Saturday, August 13, 2022

ለምን የብሔር ፖለቲካ የሙጥኝ ይባላል? (ታምራት ኪዳነማርያም)
የፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል መታጣት እና ደህና ኑሮ መኖር ያለመቻል መንስዔ የብሔር ዕኩልነት ያለመኖር ነው ብለው የሚያምኑ ፖለቲከኞች ከ30 ዓመታት በላይ የብሔር ፖለቲካ ቢያራምዱም የተፈለገው ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልም ሆነ የተሻሻለ ኑሮ ሊገኝ አልቻለም።

ሀቁን ለመናገር የ20ኛው ክፍለዘመን በኢትዮጵያ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እና የልማት እጦት የሚስተዋለው በዋናነት በብሔረሰቦች መካከል ሳይሆን በገጠርና በከተማ መካከል ነው። ምክንያቱም በብሔረሰብ ጨቆነ የተባለው አማራ ገጠር ውስጥ ቢኬድ በልማት ተጠቃሚነቱ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢ የባሰ እንጂ የተሻለ አይደለም።

ገጠሩ በተቻለ መጠን የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን እና ማንነቱና ባህሉ እንዲከበር ቢደረግ ሁሉም ብሔረሰቦች የልማት ተጠቃሚ ይሆናሉ። ምክንያቱም አብዛኛው የብሔረሰብ አባላት የሚኖሩት በገጠር እንደመሆኑ መጠን ገጠሩ የልማት ተጠቃሚ ሲሆን እነሱም ተጠቃሚ ይሆናሉ። የኢትዮጵያ ባህሎችን፣ ባህላዊ ዕውቀቶችን፣ ቁሳቁሶችን እና ምርቶችን ማበልፀግና በተገቢው ጥቅም ላይ ማዋል ቢጀመር ሀገሪቱን በዓለም መድረክ ላይ የራሷን ተፎካካሪ ሥልጣኔ እንድታሳድግ ከማስቻሉም በላይ በገጠርና በከተማ መካከል ዕኩልነትና የበለጠ መከባበር ያሰፍናል። ይህ የሀገሪቱ ብሔረሰቦች የሚገባቸውን ክብር የበለጠ እንዲያገኙ ከድረግም በላይ ሀገሪቱን ያሳድጋል።

ሌላው የአብዛኛዎቹ የብሔረሰብ ፖለቲከኞች እና መብት ተሟጋቾች አስገራሚ አካሄድ ኢትዮጵያዊነትን ጥለውና አጣጥለው ሲያበቁ በብሔረሰብ ማንነታቸው ሊከበሩ ይፈልጋሉ። የሀገሪቱን ባህልና ታሪክ አንቋሽሸው እጃቸውን ለፈረንጆች ከሰጡ በኋላ ከጣሉት ኢትዮያዊነት ውስጥ የራሳቸውን ብሔር ማንነትና ባህል አንስተው አቧራውን አራግፈው በብሔር ማንነታቸው ሊከበሩ ይሻሉ። በኢትዮጵያዊ ማንነቱ የሚያፍር እና አውሮፓን ከፍ የሚያደርግ ትውልድ እየቀረጹ የብሔር ማንነታቸውን እንዲያከብርላቸው ይፈልጋሉ። የማይሆን ነገር ነው። ኢትዮጵያዊነት ተንቆና ተዋርዶ ብሔረሰቦች የሚገባቸውን ክብር ሊያገኙ አይችሉም።

የብሔር ፖለቲከኞች በገጠርና በከተማ መካከል ያለው መስተጋብር ቢስተካከል፣ ኢትዮጵያዊነት ተገቢውን ክብር ቢያገኝ እና ወደራሳችን ብንመለስ አብዛኛው የብሔር ጥያቄ እንደሚመለስ ተገንዝበው በብሔረሰቦች መካከል ጠብ ከመፍጠርና ሀገርን ከማጥላላት ፖለቲካ ቢርቁ ጥሩ ነው። የችግሩን መንስዔና መፍትሔ በትክክል አገናዝበው፣ ሕዝብን ከማጥላላት፣ እርስ በእርስ ከማጋጨት እና ከፍረጃ ርቀው ለገጠርና ከተማ ፍትሐዊ የሀብትና ልማት ተጠቃሚነት፣ ለኢትዮጵያ ባህሎች መከበር፣ ለባህል ዕድገት፣ ለሀገራዊ ዕውቀቶች መዳበር፣ ለባህላዊ ቁሣቁሶችና ምርቶች መበልፀግ ወዘተ፣ ለኢትዮጵያዊነት ክብር፣ ለታሪኳ ከጥላቻና ከተሳሳተ ትርክት መራቅ፣ ለኢትዮጵያ በአስተሳሰብ እና በዕውቀት እራሷን መቻል ወዘተ. ቢሠሩ ጥሩ ነው።
https://amharic-zehabesha.com/archives/176576

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...