን፣ በዚያው መጠንም የከበርቴው ኃይል እንዲፈጠር የኢኮኖሚ የጥገና ለውጥም ማካሄድ ነበር። ይሁንና ይህ ተረቆ የቀረበው መርሃ-ግብር የተጻፈበት ቀለም ሳይደርቅ አንዳንዶች መልዕክቱን ባለመረዳታቸውና ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ወደ ጦር ትግል ነው ያመሩት።

ሌሎች በሶሻሊዝም ስም የተወሰዱትን እርምጃዎች፣ ለምሳሌ ኢንዱስትሪዎችን፣ ባንኮችንና መድህንን መውረስ ወይም በመንግስት ቁጥጥር ስር መደረጉ የሚያረጋግጠው አብዛኛዎቹ፣ 1ኛ) ምርታማ ያልሆኑና ለሰፊው ህዝብ የስራ-መስክ የማይከፍቱ ናቸው። የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪን አተካከል ለተከታተለ ወይም ላጠና ከ1950ዎች  ዓመታት መጀመሪያ ጀምሮ የተቋቋሙት ኢንዱስትሪዎች የመባዛት፣ የማደግና የመስፋፋት ባህርይ የሌላቸው ነበሩ;፡ ከእነዚህ ውስጥም የሲጋራ ፋብሪካ፣ የስኳር ፋብሪካ፣ የመጠጥ ፋብሪካና አንዳንድ የፍጆታ ዕቃ ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ይገኙባቸዋል። እነዚህ ሁሉ ኢንዱትሪዎች  ከውጭ የመጡ ሲሆን፣ ከሰፊው ህዝብ ፍላጎትና ከሁለ-ገብ ዕድገት አንፃር በመመርመር የተተከሉ ሳይሆኑ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ለመጥቀም ብቻ ነበር። ስለሆነም የኢንዱስትሪዎቹ መወረስ በጊዜው የነበረውን ስትራክቸራል ቀውስ ለመቅረፍ ታስቦ ነው ማለት ይቻላል። ይሁንና እንደቀድሞውም በአብዮቱ ወቅት ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገትንና የፖለቲካ ኢኮኖሚ ቲዎሪን አስመልክቶ ጥናትና ምርምር፣ እንዲሁም ክርክር ይካሄድ ስላልነበር አብዛኛው ነገር ይሰራ የነበረው በዕቅድና በተጠና መልክ ሳይሆን አምባገነናዊና ግብታዊ በሆነ ከላይ በሚመጣ ትዕዛዝ ነበር።

ያም ሆነ ይህ የአቶ ገለታው ዘለቀን በዚህ ላይ ያተኮረውን ገለጻ ሳዳምጥ የአቶ ገለታው አገላለጽ ሶሻሊዝምን ከመጥላት በመነሳት እንጂ ሁኔታዎችን በማጥናትና በማገናዘብ አይደለም። ሌላው በገለጻው ውስጥ ለማካተት ያልቻለው ለምሳሌ የሶሻሊስት አብዮትና የዕዝ-ኢኮኖሚ ተግባራዊ በሆነባቸው፣ እንደ ሶቭየተ-ህብረት፣ ኋላ ደግሞ ቻይናና ሰሜን ኮሪያ፣ ከ1975 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ቬትናም ውስጥ ለምን እንደ እኛ አገር እንደታየው ትርምስ መታየት አልቻለም? በምንስ መልክና እንዴት ከውጣ ውረድ በኋላ እነዚህ አገሮች በሙሉ የኢንዱስትሪ አብዮት ማካሄድ ቻሉ? እንዴትስ የተሟላ ለውጭ ኃይል የማይበገር የመንግስት መኪና ማዋቀር ቻሉ? ሌሎችም ደግሞ  እንደ ቡልጋርያ፣ የተቀሩት የሶሻሊስት አገሮች ራሳቸውን እንዴት ቻሉ?  እነዚህን ጥያቄዎች ሁሉ ስናነሳና መልስም ለመፈለግ ጥረት ስናደርግ፣ የእነዚህ አገሮች ህዝቦችና መሪዎቻቸው በአስተሳሰብ የበሰሉ ወይም ከእኛው በብዙ እጅ የተሻሉ መሆናቸውን ነው የሚያረጋግጡት። ሶቭየት-ህብረትም ሆነ ቻይና ኢኮኖሚያቸውን የገነቡት ሌሎች የሶስተኛው ዓለም ተብለው የሚጠሩ አገሮችን ሳይበዘብዙና በእነዚህ አገሮችም ውስጥም ጣልቃ ሳይገቡ ነው። ለማንኛውም ይህ ሁኔታ የሚያረጋግጠው ሶሻሊዝም በለው ካፒታሊዝም፣ ወይም ሌላ ስርዓት በአገራችን ምድር ቢታወጅ በቀላሉ ተግባራዊ ሊሆኑ የማይችሉት ራሳችንን ለመቆጣጠር ስለማንችልና በዲሲፕሊን ለመስራት ስለማንፈልግ ነው። በተለይም ደግሞ ምሁራዊ ብስለታችን እጅግ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኝና፣ በተለይም የፖለቲካ ኢኮኖሚ ህግን ስለማንረዳ ነው። ለማንኛውም የፈለገው ዐይነት ስርዓት ይሁን አንድን አገር ለመገንባት ከተፈለገ፣ ዕምነት፣ የሞራል ብቃትና ዲሲፕሊንና ከፍተኛ ምሁራዊ ንቃተ-ህሊና በጣም አስፈላጊዎች ናቸው። በተለይም ምሁር ነኝ የሚለውና፣ በፖለቲካ ስም እዚህና እዚያ የሚሯሯጠው አንዳቸውንም ቅድመ-ሁኔታ የሚያማሏ አይደለም። ስለሆነም የሚሆን የማይሆን ሰበብ እየፈጠርን ገና በማደግ ላይ የሚገኙ ልጆችንና ወጣቶች ባናሳስት ይሻላል።

ሌላው የአቶ ገለታው ዘለቀ ችግር በተለይም ወያኔ እንዴት ስልጣን ላይ እንደወጣና፣ ተግባራዊ ያደረገውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ አስመልክቶ ለማብራራት የሞከረው አንዳችም ነገር የለም። አትኩሮው የብሄር ቀደም በሚለው ፖለቲካ ብቻ ነው። አሁንም ለአብዛኛዎች ግልጽ ለማድረግ ህወሃት ወይንም ወያኔ የአሜሪካና የእንግሊዝ ፕሮጀክት ነበር። እነሱ የሚፈልጉትን አገርን የሚበታትን ነገር ሁሉ ተግባራዊ ለማድረግ የተቀመጠ ነው። በቋንቋ ላይ የተመሰረተውን የክልል ወይም የብሄር ፖለቲካን ስንመለከት፣ በአንድ በኩል ለወያኔ ከፋፍሎ ለመግዛት ሲያመቸው፣ በዚህ አማካይነት ደግሞ አሜሪካኖችና እንግሊዞች ኢትዮጵያ እንደ አገርና እንደህብረተሰብ እንዳትመሰረትና ህዝቡ እየተዋከበ እንዲኖር በማድረግ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ማህበረሰብ እንዳይገነባ ለማድረግ የሚከተሉት አገሮችን የማተረማመስ ስትራቴጅ ነው። ለዚህ ደግሞ የተቋም ማስተካካያ(Structural Adjustment Programs) የሚሉት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋነኛው መሳሪያ ነው። በዚህ ፖሊሲ አማካይነት አገሪቱን በነፃ ንግድ ስም በዕዳ መተብተብ፣ ወደ ውስጥ ደግሞ የተስተካካለ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ ማሳሳትና ለህዝቡ በማይጠቅሙ ፕሮጀክቶችና ሰፋ ላለ ገበያ ግንባታ የማያመቹ ነገሮች ላይ መረባረብ ነው። በነፃ ንግድ ስም የተነሳ ከውጭ የሚመጣው መዋዕለ-ነዋይ በሙሉ ወደ ውስጥ ያተኮረ ሁለ-ገብ ኢኮኖሚ መገንባት የሚያስችል ሳይሆን የፕላንቴሽን ኢኮኖሚ በማስፋፋት ህዝባችንና የጥሬ-ሀብታችንን መበዝበዝ ነው። እነዚህንና ሌሎች ከኢኮኖሚ ፖሊሲው ጋር ሰተት ብለው የገቡ ባህልን አውዳሚ ነገሮች በሙሉ አቶ ገለታው ዘለቀ ለማየት በፍጹም አልቻለም። ያም ሆነ ይህ በወያኔ ዘመንም ሆነ አሁን ደግሞ በእነአብይ አህመድና በእነሺመልስ አብዲሳ የአገዛዝ ዘመን የብሄረሰብ ጥያቄ ወይም አጀንዳ ጎልቶ የወጣው ከተሳሳተ ትረካ በመነሳት ነው። ከዚህም በላይ የብሄረሰብ ጥያቄ ጎልቶ የሚነሳው በእርግጥም የሰፊውን የትግሬም ሆነ የኦሮሞን ብሄረሰብ መሰረታዊ ፍላጎቶች ደረጃ በደረጃ አሟልቶ የሳይንስና የቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም የስነ-ጽሁፍና የጥበብ ባለቤት ለማድረግ ሳይሆን ጥቂቶች ኢሌቶች ይህንን በመጠቀም ራሳቸውን አጉልተው የሚያሳዩበትና የሚያደልቡበት መሳሪያ ነው። (https://amharic-zehabesha.com/archives/175240)ቀደም ብሎም ሆነ በኋላ፣ በተለይም ከምርጫ 1997 ዓ.ም በኋላ የህወሃት አገዛዝ የተጠቀመው ለተወሰነው ትግሬ ገንዘብ በዜሮ ወይም በትንሽ ፐርሰንት በማበደር ማሳዎችን እንዲገዙና በፕላንቴሽን ኢኮኖሚ ላይ እንዲሰማሩ፣ ኢንዱስትሪዎችንና ትላልቅ የንግድ መደብሮችን በርካሽ እንዲገዙና ሆቴልቤቶች እንዲሰሩ በማድረግ በዚህም አማካይነት ጥቂቱን በጣም የደነቆረ የትግሬ ብሄረሰብ ማደለብና የብልግና ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ማድረግ ነበር። ይህም ሂደት ከሞላ ጎደል ተግባራዊ በመሆን፣ በተለይም ለዋጋ ግሽበት ከፍተኛውን ሚና የተጫወተ የተሳሳተ የገንዘብ ስርጭት አካሄድ ነው። ዛሬም የአብይ አህመድና የሺመልስ አብዲሳ አገዛዝ አርቲፊሻል በሆነ መንገድ 500 የኦሮሞ ቢሊየነሮችን መፍጠር አለብን፣ በዚህም አማካይነት ከፖለቲካው፣ ከሚሊታሪው፣ ከፀጥታውና ከፖሊሱ ባሻገር በኢኮኖሚውም መስክ የበላይነትን መያዝና ሌሎችን ደግሞ የበታች አድርገን መግዛት አለብን በማለት ዕቅድ  ነድፎ ተግባራዊ ለማድረግ በመንደፋደፍ ላይ ይገኛል። ከዚህ አጠር መጠን ያለ ሀተታ ስንነሳ የህወሃትና የአቢይ አገዛዞች የብሄረሰቦቻቸን አቀንቃኞች ነን፣ ነፃ አውጭ ነንም ብሎ ማውራት በመሰረቱ የጥቂቶችን ጥቅም ማስጠበቂያ መሳሪያ ብቻ ነው። ከጠቅላላው የአገራችን ሁኔታ ስንነሳ ደግሞ ይህ ዐይነቱ አካሄድ ድህነትን፣ ቦዘነኔትን፣ ማጭበርበርና በዚያው መጠንም ለውጭ ኃይሎች ተገዢ የሆነን ኃይል የሚፈጥር ሁኔታ ነው። ባጭሩ የኢኮኖሚውም ሆነ ሌሎች ፖሊሲዎች በሙሉ ጠቅላላውን ህዝባችንን የሚጎዱና፣ ከብሄረሰብ ልዩነት ባሻገር እንደ አንድ አገር ህዝብ አንድ ላይ በመነሳትና ኃይላችንን በማስተባበር የተከበረችና በሳይንስና በቴክኖሎጂ የምትገለጽ አገር እንዳንገነባ የሚያደርግ አደገኛ አካሄድ ነው።

አቶ ገለታው ዘለቀ ለማብራራት ወደ ሞከረው  አሸባሪ መንግስት ወዳለው ጉዳይ ስናመራ፣ ደርግ፣ ቀጥሎ ደግሞ ወያኔ፣ አሁን ደግሞ የአብይ አገዛዝ በመንግስት የተደገፈ አመጽን ለማስፋፋት፣ የዲሞክራሲ መብት እንዲታፈን፣ ህዝቡ እንዳይነቃና እንዳይደራጅ ማድረግ፣ ባጭሩ ለነፃነቱ እንዳይታገል የሚጠቀሙባቸው የመጨቆኛ መሳሪያዎች በሙሉ መሰረታቸው በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የተጣሉ ናቸው። ደርግ በጊዜው በህዝባችንና በተለይም ማሰብ በሚችለው ላይ ዘመቻ ማድረግ ሲጀምር ይጠቀም የነበረው የወረሰውን የመንግስት የመጨቆኛ መሳሪያ በመጠቀምና በማሻሻል ነው። ወያኔም ሆነ የአቢይ አገዛዝ እነዚህን የመጨቆኛና የህዝብን መብት ማፈኛ መሳሪያዎች በሙሉ ራሳቸው አልፈጠሯቸውም። የነበረውን በመውረስና በማሻሻል፣ እንዲሁም በማደለብ ወደ መጨቆኛ መሳሪያነት የለወጡት ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ስነነሳ የመንግስትን ባህርይና አወቃቀር ማጤኑ ተገቢ ነው። ባጭሩ ማለት የሚቻለው፣ መንግስት የሚባለው ነገር በከፍተኛ ደረጃ ጭንቅላታቸው ባልዳበረና ማሰብ በማይችሉ፣ በሳይንስ፣ በፍልስፍናና በሌሎች ልዩ ልዩ ዕውቀቶች ሳይሆን በስሜት በሚመሩ ሰዎች እጅ ከወደቀ የግዴታ ወደ መጨቆኛ መሳሪያነት መለወጡ የማይቀር ጉዳይ ነው። ሌላውና በጣም ወሳኙ ነገር ደግሞ ከውስጥ ተፎካካሪ የሚሆንና የተገለጸለት የሲቪል ማህበረሰብ እስከሌለ ድረስ እንደ እኛ አገር የመሳሰሉ አገዛዞች ወደ ዘራፊነትና ወደ ጨቋኝነት ነው የሚያዘነብሉት። በሌላ አነጋገር፣ የህብረተሰብአችን አወቃቀርና የመንግስት መኪና አገነባብ መሰረታዊ በሆነ መንገድ ውይይት እስካልተደረገበትና እስካልታቀደ ድረስ ውሃ ቢወቅጡት እምቦጭ እንደሚሉት አነጋገር ነው። ስለዚህ ማሰብና መመራመር ያለብን ለምን በሶስተኛው ዓለም አገሮች የተዋቀሩት የመንግስት መኪናዎች በሙሉ ወደ ጨቋኝነት ያመራሉ?
https://amharic-zehabesha.com/archives/176606

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...