Sunday, May 21, 2023

ለዐማራ ብልጽግና በየደረጃው ላሉ አመራሮች (በተለይም ለአመራር ኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች) የዐማራ መሠረታዊ ጥያቄዎች…
 የዐማራ መሠረታዊ ጥያቄዎች…

(ክፍል ፩)

የዐማራ ሕዝብ በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ምስረታ ጉልህ ሚና ከመጫወቱም በላይ፤ በሂደቱ ፍትሐዊ ሥርዓት ለመፍጠር ታግሏል፡፡ ነገር ግን፣ ከ1966ቱ አቢዮት ወዲህ በተከታታይ በመጡ ሥርዓታት ለነጻነትና ለፍትሕ የከፈለው ዋጋ ትርጉም እንዲያጣ ተደርጎ፣ በገዛ አገሩ ተሳዳጅና ተንከልካይ እንዲሆን ተፈርዶበታል፡፡ አልፎ ተርፎም በሐሰት ትርክት የቀደሙት ሥርዓታት የ"ዕዳ" ወራሽ እንዲሆን ሰፊ ፕሮፖጋንዳ ተሠርቶበታል፡፡

 

መሬት የረገጠው እውነታ ግን፣ ዐማራው ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በጋራ ኢትዮጵያን መገንባቱ እንጂ፤ የብቻ አገር ለመፍጠር የሞከረበት የታሪክ ምዕራፍ አለመኖሩ ነው፡፡ ለአገሩ ነጻነት እንጂ፤ ለሥርዓት ጥበቃ ወይም ዕድሜ ማራዘሚያ የከፈለው መስዋዕትነት አለመኖሩ ነው፡፡

ስለዚህም የዐማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ምስረታ የከፈለው መስዋዕትነት፣ ፍትሐዊ ተጋድሎዎቹ፣ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ጋር ያለው የጋራ መስዋዕትነት ታሪክ በስፋት ሊተረክ፣ ሊፃፍና ሊነበብ ይገባል፡፡

በወያኔ የበላይነት ይዘወር የነበረው ኢሕአዴግ ፈርሶ ብዙዎቻችን ተስፋ የጣልንበት ብልጽግና እንዲወለድ ዐማራ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ዐቢይ አህመድም በድርጅቱም ሆነ በአገሪቱ የመጨረሻው የሥልጣን እርከን ላይ እንዲቀመጡ የአማራ አመራሮች የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ ይህ ውሳኔ ትላንት አያት ቅድመ አያቶቻችን አገር ለመገንባት ከከፈሉት መስዋዕትነት ጋር የሚወራረስ አሮቆ አሳቢነት እንጂ ሞኛ ሞኝ ተግባር አልነበረም። (የጋራ አመራርን ደፍቆ እኔ ብቻ ንጉሥ ባይ እብዱቱን ቀድሞ ለመረዳት ነቢይ መሆን ይጠይቅ ነበር)

ከዚህ በተፈ፣ በአሁኑ ወቅት በባህር ዳር እየተካሄደ ያለው የአመራር ኮንፍረንስ ብልጽግና ፓርቲ የዐማራን ሕዝብ ጥያቄዎች እና ፍላጎቶች እየሄደበት ያለውን መንገድ ከመቼውም በላይ በአንክሮ የሚመረምርበት ሊሆን ይገባል፡፡

(ይህን የምታደርጉት ለራሳችሁና ለቤተሰቦቻችሁ ደህንነት ነው። አሻፈረኝ ብትሉ የመንጋ ፍርድ እያንዣበባችሁ ነውና ዋጋችሁን ይሰጣችኋል)

ልብ በሉ…

በተለይም ኢሕአዴግ/ብአዴንን ፈርሶ ብልጽግና ከተመሰረተ በኋላ ባለፉት ዓመታት የነበሩ ሁኔታዎችን መለሰ ብሎ በጨረፍታም ቢሆን መገምገሙ ነገ የተሻለ ሆኖ ለመውጣት፣ እንዲሁም የዐማራ ጠላቶች ያጠመዱትን ወጥመድ ለማክሸፍ ስለሚረዳ በግልጽ መነጋገር የግድ ይላል፡፡

ለዚህ ግምገማ ይረዳ ዘንድም የተወሰኑ የማንጠሪያ ጥያቄዎችን እንደሚከተለው እዘረዝራለሁ፡-

***

የመጋቢት 24ቱ ሹመት ያዋለዳቸው 24 መዘዞችና ተጠይቆች…

 

1) ዛሬ የዐማራ ሕዝብ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ያለው የውሳኔ ድርሻ በብአዴን ጊዜ ከነበረው ያነሰ ነው ወይስ የበለጠ?

2) ሰላማችንን በተመለከተ ያለንበት ሁኔታ በብአዴን ከነበረው የተሻለ ነው ወይስ የከፋ?

3) በኢሕአዴግ ዘመን የዐማራ ተወላጅ ጥቃት የሚደርስበት ከክልሉ ውጪ፣ ያውም ከከተሞች በጣም በራቁ አንዳንድ (ጉራ ፈርዳ፣ መተከልና የወለጋና ሐረርጌ ገጠራማ፣…) አካባቢዎች ነበር፡፡ ታዲያ በብልጽግና ዘመን በገዛ ክልሉ ማንነታዊ ጥቃት ሊፈጸምበት የሚችል ክፍተት እንዴት ተፈጠረ?

4) በብአዴን ጊዜ ያልነበረው፣ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን አመራሮች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች ዋንኛ መነሾ ምንድን ናቸው?

5) በፌደራል መንግሥቱ ተቋማት እና በአዲስ አበባ ላይ ያለን ድርሻ፣ በብአዴን ጊዜ ከነበረን ጋር ሲነጻጸር ምን ይመስላል?

6) ባለፉት አምስት ዓመት በዐማራ ክልል ምን ያህል የጤና ኬላዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ መንገዶች እና የመሳሰሉት መሰረተ ልማቶች ተሠርተዋል?

7) ከኦሮሞ ወንድም እህቶች ጋር “ኦሮ-ማራ” የሚል ጥምረት ፈጥረን ባዋለድነው ዐዲስ ሥርዓት የሚገባንን ያህል ተጠቃሚ ሆነናል? ጥምረቱስ በአክራሪ ብሔርተኞች የሚሰነዘርብንን የተዛባ ትርክት መክቷል ወይስ አባብሶታል? ኦሮ-ማራ ዛሬ ወደ ኦሮ-ሴራ በተቀየረበት ሁኔታ የዓላማ አንድነት አለ ማለት ይቻላል?

ብልጽግና ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የፈጠረው ዐዳዲስ እሴቶች እና አገራዊ ሃብት አለ ወይ? (መቼም ፓርክና መናፈሻ 120 ሚሊየን የሚሻገር ሕዝብ ላላት አገር 'ቁልፍ ሀብት ናቸው' ማለት ዘበት ነው። መነሻችንም፦ “ብልጽግና አገራዊ ሀብት መፍጠር ስላልቻለ፣ የነበረውን በመቀራመት ላይ ተጠምዷል” የሚለውን መሬት የረገጠ ትችት ከግምት በማስገባት ነው፡፡)

9) ብልጽግና ውስጥ እውነተኛ የቡድን አመራር አለ ወይ?

10) ኢሕአዴግ ገና ከመነሻው ከ1983 ዓም ጀምሮ “የሽግግር ኢኮኖሚ ፖሊሲ”፣ “የገጠርና ግብርና ፖሊሰ”፣ “ግብርና-መር ፖሊስ”፣ “ግብርና-መር የኢንዱትሪ የልማት አቅጣጫ” እና በሦስት የተከፈሉ የትራንስፎርሜሽን እቅዶች (በየአምስት ዓመቱ የሚተገበሩ ሆነው ለዐሥራ አምስት ዓመት ያገለገሉ) ነበሩት፡፡ እንዲሁም የፍትሐዊነት ጥያቄ ቢነሳበትም በገቢ ዝቅተኛ የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል የሚያሳትፍ የአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማትን ለመፍጠር ሞክሯል፡፡ ብልጽግናስ?

11) ፓርቲው መንግሥት ከመሆኑ አኳያ፣ ለሕዝቡ ወደታች ወርዶ ሀሳቡን የሚሸጥበት በሳይንሳዊ ጥናት ያሰናዳው የልማት እቅድ አለው?

12) እንዲደመር የቀሰቀሳችሁት ሕዝብ በቀጣይም ከጎናችሁ ሆኖ እንዲዘልቅ በፖሊሲ እና በእቅድ የተዘጋጀ አገራዊ ለውጥ የሚያመጣ የሪፎርም አቅጣጫ አላችሁ ወይ?

13) በዘመነ ኢሕአዴግ የነበረው ኪራይ ሰብሳቢነት እና ሙስና፣ በብልጽግና ዘመን ቀነሰ ወይስ ጨመረ?በኢሕአዴግ ጊዜ የአመራር ምደባ ለማግኘት ረብጣ እጅ መንሻ ገንዘብ የሚሰጥበት ሁኔታ ነበር? አሁን ላይ ለከንቲባ ሹመት እጅ መንሻ ስንት ብር ገባ?

14) ብልጽግና ውስጥ መርህ-የለሽ አሠራር የሚስተዋለው ለምንድን ነው? የፓርቲው አባላት ላይ ብቻ ሳይሆን መላ ሕዝቡ ላይ ቅጥ ያጣ የግለሰብ አምልኮ እንዲጫን ተግቶ መስራት ለዐማራ አርሶ አደር ፋይዳው ምንድር ነው?

15) ባለፉት አምስት ዓመት ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ዐማራ ክልል የተፈናቃዮች ማከማቺያ ለምን ሆነ? በፌደራል ደረጃ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ምን ዓይነት ዕቅድ ተነድፎ ተሠርቷል? በቀጣይስ ተፈናቃዮችን ወደ ቦታቸው ለመመለስ የታሰበ ነገር አለ ወይ?

16) በፌዴራል ደረጃ ባሉ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት (መከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ብሔራዊ መረጃ፣…) ላይ ፍትሐዊ የአመራር ድልድል አለ? ከእነዚህ ተቋማት ላይ በአመራር ስምሪትም ሆነ በሙያ አገልግሎት ደረጃ ዐማራን የመግፋት ፖሊሲ እየተተገበረ ነው። በዚህ ሁኔታ አብሮነት እንዴት ሊቀጥል ይችላል?

17) ወያኔ የለኮሰው ጦርነት ቆሞ ድርድር ከተጀመረ በኋላ፣ እኛ እንደ ዐማራ በድርድሩ ላይ የነበረን የተሳትፎ ድርሻ፣ በጦርነቱ ከነበረን ድርሻ አኳያ ሲታይ የሚመጣጠን ነው ወይ? (የዶ/ር ጌታቸው ጀምበር በድርድሩ ተሳታፊነት ምን ያህል ሚዛን እንዳስጠበቀ ለሚያስተውል ሰው በፕሪቶሪያው ድርድር በጦርነቱ ላይ በነበረነን ድርሻ ልክ ተሳታፊ ብንሆን ዛሬ ላይ ሁኔታዎችን መቀየር በተቻለ ነበር) በተያያዘ ተጠየቅ፦ የፕሪቶሪያው ስምምነት ኦዲት እየተደረገ ነው?

18) በጦርነቱ የወደሙ መሰረተ-ልማቶችን መልሶ በመገንባቱ ረገድ የፌደራል መንግሥቱ ምን ያህል አስተዋጽኦ አድርጓል? (የኦሮሚያ ክልል “በጦርነቱ ለደረሰው ውድመት” በሚል ለትግራይ እያደረገ ያለውን ድጋፍ ልብ ይሏል)

19) ከኢሕአዴግ እና ከብልጽግና በተሻለ ደረጃ መንግሥትን እና ሃይማኖትን ነጣጥሎ የሚያስኬደው ሴኩላር ሥርዓት የትኛው ነው?

20) በፌደራሉም ሆነ በክልል ደረጃ በአመራሩ መካከል የሃሳብና የተግባር አንድነት አለ? ብልጽግና ፓርቲ በከፍተኛ ሁኔታ የሀሳብ ድህነት ገጥሞታል። በኢሕአዴግ ጊዜ እንዲህ አሁን እንደሚስተዋለው 'ስፖንሰርድ' የሆነ የጎጥ ክፍፍል ነበርን? ይህ የተስፋፋው የሀሳብ ድህነትና የፖለቲካ ዕውቀት ያረጠበት ብልጽግና አይደለምን?

21) በፓርቲው ውስጥ በተለይም በአመራሩ ዘንድ ስር የሰደደው ሕዝበኝነት በቀጣይም ከባድ አደጋ ሊያመጣ የሚችል ስለመሆኑ በአደጋው ልክ ትኩረት ተሰጥቶታል ወይ?

22) ለምንድን ነው በአገር ጉዳይ መንገራገጭ በተፈጠረ ቁጥር የዐማራ እና የኦሮሚያ ብልጽግና ቅርንጫፎች ብቻ በተናጠል ተሰብስበው እንዲመክሩ የሚደረገው? ፓርቲው ወጥ ከመሆኑ አኳያ ሌሎች ክልሎችም መሳተፍ የለባቸውም ወይ? (ለምሳሌ፣ በኢሕአዴግ ጊዜ በኦሮሚያ ወይም በዐማራ ሊሚፈጠር ችግር አራቱ ድርጅቶች በጋራ እንደ ኢሕአዴግ ተሰብስበው እንደሚወስኑ ይታወሳል፡፡)

23) ባለፉት አምስት ዓመት ብሔራው የሀብት ክፍፍሉ ፍትሐዊ ነው? እንደ ዐማራ በሀገር ዐቀፍ ደረጃ ባለው ገቢያ እኩል ተጠቃሚነት አለን? ብሔራዊ ባንክ፣ ልማት ባንክ እና ንግድ ባንክ ሁሉንም ክልሎች እኩል እያገለገሉ ነው?

24) በፌደራል መንግሥቱ የሚተዳደሩ ሚዲያዎች ላይ ያለው ተጠቃሚነት ፍትሐዊ ነው?

የእነዚህ 24 ጥያቄዎች ምላሾች፣ ከዚህ በኋላ ከብልጽግና ጋር መቀጠሉ ነው ወይስ መለያየቱ የሚጠቅመን? የሚለው ጥያቄ ላይ ግንዛቤ እንደሚፈጥሩ ልብ ይሏል፡፡

እነዚህ ጥያቄዎች፣ በአመራር ኮንፈረንሱ የቡድን ውይይትም ሆነ በኃይል መድረክ መነሳት ያለባቸው ጥያቄዎች ናቸው። የጽሁፉ መግፍኤም ሀሳቦቹ በመድረክ እንዲነሱ ነው።

ስለዚህም ይህ የአመራር ኮንፍረንስ እንደ አገርም ሆነ እንደ ሕዝብ ከገባንበት ቅርቃር እንድንወጣ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ላይ አተኩሮ አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጥ ካልቻለ ሕዝብ የራሱ የሆኑ አማራጭ የትግል ስልቶች አሉት። 2008ን በሚያስንቅ ሁኔታ ሆ… ብሎ ይነሳል። ከዚያኛው ጊዜ ይኼኛው እጅግ ይከፋል። …ገና እያሟሟቀ ነው።

በተለይም “የቀውስ ጊዜ እቅድ” እና በዘላቂነት መፍትሔ የሚሆኑ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችን ለያይቶ መስራት ካልቻላችሁ የዐማራ ሕዝብ የራሱን ዕጣ ፈንታ በራሱ ይወስናል። ሕዝቡ ይህን ሲያደርግ፣ በቅድሚያ እናንተ ላይ ወሰኖ ነው።

ለመሆኑ ዋነኞቹ የዐማራ ጥያቄዎች ፖለቲካዊ ቁመና ምን ላይ ነው?

 

የዐማራ መሠረታዊ ጥያቄዎች

(ክፍል ፪)

በቀዳሚው ክፍል ያለፉት አምስት ዓመታትን ፖለቲካዊ ሁኔታዎች በ24 ተጠየቆች በማንሳት ወደውስጥ መመልከት የሚቻልበትን ሀሳብ ለማንሳት ተሞክሯል።

ጽሁፉ ካላነበቡ ይህን ማስፈንጠሪያ ይዳብሱ

በክፍል ፪ ጽሑፍ ደግሞ ዋነኞቹን የዐማራ ሕዝብ ጥያቄዎች እንመለከታን፦

በቅድሚያ ኢትዮጵያ የቆመችበትን መስቀለኛ መንገድ መረዳት ይገባል። አገሪቱ ያለችበትን መንታ መንገድ በመረዳት፣ እንዲሁም በግለሰብም ሆነ በማኀበረሰብ ደረጃ የተፈጠሩ ቀውሶች ላይ ትኩረት በመስጠት (ግለሰቦችም ሆነ ማኀበረሰብ አደገኛ ሁኔታ ሊፈጥሩ የሚችሉበት እድል እንዳለ፣ የዓለምን ታሪክ ያጤኗል፡፡) መፍትሔ ማበጀት፣ መውጫ መንገዶችን መቀየስ ለነገ የማይባል የዛሬ የቤት ሥራ ነው።

ሌላው በሰሞነኛው የባህርዳሩ የአመራር ኮንፍረንስ ላይ የሚከተሉት የዐማራ ሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎቹ መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል፡-

1ኛ) ከሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ አኳያ በቅድሚያ

የክልሉ ሕገ-መንግሥት እንዲሻሻል ውሳኔ ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ እርምጃ ቀጥሎ የፌደራሉ ሕገ-መንግሥታ በተለይም ከመነሻው ጀምሮ ያለበቂ ውክልና በመጽደቁ፣ የቅራኔ መነሻ በመሆኑ፣ ይዘቱም በስሁት ትርክት ላይ በመመስረቱና የአወጣጥ መዛነፍ ያለበት በመሆኑ በመላ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎና የጋራ መግባባት እንዲሻሻል ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠይቃል፡፡ የሕገ-መንግሥታዊ መሻሻል ጉዳይ አይቀሬ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም በመሠረታዊ ይዘቶች መሻሻል ላይ አበክሮ መስራት ይጠይቃል።

2ኛ) የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች፡-

ሕገ-መንግሥቱ ከመፅደቁ በፊት፣ የኢትዮጵያ የሽግግር ጊዜ ቻርተር በአንቀፅ ቁጥር 13 “የክልሎች አስተዳደር በብሔሮች አሰፋፈር ላይ ተመርኩዞ ይቋቋማል”፣ የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 7/1984 በአንቀፅ ቁጥር 4 “የብሔር፣ ብሄረሰብ እና ሕዝብ ኩታ ገጠም አሰፋፈር ለብሄራዊ መስተዳደር ወሰን አከላለል መሰረት ይሆናል” በማለት በግልፅ የተደነገገውን ሕግ በተቃረነ ሁኔታ የወልቃይት-ጠገዴ፣ ጠለምት እና የራያና አካባቢው ሕዝብ በብሔር፣ በኩታ ገጠም አሰፈፈር፣ በማንነትና በቋንቋ ከሚመስለው የቀድሞው በጌምድር (ጎንደር ክፍለ-ሃገር) እንዲሁም የራያ፣ ኦፍላና ኮረም ሕዝብ የወሎ ክፍለ-ሃገር ነባር አካባቢዎች የተካለሉበት የዐማራ ክልል ወጥቶ ወደትግራይ ክልል በጉልበት ተካልሎ ቆይቷል፡፡ የመተከል ጉዳይም ከዚህ በትይዩ የሚታይ ነው፡፡

በዚህም ሕግን ያላገናዘበ አከላለል ያለፍቃዳቸው በፖለቲካ ውሳኔ እንዲተዳደሩ የተፈረደባቸው በእነዚህ አካባቢዎች ሕዝቡ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት በቃላት ሊገለፁ የማይችሉ የተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ግፍና እና በደል ሲደርስበት ቆይቷል፡፡

ስለሆነም የኢፊድሪ ህገ የመንግሥት አ/ቁ 46 “ክልሎች የሚዋቀሩበትን የሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፍቃድ ላይ በተመሰረተ ሁኔታ ይሆናል” በሚለው መሰረት እና የፌደሬሽን ምክር ቤት ስልጣን እና ተግባር ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1261/2013 አንቀጽ 37 (1) እና (2) እንዲሁም አንቀጽ 38 (1) መሰረት የወሰንና የማንነት ጥያቄው በሕጋዊ አግባብ እንዲመለስ ማድረግ ቀዳሚውና መሠረታዊው ጉዳይ ነው፡፡

3ኛ) በሌሎች ክልሎች ሊኖር የሚገባ የፖለቲካ ውክልና፡- የዐማራ ሕዝብ በመላ ኢትዮጵያ ተሰራጭቶ የሚኖር መሆኑ ይታወቃል፣ ስለሆነም በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች (ክልሎች) የሚኖረው ዐማራ የፖለቲካ ውክልና እንዲኖረው (ተመጣጣኝ ውክልና) ማስቻል አንዱና ወሳኙ የሕዝቡ ጥያቄ ነው፡፡

በተለይም በፌዴራል መንግሥቱ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋዎች (ለአብነት፡-ኦሮምኛ ቋንቋ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ከመወሰኑ አንፃር ከአስር ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የዐማራ ተወላጆች በሚኖሩበት የኦሮሚያ ክልል ውስጥ አማርኛ ቋንቋ ሁለተኛው የክልሉ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን መደራደር እንደዋና አጀንዳ መያዝ ይኖርበታል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ጉዳይን እንደማሳያ ተመለከትን እንጂ በሌሎች ክልሎች አማርኛ ቋንቋ በሁለተኛ የሥራ ቋንቋ በሕግ-አንዲፀና መታገል ይጠይቃል)፣ በክልሎች አማርኛ ሁለተኛ የሥራ ቋንቋ ሆኖ በሕግ እንዲፀና ማድረግ ይጠበቃል፡፡

ይህ ጥያቄ በሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ሂደት የሚፈታ ቢሆንም ጥያቄው በይዘትም ሆነ በገቢራዊነት ደረጃ የሀገር ባለቤትነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው፡፡

የዐማራ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት የአመሰራረት ታሪክ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተሰራጭቶ የሚኖር ሕዝብ እንደመሆኑ መጠኑ የቡድን መብቶቹ ሊከበሩለት ይገባል፡፡ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚኖረው የዐማራ ተወላጅ የሀገር ባለቤትነት ጥያቄው አልተረጋገጠለትም ሲባል፤ መልስ የሚፈልጉ የህግና የመዋቅር ችግሮች አሉ ማለት ነው። የሀገር ባለቤትነት ጥያቄው እንዲረጋገጥ የሕግና የመዋቅር ጥያቄዎቹ ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

4ኛ) የሕዝብና ቤቶች እውነተኛ ቆጠራና ቅቡልነት ያለው ውጤት፡- በኢትዮጵያ የዘውግ ፖለቲካ ውስጥ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት ፖለቲካዊ ዋጋው ከፍተኛ ነው፡፡ የክልሎች በጀት ድልድል በዋናነት 'ፊስካል ፖሊሲው' የሚተገበረው ሪፖርቱን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ የፓርላማ ወንበር ቁጥር እንዲሁም የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤትን የተተንተራሰ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር በ1998/9 ዓ.ም የተደረገውን የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ ተከትሎ፣ መንግሥት ባወጣው ይፋዊ የቆጠራ ውጤት፣ 2.5 ሚሊየን የሆነ የዐማራ ሕዝብ ጠፍቷል ተብሎ ለፓርላማ ሪፖርት መደረጉ ይታወቃል፡፡ በመንግሥት የታመነው እና ጠፋ የተባለው የዐማራ ሕዝብ ብዛት 2.5 ሚሊየን ቢሆንም፣ የቀደሙትን ቆጠራዎች ማለትም እ.ኤ.አ የ1984፣ የ1994 እና የ2007ን የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ ያጠኑ ምሁራን፣ የታዳጊ አገሮችን የሕዝብ ዕድገት ምጣኔ፣ የሌሎች የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የዕድገት ምጣኔ እና አስቀድሞ የነበረውን የዐማራ ሕዝብ ቁጥር መሰረት አድርገው በሰሩት ትንታኔ፣ እ.ኤ.አ 2007 ዓ.ም (በ1998/9 ዓ.ም) በተደረገው የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ መኖራቸው የተካደው ወይም እንዲጠፉ የተደረጉት አማሮች ቁጥር እስከ 6.2 ሚሊየን ሕዝብ እንደሚደርስ አረጋግጠዋል፡፡

በ1998 ዓ.ም በተደረገው የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ በዐማራ ሕዝብ ላይ የቁጥር እልቂት (numerical genocide) ለመፈፀሙ ዐቢይ ማሳያ ሆኖ ይቀርባል፡፡ በዚህ ጥያቄ ዙሪያ አብን የዛሬ አራት ዓመት በሰነድ የተደገፈ የጠራ አቋም ማሳየቱ ይታወሳል፡፡

ስለሆነም፡-የዐማራ ሕዝብ የ3ኛው ሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት እንዲከለስ/እውነተኛ ቆጠራ እንዲካሄድ ይፈልጋል፡፡ በመሆኑም፡-

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ባለሥልጣን የተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 442/97 እንደገና እንዲከለስ እና የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ በሆኑ ባለሙያ ኢትዮጵያውያን እንደገና እንዲደራጅ፡፡

የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን የተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 449/97 እንዲከለስ፤ በተለይም የአዋጁ አንቀጽ 6 ላይ የተመለከተው የኮሚሽኑ አባላት ስብጥር፣ ተመጣጣኝ እና ሚዛናዊ ውክልና ኖሮት፣ ከመንግሥት ባለሥልጣናት በተጨማሪ በሕዝብ እና በመንግሥት እምነት የሚጣልባቸው ኢትዮጵያውያን ምሁራን ተካተው ኮሚሽኑ እንደገና እንዲቋቋም፡፡

በቀጣይ ጊዜና ሁኔታዎች ሲፈቅዱ የሚከናወነው የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ የሕዝብ ዕድገት ምጣኔ ስሌት (projection) በ1998/9 ዓ.ም በተካሄደው የቆጠራ ውጤት ሳይሆን ከዚያ በፊት (እ.አ.አ በ1984 እና በ1994) የተደረጉ የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ ውጤቶችን ብቻ መሰረት አድርጎ እንዲከናወን መደረግ አለበት። በዚህ ዙሪያ ሁለም የአማራ ኃይሎች ወጥየሆነ አቋም ሊኖራቸው ይገባል።( አብን የአጀንዳው ዓይን ገላጭ በመሆኑ በድጋሚ ሊመሰገን ይገባል ከላይ የተመለከቱ ነጥቦች መነሻቸው አብን ነው)

5ኛ) በመልማት ጸጋው ልክ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን፡- የትህነግ ዘረኛ ሥርዓት ለሃያ ሰባት ዓመታት የማዕከላዊ መንግሥቱን በበላይነት ይዞ በነበረበት ጊዜ የዐማራ ክልል ከሀገራዊ የልማት ድርሻ በሚገባው ልክ ተጠቃሚ እንዳይሆን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በተለይም በማህበራዊ ልማት ተቋማት ግንባታ በኩል፣ በሜጋ ፕሮጀክቶች ስርጭት ዙሪያ ፍትሐዊነት አልነበረም፡፡ የጤና፣ የትምህርት፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የመንገድ፣…. ወዘተ ልማቶችን ከሌሎች ክልሎች ጋር በንፅፅር ብንመለከተው የዐማራ ክልል በልዩ ሁኔታ ተበድሏል፡፡

ይህ ኢ-ፍትሐዊ አሰራር አሁንም የቀጠለ በመሆኑ በኢትዮጵያ ፍትሃዊ የአገልግሎትና መሰረተ-ልማት ስርጭት ሊኖር ይገባል። ይህም ሲባል ፍትሃዊነት ማለት የልማት ማካካሻዎችንም የሚጨምር በመሆኑ፣ ከዚህ ተጨማሪ ማነጻጸሪያና አግልግሎቶቹን የማዳረሻ መመዘኛዎች ሊኖሩት ይገባል፡፡

በዚህ ረገድ አስቻይ ሕጎች እና የፍትሐዊነት ስርጭት መለኪያዎችን አውጥቶ የመከታተሉ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ የልማት ማካካሻ ያስፈልገዋል፡፡

6ኛ) የሀገር-ግንባታና የፌዴራል መንግሥት

ውክልና ጉዳይ፡- የዐማራ ሕዝብ በኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት በወርድና በቁመቱ ልክ እንዲወከልና ቀጣይነት ባለው የሀገር ግንባታው ሂደት ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጋር ንቁ ተሳታፊ የመሆን ጥያቄ አለው፡፡

በዚህ የጥያቄ ማዕቀፍ ውስጥ በዐማራ ሕዝብ ላይ የተነዙ የሐሰት ትርክቶችን በመናድ (deconstruct) እና እንደገና ቅርፅ በማስያዝ (reconstruct) መቃኘት ይገባል።

የኢትዮጵያ ብሔረ-መንግሥት (የሀገር ግንባታ ሂደት) በዋናነት፡- አንድ የፖለቲካ ማኀበረሰብ መገንባት፣ የብሔር ጉዳይን እና ሀገራዊ ብሔረተኝነትን በማስታረቅ የጋራ ማንነትን ማሳደግ፣ ሀገራዊ መግባባትና ዕርቅ እንዲሁም በሀገራዊ ጉዳዮች የልሂቃን ስምምነት በማምጣት ላይ ያተኮረ ሊሆን ይገባል፡፡

በእነዚህ ሂደቶች የዐማራ የፖለቲካ ኃይሎች በተለይም መሪ ድርጅቱ የተጣለበትን ታሪካዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ከፓርቲ-ፖለቲካ በላይ ኃይል ማሰባሰብ ይጠበቅበታል፡፡

የችግር አረዳድና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ሁለንተናዊ ቅኝት ያረፈባቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡

በዚህ ረገድ የዐማራ የሀሳብ ቋት በማደራጀት በኢትዮጵያ ፖለቲካ የአገራዊ ፖለቲካችን መገለጫ ሆኖ የኖረውን ትርክት ላይ የተመሠረተ አመፅ (Discursive Violence) በመቀልበስ፣ የ‹‹ጨቋኝ›› ‹‹ተጨቋኝ‹‹ ትርክት ጠፍቶ የጋራ ማንነትና የወንድማማችነትን እሴት ያዳበረ ትውልድ ግንባታ መሰረቱ እንዲታደስ፣ አኗኗሪ ትርክቶችን አጉልቶ ማውጣት የግድ ይላል፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ የዴሞክራሲ እና መሰል ተቋማት ግንባታዎች ለፌድሬሽኑ እጅግ ወሳኝ በመሆናቸው ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ሊገነቡ ይገባል፡፡

ኮርኳሪ ነጥቦች…

ባለፉት ዓመታት በዐማራ ክልል የተካሄዱ የዐደባባይ ሰልፎች መነሾዎቻቸው ሙሉ በሙሉ ስህተት ነው ብሎ መደምደሙ ተገቢ አይደለም። በፅንፈኝነት መፈረጁም አወዳደቅን ቢያፋጥን እንጅ መውጫ አይሆንም። ዐደባባዩ ላይ የተሰሙ ትክክለኛ የሆኑ ጥያቄዎችን እየለዩ አፋጣኝ ምለሾችን መስጠት የግድ ይላል፡፡

ወጣቱ “እንዋጋ እንዋጋ በለው…” ብሎ በይፋ እስከመጨፈር ያደረሰው ገፊ-ምክንያት ሊፈተሸ ይገባል። ከፍተኛ የሆነ የህልውና ስጋት ያለበት ሕዝብ ነው። በአናቱም በተደጋጋሚ የተካደ ሕዝብ ነውና ከዚህም በላይ ምሬቶች አሉት፡፡ በዚህ ሁኔታ የአማራ ብልጽግና መንግሥት ሆኖ ሊቀጥል አይችልም። ቁመናው ተበልቷል። የሰመረ የሕዝብና የመንግሥት ግንኙነት ቀርቶ መደማመጥ የጠፋበት እጅግ የተናቀ ሥርዓት ሆኗል። በዚህ ሁኔታ የሕዝብ ጥያቄዎችን ሳይመልሱ በሚዲያ አታሞ ተከልሎ ማለፍ አይቻልም። ጊዜው አልፏል። አሁን ጠያቂ ብቻ ሳይሆን ሞጋች ለመብቱ ታጋይ ማኀበረሰብ ተፈጥሯል። ይህን critical mass መረዳት ይጠይቃል።

በተቀረ ሕዝቡንም ሆነ የመካከለኛ እና የታችኛውን የአመራር አባላት በጅምላ በማኀበራዊ ሚዲያ የሚነዳ መንጋ አድርጎ ማሰብ ተገቢ አይደለም፡፡ በተለይ መካከለኛውና የታችኛው አመራር የሕዝብ ሰልፉን ጠብቆ መዝለቅ እንደሚያዋጣው ከዕለት ተዕለት ሕይወቱ የተማረው ጉዳይ በመሆኑ ለ"ትኩስ ድንች" ተረክ ቦታ የለውም። እናም የሕዝብ ወገንተኛ ከመሆን ውጭ ሌላ አማራጭ የላችሁም። ቀሪው ምርጫ የጋዳፊ ቀሪው ምርጫ የሳዳም ነው።

ደግሞም ጨው የሚጣፍጠው ለራሱ ነው።

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/182784

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...