ታህሳስ 9 ቀን 2015ዓም (18-12-2022)
ከስዊድን የኢትዮጵያ አንድነት ራዲዮ ስርጭት የስነጽሑፍ ክፍል የተወሰደ ያለንበትን ተጨባጭ ሁኔታ የሚገልጽ ማብራሪያ ነው።በድምጽ ስለተነበበም
www.ethiopatriots.com በሚለው ድረገጽ የዩቲዩብ ስርጭት ማዳመጥ ትችላላችሁ።
መልካም ንባብ!
ባሳለፍነው ወር ቅንብራችን በተለያዩ ዘመናትና ዓመታት ህዳር በተባለው ወር ውስጥ በአገራችን የተከሰቱትን ዋና ዋና መልካምና መጥፎ ክስተቶች ከሞላ ጎደል ያቀረብንበትና የተቸንበት ጊዜ ነበር።ያ ህዳር ወር የቀናት ገደቡን ጨርሶ አሁን ላለንበት ታህሳስ ወር አስረክቦን እንደሌሎቹ የህዳር ወራት ጥሎን ሄዷል።እያንዳንዱ ወር ወይም የዓመት ክፍል( ወቅት)የሚታወቅበት ገጸባህሪያት አሉት፣ዓመቱ ከወራት ክፍፍል ባለፈ በወቅቱ በክረምት፣በጸደይ፣በበጋ ወይም መኸር ይገለጻል።እያንዳንዱ ወርም የሚታወቅበት የግብር ስያሜ አለው። ታህሳስ የሚለው ከግእዝ የወጣ ቃል ትርጉሙ ምርመራ ማለት ነው።በአገራችን ገበሬው የተከለውን ወይም የዘራውን ሰብል( ቡቃያ) የሚመረምርበት(የሚፈትሽበት) ጊዜ በመሆኑ ለወሩ ስያሜ ሆኗል።ይህንን የፍተሻ ወርም የተለመደውን አገር እንዴት ሰነበተች የክስተቶች መፈተሻ አድርገነዋል።በዚሁ አምዳችን በዬሳምንቱ በተከታታይ የምናቀርበው ትችትና ትንታኔና ለአንድ ቀን የጆሮ ፍጆታ ብቻ እንዲሆን ሳይሆን ለአሁኑ ትውልድ ምክርን ለተተኪው ትውልድ ደግሞ በታሪክ መዝገብ ላይ ተቀምጦ በማስረጃነት እንዲማርበት ለማድረግ ነው።
ጥንቅራችንን በታህሳስ ወር ክስተቶች ስንጀምር በአገራችን ታሪክ ውስጥ ጎልቶ የሚታወቀውና አሻራው እስከዛሬ ድረስ ያልጠፋው የዛሬ 62 ዓመት ተሞክሮ በከሸፈው የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ(ወይም የታህሳስ ግርግር) በሚለው ነው። በእኛ ግንዛቤ የነበረውን ዘውዳዊ ሥርዓት ለመለወጥ የተካሄደ የፖለቲካ ግብግብ እንጂ ተራ ግርግር ብለን አንጠራውም። ይህ አባባልም መታረም አለበት እንላለን።አለበለዚያ የትም ሆነ መቼ የሚደረግ የፖለቲካ ትግል በሥልጣን ላይ ባሉ ቡድኖች ደረጃው ዝቅ እንዲልና ዋጋ ቢስ እንዲሆን የማድረጉ ሴራ የተለመደ ሆኖ ይቀራል።አሁንም የዚያ አይነቱ አባዜ በግልጽ ይታያል።መንግሥታት ሁሉ የሚነሳባቸውን የለውጥ ሃይል የሚፈርጁት አሸባሪና የሰላም ጸር በማለት ሲሆን አሁን በአገራችን ለፍትሕ፣ለእኩልነት፣ለአንድነት የሚደረገውንም ሕዝባዊ ትግል በራሳቸው መመዘኛ በተራ እረብሻና ግርግር ተራ አስቀምጠው መፈረጃቸውን እያዬነው ነው።እዚህ ላይ ግልጽ ለማድረግ የምንሻው በአገርና በሕዝብ ስም የሚከናወን ሁለት አይነት ትግል መኖሩን ነው።አንደኛው አሁን በአገራችን ሥልጣን ላይ ከተቀመጠው ቡድን ጀምሮ በልዩ ልዩ ስም የሚንቀሳቀሱ ተገንጣዮችና ጸረ ኢትዮጵያ ሃይሎች የሚያካሂዱት የሽብር እንቅስቃሴ በሕዝብ ስም ሲሆን ከዚያ የተለዬውና ብዙሃኑን የሚያካትተው ሁለተኛው አይነት ትግል ደግሞ ለአገር ልዑላዊነት፣ ለአንድነትና ለፍትህ የሚደረግ ሕዝባዊ ትግል ነው።ይህ የአገር ወዳዶች ትግል ከጥፋት ሃይሎቹ ሽብር የሚለይና ብሎም የሽብር እንቅስቃሴውን ለመግታት የሚደረግ ፍትሐዊ ትግል እንደሆነ ማወቅ ተገቢ ነው።
የሳምንቱን ጥንቅራችን የምንጀምረው በእሁድ ታህሳስ 2 ቀን 2015 ዓም ይሆናል።በዚሁ ቀን በአዲስ አበባ ውስጥ ለሳምንታት የቀጠለው የተማሪዎችና የመምህራን ተቃውሞ በስፋትም በመጠንም ጨምሮ ለማዬት ችለናል።የተቃውሞው መነሻ ተረኛው የኦነግ ኦሕዴድ ብልጽግና ሥርዓት የድፍረት ክብረወሰኑን አልፎ የኦነግ ተገንጣይ ቡድን ሰፍቶ በጫካ የሚያውለበልበውን ባንዲራና የሚያቀነቅነውን የጥላቻ እንጉርጉሮ በአዲስ አበባ ነዋሪ በተለይም በትምህርት ቤቶች ግቢ ውስጥ ተግባራዊ አደርጋለሁ ብሎ በማስገደዱ ነው።ይህ አገር አጥፊ ቡድን ቤተመንግሥቱን ከተቆጣጠረ ወዲህ ላለፉት አራት ዓመታት በከተማም በጫካም የንጹህ ዜጎችን በተለይም ለአገሩ አንድነትና ነጻነት፣ለዳርድንበሩ መከበርና ልዑላዊነት ዋጋ የሚከፍለውን የአማራውን ማህበረሰብ ከምድረገጽ ለማጥፋት የተረገዘ ጽንስ ሳይቀር
