Sunday, May 28, 2023
መግቢያ፤
ባለፈው ጽሁፌ (በክፍል-3)፤ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት በዉስጡ፤ በተለይም በሶስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች (ሕግ አዉጭ፤ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ) መካከል ያሉትን የተዛቡ መዋቅራዊ ግንኙነቶችና ችግሮች ለማመላከት ጥረት አድርጌአልሁ፡፡ ከሶስቱ ቅርንጫፎችም፤ በተለይ አንደኛዉ “ሕግ አዉጭው” አካል፤ በተደጋጋሚ ሕገመንግሥቱን እየጣሰ፤ የመንግሥት ስልጣኑን ቀስ በቀስ በመጠቅለል፤ እራሱን እያጠናከረ መሄዱንና፤ የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መርገጥንም ባህል አድርጎ እንደያዘ፤ ሁለቱን የመንግሥት ቅርንጫፎችም (ሕግ አውጭዉንና ተርጓሚዉን) በማቀጨጭ አቅም እንዳሳጣቸው ለማሳየት ሞክሬአለሁ፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግር ዋናው መንስኤም፤ በህወሐትና በጊዜው አጋሩ በነበረው ኦነግ የተተከለው፤ በብሄር ፖለቲካ ላይ የቆመው ሕገመንግሥት እንደሆነና፤ ባለፉት 30 ዓመት፤ ስር በመስደድ እያደገ የመጣዉን የዘረኝነት (“አፓርታይድ”) አምባገነናዊ ስርአትም እንዲያቆጠቁጥ ያደረገው እሱ መሆኑን ለማሳየት ጥረት አድርጌአልሁ፡፡
ይህ በብሄር ፖለቲካ ላይ የቆመው፤ አስከፊና ኋላ ቀር የዘረኝነት ስርአት፤ ሀገራችንን ለማያባራ የእርስበርስ ግጭትና የዉጭ ጣላቃ ገብነት ዳርጓት ሰላም በማሳጣት፤ ዛሬ መዉጫዉ የጠፋ አዙሪት ዉስጥ ገብታ በመዛቀጥ ላይ ትገኛለች፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያን ከእዚህ አዙሪት ለማዉጣት፤ ያለን ዋና መፍትሄ፤ ሕገመንግሥቱን ማሻሻል ወይም መቀየር እንደሆነም ያለማቋረጥ ለማሳሰብና፤ እኔም እንደብዙወች ኢትዮጵያዉያን ድምጼን ከፍ አድርጌ ለማሰማት ቢያግዝ በሚል ነው፤ በአቅሜ እነዚህን ጽሁፎች በተከታታይ ማቅረብ የጀመርኩት፡፡ ይህን የሀገራችንን ሰላም፤ አንድነትና እድገት፤ የዜጎች ነጻነትንና ህብረት እንዳይዳብር ትልቅ እንቅፋት የሆነዉን፤ ኋላ ቀር ሕገመንግሥትም፤ በሕዝብ ምክክርና መግባባት ማሻሻል ወይም መቀየር ከተቻለ፤ በተፈጥሮ ሀብትና በጠንካራ ሕዝብ የታደለችዋና፤ የጀግኖች አምባ የሆነችው እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ ዕድል ቀንቷት ትክክለኛ አመራር ካገኘች፤ በጠንካራ ዜጎቿ ከዘላለም የድህነትና የቀውስ አዙሪት በአጭር ጊዜ ዉስጥ ተላቃ ለማደግና፤ ከኋላዋ እየመጡ ቀድመዋት የሄዱትንም ለመቅደም ምንም የሚያግዳት ኃይል እንደማይኖር አልጠራጠርም፡፡ እዉነተኛዋ ፌደራላዊት፤ ዴሞክራሲያዊትና ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን በእርግጥ መገንባት የሚቻለዉም፤ ሕዝብ ጠባቂ፤ ሀቀኛ፤ ፍትሐዊና ዘመናዊ ሕገመንግሥት ስታገኝ ነው የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡
*******
በዚህ ጽሁፌ (ክፍል-4)፤ ይህን ኋላ ቀር፤ ከፋፋይ፤ ዘረኛና ብሄር ተኮር የሆነ ሕገመንግሥት ለምንና እንዴት አድርጎ ማሻሻል ወይም መቀየር ይቻላል? ለሚለዉ ጥያቄ አስተያየቴን ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ ይህን ከባድ ጥያቄ ለመመለስ ከመሞከሬ በፊት ግን፤ ለአንባቢወቸ አንድ መሠረታዊ እዉነታ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ይኸዉም፤ ዛሬ በሀገራችን ፖለቲካ መስክ ላይ፤ ሕገመንግሥቱ እንዲሻሻል (እንዲቀየር) የሚፈልጉና፤ ጭራሽ “መነካት የለበትም” የሚሉ፤ ጎራ ለይተው የሚፋተጉ ወይም ገመድ የሚጓተቱ (“tug of war”) በዋነኝነት ሁለት ኃይሎች ወይም “የፖለቲካ ልሂቃን ቡድኖች” መኖራቸዉን ነው፡፡ በሀሳብ መለያየቱ ምንም ክፋት የለዉም፡፡ ችግሩ፤ ባለፉት የሀገራችን 50 ዓመት ታሪክ እንደታየው፤ በቅርቡም ህወሐት በቀሰቀሰው አስከፊ ጦርነት እንደታዘብነው፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ልሂቃን ልዩነታቸዉን በሰላም መፍታት ሲያቃታቸው ሁልጊዜ ሥራየ ብለው ሀገራችንን ወደከፋ ቀውስ እንድትገባ ነው የሚመሯት፡፡ ሕዝብን ለማገልገል ሳይሆን፤ በመንግሥት ስልጣን ላይ በማተኮር ሲሻኮቱና እርስበርስ ሲጫረሱ፤ ንጹሀኑን ሕዝብም ያለማቋረጥ አስጨርሰዉታል፡፡ ሀገራችንን ሌሎች ከኋላዋ እየተነሱ ሲቀድሟት፤ እሷ ግን ምን ያክል ለአመታት ካለችበት ጭራሽ ወደኋላ እየራቀች እንድትሄድ እንደዳረጓትም ታሪክ ምስክር ነው፡፡ በመሀሉ በተለይም ሀገር የሚገነባዉ ወጣቱ ትዉልድ፤ በቅብብሎሽ በየተራ ይወድማል ያለው፡፡ ይህ በፖለቲከኞች ሽኩቻ ሳቢያ የተገነባዉ የደም መፋሰስ ባህል ማቆም አለበት፡፡
ስለዚህ፤ የሀገራችን ፓለቲካ ልሂቃንና መሪወች ወደቀልባቸው ተመልሰው፤ ለሀገራቸው ሰላም ሲሉ ብቻ ሳይሆን፤ ለእራሳቸዉም ደህንነትና ሰላም፤ መላዉን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያሳትፍ፤ ሁሉን አካታች የሆነ ሀገራዊ ምክክር እንዲደረግና፤ ሕገመንግሥቱ በሕዝብ ፍላጎትና መግባባት እንዲሻሻል (እንዲቀየር) አመች ሁኔታ ለመፍጠር መተባበር ይኖርባቸዋል፡፡ ያን ቢያደርጉ ትዉልድ ተሻጋሪ ታሪክ ሠርተው ለማለፍም ዕድል ያገኛሉ፡፡ የአንድ ሀገር ሕገመንግሥት በሕዝብ ፍላጎትና በስነስርአት እንደአስፈላጊነቱ ካልተሻሻለና ካልተጠገነ፤ ፈጣን የኢኮኖሚ፤ ፖለቲካና ማህበራዊ ኑሮ እድገት ማምጣት አይቻልም፡፡ ሕገመንግሥትን ያክል ሀገርን የተሸከመ ይቅርና፤ ቤት እንኳን እንዳይፈርስ በየጊዜው ይጠገናል!
“ሕገመንግሥቱ መነካት የለበትም” የሚሉት በዋነኝነት አሁን ባለው የብሔር ፖለቲካና የዘረኛ ስርአት የሚጠቀሙ፤ በህይወት እስካሉ ድረስም የደሀይቱን ሀገር ሀብት ከሕዝቡ እየነጠቁ የሚያካብቱ፤ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” በሚል፤ እነሱ ከበሉ ሌላዉ ጦም ቢያድርና፤ ሲሞቱም ሀገሪቱ አብራቸው ብትጠፋ ደንታ የሌላቸው ናቸው፡፡ በዋነኝነት ሕገመንግሥቱን መሰላል አድርገው ስልጣን ላይ ለመውጣት የሚያልሙ፤ ስልጣን ከያዙም፤ የእራሳቸዉን ጥቅም ማሳደድ እንጅ፤ ለሕዝብ ሰላም፤ ለሀገር አንድነትና እድገት የማይጨነቁ፤ በተለይም የብሄር ፖለቲካን የሚያቀነቅኑ ልሂቃን ተብየወች ናቸው ሕገመንግሥቱ እንዲቀየር የማይፈልጉ፡፡ በአንጻሩ፤ በሀገራችን ፍትሕ ተረግጦ፤ ሙስናና ዘረኝነት መረን ለቆ፤ የሚዘገንን ግፍና በደል በዜጎች ላይ ሲፈጸም ማየት ያስመረራቸውና፤ ኢትዮጵያ እንደሀገር እንድትቀጥል፤ በጋራ እንድትገነባና እንድታድግ፤ ከድህነትና ከቀውስ ተላቃም፤ ሌሎች ያደጉ ሀገሮች የደረሱበትን ደረጃ ፈጥና እንድትደርስ የሚፈልጉና የሚመኙ ናቸው ሕገመንግሥቱ እንዲሻሻል (እንዲቀየር) የሚፈልጉ፡፡
አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት፤ ለምንድን ነው ለሀገር ግንባታና እድገት ማእነቆ ስለሆነ፤ መሻሻል (መቀየር) አለበት የሚባለው? ገና ከጅምሩ ሕገመንግሥቱ በልሂቃኑ ሲረቀቅ ሁሉን አካታችና ሰፊዉን ሕዝብ ያሳተፈ አልነበረም፡፡ ለምሳሌ ቢያንስ የአንድ ትልቅ ብሄር
የአማራ ሕዝብ በሚገባ አልተሳተፈም፡፡ ታዋቂ ህብረ ብሄር ፓርቲወችን ኢሕአፓንና መኢሶንንም አላካተተም፡፡ በመሠረቱ፤ ኢትዮጵያዉያን በሙሉ፤ ያለፍቃዳቸው በጥቂት የብሄር ፖለቲካ ልሂቃን፤ ለኢትዮጵያዊነት ሳይሆን “ለብሄር ዜግነት” ታማኝ እንዲሆኑ በዚህ ሕገመንግሥት ነው የተፈረደባቸዉ፡፡ በሀገራችንም እዉነተኛ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊና ህብረብሄራዊ ሳይሆን፤ ዘረኛና ከፋፋይ፤ ነጻነት ፍትሕና እኩልነትን የሚያሰፍን ሳይሆን፤ ዜጎችን ለግፍና ለሰቆቃ የሚያጋልጥ፤ ሀገርን የሚገነባ ሳይሆን፤ የሚያናጋና ከባሰም የሚያፈርስ፤ ኋላ ቀር ስርአት የተተከለው በዚህ ሕገመንግሥት አማካይነት ነው፡፡ ሕዝቡን ለሰላምና ለፍቅር ሳይሆን ለቂም በቀልና ለግጭት፤ ለሙስና፤ ለመሬትና ሀብት ዝርፊያ፤ ብሎም ለማያባራ ድህነት፤ ለእረሀብና ለድርቅ፤ ለኑሮ ዉድነትና ለስደት እንዲጋለጥ ያደረገው በመሠረቱ ይህ ሕገመንግሥትና እሱ የወለደው ዘረኛ ስርአት ነው፡፡ ሀገራችን በጋራና በሰላም ከማደግና ወደፊት ከመራመድ ይልቅ፤ ሌትና ቀን በድህነትና በፖለቲካ ቀውስ እንድትማስን ያደረጋትም እሱ ነው፡፡
በሕገመንግሥቱ ያሉትን በርካታ የተዛቡ አንቀጾች በዚች አጭር ጽሁፍ ለመዘርዘር ቦታዉ አይበቃኝም፤ በቂ እዉቀትም አለኝ ብየ እራሴን አላሞካሽም፡፡ ይሁንና አሁን ላለውና በብሄር ፖለቲካ ላይ ለቆመው ሕገመንግሥት አንድ ዋና አዉታር የሆነዉን ጠቅሸ ማለፍ እወዳለሁ፡፡ ሕገመንግሥቱ በአንቀጽ 8 (“የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚል አርእስት በተሰጠው) በቁ/1፤ “የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው ይላል፡፡ ቀጥሎም በዚኸው አንቀጽ በቁ/3 “ሉዓላዊነታቸዉም የሚገለጸው በዚህ ሕገመንግሥት መሠረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና፤ በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ይሆናል” ይላል፡፡ ይህ እንግዲህ በእኔ አስተያየት፤ በእዚህ አንቀጽ ቢያንስ በተዘዋዋሪ መልክ የተቀመጠው፤ ማንኛዉም “ኢትዮጵያዊ ዜጋ”፤ በብሄሩ ወይም ብሄረሰቡ አማካይነት እንጅ፤ በእራሱ ወይም በግሉ እንደኢትዮጵያዊ ዜግነቱ የሀገሩ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት አይደለም ማለት ነው፡፡ ለዚያዉም እያንዳንዱ ዜጋ “በሕገመንግሥቱ መሠረት በሚመርጣቸው ተወካዮቹ አማካይነት” ነው ሉዓላዊነት ያለው የሚለው ሕገመንግሥቱ፡፡ (በነገራችን ላይ፤ በሕገመንግሥቱ “ኢትዮጵያዊ ዜጋ” ታዲያ ማነው የሚለዉ በግልጽ አልተብራራም)፡፡
እዚህ ላይ ዋናዉን ፍሬ ነገር እንድትገነዘቡልኝ በትህትና የምጠይቀው፤ በሕገመንግሥቱ መሠረት ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ፤ ወደደም ጠላም ማንነቱ (“ዜግነቱ”) የሚገለጸው ወይም በሕግ የሚታወቀው በዋነኝነት በኢትዮጵያዊነቱ ሳይሆን ለየትኛዉ ብሔር ወይም ብሔረሰብ አባል በመሆኑ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ በሕገመንግሥቱ መሠረት “ኢትዮጵያ” ወይም “ኢትዮጵያዊነት” የሚባሉት የማንነቱ መገለጫወች አይደሉም፡፡ ይህም ማለት፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በቅድሚያ ታማኝነቱ (loyalty) ለኢትዮጵያ ሀገሩ ሳይሆን “ማንነቱ” ለሚገለጽበት ለብሔሩ ወይም ለብሔረሰቡ ነው ማለት ነው፡፡ የአንድ ሀገር ዜጎች ለሀገራቸው ፍጹም ታማኝ ካልሆኑና፤ ከፍተኛ ሀገራዊ ፍቅር ከሌላቸዉ፤ ሀገርን በቁጭትና በጋራ ለመገንባት በጣም አዳጋች ነው የሚሆነው፡፡
በዚህ አይነት፤ በሕገመንግሥቱ ሳቢያ፤ ባለፉት 30 አመታት፤ ኢትዮጵያ ወይም ኢትዮጵያዊነት የሚባሉት ዳብዛቸው ቢጠፋ ምንም አያስገርምም፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ፤ በአንድ ብሔር/ብሔረሰብ ዉስጥ በመንግሥት አካል እየተመደበ፤ “ማንነቱ” እንዲታወቅ፤ የብሔሩ ወይም የብሔረሰቡ ስም በመታወቂያዉ ላይ ሲለጠፍበት ነው የኖረው፡፡ እሱ ብቻ አይደለም፤ በሄደበት ሁሉ መስክ፤ በትምህርት ቤት፤ በመሥሪያ ቤት፤ በማህበራዊ ኑሮው፤ ሁልጊዜ የሚሰማዉ ፍቅርና ስሜት ስለሀገሩ ሳይሆን ስለብሄሩና ብሄረሰቡ፤ ስለቋንቋው ትልቅነትና ከሌላዉ በምን እንደሚለይ ወይም እንደሚበልጥ በህሊናዉ እንዲያሰላስል ሆኖ ነው የተቀረጸው፡፡ ብሄሩና ብሄረሰቡ፤ የሀገሩ አንድ አካልና አምሳል እንደሆነ እንዳያስብ ነው የተደረገው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ ታማኝ በመሆን፤ ስለኢትዮያ የጋራ ልማትና ግንባታ ሌትና ቀን ባይጨነቅና ቁጭት ባይዘው፤ በአንጻሩ ሁልጊዜ ስለዘሩና ብሄሩ ቢያስብና ቢጨነቅ፤ ሌሎችንም በዘርና በብሄር መነጽር እያየ ቢጠራጠርና ቢርቅ ምን ያስገርማል፡፡ ደግነቱ ኢትዮጵያዉያን ምንም ያክል በብሄር፤ ዘር፤ ቋንቋና ሀይማኖት ቢለያዩም ለዘመናት በማህበራዊ ኑሮ ተሳስረዉ፤ ተጋብተዉና ተዋልደው በሰላምና በፍቅር ስለኖሩ ባለፉት 30 ዓመታትም ጨርስው አልተለያዩም፡፡
የህብረተሰብ እርስበርስ መተሳሰር ባህል ደግሞ፤ ሀገራችን እያደገች ስትሄድና፤ ዜጎች በመሠረተ ልማት በበለጠ ሲገናኙ፤ ሕዝቡም ከገጠር ይልቅ በከተማ መኖርን ሲያዘወትር፤ የብሄርና ብሄረሰብ ወይም የዘር ልዩነቱ እየጠበበና ለመለየትም አስቸጋሪ እየሆነ እንደሚሄድ ግልጽ ነው፡፡ ለዚህ ምሳሌ አዲስ አበባንና ባለፉት አመታት ሌሎች እንደአሸን የፈሉትን የኢትዮጵያ ከተሞች መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንደመንግሥት አያያዝ ከሆነ በዘርና በቋንቋ በተላለቁ ነበር፤ ወደ አደጉ ሀገራት ስንሄድ ደግሞ፤ ለምሳሌ የኒዮርክ ከተማ ዜጎች ከሁሉም ዓለም፤ ከጫፍ እስከጫፍ እየመጡ የሚኖሩባት ስለሆነች፤ በዉስጧ እስከ 200 ከሚደርሱ ሀገሮች (ብሄሮች) የመጡና 800 ያክል የሚሆኑ ቋንቋወች የሚናገሩ ተደባልቀው በሰላም እንደሚኖሩባት ዝናዋ ይነገርላታል፡፡ እንግዲህ የኒዮርክ ከተማ ኗሪወችን በብሄር፤ በዘርና በቋንቋ እየለዩ መታወቂያ በመስጠት፤ በእዚህ ክልል (ክፍለ ከተማ) ኑሩ ቢባሉ ምን ሊመጣ እንደሚችል መገመት ትችላላችሁ! እብደት ነው የሚሆነው!
አዲስ አበባንም ብሄረተኞች ወደኋላ ሊስቧት ቢፍጨረጨሩም፤ የእድገት አቅጣጫዋ ከኒዮርክ ብዙም አይለይም፡፡ ይህን አይነት የዜጎችና የህብረተሰብ ትስስር በከተሞች በተለይ ለማስቆም አይቻልምና፡፡ መቆምም የለበትም! አዲስ አበባን በአንድ ብሄር (ዘር) ሕዝብ እንደቀለበት አካቦ ዜጎችን እርስበርስ እንዳይገናኙና እንዳይዋሀዱ ለማድረግ መሞከር የዋህነት ወይም የህብረተሰብ እድገትን ህግ አለመረዳት ነው፡፡ ዜጎች ሲዋሀዱ፤ ለሀገር ግንባታ እድገትና ስልጣኔ ትልቅ አቅም፤ ሀብትና ዉበት ይሰጣሉ፡፡ ያ ማለት ደግሞ የመጡበትን ብሄር፤ ታሪክ፤ ባህልና ቋንቋ በግድ ይቀማሉ ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ፤ በአሜሪካን ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን፤ ምናልባትም ከኢትዮጵያ በተሻለ ሁኔታ ያለስጋት፤ በየትኛዉም የአሜሪካን ትላልቅ ከተሞች ዉስጥ፤ እንደሁሉም ዜጎች ከፈለጉ እምነታቸዉን፤ ባህላቸዉን፤ ቋንቋቸዉንና ቅርሳቸዉን፤ በመሰላቸው ዘዴና ማህበራዊ ኑሮ የማዳበር ሙሉ ነጻነትና መብት አላቸው፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ የብሄር ፖለቲከኞች ግን ይህን አይፈልጉም! ከተሞችንም ሆነ የገጠር አካባቢወችን በእነሱ ዘር ብቻ ጠቅልለው ለመያዝ ይፍጨረጨራሉ፡፡ ይህን ጉድ ነው ሕገመንግሥቱ ለሀገራችን ያመጣው!
አሁን በኦሮሚያ ክልል አስተዳዳሪወች አዲስ አበባን ዙሪያዋን እንደቀለበት ከቦ የተቋቋመዉን “የሸገር ከተማ” የኦሮሞ ተወላጅ ብቻ ይኑርበት ቢባል፤ ምን ያክል ከዘመኑና ከከተሞች እድገትና ስልጣኔ ወደኋላ የቀረ አስተሳሰብ እንደሆነ ለመገመት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡ ይህ እየሆነ ያለው ደግሞ በኢትዮጵያዉያን ላይ፤ በሀገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅና ሰብአዊ ርህራሄ በጎደለው፤ የሚዘገንንና የዘረኝነት ጭካኔ በመፈጸም መሆኑ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ይህ ነው አንዱ ሕገመንግሥቱ ለሀገራችን ግንባታ “እድገትና ስልጣኔ” ካተረፈላት “ትሩፋቶች”!
ባጠቃላይ፤ ዛሬ ባለው ሕገመንግሥት ጥላ ስር ተወልደው ያደጉት የአዲሱ ትዉልድ ኢትዮጵያዉያን ከሀገራቸው ይልቅ ብሄራቸዉና ብሄረሰባቸዉ በህሊናቸው ቢቀረጽባቸውና፤ በርካቶቹም ሳይወዱ በጠባቡ በመመልከት፤ የሌላዉን ባህል፤ ብሄርና ቋንቋ (ወይም የፈረደበትን የአማራ ሕዝብ) ወይም ሀገራቸዉን ኢትዮጵያን ቢጠሉ ምንም አያስገርምም፡፡ በዘረኝነት መርዝ መበከል ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያዊነታቸዉንና ኢትዮጵያ ሀገራቸዉን ብዙም አያዉቁምና፤ ወይም ለማወቅ ዕድል አልተሰጣቸዉምና፡፡ በተለይም ከከተማ ዉጭ በገጠር ለሚኖሩና ከእራሳቸው ወጣ ብለው የሌላ ብሔርና ብሄረሰብ ተወላጅ ወይም ቋንቋ ለማያዉቁ፤ አብረውም ላላደጉ፤ ኢትዮጵያ ወይም ኢትዮጵያዊነት የሚለው ብዙም ትርጉም ባይሰጣቸዉ ምንም ሊያስገርመን አይገባም፡፡ ስርአቱ የወለደው ነዉና! ከእራሴ ተሞክሮ ለመነሳት፤ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሰበታ፤ ቡራዩና አሸዋ ሜዳ አካባቢ የሚኖሩ በርካታ ዜጎች፤ አማርኛ መናገርና መጻፍ የማይችሉ የኦሮሞ ተወላጆች እንዳሉ ሳይና ስሰማ በጣም ነበር ያዘንኩት! 12ኛን ክፍል ኮሌጅም ሳይቀር ጨርሰው ሥራ ፍለጋ ወደሀገራቸው ዋና ከተማ ወደ አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ክልል ሲመጡ፤ እንግሊዘኛም አማርኛም በሚገባ መናገር፤ ማንበብና መጻፍ ስለማይችሉ የሚቸገሩና ተመልሰው እንደመሀይም የሚሆኑ እንዳሉም ሰምቸ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡
ይህን ነው እንግዲህ “የኦሮሞ ፖለቲካ ልሂቃን” በተለይ፤ በብሄር ፖለቲካና በሕገመንግሥቱ ሳቢያ፤ ለደጉ የኦሮሞ ሕዝብ ያመጡለት ፍትሕ፤ ነጻነትና እኩልነት! ይህ አይነት አስተሳሰብ፤ ከማንም በበለጠ የጎዳዉ የኦሮሞ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፤ በተለይም ወጣቶችን ለመሆኑ ምንም አያጠራጥርም፡፡ የኦሮምኛ ቋንቋ፤ አህጉር ተሻግረው ከባእድ ሀገር ባመጡለት የላቲን ፊደል ቀርቶ፤ በሀገራችን በግዕዝ ፊደል ቢጻፍ ኖሮ ምናልባትም እስከዛሬ ድረስ ኦሮምኛን ከአማርኛ ተናጋሪው የሚበልጥ ሕዝብ በተናገረው ነበር የሚል ግምት አለኝ፡፡ የሚገርመው የግዕዝ ቋንቋ በበርካታ የዉጭ ሀገር ታዋቂ ዩኒቨርስቲወች ካሪኩለም ተካቶ፤ ተማሮች እንዲማሩት እየተደረገና፤ ለምርምርም እየዋለ በከፍተኛ ደረጃ በማደግ ላይ ነው፡፡ ይህ ለሀገራችን ትልቅ ኩራት ነው! የእኛ “ፖለቲካ ልሂቃን” በሀገራቸው ታሪክና በዉሸት ትርክት እርስበርስ ሲባሉ፤ በአንጻሩ ፈረንጆች የሀገራችንን ታሪክና ባህል እያሳደጉልን ነው! ይገርማል!
በሕገመንግሥቱና እሱ በተከለው ዘረኛ ስርአት ሳቢያ ባለፉት 30 ዓመታት በሀገራችንና ሕዝባችን ላይ የደረሰዉን ግፍና በደል ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም፡፡ ሌላ የሚያሳዝነው ደግሞ፤ በከተማ ተዋህደው በሚኖሩት ዜጎች ላይ በተለይ ስንት ግፍ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው በሰላም ሲታገሉ፤ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በብሔራቸውና ብሔረሰባቸው በመታወቂያቸው እየተለዩ በመለቀም፤ ስንቶች በግፍ ታስረዋል፤ ተገድለዋል፤ ተጨፍጭፈዋል፡፡ ዛሬም በገፍ እየታፈኑና በየእስር ቤቱ እየታጎሩ ነው፤ ከጥቂት አመታት በፊት በህወሐት አስተዳደር እስር ቤት በብዛት የሚታጎሩትና እየታፈኑ ዳብዛቸው የጠፋዉ በአብዛኛው የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ነበሩ ይባላል፡፡ እርግጥ የአማራ ተወላጆች ህወሐት ገና ስልጣን በያዘ በበነጋዉ ነበር እልቂት የታወጀባቸው፤ ይሁንና፤ ዛሬ ደግሞ ጎልቶ እንደሚታየው በጠራራ ጸሀይ የሚታፈኑትና እስር ቤት የሚታጎሩት በብዛት የአማራ ተወላጆች ናቸው፡፡ ባለፉት አመታት በሽ የሚቆጠሩ አማሮችም በወለጋና በሌሎችም የኦሮሚያ ክልል አካባቢወች ተጨፍጭፈዋል፤ “መጤ ናችሁ ወደ ሀገራችሁ ሂዱ” እየተባሉም ተፈናቅለዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንኳን፤ በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያ (“የሸገር ከተማ”) ለአመታት ከኖሩበት ሰፈርና ቤት እየተፈናቀሉ ቤትና ንብረታቸዉም እየወደመባቸዉ ወደጎዳናና በረሀ የተወረወሩና ለአዉሬም የተዳረጉ ብዙ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ “የሸገር ከተማ” ግፍና መፈናቀል፤ እንደአማራ ተወላጆች ባይበዛም፤ ለሌሎችም ኢትዮጵያዉያን፤ እንደጉራጌና ጋሞ ብሄረሰብ ተወላጆች ላሉትም ነው የተረፈው፡፡ በአጭሩ ለእዚህ ሁሉ ግፍ መነሾ የሆነው ሕገመንግሥቱና፤ በእሱ ላይ የቆመው የብሔር ፖለቲካና የዘረኛ (“አፓርታይድ”) ስርአቱ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለች እንግዲህ እንዴት ብላ ነው ሀገራችን የምትገነባ?
*******
ባጠቃላይ ገና ከጅምሩ ሕገ መንግሥቱ ሲነደፍ፤ በቋንቋና አካባቢ ቢለያዩም፤ በታሪክና በባህል የተሳሰሩትንና ከ80 በላይ የሚገመቱትን የኢትዮጵያ ብሔርና ብሔረሰቦች አስማምቶ፤ በፍቅር አገናኝቶና አዋህዶ፤ በማግባባት ሀገርን በእኲልነትና በአንድ ላይ በጋራ ለመገንባት ታስቦ ሳይሆን፤ ሀገርንና ሕዝብን ከፋፍሎ ለመግዛትና፤ የቁርጡ ቀን ከመጣም፤ የኢትዮጵያን አንድነት አናግቶ በማፍረስ፤ የእራስን ብሔርና (ክልል) ከተሳካም በዙሪያ ካሉት ሌሎች ብሄሮችና ብሄረሰቦች መሬት በጉልበት ነጥቆ በመጠቅለል ለመገንጠል ታቅዶ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም፡፡ ለእዚህ ጥሩ ምሳሌ ደግሞ ከወልቃይት ጠገዴ፤ ጠለምትና ራያ የተሻለ ያለ አይመስለኝም፡፡ ለእዚህ ሀቅ ሌላ ጥሩ ማስረጃ ደግሞ፤ ህወሐት በትግራይ በሽህ የሚቆጠሩ የሰሜን እዝ ወታደሮችን፤ በዘራቸው በተለይም አማራወችን እየለየ በተኙበት እያረደ ጥሎ በቀሰቀሰው ጦርነት በሀገራችን የደረሰዉን ዉድመት ብቻ መመልከት ይበቃል፡፡ የጦርነቱ ዓላማም ካመቸ እንደገና ወደመንግሥት ስልጣን ተመልሶ ኢትዮጵያን አንድ ብሄር መሠረት ባደረገ የገዥ መደብ አምባገነንነት ለመግዛት፤ ያ ካልተሳካ ግን ሀገሪቱን በሕገመንግሥቱ በተከፋፈለው የብሄርና ክልል ድንበር ሰነጣጥቆና አፈራርሶ፤ ወደ ማያባራ የቀውስ አዙሪት በመክተት፤ በግርግሩ ትግራይን “ነጻ አውጥቶ” ሀገረ መንግሥት ለማቋቋም አቅዶ እንደነበር ህወሐት ወደ አስከፊው ጦርነት ዘው ብሎ የገባው ግልጽ ነው፡፡ ይህን እኔ የፈጠርኩት ሳይሆን እራሳቸው የህወሐት መሪወችና ካድሬወቻቸው ቢያንስ በጦርነቱ ወቅት የተናገሩት ስለሆነ፤ ታሪክ ምስክር ነው! እቅዳቸው የከሸፈዉና ሀገራችን ከመፍረስ የዳነችው በልጆቿ መስዋእትነት ነው!
በእዚህ እኩይ ዓላማ ብቻ ከግማሽ ሚልዮን በላይ የትግራይ ወጣቶችን አስጨርሶ፤ በሀገራችን ላይ በተለይም በሶስቱ ክልሎች በትግራይ፤ አማራና አፋር በሽ የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎችን ያስጨረሰበትንና ያወደመበትን ደጋግሞ መጥቀስ የሚገባዉ፤ ለታሪክ ምስክርነት ብቻ ሳይሆን፤ ከተቻለ ለመሪወችና ለፖለቲካ ልሂቃኑ፤ ካልሆነ ግን በተለይም ለወጣቱ ትዉልድ ቋሚ ትምህርት እንዲሆን ነው፡፡ ለእዚህ ሁሉ እልቂትና ቀውስ መነሾ ደግሞ፤ የብሄር ፖለቲካና ዘረኛ ስርአት ስር እንዲሰድ ምክንያት የሆነው ሕገመንግሥቱ እንደሆነ መርሳት የለብንም፡፡ ያንን ሀቅ ያለማወላወል በተለይም መሪወች በድፍረትና በቅንነት መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡ እንዳለፈው ዘመን የሀገራችንን ታሪክ በዉሸት ትርክት ቀይሮ፤ ሕዝቡንና አዲሱን ትዉልድ ማደናገር አይቻልም፤ ሕዝቡ እራሱ በዐይኑ አይቶታልና! “የብሄር ፖለቲካ ሊቀጠበብቱ” በተለይም የህወሐትና ኦነግ መሪወች ግን ይህን በግልጽ የታየ ሀቅም አምኖ ለመቀበል ያዳግታቸዋል፡፡ ሕገመንግሥቱ እንዳይሻሻል ወይም እንዳይቀየር ምንም ሳያፍሩ ሽንጣቸዉን ገትረው በግንባር ቀደምትነት የሚከራከሩ እነሱ ናቸው፡፡ ለእነሱ ጥቅም ሲባል፤ ኢትዮጵያ ወደኋላ ቀርታ፤ በድህነት ተቀፍዳ ተይዛ፤ ምስኪኑ ሕዝቧም ሰላም አጥቶ፤ በጦርነትና የቀውስ አዙሪት ሲማቅቅ ቢኖር ደንታ የላቸዉም፡፡
ሕገመንግሥቱን ተንተርሶ፤ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊነትን ስሜት ቀስ በቀስ ከስር ከስሩ እየቦረቦሩ የማፍረሱ ፕሮጀችት የጀመረው ህወሐት ገና የመንግሥት ስልጣን በያዘ በበነጋዉ ከ30 ዓመት በፊት ነው፡፡ ዜጎች በምንም አይነት መንገድ “ኢትዮጵያዊነት” የሚል የጋራ ትስስርና ሀገራዊ ፍቅር እንዳይኖራቸው፤ በብሄራቸውና በክልላቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩና፤ እርስበርሳቸው እንዲጠራጠሩና እንዲጋጩ፤ ሆነ ተብሎ ለአመታት በጠባብ ብሄረተኞቹ ሴራ ሲሸረብባቸው ነው የኖረው፡፡ ለዚህም ሴራ ዋናዉ መሳሪያ፤ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠናክሩ ባህሎችንና ታሪኮችን ማጥፋት ነበር ትኩረት የተሰጠው፡፡ ለምሳሌ የአድዋን ድል፤ አያት ቅድመ አያቶቻችን ብሄር፤ ቋንቋና ዘር ሳይለዩ አንግበው ሀገራቸዉን ለማዳን የወደቁለትንና፤ ከኢትዮጵያዉያን ባለፈ ለመላው አፍሪካ ኩራት የሆነዉን ሰንደቅ ዓላማችን፤ የአማርኛን ቋንቋ፤ ሌላዉ ቀርቶ በቅርቡ እንደታየው የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ከዉስጥ በመከፋፈል፤ በማጣጣልና ዝቅ በማድረግ፤ የኢትዮጵያዊነትና ዜግነት ስሜቶችን፤ የሀገር አንድነትንና ፍቅር መገለጫወችንና ማዳበሪያወችን እያደበዘዙ ማጥፋት ትልቁ ዘዴአቸው ሆኖ ነው ለአመታት የዘለቀው፡፡ በዚያ ሁሉ ሴራ፤ የሕዝቡን አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ጨርሶ ለማጥፋት ሲያቅታቸው ደግሞ፤ በዘርና በብሄር በሀይማኖት እያለያዩ በማጋጨት፤ በመጨፍጨፍ፤ ንጽሀኑን ቤታቸዉን እያፈረሱ ማፈናቀልንና ማሳደድን ሥራየ ብለው ያዙት፡፡ ይህ ሁሉ ደርሶባትም ኢትዮጵያ አልፈረሰችላቸዉም!
በዚያ ብቻ አላበቃም፤ የሀገራችን ኢትዮጵያ መሬቷ በቋንቋ ብሔርና ብሔረሰብ ተሸንሽኖ “ክልል” የሚል ስም በተሰጣቸው “ትናንሽ ሀገራት” እንድትከፋፈል ተፈርዶባት፤ ዜጎች እንደልባቸው በፈለጉት ክልል ያለስጋት የመኖር፤ የመሥራትና ሀብት የማፍራት፤ ከአንዱ ክልል ወደሌላው እንደልብ የመዘዋወር ዕድል ተነፍጓቸው ነው የኖሩት፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ አንድ ክልል ተሻግሮ ከመሄድ ይልቅ፤ ዉጭ ሀገር መሄድ ይቀላል! ሌላዉ ቀርቶ ወደ ሀገራቸው ዋና ከተማ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ዘራቸው እየተለየ በተለይም ከአማራ ክልል የሚመጡት “ፈልሰው የመጡ” እየተባሉ ወደመጡበት እንዲመለሱ በተደጋጋሚ ተገደዋል፡፡ ይህ የሆነበት አንዱም ምክንያት፤ ክልሎቹ ለስሙ ብቻ በተተከለ “ፌደሬሽን” ይሁን “ኮፌደሬሽን” ለመለየት በሚያደናግር ሀረግ እንዲገናኙ ተደርገው፤ ጠንካራ ሀገር ወይም “ሀገረ መንግሥት” እንዳይገነቡ ሆነ ተብሎ በሕገመንግሥቱ ስለተደነገገ ነው፡፡ እርግጥ ሕገመንግሥቱ በሰጣቸው መብት ተጠቅመው ብሄሮች (ክልሎች) በእራሳቸው ቋንቋ፤ አስተዳደርና ሰንደቅ ዓላማ መተዳደራቸው ምንም ጉዳት የለዉም፤ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውም ነውና፡፡ ይሁን እንጅ፤ ቋንቋን፤ ብሄርንና ክልልን ምክንያት በማድረግ ዜጎችን በዘር እየለዩ ከፋፍሎ ለመግዛትና ለመጨቆኛ፤ እርስበርስም ለማጋጫ መሣሪያ ማድረግና፤ ለዚያ የሚያመች የክልል ሕገ መንግሥት በመቅረጽ፤ ጭራሽ የማእከላዊ መንግሥቱንና የሀገሪቱን ህልዉና የሚፈታተን ስርአት መገንባት ተገቢ አልነበረም፡፡ በእዚህ አይነት ሀገራችን ዉጥንቅጡ የወጣ የህብረተሰብና ፖለቲካ ቀውስ እንድትገባ ያመቻቸዉ በመሠረቱ ይኸው በብሄር ፖለቲከኞች የተረቀቀዉና የሚወደሰው ሕገመንግሥት ነው፡፡ እነዚህ ናቸው እንግዲህ የሕገመንግሥቱና የዘረኛ ስርአቱ ትሩፋቶች፡፡ በእዚህ ሁኔታ እንዴት አድርጎ ነው ታዲያ ሀገራችን የምትገነባዉ? የሕዝቡ ድህነት እየጠፋ ልማትና እድገት የሚመጣዉ!
የሀገራችን መከራ በእዚህ አያበቃም፤ በዉስጣቸው የሚኖሩ ከተለያዩ ብሔሮች ወይም ብሔረሰቦች የሚወለዱትን በዘር እየለዩ፤ ሁሉም ዜጎች በእኩልነት የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ዕድል አንዳይኖራቸው የሚዳርግ፤ ሥራየ ተብሎ በሕገመንግሥታቸው የተደነገገ የዘረኛ (“አፓርታይድ”) አንቀጽ ያላቸው በርካታ ክልሎች ናቸው፡፡ የፌደራል መንግሥቱም የክልል መንግሥታት ዘረኝነቱን እንዲያቆሙ ለማድረግ በሕገመንግሥቱ ስልጣን አልተሰጠዉም፤ ወይም እንዲሰጠዉ የሚፈልግ አይመስልም፡፡ የእራሱ ተቋማት ከብሄሮችና ክልሎች በተዉጣጡ አባላት የተዋቀሩ ስለሆኑ፤ ያንን ለመቀየር በጣም አዳጋች ነው፡፡ ለምሳሌ በቤኒሻንጉል ክልል ሕገመንግሥቱ ስለማይፈቅድ ከተለየ ብሔር (ከአማራ ወይም ከኦሮሞ) የሚወለዱት “እንደሁለተኛ ዜጋ” ስለሚቆጠሩ የክልሉ ባለቤትነት የላቸዉም፡፡ እንደቤንሻንጉል ጉምዝ ተወላጆችም ሙሉ የፖለቲካና ኢኮኖሚ መብት ወይም ዕድል አይሰጣቸዉም፡፡ በተመሳሳይ፤ በቁጥር በጣም አናሳ የሆኑት የሐረሪ ተወላጆች ሕገመንግሥቱን ተገን አድርገው፤ የፖለቲካና ኤኮኖሚ ተቋሞችን በበላይነት በመቆጣጠር፤ በቁጥር የሚበዙትን (በተለይም የአማራና ኦሮሞ ተወላጆችን) በስራቸው እረግጠው በመያዝ እኩል ዕድሉ እንዲኖራቸዉና እንዲሳተፉ አይፈቅዱላቸዉም፡፡ በድሬዳዋ ከተማም ዘረኝነቱ ብዙ ልዩነት የለዉም፤ ለምሳሌ አማሮች የፖለቲካና አስተዳደር ስልጣን እንዲይዙ አይፈቀድላቸዉም፡፡ በሰፊው የሀገሪቱ ክልል በኦሮሚያ ጭራሽ የባሰ ነው፤ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ለአመታት በክልሉ የኖሩና ኦሮምኛ ቋንቋም አቀላጥፈው የሚናገሩ አማሮች፤ እንደኦሮሞወች እኩል የፖለቲካና ኢኮኖሚ መብት ወይም ዕድል የላቸዉም፡፡ በወለጋና በሌሎችም አካባቢወች “ነፍጠኛ” “መጤወች ናችሁ ወደሀገራችሁ ሂዱ” እየተባሉ ይጨፈጨፋሉ፤ ለአመታት ከኖሩበት ቤትና ቀያቸውም በሽ የሚቆጠሩ እየተፈናቀሉ በዱር በገደል ተሰደዋል፡፡ ይህ ነው የሕገመንግስቱ ዉጤት!
እንግዲህ ኢትዮጵያዊነት ዜግነቱስ ይቅርና፤ አሁን ባለው የሀገሪቱ ሕገመንግሥት መሠረት የተፈቀደዉን “የብሄር ወይም የክልል ዜግነት” መብት እንኳን የሌላቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን እንዳሉ ከላይ የጠቀስኳቸው ምስክር የሚሆኑ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ ሁሉ ዜጎች፤ በገዛ ሀገራቸው “ሀገርና ብሄር አልባ” የሆኑ ናቸው፡፡ ሀገራችን ይህን ሁሉ ጉድ በዉስጧ ተሸክማ ታዲያ፤ እንዴት ብላ ነው ከድህነት ልትላቀቅ፤ ልትለማና ልታድግ የምትችለው? እንዴት ብላስ ነው በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንደሀገር ልትገነባና፤ በኢኮኖሚ፤ ፖለቲካና ማህበራዊ ኑሮ፤ በቴክኖሎጅና በዕውቀት ልታድግና ልትበለጽግ የምትችለው? በአፍሪካ ብቸኛዋ ቅኝ ያልተገዛችና በነጻነቷ ኮርታ ለዘመናት የኖረች ሀገር፤ ዛሬ ከአካባቢ አልፎ አህጉሩን በነጻ ንግድና ኢኮኖሚ ለማስተሳሰርና በጋራ ለማሳደግ ግንባር ቀደም ሆና መምራት የሚገባት ኢትዮጵያ፤ በገዛ ልጆቿ ከቅኝ ግዛት በባሰና፤ ጥቁር ዜጎችን ከሰው በታች አድርጎ ለአመታት በባርነት ከገዛዉ አስከፊው የደቡብ አፍሪካ ዘረኝነት (አፓርታይድ) በማይተናነስ ስርአት አዙሪት ዉስጥ ገብታ ትማቅቃለች፡፡ ይህን ሁሉ ጉድ በዉስጧ ተሸክማ፤ ማደጉስ ቀርቶ ዛሬ እንዴት ብላ ነው ኢትዮጵያ ሀገራችን ከፖለቲካ ቀውስ ወጥታ፤ ሰላምና መረጋጋት ልታገኝ የምትችለው? ለእዚህ ነው በቅድሚያ ለእዚህ ሁሉ ምስቅልቅል፤ ቀውስና ኋላቀርነት መነሾ የሆነዉን ሕገመንግሥት በሀገራዊ ምክክር፤ በዉይይትና በብሄራዊ መግባባት፤ ማሻሻል ወይም መቀየር ያስፈልጋል የሚባለው፡፡ ይህን ለማመቻቸትና በግንባር ቀደምትነት ለመምራት ደግሞ፤ በተለይም የፌደራል መንግሥቱ መሪወች ቁርጠኝነት ማሳየት ይኖርባቸዋል የሚባለውም ለዚያ ነው፡፡
የብልጽግና ፓርቲ በድንገት ዘው ብሎ የገባበትና መዉጫዉ የጠፋበት “አጣብቂኝ”!
ሀገራችን ኢትዮጵያ ምናልባትም ባለፉት 50 አመታት ከገጠሟት ዉስጥ፤ በአጭር ጊዜ በእዚህ በያዝነው 5 ዓመት (ህወሐት ከወደቀ በኋላ) ያየችው አይነት ፈተና ያየች አይመስለኝም፡፡ እነዚህን የተወሳሰቡ ችግሮች የወለዳቸዉም፤ ከላይ ደጋግሜ እንደጠቀስኩት፤ በሕገመንግሥቱ ተወልዶ፤ ባለፈው 30 ዓመት ስር የሰደደዉና የተገነባው፤ በብሄር ፖለቲካ የቆመው ስርአት እንደሆነ አያጠራጥርም፡፡ ይሁን እንጅ፤ ባለፉት አምስት አመታት በተለይ የፖለቲካዉ ችግር፤ ከኢኮኖሚውና ማህበራዊ ቀውሱ ጋር ተወሳስቦ፤ አንዱ ከሌላዉ ጋር እየተጠመጠመ በመተብተብ ዉሉን ለይቶ ለመፍታት፤ ለሀገር መሪወችና ፖለቲከኞችም በጣም አስቸጋሪና ፈታኝ የሆነበት ወቅት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ሕዝቡም በኑሮ ዉድነት፤ ሰላም በማጣት፤ በጦርነት፤ በእርስበርስ ግጭት፤ በመፈናቀል፤ በረሀብ፤ በግፍና በሙስና በመሰቃየት ያልገጠመው አይነት መከራ አይገኝም፡፡ ችግሮችን ጭራሽ እንዲወሳሰቡና እንዲቆላለፉ ያደረጋቸው ደግሞ ዋናዉ የህወሐት ጦርነት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ጦርነቱ በተለይም ለማደግ ገና በመንገዳገድ ላይ የነበረዉን የደሀይቱን ኢትዮጵያ ኤኮኖሚ፤ ፋይናንስና መሰረተ ልማት በማዉደምና፤ ሕዝቡን ለእልቂት፤ ለረሀብና የኑሮ ዉድነት በማጋለጥ፤ ሀገራችንን ቢያንስ ሰላሳ ዓመት ያክል ወደኋላ እንደሰደዳት ለመገመት አያዳግትም፡፡
እነዚህን ሁሉ ችግሮች ለመፍታትና ሀገራችን ከገባችበት የስቃይ አዙሪት ወጥታ፤ ከህመሟም አገግማ እንድትጠነክር ለማድረግ፤ መሪወች ብቻ ሳይሆኑ፤ ሁሉም ሀገሩን የሚያፈቅር ኢትዮጵያዊ ወገቡን ጠበቅ አድርጎ አስሮ መረባረብ ያለበት ይመስለኛል፡፡ እርግጥ በመሪወች ላይ ያለው ኃላፊነት ከሁሉም ይበልጣል፡፡ በተለይም በከባድ ፈተና ወቅት፤ ሕዝብን አስተባብሮ ሀገርን ለማዳን፤ ትክክለኛ አመራር ወሳኝ ነው፡፡ ዋናዉ ቁምነገር ሕዝቡና በተለይም የፖለቲካ ልሂቃኑ የሀገራችን ችግሮች ውስብስብ መሆናቸዉንና፤ መሪወቹም አቅም ሊያጡና፤ ሊሳሳቱ የሚችሉባቸው ዕድሎች ሰፊ መሆናቸዉን ተረድተው፤ የጋራ ሀገራችን ለማዳን፤ በጋራ መፍትሄ ማፈላለግ እንጅ ማባባሱ መፍትሄ አያመጣም፡፡ ተያይዘን ከሀራችን ጋር ገደል መግባት ሊያስከትል ስለሚችል መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም የአንድ ሀገር ጥሩ መሪ ትልቁ ችሎታ ደግሞ፤ ከስህተቱ እየተማረ፤ አቅጣጫዉን ማስተካከልና፤ በተለይም ትህትናን በመላበስ፤ ዝቅ ብሎ፤ ሕዝቡን እያዳመጠ መምራት መቻሉ ወሳኝ ነው ብየ አምናለሁ፡፡
ሕዝብን በጎኑ ያላሰለፈ መሪ ሀገሪቱን ምንም ቢሆን ከተወሳሰቡ ችግሪቿ ሊያወጣት አይችልም፡፡ “ወደፈተና አታግባኝ” የሚባለው ጸሎት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ለመሪወች ደግሞ ካወቁበትና ዕድሉን ከተጠቀሙበት ፈተና መግባቱ ያን ያክል መጥፎ አይደለም፡፡ በዓለማችን ታዋቂና ታላላቅ የሀገር መሪወች እንደኔልሰን ማንዴላ፤ አብርሀም ሊንከልን፤ ፍራንክሊን ሩዝቨልት፤ ዊንስተን ቸርችል፤ ማህታማ ጋንዲና ማርቲን ሉተር ኪንግ ያሉት ትዉልድ ተሻጋሪ ታሪክ እየሠሩ መሄድ የቻሉት፤ ሀገሮቻቸው ከባድ ፈተና ዉስጥ በገቡበት ጊዜ፤ ብልሀትን፤ ቆራጥነትንና የሕዝብ ተቀባይነትን በሚገባ እያቀናጁ በመምራት፤ ከፍተኛ ስኬትና መሰረታዊ ለዉጥ ለማስገኘት በመቻላቸው ነው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ የተከሰቱት የተወሳሰቡ ችግሮችም ለመሪወች ያን የመሰለ ታሪካዊ ዕድል መስጠት አቅም እንዳላቸው ምንም አያጠራጥርም፡፡ ሀገራችን ደግሞ በተለይም 20ኛዉ ክፍለ ዘመን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ፤ በመሪወች አላድላት አለ እንጅ፤ በታሪክና በሕዝብ ጥንካሬ፤ ከእነዚህ ሁሉ ሀገራት ብትበልጥ እንጅ አታንስም ነበር፡፡
በእኔ አስተያየት፤ የዛሬው የብልጽግና ፓርቲ መሪወች ከጥቂት አመታት በፊት፤ ጠ/ሚ ዓቢይ አህመድ ስልጣን እንደያዙ፤ ለሕዝቡ ቃል ኪዳን እንደገቡት፤ ሀገራችንን ከኢሀአደግ (ህወሐት) ኋላ ቀር የብሄር ፖለቲካና ዘረኝነት ስርአት አላቀው፤ ወደኢትዮጵያዊነት ለማሻገር ህልም እንደነበራቸው የሚያመላክቱ በርካታ ምልክቶች የነበሩ ይመስለኛል፡፡ ከእነዚህም ዉስጥ አንዱ ኢህአደግን “ብልጽግና” ብለው ስሙን ቀይረው፤ ያቀፋቸዉን ድርጅቶች ለማዋሀድና፤ አንድ ሀገር አቀፍ ፓርቲ በመፍጠር ሀገራችንን አንድ አድርጎ ለመምራት ያደረጉት ሙከራ እንደአንድ ጥሩ የተስፋ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችል ይመስለኛል፡፡ ሆኖም፤ ያለበቂ ዝግጅት ከብሄር ፖለቲካ ወደ ኢትዮጵያዊነት ለመሻገር በሚል ወደ ወንዙ ዘው ብለው ገና እንደገቡ ይመስለኛል ያልጠበቁት ችግር ያጋጠማቸው፡፡ ቀጥለዉም፤ እየተንገዳገዱ የሞላዉን ወንዝ መሻገር ሲያቅጣቸው፤ ያገኙትን አለት ስር የበቀለ ቋጥኝ (ዛፍ) ሙጥኝ ብለው ይዘው፤ ወደኋላ ለመመለስም ሆነ ወደፊት ለመሄድ ግራ ገብቷቸው እየተወዛወዙ ያሉ ይመስለኛል! አንዳንዴ መሻገር ስላቃታቸው፤ ጭራሽ ፊታቸዉን ወደኋላ አዙረው ወደመጡበት ለመመለስም እየሞከሩ ያሉ ይመስላል፡፡
ወደኋላ መመለስ ግን እሳቸዉን ብቻ ሳይሆን ሀገራችንን ከህወሐቱም ጊዜ የባሰ ቀውስ ሊያስገባት ይችላል፡፡ ይልቅ፤ የሕዝቡን ጩኸት ቢያዳምጡና ቢደፍሩ፤ ጠንካራ ገመድ ሰጥቶ ወንዙን የሚያሻግራቸው እሱ ብቻ ይመስለኛል! ዋናዉ ነገር ወንዙን ለመሻገርምኮ ጉልበት ሳይሆን ብልሀት ነው የሚያስፈልገው ብየ አምናለሁ፤ ወደኋላ ለመመለስምኮ በጉልበት መሞከሩ ጥሩ አይደለም፤ አያዛልቅም! ከህወሐት ስህተት ቢማሩ ጥሩ ነው! ብልጽግና ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የብሄር ፖለቲከኞችም ይህን ሀቅ አምነው መቀበል ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ሕዝቡ ቀድሞ ሄዶአል! የሚመራዉ አጣ እንጅ፤ የብሄር ፖለቲካ አንገሽግሾታል፤ በተለይም የህወሐት ጦርነት የፖለቲካ ልሂቃኑንና መሪወችን እንጃ እንጅ፤ ሕዝቡን በሚገባ አስተምሮታል፡፡ ስለዚህ ለሀገራችን ከቀውሱ አዙሪት መዉጫ መንገዱን በጋራና በብልሀት ማፈላለጉ ለልሂቃኑም ለሕዝቡም የሚበጅ ይመስለኛል!
*******
ህወሐት (ትህነግ) ሕገመንግሥቱን ሲያረቅ ሆነ ብሎ “ብሄር ተኮር ፖለቲካዉ” እንዳይጠፋና፤ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገርም አንድ ሆና በጠንካራ ህብረ ብሄር ፓርቲ እየተመራች ለረዥም አመት እንዳትዘልቅ ነበር የወጠነው፡፡ ከህብረ ብሄር ፓርቲ ይልቅ እራሱ በበላይነት የሚቆጣጠራቸዉን “አሻንጉሊት” የብሄር ድርጅቶች “በግንባር” ስም አገናኝቶ፤ “የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር-ኢህአደግ” የሚል ስም ሰጥቶ፤ እራሱን “የትግራይ ሕዝብ ነጻ አዉጭ ግንባር” ብሎ በእኩልነት ሽፋን፤ የበላይነቱን ተቆጣጥሮ መቀጠልን ነበር የመረጠው፡፡ በበላይነት መቀጠሉ ካልተሳካለትና ግንባሩ የሚፈርስ ከመሰለው፤ ትግራይን “ነጻ አዉጥቶ” ለመገንጠል በማቀድ ነበር ሕገመንግሥቱንም ሆነ፤ በብሄር ላይ የቆሙትን ድርጅቶችና የክልል (“የፌደራል ስርአቱን”) አወቃቀር በስልት ያነጸው፡፡ ይህ ሴራዉ ደግሞ ከሞላ ጎደል ለሀያ ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያን ከፋፍሎ፤ ሕዝቡንም በሚገባ በበላይነት ቀጥቅጦ እንዲገዛ አስችሎታል፡፡ ችግሩ “ሁሉም ያልፋል እስኪያልፍ ያለፋል” እንደሚባለው፤ “መቶ አመት እቆያለሁ” እያለ በከንቱ ሲመካ የኖረዉን የህወሐት ዘረኛ መንግሥት፤ ግፉ ያንገፈገፈው ሕዝብ በአመጽ ከ27 ዓመት በኋላ ከመንግሥት ስልጣኑ ነቀለው! ያኔ ህወሐት ወደ ሁለተኛዉ (“Plan B”) ፊቱን አዞረ! ኢትዮጵያን እስከማፈራረስ በመድረስ በግርግር ትግራይን የመገንጠል ቅዠቱን ገፋበት! ይህን እቅዱን ቶሎ በተግባር ለማዋል ያጣደፈው ደግሞ የጠ/ሚ ዓቢይ አህመድ ኢህአደግን አፍርሰው በድንገት ብልጽግናን ማወጃቸው ነው፡፡ ህወሐት የበላይነትን እንጅ እኩልነት የሚባል አያውቅም፡፡ ለዚያም ነው ሌላ ቀርቶ “አጋር ድርጅቶች” በሚል ስም ምናልባት አንድ ሶስተኛ የሚሆኑትን ኢትዮጵያዉያን ብሄር ብሄረሰቦች ወደስልጣን እንዳይጠጉ አድርጓቸው የኖረ! ለነገሩ፤ ህወሐት ተደናብሮ ቶሎ “ወደሽፍትነት” አመራ እንጅ ብልጽግና ስለታወጀ፤ የብሄር ፖለቲካዉ ጨርሶ አልጠፋም፤ የሚፈራዉ ኢትዮጵያዊነትም ገና አልመጣም ነበር!
https://amharic-zehabesha.com/archives/182959
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment