ዝሆኖች ሲጣሉ
የሚጓዳው ሣር ነው ...
ይኼ ሣር የሚሉት
የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ?
እንበል ...
ህዝብ ሣር ነው ?
ገዢዎችም ዝሆን ...
አሳር የሚያሳዩት
በማብዛት ሥቃዩን ።
...
የሰው ሣርነቱ
እውነት አይደለ እንዴ
ዝሆኖች ሲጣሉ
አልተጎዳም እንዴ ?
አለተሰዋም እንዴ ?
አልተሰቃየም እንዴ ?
........................ ?
ያ ሁሉ ተረስቶ
ዝሆኖች ሲታረቁ
ተባለ ፣ ተባለ
ኑ ሣሮች ሆይ ሣቁ ።
ዝሆኖች ሲጣሉ
የሚጓዳው ሣር ነው
ይኼ ሣር የሚሉት
የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ?
እንበል ...
ሣር ህዝብ ከሆነ
ካልታየ እንደሰው
የትኛው ሣር ይሆን
" በዕረቁ " የሚሥቀው ?
በዕርቁ የሚደሰተው ?
ልጁን ፣ አባቱን ፣ እናቱን ...
ዘመድ አዝማዱን ...
በዝሆኖቹ እርግጫ
በዝሆኖች ኩንቢ
ያጣው ዜጋ ነው ወይ ?
ታዞ _ የሚስቀው ?
...................
በግድ እንዲስቅ
ህዝብ ከታዘዘ
በራሱ ሚዲያ
ከተነዘነዘ ...
እላለሁ
ይሄ ብልፅግና
ከደረግም
ከኢህአዴግም
የባሰ ጨካኝ ነው ።
በሰው ቁሥል
ሥለት ሰዶ
አመመህ እንዴ
ብሎ ጠያቂ ነው ?
ትላንትና ደርጉ
በቀይ ሽብሩ
በነፃ እርምጃ
የጥይት አረሩ
በሟች በመባከኑ ...
ክፈሉኝ እንዳለው
የጥይቴን ዋጋ
" የዩቶጵያው ብልፅግና "
የኢትዮጵያን ህዝብ
በግድ ሣቅ ይለዋል ።
ህዝብ ፍትህ አጥቶ
በሐዘን ተውጦ
ሆዱን እያከከ
ባድማ ተቀምጦ
እንዴት ሣቅ ይባላል ?
የጦረነቱ ቋስቋሾች
እነሱ ይሳቁ ...
እነሱ ያስካኩ
ሞቱን መከራውን
ለፅድቅ ነበር እያሉ
አለዩልንታ እየሰበኩ ።
እነሱ ይሳቁ
ዝሆኖች ስለሆኑ
ያሥለቅሳሉ እንጂ
ቀንበር እየጫኑ ።
እነሱ ይሳቁ ...
በወከበው ተተግነው
የሁለቱንም ንብረት
ያለከልካይ አግዘው
የሚ-ን-ደ-ላ-ቀ-ቁ ።
እነሱ ይሳቁ ...
በሀብትና በክብረት
እጅጉን የላቁ ።
ይበሉም ...
እንግዲህ ምን ትሆኑ
ዝሆኖች ታረቁ
ያለሃጢያታቸው
ሣሮች ግን አለቁ ...
ደቀቁ ...
ዝሆኖች ሲጣሉ
የሚጓዳው ሣር ነው
ይኼ ሣር የሚሉት
የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ?
እንበላ ...
አያሳዝንም ወይ ?
የሰው ልጅ ሣር ሲሆን
በእግዜር አገር
ሰብዓዊነት አክትሞ
በመቃብሩ ላይ
ግብዝ ሲጨፍር ። ...
ሲላላስ " ቀይ አንዱ " ...
አብይ ዜና ሲሆን
ሠላም ለዓለም ሲል
ጌታ ደብረፅዮን
ለገሰ በመዶሻ
አፍ ሲያዘጋ ህዝብን !
እያየ የብረት ሽመሉ ...
ሲፈጀው አማራን ።
ህዝብ በዝምታ
በአያሌው ማለቁ ።
" የሺ ጥላ የተባለው
በቅጥፈት መድረቁ ..."
በጣም አሥገርሟን
አልን .....
" እንግዲህ ትደንስ
ቁንጫ በአገሬ
እባብም ተነቀሶ
ይዘንጥ _ በሰፈሬ ።
ይሁና ...
ጊዜ ያመጣውን
ጊዜ እስኪመልሰው
ጊዜ የሰጠው ቅል
ድንጋዩን ይግመሰው ።
በሠፈረው ቁና
ኋላ እስኪሰፈር
ጅብ ቁርበት ለብሶ
እቤት ገብቶ ይደር ።
ግና ጥያቄ አለን
እኛው ለራሳችን
አያስገርምም ወይ
አያሥደንቅም ወይ
ይኼ መክሸፋችን ? "
https://amharic-zehabesha.com/archives/178829
No comments:
Post a Comment