Tuesday, January 2, 2024
ጥር 02፣ 2024
ዶ/ር መስፍን አረጋ በዮናስ ብሩ ላይ ያለውን ቅሬታ “ዮናስ ብሩ፣ የጭራቅ አህመድ አዛኝ ቅቤ አንጓች “ በሚለው አርዕስት ስር በታህሳስ 17፣ 2023 በዘሃበሻ ድረ ገጽ ላይ ያወጣውን ጽሁፉን ፣ በተለይም የእስክንድር ነጋንና የሻለቃ ዳዊትን ስም “ለማጥላላት” ያደረገውን ሙከራ የሰጠውን መልስ አነበብኩት። ዶ/ር ዮናስ ብሩ የሁለቱን ግለሰቦች ስም ሲጠቅስ ከምን የፖለቲካ ርዕይ በመነሳት እንደወነጀላቸው በፍጹም ግልጽ አላደረገም። የራሱንም የፖለቲካ አቋም ወይም የፖለቲካ ርዕይና ፍልስፍና ምን እንደሆነ በፍጹም አላስታወቀም። የቀኝ፣ የግራ፣ የኮሙኒስት፣ ወይም የሶሻሊስት፣ የሊበራል፣ የኮንሰርቫቲቭ ወይም ሌላ የፖለቲካ አመለካከት እንዳለውና እነሱ ያራምድሉ ብሎ ከሚገምተውና ከሚያስበው ጋር በማገናዘብ ሲተቻቸው አይታይም። በሌላ ወገን ግን ግለሰቦችን በትዊተር ዝም ብሎ እንደጠየቀና በተለይም አብዛኛዎቹ ስለእስክንድር የሰጡት መልስ “እንደሚያምኑትና የፀና አቋምም እንዳለው፣ ራሱን ለመሰዋት የተዘጋጀ፣ እንደ ማህተመ ጋንዲ ያለ፣ የሚከበር፣ ጀግና፣ ሀቀኛና ታላቅም እንደሆነ” እንደተናገሩ ነው ዮናስ ብሩ የሚነግረን። ይህ ዐይነት አጠያየቅ ተገቢ ነው ወይም ተገቢ አይደለም የሚለውን ወደ ጎን በመተው በመሰረቱ በዮናስ ብሩም ሆነ በሻለቃ ዳዊት መሀከል ይህንን ያህልም የሃሳብ ወይም የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት ያለ አይመስለኝም። ዮናስ ብሩም ሆነ ሻለቃ ዳዊት “በአሜሪካን የበላይነት፣ በሊበራል ዲሞክራሲ አስተሳሰብና ዲሞክራሲን በዓለም አቀፍ ደራጃ አራማጅነትና፣ ለሰላም መቆም” እንደሚያምኑ ግልጽ ነው። በሌላ አነጋገር፣ አሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረአበሮቹ ዓለምን ለመግዛትና በተለይም የሶስተኛውን ዓለም የጥሬ ሀብቶችን ለመቆጣጠር የሚያስፋፉትን የነፃ ንግድ ፖሊሲ፣ በመሰረቱ ፀረ-ሳይንስና ፀረ-ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም የተሟላ ዕድገት ተቀናቃኝ የሆነውንና የዓለም ማህበረሰብ በሙሉ በአንድ ወጥ ህግ ወይም ደንብ መሰረት(Rules Based Order) መመራት እንዳለበት ጫና የሚደረገውን ይህንን በመቃወም ዮናስ ብሩም ሆነ ሻለቃ ዳዊት አንዳችም ቦታ ላይ ሀተታና ትምህርታዊ ጽሁፍ በመጻፍ አላስነበቡንም። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በተለይም አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ነፃ ወጡ ከተባለበት ከ1960ዎቹ ጀምሮ የተሳሳተ ወይም ኢ-ሳይንሳዊ የሆነና፣ ወደ ውስጥ ያተኮረንና የተስተካከለና የተሟላ ዕድገትን የማያመጣውን በተለያዩ ጊዜያት የተለያየ ስም የያዙ በመሰረቱ በይዘት አንድ የሆኑ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ብለው የሚጠሩትን በዓለም ኮሙኒቲው ተገደው ያደረጓቸው የቱን ያህል ዛሬ እንደምናየው በሁሉም አቅጣጫ የሚገለጽ መቀመቅ ውስጥ እንደከተታቸው በመጻፍና ሰፋፊ ሀተታዎች በመስጠት አላስነበቡንም።
ከእነዚህ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ውስጥ አንዱ አገር አፍራሽና ባህልን አውዳሚ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ “የተቋም መስተካከያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ” (Structural Adjustment Programs) በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህም ፖሊሲ የአፍሪካ ኢኮኖሚስቶችና የሳይንስ ሰዎች በ1980 ዓ.ም በሌጎስ ከተማ ላይ በመገናኘት ከብዙ ቀናት ጥናትና ውይይት በኋላ የደረሱበትና፣ አህጉሩንም ካለበት ቀውስ ሊያወጣው ይችላል ብለው ያመኑበትን „The Lagos Plan for Action“ ብለው ያወጡትን በመቃወም የወጣ መሆኑ ይታወቃል። የአፍሪካ መንግስታትም ይህንን የአፍሪካ ምሁራን ያወጡትን ሳይሆን የግዴታ “የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው” የሚለውን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ጭነት እንደተደረገባቸው የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ቀደም ብሎ ከዘይት ዋጋ መወደድ ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዶላር መትረፍረፍና የፋይናንሺያል ገበያው በገንዘብ መደለብ የተነሳ የአፍሪካን አገሮች ቀስ በቀስ የዕዳ ወጥመድ ውስጥ እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ፣ የተቋም ፖሊሲው ሲካተትበት እነዚህ አገሮች የባሰ የዕዳ ወጥመድ ውስጥ እንደገቡ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። በዕዳ የተበተቡ የአፍሪካ አገሮች ዕዳውን ማሸጋሽግ(Debt Rescheduling) አለባቸው እየተባለ እንደገና ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ገንዘብ በመበደርና ዕዳውን በመክፈል የወለድ ወለድ(Compound Interest) እንዲከፍሉ በመገደድ ከዕዳ ወጥመድ ውስጥ ለመላቀቅ እንዳልቻሉ እንመለከታለን። ይህንንና ሌሎችንም ጉዳዮች በሚመለከት የአፍሪካ አገሮችና የአገራችንም ተቆርቋሪ በመሆን ሁለቱም ምሁራን በዝርዝር ለንባብ ያቀረቡት አንዳችም ጽሁፍ የለም። ከዚህም በላይ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በእስላም አክራሪዎችም ሆነ የጥሬ-ሀብትን ለመቀራመት የሚካሄደው የርስ በርስ ጦርነት የውክልና ጦርነት ወይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በቀጥታ እጁ እንዳለበት እየታወቀ አንዳችም ሀተታ ወይም ጥናታዊ ጽሁፍ ከዮናስ ብሩም ሆነ ከሻለቃ ዳዊት የቀረበ ነገር የለም። ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በ2918 ዓ.ም “በጦርነት የምትማምቀው አፍሪካ” በሚለው አርዕስት ስር የጻፈውን ካነበቡኩኝ በኋላ ወደ 18 ገጽ የሚጠጋ ትችታዊ ጽሁፍ ለንባብ በማቅረብ ካነበቡት ውስጥ ሁሉም በጽሁፍ ሚዛናዊነትና ትክክለኝነት እንደተደሰቱ ገልጸውልኛል። በእኔ ዕምነትና የፀና አቋም በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት በሙሉ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ እንደሚለው የአፍሪካውያን ሳይሆን የአሜሪካኖችና የአውሮፓውያን ነው የሚል ነው። ጽሁፉን በቀጥታ የድረ-ገጼ ውስጥ በመግባት ልዩ ልዩ ጥናቶች በሚለው ስር ማግኘት ይቻላል።
በተጨማሪም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በኢትዮጵያ ላይ የተጫወተውን አገር አፍራሽ ሚና፣ እንዲሁም ወያኔንና ሻቢያን ስልጣን ላይ በማውጣት የጎሳ ፌዴራሊዝም ተግባራዊ እንዲሆን ግፊት ስለማድረጉና፣ ይህንንም አማራጭ የሌለው መፍትሄ እንደሆነ አዲስ አበባ የነበረው የአሜሪካን አምባሳደር እንዳበሰረ ይህንን አስመልክቶ ከዮናስ ብሩም ሆነ ከሻለቃ ዳዊት አንዳችም መግለጫና ሀተታ በፍጹም አልተሰጠም። ወያኔና ሻቢያ አዲስ አበባ ከመግባታቸውና ስልጣንን ከመረከባቸው በፊት ወያኔ፣ ሻቢያና ኦነግ በኸርማን ኮኸን ሰብሳቢነትና መሪነት ለንደን ላይ እንደተሰበሰቡና ኢትዮጵያን በጎሳ ፌደራሊዝም ስለመሰነጣጠቁ ጉዳይና፣ ይህንንም ተግባራዊ ስለመደረጉ ጉዳይ፣ ወያኔም ይህንን ሲቀበል ብቻ ስልጣን ላይ መውጣት እንደሚችልና፣ ይህም እንደቅድመ ሁኔታ እንደቀረበለት እየታወቀ ይህንን አስመልክቶ ከሁለቱም ግለሰቦች አንዳችም ተቃውሞና ሀተታ በፍጹም አልተሰጠም። በሁለቱ ግለሰቦች የጎሳ ፌዴራሊዝም ማርቀቅና ተግባራዊ ማድረግ የወያኔ አሻጥር ስራ ብቻ ነው ተብሎ በሁለቱም ግለሰቦች የታመነው።
ወያኔም አገርንና ባህልን አውዳሚ፣ እንዲሁም ሰፊውን ህዝብ ወደ ድህነት የሚገፈትረውንና የገፈተረውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን(Structural Adjustment Programs) አስመልክቶ ከዮናስ ብሩም ሆነ ከሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ይህንን የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን አሉታዊ ሚናና አገርን በሁለመንታዊ ጎን የሚያፈራርስ የኢኮኖሚ ፖሊስ ብለው የሚጠሩትን፣ በመሰረቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ያለሆነን፣ ይህንን አስመልክቶ ምንም ዐይነት ሀተታና መግለጫ በፍጹም አልሰጡም። ወያኔ ስልጣን ላይ ከመውጣቱም በፊት ሆነ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ተግባራዊ ያደረጋቸው “ፖለቲካዎችና የኢኮኖሚ ፖሊሲ” በሙሉ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ዕውቅና ውጭ ናቸው የሚል አስተሳሰብ በሁለቱም ዘንድ ሲንፀባረቅ ይታያል። የወያኔም ፖለቲካ፣ ፖለቲካ ካልነው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚያስፋፋው ኢ-ዲሞክራሲያዊና የጦረነት ፖሊሲ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ለመሆኑ ለሁለቱ ምሁራን ግልጽ የሆነላቸው አይመስልም። ስለሆነም በሁለቱ ግለሰቦች መሀክል ይህንን ያህልም የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት በፍጹም አላይም። በሌላ ወገን ግን የዮናስ ብሩን ተገቢ ትችት በተለይም ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ “ኢትዮጵያ የአማራ ነች... ኢትዮጵያን እዚህ ያደረሳት አማራ ነው” በመቀጠልም ”ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት አማራ አማራ የሚሸት መንግስት ነው” የሚለው አነጋገር ፖለቲካዊ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛ አባባልም ለመሆኑ አምንበታለሁ። በእርግጥ በአማራው ላይ የደረሰው በደልና አሁንም የሚፈጸምበት ውርጅብኝ ሁላችንንም ቢያሳስበንምና የግዴታም ይህ ዐይነቱ ፋሺሽታዊ አገዛዝ በአስቸኳይ ከስልጣን እንዲወርድ ብንታገልም እንደዚህ ዐይነቱን ፖለቲካዊ ያልሆነና በህብረተሰብ ግንባታ ሂደት ውስጥ ትክክል ያልሆነን አባባል ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ለራሱ ለአማራው ብሄረሰብ የሚጠቅመው አይደለም። ለግለሰብ ነፃነትና ለህግ-የበላይነት መከበርና ለጠቅላላው ህዝብም የሚጠቅም ዕድገት በአገራችን ምድር ዕውን እንዲሆን እንታገላለን የምንል ከሆነ የግዴታ አካሄዳችንና አጻጻፋችን በሙሉ ኢትዮጵያ የሁሉም