በሬ ያዘመረው ግርድ እየቃምክ፣ ፈረስ የጠበቀው መስክ እየጋጥህ፤
ላምን ወደ “እምቧ” ሰፈር፣ በግም ወደ “በኣ መንደር ይሂድ ያልክ፤
ነገ ተሚገምጥህ ጅብ ተሻርከህ፣ ወይስ ያንን ግፊያህን ተማምነህ?
ኧረ ተው ወሼ ተለመን፣ ጥጋብህ ይኑረው ገደብና ልክ፤
ተንጋለህ ሽቅብ አትሽና፣ ጊዜና ወቅትን ጠብቀህ፡፡
ኮርማ የወቃው እንክርዳድ፣ ሌት ተቀን ውጠህ ጠብድለህ፤
እናቱን ላሟን በእርግጫ ደልዘህ፣ ጥርሷን በኮቴ የሰበርክ፤
ክብርህን እደ ፋንድያህ በትነህ፣ ይሉኝታን እንደ ቅይድህ ቦጫጭቀህ፤
ምድርስ መቼም ዳኛ የላትም፣ የሰማይ ንጉስ ፍርድ ይስጥህ፡፡
ተው እባክን አህያ ተለመን፣ መንከሱን አቁም አንበሳ፤
እንቅልፍ አሸልቦት ተኝቶ፣ ቢመስል አቅም የሌለው ኮሳሳ፡፡
አዙሮ ማያ አንገትን ቀልጥመህ፣ ተባእዳን ጅቦች አብረህ፤
ነጣ ያወጣህ ፈረስን፣ መርገጥህ ባልተገረዘ ሸኮናህ፤
እንኳንስ በምድር ዱርና ገደል፣ በሰማይ ጫካስ አያሸፍትም ትላለህ?
ምንግጭል ተምርት ቸክለህ፣ ወርችህን ተምድር አምቧትረህ፤
ኧረ ተው አቁም መራገጥ፣ “ሁሉም የኔ ነው” ብለህ እየጮህክ!
ወተት ለጋሽ ላም ገፍትረህ፣ ምርት አምራች በሬን እረግጠህ፤
መስኩን በውርንጭሎችህ ያስወረረክ፣ በረቱን በፋንዳያ ኩስ የሞላህ፤
የአተላ ጥጋብ አስክሮህ፤ ወይስ ፈረንጅ ፉርሽካ አጉርሶህ?
በጋሪ ሸክም ጎትተው፣ ተቅርቀብ ጭነት ያወጡህ፤
ጀርባህን በድብዳብ ኮተት፣ ግሽልጥ ተማለት ያዳኑህ፤
የግላስ ሸማ ደርበው፣ መልካቸው አምሮ ስላየህ፤
ዝቅ ያለ መንፈስ አናውጦህ፣ የእንቁላል ሥፍራህ ጠፍቶብህ፤
ፍቅር በማያውቅ ለንጨጭህ፣ የተኛ ፈረስ መንከስህ፤
ተፈናጦህ ነው ይሁዳ፣ ወይስ ዲያብሎስ ተላይ አዝዞህ?
ተሁለት ሰይጣን አንድ ምረጥ፣ ተብሎ የተጠየቀ አንድ ውሻ፤
“ወቢ ተተፋው አለሌ፣ ጅብ በስንት ጣሙ” ብሎ መለሳ!
ዓለም በጥበብ አንድ ሆና፣ ሲገናኝ ፍጥረት ተዳር ዳር፣
አንተ ብሶብህ አረፈው፣ በቂጥ ተጋፍተህ ማባረር፡፡
ዓይኖችህ ጥቅጥቅ ተደፍነው፣ በጥላቻ ጩቅ ስብ ሞራ፤
የፊት መስታወት ሰባብረህ፣ ቡጭቅጭቅ አርገህ ህሊና፣
ያለ አንዳች አፍረት ትላለህ፣ ፈረስን ሃሬና አህያ፡፡
ተሞትኩ ሰርዶው አይብቀል” በሚባል ቅንቀና፣ “ግፊያ በሚባል ድለቃ፤
ዘረ ተክል ተምድር ነቅለህ፣ ቆፍረህ ባልተጣፈረ ሸኮና፤
አገርን ወና ሳታደርግ፣ መስኩ የኔ ነው ያክላላህ በልግ ያጠገበህ አህያ!
በጊዜ አደብ ብትገዛ ይሻላል፣ ብትንትን ብለህ ሳትወድቅ እንደ ፋንድያ!
በላይነህ አባተ ((abatebelai@yahoo.com)
ጥቅምት ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ. ም.
https://amharic-zehabesha.com/archives/186511
Wednesday, October 18, 2023
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
The west is rigidly stuck in its heydays of colonialism and slavery. And it has a very good reason for being so stuck, albeit sentimental. ...
-
By Dr. Suleiman Walhad July 10th, 2022 It is fully defined now, the Horn of Africa States! It is marked by droughts , secessionism, inte...
-
ዛሬ አንድ የፌስ ቡክ ጓደኛየ የአቶ በቀለ ገርባን ሽሽት ከተመለከተ በኋላ የሚከተለውን መልእክት ጻፈ። " አገሩን አርማጌድዮን አደገህ ብልሆች ወደ ሰሩት አገር በነጻነት ለመኖር ሄድክ? " አባባሉ እኔንም...
No comments:
Post a Comment