Thursday, January 19, 2023

ከሁለቱም ወገን በጦርነቱ ሰበብ ለሞቱት ከ600 ሺ በላይ ዜጎች አካላቸው ለጎደለ ተጠያቂው ማነው? - ሴና ዘ ሙሴ
 የፐሮ መስፍንን ሃሰብ የጽሑፌ  መግብያ አድርጌለሁ ።

″ ያንጊዜም ሆነ ዛሬ ፣ በበኩሌ  የጎሣ መነፅር የለኝም ። ልሳሳት እችላለሁ ። አሥተያየቴ ለአንዳንድ ሰዎች አይጥምም ። ... ይሆናል ። ነገር ግን እግዚአብሔር ይመሥገን የጎሣ ምንም ነገር በውስጤ የለም ። ለእኔ በጎሣ ደረጃ ወርዶ ማሠብ ከሰውነት ደረጃ መውጣትና ወደአዘቅት መውረድ ነው ። እዚያ ተርታ በአካልም፣ በአስተሳሰብም በስሜትም አልገኝም ።

( " አዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ " ገፅ 27 ፤ የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም መፅሐፍ ) “ሦሥት  ነገሮች አሉ ። እነዚህም ፦ የሁላችንም ኢትዮጵያ ፤ በተለያዩ ዘመኖች በኢትዮጵያ ውሥጥ የነበረው ሥርዓት ፤ በተለያዩ ዘመናት ሥርዓቱን የሚያንቀሳቅሱት ሰዎች ናቸው ። የመክሸፉ ሰንኮፍ ያለው እነዚህ ሦሥት የተለያዩ ነገርች ለይቶ ማየት ያለመቻል ላይ ነው ። አንዳንደ ሰዎች ይኼንን ሁሉ ከነጉድለቱ ለመወረስ አይፈልጉም ። መፍትሄው ነፃነት ነው ብለው በቅዠት ይነቃሉ ። ቅዠት  የምለው ለማዋረድ አይደለም ። እውነቱን ለመግለፅ ነው ። ማስረጃ የሚፈልግ ለአንድ  ሠዓት ያህል ብቻ ኤርትራና ሱማሊያ ያሉበትን ሁኔታ  ያጥና ። በሁለቱም አገሮች ያለው ሁኔታ በሽታው ያው በሥርዓቱ ላይ መሆኑንን ለመገንዘብ አያዳግተውም ። ህዝብን ሁሉ በነፃነት ፣ በእኩልነት ፣ የሚያቅፍ ህጋዊ ሥርዓት ከሌለ መበታተኑ የማይቀር ይሆናል ። መበታተኑም ቢሆን አይቆምም ።

ግን ማነው ነፃ የሚያወጣው ? ከማንስ ነው ነፃ የሚወጣው ? የወያኔ ፕሮግራም ኢትዮጵያን አማራ አድርጎ ሌላው ሁሉ ከአማራ ነፃ እንዲወጣ ነው ። ተገነዘቡትም ፣ አልተገዘቡትም የኢትዮጵያ ታሪክ ሁሉ አማራ  ለሚሉት አስረክበው ባዶ እጃቸውን ነፃ ሊወጡ ነው !? ግን አሥቸጋሪ ነው ። ኢሣያስ አፈወርቂ የሆነለት በመንግስት ደረጃ የኢትዮጵያን የቀን አቆጣጠር በፈረንጆች መለወጥ ብቻ ነው ። ዛሬም ኢትዮጵያዊነት በኤርትራ ውስጥ ጎልቶና ደምቆ ይታያል ። ራሱ ኢሣያሥም ቢሆን ኢትዮጵያዊነቱን በውስጡ ቀብሮ ይዞል ። ይኽ እኔ ራሴ ያረጋገጥኩት ነው ።

ገፅ 34 እና 35  ፤ " አዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ " የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም መፅሐፍ )

 

አዳፍኔ እና መክሸፍ

ለአለፉት 50 ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ  የተጎዙበት መንገድ በአያሌ አበሳና ስቃይ እንዲሁም እጅግ በበዙ  እንቅፋቶች ፣ ወጥመዶች ፣ ጋሬጣዎች ፣ እሾኮች ፣ ጉድጎዶች ፣ አደናቃፊ ዲንጋዮች ፣ በአጠቃላይ በአዳፍኔ እና በመክሸፍ ለምን ተሟላ ?

በአዳፍኔ እና በመክሸፍ  የተሞላው በህዝብ ሥም ወደ ሥልጣን የሚመጡት ፣ በሥልጣን መገልገልን እንጂ ማገልገልን የማይፈልጉ ፣ እንደቀደሙት ጨቋኞች እነሱም በህዝብ ሥም ፤ በሤራ በተሞላ አገዛዝ ያውም  መርጠው በመጨቆን የአገዛዝ ዕድሜያቸውን ለማራዘም የሚጥሩ ሆነው በመገኘታቸው ነው ።

ዛሬና አሁን በኢትዮጵያ  የፖለቲካ  መንገድ ላይ በህዝብ ሥም ፣ ሥልጣን ይዘው ፣ ሠልፉን የሚመሩት ከመሳፍንት ዘመን ፖለቲካ ያልተላቀቁ ፣ ነፃ የህነውን ዜጋ ፣ “ በባርነት ውሥጥ ነህ ። “ ብለው የሚሰብኩ ።  በጠብመንጃ  ኃይል ፣ በተጭበረበረ ፍትህ ና እሥር እውነትን እሥካዳፈንክ  ... ህዝባዊ ተቃውሞን በማክሸፍ ፣  ሥልጣኔን አይደፈሬ እሥካደረክልኝ  ጊዜ ድረስ ድሎትና ምቾትህን አላጎድልብህም ። “ ባዮች ናቸው ። ይኽ ድለላ ግን እሥከመቼ “ ደምቆ ና አሸብርቆ “ እንደሚቀጥል እግዜር ነው የሚያውቀው ። “ ዘርፈህ ሀብታም ሁን “ የሚሉ ።  ከወረዳ ጀምሮ  በሞዳሞድ ሥልጣን የያዙ ፤ በአገሪቱ ነገሰው ፤ ነገ  ሥልጣናቸውን  ለልጆቻቸው አውርሰው  ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ በፍትህ እና በዴሞክራሲ እጦት እያሰቃዩ ይቀጥላሉ ወይሥ ? ፈጣሪ ከወዲሁ “ በቃችሁ ! “ ይላቸዋል ? ...

ዛሬ በኢትዮጵያ ፣ “ የተሥተካከለ ፣ ከህግ በታች የሆነ ፣ ለህግ የሚገዛ ፣ ህግን የሚያከብርና የሚያሥከብር  ፣ ህግ አሥፈፃሚ የለም ። “ ብሎ ለመናገር  የማያሥደፍሩ የህግ ጥሰቶች አጅግ በዝተው ፣ ህዝብን እያሥመረሩ  ነው ።

በጎበዝ አለቃ የምንመራ  እስኪመስል የህግ የበላይነት ተደምስሶ ፣ ግብዝ ባለሥልጣናት ና  የክልል መንግሥታትት በራሳቸው ዛሬና አሁን  “ ጃንሆይ ! “ሆነውብናል ።

ጃንሆይዎቹ ፣ ሥልጣንን ፣ ጥቅምን ፣ በአበልጅነት ፣ በሙዜነት ሣይቀር ያከፍላሉ ። አሽቃባጩን  ጨምሮ በሚገዙት ክልል ውስጥ   ፣ ዘመድ ፣ አዝማዱ  መሬት በየወረዳው እየተሰጠው በመቸብቸብ ሚሊዮነር ሆኗል ።

ዛር፣ዛሬ ፣ በዶ/ር  ጠቅላይ ሚኒሥቴር አብይ ሥልጣን ሥር ( ለምን ዶ/ር ትላለህ አትበሉ ። ዛሬ በአሣፋሪ መልኩ ዲፕሎማ ሊሰጠው የማይገባ አይደል እንዴ ማሥትሬትና ዶክተሬት ያለው ። በዕውቀት የማይታማን ሰው ማማትም ጡር ነው ። ይልቅየስ “ ሣክሥ በቃን “ ሠለቸን ። በማለታችሁ አደንቃችኋለሁ ። ) ኧረ ሥንት ጉድ ይታያል ? ሥንትና ሥንት ጉድሥ ይሰማል ? “…ታንታለሙ በጉጂ በኩል ወደኬንያ ተጋዘ ።ደሞ እኮ ፣ ሥለ ኬንያ ታንታለም ሻጪነት ይወራል   ጅሌ ! አትሞኝ ።   እከሌ እና እከሊት  የእንትና የቢዝነስ ሸሪክ ናቸው ። ያጋበሱት ሀብት ለአሥር ተውልድ የሚበቃ ሥለሆነ ፣ ሥልጣን በመልቀቃቸው ተደስተዋል ። ከህዝባዊ ቁጣና  መዓበል በፊት  በቦሌ በክብር መሸኘትን ማን ያገኘዋል ። “ ይሉሃል ።

ሌላው ይቀጥላል “እንትናም በአሜሪካ ኔቪ በኩል ፣ ከባይደን ጋር ተሻርኮ ወርቁን በበዙ ኩንታል ቋጥሮ ፣ የነገ መጦርያውን ብቻ ሳይሆን ዘር ማንዘሩን ለሺ ዓመት የሚደላቅቅበትን ጥሪት በአደራ አስቀምጧል  ።  ጤናዋም ጥሩ ሥላልሆነ ነገ ፣ ተነገወዲያ በቦሌ እብሥ ማለቱ አይቀርም ።  ያም ወሬኛ አጃቢው ሆኖ ለትምህርት ይባልና አብሮ መሄዱ ሳይታለም የተፈታ ነው ። “ ይልሃል ። “ እሽ  ሌላስ የለህም ?  ትርትሩ ! ጋ ሼ ቆርጦ ቀጥል ! “ ብትሉት በእናንተ ያለማመን እየሳቀ   ጥሏችሁ ይሄዳል ።

አንዳንዴ ፣ ″ ምነው ጆሮ ባልኖረኝ ! ″ ብላችሁ እሥከምትማረሩ ድረስ  ፤ ″ አይኔ ግንበር በሆነ ! ″ ብላችሁ ራሳችሁን እሥክትረግሙ ድረስ ፤ በአገረ ኢትዮጵያ ፣ ከከንቲባ ጀምሮ ያሉ ሹመቶች በትውልድ ቦታ ፣  በሥጋ ዘመድ ፣  ፣ በሠፈር ፣ በአበልጅ ፣ በሙዜ እና በልቶ የሚያበላ ፤ በሚል የዘረፋ ደቀመዝሙርነት እየተገመገመ ፤ በክልል በለሥልጣናት  ሲሰጥ ና   አጫፋሪው ሣይቀር ፣ በሦሥትና በአራት አመት ውስጥ ወደ ቢሊዮነርነት ሊሸጋገር አንድ ሃሙሥ ቀርቶት ሥታዩ ፤ “ እንዴ ! እንዴት እንዲህ ዘረፋው ከረረ ? የወያኔ   አዳፍኔ ፤  በምን ቅፅበት    ብልፅግናንን ወረሰው ! “ ማለታችሁ አይቀርም  ።

መገረማችሁን ወደ ሰላማዊ ትግል መቀየር እና  “  ለምንድነው የእኛ ፖለቲከኞች በዓለም አገራት ዜጎች ፈፅሞ በማይስተዋል መልኩ ሰው መሆናቸውን ዘንግተው ወይም ለሆዳቸው  በማድላት  ፣ እንደእንሥሣ ለማሰብ እና በቋንቋ ተቧድነው ፣  የኔ ቋንቋ ትልቅ ነው ፣ እኔ በቋንቋዬ ልዩ በመሆኔ ብቻ ከሌላው ሰው እለያለሁ እናም የላቀ መብት አለኝ    ። ″ በሚል ሣይንሣዊም ሆነ ኃይማኖታዊ እውነት እና በሰው ለሰው መስተጋብር ውሥጥ ፣ ዓለማቀፋዊ ቅቡልነት በሌለው ፣  የአየር ላይ ፣ በመዳከር ፤ በውሥጥም ሆነ በውጪ ጎራ ለይተው ፣ከዛሬው ሥልጡን ሰው  የአሥተሣሠብ ደረጃ ዝቅ በማለት ፣  ዛሬም አገሪቱን ና ህዝቧን ሠላም እየነሷት የሚገኙት  ?  በማለት ብጠይቁና “ ሀገር በጭለማ ውሥጥ በደመነፍስ እየተወራጩ ባሉ ፣ የሚሰሩትን በማያውቁ ፣ ለሆዳቸው በተደራጁ ቡድኖች እሥከመቼ የኋሊት ሩጫ ተሮጣለች ? “ በማለት ይኽንን ወደ ገደል የሚወስድ ሩጫ ለማሥቆም በየፈርጃቸው  ጥረት ብታደርጉ መልካም ይመሥለኛል ።

ሠላማዊ ትግል ዛሬ ና አሁን በእጅጉ ያሥፈልገናል ። ይኽ ትውልድ ገዢዎችን የሚሞግት እንደሆነ በተግባር ያሳያልም ብዬ ተሥፋ አድርጋለሁ ። ፈጣሪ  የፊታችንን  ቢያውቅልንም ዛሬ እየኖርነው ያለው ህይወት እጅግ አሳፋሪና  አስፈሪ ነው ።  እምነታችንን ከበሉ ፤ ልጆቻችንን ከበሉ ፤ ሀብትና ንብረታችንን ከበሉ ፤ ካወመኑ ጋር ያለ አንዳች ፍትህ የአገረ መንግሥቱ ዘዋሪዎች ፣ ባለሥልጣናቱ  ታርቀዋል ።

እርቁ የተደረገው በአውሮፖና በአሜሪካ መንግሥታት  ጫና  ነው ተብሎ ይገመታል ።  ለእነዚህ መንግሥታት ሥልጣን የሰጣቸው የአገራቸው ዜጋ ወይም ህዝብ ነው ። እናም  በየምክር ቤቶቻቸው “የፍትህ  ጥያቄ ለምን አልተመለሰም ፣ ሠለሰላም ሥናወራ ፣ ፍትህና ዴሞክራሲን ጨፍልቀን ከሆነ ታጥቦ ጭቃ ነው ። ነገሩ ና በግል ለራሳችሁ ጥቅም ካላሰባችሁ በሥተቀር ፣ ፍትህና ዴሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማንበር እውነተኛ ና ተጠያቂነትን ያካተተ እርቅ እንዲፈጠር ታደርጉ ነበር ። “ ብሎ መጠየቁ አይቀርም ። ህዘብም በምርጫ ወቅት በካርዱ ይቀጣቸዋል ።

የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ፣ የዛሬዎቹን ባለሥልጣናት  በምርጫ እንኳን ለመቅጣት ፣ የሚያሥችል ህገ መንግሥታዊ ነፃነት የለውም ። ለምን ቢሉ ፣ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠረው ዜጋ መራጭ እንጂ ተመራጭ የሚህንበት ፍትሃዊነትን ያነበረ የመወዳደሪያ ሜዳን ህገ መንግሥቱ ባለመፍጠሩ አንዱ በቋንቋ ሥም ገዢ ሌሎች ተገዢ ሆነዋልና ። ይኽ ብቻም አይደል  የአዳፍኔ ኔት ወርክ ከቀበሌ ጀምሮ መዘርጋቱ በየአምሥት ዓመት የሚመጣውን አገራቀፍ ምርጫ ተአማኒነቱን ይቀንሰዋል ።

ያም ሆነ ይህ በፍቅርና በህብረት መኖርን የምንወድድ  ዜጎች ፣ ምንም ሰብዓዊ መብታችን የምናስከብርበት መፈናፈኛ በህገ መንግስቱ ውስጥ አልተቀመጠልንም ። በዚህ በሸፍጥ በተሟላ ህገ መንግሥት እና በኔት ወርክ በመደራጀት ሁሉም ለዘረፋ በሚሯሯጥበት ሥርዓት ውሥጥ ፣ “ በዓለም አቀፍ ጫና ጦርነቱ ቆመ ። የሠላም ሥምምነት ተፈረመ ። “ ተብለናል ። ሠላም ለደሃው ዜጋ በመላ መምጣቱ እልል ያሰኛል ። የሚገርመው ግን “  ዜጎች እንዲጨፈጨፉ ትዕዛዝ የሰጡ ወንጀለኞች   ያለመጠየቃቸው ነው ።

ኢትዮጵያዊነታቸው  ጭምር የካዱ  ፤ የእናት አገርን ፣ ሀብቷን ብቻ በመውደድ በጎጣቸው እየማሉ ፣ ለዘረፋ ህዝብን አሰማርተው የሠላማዊ ዜጎችን ሀብትና ንብረት ካዘረፉ  ፤ ዜጎቻችንን በደቦ እንዲደፈሩ በማድረግ ፣ ካዋረዱ ፣  ( የኢትዮጵያን መከላከያ አባላትን  እና ዜጎችን  አካለ ጎዶሎ ካደረጉ  ... ተዘርዝሮ የማያልቅ ግፍ በዚህ ፣ በዘመነ ፣ 21 ኛው ክፍለ ዘመን ፣ በየዋሁ እና በኃይማኖተኛው ህዝብ ላይ ከፈፀሙ ...)  ሰው መሠል አራዊቶች ጋር ፣ ያለ አንዳች ፍትህ  ″ ለሠላም ሲባል ሁሉንም ነገር ይቅር ብለናል ። ″ ማለት ፤ ምን ማለት ነው ? የመንግሥት ባለሥልጣናት እግዜር ናቸው እንዴ ?

" ጁንታ እና የናት ጡት ነካሽ " ተብሎ ከተፈረጀው በንፁሃን ደም እጁ ከተጨማለቀ  ጋር ያለ " ኢትዮጵያ ህዝብ ይሁንታ ! " ታርቀናል  ። ብሎ መሞዳሞድን ከማየት ፣ በእውነቱ " በዚህ ፍትህ በተቀበረችበት ዘመን ምነው ባልተፈጠርኩ  ?! " የሚያሰኝ ነው ።

በነገሬ ላይ ልባዊ ዕርቅን የሚጠላ የለም ። ይቅር መባባል የሠላም መሠረት ነው ። ሆኖም ሳያውቁ በወያኔ መሪዎች አሥገዳጅነት ወይም እንጀራ በልተው ለመሠንበት ባላቸው ሰብዓዊ ጉጉት  ፣ የህውሀትን የጦርነት ትዕዛዝ የፈፀሙ ፣ ልዩ ኃይሎች ፣ ሚሊሻዎች ፣ የትግራይ ወጣቶችና ሽማግሌዎች ፣ በደሉ በግበር ቀደም ፣ ከደረሰበት የአፋር ና የትግራይ ህዝብ ጋር ፣ " መሪዎቻችን ለሥልጣናቸው ሲሉ  በሐሰት ትርክት ወደ ጦርነት አሥገብተውን ፣ ምንም ያልበደላችሁንን ወንድምና እህቶቻችንን ለሥቃይና ለሥደት በመዳረጋችን  ይቅር ለእግዛብሔር በሉን ። " ሊሉና ለሠላም ሲባል ይቅር ሊባባሉ ይችላሉ ።   ማንም ህሊና ያለው ፍጡር ይህ እውነት  አያቀረሸውም ። ...

ገዢው ፖርቲ  ብልፅግና ፣ " የእናት ጡት ነካሽ " እያለ ሲጠረው የነበረን አገር አፍራሽ ተላላኪ ቡድን ፤ ወንድምና ወንድምን አጋዳይ ሤጣን ቡድን  ፤ " እሥከ ሥሙ ይጥፋ ! እንደ አያ ጅቦ    ወያኔ  የተሰኘ ሥም ለመጪው ትውልድ ማሥፈራሪያ ይሁን ! ! "  ተብሎ በአደባባይ የተወገዘን ቡድን ግን ይቅር ማለት ህዝቡን ከማቀርሸትም አልፎ የጨጎራ ህመምተኛ አድርጓታል ። እርር ድብን ነው ፣ ያለው ። አብሶ ከመለስ ዜናው ጊዜ ጀምሮ በማሥመሠል በተካኑ ሰዎች ለሠላም ሲባል ያለ አንዳች ፣ ፍትህና ካሣ ፣ ከሁለቱም ወገን በጠፉ ዜጎች መቃብር ላይ ቆመን ሠላምን ፈጥረናል መባል እጅግ ያማል ።

ከመለስ ዜናዊ አምባገነናዊ አገዛዝ ጀምሮ ጭራቸውን በመቁላትና እንደመለሥ ካልተናገርን ሞትን እንገኛለን ከሚሉ ( ዛሬም ያ ማሥመሠላቸው በግልፅ ይታያል ። ) አስመሣዩ ጭራቸው ፣ ዛሬም ድረስ ረዝሞ የሚታይ ጉድች ፤  በቃላት ጭምር  ከአዋረዳቸው ጌታቸው ረዳ እና ከናቃቸው ደብረፅዮን ጋር ሲተቃቀፉ ማየት ፣ ለዚች ሰንደቅ ፣ ለዚች አገር ፣ ለዚች ምሥኪን እናት አገር ብለው የተሰው ጓዶቻቸውን ፣ ልጆቻቸውን ፣ ወገኖቻቸውን  ለማይረሱ ሁሉ የሞት ሞት ነው ።

ከዚህ ውርደት ከማይገልፀው ደባሪ  ኩነት አንፃር  አሁን ያለንበት ሁኔታ በታሪክ እጅግ የጠቆረ " አሥጠሊ እና አሣፋሪ "ተብሎ  ይመዘገባል ። ...

አንድ የታሪክ አደራ ያለበት ይትልቅ አገር መንግሥት  በግፈኞች  ለተሰቃዩት ፣ ለተዋረዱት ፣ ለቁሰሉት ፤ በሁለቱም ወገን በጦርነቱ ሰበብ  ለሞቱት ከ600 ሺ  በላይ ዜጎች ፤ ለቆሰሉትና  አካለ ሥንኩል ለሆኑት ከ 50  ሺ በላይ ዜጎች ፣ ( በግምት )  እንዴት ፍትህን ይነፍጋቸዋል ? ህዝብ ለአገር ሉአላዊነት ፣ ለነፃነቷና ለክብሯ እንጂ  ለግለሰቦች ብሎ እኮ ከንቱ መሰዋትነት አልከፈለም ። መንግሥት ይኽንን እውነት  እያወቀ ሌላ አጀንዳ በመፍጠርና በማደናገር  ከዘለቀም “ እንደ ሁለቱ አሥቂኝ ለማኞች ወግ “ ድርጊቱን በትዝብትና ያለአዋቂነት ነው ። በማለት  በመሳቅ  አናልፈውም ።

″ የሁለት ለማኞች ወግ ″ የጽሁፉ ማሰረጌ

በጊዮርጊስ  ቤተክርስቲያን በራፍ ላይ ሁለት የእኔ ብጤዎች ጎን ለጎን ሆነው ይለምናሉ ።   አንዱ ለማኝ  ጀማሪ ና የዋህ ለማኝ ነው ። ፊደል ያለቆጠረ ከመሆኑም በላይ ሥለ ኃይማኖት የጠለቀ ዕውቀት የለውም ። አጠገቡ ያለው ደግሞ የ30ውንም ቀን  ድርብና ነጠላ የመላእክት ና የሰማዕታትን ቀን ጠንቅቆ የሚያውቅ ነው ።

ዕለቱ ጊዮርጊስ እንደመሆኑ ይኼ የነቃው የእኔ ብጤ " ጋሼ ! አባባ ! ልጄ! ሥለ ፈረሰኛው ጊዮርጊስ ! ሥለ ፈረሰኛው ጊዮርጊስ ! ..." እያለ ሲለምን ይሰማል ጎኑ ያለው የዋህ ለማኝ ። ከእርሱ ለየት አድርጌ መለመን አለብኝ በማለት ፣ " ሰለ ፈረሰኛው ገብርኤል ! ሥለ ፈረሰኛው ገብርኤል ! ..." እያለ መለመን ሲጀምር ፣ አጠገቡ ያለው የነቃው ለማኝ " ገብርኤል ፈረስ የለውም ። " ይለዋል ። ይኽንን እንደ ሰማ አጠገቡ ያለው ለማኝ ደንግጦ " ወይ ! በምትኩት ! ነበረው እኮ ! ቸግሮት   ሸጠው እንዴ ?! " አለ ይባላል ።

መቼም መላዕክት  ሰው እንዳይደሉ ይታወቃል ። ተጠሪነታቸውም  ለኃያሉ እግዚአብሔር ነው ። መንግሥትሥ  ተጠሪነቱ  ለህዝብም  አይደል ?
https://amharic-zehabesha.com/archives/178949

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...