ብሄረሰቦች አገር እንደሆነችና፣ ሁሉም በመከባበር አዲስና የተከበረች ኢትዮጵያን መገንባት እንዳለባቸው ማስተማር አለብን። እስላሙም ሆነ ክርስቲያኑ፣ ከዚኸኛው ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ የሚወለድ በሙሉ በአንድነት በመነሳት በጋራ አገራቸውን መገንባት አለባቸው የሚል የፀና ዕምነት አለኝ። አንዱ የሌላውን ሃይማኖት ሲያከብርና፣ በተለያዩ ብሄረሰቦች መሀከልም መከባበርና መፈቃቀር ሲኖር ብቻ ነው በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚደገፍ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ሊጠቅም የሚችል ሁለ-ገብ ኢኮኖሚ መገንባት የሚቻለው። ለዚህ ዋናውና ተቀዳሚው ቅድመ-ሁኔታ ደግሞ በአገራችን ምድር የሰላም መስፈንና በብሄረሰብ ላይ የተመሰረተ የጎጠኝነት አስተሳሰብ ሲወገድ ብቻ ነው። ባጭሩ ዘመኑ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዘመን እንደመሆኑ መጠን፣ በተለይም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገሮች ከዜሮ በመነሳት የሚሰሯቸው አያሌ የስልጣኔ ስራዎችና የአገር ግንባታ ተልዕኮዎች ስላሏቸው ማንኛውም በአማራ ስም የሚነግድ ግለሰብም ሆነ ቡድን ከእንደዚህ ዐይነቱ ጎጂና ከፋፋይ አስተሳሰብ መራቅ አለበት። አስተሳሰባችን ሁሉ በስሜት ላይ የተመረኮዘ መሆን የለበትም። በሰለጠነና በአርቆአስተዋይነት መንፈስ ስንመራ ብቻ ነው በአገራችን ምድር ሰላምን ማስፈንና አገርን መገንባት የምንችለው።
እስክንድር ነጋ ይህንን በሚመለከትና በሌሎች የዓለም አቀፍ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሰጠው ሀተታ ወይም ጽሁፍ ስለሌለ ለመተቸትም ሆነ አስተያየት ለመስጠት አልችልም። ያለበትም ሁኔታ በጣም አደገኛና አስቸጋሪ ስለሆነ በእሱ ላይ አስተያየት ከመስጠት ለመቆጠብ ተገድጃለሁ። በሁለቱ ግለሰቦች ላይ ያተኮርኩት በየጊዜው ለድረ-ገጾች መጣጥፎችን ስለሚያቀርቡ ነው። ይሁንና ግን እስክንድር ነጋ የህውሃትንም ሆነ የፋሺሽቱን የአቢይ አህመድን አገዛዝ ፋሺሽታዊና ከፋፋይ ድርጊቶች፣ እንዲሁም ህዝብን ከቤቱ እያባረሩ ሜዳ ላይ እንዲወድቅ ያደርጉ የነበረውን ፀረ-ህዝብ ድርጊታቸውን በመኮነንና በመዋጋት እንደተጋፈጣቸውና ለዚህም ቆራጥ ድርጊቱ ብዙ መንገላታት እንደደረሰበት የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ይህንን ሀቅ ይህ ፀሀፊ በሚገባ ይገነዘባል። የእኔ አስተያየትና የፀና አመለካከት ግን እነዚህ ዐይነት በህውሃትም ሆነ በአቢይ አህመድ የፋሺሽቱ አገዛዝ የተፈጸሙትና የሚፈጸሙት ፀረ-ህዝብና ፀረ-አገር ድርጊቶች በሙሉ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ከሚከተለው ዓለምአቀፋዊ የሶሻል ዳርዊንዝም ድርጊቶች ተነጥለው መታየት የለባቸውም የሚል ነው። በተለይም በግሎባላይዜሽንና በነፃ ንግድ ስም አሳቦ ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ ወይም ህዝባዊ ሀብት የማይፈጥር፣ ድህነትንም ሊቀርፍ የማይችልና የተስተካከለ የኢኮኖሚ ዕድገት በሁሉም አገሮች እንዳይዳብር ማድረግ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የተቀሩት የካፒታሊስት አገሮች ዋናው ዓላማ ሰለሆነ ይህንን በተጨባጭ የሚታይና ህዝብን ሰቆቃ ውስጥ የሚከተውን በቁጥር ውስጥ ሳያስገቡ ለአንድ አገርና ህዝብ ነፃነት እታገላለሁ ማለት ትልቅ ታሪካዊ ወንጀል እንደመፈጸም ይቆጠራል የሚል ዕምነት አለኝ። በተለይም ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ትላልቅ የኢትዮጵያ ከተሞች እንደ አሸን የፈለቁት የቆሻሻ መኖሪያ ቦታዎችና፣ ሰፊው ህዝባችንም በእንደዚህ ዐይነቱ ለዐይን በሚዘገንን ቦታዎች እንዲኖር መገደዱ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋናው መገለጫ መሆኑን መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ነው። እንደዚህ ዐይነቱ ህዝብን በቆሻሻ ቦታዎች ወይሞ በፓርኮችም ውስጥ እንዲያድር ማድረግ በአሜሪካንም ትላልቅ ከተማዎች፣ በተለይም እንደ ሎሰአንጀለስና ኒዎርክ በመሳሰሉት ከተማዎች የተስፋፋና በግልጽም የሚታይ ጉዳይ ነው። በሌላ ወገን በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎች መጠለያ አጥተው በየፓርኩና በየመንገዱ ሲያድሩ በባይደን የሚመራው የአሜሪካን መንግስት ዩክሬይንን በተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ለማስታጠቅና በሩሲያም ላይ ድልን መቀዳጀት አለባት በሚል ጦርነቱ ከተከፈተ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ወድ 44 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዝብ በዕርዳታ መልክስ ሰጥቷል። እንደዚሁም የጀርመን መንግስት 17 ቢሊዮን ኦይሮ ለዩክሬይን አገዛዝ በዕርዳታ መልክ ሰጥቷል። በአሁኑ ወቅት በሁለቱም አገሮች ውስጥ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ይታያል። ይሁንና በዚህ ዐይነቱ ጦርነትን ማፋፋም ስትራቴጂ ዩክሬይን በፍጹም ማሸነፍ እንደማትችል የታወቁ የሚሊታሪና የጦር ተንታኞች ይገልጻሉ። እንደምናየውም በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ንጹህ የዩክሬንያን ዜጎችና ወታደሮችም ጭምር በየቀኑ እየረገፉና ከተማዎችም እየወደሙ ነው። በአሁኑ ጊዜ ዩክሬይን የሚሰራና የሚንቀሳቀስ ኢኮኖሚ በፍጹም የላትም። ስለሆነም ህዝቡ በፍርሃት ስለተዋጠና የመኖር ዕድሉ የመነመነ ሰለሆነ ወደ አቃራቢያው አገሮች በተለይ ወደ ጀርመን እየፈለሰ ነው። ከዩክሬይንም ወደ ጀርመን የሚመጡትን ዜጎችን ለማስተናገድና የስራ ቦታም ለማሲያዝ እንደዚሁ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ኦይሮ የጀርመን መንግስት ያወጣል። በዚህ መልክ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስፋፋው ጦርነትና ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አብዛኛውን የዓለም ደሃ ህዝብ የሚጎዳ ብቻ ሳይሆን ከማንኛውም ህብረተሰብአዊ ስራዎችና ባህላዊ ክንዋኔዎች እንዲገለልና ሞራሉም በመሰበር እንደ ነፃ ዚጋ እንዳይቆጠር ከማድረግ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው፤ የሰብአዊ መብትንም በከፍተኛ ደረጃ የሚፃረር ድርጊት ነው። ይህ ዐይነቱ ሰፊውን ህዝብ ከቤቱ እያባረሩ ቆሻሻ ቦታዎች ላይ እንዲኖርና ከዚያው ምግብ እየፈለገ እንዲመገብ ማድረግ ትችታዊ አመለካከት ባላቸው የከተማ ዕቅድ አውጭዎችና የሶስይሎጂ ምሁራን የኒዎ-ሊበራል የከተማ ዕቅድ(Neo-Liberal Urban Project) በመባል ይታወቃል። ይህ ዐይነቱ የህንጻ አገነባብ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ በአንዳንድ ቦታዎች ሬል ስቴትና ስማርት ሲቲ በሚል ስም በመስፋፋት ሰፊውን ህዝብ ከመሀል ከተማ እያባረረና ወዳለመዱበት ቦታ እየሄዱ እንዲኖሩ እያስገደዳቸው ለመሆኑ በገሃድ የሚታይ ጉዳይ ነው። ይህ ዐይነቱ የሪል ስቴት አሰራር ኢ-ማህበራዊ፣ ኢ-ባህላዊ የሆነና እንዲሁም ብልግናና ሌሎች የውንብድና አሰራሮችን የሚያስፋፋ ነው። የህንጽ አሰራሩም እንደዘመናዊነት ይቆጠራል ቢቆጠርም ለዕውነተኛ ስልጣኔ የማይስማማና መንፈስንም የሚያድስ አይደለም። ይህ ዐይነቱ የህንጻ አሰራር በቀጥታ ከኒዎ-ሊበራሊዝም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ሲሆን፣ ከበስተጀርባውም ማን እንዳለበት ለማወቅ በጣም ያስቸግራል።
በሌላ ወገን ይህ ጸሀፊ ወያኔ በተለይም የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረመበት ጊዜ ጀምሮ አሉታዊ ሚናውን አስመልክቶ በተለያዩ አገር ቤትውስጥ በሚታተሙ መጽሄቶች ላይ፣ እንደ አውራምባ ታይምስና ጦቢያ፣ እንዲሁም በውጭ አገር በሚገኙ እንደ ኢትዮ-ሚዲያ፣ ሳተናውና ዘሃበሻ በሚባሉ ድረ-ገጾች ላይ በዝርዝር በመተንተን አንባብያን የነገሩን አደገኛነት እንዲረዱት ለማብራራት ሞክሯል። በተጨማሪም የነፃ ንግድ ፖሊሲን አስመልክቶና፣ በተለይም ኢትዮጵያ “የዓለም የንግድ ድርጅት” (WTO) አባል ለመሆን ያቀረበችውን ማመልከቻ በመቃወምና ምክንያቱን በማስረዳት በሰፊው ለማብራራት ሞክሯል። እንዲሁም በእንግሊዘኛ ቋንቋ ከሰላሳ ገጽ በላይ በሚሆን ሀተታ የነፃ ንግድ ፖሊሲን ጠንቅነትና፣ የማንኛውም በዚህ ስም የሚንቀሳቀስ ድርጅት አባል መሆን የሚያስከትለውን አሉታዊ የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ጠንቅ፣ እንዲሁም የሚያስከትለውን የባህል ውድመት ለማብራራት ሞክሬያለሁ። በተጨማሪም „African Predicaments and the Method of Solving them Effectively“ በሚለው መጽሀፌ ውስጥ የአፍሪካ አገሮች በዓለም አቀፍ ኮሙኒቲውና በአፈቀላጤዎቻቸው፣ ማለትም በዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) በዓለም ባንክ(World Bank) ተገደው ተግባራዊ ያደረጓቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ ወደ ውስጥ ያተኮረና በሳንይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራና ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ ማስገንባት እንዳላስቻላቸው ለማሳየት ሞክሬያለህ። ይህንንም ከካፒታሊስት አገሮች የኢኮኖሚና የአገር ግንባታ፣ እንዲሁም ከጃፓንና ከደቡብ ኮሪያ ሰፋ ያለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በማነፃፀር አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ተግባራዊ ያደረጓቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ የካፒታሊዝምን የኢኮኖሚ ዕድገት ህግና የውስጥ አሰራር ስልት እንደሚፃረር አመልክቻለሁ። እነዚህ ሁሉ ጽሁፎች ደረጃ በደረጃ www.fekadubekele.com በሚለው ድረ ገጽ ላይም በሚገባ ሰፍረዋል። ታዲያ ይህ ሁሉ ስራ የአገርን ህልውና እንደ መከላከል የሚታይና የፖለቲካ ትግልም አንዱ አካል አይደለም ወይ? ለፖለቲካ ስልጣን ትግል ሲካሄድ የነገሮችን ውስብስብነትና፣ በተለይም እንደኛ ባሉ አገሮች ስልጣን ላይ የሚወጡ አገዛዞች በራሳቸው አስተሳሰብና ፖሊሲ ለመራመድ እንደማይችሉና፣ ይህንንም በሰፊው በማተት ለአንባቢያን በጽሁፍም ሆነ በመጽሀፍ መልክ ማቅረቡ ዋናው የፖለቲካና የነፃነት፣ እንዲሁም የብሄራዊ ነፃነት ትግል ዋናው ተግባር ሊሆን አይችልም ወይ?
ወደ ዮናስ ብሩ መሰረታዊ አስተሳሰብ ጋ እንምጣ። ዮናስ ብሩ ስለፖለቲካል ራሺናሊቲ ሲነግረን ከምን አንፃር በመነሳት ይህንን ግዙፍ ፅንሰ-ሃሳብ እንደሚጠቀምና፣ ከእስክንድርም ሆነ ከሻለቃ ዳዊት፣ እንዲሁም ከሌሎች የሚለይበትንና ምን ዐይነትስ ፖለቲካል ራሺናሊቲ እንደሚጠብቅ ግልጽ አላደረግልንም። በአጠቃላይ የፅንሰ-ሃሳቡን አመጣጥ ስንመለከት በግሪክ ስልጣኔ ዘመን የፈለቀና በተለይም በአውሮፓ ምድር በ15ኛው ክፍለ-ዘመን በሬናሳንስ ጊዜ፣ በኋላ ደግሞ በ17ኛው ክፍለ-ዘመን በኢንላይተንሜንት እንቅስቃሴ ዘመን በተለይም ስለሰው ልጅ ባህርይና ስለ ዕውቀት አፈላለቅ ክርክር በሚደረግበት ዘመን ለፖሊተከኞች እንደመመሪያ እንዲወሰድ የዳበረ ትልቅ አስተሳሰብ ነው። ከዚህም በላይ የፖለቲካ ራሺናሊዝም ዲስፖታዊ አገዛዝን፣ ወይም የአንድን ግለሰብ የፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ በመቃወም ማንኛውም አገዛዝ በህግ-የበላይነት በመገዛትና የሪፓብሊካንን አስተሳሰብ በማስፋፋት ግለሰብአዊ ነፃነት መከበር እንዳለበት በታላላቅ ፈላስፋዎች ቅስቀሳ የተደረገበትና ቀስ በቀስም ተቀባይነት ያገኘ መሰረታዊ መመሪያ ነው። በዚህም መሰረት ስልጣን የያዘ ግለሰብ በሙሉ ስልጣን ያዝኩኝ በማለት መመፃደቅ ያለበት ሳይሆን ራሱም የህግ ተገዢ በመሆን ህዝብንና አገርን ማገልገል እንዳለበት የሚያሳስብ ነው። ራሺናሊዝም የሚለው ጽንሰ-ሃሳቡም ከሰብአዊነት(Humanism) ተነጥሎ መታየት የሌለበት መሰረታዊ ጉዳይ ሲሆን፣ ፅንሰ-ሃሳቡም ከፍትሃዊነት ጋር የተያያዘና ከጉልበት ይልቅ የጭንቅላትን ወይም በፍልስፍና ላይ የተመሰረተና ችግርን ፈቺ ሳይንሳዊ የአሰራር ጥበብን የሚያስቀድም ነው። ሰብአዊነት የሚለው አስተሳሰብ ደግሞ የሰው ልጅ ከእንስሳ የሚለይበት መገለጫ ሲሆን፣ የሰውን ልጅ አንቀው ከያዙት ልማዳዊ የአኗኗር ወይም የትንግርት ስልቶችና ከእልከኝነት በመላቀቅና አዕምሮውን ክፍት በማድረገና ለትችትም ዝግጁ በመሆን ለሁለ-ገብ ዕድገት እንቅፋት ከሆኑ ከኋላ-ቀር ስርዓቶችና አስተሳሰቦች በመላቀቅ በማሰብ ኃይሉ አማካይነት በሁሉም መልክ የሚገለጽ አዲስ የአኗኗር ስልት ማዋቀርና ከተማዎችንና መንደሮችን መንፈስን እንዳይረብሹ ሆነው ከተፈጥሮ ጋር በመያያዘ መሰራት እንዳለባቸው የሚያስተምር ታላቅ መመሪያ ነው። ይህ ዐይነቱ ዕድገትም በማቴሪያል ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን የሰው ልጅ መንፈሱንም በማጎልበስ እየተፈቃቀረና የተፈጥሮ ጠላት ሳይሆን የተፈጥሮ ጓደኛ በመሆን ከሞላ ጎደል ስምምነት(Harmonius) ያለበትን ህብረተሰብ መመስረት ማለት ነው።
ይሁንና ይህ ዐይነቱ ከሰብአዊነት ጋር የተያያዘው ራሺናሊዝም ወይም የአርቆ-አሳቢነት ፅንሰ-ሃሳብ ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት ከካፒታሊዝም ዕድገትና ዓለም አቀፋዊ ባህርይ መውሰድ ጋር ልዩ ዐይነት ባህርይ እየወሰደ ለመምጣት ችሏል። በተለይም የአውሮፓ የቅኝ ገዢዎች ይህንን ዐይነቱን የአርቆ-አሳቢነት መርሆ ለመከተል ባለመቻላቸው የአፍሪካን ዕድገት ወደ ኋላ ለመጎተት ችለዋል። ተፈጥሮንም ሆነ የሰውን ልጅ ወደ ተራ ተበዝባዥነት በመለወጥ በአምላክ ምስል የተፈጠረውን የሰው ልጅ በማሰብ ኃይሉ ራሱ በመሰለው መንገድ አዲስ ማህበረሰብ እንዳይመሰርትና እንዳይገነባ ሊታገድ በቅቷል። ስለሆነም ፖለቲካ ራሺናሊዝም የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት፣ በተለይም ደግሞ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በተከሰተው ልዩ ዐይነት የሆነ የኃይል አሰላለፍ እንዳለ ደብዛው ሊጠፋ ችሏል። ከአርቆ-አሳቢነት ይልቅ አመጽና ማስፈራራት ቦታውን በመያዝ በተለይም አላደጉም ወይም በማደግ ላይ ያሉ አገሮች የሚባሉት ህልውናቸው ሊገረሰስ በቅቷል። በእነዚህ ደካማ አገሮች ውስጥ ስልጣን ላይ የሚቀመጡ አገዛዞችና የመንግስታት መኪናዎች፣ ማለትም የሚሊተሪው፣ የፀጥታው፣ የፖሊስና የሲቭል ቢሮክራሲውም በግሎባል ካፒታሊዝም ወይም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ቁጥጥር ስር በመወደቅ ሁለ-ገብና ሚዛናዊነት ያለው ዕድገት እንዳይመጣ ማገድ ብቻ ሳይሆን፣ አገሮችም የተለያዩ ማህበረሰባዊ፣ የሃይማኖትና የጎሳ ግጭቶች የሚፈለፈልባቸው መድረኮች በመሆን ሰፊው ህዝብ ተረጋግቶ እንዳይኖር ለመደረግ በቅቷል። ማንኛውም አገር ከባህሉና ከእሴቱ ውጭ አንድ ወጥ አመለካከትና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ አለበት በማለትና ከፍተኛ ጫና በማድረግ፣ ይህንን የአሜሪካን ኤሊት የብልግና አካሄድ አልቀበልም ያለ ሁሉ እንደጠላት በመታየት ሁለ-ገብ ጦርነት ይታወጅበታል። በቬትናም በ1960ዎቹ ዓመታት በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የተካሄደው ጦርነትና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ የቬትናምን ህዝብ የጨረሰው ጦርነትና መሬቱም እንዳያበቅል ኤጀንት ኦራንጅ(Agent Orange) የሚባል በጣም መርዛማ የሆነ የተበጠበጠ ኬሚካል መርጨት የአሜሪካንን የፖለቲካ ኤሊት መንፈሰ-አልባነትና አረመኔያዊ ባህርይ የሚያረጋግጥ ነው። የኬሚካሉ መዘዝ አሁንም ቢሆን በጉልህ የሚታይና፣ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ አዳዲስ የሚወለዱ ህጻናት ካለጆሮ፣ ካለአፍንጫና ካለዐይን፣ ወይም በሌላ የአካል ጉድለት እንደሚወለዱ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። በመሰረቱ ቬትናምንና አሜሪካንን ምንም የሚያገናቸው ነገር የለም። ቬትናም አሜሪካ ድረስ በመዝለቅ በአሜሪካ ላይ ጦርነትን አላወጀችም። ይህ ዐይነቱ የማንአለኝበት ባህርይ ምንድነው የሚያሳየን። የአውሮፓውና የአሜሪካ የፖለቲካ ኤሊት፣ እንዲሁም የሚሊተሪ-ኢንዱስትሪ ውስብስብ(Military Industrial Complex) በሶስት መንፈስን በሚያድስና ከአውሬ ባህርይ በሚያላቅቅ ሂደት ውስጥ ቢያልፉም ጭንቅላታቸው አሁንም ቢሆን የሰብአዊነትን ባህርይ እንዳልተላበሰ ነው የሚያረጋግጠው። የጀርመኑ ፈላስፋና ገጣሚ የነበረው ታላቁ ፍሪድሪሽ ሺለር እንደሚለን፣ ከአሪስቶተለስ ጀምሮ ስለ ዲሞክራሲ ብዙ ሰምተናል፤ ብዙም ተጽፏል። ይሁንና ግን አሁንም ቢሆን የሰው ልጅ ከአረመኔያዊ ባህርዩ በፍጹም አልተላቀቀም ይላል። ለሰው ልጅ ዕድገትና ስራን ለማቃለል ሳይንስና ቴክኖሎጂ አስፈላጊ የሆኑትን ያህል እንደ ሩሶው የመሳሰሉት ፈላስፋዎች እነዚህ በራሳቸው ብቻ የግዴታ የስልጣኔ መገለጫዎች እንዳልሆኑ ያመለክታሉ። ለማለትም የሚፈልገው በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዕድገት የተነሳ የስው ልጅ መንፈስ ርኅሩህ ለመሆን እንዳልቻለ፣ በተለይም ስልጣን ላይ የሚወጡና አገርን እንገዛለን የሚሉ ወደ አረመኔነት ሊለወጡ እንደሚችሉ ነው። በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነቶችና፣ ከዚያም በኋላ በተወሳሰቡና በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች በመደገፍ የሰውን ልጅ እንዳለ ማጨድ የሚያረጋግጠው ሳይንስና ቴክኖሎጂ የግዴታ የስልጣኔ መገለጫዎች መሆናቸው ቀርቶ የጥቂት ሰዎች ውስጣዊ ፍላጎት ማርኪያ ለመሆን እንደሚችሉ ነው። በተለይም የቴክኖሎጂን አጠቃቀም ጉዳይ ስንመለከት ለቴክኖሎጂ ግኝት መሰረት የጣሉት እንደነ ጋሊሌዮ፣ ኬፕለር፣ ዲካ፣ ላይብኒዝና ኒውተን፣ እንዲሁም አይንስታየንና ሌሎችም ሳይንቲስቶችና የቴክኖሎጂ አፍላቂዎች ሳይንሳዊ ምርምር ሲያደርጉና ራሳቸውንም ሲያስጨንቁ የሰውን ልጅ በጊዜው ከሚኖርበት ከጨለማና ከእንስሳ በማይተናነስ የአኗኗር ዘዴ በማላቀቅ በቴክኖሎጂ አማካይነት ምርታማነትን በማሳደግና አዳዲስ የአኗኗር ስልት በማዳበር ሰው መሆኑን እንዲገነዘብ ለማድረግ ብቻ ነበር። በሌላ አነጋገር፣ ታላላቅ ፈላስፋዎችም ሆነ ሳይንቲስቶች የሰውን ልጅ ከጨለማ ለማውጣት ሲታገሉና ለቴክኖሎጂ ግኝት ሳይንሳዊ የምርምር መሰረት ሲጥሉ ምርምራቸው ወደ መጥፎ ነገር ይለወጣል ብለው በፍጹም አልገመቱም ነበር። እንደ አቶም ቦምብ፣ የባይሎጂና የኬሚካል የጦር መሳሪያዎች በመፈጠርና በመሰራት የሰውን ልጅ ለመጨረስ ጠቀሜታ ላይ ይውላሉ በለው በፍጹም አላሰቡም ነበር። ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችም በዚህ ፍጥነትና ምጥቀት በመፈጠርና በመሰራት የዓለምን ህዝብ ማስፈራሪያ ይሆናሉ ብለው በፍጹም አላለሙም ነበር። ይሁንና በካፒታሊዝም ውስጣዊ ሎጂክና የአገዛዝ አወቃቀር የተነሳ መንፈሳቸው ቀና በሆኑና ልዩ ዐይነት ተልዕኮ ባላቸው ግለሰቦች የተፈጠሩ ቴክኖሎጂዎች ለጥፋት እንዲውሉ ተደርገዋል። ይሁንና ይህ ዐይነቱ ቴክኖሎጂን ሰውን ለማስፈራሪያና ለመግደያ መጠቀም በእኛ ኢትዮጵያውያንና በተቀረው በምስኪኑ የዓለም ህዝብ ልክ እንደ ተፈጥሮ ህግ በመወሰድ ሲወደስ ይገኛል።
ከዚህም ባሻገር በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ በራሱ የካፒታሊዝም ውስጠ-ኃይልና ሲወርድ ሲዋረድ በመጣ የጥቂቶች ምሁራዊ ጥረት የተነሳ የሊበራሊዝም አስተሳሰብ ቢዳብርምና ሰፋ ያለ የሲቭል ማህበረሰብ ቢፈጠርም፣ የሊበራሊዝም ፅንሰ-ሃስብ ግን በውጭ ፖለቲካው ላይ የሚሰራ አይደለም። ይህም ማለት እያንዳንዱ አገር ነፃ እንደመሆኑ መጠን የራሱን ኢኮኖሚ፣ ባህል፣ የከተማ አገነባብ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጉዳይና፣ እንዲሁም በየአገሮች ውስጥ የሚኖረውን ሰፊ ህዝብ አስመልክቶ ደረጃ በደረጃ መወሰድ ስላለበት የአገር ግንባታና ድህነትን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ማስወገድ የሚለውን ተፈጥሮአዊና የህብረተሰብ ህግ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የፖለቲካና የሚሊተሪ ኤሊቱም ሆነ የአውሮፓ ካፒታሊዝም ኤሊቶች በፍጹም አይቀበሉም። ሁሉንም ነገር እኛ መደንገግ አለብን፤ ማንኛውም አገር ከእኛ ቁጥጥርና ፈቃድ ውጭ የፈለገውን ነገር ማድረግ አይችልም የሚል የፀና አስተሳሰብ በአሜሪካን የፖለቲካና የሚሊተሪ-ኢንዱስትሬ ውስብስብ ጭንቅላት ውስጥ ተቀርጿል። ይህ ዐይነቱ ዲስፖታዊ አስተሳሰብ ወይም አመለካከት ደግሞ በመሰረቱ ታላላቅ የአውሮፓ ፈላስፋዎች፣ ማለትም ላይብኒዝ፣ ካንት፣ ሄገል፣ ጎተና እንዲሁም አንዳንድ የእንግሊዝ የኢንላየተንሜንት አፍላቂዎችና አስተማሪዎችን ያፈለቁትንና ያስተማሩትን መመሪያ የሚቃወም ነው። በካንትም ዕምነት ዘለዓለማዊ ሰላም(Perpetual Peace) በሚለው መጽሀፉ ውስጥ ሊያስተምረን የሚሞክረው በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘለዓለማዊ ሰላም ሊሰፍን የሚችለው ማንኛውም አገር የሌላውን አገር ልዕልና ሲያከብርና በውስጡ ፖለቲካው ጣልቃ ያልገባ እንደሆነ ብቻ ነው ብሎ አጥብቆ ያሳስባል። ስለሆነም ይላል ካንት፣ አንድ የበላይነት የሚሰማው ወይም ኃያል ነኝ የሚል አገር የግዴታ ደካማና ያላደገውን አገርም ነፃነቱን ማክበር አለበት ይላል። በዚህ መንፈስ መገዛት ሲቻል ብቻ ነው በአገሮች መሀከል ሰላም ሊስፍን የሚችለው። ይህንንም መሰረተ-ሃሳብ ያፈለቁትና ያዳበሩት ኮሙኒስቶች ሳይሆኑ- በጊዜው ኮሙኒዝም የሚባል አስተሳሰብ የሚታወቅ አልነበረም- ንፁህ መንፈስና ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያላቸው ፈላስፋዎች ናቸው።
በየአገሮች መሀከል ሊኖር የሚገባው ግኑኝነት ልክ ካንት ባለው መልክ መዋቀር ሲገባው በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና አፈቀላጤዎቹ፣ ማለትም የዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ(World Bank)፣ እንዲሁም የአሜሪካን የጥሬ-ሀብት ተቀራማች ትላልቅ ኩባንያዎች የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች ውስጥ አገዛዞችን በማባለግና በገንዘብ በመግዛት የየአገሬውን ህዝብ በሰላም ሰርቶ እንዳያድርና ስርዓት ያለው ማህበረሰብ እንዳይገነባ ከፍተኛ እንቅፋት ፈጥረውበታል። የዚህ ዐይነቱ የጥሬ-ሀብት ቅርምትና አገዛዞችን በማባለግ ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማስገደድ በየአገሮች ውስጥ መጠነ-ሰፊ የስራ አጥ ቁጥር እንዲፈጠርና አገዛዞችም አገሮቻቸውን ለማስተዳደር የማይችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር ተደርጓል። በየአገሩ መኖር፣ መስራትና ራሱንና ቤተሰቡን ማስተዳደር የማይችለው ደግሞ ከየአገሩ እየተሰደደ በተለይም ወደ አውሮፓና ወደ አሜሪካ እንዲሰደድ ለመደረግ በቅቷል። በዚህም ምክንያት የተነሳ በየአገሮች ውስጥ እየገባ አገዛዞችን እንደፈለገው የሚበውዘው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና አፈቀላጤዎቹ ሳያስቡት በአገራቸው ውስጥም ከፍተኛ የጎሳ ቅይጥ እየፈጠሩና ነጭ ነኝ የሚባለው የህብረተሰብ ክፍል በአገሩ ውስጥ ተዝናንቶ ሊኖር የማይችልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ለመደረግ በቅቷል። በተለይም በአሜሪካን በአንዳንድ ከተማዎች ውስጥ የላቲኖ ህዝብ፣ የህንድና የቻይናዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣት በአጭር ዓመታት ጊዜ ውስጥ የነጩ ህዝብ ቁጥር ከሌላው ከውጭው ከመጣው ጋር ሲወዳደር በቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ እንደሚል ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ባጭሩ እንደዚህ ዐይነቱ ከአርቆ-አሳቢነት ውጭ በማንአለኝበት የሚካሄድ የውጭ ፖለቲካ የመጨረሻ መጨረሻ ማንም የሚነካኝ የለም የሚለውንም ኃይል መንግስት ቀስ በቀስ ከስሩ እንደሚቦረብረውና የበላይነት ዘመኑን በከፍተኛ ፍጥነት እንደሚያሳጥረው ነው።
ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በአገራችን ምድር በፅንሰ-ሃሳብና በአመለካከት ዙሪያ በማንኛውም የትምህርት ዘርፍ የጠራ አቋምና ትግል የማካሄድ ልምድ ስለሌለ ከፍተኛ አለመግባባት አለ። አንዱ በጥሩ እንግሊዘኛ ወይም በጥሩ አማርኛ ሲጽፍ በጣም ጥሩ ትንተና እንዳቀረበ ተደርጎ ይወሰዳል። እዚህ አውሮፓ ውስጥ ክሪቲካል አመለካከት የሚባል ነገር አለ። ማንኛውም አነጋገርና ጽሁፍ በሳይንስ መነፅር መመርምርና መነበብ አለባቸው። አስቸጋሪው ነገር በሶሻል ሳይንስ ዘንድ፣ በተለይም በኢኮኖሚክስ ዘንድ ብዙ የተምታቱ ነገሮች ስላሉ አብዛኛዎቻችንም በፍልስፍናና በሶስዮሎጂ ዕውቀቶች ያልሰለጠን ስለሆንና ከትምህርት ዘርፋችን ወጣ ብለን ሌሎች ሰነ-ጽሁፎችንና ዕውቀቶችን የማንበብ ልምድ ስለሌለን በምድር ላይ የሚታዩ ነገሮችን ለማየት አንችልም፤ ወይም እያየን እንዳላየ ሆነን እናልፋለን። ባጭሩ ቆም ብለን ይህ ዐይነቱ አስቀያሚ ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? ምክንያቱስ ምንድነው? ብለን በፍጹም የመጠየቅ ልምድና ባህልም የለንም። ስለሆነም ስለፖለቲካል ራሺናሊቲ በሚወራበት ጊዜ የዚህን ፅንሰ-ሃሳብ አመጣጥና ከምን ነገር እንደተያየዘና፣ በየትኛውም ክፍለ-ዘመን እንደፈለቀ ማወቅና ማስረዳትም በጣም ያስፈልጋል። ይሁንና ፅንሰ-ሃሳቡ ደግሞ የግዴታ ዘለዓለማዊ እንደሆነና ከጭንቅላት ተሃድሶና ራስን መልሶ መላልሶ ከመጠየቅ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። ዮናስ ብሩ ግልጽ ማድረግ የነበረበትም ይህንን ጉዳይ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታና ሰፋ ካለ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አለመኖርና የመንፈስ ተሃድሶ ተግባራዊ ካለመሆን ጋር ነበር ማያያዝ የነበረበት። ለማንኛውም እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ፖለቲካል ራሺናሊቲ ከሰብአዊነት እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ይህ በራሱ ደግሞ አንድን ህብረተሰብ ከተለያዩ አንፃሮች በመመርመርና እንደማህበረሰብ ለመቆም የሚጎድሉቱን ነገሮች በማጥናት አስፈላጊዎችና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ፖሊሲ ነክ ነገሮችን ማዳበርና ወደ ተግባርም እንዲመነዘሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ነው። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብም በአንድ ግለሰብ ጫንቃ ላይ ብቻ የሚጣል ሳይሆን በብዙ ሰዎች ትከሻ ላይ በመውደቅ በልዩ ልዩ የዕውቀት ዙሪያ በመሰባሰብ ጥናት ማካሄድና መፍትሄም ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉ ነገሮችን መሰንዘር በጣም አስፈላጊ ነው። ባጭሩ ከአንድ ግለሰብም ሆነ ከሁለት ሰዎች ወይም ከአንድ ድርጅት ፖለቲካል ራሺናሊት መጠበቅ ቢያንስ ከአውሮፓው የኢንላይተንሜንት እንቅስቃሴ ታሪክ ሲታይ ሊያስኬድ የሚችል ነገር አይደለም። የራስን የጠራ የፖለቲካ ርዕይ ሳያስታውቁና በተለያየ የህብረተሰብን ጥያቄዎች በሚመለከቱ ነገሮች ላይ ለምሳሌ የፖለቲካ አደረጃጀት፣ የፖለቲካ ተቋማት ግንባታ፣ ሰለመንግስት መኪና አወቃቀርና ዲሞክራሲያዊ ባህርይ እንዲኖረው ሰለማድረግ ጉዳይ፣ በመንግስት አማካይነት ጠቅላላውን ህዝብ የሚጠቅም ሀብት እንዴት ሊፈጠር ይችላል? መንግስትስ በኢኮኖሚውና በማህበራዊ ነክ ነገሮች ላይ ምን ዐይነት ሚና ሊጫወት ይችላል? የኢኮኖሚ ዕድገትንና የስራ-መስክን መፈጠር ጉዳይ በሚመለከት የግለሰቦችስ ሚና እንዴት ይታያል? እንዴትስ ሊነቃቁና ሊደገፉ ይችላሉ? ከዚህም ባሻገር ሊሰራ የሚችለውን ህዝብ በማንቀሳቀስ እንዴት ተደርጎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተማዎችን፣ መንደሮችን፣ ልዩ ልዩ ተቋማትን፣ የህዝብ መኖሪያ ቤቶችንና ባህላዊ የገበያ አዳራሾችንና የባህል ተቋማትን...ወዘተ. መገንባት ይቻላል? ገንዘብና ሌሎች ሪሶርሶችንስ በምን መልክና ዘዴ በማንቀሳቀስ ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል? በእነዚህ መሰረታዊ ነገሮች ላይ መወያየት የፖለቲካል ራሺናሊቲና የሰብአዊነት መሰረተ-ሃሳቦች ናቸው። ባጭሩ በጠቅላላው አገርን ስለመገንባት ጉዳይ የራስን አቋም በግልጽ ሳያስቀምጡ ወይም በሀተታ መልክ ሳይጽፉ ከሌላው ሰው ፖለቲካ ራሺናሊቲ መጠበቅ እኔ ብቻ ነኝ ራሺናሊ ማሰብ የምችለው ብሎ እንደመመጻደቅ ይቆጠራል።
ዮናስ ብሩ ይህንን ጉዳይና በተለይም ለሁላችንም ግልጽ እንዲሆንልን ራሱ የሚያራምደውን የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ቢነግረን ኖሮ ምናልባት ምንነቱን ልንረዳው እንችል ይሆናል። ካለበለዚያ እንዲያው በደፈናው በራሺናሊቲ ስም ከፍተኛ ወንጀል ስለሚሰራ የግዴታ የራስን የፖለቲካ አቋም መናገር ያስፈልጋል። የፖለቲካ አቋም ሲባልም ቀኝ፣ ግራ፣ ፋሺሽስት፣ ወይም ኮንሰርቫቲቭ...ወዘተ.
https://amharic-zehabesha.com/archives/187978
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment