Monday, September 4, 2023

አክራሪ ብሄረተኛነት ምንድነው? ተከታዮቹ በሆኑት የአንድ ነገድ ተወላጆችስ ላይ የሚያስከትለው ስነልቦናዊ ለውጥ ምን ይመስላል?
በዶክተር አሰፋ ነጋሽ ---› የኢሜይል አድራሻ --›

Debesso@gmail.com Amsterdam (the Netherlands)

- ሀምሌ 5 ቀን 2010 ዓ. ም.

ክፍል አንድ -----›

ስለ ብሄረተኛነት ጥቂት ሃሳቦች፤

ኤሊ ኬዱሪ የተባለ፤ በብሄረተኛነት ርዕሰ-ጉዳይ ላይ በጻፋቸው ጽሁፎቹ የሚታወቅ አሜሪካዊ ሊቅ “ብሄረተኛነት በአስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአውሮፓ የተፈጠረ እምነት ነው1” በማለት የዚህን ፍልስፍና ታሪካዊ አመጣጥ ገልጿል። ኤሪክ ሆብስብዋም2 የተባለው በዚህ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ጥልቅ የሆነ ግንዛቤ አስጨባጭ ጽሁፎችን የጻፈ እንግሊዛዊ ሊቅም ሆነ ሃንስ ኮህን3 ይህንን የኤሊ ኬዱሪን ሃሳብ ይጋራሉ። ሌላው ጌልነር የተባለው አንድ እውቅ የእንግሊዝ ሊቅ ደግሞ “ብሄረተኛነት አይቀሬ (የማይቀር) የዘመናዊነት ውጤት ነው4” በማለት ይገልጸዋል። ሆብስብዋም ብሄረተኛነት ከአንድ ነገድ የወጡ ብሄረተኛ ልሂቃን የማህበረሰባዊ ምህንድስና ዘዴ (social engineering methods5) ተጠቅመው በአንድ ነገድ ባህላዊ(ቋንቋ፤ ኃይማኖት) ማንነት ላይ በመንተራስ ህዝባችን የሚሉትን ያንድ ቋንቋ ተናጋሪ ወይም አንድ ባህል-ተጋሪ ህዝብ ተጨባጭነት ባላቸው ማህበረሰባዊ ጉዳዮች (የኢኮኖሚ ጥቅሞች፤ የባህልና የፓለቲካ መብቶች ወዘተ) ዙሪያ በማሰለፍ ስልጣን ላይ ለመውጫነት የሚገለገሉበት መሳሪያ ነው ይለናል6። ማህበራዊ ምህንድስና አንድ አክራሪ ብሄረተኛ ወገን የሌሎችን ነገዶች ታሪክና ማንነት በማጥፋት የራሱን ነገድ ተወላጆች የጥቅም የበላይነት የሚያረጋግጥበትን፤

 

- - Social engineeringወይም በአማርኛ ትርጉሙ ማህበራዊ ምህንድስና ብዬ የምጠራው ክህስተት አንድ አምባገነናዊ መንግስት አንድን ህብረተሰብ በተከታታይና ያላሰለሰ ፕሮፓጋንዳ አማካይነት፤ እንደዚሁም የኃይል እርምጃንና ሌሎችንም በርካታ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ተጽዕኖዎችን ጭምር በመጠቀም አንድን ህብረተሰብ አንድ-ወጥ የሆነ አመለካከትና የአንድ ዓይነት ስነ-ምግባር ተጋሪ ለማድረግ የሚሞክርበትን ዘዴዎች የሚያመለክት ነው። የማህበረሰባዊ ምህንድስናን ዘዴዎች በመጠቀም አንድ አምባገነን መንግስት የአንድን ማህበረሰብ የወል ትውስታ፤ ታሪክ፤ ባህላዊ እሴቶች ወዘተ በማጥፋት አንድን ህብረተሰብ እንደ አዲስ ለመፍጠር ይጥራል። የወያኔ ትግሬዎች የወልቃይት ጸገዴን፤ የጸለምትንና አጎራባች የሆኑትን የጎንደሬዎች የቀድሞ ይዞታዎች በኃይል ወረውና የነባሩን ህዝብ መሪዎች፤ ሀገር-አውል ሽማግሌዎች በመግደልና በማሰር ነባሩ ህዝብ በእነዚህ ሀገር-አውል መሪዎቹ ስር ተደራጅቶ ይህ መሬት የእኔ ነው ብሎ እንኳን ብሎ እንዳይከራከርና እንዳይሟገት ታሪክ ነጋሪ መሪዎቹን አሳጥተውታል። ታሪኩን የማያውቅን ህዝብ ደግሞ ማጥፋት እጅግ ቀላል ነው። የወያኔ ትግሬዎች የአካባቢውን ታሪክ የሚያውቁትን አዋቂዎች በማጥፋትና በማሰደድ አካባቢው በታሪክ የትግሬዎች ይዞታ ነበር የሚል አዲስ ትርክት ፈጥረው ከትግራይ ያመጧቸውን ከሰባት መቶ ሺህ በላይ ሰፋሪዎች (የጦር መሳሪያ የታጠቁ ሰፋሪዎች ናቸው) በእነዚህ ቀድሞ የጎንደር ህዝብ ይዞታዎች ላይ ያሰፈሩበት ሂደት የአንድን ፋሽስት መንግስት የማህበራዊ ምህንድስና ፓሊሲዎች በተግባር የሚያሳዩ ምሳሌዎች ናቸው። ይህ የወያኔ ትግሬዎች ድርጊት በዓላማውም ሆነ በሚመራበት ፍልስፍና ሂትለር ለጀርመን ህዝብ የህይወት ማቆያ (Lebensraum) ያስፈልገኛል ብሎ አጎራባች የሆኑትን ፓላንድንና ቼኮዝሎቫኪያን በኃይል ወሮ ከያዘበት የናዚዎች ድርጊት፤ የፋሽስቱ የጣሊያን መንግስት መሪ ሙሶልኒ እስሎቬኒያን በኃይል ወሮና በቋንቋቸው እንዳይጠቀሙ፤ ባህላቸውን እንዳይገልጹ ካደረገበት፤ የእስሎቬኒያ ተወላጆች በግዴታ የጣሊያንን ቋንቋ እንዲጠቀሙ ካስገደደበት ድርጊት ከቶ የሚለይ አይደለም። ዛሬ በወልቃይትና ጸገዴ፤ ሁመራ ወዘተ በአማርኛ መናገር ያስቀጣል። እዚያ ያሉት አማሮች በአማርኛ መናገር፤ በአማርኛ አቤቱታ ማቅረብ፤ መዳኘት፤ መገበያየት፤ ሥልክ መደዋወል ወዘተ አይችሉም። ሚልበርን አግኝቼ ያነጋገርኳቸው የወልቃይት ተወላጅ ወልቃይት የሚኖረው የወንድማቸው ልጅ በአማርኛ ቋንቋ በሥልክ ሲያናግራቸው እየተሳቀቀ መሆኑንና አንዳንዴ ጥሻ ውስጥ ተደብቆ እንደሚያናግራቸው ገልጸውልኛል።

- - Eric Hobsbawm & Terrence Ranger, The Invention of Tradition, 1983 Cambridge University Press,

 

የሌሎችን ነገዶች ህልውና በማጥፋት የራሱን ዝርያዎች ህልውና የሚያስቀጥልበትን የጥፋት ዘዴዎችም ያካታታል። ብሄርተኛነት ሰዎች ራሳቸውን የሚገልጹባቸውን የተለያዩ7 መንገዶችና ዘርፈ-ብዙ ማንነቶችን ሁሉ ወደጎን በመተው ሁሉም ሰው ቋንቋን ወይም ኃይማኖትን በመሰሉ እጅግ ጠባብ የሆኑ የባህል መገለጫዎች አማካይነት ራሳቸውን እንዲገልጹ ያስገድዳል። ብሄረተኞች የጋራ ባህልን፤ የጋራ ታሪክን፤ የጋራ ትውስታን፤ ኩታ-ገጠም አሰፋፈርን ወዘተ የመሳሰሉ እጅግ ውሱን የሆኑ ገጽታዎችን ብቻ መዘው በማውጣት የማንነት ማጠንጠኛ አድርገው የብሄረተኛነትን8 ስሜት ይፈጥራሉ፤ ይቀሰቅሳሉ። ብሄረተኛነት ዛሬ በምናየው መልኩ በዓለም መድረክ ላይ ስሜታዊነትን አንግሶ ህዝብን በማንነቱ ማንቀሳቀስ ከጀመረ ሁለት መቶ ዓመታት በላይ ሆኖታል። በዓለም ታሪክ ውስጥ የብሄረተኛነት መብቀያና የብሄረተኞች ዋና የመፏከቻ ምድር ሆና የቆየችው አውሮፓ ነች። ብሄረተኛነት ወደ ሶስተኛው ዓለም ደግሞ የገባው በሃያኛው ክፍለ ዘመን ነው። በሀያኛው ምዕተ ዓመት ብቻ በብሄረተኛነት ሥም በተከሰቱ ጦርነቶች በዓለም ውስጥ አንድ መቶ ሚሊዮን ያህል ህዝብ ህይወቱን አጥቷል። በተለይም በአውሮፓ ውስጥ ከዚህ የበለጠ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ተፋናቅለዋል። እንደ አውሮፓ በብሄረተኛነት ብዙ ህዝብ ያለቀበት የዓለም ክፍል አይገኝም። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንኳን ሂትለርና ሙሶልኒ የሚባሉት የጀርመንና የጣሊያን መሪዎች በጀርመንና በጣሊያን ህዝብ ማንነት ላይ ያጠነጠነ አክራሪ ብሄረተኛነትን በመቀስቀስ፤ ከ60 ሚሊዮን በላይ ለሆነ የአውሮፓ ህዝብ ፍጅት እንደዚሁም ለአውሮፓ መፈራረስ ምክንያት ሆነዋል። የኤርትራ ብሄረተኛነት ምን ያህል የሰውና የቁሳዊ ሀብት ጥፋት እንዳስከተለ እዚህ ጋ መዘርዘር አያስፈልገኝም። በብሄረተኛነት ስሜት ፈንድቆ የነበረው የኤርትራ ህዝብ ያ ጊዜያዊ ደስታ በታላቅ ፍጥነት ወደ ታላቅ ሃዘን እንደተቀየረበት አይተናል። በሀገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ በትግራይ ህዝብ ማንነት ላይ መሰረቱን የጣለው የአክራሪ የትግራይ ብሄርተኛነትና የእሱ መገለጫ የሆነው የፋሽስት ሥርዓት በተለይ ከትግራይ በታች ለሚኖሩ በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ህይወት መጥፋትና መፈናቀል ምክንያት ሆኖአል። እዚህ ላይ ከሃያ ዓመት በፊት ህወሃትና ሻቢያ ከትግራይ በታች ያለውን የኢትዮጵያ ክፍል በኃይል ተቆጣጥረው ሀብቱን በህብረት እየዘረፉ ወደ ትግራይና ኤርትራ ሲያግዙ፤ ከዘረፉት የኢትዮጵያ ሃብት የአንበሳው ድርሻ ለእኔ ይገባኛል በሚል ምክንያት በፈጠሩት ጸብ ጦርነት ተነስቶ 80,000 ኢትዮጵያውያንና 20,000 ኤርትራውያን በጦርነቱ አልቀዋል። ይህንን የወንድማማች ህዝብ ጦርነት ተከትሎም በኤርትራ ድንበር ላይ የሚኖረው የትግራይም ሆነ የኤርትራ ህዝብ በጦርነቱ ምክንያት መፈናቀሉንና መጎዳቱን ሳልገልጽ አላልፍም።

 

ስለ ብሄረተኛነት ጥቂት ሃሳቦች

 

ብሄረተኛነት ከምንም ነገር በላይ የራስን ነገድ እጅግ አብልጦ መውደድን፤ የራስን ነገድ ምስል ማምለክን (የራስ አምልኮን) የሚያመለክት ጽንሰ-ሃሳብ ነው። ብሄረተኛነት አንድ ግለሰብ ከምንም ነገር በላይ ለነገዱ ያለው ታማኝነትና ተቆርቋሪነት ለሌሎች ሰዎች ወይም ጉዳዮች ካለው ታማኝነት ልቆ እንዲገኝ ያስተምራል። ብሄርተኞች ተከታዮቻቸው ለራሳቸው ነገድ ተወላጆች እጅግ የተጋነነ ፍቅር እንዲያሳዩ ያስተምራል። በዚያው መጠን ብሄርተኞች ተከታዮቻቸው የሆኑ የእነሱ ነገድ ተወላጆች ከእነሱ ነገድ ውጭ ያሉ የሌሎች ነገዶች ተወላጆችን እንዲጠሉ፤ እንዲጠየፉ፤ እንዲጎዱና ህልውናቸውን ጭምር እንዲያጠፉ ያበረታታሉ፤ ያነሳሳሉ። ብሄርተኛነት የአንድን ነገድ ወይም ህዝብ የወል ማንነት ዋነኛ የፓለቲካ ስልጣን ምንጭ አድርጎ ይወሰዳል። በዚህም ምክንያት ብሄረተኞች አንድ ግለሰብ ከራሱ ነጻ ፈቃድ በሚወጣ ምርጫ ይወክሉኛል የሚላቸውን የህዝብ ወኪሎች በመምረጥ ባንድ ሀገር የፓለቲካ ህይወት ውስጥ የሚሳተፍበትን ዲሞክራሲያዊ የሆነ ሥርዓትም ሆነ አሰራር አያከብሩም፤ አይቀበሉም። ብሄረተኞች እያንዳንዱ የአንድ ሀገር ዜጋ የሆነ ግለሰብ በራሱ አይምሮና ህሊና ተመርቶ በነጻነት የሚያደርገውን ምርጫ እጅግ አድርገው ይጠሉታል፤ ይዋጉታልም። ብሄረተኞች ለስሙ የራስን ዕድል በራስ በመወሰን መብት እናምናለን ይበሉ እንጂ የዚህ መብት መሰረት የሆነውን የግለሰብ ነጻነት የተባለውን የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ዋነኛ መገለጫ የሆነ መብት መከበር አምርረው ይጠላሉ። ብሄረተኞች ነጻ የሆኑ ግለሰቦች በራሳቸው ሃሳብ ተመርተው የሚያደርጉትን ምርጫም ሆነ ውሳኔ

አጥብቀው ይቃወማሉ። ብሄረተኞች ከግለሰብ መብት (individual rights) ይልቅ የቡድንን መብት (group rights) በማስቀደም ጥቂት ልሂቃን በአንድ ህዝባችን ወይም ነገዳችን ነው በሚሎት ህዝብ ስም ዴሞክራሲያዊ ሳይሆን የአምባገነናዊ የፓለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ይደግፋሉ፤ ያበረታታሉ። ብሄረተኞች የግለሰብ መብት በዋናነት መከበር ለቡድን መብት መከበር መሰረታዊ ዋስትና መሆኑን አይቀበሉም።

ብሄረተኞች ሰላምና ፍትህ ሊረጋገጥ የሚችለው ቡድን-ተኮር የሆነ በነገድ ማንነት ላይ የተመሰረተ መብት የመብቶች ሁሉ መሰረት ሲሆን ብቻ ነው ብለው ያምናሉ። ብሄረተኞች የቡድንን መብት ለማስቀደም ያላቸው ጭንቀትና የባህል መስፈርቶችን (ቋንቋን፤ ልማድን፤ ኃይማኖትን) ብቻ ዋነኛ የማንነት መገለጫዎች ለማድረግ የሚያደርጉት ሩጫ ዓይነተኛ የፓለቲካ ባህርያቸው መገለጫ ነው። ወያኔ በመሳሪያነት የተጠቀመበትና ኢትዮጵያን የከፋፈለበት፤ ይህ የአንተ ክልል አይደለምና ከክልሌ ለቀህ ውጣ የሚልበት የብሄር-ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሚለው በቡድን መብት ላይ የተመሰረተ የፓለቲካ ሥርዓት፤ የዜግነት መብት ዋና መሰረት የሆነውን የግለሰብ ነጻነት የሚጻረርና በነገድ ማንነት ላይ የተመሰረተን የቡድን መብት የሚያስቀድም ነው። የግለሰብን መብት በሚደፈጥጥ የቡድን መብት ላይ የሚመሰረት የፓለቲካ ሥርዓት ምንጊዜም ቢሆን ዲሞክራሲንም ሆነ ነጻ የሀገር ዜግነትን መብት ማረጋገጥ አይችልም። ዲሞክራሲያዊ የፓለቲካ ሥርዓት የእያንዳንዱን ግለሰብ መብት፤ ህልውናና ነጻነት በሚጋፋ የቡድን መብት ላይ ከቶ ሊመሰረት አይችልም። የዲሞክራሲ እሴቶች የእያንዳንዱን የአንድ ሀገር ዜጋ ሰብዓዊነት ያስከብራሉ እንጂ በቡድን መብት ላይ የተመሰረተን ለነገድ ማንነት ቅድሚያ የሚሰጥ ህገ-መንግስት በመደንገግ አንተ የዚህ ነገድ አባል ስላልሆንክ ይህ መብት ለአንተ አይገባህም አይልም። የእያንዳንዱን የአንድ ሀገር ዜጋ የግል መብት የሚያረጋግጥ ዲሞክራሲያዊ የፓለቲካ ሥርዓት አንተ መጤ ስለሆንክ በዚህ ክልል ውስጥ ሙሉ መብት አይገባህም፤ በዚህ ክልል ውስጥ ባለ ሙሉ መብት የሆኑት የክልሉ ባለቤት የሆኑት የእከሌ ነገድ ተወላጆች ናቸው እያለ በአንድ ሀገር ዜጎች መካከል ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ እንደታየው ልዩነትን አይፈጥርም። በግለሰብ መብት ላይ የተመሰረተ ዲሞክራሲያዊ የፓለቲካና የህግ ሥርዓት አንዱን ኢትዮጵያዊ አብልጦ ሌላውን ኢትዮጵያዊ አያሳንስም። ዛሬ በኢትዮጵያ ሥራ ላይ የዋለው የቡድን መብትን መሰረት ያደረገው የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ዘረኝነትን ህጋዊ ያደረገ፤ የአፓርታይድን ሥርዓት አራማጅ የሆነ ህግ ነው የሚባለው በማንነት ላይ ለተመሰረተ የቡድን መብት ቅድሚያ የሚሰጥ በመሆኑ ነው። ይህ የነገድ ማንነትን መሰረት አድርጎ የሚረቀቅ ህገ-መንግስት በተፈጥሮው አግላይና ከፋፋይ የሚሆንበት ምክንያት የራስን ነገድ ከሁሉ ነገዶች አብልጦ በሚያይ የብሄረተኛነት ፍልስፍና ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው። ማንም ተራ ሰው እንኳን ሊረዳው እንደሚችለው ፓለቲካ ቡድን-ተኮር በሆነ የነገድ ማንነት ላይ ተመስርቶ ሲደራጅ አንድን ሰው በነገድ ማንነት ሚዛንና መስፈርት እየለካ ያገለዋል። በዚህም ምክንያት የነገድን ማንነት መሰረት ያደረገ ባለመብትነት ሥራ ላይ በዋለበት ኢትዮጵያን በመሰለች የብዙ ነገዶች ሀገር ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ ነገዶች ተወላጆች በቡድን መብትና በነገድ ማንነት ላይ በተመሰረተ ህገ መንግስት በሚመራ ሀገር ውስጥ በእኩልነት ሊታዩና ሊስተናገዱ አይችሉም። አንድ በውስጧ የሚኖሩትን የተለያዩ ነገዶች በእኩልነት የሚያስተናግድ፤ የግለሰብን መብት ዋነኛ የመብቶች ሁሉ መሰረት ያደረገ ህገ-መንግስት የሌላት ሀገር ደግሞ ህዝቧ አንድነትና ስምምነት ሊኖረው አይችልም፤ ፓለቲካዊ ሥርዓቱም ዲሞክራሲንና የአንድን ሀገር ዜጎች እኩልነት የሚያረጋግጥ አይሆንም። ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሰውን በነገድ ማንነቱ ምክንያት አያገልም፤ አይለይም። በነገድ የተደራጁ የፓለቲካ

 

ድርጅቶች ደግሞ የብዙ ነገዶች(multi-ethnic) መኖሪያ ለሆነች ኢትዮጵያን ለመሰለች ሀገር ዲሞክራሲን ሳይሆን አምባገነንነትን፤ አንድነትን ሳይሆን መከፋፈልን ነው የሚያመጡት። የወያኔ መንግስት ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ያደረገው ይህንን ነው። ዲሞክራሲያዊ የፓለቲካ ሥርዓት በግለሰብ መብት ላይ ስለሚመሰረት የቡድን መብትን የሚያስቀድሙ ብሄረተኞች እንደሚያደርጉት አንድን ግለሰብ በነገድ ማንነቱ መብት አይነሳውም ወይም አይሰጠውም። ቬስና ፓኦፖቭስኪ የተባለችና በሀገሯ ውስጥ ስለተከሰቱ የነገዶች ግጭት ላይ በጻፈቻቸው ጥልቅ የጥናት ጽሁፎቿ የምትታወቅ የዩጉዝላቪያ ምሁር የሰው ልጆች በነገድ ማንነት ላይ በሚመሰረት መብት ነጻነታቸውን ሊጎናጸፉ እንደማይችሉ

በሚከተለው መልክ ታስረዳለች። “ዘመናዊ የዲሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ የተመሰረተው በነገድ ማንነት ላይ ሳይሆን በግለሰብ ነጻነትና ምርጫ ላይ ነው። አንድ ግለሰብ የፖለቲካ ነጻነቱን (የዜግነት መብቱን)  የሚቀዳጀው በነገዱ አማካይነት ሳይሆን ራሱ ነጻ ሰው ሆኖ የሚፈልገውን መምረጥ ሲችል ብቻ ነው። በትክክለኛ መንፈሱ አንድ ግለሰብ የፖለቲካ ነጻነቱን የሚጎናጸፈው በነገዱ አማካይነት ሳይሆን ራስ-

በቅ/ነጻ (independent) ዜጋ ሆኖ ነው9”(ጥቅሱን ከእንግሊዘኛው ወደ አማርኛ የተረጎመው - አሰፋ ነጋሽ)። ብሄረተኛነት ሄዶ ሄዶ መጨረሻው ላይ የዚያን ብሄረተኛ ማህበረሰብ መገለጫ የሆነ የራስ ሰንደቅ ዓላማ ከሚያውለበልብ የአዲስ ሀገር ምስረታ ሂደት ውስጥ ይገባል። ብሄረተኞች ያንድ ባህል፤ ታሪክና መልክዓ-ምድራዊ አሰፋፈር ተጋሪዎች ናቸው የሚሏቸውን አንድ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ የአንድ ነገድ አባላት ኩታ-ገጠም በሆነ አከላለል ሥር አንድ ላይ በማምጣትና በአንድ ዓይነት ብሄረተኛ አመለካከት አይምሮአቸውን በመቅረጽ በአንድ ነገድ ማንነት ላይ የተመሰረተ የፓለቲካ ሥርዓትና መንግስት ማቋቋም ዋነኛ ግባቸውና ዓላማቸው ነው። ኩታ-ገጠም ቦታ ላይ አንድን ነገድ ለማስፈር የሚደረገው ጥረት ደግሞ ወያኔ በወልቃይትና ጸገዴ፤ በጸለምት፤ በሰሜን ወሎ፤ በቤኒሻንጉል፤ በጋምቤላ ወዘተ እንዳደረገው በግዴታ የሌሎችን ነገዶች ዘር ወደ መመንጠርና (ethninc cleansing) ወደ ጅምላ የዘር ፍጅት (genocide) ያመራል። ብሄረተኞች በጥላቻ መንፈስ ተነስተው ከእነሱ ውጭ ያሉ ነገዶችን ዝርያዎች በጅምላ የሚመነጥሩበትን ምክንያትና ይህንን ለማድረግ የሚያስችላቸውን የስነልቦና ዝግጅት ከዚህ ቀጥዬ አስረዳለሁኝ።

 

ከራስ ነገድ ውጭ ያለውን ሰው ከሰውነት ደረጃ ዝቅ አድርጎ የመመልከት ዝንባሌ ምን ያስከትላል? ኤሪክ ኤሪክሰን የተባለ አሜሪካዊ የስነልቦና ሊቅ (ሳይኮሎጂስት/ሳይኮአናሊስት) የሰው ልጆች የሆኑ የአንድ ነገድ ተወላጆች ብሄረተኛነት በሚፈጥረው እብደት ህሊናቸውን አሽቀንጥረው በመጣል በቋንቋም ሆነ በባህል መገለጫዎቻቸው ከእነሱ ነገድ የተለዩ ናቸው የሚሏቸውን የሌሎች ነገዶች ተወላጆች እንደ ክፉ አውሬ ቆጥረው የሚያጠፉበትን ስነልቦናዊ ሂደት ሲውዶስፔስዬሽን

speciation10) ብሎ ሰይሞታል። ይህም ማለት የአንድ ነገድ ተወላጆች ቋንቋን በመሳሰሉ የባህል መገለጫዎች ከእነሱ የሚለዩትን የሌላ ነገድ ተወላጆች ከሰብዓዊነት ደረጃ ዝቅ አድርገው በመመልከት ለጥቃትና ለፍጅት ይዳርጓቸዋል ማለት ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ለጅምላ ፍጅት የሚዳረጉ ወይም ለጅምላ ፍጅት በሰለባነት የሚታጩ የአንድ ነገድ ተወላጆች እንደ ሰው ሳይሆን ከሰው በታች በሆነ ደረጃ ላይ ያሉ ፍጥረቶች ተደርገው እንዲታዩ ይደረጋል። ከዚህ ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ፍልስፍና በመነሳት ነው የጀርመን ናዚዎች አይሁዶችን ከሰው ደረጃ በታች ዝቅ ያሉ (በጀርመንኛው unter-mensch ወይም በእንግሊዘኛው sub-human) ናቸው ብለው በመፈረጅ ስድስት ሚሊዮን ይሁዲዎችን እንደዚሁም ሌሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ የእስላቭ (Slavic race/people) ዝርያ ያላቸውን ህዝቦች የፈጁት። በሩዋንዳ የሚኖሩት የሁቱ ነገድ ተወላጆች የሆኑ አክራሪዎችም የቱትሲን ነገድ ተወላጆች በጅምላ ከመፍጀታቸው በፊት ቱትሲዎች በረሮዎችና (cockroaches) እባቦች (snakes) ናቸው ብለው በነፍሳት ምስል መስለው ይገልጿቸው ነበር። ከዚያ በኋላ ሁቱዎች እነዚህን እንደ በረሮም ሆነ እንደ እባብ የሚያዩአቸውንና በነፍሳት የመሰሏቸውን ቱትሲዎች ሲፈጁ አንዳችም ዓይነት የህሊና መሸማቀቅ አልደረሰባቸውም። ደርግን በጋራ በሚታገሉበት ጊዜ የወያኔ ትግሬዎችም ሆነ ኤርትራውያን ወንድሞቻቸው የሆኑት ሻቢያዎችና ጀብሃዎች የአማራን ተወላጆች በትግርኛ ሃድጊ (በአማርኛ አህያ ማለት ነው) እያሉ በእንስሳነት ይመስሉ እንደነበር ማስታወሱ ተገቢ ነው። እንግዲህ በዓለም ላይ የተፈጸሙ የጅምላ ፍጅቶችን ስንመለክት የአንድ ነገድ ተወላጆች ተነስተው የሌላውን ነገድ ተወላጆች በጅምላ ከመፍጀታቸው በፊት እነዚህን ለጅምላ ፍጅት የሚዳርጓቸውን ህዝቦች ከሰው በታች በሆኑ የእንስሳነትና የነፍሳት መገለጫዎች እንዲወከሉ ያደርጋሉ (dehumanization and animalization of the enemy)። ከዚያ በኋላ እንደ እንስሳም ሆነ ነፍሳት የሚታይን ሰው ወይም ህዝብ መፍጀት ለህሊና የሚሰቀጥጥ ጉዳይ አይሆንም። ከዚሁ ርዕስ ሳልወጣ በወልቃይትና ጸገዴ ውስጥ ስለሆነው ነገር ትንሽ ላካፍላችሁ። በወልቃይትና ጸገዴ ውስጥ በርኖስ የሚባል አልፎ አልፎ የሚታይ ክፉ የሆነ ጸረ-ሰብል ትል አለ። ይህ ትል ማናቸውንም ተክል፤ ቅጠልም ሆነ ቡቃያ ሁሉ ያጠፋል። ስለዚህ ይህ ትል በታየበት ዓመት ገበሬዎች በመሬት ላይ ዘርተው ያበቀሉትን ሰብል ሁሉ ስለሚያውድመው ገበሬዎቹን ለረሃብና ለሞት ይዳርጋቸዋል። የወያኔ ትግሬዎች በ1972 ዓ. ም. መኮንን ዘለለው በሚባል በግማሽ ወልቃይቴ፤ በግማሽ ትግሬ የሆነ የውስጥ አዋቂ ጥናት በመታገዝ፤ በእሱ መንገድ መሪነት የወልቃይትና ጸገዴን መሬት ወረው11 ከያዙ በኋላ የአካባቢውን ነባር ህዝብ በጅምላ ለማጥፋት ተነሱ። ታዲያ ነባሩን የአማራ ህዝብ በጅምላ ከማጥፋታቸው በፊት እነዚህን የአማራ ተወላጆች የሆኑ የወልቃይትና ጸገዴ ተወላጆች ሰብል አጥፊ በሆነ ክፉ ትል በመመሰል በርኖስ እያሉ ይጠሯቸው እንደነበረ በዚህ ዓመት ውስጥ በየካቲት 23 ቀን 2010 ዓ. ም. ከሙያዬ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ለስብሰባ (psychiatric conference held at Melbourne) ሜልበርን (አውስትራሊያ) ሄጄ በነበርኩበት ጊዜ እዚያ ፈልጌ ቃለ-መጠይቅ ያደረግሁላቸው የወልቃይት አዛውንት ነግረውኛል። እንግዲህ የወያኔ ትግሬዎች አክራሪ የትግራይ ብሄረተኛነት በፈጠረው የፋሽስት አመለካከት ህሊናቸው ስለታወረ የወልቃይትና ጸገዴን አማራዎችን በርኖስ እየተባለ በሚጠራ ሰብል አውዳሚ የሆነ ክፉ ትል መስለው ለጅምላ ፍጅት ሊዳርጉ ችለዋል። ገብሩ አስራት12 የተባለው በጸረ-ደርጉ ትግል ወቅት የወልቃይት አስተዳዳሪ የነበረና በጊዜው ከወያኔ ድርጅት መሪዎች አንዱ የነበረው ባለሥልጣን የወልቃይት ተወላጆች የሆኑ ሰዎች ለአቤቱታ እሱ ጋ በመጡበት ጊዜ እናንተ በርኖስ ናችሁ ከፊቴ ጥፉ ብሎ እንዳባረራቸው እኚህ ሚልበርን አግኝቼ ያነጋገርኳቸው የወልቃይት ሰው13 ገልጸውልኛል። እንግዲህ የትግራይ ፋሽስቶች የበቀለውን ቡቃያ ሁሉ በሚያጠፋና በሚያወድም በርኖስ በሚባል ክፉ ትል የመሰሏቸውን የወልቃይትና ጸገዴ አማሮች ጉድጓድ ውስጥ ከተው እርጥብና ደረቅ እንጨት ቀላቅለው በማንደድ በጭስ14 እያፈኑ በጅምላ ሲፈጁ፤ ወንዶቻቸውን እየገደሉ ሴቶቻቸውን እብሪተኛ

 

- -በ1972 ዓ. ም. የወያኔ ትግሬዎች የወልቃይትንና ጸገዴን አካባቢዎች ወረው መሬቱን በኃይል ሲቀሙ ለወያኔዎች በዚህ አካባቢ ስላለው ሁኔታ ቅደመ-ጥናት አድርጎ የወያኔ ትግሬዎችን ጦር መንገድ እየመራ የመጣው መኮንን ዘለለው የሚባለውና እዚያው ወልቃይት ያደገ ሰው ነው። ይህ ሰው አዲ-ጎሹ (ወልቃይት ውስጥ የሚገኝ ሥፍራ) አካባቢ ክፍለ-ህዝቢ በሚባለው የህወሃት ድርጅት አካል ውስጥ ይሰራ ነበር። መኮንን ዘለለው በዚህ ኃላፊነቱ ተመድቦ በሚሰራበት ወቅት የህወሃትን አገዛዝ የሚቃወሙትን የወልቃይት ተወላጆች የሆኑ ተቃዋሚዎችን በመግደል፤ በማሰር፤ አሳፍኖ ደብዛቸውን በማጥፋት፤ በማሰደድ ወዘተ ተግባሮች ላይ ተሰማርቶ ቆይቷል። ይህ ሰው ወልቃይትና ጸገዴን ጥያቄ አስመልክቶ ከአውስትራሊያ በሚተላለፍ SBS በሚባል የአማርኛ ሬድዮ ለቀረበለት ጥያቄ የሚከተለውን አስገራሚ መልስ ሰጥቷል። ‹‹መጀመርያ ማን ነበረ የሚለው ጥያቄ መልሱ ትግርኛ ነው። ወልቃይት ከመጀመሪያው ጀምሮ ትግሪኛ ተናጋሪ ነው። ወደ ወልቃይት የመጣው አማርኛ እንጂ ትግሪኛ አይደለም። አማርኛ የመጣው ደግሞ በፖሊስ፣ በበለጠ ደግሞ አዝማሪዎች መጥተው ነው ያስፋፉት” (ምንጭ SBS Amharic Radio April 22, 2016) በማለት በእብሪት ምላሽ የሰጠ ሰው ነው። በወልቃይትና ጸገዴ ለተፈጸመው የዘር ማጥፋት ሊጠየቅ የሚገባው መኮንን ዘለለው በአሜሪካን ሀገር በነጻነት በስደት የሚኖር ሰው ሲሆን Tigrean Alliance for National Democracy (TAND) የሚል የዳቦ ስም ያለው የወያኔ ተቃዋሚ ነኝ የሚል ሀሰተኛ ድርጅት አባል ነው። ይህ ሰው በቅርቡ አረጋዊ በርሄና ግደይ ዘርዓጽዮን ከሚባሉት የፋሽስታዊው የህወሃት ድርጅት የቀድሞ መሪዎች ጋር ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል።

 

- -ገብሩ አስራት የትግራይ ተወላጅ ሲሆን የህወሃት አንዱ መሪ ነበር። በአስራ ሰባቱ የጸረ-ደርግ ትግል ዘመን ወቅት ህወሃት በታህሳስ 1972 ዓመተ ምህረት የወልቃይትና ጸገዴን ግዛቶች ከተቆጣጠረ በኋላ በእነዚህ ቦታዎች በአስተዳዳሪነት ሰርቷል። ገብሩ ከእነ መለስ ዜናዊ ቡድን ጋር በሥልጣን ሽኩቻ ተጣልቶ ተቃዋሚ ሆንኩኝ ካለ በኋላ በ2006 ዓ. ም ጽፎ ባሳተመው “ሉአላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ” በሚለው መጽሃፉ ውስጥ ወልቃይትና ጸገዴ ውስጥ እሱ አስተዳዳሪ በነበረበት ጊዜ ስለተፈጸመው መጠነ-ሰፊ የሆነ የአማራን ህዝብ ዘር የማጽዳት ድርጊት መጸጸቱን የሚገልጽ አንዳችም ነገር አልጻፈም። ይህ ሰው የአክራሪ ብሄረተኛ ድርጅት መሪ እንደነበር ቢታወቅም ወያኔን የሚቃውም አረና ትግራይ የሚባል የተቃዋሚ ድርጅት ፈጠረ ተብሎ በተቃዋሚው ጎራ ይጨበጨብለት ነበር። በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ይህንን ሰው የመሳሰሉ፤ ወልቃይትና ጸገዴን በመሳሰሉ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ በዜጎቻችን ላይ አስከፊ የዘር ፍጅት ያስፈጸሙ፤ ህዝብን በማንነቱ ምክንያት በማፈናቀል ተግባር የተሳተፉ አክራሪ የትግራይ ብሄረተኞች በተቃዋሚነት ስም ሲሞካሹ ማየቱ ያሳዝናል። የኢትዮጵያ ህዝብ መረዳት የሚገባው ነገር ቢኖር ፋሽስቶችን በሽንገላም ሆነ በፍቅር ማሸነፍ እንደማይቻል ነው።

 

- -ይህ መረጃ ከአራት ወር ተኩል በፊት ወደ ሚልበርን (አውስትራሊያ) በሄድኩበት ወቅት በየካቲት 23 ቀን 2010 ዓ. ም. ከሁለት በህወሃት ጥቃት ምክንያት ከሀገራቸው ወጥተው በስደት በአውስትራሊያ ከሚኖሩ የወልቃይት ጸገዴ ተወላጆችና አዛውንቶች ጋር ካደረግሁት ቃለ-መጠይቅ የተወሰደ ነው። የእነዚህ ቃለ መጠይቅ ያደረግሁላቸው ሰዎች አንዳንድ የተረፉ ዘመዶች አሁንም ድረስ በወልቃይት ውስጥ ይኖራሉ። በዚህ ምክንያት ወያኔዎች እጅግ በሚታወቁበት የበቀል ስሜት ተነሳስተው በዘመዶቻቸው ላይ ጥቃት ሊያደርሱባቸው ስለሚችሉ ለእነዚህ ዘመዶቻቸው ደህንነት ስል ይህንን መረጃ የሰጡኝን ሰው ሥም እዚህ ጋ ከመግለጽ ተቆጥቤያለሁኝ።

 

- -የትግራይ ፋሽስቶች አማራውን ህዝብ ጉድጓድ ውስጥ እየከተቱ በጭስ አፍነው እንደገደሏቸው ያሳወቀን የቀድሞው የህወሃት አባልና ዛሬ በአውስትራሊያ የሚገኘው አቶ ገብረመድህን ዓርዓያ ነው። ይህ ሰው ወያኔን ከሚታገሉት በጣት ከሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ውስጥ አንዱ ነው።

 

የሆኑ የወያኔ ትግሬዎች መጫወቻ ሲያደርጉዋቸው15 ምንም ዓይነት የሰብዓዊነት ስሜት አልተሰማቸውም። ለምን ቢሉ እነዚህ የወያኔ ትግሬዎች እየፈጁ ያሉት አማራ የሚባል ሰው ሳይሆን አውዳሚና አጥፊ የሆነውን በርኖስ የሚባል ጸረ-ሰብል የሆነ ክፉ የሰው ልጆች ጠላት ስለሆነ። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በፋሽስቱ የወያኔ ትግሬዎች መንግስትና ግብረ-አበሮቹ በሆኑ በየነገዱ ሥም የተደራጁ አገልጋዮቹ የተፈጸመው ኢ-ሰብዓዊና ለህሊና የሚሰቀጥጥ ማንነትን መሰረት ያደረገ ፍጅት የተካሄደው በዚህ ዓይነት መንገድ ህሊናቸው በታወረ አክራሪ ብሄረተኞች ነው። ባለፈው ሰሞን በአሶሳ ደገኛ በሚባሉ የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች ላይ በወያኔ ትግሬዎች መንግስት አስተባባሪነትና በተደራጁ አንዳንድ የአካባቢው ነባር ተወላጆች በሚባሉ ግብረ-አበሮቻቸው ፈጻሚነት የተካሄደው ዘግናኝ ጭፈጨፋ፤ በአዋሳ ውስጥ በሲዳማ ተወላጆችና በወላይታ ተወላጆች መካከል ሆን ተብሎ በወያኔ ትግሬዎች መንግስት የተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት ያየነው እጅግ ዘግናኝና ሰብዓዊነታችንና ኢትዮጵያዊ የወል ማንነታችንን ጥላሸት የሚቀቡ ድርጊቶች የተፈጸሙት ባለፉት አርባ ሶስት ዓመታት ውስጥ የአክራሪ የትግራይ ብሄረተኛነት በፈጠራቸው፤ የእነዚህ የክፋት ድርጊቶች ባለቤትና አስፈጻሚ በመሆናቸው ጀግንነት በሚሰማቸው የትግራይ ፋሽስቶች ነው። ይህ ሁሉ ጥፋት በወያኔ ትግሬዎች የሚፈጸመው ኢትዮጵያን በመከፋፈልና በማዳከም የአንድን አናሳ ነገድ ጥቅም የበላይነት ለማረጋገጥና ለማስከበር ነው። በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ በሚደረግ ነጻ ምርጫ በሚመሰረት መንግስት ውስጥ በቁጥር አናሳ የሆኑት የወያኔ ትግሬዎች ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት እንዳደረጉት የኢትዮጵያን ሀብት የአንበሳ ድርሻ መውሰድ እንደማይችሉ ይረዳሉ። ስለዚህ ለእነሱ ይህንን መሰል በዘር ማንነትና በቡድን መብት ላይ የተመሰረተን አገዛዝ ማስቀጠል የህልውናቸው መሰረት ነው።

 

-----------------------------------------የክፍል አንድ መጨረሻ------------------------------------------

 

ይህ ጽሁፌ ክፍል አንድ ሲሆን ክፍል ሁለት ከዚህ ቀጥሎ ይመጣል።

 

- -ከላይ ሚልበርን ቃለ-መጠይቅ ያደረግሁላቸው የወልቃይት ሰዎች እንደ ነገሩኝ አንድ የትግራይ ተወላጅና ታጣቂ የሆነ ባለ ጊዜ አዲ ኸርድ እና አጠቀር በሚባሉ ሁመራ ውስጥ በሚገኙ ስፍራዎች ላይ ባሎቻቸው በወያኔ ትግሬዎች ጦር እንዲሰደዱ ከተደረጉ የአማራ ሴቶች ላይ 16 ልጆችን ወልዷል። እንደዚሁም አንድ የወያኔ አባል የሆነ ትግሬ ወንድ ባሏን ያሰረባትን አንዲት የወልቃይት ተወላጅ የሆነች የአማራ ሴት በማስገደድ ሶስት ልጅ አስወልዷታል። ይህ ድርጊት አንድ ግለሰብ በአንዲት ሴት ላይ የሚፈጽመው ተራ የግል ጥቃት ሳይሆን ሆን ተብሎ ሴቷ የወጣችበትን ነገድና ማህበረሰብ ለማዋረድና የዚህን ነገድ ማንነት ለማጥፋት የሚደረግ

የዘር ማጥፋት ድርጊት አካል ነው (sexual violence in a context of ethnic conflict is a systematic way of humiliating an ethnic group identified as an enemy by way of destroying the collective identity of this group designated as a mortal enemy)። ከታህሳስ 1972 ዓ. ም. ጀምሮ

የወልቃይትና ጸገዴ ተወላጆች በሆኑ የአማራ ተወላጆች ላይ ሥልታዊ በሆነ መንገድ የተፈጸመው ይህን መሰል ወሲባዊ ጥቃት ማንነትን መሰረት ያደረገ የዘር ማጥፋት እርምጃ አካል ነው። በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በዚህ ደረጃና ስፋት ይህን መሰል ማንነትን መሰረት ያደረገ ወሲባዊ ጥቃት አልተካሄደም። በወልቃይትና ጸገዴ የሚደረገው የወሲብ ጥቃት በወያኔ ወታደሮች ብቻ ሳይሆን እዚያ በሰፈሩና ልዩ የባለመብትነት ስሜት በሚሰማቸው መሳሪያ የታጠቁ የትግራይ የወንድ ሰፋሪዎች ጭምር የሚፈጸም ነው። ዛሬ በወልቃይትና በጸገዴ የአማራ ወንዶች በስፋት እንዲገደሉና እንዲሰደዱ ስለተደረገ የእህት ልጅ እንጂ የወንድም ልጅ አለኝ እንደማይባል እኔ ያነጋገርኩዋቸው የወልቃይትና የጸገዴ ተወላጆች በሀዘንና በቁጭት ስሜት ነግረውኛል። ከወልቃይት ቀጥሎ በኦጋዴንም በኢትዮጵያውያን ሶማሌ ሴቶች ላይ የወያኔ መንግስት ጦር ከኦጋዴን ነጻ አውጭዎች ጋር በሚያደርገው ጦርነት ሳቢያ በተደጋጋሚ ወሲባዊ ጥቃት እንደፈጸመ Amnesty International እና Huaman Rights Watch የተባሉት ድርጅቶች ዘግበዋል። በኦጋዴን ውስጥ በኢትዮጵያ ሶማሌዎች ላይ የተፈጸመው ግፍና መከራ በተመለከተ የግፉ ሰለባዎች Graham Peebles ለሚባል ጋዜጠኛ ተሰደው ከሚገኙበት ከኬንያ የስደተኛ ጣቢያ የሰጡትን እጅግ አሳዛኝና ዘግናኝ የሆነ ምስክርነት Ogaden: Ethiopia’s Hidden Shame በሚል ርዕስ በዩቲዩቭ ተለቋል። ማንኛውም ኢትዮያዊ ይህንን ቃለ-መጠይቅ አይቶትና ሰምቶት በኦጋዴን በወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ የተፈጸመውን ግፍ እንዲረዳ ጥሪ አደርጋለሁኝ። በኢትዮጵያ ጉዳይ ሳይታክት የሚጽፈውና ይህንን ግፈኛ ሥርዓት በሀቀኝነት ሳያሰልስ እያጋለጠ ላለው ለዚህ ጋዜጠኛ ባርኔጣዬን በአክብሮት አንስቼለታለሁ።

 

1- Ellie Kedourie, Nationalism, 1960

2- Eric Hobsbawm, Nations and Nationalism Since 1780, Cambridge University Press, 1990

3- Hans Kohn, Nationalism: Its Meaning and History, 1965

4- Ernest Gellner, Thought & Change, 1964

5- Social engineering ወይም በአማርኛ ትርጉሙ

7- Eric Hobsbawm, Nations and Nationalism Since 1780, Cambridge University Press, 1990

8- John Hutchinson and Anthony D. Smith, Ethnicity, Oxford University Press, 1996

9-Vesna Popovski, Yougoslavia: Politics, Federation, Nation, in Federalism, the Multiethnic Challenge, Graham

Smith et al 1995

10- Erik H. Erikson, Identity, Youth and Crisis, 1968
https://amharic-zehabesha.com/archives/185679

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...