እዬገደለ የዘር ሃረጉን ለማጥፋት ከተነሳ ውሎ ያደረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን የልብ ልብ ተሰምቶት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዋና ከተማ በሆነችው በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚያደርገው የነጠቃ ሙከራ ድንቁርና የወለደው ዃላ ቀርነት ብቻም ሳይሆን፣ እብደት፣እብደት ብቻም ሳይሆን ጅልነት ፣ጅልነትም ብቻ ሳይሆን ጅብነት የፈጠረው መሆኑን የውጭ አገር ዜጎችም እያዩና እዬታዘቡት ነው። ታዲያ ለዚህ ድፍረት መምህራኑ፣ወላጆችና ተማሪው እጅ አልሰጡም። በዬትምህርት ቤቱ ይህንን ዓላማ የሚያስፈጽሙ በመምህራን ስም ቀደም ብሎ በሥርዓቱ የተመደቡት የኦሮሙማ ተላላኪዎች ከፖሊስ ጋር ተባብረው በተቃዋሚው ላይ ጉዳት ቢያደርሱም ትግሉን ሊያስቆሙት አልቻሉም። የሴራው ጠንሳሽ የሆነው አስተዳደር ውይይት በሚል ማታለያ በአምሃ ደስታ ት/ቤት ውስጥ በተሰበሰቡት ወላጆች፣ተማሪዎችና መምህራን ላይ የፖሊስ ሃይል መድቦ እንዳይወጡ በሩን ቆልፎ በዱላ ከተቀጠቀጡት መሃል ብዙዎች ቆስለው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል፤ብዙዎችም ታፍሰው ወደ አልታወቀ እሥር ቤት ተወስደዋል።ይህንን ተከትሎ በሽሮ ሜዳ፣በመርካቶ፣በጉለሌ፣በንፋስ ስልክ፣ በአዬር ጤና ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተመሳሳይ ተቃውሞ ተቀጣጥሏል። በብዛት የመንግሥት ደጋፊ ይኖርበታል ብለው በሚመኩበትም የለሚኮራ ክፍለከተማ ያሉ ትምህርት ቤቶች የተቃውሞው አካል ሆነዋል።ከፖለቲካ ድርጅቶችና ከሲቪክ ተቋማትም በኩል የተቃውሞ ድምጾች እዬተሰሙ መጥተዋል። የሥርዓቱ አካል ከሆኑትም ድርጅቶችና ግለሰቦች በኩልም እንዲሁ ለእውነት ከመቆም ይሁን እራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማዳን ሲሉ ዳር ዳር እያሉና የተቃውሞ መግለጫ ከማውጣት ላይ ደርሰዋል።ከነዚህ መካከል ኢዜማ የተባለው የሥርዓቱ አጃቢ ድርጅት መሆኑ አስገራሚ ሆኗል።ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርገው በትምህርት ፖሊሲና በትምህርት ቤቶች ጉዳይ ላይ ተጠያቂ የሆነው የትምህርት ሚኒስቴርነቱን ቦታ የያዘው የዚሁ ድርጅት መሪ ብርሃኑ ነጋ መሆኑ ነው። ይህ የፖለቲካ ነጋዴ ማድረግ የነበረበትን ሥራ ሳይሠራ በመቅረቱ አሁን ለደረሰው ቀውስ ተጠያቂ ነው እንላለን።
በአገራችን የለውጥ ትግል ውስጥ የተማሪው ሚና የሚናቅ አይደለም። እንዳለፉት ትግሎች ሳይጠለፍና ሳይጨነግፍ ፣ለውጤት እንዲበቃ በበሰለ አመራር መመራትና ከሌሎቹ ንቅናቄዎች ጋር በአንድ የትብብር አካል መተሳሰር ይኖርበታል።ይህ ጅማሮ አገራችን ለምትሻው እውነተኛ ስር ነቀል ለውጥ መንደርደሪያ ይሆናል የሚል ግምት አለን።ባለፉት ስርጭቶቻችን ደጋግመንን ብሔራዊ የትብብር መድረክ(National Solidarity Forum)ይፈጠር ያልነው ይህንን የተበታተነ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ እንዲያስተባብርና እንዲመራ ነው።አሁንም ጥሪያችንን እንደግማለን።ይህንን የተጀመረውን የመምህራንና የተማሪዎች ትግል በሞራልም፣በሃሳብም፣በሚያስፈልገው ሁሉ መደገፍ የሁሉም አገር ወዳድ ግዴታ ነው።እኛም በርቱ ከጎናችሁ ነን፤ ትግላችሁ ትግላችን ነው እንላለን።
የጎሰኞቹን ድፍረት የኮነነው ሌላው እምባ ጠባቂ የተባለው የመንግሥት ተቋም ነው።ባለፉት ዓመታት እምባ ብቻ ሳይሆን ደም ጭምር ሲፈስ ድምጹን ያላሰማው ተቋም አሁን በመረረ ቃላትና ሕጋዊ ድጋፍ ባለው ማስረጃ የኦነግን ባንዲራና መዝሙር በአዲስ አበባ ከተማና ነዋሪው ላይ መጫን ሕገወጥ ነው በማለት ኮንኗል።
በዚሁ አገር በምትታመስበት በታህሳስ 2 ቀን የቀውሱ ቁንጮ የሆነው አብይ አህመድ ሚስቱን አስከትሎ ወደ አሜሪካ ተጉዟል።ይህ አራት ቀናት የሚፈጅ ስብሰባ በአሜሪካ መንግሥት አዘጋጅነት ለትብብርና ግንኙነት በሚል ሰበብ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር ለመነጋገር የታቀደ ሲሆን፣ ለሁለተኛ ጊዜ መደረጉ ነው።የመጀመሪያው ስብሰባ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት በባራክ ኦባማ ከሰባት ዓመት በፊት በ2015 የተደረገ ነበር።የስብሰባው ጭብጥ በፖለቲካ ተንታኞች ሲብጠለጠልና ሲተች ፣እኛም ስብሰባውን ስንፈትሸው እውነቱ አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር ለሚኖራት የመልካም ግንኙነት የሚረዳ ሳይሆን የባሪያና የጌታ ግንኙነትን ለማጽናት የሚደረግ ኮንትራት ማደሻ ለመሆኑ ከማያጠራጥር ድምዳሜ ላይ ደርሰናል።
የአፍሪካ ሕዝብ በምዕራባውያን በተለይም በአሜሪካን ላይ ያለው አመለካከት እዬተቀዬረ በመምጣቱ፣ የተቃውሞውና የጥላቻው መጠን በመጨመሩ፣የቻይናዎችና የሩስያ በአህጉሩ እዬተጠናከሩና ተቀባይነት እያገኙ በመምጣታቸው ከፈጠረው ስጋት የመነጨ ለመሆኑ ማስረጃ መጎተት አያስፈልግም።የአፍሪካ አገራት በአምባገነኖች መዳፍ ሥር ሲጨቆኑ የኖሩት በምዕራባውያን በተለይም በአሜሪካኖች ትብብር መሆኑ አይካድም።አገር ወዳድ መሪዎች የተገደሉት፣በኩዴታ አምባገነኖች ሥልጣኑን የሚይዙት በምዕራባውያኑ ድጋፍና ምክር ለመሆኑ ታሪክ ይመሰክራል። ከሕዝቡ ይልቅ የተፈጥሮ ሃብትና ማዕድን የሚያሳስባቸው እነዚሁ አገራት የቻይናንና የሩስያን መቀራረብ በፍጹም አይፈልጉም።የለመዱት የብዝበዛና የተጽእኖ ሃይላቸውን የሚያሳጣቸው በመሆኑ በቻሉት መንገድ ለመከላከል ይሞክራሉ። ከሙከራቸውም አንዱ እንዲህ አይነት ስብሰባ በማዘጋጀት ነው።
በዚህ ስብሰባ ላይ ከሃምሳ ያላነሱ በአሻጥርና በሸፍጥ ሥልጣን ላይ የተቀመጡ የአፍሪካ መሪዎች ተገኝተዋል።አብይ አህመድም አንዱ ነው። እንዳይገኙም የታገዱ የአፍሪካ አገሮችና መሪዎች አሉ፤ ከነዚያም ኤርትራ አንዷ ነች።ከዚህ ስብሰባ በፊት አሜሪካ ለአፍሪካ ልማትና የንግድ ዘርፍ ማስፋፊያ ከ55 ቢሊዮን ዶላር በላይ መመደብዋ ታውቋል።ይህ ገንዘብ ለአፍሪካ ቢባልም ለሕዝቡ ቤሳ ቢስትኒ አይደርሰውም።በመሪዎቹ በውጭ አገር በተከፈተ የግል ባንክ ቁጥርና የአሜሪካኖቹ ፋብሪካዎች በሚያመርቱት የጦር መሣሪያና በሌላ ቁሳቁስ ግዢ፣በእርዳታ ድርጅቶች ካዝና፣በደላሎችና በሎቢስቶች ክፍያ ተመልሶ ከአሜሪካኖቹ ካዝና ውስጥ የሚገባ ነው።አሜሪካኖቹ በሚያሽከረክሩትና በሚቆጣጠሩት የዓለም ባንክና አይ ኤም ኤፍ(World Bank and IMF)በኩል የሚሰጡትም ብድርና “እርዳታ” ከታሰበው ቦታ ሳይደርስ ወይም ደርሶ የሚወጣ መሆኑን አይክዱትም።ባለፉት ዓመታት በአገራችን ገባ ከተባለው 37 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ እንደወጣ በሙያው በሰለጠኑ ኢትዮጵያውያን የቀረበው ማስረጃ ያረጋግጣል።ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ የተረፈው ላገር ጥቅም ላልዋለ ገንዘብ ዕዳ ከፋይ መሆኑ ብቻ ነው። አሁንም ለአፍሪካ አገሮች ይሰጣል የተባለው 55 ቢሊዮን ዶላር ካለፈው የተለዬ መዳረሻ ይኖረዋል ብለን አንጠብቅም።አሜሪካኖቹም ሆኑ ሌሎቹ የምዕራብ አገሮች የአፍሪካን መሪዎች የሚያንበረክኩበት ሁለት መንገድ አላቸው።እነሱ ካሮትና ዱላ(Carrot and Stick)ይሉታል።በገንዘብ መደለል ወይም በሃይል ማንበርከክ መሆኑ ነው።ሁሉም ያፍሪካ በተለይም የኢትዮጵያ ሕዝብ ማወቅ ያለበት በነዚህ መሪዎችና በሚካሄደው ስብሰባ የሚፈልገው ሰላምና እድገት ሊመጣለት እንደማይችል ነው።የስብሰባው መደምደሚያ የባርነትና የጌታነት ቃል ኪዳን በፊርማ የሚረጋገጥበት ይሆናል።ስለሆነም የአፍሪካ ሕዝብ ለነጻነቱና ለክብሩ ብሎም ለእድገቱ ከራሱ በላይ ወሳኝ ስለሌለው ችግሩን ተባብሮ ፣በራሱ ሊወጣው ይገባል።እራሱንና አገሩን ካከበረ ሌሎቹ ያከብሩታል።እራሱን ካዋረደ ደግሞ መቀለጃ ሆኖ ይኖራል።
ባርነትን አንቀበልም ብለው የህይወት ዋጋ የከፈሉ ያፍሪካ መሪዎች ጥቂት አይደሉም።ቆመውም እስከመጨረሻው እምቢ ያሉ አልጠፉም።ከነዚያ ውስጥ አንዱ አሁን በሕይወት የሌለው የዝምባብዌ መሪ የነበረው ሮበርት ሙጋቤ ነው። እሮበርት ሙጋቤ በተለያዩ ጊዜያቶች የምዕራባውያኑን ሴራ ሲያጋልጥ ኖሯል።ከነዚያም ውስጥ ይድረስ ለነጮች በሚለው ደብዳቤው የሚከተለውን ብሏል።
የተከበራችሁ ነጮች፣- ለአገራችን አዬር ተስማሚ የሆነውን የባሕል ልብሳችንን አውልቀን የናንተን የሚሞቅ ባለሶስት ተደራቢ(Three pieces)ውድ የሱፍ ልብስ እንድንለብስና በሙቀት እንድንሰቃይ አደረጋችሁ፤በዚያም አልቆመም ገመድ አንገቷ ላይ እንደሚታሰርባት ፍዬል ቀጭን የጨርቅ እራፊ ከረባት ብላችሁ አንገታችን ላይ እሰሩ አላችሁን ፤ያንንም አደረግን።ያገራችን ሴቶች ተፈጥሮ ያደላቸውን ጠንካራ ፀጉር በብዙ ገንዘብ በምትሸጡት በሙታን ጸጉር እንዲሸፍኑና ለዓይናችሁ ማራኪ እንዲሆኑ አደረጋችሁ፣ከዚያም በተረፈ ብዙ ሴቶች ባሉበት አገራችን ወንዱ ብዙ ሴት አግብቶ እንዳንራባ አንድ ወንድ ለአንድ ሴት ብላችሁ ደነገጋችሁብን።በዚህም አልቆመም ግንኙነት ስናደርግ ልጅ እንዳንወልድ ላስቲክ (ኮንዶም)ተጠቀሙ አላችሁን፤ያንንም እሺ ብለን ተቀበልን።በመጨረሻው ላይ ቁጥራችን እዬጨመረ ሲመጣና አንጠፋም ስንል ሴት ከሴት ፣ወንድ ከወንድ ጋር ይጋባ ብላችሁን አረፋችሁ። ውድ ነጭ ሆይ ይህ የሶዶምና ጎሞራ ተግባር በፈጣሪ የተከለከለ በመሆኑ ከሚደርስብን መለኮታዊ ቅጣት ለመዳንና ዘራችንንም ለማስቀጠል ስንል እምቢ ብለንሃል!
እንዲህ በመሰለው እምቢባይነት የተነሳ አገሩ ብዙ ዋጋ ከፍላለች፤ሙጋቤም ካለስሙ ስም ወጥቶለት በሕዝቡ እንዲጠላ ቢሞከርም ግን አይበገሬው ሙጋቤ በዕድሜው ጫና የተነሳ ሥልጣኑን አስረክቦ ጥቂት ዓመታት ከኖረ በዃላ አርፎ በክብር ሊቀበር ችሏል።የሱ አፍሪካዊ መንፈስ በሌሎቹ ላይ ይስፈን ፣የሮበርት ሙጋቤን ነፍስ ይማር! አፍሪካ ብዙ ሙጋቤዎች ይወለዱባት! እንላለን። ሌላው የአፍሪካ መሪ የኡጋንዳው ሞሳቬኒም አውሮፓውያን በገንዘብ ደልለው የግብረሰዶምን ብክለት በሕገመንግሥቱ ውስጥ እንዲያካትት ቢጠይቁት አሻፈረኝ ብሎ ከነገንዘባቸው ወደመጡበት መመለሱን ባለፈው ጥንቅራችን ገልጸነዋል።
በእኛም በኩል የምናነሳው ጥያቄ ብዙ አፍሪካውያንን የፈጀውና በመፍጀትም ላይ ያለው ኤድስና ኤቦላ ቫይረስ ምንጩ ከዬት ይሆን? የሚል ነው። ነጮቹ የአፍሪካ ዝንጀሮ ያመጣው ነው ይላሉ።ፈጣሪ ለአንድ ቀን የጅንጀሮን ልሳን ሰው በሚናገረው ቋንቋ እንዲናገር ቢያደርገው ጅንጀሮ እራሱን ይዞ ኡኡ በኔ አታመሃኙ የናንተው ፈጥራችሁ መሞከሪያ አደረጋችሁኝ እንጂ እኔ በሽታውን አላመጣሁትም ብሎ ባጋለጣቸው ነበር።ብዙ ሰዎችም ለጦርነት የተቀመመ የባዮሎጂካል መሣሪያ ነው ይላሉ። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ብዙ ሚሊዮን ሕዝብ በኩፍኝና ፈንጣጣ ተላላፊ በሽታ በመሞቱ አሁንም ኤድስና ኤቦላ ለውጊያው እንደ አንድ የጦር መሣሪያ በላብራቶሪ ተባዝቶ የተሰራጨ ነው የሚሉ አልጠፉም። ሌሎቹም የዓለም ሕዝብ ቁጥር እያደገ በመምጣቱ ያንን ለመገደብ ነው የሚል ሃሳብ ይሰነዝራሉ።ያለንባት ዓለም ለሁሉም በቂ ናት።የተወለደ ሁሉ ዘላለም አይኖርም፣በሞትና በልደት እዬተቀባበለ ይኖርባታል።ችግሩ የሕዝቡ ብዛት ሳይሆን ሊኖር የሚገባው የዜጎች የሐብት ክፍፍል መዛባቱ ነው።ጥቂቶች ሥልጣንን ተገን አድርገው ዘርፈውና ሰርቀው መጠን የለሽ ሃብት በማግበስበስና መረን የለቀቀ የቅንጦት ኑሮ እዬኖሩ ብዙሃኑ በጭርንቁስና በአሰቃቂ ድህነት ውስጥ መኖሩ ነው።ይህ የመኖርና ያለመኖር፣ኢፍትሃዊነት ጥያቄ ነው የትግሉ ሁሉ መነሻ!
በባርነት ሰልፍ ውስጥ ገብተው አሜሪካኖቹ ከመደቡት የመደለያ ገንዘብ የአንበሳውን ድርሻ ለመውሰድ ከሚሽቀዳደሙት መካከል ኬንያ፣ጋናና ዛምቢያ ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።የአፍሪካ ህብረት ባለሥልጣኖችም ለሚያገኙት ጥቅም የድለላ ሥራውን ተያይዘውታል። የኛዎቹም ያንን ዕድል ለማግኘት የማይፈነቅሉት ድንጋይ፣ለሽያጭ የማያቀርቡት ያገር ተቋም እንደማይኖር ያለፈው ተግባራቸው ምስክር ነው። ያለነገሩ አይደለም በባይደን ሳሎንና በውጭ ጉዳዩና በደህንነት አላፊው ቢሮ ውስጥ አቀባበል የተደረገለት። ገና ከጅምሩ ከመጋረጃው (ከስብሰባ አዳራሽ) ጀርባ አብይ አህመድ የባርነት ውሉን በመፈራረም ላይ እንደሆነ ታውቋል።ሥልጣኑን ካስከበሩለት የጠዬቁትን ለማድረግ የመሃላ ቃሉን ከመስጠት ወደዃላ አይልም። ሙጋቤና ሙሳቬኒ የተጠዬፉት የግብረሰዶም ወረራና መስፋፋት በወያኔ ጊዜ ተጀምሮ አሁን በአብይ አህመድ በሚመራው የኦነግ ኦሕዴድ ብልጽግና አገዛዝ ተስፋፍቶ ይገኛል።በታላላቅ ሆቴሎችና መዝናኛ ቦታዎች ግብረሰዶማውያን ይርመሰመሱበታል።የቦሌ ጎዳና ይመስክር!ይህ የሰው ዘርን የሚያጠፋ ልማድ እንደ ሰብአዊ መብት ተቆጥሮ ለአገሮች ግንኙነት አንዱ ወሳኝና አስገዳጅ ነጥብ ሆኗል።የኦነግን ባንዲራ እምቢ ስንል ሌላ የባለብዙ ቀለማት የግብረሰዶማውያን ባንዲራ ስቀሉ እንዳንባል እንሰጋለን።በተለይም በአውሮፓዊያኑ በኩል ለዚህ በካይ ምግባር ትልቅ ቦታ የተሰጠው ሲሆን ለአፍሪካና ለሌሎቹ አገሮች ግንኙነታቸው ወሳኝ ቅድመ-ሁኔታ አድርገውታል። ለአሜሪካኖቹም ሆነ ለለአውሮፓ መግሥታት በኢትዮጵያና በሌላው አፍሪካ አገሮች ላይ ካላቸው አቋም ዋናዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።
1 በአፍሪካ ውስጥ እያደገ የመጣው የምዕራባውያን ጥላቻና የቻይናና የሩስያ ተቀባይነትን መቀልበስ
2 በመዳፋቸው ውስጥ አንገባም ብለው ያስቸገሩ ቢኖሩ በሃይል ማንበርከክ።ከነዚያም ውስጥ አንዷ ኤርትራ ስለሆነች ኢሳያስ አፈወርቂን ማሶገድና ለነሱ ተገዥና አገልጋይ በሆነ ባርያ መንግሥት መቀዬር
3 የግብረሰዶም ጸረ ትውልድ ግንኙነት እንዲስፋፋ ጫና በማድረግ፣በርሃብ፣በበሽታና በጎሳ የእርስ በርስ ጦርነት የአፍሪካውያንን ቁጥር ማመናመን
እነዚህን ለማስፈጸም ይረዳሉ ካሏቸው መሪዎች መካከል አንዱና ዋናው በራሳቸው ተመልምሎና ሰልጥኖ ሥልጣን ላይ የተቀመጠው አብይ አህመድ ነው።
በዚህ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያን ወክላ ትገኛለች የተባለችው ፕሬዚዴንቷ ሳህለወርቅ ዘውዴ እንደነበረች ተባራሪ ወሬ ነፍሶ ነበር።እኛ ግን ካለን ግንዛቤ ጉንጉን አበባ ከማስቀመጥና የሥርዓቱ ካባ ለባሽ ከመሆን በተረፈ በአገሪቱ የፖለቲካ ውሳኔ ላይ ምንም ሚና የሌላት ሴት በዚህ አይነቱ ስብሰባ ላይ ትገኛለች ብለን አላሰብንም።የሆነውም ይኸው ነው።አብይ አህመድ እንደዚህ አይነቱን ዓለም አቀፍ ትኩረት የሚስብ መድረክ ቀርቶ የሰፈር ሰው ሊያተኩርበት የሚችለውን ድርጊት ለሌላው አሳልፎ የመስጠት ፍላጎት የለውም።ባይጠራም እንዲጠራ ብዙ ያደርጋል።ሙከራውም በመሳካቱ ነው ለመሄድ የቻለው። ሆኖም ግን ከአራት ዓመት በፊት ዋሽንግተን ሲደርስ በብዙ ሽህ ኢትዮጵያውያን ጭፈራና እልልታ አቀባበል በተደረገለት የዋሽንግተን አዬር ጣቢያ አሁን ላይ እንደሌባ በድብብቆሽና በፊት ከልል አለባበስ አቀርቅሮ ሹልክ ብሎ በጓዳ በር መውጣቱ ምን ያህል ብርክ እንደለቀቀበት ያረጋግጣል።አብይ አህመድ የዘነጋው ቢኖር ከዓይን ለመሰወር ቢችልም ከሰራው ወንጀልና ከፍትሕ ሊያመልጥና ሊሸሸግ እንደማችል ነው።የንጹሃን ደም በዬሄደበት ያሳድደዋል።አብይ አህመድ ኢሳያስ አፈወርቂን ማጋለጥ ብቻ ሳይሆን ውጋ ካሉት ከመውጋት እንደማይመለስ የሚነፍሰው ንፋስ ያመላክታል።ለአብይ አህመድ ሥልጣንና ገንዘብ ከሁሉም በላይ ናቸው።ከማድረግ አይመለስም።አውሮፓውያንም ለወያኔ ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩት ለዚሁ ዓላማ ነው።ሁለት ባላ ትከል አንዱ ቢሰበር በሌላው ተንጠልጠል የሚለውን ምክር ይከተላሉ።ለትግራይ ደሃ ሕዝብ አስበውና ተጨንቀው ሳይሆን ታማኝ ውሻና የጥቅም አጋር የትኛው ነው ከሚለው መስፈርት በመነሳት ነው።ሰብአዊነትማ ቢኖራቸው ኖሮ በዬቀኑ በአብይ አህመድ መንግስትና ጎሰኛ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚጨፈጨፈው አማራ ባሳሰባቸው ነበር።የእነሱ ሰብአዊነት ከኪሳቸው መሙላት አለመሙላት ጋር የሚያያዝ ነው። አማራው ለሚፈልጉት የእጅ አዙር አገዛዝ የሚመች ስላልሆነና ለአገሩ ልዑላዊነት፣ነጻነትና አንድነት ስለሚቆም ያንንም በታሪኩ ስላዩት ዋናው ጠላታቸው አድርገው ይቆጥሩታል።ማለቁን እንጂ መኖሩን አይፈልጉም።
በሰኞው እለት ከሰማናቸው አሳዛኝ ክስተቶች መሃል የብዙሃኑን ልብ የሰበረው ዜና በዛምቢያ ምድር 27 ኢትዮጵያውያን ተገለው እሬሳቸው ሜዳ ላይ ተጥሎ መገኘቱ ነው።አንድ ወጣትብቻ ህይወቱ ሳታልፍ ተገኝቶ ለሕክምና ወደ አገሪቱ ከተማ ሉሳካ ሆስፒታል መላኩንና የሟቾቹም አስከሬን ለምርመራ መላኩን ያገሪቱ ፖሊስ አስታውቋል።እነዚህ ዕድሜያቸው ከሃያ እስከ ሰላሳ የሚደርሱ ወጣቶች ባገራቸው በሰላም የመኖር ተስፋቸው ጨልሞ ለተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከሚወጡት መካከል ናቸው። ብዙዎችም ባሕር ሲያቋርጡና በጨካኞች እጅ ላይ ወድቀው የሰውነት ክፍላቸው እዬወጣ ለገበያ እንደሚቀርብና በአሰቃቂ መንገድ ህይወታቸው እንዳለፈ ይታወቃል። ካሰቡበት የደቡብ አፍሪካ ምድር ከደረሱም በዃላ በአገሩ ተወላጅ በሆኑት ዝቅተኛ ማህበረሰብ አባላት በቆንጨራ የሚጨፈጨፉና ያላቸውን የሚዘረፉት ጥቂቶች አይደሉም።ያገራችን ወጣት ከአገሩ የወጣ ሁሉ ደልቶት እንደማይኖር እግሩን ከማንሳቱ በፊት ሊያስበው ይገባል።በአገሩ ላይ እንዳይኖር ካደረገው ሥርዓትና ካሰማራው የቄሮ ገዳይ ቢያመልጥ በተመሳሳይ ጥላቻና ምቀኝነት ያወረው የያገሩ ጨፍጫፊ ቡድን ቆንጨራ ይዞ እንደሚጠብቀው ልብ ሊለው ይገባል። ወጣቱ መሞቱ ላይቀርለት ለነጻነቱና ለሰላማዊ ኑሮው በአገሩ ውስጥ ቢታገል የተሻለ ውጤት ባለቤት የመሆን ዕድሉ ትልቅ ነው።ሌላው ወጣት ደግሞ የጫት፣ የሺሻና የአልኮል ሱሰኛ ሆኖ ደንዝዞ ለቤተሰቡ ና ለአገሪቱ ሸክም የሆነው ቁጥሩ ቀላል አይደለም።ይህንንም ማስተካከልና ማረም የትግሉ አንዱ አካል ሆኖ መወሰድ አለበት። በውጭ አገር ከባድና ዝቅተኛ ሥራ እዬሠራ ገንዘብ ለቤተሰቡ የሚልከው ለፍቶ አደር ወንድሞቹና እህቶቹ በምን ተግባር ላይ እንደተሰማሩ መከታተል ይኖርበታል።አብዛኞቹ የሚያገኙትን ገንዘብ ለጫትና ለአልኮል እንደሚጠቀሙበት የሚወጡትን መረጃዎች ሊያጤነው ይገባል።በሌላም በኩል ሰብሳቢና እረዳት አጥተው በየከተማው የተበተኑት ከ5ሚሊዮን በላይ የሚጠጉ ወላጅ አልባ ሕጻናት ለአሸባሪዎቹ መሣሪያ ለመሆን የተጋለጡ ናቸው።እነሱንም ከጥፋት ተግባር ለማራቅ ከጎዳና ተዳዳሪነት ማውጣት ትልቅ አገራዊ ፈተና ነው።
በዋሽንግተን የሚገኙ በዚህም በዚያም ከአብይ አህመድ ጋር የተሳሰሩ አሜሪካኖችና ድርጅቶች ለዓለም የአዬር ለውጥ ዘመቻ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ የአፍሪካ መሪ ብለው እውቅና ሰጥተውታል። እንደ አግባቡማ ቢሆን ኖሮ ይህንን ሽልማት ማግኘት የነበረበት በቅርቡ በግብጽ የቱሪስት ከተማ በሆነችው በሻርም ኤል ሸክ ውስጥ በተካሄደው የዓለም አዬር ለውጥ ጉባኤ ላይ ነበር።የእነዚህ የድርጅትና የፕሮቴስታንት ብልጽግና ሃይማኖት መሪዎች ዋና ዓላማቸው የአብይ አህመድን ገበናና ሃጢያት መሸፈን ነው።የካዱት ነገር ቢኖር ለዜጎቹ ክብርና ዋጋ ያልሰጠ፣ከሰው ልጅ ህይወት ይልቅ ለቅጠላ ቅጠልና ለቁጥቋጦ ቅድሚያ የሚሰጥ ፣የዓለም ጸር የሆነ የዘር ፖለቲካ የሚያራምድና የሚመራ ግለሰብ መሆኑን ነው።የሕዝቡ ትግል ወሳኝ ደረጃ ላይ ሲደርስ ወይም ያስተሳሰራቸው የጥቅም ክር ሲበጠስ ስቀለው ስቀለው የሚሉበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም ብለን እናስባለን።
በአገር ውስጥም የተጀመረው የተማሪው ትግል ቀጥሏል፣የሰብአዊ መብት ተቋሙም መንግሥትን ተጠያቂ በማድረግ ድርጊቱን ኮንኖ መግለጫ አውጥቷል።የጅዋጅዌ ፖለቲካ ተጫዋቹም ኢዜማ የከተማው አስተዳደር ለሚደርሰው ሁሉ ተጠያቂ ነው ብሏል። በገዢው መደብ ውስጥ ትርምሱ ተፋፍሟል።ሌባና ሙሰኛ፤እዬተባባለ ጎራ ለይቶ አንዱ አሳሪ ሌላው ታሳሪ ሆኗል።የአብይ አህመድ የቅርብ አጋሮቹም በተለያዩ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ እዬተመደቡ እግሬ አውጭኝ በማለት ላይ ናቸው።ለነዚህ ወንጀለኞች ጎሳቸውና የዓለም አቀፍ ድርጅት የሚደበቁበት ዋሻ ሆኗል።
በዚሁ ሰኞ ቀን ወደ ደምቢዶሎ በሚወስደው መንገድ የሰባት ተማሪዎች መታፈን ይፋ ሆኗል። ተማሪዎቹ ሁሉም አማራዎች ሲሆኑ በዚሁ ከተማ ባለው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚማሩ ነበሩ።ይህ ጠለፋ ካለፈው ሶስት ዓመቱ ጠለፋ ጋር የሚመሳሰልና የት እንደገቡ ለማወቅ አዳጋችም እንደሚሆን ጭንቀታቸውን የሚገልጹት ብዙዎች ናቸው።እኛም ለብዙ ጊዜ ስንጮህላቸው የነበረው የ17 ወጣቶች መጥፎ ዕድል ይገጥማቸዋል ብለን እንሰጋለን።
ከዚሁ ሰኞ ቀን ሳንወጣ “የሸገር ልጆች ወደ መስቀል አደባባይ”በሚል ጥሪ የተላለፈው የተቃውሞ ሰልፍ ፖሊስ የተፈቀደለት ሰልፍ የለም፣ በሚወጣው ላይ ነጻ እርምጃ እወስዳለሁ በማለቱ ሳይካሄድ ቀርቷል።እንኳንስ በሰልፍ ይቅርና በቤቱም አርፎ የተቀመጠ ሰው በጥርጣሬ የሚያስረው ፖሊስ ከዚህ አስፈሪ ዛቻ ይታቀባል ተብሎ አይጠበቅም። በሕገ ጥፋቱ ውስጥ ቢሆንም ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የማሳወቅ እንጂ ፈቃድ የመጠዬቅ ግዴታ የለም።ይህንን የራሴ ነው የሚለውን የሕግ መመሪያ በመጣስ ነው የተረኞቹ ፖሊስ ዱላ መዞ ብዙዎችን ከጉዳት ላይ የጣለው፣ለከፋ ማጥቃትም የዛተው። የመንግሥትን ድንፋታ የሚያራግቡ ቡድኖች የሚካሄደውን የሕዝብ ትግል አላስፈላጊ መስዋእትነት ያስከፍላል እያሉ በማውገዝ ላይ ተሰማርተዋል።በጨካኞች ስርዓት ውስጥ ሆኖ የሚደረግ ማንኛውም ትግል መስዋእት ይጠይቃል። እርግጥ ነው ከአቅም በላይ የሆነን የታጠቀ ሃይል በባዶ እጅ ለመቋቋም መሞከሩ ጀብደኝነት ቢመስልም ከሁኔታው ጋር የሚጣጣም ትግል ማድረግ ግን ተገቢ ነው።ሰላማዊ ትግል የግድ አደባባይ ወጥቶ ከአረመኔዎች ጋር መጋፈጥ ብቻ አይደለም ፣በቤት ውስጥ የመቀመጥ፣ በሥራ የመለገም፣ግብር ባለመክፈል፣በቤተ-እምነቶች ግቢ ውስጥ የጸሎትና የውግዘት ድምጽ በማሰማት፣ለውጭ አገር የመንግሥታት ተጠሪዎችና ጋዜጠኞች፣ለዓለም አቀፍ ተቋማት በደብዳቤ የማሳወቅ፣ከመንግሥት ጋር ያለመተባበርና በእቅዶቹ ያለመሳተፍ… ወዘተ የመሳሰሉትን ያጠቃልላል። ከሥራ ቢቀሩ ወይም ከእለታዊ የግል ሥራ ቢነጠሉ ገቢ ስለማይኖር ችግር ሊከሰት ይችላል፤ይህንን ለመቋቋም ግን ቀደም ብሎ የመዘጋጀት፣አንዱ ለሌላው ማሰብና ማካፈልን የበጎ ምግባር ትብብርን ይጠይቃል።ለዚያም ነው የትብብር መድረክ አስፈላጊነት።
በተከታዩ ማክሰኞ በአዲስ አበባ የተማሪውና የመምህራኑ ትግል ቀጥሎ ብዙ ጉዳት የደረሰ ከመሆኑም በተጨማሪ በአሜሪካን አገር በተለይም ስብሰባው በሚካሄድበት የዋሽንግተን ከተማ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን የአብይ አህመድን መንግሥት ለማጋለጥ ሰልፍ የወጡበት ቀን ነበር።ብዙ ኢትዮጵያዊ በሚኖርበት ዋሽንግተን ከተማ በሰልፉ ላይ የተገኘው ቁጥሩ ከሚኖረው ያነሰ ቢሆንም የተሳካ ነበር።ሰልፉን ለማሰናከል የአብይ አህመድ ውታፍ ነቃዮችና በንግድ ዘርፍ ተሰማርተው ከአገር ቤቱ ሸቀጥ ዝውውር ጋር የተሳሰሩ፣በአገር ቤት ፎቅና ቪላ ያሠሩ ጥቅመኞች ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም።ሰልፈኛውም ከነዚህ ጋር ያለመገበያዬትና ከሚሰጡት አገልግሎት እራሱን ለማግለል(ቦይኮት)ለማድረግ ወስኖ በቀጣዩ ሃሙስ ቀን በኤምባሲ ግቢ ለማካሄድ ባሰቡት የድጋፍ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ተቃውሞ ለማድረግ ወስነዋል።እኛም በያገሩ የሚኖሩ ኢትዮጵያኖች ከአለው ሥርዓት ጋር የተሳሰሩ ነጋዴዎች ከሚሰጡት አገልግሎት እራሱን እንዲያርቅ ጥሪ እናደርጋለን።
አድር ባይነት በእኛ አገርና ዘመን ብቻ የተከሰተ አይደለም።የሰው ልጅ ባለፈበት የታሪክ ጉዞ ውስጥ የተንጸባረቀ ድክመት ነው።ከነዚያም አንድ ሁለቱን ብንጠቅስ፣
በዚችው ጉደኛ አሜሪካ ነጮቹ ባሰፈኑት የባሪያ ሥርዓት ጊዜ ከአፍሪካ እንደ አባ ጅፋር፣ ጦናና ጆቴ ባሉ ባርያ ፈንጋዮች ተሸጠው የወጡ አፍሪካውያን በሁለት ጎራ ተከፍለው አንዱ በሌላው ላይ የጭካኔ ተግባር እንደፈጸመበት በሚከተለው ታሪክ እንረዳለን።ባርያው የቤት ውስጥና የመስክ ባሪያ ተብሎ በመመደብ፣የቤት ውስጥ ባርያ ለጌታው ምግብ ቀቃይና የቅርብ አገልጋይ በመሆን ሲመደብ ሌላው ብዙሃን ደግሞ ጌታው ባለው ሰፊ የጥጥና የሌላም ምርት ማሳ ላይ በሰንሰለት ወገብ ለወገብ ታሥሮ የሚሠራ ነበር።የጸሃይ ሃሩርና የማለዳ ቁር እዬተፈራረቀበት በከባድ ሥራ ላይ የተጠመደው ባርያ ሲሳነው፣ካቅሙ በላይ ሲሆንበት መቆም ያቅተውና ይወድቃል።ያንን የወደቀ በበሽታና በድካም የዛለና የመነመነ ሰውነት በወፍራም ጅራፍ ለሚገርፈው ጌታ ጅራፍ ተሸክሞ የሚያቀርበውና ጌታው መግረፍ ሲደክመው ተቀብሎ ታማኝነቱን ለማሳዬት ሲል እዬተንጠራራ የሚገርፈው የቤት ውስጡ ባርያ ነበር።በዚህ ጨካኝ ፣ወጠምሻ፣አድርባይ የሚሰነዘረው ጅራፍ እንኳንስ የሰው ገላ ቀርቶ መሬት ይሰነጥቃል።ከጌታው የተረፈውን እየላሰና እዬጠራረገ፣በበዓል ቀን ከሚታረደው አሳማ የጨጓራና የተርኪ ጉሮሮ ጉርሻ ሲጣልለት በመብላት የፈረጠመ ሰውነቱን ጥንካሬ የሚያሳዬው ከአሳማ ጆሮ፣ ጅራትና ሸኮና የተሰራ ቀጭን ሾርባ አይሉት መረቅ በልቶ፣በሥራ ብዛትና በእረፍት ማነስ በመነመነው በመሰል ጥቁር ወገኑ ላይ ነበር። ታዲያ የአሁኖቹም የአሜሪካ ባሮች በዓለም ባንክና በአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የሚሠሩት የካሮትና ዱላ ተሸካሚ የሆኑ በትውልድ ኢትዮጵያውያን በግብራቸው ግን አሜሪካውያን የሆኑ መምህራን ነን ባዮች የነጮቹን መመሪያ ለማስከበር ደፋ ቀና ሲሉ እናያለን።አዋ ውሻ በበላበት ይጮሃል!
ሌላው የከሃዲዎች ታሪክ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ከናዚዎች ጋር ተባብረው የራሳቸውን ወገን ባስጨረሱትና በመጨረሻም እራሳቸውን የስጨረሱትና በጋዝ ምድጃ ውስጥ አመድ ሆነው የቀሩትን የአይሁድ ነጋዴዎችን ታሪክ የሚመለከተው ነው። በናዚዎች አይሁድ እዬተባለ የሚታፈሰውን ነዋሪ ስምና አድራሻ እዬሰጡ ካሳፈሱት መካከል ትልቁን ድርሻ የያዙት እራሳቸው አይሁዶች ነበሩ።እነዚህ በጥቃቅን ንግድና የተለያዩ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ አይሁዶች የሚተርፉ መስሏቸው ወገናቸውን ለናዚዎች አሳልፈው ሰጥተዋል።የዃላዃላ ግን ከተጠቀመባቸው በዃላ እነሱንም አፋፍሶ ወፈር ወፈር ያሉትን በፋብሪካ ጨፍልቆ የሞራ ሳሙና ሠርቶባቸዋል። የተበሳቆሉትም በምድጃ ነደው አመድ ሆነዋል።ይህ ነው የአድርባዮች የመጨረሻ እጣ ፈንታ።የእኛንም አገር አድር ባዮች የሚገጥማቸው ዕድል ከዚህ የከፋ ስለሚሆን ፣ ሲሆን በሰውነታችሁ ለሌላው ሰው ክብርና መብት ቁሙ፣ለትውልድ አገራችሁም ህልውና ታገሉ አለያ ግን ከአሁኑ ድርጊታችሁ ታቀቡ እንላለን።በያዛችሁት ከቀጠላችሁበት ግን ከኦነግና ከወያኔ ጅራፍ አታመልጡም፣ብታመልጡም ከፍትህ አታመልጡም እንላቸዋለን።
አብይ አህመድን ተቃውመው ከወጡት መሃል የጨፍጫፊዎቹ የኦነግና የወያኔ ደጋፊዎችም ነበሩ። ጅራፍ እራሱ ገርፎ መልሶ ይጮሃል እንደሚባለው እነዚህ በውጭ አገር በስደተኛ ስም የተበተኑት ስብስቦች በአገር ወዳዶች በተለይም በአማራው ላይ የሚፈጸመውን ጭፍጨፋ ለመሸፈንና ትኩረት ለመለወጥ ሲሉ እንጂ ከአብይ አህመድ ጋር የተለያዬ ዓላማ ኖሯቸው አይደለም።የነዚህ የጥፋት ሃይሎች ድምጽ የአድማጭን ጆሮ ሊስብ የሚችለው የሌላው ድምጽ ከኮሰሰና ተቃውሞውን አጠናክሮ ካልቀጠለበት ነው።የእነዚሁ ክንፍ የሆነው የቄሮ መንጋ በአገር ቤት የአማራውን መጨፍጨፍ ደግፎ ሰልፍ ሲያደርግ በፖሊስ ታጅቦ ነው።ከዚያም ባለፈ ታጥቆ ጥቃት እንዲፈጽም በመንግሥት የወጣው ዕቅድ በተግባር ላይ ለመዋል ትእዛዝ በመጠባበቅ ላይ ነው። ለምላሹ ሁሉም ይዘጋጅ!
በአገር ቤትና በውጭ አገር የተቃውሞ ሰልፍ በተካሄደበት እለት በተረኛው ቡድን ከኦሮሞ ክልል ተሰብስቦ በአዲስ አበባ ፖሊስ ስም የተሰማራው እንግዳ ሃይል ከዱላው ባሻገር ይቃወማሉ የሚላቸውን ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ድርጅት አባላትን እያፈሰ በማሰሩ ላይ ተሰማርቷል ፣በዚህም መምህርት መሥከረም አበራና የባልደራስ አባላት መታሰራቸው ይፋ ሆኗል።ይህ እርምጃ አምባ ገነኖች በሕዝብ ትግል ሊወድቁ ሲሉ የሚያደርጉት የመንፈራገጥ የአልሞት ባይ ተጋዳይ እርምጃ ከመሆን ያለፈ የጥንካሬያቸው ማሳያ ነው አንልም።
ባለፈው እሮብም በሕዝቡ የታጀበው የመምህራኑና የተማሪው ተቃውሞ አይሎ የታዬበት ቀን ነበር በዚህ ቀን የተቃውሞውና የመፈክሩ ክብደት የጨመረበት ሆኖ ታይቷል። በልደታ አካባቢ ባለው ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣አስተማሪዎችና ወላጆች በተሳተፉበት ሰልፍ ላይ አንድ አገር! አንድ ሕዝብ! አንድ ሰንደቅዓላማ! በሚለው ተተክቷል።አሣ ጎርጓሪ ዘንዶ አወጣ ማለትም ይህንን ይመስላል። እነአዳነች አቤቤ የቆፈሩት ጉድጓድ መቃብራቸው ሊሆን እንደሚችል ይህ ማሳያ ነው።
በአገራችን ሰው እያገቱ ገንዘብ መጠዬቅ አዲስ የሥራ ዘርፍ እዬሆነ መጥቷል።ዘመድ ሳይቀር የቤተሰብ ልጅ እያገተ ገንዘብ አምጡ ይላል።በቅርቡ በሰሜን ጎንደር የእህቱን ልጅ አግቶ 150,000(መቶ ሃምሳ ሽህ ብር)ጠይቆ ያልተሳካለትን ሰው ታሪክ ሰምተናል። በአገራችን እገታ የተለመደ ቢሆንም የሰው ሳይሆን የከብት ነበር። የአንዱ ሰው ከብት ከሰው ማሳ ውስጥ ገብቶ ሲግጥና ሲረጋግጥ ታግቶ ባለቤቱ ለወደመው ሰብል ወይም ቡቃያ ካሳ እንዲከፍል ይጠዬቅ ነበር።ያ እገታ አሁን የፖለቲካ እርምጃ ሆኖ ክልል በተባለ መሬት ላይ የሚኖር ወይም አላፊ መንገደኛ እዬታገተ የሚገደልበት ወይም ብዙ ብር ከፍሎ ከሚለቀቅበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ኢትዮጵያዊ በአገሩ የውስጥ ድንበር ተጥሎበት በነጻ እንዳይንቀሳቀስ ሲደረግ ባለሥልጣኖቹና ወንበዴዎቹ የዘረፉትን ሃብት በድንበር ተሻጋሪ ባንክ ያንቀሳቅሳሉ።
በዋሽንግተን ለሃሙስ ተጠርቶ የነበረው ድጋሚ የተቃውሞ ሰልፍ ጥቂት ሰዎች የተሳተፉበት ነበር። በቦታው የተገኙትም የመንግሥት ደጋፊዎች እንዲሁ በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ።ለብዙዎች አለመገኘት የሥራና የአዬሩ አለመመቸት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለን።በቦታው በተገኙት በሁለቱም መካከል የቃላትና የመገፋፋት እርምጃ ከማዬት ባለፈ ብዙም ግጭት አልታዬም።በዚሁ ሃሙስ እለት በኤምባሲው አዘጋጅነት በተካሄደው ግብዣ ላይ በከባቢው የሚኖሩ ሆድ አደር ነጋዴዎች፣ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች(ጳጳስና መነኩሴዎች)የሥርዓቱ ደጋፊ ጎሰኞች ተገኝተው ከአብይ አህመድ ጋር የደም ገበታ ተካፍለዋል።በዚህ ግብዣ ላይ ጥቁር ካባና ቆብ ደፍቶ የታዬው ጳጳስና ተከታዮቹ በጣልያን ወረራ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የሚዘምተውን ጦርና ታንክ ባርኮና ጠበል እረጭቶ የላከውን ጳጳስ መስሎ ታይቶናል።የቤተክርስቲያናችን ክብር የወረደው በዚህ አይነቱ አድርባይ ጳጳስ ነው።
በአማራው ክልል ብአዴንም የኦነግ ኦሕዴድን ተልእኮ መፈጸሙን ቀጥሎበታል።የፋኖና ልዩ ሃይል አባላት ናቸው፣ሥርዓቱን ይቃወማሉ የሚላቸውን የአማራ ተወላጆች እያሳደደ በማሰር ላይ ሲሆን ይባስ ብሎም ለኦነግ ፍርድ ቤት አሳልፎ ለመስጠት መዘጋጀቱ ተሰምቷል።ይህ ከሃዲ ቡድን ካልጠፋ በቀር የአማራው ሰቆቃ ማለቂያ የለውም።ለዚያም ነው አስቀድሞ ማሶገድ ብአዴንን ነው የምንለው።
ሳምንታትን ያስቆጠረው የተማሪዎችና የመምህራን እንዲሁም የወላጆች ተቃውሞ አሁንም እዬቀጠለ ሄዷል።ይህንን ተቃውሞ ለመግታት አዳነች አቤቤም ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም።ይህንን ሕጻናትን ሳይቀር ያካተተ የመብት ተቃውሞ አገር ለማፍረስና የተጀመረውን ጸረ ሙስና እንቅስቃሴ ለማጨንገፍ ከአሸባሪው ፋኖ የተሰጠ ተልእኮ ነው በማለት በለመደው የባለጌ መግለጫዋ አሳውቃለች።በዚያም አላቆመችም የኦሮሚያ ባንዲራ በውድም በግድም ይሰቀላል፣መዝሙሩም ይዘመራል፣እምቢ ያለም ከከተማዋ ይባረራል ብላለች።ይህንን ያህል ድፍረት ከአብይ አህመድ እውቅናና መመሪያ ውጭ ሊኖራት እንደማይችል የታወቀ ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም አዲስ አበቤ የታቀደልህን የጥፋት ድግስ ተረድተህ ሕጻናት ልጆችህ ደፍረው በተሰለፉበት ትግል ውስጥ ከመግባት የተለዬ አማራጭ የለህምና እጅ ለእጅ ተያይዘህ በስር ነቀል ለውጥ እራስህንና አገርህን አድን እንላለን።
ሕዝባዊ ትግሉ ይፋፋም!ኢትዮጵያ በአንድነትና በነጻነት ለዘለዓለም ትኑር!!
የአዳነች አቤቤን ስለጸረ ሙስና የመሆኗንም ተረት ተረት የሚያጋልጥ ታሪክ በልዩ ልዩ የሥልጣን ቦታ ላይ ሆና የፈጸመችውን የሙስና ተግባራት የሚያውቁ ሰዎች እዬተናገሩ መጥተዋል።ከሰሞኑ በኢትዮ360 ስርጭት ላይ በሃብታሙ አያሌው ዝግጅት ቀርባ የምስክርነት ቃሏን የሰጠችው በኢሕአዴግ አገዛዝ በኦሕዴድ አባልነቷ የፈረደባት አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ቁልፍ ቦታ ይዛ ኖራ አሁን በአሜሪካ የምትኖረው ወ/ሮ አበባ የተባለችው አንዷ ስትሆን እንዲህ ስትል አጋልጣታለች።ማን ይናገር የነበረ፣ማን ያርዳ የቀበረ፣ ወይም እሾህን በሾህ ነውና የምትለውን እንስማ።
በቅድሚያ ግን ላለፉት ዓመታት መረጃ እዬሰበሰበና ትንታኔ እዬሰጠ ለትግሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ያለውን ኢትዮ360 ለማመስገን እንወዳለን።የነገው መዳረሻ ባይታወቅም እርሻ ላይ ይውላል ተብሎ ገደል ገብቶ ከሞተው ወይፈን ታሪክ ጋር ከሚመሳሰል አደጋ ይጠብቃችሁ እንላለን።
https://amharic-zehabesha.com/archives/178351
Monday, December 19, 2022
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment