Monday, January 1, 2024

ብፁዕ አባታችን አቡነ ሉቃስ ይፍቱን!
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

የሉቃስ ወንጌል 12፡4 “ለእናንተም ለወዳጆቼ እላችኋለሁ፤ ሥጋን የሚገድሉትን በኋላም አንድ የሚበልጥ ስንኳ ሊያደርጉ የሚችሉትን አትፍሩ፡፡ እኔ ግን የምትፈሩትን አሳያችኋለሁ ከገደለ በኋላ ወደ ገሀነብ ለመጣል ስልጣን ያለውን ፍሩ፡፡” ይላል፡፡

መጣፉ “ሥራ የሌለው እምነት የሞተ ነው!” የሚለውን ተከትለው በዚህ ዓመት እምነታቸውን በግብር በማሳየት ላይ ያሉትና የቅዱስ ሉቃስን ሥም የወረሱት አቡነ ሉቃስ ከላይ በቅዱስ ሉቃስ ቁልጭ ብሎ የተቀመጠውን የመጣፍ ቃል በተግባር እያሳዩ ነው፡፡ አቡነ ሉቃስ ሥጋን የሚገድሉትን ንቀው ከገደለ በኋላ ገሀነብ ሊከት የሚችለውን አንዱን አምላክ ወይም ክርስቶስን እየፈሩ ነው፡፡ ሳጥናኤልን የፈራ ክርስቶስን የናቀ ነው፡፡ ክርስቶስን የፈራ ደሞ ሳጥናኤልን የናቀ ነው፡፡ ከሳጥናኤል ጋር ቆሞ ወይም ለሳጥናኤል ተላላኪ ሽማግሌ ወይም ግብር ገባሪ ሆኖ ክርስቶስን እወዳለሁ ማለት ሰው ከመግድልም የከፋ ኃጥያት ነው፡፡

“ጽንሱ ሲያድግ ነፍጠኛ ይሆናል” በሚል እርኩስ መንፈስ ሰክሮ የእርጉዝ ሆድ ቀዶ ጽንስ የሚገድል በደፈናው የሚታወቀው ሳጥናኤል ሳይሆን በሐሺሺ ጥንብዝ ብሎ የሰከረው ቀንዳም ሳጥናኤል ነው፡፡ አማራን በርሃብ እንጨርሰው በሚል ለፍቶና ማስኖ ያዘመረውን አዝመራና ክምር በእሳት የሚያቃጥል፣ ከብቶቹን በጥይት የሚገድል ባለ ቃልቻው ሳጥናኤል ነው፡፡ በሕዝብ ግብር በተገዛ ድሮን ሕዝብን የሚጨፈጭፍ ጭራቅ ቀንዳሙ ሳጥናኤል ነው፡፡ ሰውን በዘሩ እየለየ የሚጨፈጭፍ፣ ቤቱንና የእምነት ቦታውን የሚያቃጥል፣ የሚያሰድድ፣ የሥራና የትምህርት እድል የሚከለክል ከርስቶስን ከተራራ ላይ ሰቅሎ ሊፈትነው ተሞከረውም የከፋው ባለዛሩ ሰይጣን ነው፡፡

ከሰላሳ ዓመታት በላይ በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ የወደቀባት ሳጥናኤል እነዚህን ፋሽሽቱ ጣሊያን እንኳን ያለደረጋቸውን ወንጀሎች የፈጠመ ነው፡፡ አቡነ ሉቃስ ድል የነሱት ይኸንን ሰይጣን ነው፡፡ አቡነ ሉቃስ ይኸንን መፈራት የሌለበትን ቀንዳም ሰይጣን በመስቀላቸው ደልዘው መፈራት ካለበት ከክርስቶስ ጉያ እንደገቡ የሰሩት ሥራ ምስክር ነው፡፡ እንደ አለመታደል ሌሎች ጳጳሳት ግን አሁንም ከዚህ ሰይጣን ጉያ ተለጥፈው ይኸንኑ ሰይጣን አንዴ ተቃውሞውን በማርገብ ሌላ ጊዜም “ሽማግሌ” በመሆን እያገለገሉት ነው፡፡ የክርስቶስን መስቀል ጨብጦ እንደዚህ ዓይነቱን ቀንዳም ሰይጣን ማገልገል የኃጥያቶች ሁሉ ቁንጮ ነው፡፡

“ሥጋን የሚገድሉትን በኋላም አንድ የሚበልጥ ስንኳ ሊያደርጉ የሚችሉትን አትፍሩ፡፡” የሚለው ትእዛዝ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ እንደዚህ ዓይነት ሰይጣን እንደሚመጣ የተነበየ ይመስላል፡፡ “በኋላም አንድ ስንኳ የሚበልጥ ስንኳ ሊያደርጉ የሚችሉትን...” የሚለው ሐረግ ላይ ብናተኩር በኢትዮጵያ ላይ በገዥ መልክ የሰነፈነው ሰይጣን ሥጋ ከመግደል እንኳ የሚበልጥ አሰቃቂ ወንጀል ሰርቷል፡፡ የአማራ ዘር ለማጥፋት ሴቱንም ወንዱንም አምክኗል፡፡ ሰው ከገደለ በኋላ ዘቅዝቆ ሰቅሏል፣ አንገቱን ቆርጧል፣ በእሳት አቃጥሏል፣ በግንዲደር እየዛቀ ተአፈር ጨምሯል፣ መሬት ለመሬት ጎትቷል፣ ወደ ገደልም ወርውሯል፡፡ ይኸ ሰይጣን ዛሬ እመነታቸውን በሥራቸው ባስመሰከሩት አቡነ ሉቃስ በግልፅ ተገስጿል፡፡

ከመጽሐፈ መነኮሳት አንዱ የሆነው ማር ይስሐቅ ገፅ 106 ላይ “አቡነ” ኤርምያስ ስሙን የዘረፉትን ቅዱስ ኤርምያስን ከጠቀሰ በኋላ “ እግዚአብሔር ሳንፈራ ሳንበርድ ጸላታችንን (ሳጥናኤልን ማለቱ ነው) እንገጥመው ዘንድ ያዝዛልና” ብሎ “ሳይቀድምህ ቅደመው...ትወጋው ዘንድ መር ብለህ ቁንጮውን ያዘው”* እያለ ያዝዛል፡፡ ምንኩስናቸው የሚያዝዛቸው አቡነ ሉቃስ መስቀላቸውን ይዘው ሳይፈሩ ይኸንን ቀንዳም ሳጥናኤልን ገጥመውታል፡፡ የሳጥናኤልን ሥራ የሚጠላ ሰው ሁሉ ከአቡነ ሉቃስ ጀርባ ሊሰለፍ ይገባል፡፡ ሳጥናኤልን ማገልገል ብቻ ሳይሆን ሳጣናኤልን በመፋለም ላይ ካሉት አባቶች ጀርባ አለመቆምም በሰማይ ቤት በመለኮት፤ በምድር በታሪክና በትውልድ ሲያቃጥል ይኖራል፡፡

አቡነ ሉቃስ ሆይ፡- የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአያሌ ዘመናት በእውነተኛ አባት ጥማት መንፈሱ እንደ በጋ ምድር ተሰንጥቆ ኖሯል፡፡ በምድር ጠብ የሚል የእውነተኛ አባት ዝናብ ጠፍቶ በሰማይ ያሉትን እነ አቡነ ጴጥሮስን፣ አቡነ ሚካኤልና መላከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬን እያነሳ ጉረሮን ለማርጠብ ጥሯል፡፡ በመጨረሻም አቡነ ሉቃስ የሚባል ዝናብ ወርዶ በውስጥም በውጪም ያለው ኢትዮጵያዊ በዋንጫ እየገደበ እየጠጣው ይገኛል፡፡

የእኒያ በአድዋ ታቦታቸውን ተሸክመው ጣሊያንን ያርበደበዱት ካህናት አምላክ፣ የእኒያ ምድሪቱም ሕዝቡም ለሳጣናኤል እንዳይገዙ ገዝተው ሰማእት የሆኑት የአቡነ ጴጥሮስ አምላክ፣ የእኒያ ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ወጥተው ጣልያንን በሚኒሽር ያርበደበዱት እንደነ አባ ገብረየሱስ ያሉ መነኮሳት አምላክ፣ የእኒያ በአምስቱ ዘመን ፋኖዎችን እያደራጁ የእምነት ቦታቸውን ከመርከስ፣ ሕዝቡን ከባርነት ያወጡት የእነ መላከ ብርሃኑ አድማሱ ጀምበሬ አምላክ ዛሬም “የእርጉዝ ሆድ ለሚቀድ ሳጥናኢል አትገዙ!” ብሎ የሚገዝት አባት ስለሰጠን ለዘላለም ይመሰገናል፡፡ በአንጻሩ ሳጥናኤል አገሪቱን ሲያረክስና የደም አበላ ሲያደርግ ከሳጥናኤል ጋር የቆምን አለዚያም ያላዬ ያልሰማ መስለን እንደ ቅንቡርስ በልተን ለመሞት የቆረጥን ሆድ አምላኪዎች ብዙ ስላልን በያዙት መስቀል ጭንቅላታችንን ወቅረው ይኸንን የሆድ ቃልቻ አስጎርተው እንዲያስወጡልን ለምነናል፡፡

እምነትን ከሥራ ያዋሃዱ አባቶች ተጠምተን “ይፍቱን” እንኳ ሳንል ብዙ ዓመታት አሳልፈናል፡፡ እግዚአብሔር ምስጋና ይግባውና ዛሬ አባት ስላገኘን አቡነ ሉቃስ ይፍቱን ብለናል፡፡

እግዚአብሔር ሆይ! ኢትዮጵያን ከሳጥናኤል አላቀህ እንደ በፊቱ “የተናገርኩት ከሚጠፋ የወለድኩት ይጥፋ” በሚሉ ሽማግሌዎችና እምነትን ከሥራ በሚያዋህዱ የሃማኖት አባቶች ዳግም ትሞላት ዘንድ፣ እነ አቡነ ሉቃስም በእምነታቸው ጸንተው የበለጠ ብርታትን ያገኙ ዘንድ ጸሎታችንን ቀጥለናል፡፡ አሜን፡፡

 

*መጻሕፍተ መነኮሳት ማር ይስሐቅ ገጽ 106  ብርሃንና ሰላም እትም 1929 ዓ.ም

 

ታህሳስ ሁለት ሺ አስራ ስድስት ዓ.ም.

 

 

https://youtu.be/RlwtciRfhGs?si=fR66u2i5Vo6uryye
https://amharic-zehabesha.com/archives/187969

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...