
ለነፃነት፤ ለእኩልነትና ለወንድማማችነት፤ ለሚታገሉ የለሕሊና እስረኞችና ለኢትዮጵያ ትንሳኤ ለሚዋደቁ የፋኖ ጀግኖች መታሰቢያ ትሁንልኝ ::
አልጠብቅም ሞትን - ተኝቼ ባልጋዬ ፤
እኔው እሄዳልለሁ - ፈረሴን ቼ ! ብዬ ፤
አልፈልግም ዋሻ - የምደበቅበት ፤
አልፈልግም ጢሻ - የምሸሸግበት ፤
አልሰብርም አንገቴን - አላዞርም ፊቴን ፤
አይዝልም ጉልበቴ - አላጥፈውም ክንዴን ፤
እጠብቀዋለሁ - ደረቴን ነፍቼ ፤
በኩራት በድፍረት - አንገቴን አቅንቼ ፤
አልንበረከክም - ቆሜነው እምሞተው ፤
የጀግና ልጅ ጀግና መሆኔን ይወቀው !!
በ’ንባ አልታጠብም - ቁጭብዬ አላለቅስም ፤
ጉልበቴን አጥፌ - አልንበረከክም ፤
አልጠብቅም እሱን - ወደኔ እስቲመጣ ፤
እኔው እሄዳለሁ - ወደሱ እንዳይመጣ ፤
ኩራቴን ይረዳው - ድፍረቴን ይወቀው ፤
ተጋድሜ አልሞትም - ቆሜነው እምሞተው !!
አልጠብቅም ሞትን - ማታ በጨለማ ፤
እንዲወስደኝ ብዬ - ሰው ሳያይ ሳይሰማ ፤
አለምንም ከቶ - ዛሬን እንዲተወኝ ፤
ዘግይቶ እንዲመጣ - ዕድሜ እንዲለግሰኝ ፤
ወይ እንደ ባለጌ - እያሞላቀቀ ፤
ሞት መጥቶ እስቲወስደኝ እያጨማለቀ ::
ጭራሽ !
እጠብቀዋለሁ - በጠራራ ፀሐይ ፤
መሃላዬ ይሁን - ቃል ለምድር ለሰማይ ፤
ዳግም ድል አድርጌ - እስክነሳ ድረስ ፤
ቆሜነው እምሞተው እንደ ክርስቶስ ::
አገኛለሁ ብዬ - ትርፍራፊ እድሜ ፤
አልጠብቅም ከቶ - እኔ ተጋድሜ ፤
ወደሱ እሄዳለሁ - ወደ’ኔ እንዳይመጣ ፤
ግንባሬን አላጥፍም - የመጣው ቢመጣ ፤
ተኝቼ አልጠብቅም - ሞት መጥቶ እስቲወስደኝ ፤
እኔው እሄዳለሁ - በቁሜ እንዲያገኘኝ ::
ለመኖር ጓጉቼ - አልንበረከክም ፤
ዛሬን ተወኝ ብዬ - አልለማመጥም ፤
አልንበረከክም - ቆሜነው እምሞተው ፤
የጀግና ልጅ ጀግና መሆኔን ይወቀው !!
ኅዳር 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ( November 17. 11. 2023 )
https://amharic-zehabesha.com/archives/187121
No comments:
Post a Comment