Saturday, December 17, 2022
በዲ/ን ተረፈ ወርቁ*
(ጸሐፊው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ በምዕራብ እና በደቡብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት በዋና ጸሐፊነት፤ በታሪክ ጥናትና ቅርስ ጥበቃ ምርምር ሥራ ያገለገሉ ናቸው፤)
- እንደመንደርደሪያ
በዚህ ሰሞን የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆነ ዮናስ አክሊሉ የተባለ ‘‘አገልጋይ’’፤ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለመንፈሳዊ አገልግሎት፣ ምእመኖቿን ለማጽናት፣ ለምክርና ለተግሣጽ የምትጠቀምባቸውን እንደ ተኣምረ-ማርያም እና ገድለ-ተክለሃይማኖት የመሳሰሉ አዋልድ መጻሕፍትን እያጣቀሰ- ‘‘…ይህ በቅዱስ ወንጌል ላይ የተደረገ ክህደት፣ ምንፍቅና ነው፡፡ ስለሆነም እንደ ተኣምረ ማርያም እና ገድለ ተክለሃይማኖት የመሳሰሉ መጻሕፍት ‘‘ወንጀለኞች’’ ናቸውና ሊወገዙ ይገባቸዋል!’’ የሚል መልእክትን አስተላልፏል፡፡
ዮናስ አክሊሉ ያለበትን የእምነት ተቋም አስተምህሮ ለተከታዮቹ ከማስተማር ባለፈ በምን ምክንያት ወደሌላ የእምነት ተቋም ተሻግሮ እንዲህ ዓይነቱን ፍጹም ድፍረት የተሞላበት ዘለፋና የውግዘት ቃል ለማስተላለፍ እንደፈለገ አልገባኝም፡፡ ይህን በጊዜው ግለሰቡ መልስ ይሰጥበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለኹ፡፡
በመሠረቱ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለአገልግሎት በምትጠቀምባቸው መጻሕፍት ዙሪያ አገልጋይ ዮናታንን ተከታዮቹ ላለባቸው ጥያቄና ላስተላለፉት የውግዘት ቃል እንደየደረጃው - ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ የቤተክርስቲያኒቱን አስተምህሮ /ዶግማዋንና ቀኖናዋን/ በተመለከተ ምላሽ የሚሰጥ ዝግጁ የኾነ ‘የሊቃውንት ጉባኤ’ ስላላት በእነርሱ በኩል ተገቢውን ምላሽ ያገኛል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አስገራሚው ነገር ዮናታን በውግዘትና በወንጀለኛነት ከጠቀሳቸው የኢትዮጵያ ቤ/ክን መጻሕፍትም ባሻገርም፤ ‘‘የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ የድኅነትና የጉስቁልና ምክንያት መሆኗን፤’’ ጭምር በአደባባይ ለማወጅ ደፍሯል፡፡ ለነገሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን የድኅነትና የጉስቁልና ተምሳሌት አድርጎ የመግለጽ ሁኔታ አዲስ ክሥተት አይደለም፡፡ ይህን እሳቤ ከጥቂት ዓመታት በፊትም ፓ/ር ቶሎሳ ጉዲና (ዶ/ር) የተባሉ የፕሮቴስታንት እምነት አገልጋይና መሪ የኾኑ ሰው፤
‘‘…የኢትዮጵያ ቤ/ክ ለምእመኖቿና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የድኅነትን፣ የጉስቁልናን እና የመከራ ቀምበር የጫነች ተቋም ናት…’’ በሚል በአደባባይ ተናግረው እንደነበር እናስታውሳለን፡፡
ይህ የፓስተር ቶሎሳ ንግግርም በወቅቱ በአባቶችና በምእመናን ዘንድ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር፡፡ በዛው ሰሞንም የአሜሪካ ሬዲዮ መምህር ዶ/ር ዘበነ ለማንና ፓስተር ቶሎሳ ጉዲናን ጋብዞ- ፓስተሩ ቤተክርስቲያኒቱን የወቀሱበት ሐሳብ ላይ በመመርኮዝ አከራክሮቸው እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ እንደገና ከዓመታት በኋላም ‘‘አገልጋይ’’ ዮናታን ተመሳሳይ የኾነ ክስንና ዘለፋን በአደባባይ አቅርቧል፡፡
በመሠረቱ ‘የብልጽግና ወንጌል/the Prosperity Gospel’ ሐሳብ አቀንቃኞች የኾኑ የፕሮቴስታንት አማኞች- ‘‘የኢትዮጵያ ቤ/ክን በሕዝቦቿ ላይ የጉስቁልና፣ የመከራ ቀምበርን የጫነች ተቋም ብቻ ሳይሆን የዕድገትና የብልጽግና እንቅፋት መሆኗን…፡፡’’ ጭምር በግልጽ መናገር ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡
ይህን የተሳሳተ እሳቤ ማረም ያስፈልጋልና በዚህ በዛሬው ጽሑፌ፤ ‘‘የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የነጻነትና የአንድነት፣ የሰላምና የልማት ትእምርት/Symbol እንጂ የድኅነት እና የጉስቅልና ምንጭ ወይም ምክንያት አለመኾኗን፤’’ ከታሪክ መዛግብት በማጣቀስ ጥቂት ነገር ለማለት እፈልጋለኹ፡፡
ስለሆነም በቅድሚያ፤ ‘‘የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤ/ክን የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ፣ የመላው ጥቁር ሕዝብና በአጠቃላይም የሰው ልጆች ሁሉ የነጻነትና የአንድነት ትእምርት/ሲምቦል መሆኗን’’ ከመግለጽ ለመጀመር እወዳለኹ፤
- የኢትዮጵያ ቤ/ክን እንደ ‘የነጻነት እና የአንድነት ትእምርትነት’
ታሪክ እንደሚመሰክረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሰማያዊው፣ መንፈሳዊና ሐዋርያዊ ተልዕኮዋ ባሻገር በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ኪነ-ጥበብ፣ ኪነ-ሕንፃ፣ ሥነ ጽሑፍ… ወዘተ ውስጥ ግዙፍና ደማቅ አሻራ ያላት ሃይማኖታዊ ተቋም ናት፡፡ በተለይም ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከአገራችን ነጻነት፣ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ክብር ጋር በተያያዘ ስሟ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስላት፣ ስለ ነፃነት፣ ፍትሕና የሰው ልጅ ክብር በቃልም በተግባርም ጭምር ያስተማረች ናት፡፡
ከዚህም የተነሣ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን በተለያዩ ጊዜያት የውጭ አገር ወራሪዎች ዒላማ ሆና መቆየቷን የሚመሰክሩ በርካታ የታሪክ ድርሳናት አሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋንኛ ምክንያቱ ቤተክርስቲያኒቱ ስለ አገር ክብር፣ ስለ እውነት፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ ነፃነትና አንድነት የምታስተምር ተቋም በመሆኗ ነው፡፡ እናም ይህች ጥንታዊትና ጠንካራ ሃይማኖታዊ ተቋም መምታት ለብዙዎቹ የኢትዮጵያንን የነፃነትና የአንድነት ዋልታ ከመሠረቱ ማፍረስ መስሎ ስለሚሰማቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሲያጠቋት ኖረዋል፡፡
ይሁንእንጂ የኢትዮጵያ ቤ/ን እነዚህን የውጪ ሀገራት ወረራና ጥቃት በማወግዝ ሕዝቡ በአገሩ፣ በነፃነቱ፣ በአንድነቱና በሃይማኖቱ ላይ የመጣውን ወራሪ ኃይል ሁሉ በአንድነት ሆኖ እንዲመክት፣ ከአምላኩ ዘንድ ለተቸረው ነጻነቱና ሰብአዊ ክብሩ ቀናኢ በመሆን ዘብ እንዲቆም ስታስተምር የኖረች መኾኗ በታሪክ ድርሳናት የተመዘገበ ሐቅ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነትና አንድነት የነበራት ልዩ ስፍራና የከፈለችው ዋጋ ከሀገራችን ምድር ተሻግሮም በመላው ጥቁር ሕዝብ ልብ ውስጥ የሰረጸ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክን በመላው ዓለም የነፃነት ተምሳሌት ሆነው ተደርገው እንዲሳሉ አድርጓል፡፡
ታሪክ እንደሚነግረን፤ እ.ኤ.አ በ1884 ዓ.ም. በተካሄደው የበርሊኑ ኮንፈረንስ አውሮፓውያን አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ በተቀራመቱበት ወቅት ኢትዮጵያውያን የረጅም ዘመን አኩሪ ነጻነታቸውን፣ ታሪካቸውንና ሥልጣኔያቸውን በመጠበቅና በማስከበር- በዐድዋ ላይ ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ የነፃነት ቀንዲል የለኮሰውን የኢጣሊያንን ወራሪ ኃይል ድል በማድረግ ለመላው አፍሪካና ጥቁር ሕዝብ ታላቅ ታሪክን በደማቸው ጽፈዋል፡፡ ይህን የታሪክ ሐቅ በተመለከተ አንዳንድ የውጪ የታሪክ መዛግብትን በጥቂቱ ለማየት እንሞክር እስቲ፤
ጋዜጠኛ ዳንኤል ሮፕስ የተባለ የፈረንሳይ ጋዜጠኛ እ.ኤ.አ. 1963 ዓ.ም ‹‹አክሌዥያ›› በሚባል ጋዜጣ፤ ‹‹ኢትዮጵያውያን ለሃይማኖታቸውና ለነፃነታቸው ቀናዒዎች ናቸው፤ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ታውቋታላችሁን?!›› በሚል ርዕስ ባሰፈረው ሐተታ፡-
‘‘…ኢትዮጵያን ወራሪዎች ምድርዋን በግፍ ለመያዝ ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረጉባት ሀገር መሆኗን ታሪክ ያወሳል፤ ነገር ግን ሃይማኖት የእንቅስቃሴዋ መሳሪያ ሆኖ በመገኘቱ ነጻነቷን አስከብራ ቆይታለች፡፡ በማዕከላዊው ክፍለ ዘመን ‹‹የካህን የዮሐንስ ግዛት›› በአረመኔው ዓለም ተከቦ የክርስቲያን ምሽግ ሆነዋል እየተባለ ስለ ኢትዮጵያ ይነገር የነበረው ሁሉ ፍጹም ልበ ወለድ ታሪክ አይደለም፡፡
ከሁለት ሺ ሜትር በላይ ከፍታ ያለውን ደጋማና ለምለም መሬት ቁልቁል የሚያዩት ቀይ፣ ጥቁርና ሰርጥነት ያላቸው የእሳተ ገሞራ ውጤት ባሕርይ ያላቸው ጠረጴዛ መሰል ተራራዎች የጊዜን ውሽንፍር እንዳሳለፉትና የባሕር ዓሳም ሳይበገርና ሳይላላ ማዕበሉን እንደሚያሳልፍ ክርስቲያኒቷ ኢትዮጵያም በታሪክ ውስጥ ጠንካራ ስፍራዋን ይዛ ቆይታለች…፡፡’’ በማለት ምስክርነቱን አስፍሯል፡፡
በሌላ በኩል አሜሪካዊው የማኅበረሰብ ሳይንስ ምሁር እና በኢትዮጵያ ዙሪያ ሰፊ ምርምር ያደረጉት ዶናልድ ሌቪን- በተለይ ደግሞ በብዙዎቻችን ኢትዮጵያውያን ዘንድ ‘‘Wax and Gold’’ በሚለው ድንቅ መጽሐፋቸው የሚታወቁት እኚህ ምሁር ኢትዮጵያውያን በዐድዋው ጦርነት ወቅት- የኢትዮጵያ ቤ/ክን ወንድ፣ ሴት፣ ቄስ፣ መነኩሴ ሳይባል ተባብረው ወራሪውን የኢጣሊያን ጦር ድል ያደረጉበትን ጦርነት በጸሎት ተጋድሎና በማስተባበር ያደረገችው ተሳትፎ በአፍሪካና በመላው ጥቁር ዓለም ልዩ ስፍራና ክብር ሊያሰጣት እንዳቻለ The Battle of Adowa as Historic Event በሚለው ጥናታዊ ጹሑፋቸው እንዲህ ገልጸውታል፤
For a number of colonized African countries, the Ethiopian victory at Adowa symbolized and signaled the possibility of the future emancipation. Hence the Black South African of the Ethiopian Church came to identify with the Christian kingdom in the Horn, a connection that leads South African leaders to write Menelik for help in caring for the Christian communities of Egypt and the Sudan.
በዚህ በዐድዋ ጦርነት በወራሪው የኢጣሊያ ጦር ላይ ኢትዮጵውያን የተጎናጸፉት ድል በአፍሪካ አሜሪካውያን፣ በካረቢያንና በጃሜይካ እንዲሁም በመላው አፍሪካ ትልቅ የሆነ ብሔራዊ ኩራትንና ጽናትን ፈጥሮ ነበር፡፡ በዚህም አፍሪካውያን፣ አፍሪካ አሜሪካውያንና መላው ጥቁር ሕዝብ ለነጻነት ትግላቸው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን የነጻነት ትግላቸው ዓርማቸውና ሰንደቃቸው አድርገው ተቀበሏት፡፡ በተለይ ለደቡብ አፍሪካውያን የፀረ-አፓርታይድና የፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል ቤተክርስቲያኒቱ በትልቁ ትነሳለች፡፡ ለአብነትም፤
አፍሪካዊው የነፃነት አርበኛ፣ የዓለም የሰላም ኖቤል አሸናፊ የሆኑት ኔልሰን ማንዴላ ስለ ዐድዋ ድል፣ በአፍሪካ አሜሪካውያንና በኋላም በአገራቸው በደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ፣ በጥንታዊቷና በነፃይቱ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስምና ጥላ ስር የተቀጣጠሉ የፀረ-ቅኝ ግዛትና የፀረ-አፓርታይድ የነፃነት እንቅስቃሴዎችን በማስመልከት ከእስር በተፈቱ ማግሥት በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ቤ/ን ተገኝተው ባደረጉት ንግግራቸው፤
Fundamental tenets of the Ethiopian Movement were self-worth, self-reliance and freedom. These tenets drew the advocates of Ethiopianism, like a magnet, to the growing political movement. …The Adwa victory provided practical expression to Ethiopianism: self-worth, dignity, unity, confidence, self-reliance, race pride, spirituality and freedom from colonialism.
(Nelson Mandela, Speech to the Free Ethiopian Church of South Africa፣ 1991)
በተጨማሪም ይህን የታሪክ ሐቅ አስመልክቶ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ2002 ዓ.ም. የክብር ዶክትሬት የተሰጣቸው የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የሆኑት ታቦ እምቤኪ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአፍሪካ በተለይም ደግሞ ለደቡብ አፍሪካውያን የነፃነት ትግል ትልቅ ኩራትና መነቃቃት የፈጠረች መሆኗን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ልደት አዳራሽ ባደረጉት ንግግራቸው እንዲህ ገልጸውት ነበር፤
‘’...The Ethiopian Church would the authentic African church serve as a repository of the aspirations of all Africans for freedom and respect for their cultures, their identity and their dignity. It was therefore not by accident that the independent African churches I have mentioned called themselves the Ethiopian Church…’’
የደቡብ አፍሪካው የቀድሞ ፕ/ት ታምቦ ኢምቤኪ- በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስለ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የነጻነት የተጋድሎ ታሪክና የኢትዮጵያ ቤ/ን ታላቅ አስተዋጽዖን በተመለከተ ያደረጉት ንግግራቸውን የአማርኛ ትርጉም በጥቂቱ ቀንጭቤ ላስነብባችኹ፡-
ዘመናዊው የአፍሪካ የነፃነት ንቅናቄ የመነጨው ወደ ፲፱ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ አካባቢ በደቡብ አፍሪካ ነበር፣ የዚህ ንቅናቄ የቀድሞ መስራቾች የሀገራችን የመጀመሪያዎቹ ዘመናዊ አፍሪካውያ ልሂቃን ናቸው፤ የተነሱትም ከአብያተ ክርስቲያናት ትምህርት ቤቶች ሲሆን፣ የመጀመሪያዎቹ አፍሪካውያን የቤተክርስቲያን አገልጋዮችም ነበሩ፡፡ እነዚህ ዘመናዊ የአፍሪካ ልሂቃን ከአውሮፓውያን ሚስዮኖች እራሳቸውን አላቀው በቤተክርስቲያናቱ ላይ ባለቤትነታቸውን ሲያውጁ፣ እንደመነሻ የተጠቀሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በመዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፷፰ ላይ ይገኛል፤ ይህም፡-
‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፡፡›› የሚለው ነው፡፡ እንደ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካ የአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት እሽቀድድም ሰለባ ሆና በኖረችበት ወቅት ኢትዮጵያ ነፃነቷን እንደያዘች መቀጠሏ መነሳሳትን ይሰጣቸው ነበር፤ እናም በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተተነበየው ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ስትዘረጋ ቤተክርስቲያናችን በአፍሪካዊ ስነ ምግባር ትሞላለች ብለው ያምኑ ነበር፡፡
ይህች እውነተኛ የአፍሪካ ቤተክርስቲን ደግሞ አፍሪካያን በሙሉ ነፃነታቸው፣ ባህላቸው፣ ልዑላዊነታቸው፣ ማንነታቸውና ሰብአዊነታቸው እንዲከበር ላላቸው ህልም እንደማከማቻ ቦታ ሆና ታገለግላለች ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ እውነታ እና ታሪካዊ ሐቅ ላይ ተመስርተው ነበር እነዚህ የጠቀስናቸው ቤተ ክርስቲያናት እራሳቸውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብለው የሰየሙት፡፡ በአህጉራችን ላይ የመጀመሪያው ዘመናዊ የብሔራዊ ንቅናቄ የሆነው የደቡብ አፍሪካው አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ (ANC) የተወለደውም ከነዚሁ ከሀገራችን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው…፡፡’’
(ይቀጥላል…)
ሰላም ለኢትዮጵያ!!
https://amharic-zehabesha.com/archives/178276
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment