Saturday, April 22, 2023

   እመአፈ ደቂቅ ወሕጻናት…( ከሕጻናት አንደበት…)
እኔ ባደኩበት ባህል ስለ ሕጻናት የሚነገሩ አባባሎች አሉ፡፡ "ሕጻን ያቦካው ለራት አይበቃም" እና "የልጅ ነገር ሁለት ፍሬ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ" የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በመጀመሪያው አባባል ላይ ለምሳና ቁርስ ግን መሆን ይችላል የሚል አንደምታ ያአለው ይመስለኛል፡፡ መቼም ቡኮ ሁለት ሶስት ቀን ሊሆን ይችላልና፡፡ ሁለተኛው ላይ ግን፣ ልጅ ነገሩ ሁለት ነው፣ አንደኛው የበሰለና መሬት የያዘ ሲሆን ሁለተኛው ግን ግዜ የሚፈለግ መሆኑን ነው የሚገልጸው፡፡

አንቺ ሃገር ንጉስሽ ህጻን የሆነ… የሚል አባባል ሰምቼም ነው ያደኩት፡፡ ባደኩበት ሴማዊ-ኩሺቲክ ባህል መቼም የግድ ሃማሴን(ካምና ሴም) የኩሽ ልጅ ሃምና የሴም ልጅ የመጀመሪያ መደባለቂያ ስፍራ መጥቀስ አይገባኝም፣ ባህሌ በብዙው ኦሪታዊ - ክርስትያን (Judeo- Christian) ነው፡፡ ኢሰላሚክ የሆን የባህል ትስስርም በደንብ አለኝ፡፡

በሃገሬ ባህል ዘንድ "አንተ ሰው እረኛ ምን አለ?" የሚለው አባባል፣ ስለ የሚመጣው ትንቢት አመላካች ነገርን ይዞ የሚነገር ነገር ነው፡፡ እረኛ ሲል ከስድስት ዓመት እስከ አስራ ሁለት አመት ያለውን እድሜ በአትኩሮት ይዞ የሚነገር ነው፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ባህል እረኛን እንደ ነብይ መቁጠር ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ ኢትባህል ነው፡፡ ይኸውም ከሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለት ላይ ይቀዳል፡፡ በዚህ ወንጌል ላይ መላእክት ከሰማይ ወርደው የክርስቶስን መወለድ ለእረኞች ስለገለጹና ሰውና መላእክት በአንድ ላይ የዘመሩትን መዝሙር በመጥቀስ፣ እረኛን ቅሩበ ቅዱስ መናፍስት አድርጎ የመግለጽ ነገር በደገኞቹ ክርስትያኖች ዘንድ ይስተዋላል፡፡

ጠ/ሚ መለስ ከመሞታቸው አንድ- ሁለት አመት በፊት በዘመዶቼ ወለዬዎች ዘንድ የጊምባ እረኞች ይሉት የነበረው ነገር ትዝ ይለኛል፡፡

አህያ መጣች ተጭና ቁል∙ቋል

መለስ ዜናዊ እዚያ ጋር ወድቋል

እንዳላነሳው አንጀቴ ቆስሏል፡፡

ይህ ከተባለ በኃላ ጠ/ሚ ህይወታቸው አለፈ፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ የሞቱት በአንጀት ካንሰር መሆኑነ ነው፡፡ የሆነ ያክል ሳ.ሜ. እርዝመት ያለው ያንጀታቸው ክፍል ተቆርጦ ከወጣ በኃላ፣ ትንሽ ተሸሎቸው አራት ኪሎ ጆሊ ባር አካባቢ የነበረ ሬስቶራንት ውስጥ የሚወዱትን ሽሮ እንደበሉ ግን ድጋሚ ህመማቸው በማገርሸቱ ወደ ውጭ ለህክምና መሄዳቸውን ሰምቼለሁ፡፡ "አንጀቴ ቆስሏል" ማለት እንግዲህ ይሄ ነው፡፡

ነገሩ በአባታችን በልበ አምላክ ዳዊት እንደተነገረው፣

እመአፈ ደቂቅ ወሕጻናት አስተዳሎከ ስብሐት፣

በእንተ ጸላኢ ከመ ትነስቶ ለጸላኢ ወለገፋኢ

ትርጉሙም፣   ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አንደበት ምስጋናን አዘጋጀህ፣

ስለ ጠላትህ ጠላትንና ግፈኛን ታጠፋው ዘንድ፡፡

ጠ/ሚ አብይ አህመድ "እኛ ኢትዮጵያን አናፈርስም" በሉበት እሰየው ንግግራቸው የቀደመውን የራሳቸውን አባባል ተቃርነው ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ ምክነያቱም "ከፈለግን ማንም አያቆመንም" የሚለው ተከታይ ንግግራቸው ከእብሪተኞች ጎራ ይደበልቃቸዋልና፡፡

በኮንፊዩዝና ኮንቪስ የሚመራው ፖለቲካ ተከታታይ አጀንዳዎቻቸው፣ በሐይመኖት፣ ቤት ፈረሳ… ለምን ለኢትዮጵያውያን ይሰጣል ብለን እራሳችን ከጠየቅን፣ የኃይሉ ገ/ዮሐንስ(ጎሞራው) ግጥም መልስ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የከሸፈ ፖለቲካ!

ያሰብከው አላማ አለሆን ብሎ ሲከሽፍ

ሁኔታው ሲጠጥር፣

ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር፡፡

መቼም በእምነታቸው ፕሮቴስታንት ቢሆኑም፣ መገለጥን ይዤ መጥቻለሁ ሲሉ ደገግመን ሰምተናቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ አትፈርስም ሲሉ በአምላካቸው ሃይል እንደሆነ በጦርነቱ ወቅት ሲያንጸባርቁ አድምጠናቸዋል፡፡ ንጉስሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም፣ ኃይልም በኃይሉ ብዛት አያመልጥም፡፡ ፈረስም ከንቱ ነው አያድንም፡፡ በኃይሉም ብዛት አያመልጥም፡፡ እግዚአብሔር ቤትን ካልሰራ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ፣ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል፡፡ የሚሉትን የመዝሙረ ዳዊት ጥቅሶች ጠ/ሚ ዛሬ ረስተው፣ ጠንካራ መከላከያ ገንብተናል ይሉናል፡፡

መቼም እሳቸውን ጨምሮ ተከታዮቻቸው በቅዱስ ልሳን በመንፈስ ቅዱስ ልሳን ተናጋሪዎች ነን ይላሉ፡፡ ምድራዊ ስልጣናቸውን ለማጽናት ግን በባቢሎን ግንብ ላይ ድብልቅልቁ የወጣውን ምደራዊ ቋንቋ የፖለቲካ ግዛት መፍጠሪያ አድርገው የጭንብስ ሲጓዙ ይስተዋላሉ፡፡

ላለፉት ሃምሳ አመታት ነገሰታቱ እንዴት ወደቁ ብለን ብንመረምር፣ እንደ የግዜያቸው መልሱ ግዜውን የሚመጥን መልስ ከማዘጋጀት ይልቅ እስከ ህልፈተ ሞታቸው ድረስ የሙጥኝ ዘይቤ በመከተላቸው ነው፡፡ ይህ ጠ/ሚ ኃ/ ማርያም ደሳለኝን አይመለከትም፡፡

የዛሬ ዘጠኝ አመት ገደማ፣ በብሔራዊ ቤተመዛግብት አዳራሽ የብርሃኑ ድንቄ "ቄሳርና አብዮት" መጽሐፍ ይገመገም ነበር፡፡ እኔ እዛ መርሃ ግብር ላይ አወያ ስሆን ዲፐሎማት ቢነጋ ተወልደ ደግሞ ለውይይቱ መነሻ ጽሑፍ አቅራቢ ነበር፡፡

ደራሲው አምባሳደር ብረሃኑ ድንቄ በመጽሐፋቸው ውስጥ አጼ ኃ/ ስላሴን ፈጣሪ በወሰነው በእጣ ፋንታ(Fatalist) አማኝነት ይገልጷቸዋል፡፡ ምክነያቱም እሳቸው ከሞቱ በኃላ ፈጣሪ ያመጣውን ያምጣ በሚል እምነት ነገሮች ተበላሽተዋል ወደሚል መደምደሚያ ያደርሰናልና፡፡

ቢነጋ ይህን ሃሳብ ይዞ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊም ያው ፋታሊስት ነበር ብሎ ደመደመ፡፡ የአጼውን ፋታሊስት አለመሆን ለመስረዳት አንዳንድ ነጥቦች ጠቅሼ ለመተንተን ሞከርኩ፡፡ በንጉሳዊ አገዛዝ ወንድ ልጅ ዙፋኑን ለማስቀጠል እጅግ በጣም ተመራጭ ነው፡፡

አጼ ኃ/ ስላሴ ደግሞ ልዑል መኮንንን በመኪና አደጋ፣ ሳህለስላሴን በጤና እክል ሞት አጥተዋል፡፡ አልጋ ወራሽም በስትሮክ ምክንያት ከወገብ በታች ሽባ ሆነው ነበር፡፡ ስልጣናቸውን ገና ላልደርሱ የልጅ ልጆቻቸው መስጠት አልቻሉም፡፡ ለሴት ልጆቻቸው ቢሰጡ ደግሞ ዙፋኑ ወደትግራይ፣ ወለጋ…ሊሄድ ሆነ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ደርጉ ቀደማቸው፡፡

የመለስ ዜናዊ ነገር ይለያል፣ ከመሞታቸው በፊት ድርጅታቸውን ቢያንስ ለአስር አመታት በብቸኝነት ገዝተዋል፡፡ አቶ ጌታቸው አሰፋ ሰውሩ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ እሰኪባል ድረስ በኢህአዲግ ውስጥ ጉልህ ሚና ያልነበረውን አቶ ኀ/ማርያም ደሳለኝን  ወደ ፊት እንዲመጣ ለምንድን እንደፈለጉ ግልጽ አይደለም፡፡ ታመው ሆስፒታል በሚመላለሱበት ግዜ ነው ደመቀ መኮንንን ወደ ውጭ ጉዳይ እንዲገባ የተናዘዙለት፡፡

አንድ የትግራይ ሽማግሌ እባካችሁ የራሳችንን ሰዎች እየተዋጋን ነው ሲሉ ብቅ አሉ፡፡ በግዜው የነበረው ወያኔ ፣ ወታደሩ በእኛ እጅ ነው፡፡ ምን የሚያሰጋን ነገር አለና…ብሎ ተንዘባዘበ፡፡ ሽማግሌው ግን እንዲህ አሉ "መለስ ቢኖር ኖሮ አንዳርጋቸው ጽጌን አጠልፉትም ነበር" ያሁሉ ሆን፡፡ ወያኔ ስንት ዘመን ከዚያን በኃላ በስልጣን ቆየ?

ጠ/ሚ አብይ አህመድ ተልመውት የተነሱበት የብልጽግና ቢጫ ፍኖት ተጠምዝዞ መጥቶ እግራቸው ስር ከወደቀ ውሎ አድሯል፡፡ አብረዋቸው የነበሩ ሁሉ ምስላቸው ቀስ በቀስ እየፈዘዘ ጠፍቷል፡፡  በእሳቸው ዘመን የባንዲራው መአከለኛ ቢጫ ክፍል ወደ ቀይነት ደምነት ተቀይሯል፡፡ የሚነዱት የፖለቲካው መኪናን መሪ የሚያሽከረክሩት ድጦሽ( Slippery slope) ውስጥ ገብተው ነው፡፡

ዘንድሮ ከአድዋ በዓል ጀምሮ ህጻናቱ ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ማውራት ጀምረዋል፡፡ ጌዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንዲት ልጅ በጭስ ታፍና የተናገረቸውን ሰምተናል " ሰመአቱ ይመጣል (ይፈርዳል)… እንዲህ እንዳለቀስን አንቀርም…" ሰሞኑን አንዲት ህጻን ደግሞ አማራና ትግሬ አለቀ እያለች ነው፡፡ ልጂቱ በዩቲዩብ እንደሰማኃት ትግሬ ለመሆኗ  ማረጋገጫ ባይኖረኝም፡፡

ሕጻን መውሱድ ደግሞ በዶነኪ ቲዩብ ላይ ለምን ቤት ይፈርሳል፣ይህ እርግማንን ያሰከትላል ከፍ ያለ ቦታንም ያሳጣል፡፡ ቤት አታፍርሱ ስሩ እንጂ…ብሎ ተናገረ፡፡ አክትቪሰት ነን የሚሉ የሰፈር ብሽሽቋሞችም ላመኑት የዩቲዩብ ጥቅማቸው ልጁ ላይ ቢዝነስ ከፍተውበታል፡፡

ልጁን በዶንኪ ቲዩብ እና በሌሎች ሶሸል ሚዲያዎች እንዳየሁት፣ ፈጣን መልሶችን መመለስ የሚችል፣ መተወንም የሚችል፣የአዋቂ ወሬ የገባው፣ ከይርጋ ጨፌ የመጣ አራዳ ነው፡፡ በዶንኪ ቲዩብ ላይ የጨፌ ልጆችን ከአዳማ(ናዝሬት) ልጆች ጋር አወዳድሮ በእራሱ ተርም ካሸነፈ በኃላ እኔም የአዳማ ልጅ ነኝ ብሎ አረፈ፡፡ በፈጣን ጭንቅላቱ በዳንስም ይሁን በዘፈን ያሰኬዳቸዋል፡፡

ሲፈልግ ደግሞ እሸቱ እራሱኑ ጸጥ ለማድረግ ሲፈልግ ዘፈን ፈጥሮ ህዝቡን ያስጭፍራል፣ ያንቀሳቅሳል፡፡ በሚገባ ሐይማኖቱን ውስጥ ያሉ ነገሮችን በስእላዊ መልክ እግሩን አንሻፎ ሰውነቱን በማጣመም፣ የመጨረሻዋ ቀን(ቂሚያ) ይተውናል፡፡ ኢትዮጵያዊው ዳንቴ እንበለው? በምኖርበት ሰሜን አሜሪካ እንዲ አይነት ልጆችን ኢንዲንጎ ችልድረን(Indigo children) ይሏቸዋል፡፡

ይህ ልጅ በጥሬነቱና በፍሬነቱ መካከል ሆኖ ነገ ወደ ፈለገው አቅጣጫ ቢናገር ተመክሮ ነው ማለት አንችልም፡፡ እንዲህ ያሉ ልጆች ላይ ቢሰራ ግን ኢትዮጵያ ከሃያ አምስት አመት በኃላ በአለም መድረክ የሚወክሏት ሰዎችን ታፈራለች፡፡ እንሂን ልጆች ወደ ፊት በማምጣቱ የዶንኪ ትዩቡ እሸቱ ይበል ሊባል ይገባዋል፡፡

እርግጥ ነው ኢትባህሉ እነደሚለው ትንሽ ጋኖች ትልልቅ ጆሮ አላቸው፡፡ እየተጫወቱም ቢሆን ትልልቅ ሰዎች የሚያወሩትን ያዳምጣሉ፡፡ የወላጆቻቸውን ፍርሃትም በሚገባቸው ያህል ይጋራሉ፡፡ እንዲሁም  የንጽህና አምላካቸው ሹክ የሚላቸውንም ይተነፍሳሉ፡፡ በቃ ሕጻን መውሱድን በዚሁ እንለፈው፡፡

አሁን ደግሞ አንድ ወዳጄ የጊንባ እረኛ ያን ሰሞን እንድሂ አለ ብሎ ያጫወተኝን ግጥም እንሆ ልበልና ነገሬን ልቋጭ፣

የቋንቋ እድፉን ሊያጋባ ለሰው

ከወዲያ ወዲህ ሲያተራምሰው፣

ፍም እሳት ለብሶ ድፎው ተጋግሯል

አንተም ተበልተህ አረህ ከስለሃል፡፡

 

 

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/181992

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...