Saturday, December 31, 2022
አዲሱን የአውሮጳውያንን ዓመት 2023 ዓ/ምን ሥንቀበል ፦ " በኢትዮጵያዊነታችን ፣ በዜግነታችን እንኮራለን ። አንዳችም የምንረሳው የታሪክ ጠባሣ የለም ። የደበዘዘ ትውሥታም የለንም ።አምባገነኖችን ዛሬም ከመዋጋት ወደ ኋላ አንልም ። "
ሲና ዘ ሙሴ
አምባገነኖችን የምትዋጋ ኪነት በኢትዮጵያ ትላንት እንደነበረች ዛሬ ታወቀ ። ቴዲዮ እና አቡሽ መሠከሩ ። “ ኢትዮጵያ ትቅደም ! ዘረኝነት ይውደም ! “ አሉ ። ትላንት ቴዲ አፍሮ ነበር በሙዚቃ ለኢትዮጵያ ከፍታ የታገለው ። በግጥሙ ደግሞ በዘመኑ አቻ ያልተገኘለት በለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ቀዌሣ ነበር ደጋግሞ ኢትዮጵያን ያሥቀደመው ።
ቴዲዮ እንዲህ አለ ፦
የወንዜ ! የወንዜ ! የወንዜ ! ትርምሥ
ጥያቄ ብቻ ነው መልሱ ላይመለሥ
የወንዜ ! የወንዜ ! የወንዜ ! አራት ኪሎ
ወንበርሽ ይፋጃል ጠፋ ሁሉ ጥሎ !
ቀዬ ፈርሶ ህንፃ ቢደረደር
ላይቀረፍ ችግር ...
( ቴዲ ዮ ) ያንጎራጎረው ጥቂቱ ሥንኝ ነው ። ቴዲዮ አዲስ አበቤ በደናቁርት እና በሥግብግብ ባለሥልጣናት እየተመራች በመሆኑ ኗሪው ሰብዓዊ መብቱ ተከብሮ እንደ ሰው መኖር እንዳልቻለ ጮክ ብሎ በዘፈን ተናግሯል ።
ይኽንን ሰው መሆኑንን የካደ ፣ ራሱ አመድ ሆኖ በዱቄት የሚስቅ መንግሥት በክሊፑ ማንነቱን አሳይቷል ። እውነት ነው ፣ ሃቅን የተናገሩ ጋዜጠኞች እና የኪነጥበብ ሰዎች እየታፈኑ በየማጎሪያ ከምፑ ሲወረወሩ አይተን እና ሰምተን ታዝበናል ። ገጣሚ በቀለ ወያ ከተፈታ በኋላ ሥንቴ ሞባይሉን በፖሊሶች ወይም ደህንነት ተብየዎች ተዘረፈ ። ግልፅ አድርጎታል ። ከወያኔ / ኢህአዴግ በባሰ መልኩ ሃሳብን የሚፈራው አብይ አህመድ ነው ። ብልፅግና በሉት የራሱ የአብይ አህመድ ድርሰት ነው ። በብልፅግናም የተመረጠው “ አንዱን ዳቦ ሦሥት ቦታ ቆርሶ ፣ አንዱን ለቆራሹ ፣ አንዱን ዳቦውን ጋግሮ ላመጣው ፣ አንዱን ደሞ ሻሞ ! እላለሁ የቀለበ ይውሰድ ። “ ብሎ እራሱ ቀልቦ ዘውድ የጫነ ፈጣጣ ሰው ነው ። አወቅህ ፣ አወቅህ ፤ ሥንለው የማይሆን ሥራ እየሰራ ደጋግሞ አሳይቶናል ። በትዕግሥት ብንመክረውም ንቆናል ። አዋርዶናል ! እንሆ ዛሬ በአደባባይ አጋድመው ካረዱን ጋራ ቁጭ ብሎ በማላገጥ ላይ ይገኛል ።
ከዚህ የዛሬ እውነት አንፃር ሥናየው አብይ መራሹ መንግሥት በህግ የማይገዛ አምባገነን እና ፈላጭ ቆራጭ የጥቂት ዘራፊዎች ሥብሥብ እንጂ ጨዋ ና ሥነምግባር ያለው ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት ያለመሆኑንን እንገነዘባለን ።
ይኽ መንግሥት እራሱ "የቀን ጅብ " ሆኖ ሳለ ፣ ሌሎቹ ላይ ጣቱን እየቀሰረ "የቀን ጅብ " በማለት የሚሳደብና ድራማዊ በሆነ መንገድ የሚያሳድድ ማፈሪያ የህነ መንግሥት ነው ።
ሞራል ና ህሊና አልባ መንግሥት መሆኑንም ዛሬ ለጨዋው ፣ ለኩሩ ና በፍቅር ለሚኖረው ህዝብ ፍንትው ብሎ ተገልፆለታል ። አሁን እና ዛሬ አብይ አህመድ አጭበርባሪ ፣ እጅግ እራስ ወዳድ ፣ ለሥልጣኑ ዘላለማዊነት ሲል የማይፈጥረው ውሸት እንደሌለ የተገነዘብነበት ወቅት ላይ እንገኛለን ። እነ ለማ መገርሳንም በተቀነባበር ውሸት ከመድረኩ ዞር እንዳደረጋቸው ዛሬ ለይ ማሰብ እንችላለን ።
ለማ መገርሳ ከአብይ አህመድ መቶ እጅ እንደሚሻል በግንባሩ ላይ በሚነበበው እውነት መረዳት ይቻል ነበር ። ይሁን እንጂ በረቀቀ ሤራ አብይ ከፖለቲካ ጫወታ ውጪ አድረጎታል ። " አቤት ፣ አቤት አብይ የነቃን የበቃን ነን ። "የምንለውን ሥንቶቻችንን አቄለን ?
ዛሬ ና አሁን ፣ በምኒልክ ወንበር ላይ በታላቅ ሸፍጥ እና በድራማዊ ዘዴ አብይ ተቀምጧል ። እንዳለመታደልም ሆኖ ከምኒልክ ሞት በኋላ በብዙሃኑ ህዝብ የሚወደድ መሪ ይኽቺ አገር አላገኘችም ። መንግሥቱ ኃይለማርያም በተወሰነ ደረጃ የህዝብ ቅቡልነትን አግኝቶ እንደነበር ግን አይካድም ።እርሱ አማራ፣ኦሮሞ፣ትግሬ፣ወዘተ እያለ ሰውን ከሰው ለማባላት የቆመ መንግሥታዊ ሥርዓትን አላዋቀርም ። በኢትዮጵያ ከሰማኒያ በላይ የሆነ ጎሣ ወይም ነገድ ሁሉ የኢትዮጵያ ዜጋና ልጇ እንደሆነ ያረጋገጠ መንግሥታዊ ሥርዓትን ነበር ለ17 ዓመት የመራው ። ያው እንደምታውቁት ሶሻሊዝም ሲንኮታኮት እርሱና መንግሥቱ ተኮታኮተ ። በእርሱ ምትክ አሜሪካ መራሹ ህውሃት " ኢህአዴግ " ነኝ ፣ ብሎ የገበሬ ጦሩን እያርመሰመሰ አራት ኪሎ ገባ ። እናም ዜግነት ክብር ከኢትዮጵያ ጋራ እንዲቀበር ለማድረግ ሥራውን ጀመረ ። በቋንቋ የኢትዮጵያን ህዝብ ከፋፈለ ና ለጥቂት ሆዳሞች ሥልጣን እና ጠመንጃ በመሥጠት እያሥፈራራችሁ ህዝቡን ግዙ በማለትም "የእንሥሣት ጉባኤ " አይነት መንግሥት በክልል ሥም አዋቀረ ። ይኽ መንግሥትም ከ27 ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ ህዝብ " በቃ ! " ተባለ ሆኖም ሥርዓቱን ከመውደቅ ለማዳን " በባላ በመደገፍ " እነ " ቲም ለማ " ሚና ተጫወቱ ። በጫወታቸው ወቅትም የትግራይን ኗሪ ህዝብ በመርሳታቸው ተሸወዱ ። ወያኔ አማራን እንደ ትግራይ ህዝብ ጠላት እንዲቆጠር ከፍተኛ የቅስቀሳ ሥራ ሰራ ። ዜጎች እንደ ዜጋ ከማንም ጋር ፀብን ሣይፈልጉ በደንቆሮ መሪዎች የሤራ ቅስቀሳ ደም እንዲቃቡ አደረገ ። ይኽ በእውነቱ አሣፋሪ ነበር ።
እሥቲ በ2 ዓመት ውሥጥ የወደመውን የደሃ አገራችንን ሀብት ተመልከቱ ። የጠፋውን የሰው ህይወትም አሥተውሉ ። የቆሰሉት እና አካላቸው የጎደለ የኢትዮጵያ ልጆችንም እዩ ፤ ይህንን እውነት ማነው የሚያሥተባብለው ? "እኛ ኢትዮጵያዊያን ሃፍረትን በማያወቃት በአብይ አህመድ አመረራ በቁም አልሞትንምን ? " ሠላም የሚመጣው ገሃነም መግባት ያለበት ገነት ሲገባ ነው ። " ለምን ትለናለህ ? ይህ ትራጀዲ ድራማህ ማብቂያው የት ይሆን ?
እንሆ አሁን እና ዛሬ ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ልብ ያገኘ ኃቀኛ ፣ ሰው ፣ ሰው የሚሸት መንግሥት ያለመኖሩን አውቀናል ።
በሸፍጥ ፣ በራስ ወዳድነት ፣ በውሸት፣ በማጭበርበር ና በህዝብ ንቀት ህሊናው ተጠቅጥቆ ፣ ዕይታው ተንሸዋሮ ዜጎችን እንደ እንሥሣ በመቁጠር በጠብ መንጃ ልምራ የሚል መንግሥት ፣ አራት ኪሎን እንደተቆጣጠረም ተገንዝበናል ። አብይ አህመድንም ከእንግዲህ “ እህ ? “ ብሎ የሚያዳምጠው ኢትዮጵያዊ የለም ። ...
በበኩሌ ለውዶቻችን ለአቡሽ ና ለቴዲዮ ፣ ለጀግኖቹ ጎበስ ብዬ እጅ ነሥቻለሁ ። በቀደመ ፅሑፌ እንዳልኩት " ሰው ያሳደከው ውሻ ወይም የቤት እንሥሣ አይደለም ። እንዳንተው በአርያ ሥላሤ የተፈጠረ ነው ። እናም የእያንዳንዱን ግለሰብ አእምሮ ልትቆጣጠር አትችልም ። የጆርጅ ኦርዊል 1984 የተሰኘ መፅሐፉን አላነበብክ እንደሆን አንብብ ።በዛ አይነት ከፍተኛ የአፈና ማዋቅር ባለው መንግሥት ውሥጥ እንኳን የግለሰብን አእምሮ መቆጣጠር አልተቻለም ። እንደ “ እንሥሣ ጉባኤ “ አይነት መንግሥት በማቋቋምም አገርን መምራት ከቶም አይቻልም ። ወዳጄ ጠብ መንጃውን የጨበጠው እና የሚጠብቅህም ሰው መሆኑንን እወቅ ። በማሽን እሥካልተጠበቅህ ጊዜ ድረስ ዋሥትና የለህም ። ተጨቋኙ ምንጊዜም ከተጨቋነው ጋር መሆኑንንም እወቅ ። ