Saturday, August 13, 2022
ነሓሴ 7 ቀን 2014 ዓም(13-08-2022)
ዕድሜ ለሸጋው አማርኛ ቋንቋችን እንጂ ብዙ ትምህርትና ምክር የምንቀስምባቸው፣በተግባር የተፈተኑ አባባልና ምሳሌዎች አሉን።እነዚህ ትምህርተ ጥቅሶች ለበጎ፣ለመጥፎ፣ ለደስታ፣ ለሃዘን፣ ለምስጋና፣ ለወቀሳ፣ ፣ለምክር---ወዘተ የምንጠቀምባቸው ባለብዙ ትርጉም እሴቶቻችን ናቸው።ዕድሜ ቋንቋውን ከፊደል ጋር አዛምደው ላወረሱን አያት ቅድመአያቶቻችን ይሁንና ከሞላ ጎደል በተግባር ስንተረጉማቸውና ስንጠቀምባቸው ኖረናል።የዚህ ዕርእስ ሆኖ የቀረበው ምሳሌ የዚያው ቁም ነገር ገላጭ የሆኑት አባባሎቻችን አካል ነው።
እንደሚታወቀው ዕድሜ ጠገብ የሆነ፣ግዙፍና ግንደ-ሥሩ የተስፋፋ ዛፍ በትንሿ ምሳር ወይም ጥልቆ ተገዝግዞ ይወድቃል።በዚህ ተገዝግዞ በወደቀው ዛፍ ምሳሌ አድርጌ የወሰድኩት የኮሶ ዛፍ ነው።ኮሶ ጣዕመ መራራ ቢሆንም በስሙ ለተሰዬመው ለሆድ ትላትል ማሶገጃ መድሃኒት ይሆናል።ያ ሊሆን የሚችለው ኮሶ በአግባቡ ለጥቅም ለመዋል በሚያስችል መጠን ሲዘጋጅ ብቻ ነው።አለያ መርዝ ይሆንና ከመምረሩ በላይ የጥፋት ምክንያት ይሆናል።
ይህንን የኮሶ ዛፍም ሆነ ሌላውን ዋርካ ግንድ በመጠን ትንሽ የሆነችው ምሳር (ጥልቆ) ገዝግዛ ትጥለዋለች።በመጠን በልጣ ሳይሆን ስለታማ በመሆኗ ነው።ምሳሯ ብቻዋንም ግንዱን አትጥልም፣ከምሳሯ ስለት ጋር የተቀናጀ የዛው የዛፉ ዘር የሆነው እጀታውና የሁለቱም ፈጣሪና አዛዥ የሆነው የሰው ጉልበትና እውቀት ሲጨመርበት ነው።ሰው ያለምሳር ምሳርም ያለእጀታና ሰው ትልቁን ዛፍ ቀርቶ ቅርንጫፉን አይደፍሩትም፤የሁሉም የተቀናጀ ትብብር ያስፈልጋል።
ይህንን ምሳሌ ወደ ሕብረተሰብ ስንተረጉመው ላለበት ችግር መፍትሔ ለመፈለግ የግድ እንደምሳሯ ወይም ጥልቆዋ ስለት(ራዕይ) ያለው በሳል አመራር ፣የአመራሩ እጀታ የሚሆነው ድርጅትና፣ ጉልበት የሚሆነው የሰው ወይም የሕዝብ ድጋፍ ሊኖረው ይገባል።እነዚህን አጣምሮ ያልያዘ ሕብረተሰብ ከሚያስበው ቦታና ግብ አይደርስም።ሊያሶግድ የሚፈልገውንም ጸረ ሕዝብ ሥርዓት ሊገረስስ አይችልም።
ከዚህ ስንነሳ በአገራችንና በሕዝባችን ላይ በኢሕአዴግና በብልጽግና ስም ላለፉት 32 ዓመታት የተጫነውን የጎሰኞች ሥርዓት እንደኮሶው ዛፍ ብንወስደው ስርዓቱን ለመጣል ብዙ ተሞክሯል፣ግን ሊወድቅ አልቻለም።ያልወደቀበት ምክንያቱ ደግሞ እንደምሳሩ ስለት(ራዕይ) ያለው አመራር፣ድርጅትና የተባበረ የሕዝብ ድጋፍ ባለመኖሩ ነው። በዚህም ድክመት የተነሳ ጎሰኞቹ ስምና ወንበር እዬቀያዬሩ የተነሱበትን አገር የማጥፋት ጉዞ ቀጥለውበታል።ሕዝቡም እዚያና እዚህ በቅጡ ባልተደራጀና ባልተያያዘ መልኩ ትግሉን ማካሄድና መስዋዕት መክፈሉን አላቆመም።ከአራት ዓመት ወዲህ በተረኝነት ሥልጣኑን የያዘው የኦሮሙማው ቡድን የድርጅቱን አርማ የሆነውን የኮሶ ዛፍ በባንዲራው ላይ ለጥፎ፣የድልና የነጻነት ምልክት የሆነውን ባለታሪኩን አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ቀዶ በምትኩ የራሱን ባንዲራ በሁሉም ቦታ ለማንጠልጠልና አገዛዙን በተረኝነት ለማስፈን ሲዳክር ቆይቷል።ብዙ ኢትዮጵያንንም ገሏል፣ጨፍጭፏል፣አፈናቅሏል።አሁንም በዚያው የወንጀል አድራጎቱ ቀጥሎበታል።አልፎ አልፎ በአድር ባዮችና ከሃዲዎች እዬታገዘ የሌሎቹን ማህበረሰቦች ማንነትና የሚኖሩበትን አካባቢ ነጥቆ ለመውሰድ ያልሸረበው ሴራ የለም።አንዳንዶቹንም በመክበብ ለመዋጥ ከሚችልበት ደረጃ ላይ ነው።እዬቦረቦረ ማመናመኑን ተያይዞታል።በአዲስ አበባ ዙሪያና በሌሎቹ ጥቃቅን የክልል አስተዳደሮች ላይ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ለመዋጥ የሚያደርገው ዘላቂ ዓላማ መንደርደሪያ ነው። ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፈልጉት የውጭ ሃይሎችም ለዚሁ እኩይ ሴራው ተባብረውታል።
በዚህ የሞት የሽረት ትግል ባልታሰበና ባልተጠበቀ ጊዜ የኦሮሙማው አገር አጥፊ ቡድን እንደ ምሳሯና እጀታው የተባበረ ሕዝባዊ ተቃውሞ በጉራጌው ማህበረሰብ በኩል ገጥሞታል።የጉራጌን ማህበረሰብ ነጣጥሎ ለመምታትና ለመዋጥ ብሎም ማንነቱን ለመግፈፍ ያደረገው ሴራ እንዳይሳካለት ሕዝቡ ተባብሮ የራሱን ማንነት በክልል ደረጃ ለማስከበር ባደረገው ያጭር ጊዜ የተቀናጀ ትግል ወራሪና ጨፍጫፊው የኦነግ ኦሕዴድ ቡድን በሕዝብ ተቃውሞ ይዞት የመጣው እንደ ኮሶ የሚመር የፖለቲካ መርዛማ ውሳኔ ወግድ ተብሏል። የሕዝቡ ትግል ወጣትና ያገር ሽማግሌዎች ብቻም ሳይሆኑ የብልጽግና ተወካዮች፣አባላትና ደጋፊዎች ፣ሳይቀሩ የተሰጣቸውን የሹመት ቦታ ና አባልነት እዬጣሉ ከሕዝባዊ ትግሉ እንዲቀላቀሉ አድርጓቸዋል።ይህ የተቀናጀ የሕዝብ እምቢተኝነት ትግልና ያገኘው ውጤት ለሌላው ቀሪ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም በብዛትም ፣የስቃይና መከራ ኑሮ በመግፋት ብዙ በደልና መስዋዕትነት ለከፈለው ለአማራው ሕዝብ ትልቅ ምሳሌና ትምህርት ሰጪ ነው።በጉራጌ ቆራጥ ሕዝብ ኦነግ ኦሕዴድ ደፍሮ እተክለዋለሁ ያለው ባለኮሶ ዛፍ ባንዲራ ተቀዳዶ ወድቋል።ይህ የትግል ውጤት ለቀጣዩ ትልቅ ድል መንደርደሪያ ነው።የክልል ጥያቄና አወቃቀር የማይደገፍ ቢሆንም በዚያ ዙሪያ የታዬውን የሕዝብ አንድነትና ቆራጥነትን በማድነቅ ወደ ወሳኙና ከፍ ያለ እርከን ወደ ኢትዮጵያዊነቱ ደረጃ እንዲሸጋገር ማድረግና መደገፍ ከሁሉም አገር ወዳድ ይጠበቃል።በወልቂጤ ከተማ የታዬው የተባበረ ሕዝባዊ እምቢተኝነት በተለያዩ ያገሪቱ ክፍሎች በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ መቀጣጠል ይኖርበታል።የተንዘራፋውን መራራ አገዛዝ እንደ ኮሶ ዛፉ ገዝግዞ የሚጥል ስለት ያለው ሕዝባዊ ግንባር መመሥረት የግድ ይላል።የጉራጌ ተወላጆች ወገኖቻችንን እንደምሳሌ አድርጎ መውሰድና ከጎናቸው መቆም ለነገ የማይባል እርምጃ ነው።ለዘላቂ የጋራ ድሉም ዋስትና ነው።
የጉራጌ ተወላጆች በኢትዮጵያዊነታቸው የማይጠረጠሩ፣ለኢትዮጵያ አንድነትና እድገት ከፍተኛ ድርሻና አበርክቶ ያላቸው፣ የሥራ፣የጥንካሬና የመዋደድ ብሎም የመረዳዳት ምልክት ናቸው።የጉራጌ ተወላጅ ያረገጠውና ያልኖረበት የኢትዮጵያ መሬት የለም፣የሁሉንም ባህል፣እምነትና ኑሮ በቅርበት ያዬና የተካፈለ፣የተዋለደ ሕዝብ ነው።ይህ ታሪካዊ አብሮነታቸው ለኢትዮጵያ አንድነትና ለኢትዮጵያዊነት መከበር የጥንካሬ መግለጫ ነው።አሁንም በጀመሩት የትግል ጉዞ ያንኑ ሊያረጋግጡበት ይችላሉ።
በሁሉም የሕዝብ ትግል ውስጥ ሰርገው የሚገቡ ከኢትዮጵያዊነት ሃዲድ ውስጥ የሚያስወጡ አሳሳቾች መኖራቸው ስለማይቀር የጉራጌ ማህበረሰብም በነዚህ ከይሲዎች ላለመታለልና በጠባብ የክልል እይታ ተወስኖ እንዳይቀር ተጠንቅቆ ትግሉን ለትልቁ አገራዊ ጥያቄ፣ለኢትዮጵያ ልዑላዊነትና አንድነት እንደሚያደርገው እተማመናለሁ።የትግሉ መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ ጎሰኝነትን መታገልና ማሶገድ ነው።ለዚያም የጎሰኞቹን አገራዊ የክልል አወቃቀርና ድርጅታዊ ተቋማትን ፣ኢሕአዴግ /ብልጽግና የፈለፈላቸውን መዋቅሮችና በሕገመንግሥት ስም የጫኑትን የጥፋታቸውን ሰነድ ማሶገድ ነው።
የሕዝብ ትግል ያሸንፋል!ኢትዮጵያዊነት ከጎሳና ከክልል በላይ ነው!!
አገሬ አዲስ
https://amharic-zehabesha.com/archives/176574
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment