Thursday, June 22, 2023
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ሰኔ 19፣ 2023
በቅርቡ ከላይ በተጠቀሰ አርዕስት ስር በባይሳ ዋቅ-ወያ የተጻፈውን በጣም አሳሳችና በትውልድ ኢትዮጵያውያን፣ ነገር ግን ደግሞ የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው፣ በአቢይ አገዛዝ ላይ የሚያደርጉት በተለያየ መልክ የሚገለጽ ዘመቻ ተገቢ አለመሆኑና እንደ “ወንጀልም የሚቆጠር” ነው የሚለውን ጽሁፉን በጥሞና አነበብኩት። ባይሳ ዋቅ-ወያ ሀተታውን የሚጀምረው “ህዝብ ለህዝብ” በሚለው መድረክ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ምሁራን በሚሳተፉበት መድረክ ላይ በአቶ በቀለ ገብረዔል የቀረበውን ጥያቄና፣ ጠያቂውም ለጥያቄውም መልስ ለማግኘት ያልቻለበትን ጉዳይ በማንሳት ነው። በባይሳ ዋቅ-ወያ ዕምነትም አቶ በቀለ ገብርዔል ለጥያቄው መልስ ለማግኘት ያልቻለው ዋናው ምክንያት በመድረኩ ውስጥ የተሳበሰቡት ምሁራን “በራሳቸው ላይ ዕምነት ስላጡ ነው” በማለት በጭፍን ይወነጅላል። ይሁንና የአቶ በቀለ ገብርዔልን ጥያቄ አስመልክቶ በዚህ ጸሀፊ በቂ ሀተታ እንደተሰጠውና፣ ይህንንም ሃሳቤን አንዳንዶች በመጋራት የአቶ በቀለ ገብርዔል ጥያቄ በኢትዮጵያ ምድር ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ካለማንበብና፣ የአቢይ አገዛዝ የሚፈጽመውን ወንጀለኛ ድርጊት በሚገባ ግንዛቤ ውስጥ ለማስገባት ካለመቻል የሚነሳ አላስፈላጊ ጥያቄ ነው በማለት ውድቅ ለማድረግ ተችሏል። ባይሳ ዋቅ-ወያ የመድረኩ ተሳታፊ ቢሆንም፣ በእኔም ሆነ በአንዳንዶች ለአቶ በቀለ ገብርዔል ጥያቄ የተሰጠውን መልስ ሳያነብ፣ ወይም ደግሞ አንብቦ ምንም መልስ እንዳልተሰጠ በጭፍኑ ምሁራኑን መወንጀሉ ተገቢ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን በጣምም አሳሳች ነው።
ለማንኛውም ባይሳ ዋቅ-ወያ ሰፋ ባለው በሰባት ገጽ ሀተታውና ውንጀላው ለማለትና ሊያሳምነን የሚፈልገው፣ የአቢይ አህመድ አገዛዝ የማህበራዊ ውል(Social Contract) ያደረገው ከኢትዮጵያ ህዝብ፣ በተለይም ከመረጠው ህዝብ ጋር ስለሆነ በውጭ አገር የምትኖሩና የውጭ አገር ዜግነት ያላችሁ፣ ነገር ግን ደግሞ ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የሆናችሁ በተለይም በአቢይ አህመድና በአገዛዙ ላይ የምታደርጉት ዘመቻ ትክክል አይደለም፤ “የስርዓት ለውጥ መምጣት አለበት”፤ “የሽግግር መንግስትም መቋቋም አለበት”፤ “አገዛዙም በጦር ትግል ከስልጣኑ መወገድ አለበት” እያላችሁ የምታስተጋቡት ጩኸት “ሁኔታውን የሚያባብስና” በዓለም አቀፍ ህግም እንደ ወንጀለኛ የሚያስቆጥር ስለሆነ መቆም አለበት ነው የሚለን። እናንተ በትውልድ-ኢትዮጵያውያን ነገር ግን ደግሞ የውጭ አገር ዜግነት ያላችሁና በውጭው ዓለምም የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአገዛዙ ቀረጥ የማትከፍሉ ስለሆነ በአገር ቤት የሚፈጸመው ማንኛውም ድርጊት ቢያሳስባችሁም በቀጥታ ጣልቃ በመግባት ልክ የአገሪቱ ዜጋ የሆናችሁ ይመስል አገዛዙን የመጋፈጥና ከስልጣንም ይወገድ የማለት መብት የላችሁም ነው የሚለን። በሌላ ወገን ግን ባይሳ ዋቅ-ወያ እንደሚለን የአቢይ አገዛዝ “በአብላጫ ድምጽ” ስልጣኑን ከተረከበ በኋላ ለኢትዮጵያ ህዝብ “የገባው የማህበራዊ ውል ስምምነት” ምን እንደሆነ በግልጽ ለማብራራት በፍጹም አልቻለም። ስንሰማና ሲያታልለን የከረመው “በምንም መልክ ኢትዮጵያ አትፈርስም”፣ ወይም “አትበታተንም” እያለን ነበር። በሌላው ወገን ደግሞ እዚያው በዚያው አገሪቱን ለመበታተን የማይተበትበው ተንኮልና የማይፈነቅለው ዲንጋይ የለም። አሁንም እንደምናየው አቢይ አህመድና ግብረአበሮቹ ኢትዮጵያ እንድትበታተን በቋፍ ላይ ያለች አገር አድረገዋታል። ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ራሳቸውን ለማስከበር ደፋ ቀና ሲሉ፣ አቢይ አህመድና ግብረአበሮቹ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ተላላኪ በመሆን ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች የነፃነት ጮራ የነበረችው አገር እዚህ ዐይነቱ አሳፋሪ ደረጃ ላይ እንድትድርስ ለማድረግ በቅተዋል።
ወደ ማህበራዊ ውል ( Social Contract) ቲዎሪ አፀናነስና አስተዳደግ ስንመጣ ቲዎሪው ለመጀመሪያ ጊዜ የፈለቀው ቶማስ ሆበስ በሚባለው ኢንግሊዛዊው ፈላስፋ በ17ኛው ክፍለ-ዘመን ነው። ይህ ጉዳይ በሌላ መልክ በግሪክ ፈላስፋዎች ዘመን በአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ከክርስቶ ልደት በፊት የቀረበና አገዛዞችም በምን መልክ ህዝቦቻቸውን ማስተዳደር እንዳለባቸው በሰፊው ፍልስፍናዊ ትንታኔ የተሰጠበት ነው። በጊዜውም የቀረበው ሃሳብ የማህበራዊ ውል ሳይሆን ፍትሃዊነት መንገስ እንዳለበትና፣ የዲሞክራሲን ጥያቄ ማዕከላዊ በማድረግ አገዛዞች በጭፍን ወይም አርቆ ካለማሰብ ከሚያደርጉት ፖለቲካዊ አካሄድ እንዲቆጠቡና፣ ህዝባቸውን በስርዓትና በጥበብ እንዲያስተዳድሩ ነው። በግሪክ ፈላስፎችም ዕምነት በአንድ አገር ውስጥ የሚነሱ ብጥብጦች በራሱ በተራው ህዝብ ሳይሆን ስልጣንን በተቆናጠጡ ኃይሎች አማካይነት ስግብግብነትንና የስልጣን ጥመኝነትን በማስቀደም ብቻ ነው በማለት ለማረጋገጥ ችለዋል፤ ትክክልም ነው። ወደ ቶማስ ሆበስ ቲዎሪ ስንመጣ፣ ሆበስ ሊለን የሚፈልገው የሰው ልጅ በአፈጣጠሩ ስግብግብና ለራሱ ብቻ የሚያስብ እንደመሆኑ መጠን አንዱ ሌላውን እየፈራ የሚኖርና፣ አንዱ በሌላው ላይ በመዝመት(War of All against All) የማያቋርጥ ጦርነት የሚሰፍነበት ስርዓት ስለሆነ ለዚህ ዐይነቱ አስጨናቂ ሁኔታና ስርዓተ-አልባተኝነት መፍትሄው ሁሉንም አንቀጥቅጦ የሚገዛና፣ ሁሉም ካለምንም ማመንታት የሚታዘዙት ሶቨሬን ወይም ዲስፖታዊ አገዛዝ መፈጠር አለበት ነው የሚለን። ይህ የሆበስ አባባል ወይም ቲዎሪ በጊዜው በነበሩ በሌሎች የእንግሊዝ ፈላስፋዎችና በፈረንሳዊው ፈላስፋ በሩሶው የሚደገፍ አልነበረም፟። በተቀሩት የእንግሊዝ ፈላስፋዎች፣ በጆን ሎክና በሂዩም ዕምነት ሆበስ እንደሚለው የሰው ልጅ የስግብግበነት ባህርይ ቢኖረውም፣ በዚያው መጠንም አሳቢና ለሌላውም የሚያዝን እንደሆነ በሚገባ ያረጋግጣሉ። በተለይም በሩሶው ዕምነት የሰው የስግብግበነት ባህርይ ተፈጥሮአዊ ሳይሆን የግል ሃብት ከተፈጠረበትና ሀብት በጥቂት ሰዎች እጅ መያዝ ከጀመረ ወዲህና፣ ዘመናዊነት የሚባለው ነገር ብቅ ማለት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ ለማመልከት ሞክሯል። ይህም ጉዳይ ከዚያ በኋላ ብቅ ባሉና፣ አሁንም በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ባሉ ተመራማሪዎች የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በሰው ልጅ የዕድገት ታሪክ ውስጥ በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ በነበረበት ዘመን፣ በአዳኝነትና ፍራፍሬ ለቅመው በመመገብ ይኖሩ በነበሩና በዘላን ማህበረሰብ ውስጥ ሆበስ እንደሚለን አንዱ በሌላው ላይ እየተነሳ ተንኮል በመሸረብ የሚገድለው ሳይሆን እየተጋገዙ እንደሚኖሩ የአንትሮፖሎጂ ጥናቶች ያመለክታሉ። ስለሆነም ሆበስ እንደሚለው የሰው ልጅ በአፈጣጠሩ እንደ ቀበሮ የሚታይና፣ አንዱ ሌላውን ባለማመን እየተፈራሩ የሚኖሩ ሳይሆን አንዱ ለሌላው እንደሚያስብና ተጋግዘውም ታላላቅ ስራዎችን እንደሚሰሩ አሁን በቅርብ የወጣ መጽሀፍ በሚገባ ያረጋግጣል።
ወደ ሌላው እንግሊዛዊው ፈላስፋ ወደ ጆን ሎክ የማህበራዊ ውል ቲዎሪ ስንመጣ ጆን ሎክ የቶማስ ሆበስን ቲዎሪ እንዳለ የሚጻረር ነው። በጆን ሎክ ዕምነት በአንድ አገዛዝና በህዝብ መሀከል ስምምነት ሊኖር የሚችለው አገዛዙ የእያንዳንዱን ግለሰብ ተፈጥሮአዊ መብት ሲያከብርና ሰላምም ሲያሰፍን ብቻ ነው። በተጨማሪም እያንዳንዱ ግለሰብ የግል ሀብት(Private Property) እንዲኖረውና፣ ይህም በህግ እንዲታወቅለት ያስፈልጋል። የአንድ አገዛዝም ግዴታ እነዚህን ነገሮች ተግባራዊ ማድረግ ሲሆን፣ ይህንን የማህበራዊ ውል ተግባራዊ ለማድረግ የማይችልና ከህግ-የበላይነት ውጭ በራሱ ፈቃድ እየተነሳ የሚወስዳቸው እርምጃዎች በሙሉ ውሉን የሚያፈርሱ ስለሆነ፣ እንደዚህ ዐይነቱ ዲስፖታዊ አገዛዝ የግዴታ በአንዳች መንገድ ከስልጣኑ መወገድ አለበት ይለናል። በሌላ አነጋገር፣ አንድ አገዛዝ ስልጣንን በምርጫም ቢይዝ ለህዝብ የገባውን ቃል-ኪዳን ተግባራዊ ለማድረግ የማይችል እስከሆነ ድረስና፣ ገፍቶም በመሄድ ሰላምን የሚነሳና እንደፈለገው እገዛለሁ የሚል ከሆነ አንድ ህዝብ ዝም ብሎ ማየት የለበትም፤ የተመረጠበት ዘመኑም እስኪያልቅ ድረስ የአገዛዙን ግፍ እየቀመሰ መኖር የለበትም ይለናል። በጆን ሎክ ዕምነት የህግ የበላይነትን የማያከብር ማንኛወም ዲስፖታዊ አገዛዝ ስልጣንን ተቆናጠጥኩኝ ብሎ በህዝብ ላይ መቀለድ አይችልም፤ ስለሆነም እንደዚህ ዐይነቱ አገዛዝ በአመጽ ከስልጣኑ መወገድ አለበት በማለት የቅጩን ይነግረናል።
የባይሳን ዋቅ-ወያን ትንተና በሚገባ መስመር በመስመር ሳነብ በህግና በማህበራዊ ውል አሳቦ አንድ አገዛዝ የፈለገውን ያህል ግፍ ቢፈጽምም፣ ህዝብን ቢያፈናቅልም፣ ብሄራዊ ነፃነትን ቢያስደፍርም፣ ህዝቡና በህዝብ የተመረጡ ተወካዮች ሳያውቁትና ሳይከራከሩበት ከወንበዴዎች ጋር አንዳች ዐይነት ድርድር ቢያደርግም፣ አገርን በመዋዕለ-ነዋይ ስም ለሚመጡ የውጭ አገር ኩባንያዎች የጥሬ-ሀብት ዘራፊዎች ሀብትን ቢሽጥና ቢያዘርፍም፣ የራሱን ስልጣን ለማስከበር ሲል አጠቃላይ ጦርነት በህዝብ ላይ ቢያውጅም፣ እንደዚህ ዐይነቱ አገዛዝ በህዝብ የተመረጠ ስለሆነ ራሱ ህዝቡ ሌላ የምርጫ ቀን ደርሶ ከስልጣን ላይ እስካላስወገደው ድረስ በአንዳች ነገር አገዛዙን ከስልጣን ላይ ማስወገድ አልአግባብና እንደ ወንጀልም የሚያስቆጥር ነው ይለናል። በሌላ ወገን ደግሞ ተካሄደ የተባለውን ምርጫና አቢይና “ፓርቲው በአባላጭ ድምጽ አሸነፉ” የተባለበትን ሁኔታ ስንመለከት በጣም የሚያስቅ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የራሱ የአቢይ ፓርቲ በደንብ ያልተደራጀና፣ አንድ ፓርቲ ማሟላት ያለበትን መሳፍርቶች በሙሉ ሊያሟላ የሚችል አይደለም። የኦሮሞ “ብልጽግናም” ሆነ ሌሎች የብልጽግናን ስም የተከናበቡ የየብሄረሰቡ ፓርቲዎች ነን የሚሉ በምሁራዊ ሂደት ውስጥ ያላላፉና፣ ማንኛውንም ምሁራዊ መሳፍርት የሚያሟሉ አይደሉም። ለአንድ አገር ግንባታ የሚያስፈልጉ እንደ ፍልስፍና፣ ሶስዮሎጂ፣ ፖለቲካል ሳይንስ፣ የኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም የከተማ ዕቅድና፣ ለሰፊው ህዝብ የሚዳረስ የቤት አሰራር ዕውቀት የላቸውም፤ ወይንም አገርን በመገንባት የሰለጠኑ ሙያተኞች የተመከሩና፣ እንደፓርቲም ዕውቅና አለን ካሉበት ጊዜ ጀምሮ ህዝብን የሚያስተምሩበት ሳምንታዊ ጋዜጣና ወርሃዊ መጽሄት ያልነበራቸውና የሌላቸው ናቸው። በሌላ አነጋገር የብልጽግናን ስም ይዘው ስልጣን ላይ ቁጥጥ ያሉት ኃይሎች በሙሉ ያልተገለጸላቸውና እንደ ኢትዮጵያ የመሰለን ታላቅ አገር የመምራት ችሎታና መብትም የላቸውም። ባጭሩ የብልጽግናን ስም የያዘው የአቢይ አህመድ “ፓርቲ” በመሰረቱ የዱርዬዎች ስብስብ ነው ማለት ይቻላል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ምርጫው የተካሄደው የተለያዩ ፓርቲዎች በበቂው ባልተደራጁበት ወቅትና፣ በየክልሉ ዋና ከተማዎች፣ አውራጃዎችና ትናንሽ ወረዳዎችና መንደሮች ድረስ በመዝለቅ ቢሮዎች ከፍተው የህዝቡን የአኗኗር ሁኔታ በማጥናትና ለህዝቡም የሚፈለገውን ነገር ለማድረግ ያልተዘጋጁና፣ “የተዘጋጁ ቢኖሩም” በየቦታው፣ በተለይም በኦሮሚያ ክልል በሚባለው ቦታ ቢሮዎች የመክፈትም ሆነ የመንቀሳቀስና ህዝቡን የማስተማር መብት አልነበራቸውም። ባጭሩ የአቢይ ፓርቲ ያሸነፈው ብቻውን ሮጦ ብቻውን ነው ማለት ይቻላል። በሶስተኛ ደረጃ፣ ለምርጫ የተመዘገበው ሰፊው ህዝብ የተለያዩ ፓርቲዎችን የማነፃፀር፣ ፕሮግራማቸውን የማንበብና የመረዳት፣ እንዲሁም በህገ-መንግስቱ ውስጥ የሰፈረውን መብቱን ለማንበብና ለመረዳት በቂ ችሎታ የለውም። በሌላ አነጋገር፣ ሰፊው ህዝብ ባልተማረበት፣ ንቃተ-ህሊናው ባልዳበረበትና፣ የሚኖርበትን ሁኔታ በበቂው ማገናዘብ በማይችልበት አገር ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ በፓርቲ ስም ተደራጀሁ የሚለውን ጨቋኝና ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር ሀብትን የሚያዘርፍን የንዑስ ከበርቴውን ስብስብ ነው የሚመርጠው ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ እንደኛ ባለ በብዙ መንገዶች ወደ ኋላ በቀረ አገር ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ፣ በምርጫ ውስጥ የሚሳተፍና የሚመርጠው ህዝብ ሳያውቀው የሚጨቁነውንና የሚያዘርፈውን የንዑስ ከበርቴ ስብስብ ነው የሚመርጠው ማለት ነው። ባጭሩ እንደኛ ባለው አገር ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ ለፋሺሽታዊና ለከሃዲ ኃይሎች በሩን የሚከፍትና ሁኔታዎችን አመቻችቶ የሚሰጥ ነው ማለት ይቻላል። ለዚህ መፍትሄው በሳይንስና በፍልስፍና፤ እንዲሁም በኢንጂነሪንግ፣ በኢኮኖሚ ቲዎሪና በአገር ግንባታ የሰለጠኑና ይህንንም እንደሙያቸው የያዙና የአገር ወዳድ ስሜት ያላቸው አገር ወዳድ ኃይሎች ስልጣንን ቢይዙና ህዝቡን ለማንቃት አስፈላጊውን ተቋማት ገንብተው ሰፊውን ህዝብ በማደራጀት በአገር ግንባታ ውስጥ እንዲሳተፍ ቢያደርጉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያመረቃና አስተማማኝ መሰረት መጣል ይቻላል። ይህንን የተቀደሰ ዓላማ ዕውን ለማድረግ ከፍተኛ የሞራል-ብቃትነት፣ ንቃተ-ህሊናና ፅናት ያስፈልጋል።
ወደ ሌላው ቁም ነግር እንምጣ። የማህበራዊ ውል( Social Contract) ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ምን ማለት እንደሆነና ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜም ምን ምን ነገሮች በምን መልክ መገለጽ እንዳለባቸው መመርመር ያስፈልጋል። ቶማስ ሆበስ፣ ጆን ሎክም ሆነ ሩሶው ያፈለቁት ቲዎሪ ከ17ኛው ክፍለ-ዘመን ከነበረው የፖለቲካ ሁኔታ በመነሳት የነደፉት ስለሆነ፣ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ባለው ሁኔታ ውስጥ የማህበራዊ ውል ተግባራዊ ሲሆን መሳፍርቶቹ ለየት ይላሉ። ምክንያቱም በ17ኛው ክፍለ-ዘመን በተለያዩ አገሮች ውስጥ እየገቡ የሚፈተፍቱ ኃያላን መንግስታት የሚባሉ አገዛዞች ስላልነበሩ በጊዜው የ17ኛው ክፍለ-ዘመን የማህበራዊ ውል ንፁህ በንፁህ አገራዊና፣ እንደ ብሄራዊ ነፃነት፣ ብሄራዊ ኢኮኖሚን መገንባት፣ ባህልን መጠበቅና መንከባከብ፣ ባጭሩ አንድን አገር በሳይንስና በቴክኖሎጂ መሰረት ላይ በመገንባት ኢምፔሪያሊስታዊ ኃይሎች እየመጡ እንደፈላገቸው መፈንጫ መንገድ እንዳያገኙ የሚባሉት መሰረተ ሃሳቦች የመወያያ ነጥቦች አልነበሩም። ይሁንና እነ ጆን ሎክ ያነሱት የህግ-የበላይነትን ማክበር፣ በሌላ አነጋገር የአንድን ግለሰብ የፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ መቃወም፣ ግለሰብአዊ ነፃነትን ማክበር፣ እያንዳንዱ ግለሰብ በተቻለ መጠን የራሱ የሆነ የግል መሬት እንዲኖረው ማድረግ፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ራሱ ለፍቶ ጥሮ ግሮ ያካበተው ሀብት እንዲጠበቅ ማድረግ... ወዘተ. እነዚህ ሁሉ ነገሮች መከበርና ተግባራዊም መሆን ያለባቸው ናቸው። ይህም ተገቢ የሆነና ማንኛውም አገዛዝ በምርጫ ስልጣንን ያዘ ወይም በሌላ መንገድ ማክበር ያለበትና፣ ለሰላምና ተስማምቶ አብሮ ለመኖርም የሚያመች የተቀደሰ ዓላማ ነው።
ይህንን መሰረት በማድረግ አቢይና ፓርቲው ስልጣንን በምርጫ ተረከቡ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ተግባራዊ ያደረጉትን እርምጃዎች እንመርመር። እንደሚታወቀው የትግሬ ኤሊት ነን በሚሉ በህወሃት ወይም በወያኔ በሚመራው ዘራፊና ፋሺሽታዊ ቡድን የኢትዮጵያ ህዝብ መጠነ-ሰፊ ጥቃትና የሀብት ዝርፊያ ተካሂዶበታል። በተለይም በእንግሊዝና በአሜሪካን አገዛዝ ተጠሪዎች ለንደን ላይ ስምምነት የተደረሰበት የጎሳ ፌዴራሊዝም ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የአገራችን ህዝብ እንደ አንድ ህዝብ የሚተያይ ሳይሆን ጎሳዊ አስተሳስብ እንዲኖረውና ርስ በርሱ እንዲናቆር አመቺ ሁኔታ ተፈጥሮለታል። ወያኔም ይህንን በመጠቀም በየክልሉ ውስጥ እየገባ እንደ ልቡ የሚፈተፍትና የሀብት ዘረፋም የሚያካሂድ ነበር። ይህንን ዐይነቱን ዐይን ያወጣ አካሂዱን የተቃወሙ ሁሉ አንዳንዶች ለእስርና ለስቃይ ሲዳረጉ፣ ሌሎች ደግሞ በአንዳች መንገድ እንዲገደሉ ይደረጉ ነበር። የትግሬ ኤሊት ያገኘውን የታሪክ አጋጣሚ በመጠቀም ተንኮል የተሞላበት ስራ የሚሰራና አገሪቱን፣ በተለይም አዲስ አበባን ወደ ብልግና መድረክ ለመለወጥ ችሏል፤ ግብረ-ሰዶማዊነት እንዲስፋፋም በተለይም የወጣቱን መንፈስ መርዞታል። የብልግና ኢንዱስትሪን ለማስፋፋትና የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ለማባለግ ደግሞ የተጠቀመው በዓለም አቀፍ ኩሙኒቲ በመባል በሚታወቀው፣ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ የሚደነገገውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ነው። ስለሆነም ይህንን ያህል ግፍ የተፈጸመበት ህዝብ አዲስ አገዛዝ ሲመጣ የሚጠብቀውና ተግባራዊ እንዲሆንለት የሚፈልገው ነገር ከላይ የተዘረዘሩትን አፀያፊና አገር አፍራሽ ድርጊቶች በሙሉ እንዳለ የሚፃረር መሆን አለበት። በተግባር ሲመነዘር ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ይህም ማለት ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በህዝቡና በአገር ላይ የፈጸማቸው ወንጀሎች በሙሉ ተመርምረው ወንጀሉን የፈጸሙት በሙሉ ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለባቸው። ወያኔዎችና ግብረአበሮቻቸው በማንኛውም አገር ያልታየና ያልተለመደ፣ በተወለዱበት አገር ልክ ጠቅላላው ህዝብ እንደበደላቸው ታሪክን በማጣመም ጠቅላላው ህብረተሰብ እንዲመሰቃቀል ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበርና የእነሱን አጀንዳ በማስፈጸም በቀላሉ ሊፋቅና ሊስተካክል የማይችል መጠነ-ሰፊ ወንጀል ፈጽመዋል። ወያኔና ግብረአበሮቻቸው በዚህ ዐይነቱ ወንጀላቸው ያስመስከሩትና ያረጋገጡት ማንኛውም ሰው ሊኖረው የሚገባውን እሴቶች፣ ማለትም ስነ-ምግባርና ሞራል፣ አርቆ-አሳቢነትና ለሌላው ሰው ማሰብ ወይም ርህሩህ መሆን፣ የታሪክና የባህል ኃላፊነት መሰማት፣ የአገር ወዳድነት ስሜት መኖር፣ በታሪክ ውስጥ የተሰሩ ስህተቶችን እንደ ወንጀል ሳይቆጥሩ ታሪክን በተስተካከለና ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ ማደስና አገር መገንባት፣ የማንም ኃያል መንግስት ተላላኪ በመሆን ብሄራዊ ነፃነትን አለማስደፈር...ወዘተ. እነዚህን የመሳሰሉ መሰረታዊ ነገሮችን በመጣስ አገርን ወደ መበታተን ነው ያመሩት። ለተከታዩም አገዛዝ የስርዓተ-አልበኝነት ሁኔታን አመቻችተው ነው የሄዱት። ባጭሩ ወያኔዎችና ግብረአበሮቻቸው ቅል ራሶች ናቸው ማለት ይቻላል፤ በጭንቅላታቸው ውስጥ ከቂም በቀልና ከዘራፊነት፣ እንዲሁም ተንኮልን ከመስራትና ዘረፋን ከማስፋፋት በስተቀር ምንም ነገር የለም። ይህንንም ለሰፊው የትግሬ ህዝብና፣ በተለይም ለወጣቱ የትግሬ ትውልድ አስተምረው አልፈዋል። ማስብ የማይችልና ማህበራዊ እሴት ኖሮት በአገር ግንባታ ውስጥ ሊሳተፍ የማይችልና፣ እንደዜጋና እንደ ሰው እንዳይታይ ለማድረግ በቅተዋል። በሌላ አነጋገር፣ እንወክለዋለን በሚሉት የትግሬ ብሄረሰብም ላይ በአንድና በሁለት ትውልድ ጊዜ ውስጥ ተፍቆ ሊያልቅ የማይችል የጭንቅላት በሽታ አስረክበውት አልፈዋል። ይህ ዐይነቱ በሽታም፣ ማለትም በሰፊውና በጥልቀት አለማሰብ፣ ማህበራዊ ባህርይ አለመኖር፣ ስነ.ምግባር አለመኖርና ለሌላው አለማሰብ ወደ ተቀረው የህብረተሰብ ክፍል በመዛመት በአገራችን ምድር አዲስና በቀላሉ ሊታደስ ወይም ሊሻሻል የማይችል የህብረተሰብ ክፍል ፈጥረው ሄደዋል። ባጭሩ በህብረተስባችን ውስጥ የህብረተሰብን ዕድገትና ተስማምቶ መኖርን የሚቀናቀን የብልግናና የአጭበርባሪነት ባህርይ እንዲስፋፋ ለማድረግ በቅተዋል።
የአቢይ አህመድ አገዛዝ ስልጣንን ሲረከብ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ባጠናና ተገቢውን እርምጃ መውሰድ በቻለ ነበር። ይህንን ከማድረግ ይልቅ ስልጣኑን ያደላደለ ከመሰለውና አብዛኛውን ህዝብ፣ በተለይም ንዑስ ከበርቴውን አታሎ አጋሩ ካደረገና በጥቅማ ጥቅም ከገዛቸው በኋላ የተከተለው መንገድ የወያኔን አካሄድ በብዙ መቶ እጆች የሚያጥፍ ነው። የኦርቶዶክስን ሃይማኖት ለማዳከም ቀሳውስቱንና ደብተራዎችን ማሳደድ፣ ቤተክርስቲያናት እንዲወድሙ ማድረግ፣ ኦነግ ሸኔ የሚባለውን አረመኔ ኃይል በማስታጠቅ ከተማዎችን ማፈራረስ፣ አማራውን አሰቃቂ በሆነ መንገድ ማረድና ማሳደድ፣ ወያኔ ያስገባውን የብልግና ኢንዱስትሪ ማስፋፋት፣ ወያኔ ተግባራዊ ያደርግ የነበረውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አሁንም ተግባራዊ በማድረግ ሀብትን በፍጥነት መዝረፍና በህገ-ወጥ መንገድ የኦሮሞ ኤሊቶችን ማበልጸግና የብልግናው አካል እንዲሆኑ ማድረግ ነው። ምርጫም ተካሄደ ከተባለ በኋላ ባይሳ ዋቅ-ወያ እንደሚለን አቢይና ግብረ-አበሮቹ ከህዝቡ ጋር “የተስማሙበትን የማህበራዊ ውል” ተግባራዊ ያደረጉ ሳይሆን ለሁላችንም በግልጽ እንደሚታየው ፋሺሽታዊ አገዛዝ በመመስረት የሚቃወማቸውን ሁሉ ወደ ማፈንና ወደ መደብደብ ነው ያመሩት ማለት ይቻላል። በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ምድር ፋሺሽታዊና የወንበዴ አገዛዝ ተስፋፍቷል ማለት ይቻላል።
ይህንን ድርጊቱን የሚቃወመውንና፣ ማንም ኃይል በአገዛዙ ላይ ጦርነት ሳይከፍትበት አማራውን አንበረክከዋለህ፣ ኃይሉን አዳክመዋለሁ፣ የኦሮሙማንም የበላይነት በአገሪቱ ምድር ላይ በሙሉ ተግባራዊ አደርጋለሁ በማለት የአማራውን ልዩ ኃይልና ፋኖዎችን ትጥቅ አስፈታለሁ በማለት በአማራው ወገናችን ላይ መጠነ-ሰፊ ጦርነት በመክፈት ቁጥራቸው የማይታወቁ ወገኖቻችን እንዲገደሉና፣ አንዳንዶችም አካለ-ስንኩላን እንዲሆኑ አድርጓል። በዚህ አደገኛና አገር አፍራሽ ድርጊቱ አንድም ጄኔራል ጥያቄ ሳያቀርብ በጭፍን እየተከተለው በአገሪቱ ምድር ስርዓተ-አልባተኝነት እንዲስፋፋ አድርጓል። ባጭሩ አንድ ፓርቲ በምርጫ አሸንፎ ስልጣንን ከተረከበ በኋላ ማድረግ የሚገባውን፣ በተለይም ሰላም እንዲሰፍንና ፍትሃዊነት ተግባራዊ እንዲሆኑ ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ አላዳረግም። በተጨማሪም እንደ ኢትዮጵያ በመሰለው አገር ሰፊው ህዝብ መንቃትና መደራጀት ሲገባው፣ ይህ ዐይነቱ ለአገር ግንባታ በጣም አስፈላጊ የሆነው እርምጃ፣ ማለትም ህዝብን ማስተማር፣ ማንቃትና ማደራጀት ተግባራዊ እንዲሆኑ የወሰደው አንዳችም ነገር የለም ማለት ይቻላል። ሰለሆነም ፈሺሽታዊ አገዛዝ በሰፈነበትና የህዝብን ሰላም በነሳበት አገር ውስጥ የትጥቅ ትግል የማድረጉ ጉዳይ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ሻቢያና፣ ህወሃት፣ እንዲሁም ኦነግ ምንም ሳይደረጉ፣ ሳይበደሉ፣ ህዝባቸው ሳይጨፈጨፍ፣ ኤርትራውያን፣ ትግሬዎችና ኦሮሞዎች ናችሁ፣ ስለሆነም እንደ ተቀረው ኢትዮጵያዊ ምንም ዐይነት መብት ሊኖራችሁ አይገባም ሳይባሉ፣ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የመማር፣ ተምሮም የስራ ዕድል ማግኘት፣ ይህ ሁሉ ሳይነፈጋቸው ነው እነዚህ ተስፈንጣሪና የውጭ ኃይሎች ተቀጣሪዎች በአገራችንና በህዝባችን ላይ ጦርነትን አውጀው ፍዳውን ሲያሳዩ የከረሙት። ይህ ዐይነት ድርጊትም በሌሎች አገሮች ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። ከዚህ ዐይነቱ የታሪክን ሁኔታ በማጣመም ከተደረገ “የነፃነት ትግል” ከሚሉት ጋር ሲነፃፀር ፋኖዎችና የአማራው ልዩ ኃይል በመተባበር የተከፈተባቸውን ጦርነት መመከታቸውና ወደ ማጥቃጥም መሸጋገራቸው ዕውቅና የሚሰጠውና በህግም የሚደገፍ ነው። ምክንያቱም የእነ አቢይና የእነ ሺመልስ አብዲሳ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ የምትባለውን አገር እንዳለ መበታተን ስለሆነ ነው።
ከዚህ ዐይነቱ ብልግናና ወንጀል ስንነሳ የአገራችን ጉዳይ የሚያገባው በአገራችን ምድር የሚኖረው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን በውጭው ዓለምም የሚኖረው ማንኛውም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ነው። በውጭው ዓለም የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ልክ በኢትዮጵያ ምድር እንደሚኖረው፣ የውጭ አገር ዜግነት ይኑረው አይኑረው አገሩንና ህዝቡን የመከላከልና የትጥቅ ትግልንም የመደገፍ ታሪካዊ ግዴታ አለበት። የነቃና የተደራጀ ኃይል እስካለ ድረስና፣ የኢትዮያዊነትን አርማ አንግቦ ለመላው ህዝብ ነፃነት የሚታገልና ኃይሉን አጣምሮ አዲስ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚታገል ኃይል በሙሉ መደገፍ ያለበት ነው። የዓለም አቀፍ ህግ በለው ሌላ ነገር ሊያግደው የሚችል ምንም ነገር የለም፤ እንደ ወንጀልም፣ ሊቆጠር የሚችል አይደለም። ከፋሺሽታዊ አገዛዝ ለመላቀቅ ሲሉ አንዳንድ አገሮችና ህዝቦች ከሌላ ዜጋ ከሆኑ ግለሰቦችና ከተደራጁ ሰዎች ማንኛውም ድጋፍ ይሰጣቸው ነበር። በ1930ዎቹ ዓመታት የነቁና የተደራጁ የስፔይን ተወላጆች ከፋሺሽቱ የፍራንኮ አገዛዝ ጋር የትንቅንቅ ትግል ሲያካሂዱ ከአውሮፓ ምድር የተውጣጡ የነቁ ኃይሎች ስፔይን ድረስ በመሄድ በፋሺሽቱ የፍራንኮ አገዛዝ ላይ የጦር ትግል ያካሂዱ ነበር። ይህም ዕውቅና ተስጥቶት የሚደገፍ ነበር። የዓለምን ህግ የሚፃረር ነው በማለት ቅስቀሳ አልተካሄደባቸውም፤ እዚያም ድረስ ሄደው በጦር ሜዳ ላይ ህይወታቸውን ይሰዉ የነበሩ የሌላ አገር ዜጎች ናቸው በመባል አልተወነጀሉም፤ በህግም ክትትል አልተደረገባቸውም። ይህ በታሪክ የተረጋገጠና ዕውቅና የተሰጠው ነው። ወደ ሌላ ጉዳይ የዓለም አቀፍን ህግ ወደሚፃረረው ስንመጣ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የበላይነትን ከተጎናፀፈ ከ1945 ዓ.ም ጀምሮ፣ ከኮሪያ እስከቬትናምና፤ ኢራቅ፣ ሊቢያ፣ ሶሪያና አፍጋኒስታን ድረስ ዘልቆ በመሄድና በቦንብ በመደብደብ በስነ ስርዓት ይተዳደሩ የነበሩ፣ እንደ ኢራክና ሊቢያን የመሳሰሉ አገሮች ድምጥማጣቸውን አጥፍቷል። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የቬትናም ታጋዮችን ለማጥፋት ሲል በየጫካውና በየሜዳው ላይ መርዝ በመርጨት መሬቱ እህል እንዳይበቅልበትና፣ በዚያም አካባቢ የሚወለዱ ህፃናት አንዳንድ ኦርጋኖቻቸው በመጉደል ወይም በመበላሸት አካለ-ስንኩላን ሆነው በመወለድ የህይወት ጣዕምን እንዳይቀምሱና ለወላጆቻቸውም ከፍተኛ ሸክም ሆነው እንዲቀሩ ከፍተኛ የታሪክ ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል። ይህ ሁኔታ እስከዛሬም ድረስ አፍጦ አግጦ ያለና፣ ብዙ ህጻናትም ካለ አፍንጫ ወይም ካለጆሮ ወይም በሌላ ኦርጋን ጉድለት እየተወለዱ እስኪሞቱ ድረስ እንዲሰቃዩ ለመደረግ የበቁበትን ሁኔታ እንመለከታለን።
ወደ ኢራቅ ስንመጣ፣ በኢራቅ ብቻ ከአንድ ሚሊዮን ህዝብ በላይ አልቋል። መጠነ-ሰፊ የሆነ የታሪክ ቅርስ ወድሟል። እንደሚታወቀው ኢራቅ የስልጣኔ መዲና በነበረችበት በስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ለጠቅላላው የሰው ልጅ የሚያገለግሉ እንደ አልጄብራ የመሳሰሉ ሂሳቦች የተፈጠሩበትና ለዓለም ህዝብ የታሪክ በረከት ሆነው የተሰጡ ናቸው። ይህ አልዋጥለት ያለው የአሜሪካ የፋሽሺቱ አገዛዝ፣ በመጀመሪያ ላይ ሳዳምን አስታጥቆ በኢራን ላይ ካዘመተ በኋላና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ህዝቦች እንዲገደሉ ካደረገ በኋላ ራሱ ያጠናከረውን የሳዳምን አገዛዝ ለማውደም ሲል ደግሞ ልዩ ዘዴ መፍጠር ነበረበት። ይኸውም ኩዌትን እንዲወር ማስገደድና አረንጓዴ መብራት መስጠት ነው። ይህን አሳቦና የኋላ ኋላ አቶም ቦንብ ሊያሰራ የሚያስችል ዩራኔየም ከቻድ አስመጥተሃል በማለት በሃሰት በመወንጀል ነው ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ሳዳምን በማስወገድ ኢራቅን ድምጥማጧን ለማጥፋት የቻለው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእስላም መንግስት(IS-Islamic State) የሚባለው የአሸባሪ ቡድን እንደ እንጉዳይ በመፈልፈል አካባቢውን ሊያዳርስና፣ አሁን ደግሞ ወደ ኒጀር፣ ቡርኪና ፋሶና ማሊ፣ እንዲሁም ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ሊስፋፋ የቻለው። ከዚህ የበለጠ የዓለም አቀፍን ህግ የሚፃረር ወንጀል የለም። ስለሆነም ባይሳ ዋቅ-ወያ ሰው ብትሆንና ንቃተ-ህሊና ያለህ ቢሆን ኖሮ እንደነዚህ ዐይነቶችን ድርጊቶች በማጥናት ሰፋፊ ገለፃ መስጠት በቻልክ ነበር። ካልቻልክ ደግሞ በስተርጅና ዘመንህ የዘረፍከውን ሀብትና የጡረታ አበል እየበላህ በሰላም መኖር ነበረብህ። ሳያገባህና ምንም ነገር አስተዋፅዖ ሳታደርግ በሰው አገር ውስጥ ገብተህ አንተም ትፈተፍታለህ። አንተ እኛን በድርጊታችን ስትወነጅለን፣ ያልተገነዘብከው ነገር ቢኖር የአቢይን አገዛዝ ስትደግፍ አንተም ራስህ “የዓለም አቀፍ ህግን መጣስህ” ነው። ፋሺሽታዊና አገር በታታኝ የሆነን አገዛዝ የምትደግፍና የሚሰራውን ወንጀል ሁሉ እንደተራ ድክመት በመቁጠር ከሱ ጎን መሰለፍህ በታሪክ ውስጥ ተጠያቂ የሚያደርግህ ብቻ ሳይሆን፣ የወንጀሉ ተባባሪ በመሆንና ፋሺሽታዊ ድርጊቶችን የሚቃወሙና እንደዚህ ዐይነቱ አገዛዝ ከስልጣን ላይ እንዲወርድ የሚታገሉትን፣ በተለይም በውጭው ዓለም የሚኖሩትን የውጭ አገር ዜግነት ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን ወንጀለኞች ናችሁ ብለህ መክሰስህ ራስህን እንደ ወንጀለኛ የሚያስቆጥርህ ነው። አንተን ያሳሰበህ የኢትዮጵያ ህዝብና የአገራችን ዕጣ፣ የህዝባችን ስቃይና መገደል ሳይሆነ በአቢይ ላይ የሚሰነዘረው ወንጀልና ከስልጣንም ይወገድ የሚለው ዘመቻ ነው። ከ120 ሚሊዮን ህዝብ ህይወትና የወደፊት ዕድሉ ይልቅ የአቢይና የተከታዮቹ ህይወት ያሳሳበህ ይመስላል። በዚህም ሚዛናዊ ፍርድ ለመስጠት የማትችልና ተጨባጭ ሁኔታዎችን በማንበብ የአቢይን አገዛዝ የታሪክ ወንጀል ለመኮነን የሞራል ብቃት እንደሌለህ አረጋግጠሃል።
ውድ ወንድሜ አቶ ባይሳ ዋቅ-ወያ በተለያዩ ጊዜያት የምታወጣቸውን ጽሁፎችህን ሳገላበጥ የምረዳው ነገር ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ ዕውቀት እንደሚጎልህ ነው። በተጨማሪም አገርና ህብረተሰብ ምን ማለት እንደሆኑ የተረዳህ አይመስለኝም። ከዚህም በላይ አንድ አገር ከታች ወደ ላይ ኦርጋኒካሊ በስርዓትና በጥበብ መገንባት እንዳለበትና፣ የትኛውስ የኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ ከሌሎች ዕውቀቶች ጋር በመጣመር አገርን ለመገንባት እንደሚያስችል የተገነዘብክና የተመራመርክ እንዳይደለህ ለመገንዘብ ችያለሁ። መንግስትና አገዛዝ የሚባሉትንና፣ አገርንና ህብረተሰብን በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት መከተል ያለባቸውን ፍልስፍናም የምታውቅ አይመስለኝም። የዓለም አቀፍ ህግ ነው የተማርኩት፣ በዚህም ሙያዬ በተባበሩት መንግስታት የተራድዖ ድርጅት ስር በመስራት የስራ ልምድ አለኝ እያልክ ሰውን ለማወናበድ ትሞክራለህ። የዋሁም´ ኢትዮጵያዊ ስትዘላብድ ዝም ብሎ ይመለከትሃል። ለዚህም ነው ከላይ በተጠቀሰው አርዕስት ሰለጻፍከው የተዘላበደ ሀተታ በቂ ትችት ያልተሰጠው። ለማንኛውም ከዚህ ዐይነቱ ህዝብን ከማወናበድ ተግባርህ መቆጠብ አለብህ። ድረ-ገጾችም ለእንደዚህ ዐይነቱ ህዝብን አሳሳች ጽሁፎች ክፍት መሆን የለባቸውም። በመሰረቱ ድረ-ገጾች ሳይንሳዊ አስተሳሰቦችና አገርን ለመገንባት የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ዕውቀቶች የሚንሸራሸሩባቸው ክፍት መሆን ነበረባቸው፤ አለባቸውም። በየድረ-ገጾች ላይ የሚወጡና፣ በጋዜጠኝነት ስም የሚሰጡ ሀተታዎቻና የቃለ-መጠይቅ ምልልሶች በተለይም የወጣቱን ትውልድ መንፈስ በማነጽ ለአገር ግንባታ የሚያገለግሉ አይደሉም። ካለፈው ስህተት በመማር ድረ-ገጾች የበለጠ ሳይንሳዊ አስተሳሰቦች የሚንሸራሸሩባቸው መሆን አለባቸው። በዚህ መልክ ብቻ ነው ታሪካዊ ግዴታን መወጣት የሚቻለው። መልካም ግንዛቤ!!
fekadubekele@gmx.de
www.fekadubekele.com
https://amharic-zehabesha.com/archives/183666
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment