Friday, November 24, 2023
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ከመጻሕፍተ መነኮሳት አንዱ የሆነው ፊልክስዩስ ገጽ 106 ላይ “እንኪያስ መነኮሳት ነውር ነቀፋ የሌለባቸው ሁነው በፍጹም ሥራ ሊኖሩ ይገባቸዋል” ይላል፡፡* ሌላኛው መጽሐፍ መነኮሳት ማር ይሳቅ እንደዚሁ ገፅ 106 ላይ “አቡነ” ኤርምያስ ስሙን የዘረፉትን ቅዱስ ኤርምያስን ከጠቀሰ በኋላ “ እግዚአብሔር ሳንፈራ ሳንበርድ ጸላታችንን (ሰይጣንን ማለቱ ነው) እንገጥመው ዘንድ ያዝዛልና” ብሎ “ሳይቀድምህ ቅደመው...ትወጋው ዘንድ መር ብለህ ቁንጮውን ያዘው”* እያለ ያዝዛል፡፡
ሰይጣን እግዚአብሔርን የከዳ ቀደም ሲል ከመላእክት አንዱ እንደነበር ይታወቃል፡፡ መላእክት ደሞ እንደ ሰው አካል ወይም እጅና እግር እንደሌላቸው ይታወቃል፡፡ ሰይጣን ወይም ሳጥናኤል የሚጠቀመው እጅና እግር ያላቸውን ዋሾዎች፣ ቀጣፊዎች፣ ከሃዲዎችትን፣ ዘራፊዎች፣ አረምኔዎችና ጭራቆችን መሆኑን “አቡነ ኤርምያስና ጓዶቻቸው” የዘነጉት ይመስላል፡፡ ሰይጣን የእርጉዝ ሆድ በመቅደድ፣ ሰው ዘቅዝቆ በመስቀል፣ ሕዝብን ከነነፍሱ በማቃጠል፣ እሬሳ በመጎተት፣ ገዳማትና ቤተከርስትያንን በማቃጠል እንደሚከሰት ለማመን ለግመዋል፡፡ “ይሁን ይሁን፤ አይሆንምን አይሆንም በል” የሚለውን የመጣፍ ቃል ተላልፈው እንኳን ሰይጣንን ቁንጮውን ሊይዙ ሰይጣንን ሰይጣን ለማለትም እንጀራ አንቋቸዋል፡፡
አደራቸውን ለመወጣት ከመልገምም አልፈው “አቡነ ኤርምያስ” የአማራን ሕዝብ በሚጨፈጭፉት ሰይጣን በተሰቀላቸው ወታደሮች ታጅበው ፋኖን ስለመወረፋቸው ሲጠየቁ ሕዝቡን እየራበው ስለሆነ ለሆዱ ሲል ላጀቧቸው ጪራቅ ገዥዎች እጅ ይስጥ ዓይነት ቃለ መልስ ሰጥተው አርፈዋል**፡፡
“ጳጳሱ” ቅዱስ ዳዊትን በጎልያድ ላይ ያነሳው እግዚአብሔር ፋኖን በጭራቆች ላይ እንዳስነሳው ለማመን ተቸግረው ፋኖን ተማብጠልጠል አልፈው ጳጳስ ነኝ በሚሉበት አገር እሬሳ እንደ ግንድ መሬት ለመሬት የጎተተውን አረመኔ ትተው በውጭ ያሉ የፋኖ ደጋፊዎችን “የሬሳ ነጋዴዎች” ብለው ትርፍ ቃል ተናግረዋል፡፡
“ዶሮ ብታልም ጥሬዋን” ይባላል፡፡ ሆዳም እሚያልም ምግቡን እንጅ እውነትን፣ ፍትህን፣ ክብርንና እምነትን ስላልሆነ እንደ ”አቡነ” ኤርምያስ ምክር ወይም ትዕዛዝ ተሆነ አማራ ለሆዱና ለህክምና ሲል ክብሩን፣ ማእረጉን፣ እምነቱን፣ ፍትህና እውነትን መጣል አለበት፡፡ እኒሁ “ጳጳስም” ሆነ ሌሎች ጓደኞቻቸው የአማራ ሕዝብ ለግማሽ ክፍለ-ዘመን በእቅድ አገር አልባ እንዲሆን ከተቻለም እንዲጠፋ የተፈረደበት መሆኑን ያውቃሉ፡፡ መስቀል ጨብጠውና ቆብ ደፍተው ግን ይኸንን በአማራ ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ የክቡር አቶ ታዲዎስ ታንቶን ያህል የመናገር የእምነትም ሆነ የሞራል ብቃት አላገኙም፡፡
ጳጳሳት ከወራት በፊት እነ ሄሮድና ጲላጦስ ስልጣናቸው ሊነጥቋቸው ሲሉ ለሕዝቡ የድረሱልን ጥሪ አቅርበውና ሕዝብ አስፈጅተው ስልጣናቸውን ታረጋገጡ በኋላ ሕዝቡን ከፈጁት አረመኔዎች ጋር መላላስ እንደ ጀመሩ የሚታወቅ ነው፡፡ ህፃናት ሳይቀር በሚያርዱት በእነ ሄሮድስ ተገደውም አሜሪካን አገር በአስገድዶ መድፈር ሙከራ የተከሰሱ “ መነኩሴ ነኝ” ባይ ጣኦተኛ ጳጳስ አድርገውን ስልጣን እንደሰጡ የሲኖዶስ ተብየው ስራ አስኪያጅ የተናገሩትን ልብ ያለው የሚያስታውሰው ነው፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ “አቡነ ኤርሚያስ” ቤተክርስትያኗን እየጠበቁ እንደሆነ ሲናገሩ መስቀላቸውን ያነገቱበት ማተብ ትንሽም አልገታቸው፡፡
ምእመናን ሆይ፡-ቤተከርስትያን ማለት የቤተክርስቲያናን አእዋፍ (ራስ) ክርስቶስን፣ ሕዝብና የአምልኮት ሥፍራን (ቤተክርስትያናትና ገዳማትን) የሚያጠቃልል ነው፡፡ እነደሚታወቀው ቤተክርስትያኗን ቀጥ አርጎ የያዘው የአማራ ሕዝብ የህልውና አደጋ የተጋረጠበትና በድሮን በመጨፍጨፍ ላይ ያለ ሕዝብ ነው፡፡ የአምልኮት ቦታውም በአህዛብና በአውሬዎች እየተቃጠለ ነው፡፡ ክርስቶስም ከእርሱ ይልቅ ይህቺን ምድራዊ ዓለም በመረጡ ጳጳሳትና አቡን እየተከዳ ነው፡፡ ታዲያ ቤተክርስትያኗን እየጠበቅን ነው የሚሉት የትኛውን የቤተክርስትያን ክፍል ጠብቀውት ነው?
ፋኖን ያብጠለጠለው የአቡነ ኤርምያስ አንደበት ለምእመናኑም እውቅና ባይሰጥም እግዚአብሔር ምስጋና ይግባውና የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን እየተጠበቀች ያለችው ለምኖ ሳይቀር አስራት በሚከፍለው ጽኑ እምነት ባለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ ቤተክርስትያኗ እየተጠበቀች ያለችው አንገቱን ለሰይፍ ሊሰጥ በተዘጋጀ አማኝና ሰማእት በመሆን ላይ ባሉ የቤተክርስትያን አገልጋይ ካህናት ነው፡፡ ጳጳሳትና አቡኑ ሰማእትነታቸውን የስልጣን ማደላደያ ያደረጓቸው የሻሸመኔ መእመናንና ካህናት ለዚህ ምስክር ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን እየተጠበቀች ያለችው በህይወት ሳሉ በተዋደቁላት ቅዱሳን በአቡነ ጴጥሮስ፣ አቡነ ሚካኤል፣ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬና በሌሎችም መንፈስ ነው፡፡
የዛሬዎቹ አቡንና ጳጵሳት ያልሰነፉት የምእመናን አስራት በደሞዝና ውሎ አበል ስም መላፍና ቁንጣን ሲይይዛቸውም ወደ ውጪ ሄደው መታከሚያ ማድረግ ነው፡፡ “አቡነ ኤርምያስ” የቤተ-ክርስትያኗ ግድግዳና ማገር የሆነው የአማራ ሕዝብ እየተራበና የህክምና አገልግሎት እንደማያገኝ በተናገሩበት ምላስ አንዱ ጓደኛቸው በአሁኑ ሰዓት ዘመናዊ ሕክምና ለማግኘት አሜሪካን አገር እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊቱም ብዙዎቹ አሜሪካና አውሮጳ እየሄዱ ህክምናውንም ሽርሽሩንም አድርገዋል፡፡ መታከሚያ ያጣ ቁስለኛ በቁስሉ እየለመነ አስራት ይከፍላል ጳጳስና አቡን ዶላሩን እንደ ሳር ነስንሶ አውሮጳና አሜሪካ ይታከማል፣ ይዝናናል፡፡ ቲኬት ቆርጦ፣ ለወራት ሆቴል ተከራይቶ፣ ካለምንም ኢንሹራንስ አሜሪካን አገር መጥቶ ለመታከም የሚያስፈልገው ገንዘብ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያንስ አንድ ሺህ ክሊኒክ አሰርቶ ሥራ ያስጀምራል፡፡ ጳጳስት ምእመናኑ ሲታመሙ ተጠመቁን እየሰበኩ ወደ ፀበል ሥፍራዎች እየላኩ የእነሱ ፀበል ቦታዎች ዘመናዊ የአውሮጳና የአሜሪካ ሆስፒታሎችና ክልኒኮች ሆነዋል፡፡ አስራት ከፋዩ ሕዝብ ሲኖድን በሚያሽከረክሩት ጭራቅ ገዥዎች በችጋርና በበሽታ ሲያልቅ ጳጳስና አቡን እንደሚሰግዱላቸው አረመኔ ገዥዎች ሁሉ አውሮጳና አሜሪካ እየነጎዱ ሆድ ቁርጠትና ራስ ምታት ሲታከሙ ይታያል፡፡ ይኸም ሆኖ ዓይናቸውን በጨው ታጥበው ምዕመናኗ እየተጨፈጨፈ ያለውንና ገዳሟና ሕንፃዋ የሚነደውን ቤተክርስትያን እየጠበቅን ነው ይሉናል፡፡
እንደ ሌሎች የሲኖድ ጓደኞቻቸው ሁሉ በትምህርት፣ በእምነትና በመንፈስ ልዕልና የበሰሉ የማይመስሉት “አቡነ ኤርምያስ” አንዲትም የመጽሐፍ ቃል ሳይጠቅሱ ቃለ መጠየቁን በካድሬ ቃላት ጨርሰዋል፡፡ ለሆዱ ሲል የአማራ ሕዝብ ክብሩን፣ እምነቱን፣ ማእረጉን፣ ህልውናውንና አገሩን ለሰይጣን አሳልፎ ይስጥ ዓይነት የሚያሳፍር ንግግር አድርገውን ተድጡ ወደ ማጡ ወርደዋል፡፡ እግዚኦ!
*ምእመናን ሆይ የመነኮሳት፣ ጳጳሳትና አቡኑን መለኮታዊ ግዴታ ለማወቅ እባክዎን መጻሕፍተ መነኩሳትን ያንብቡ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡ መጻሕፍተ መነኮሳት 1929 ብርሃንና ሰላም እትም፡፡
**ቃለ መጠይቁ የአማራ ህዝብ ተበድሏል። ይህ መንግስት ለሁሉ ነገር ጥፋተኛ ነው። እኔ ፋኖን አልወቀስኩም። ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ - (amharic-zehabesha.com)
https://amharic-zehabesha.com/archives/187352
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment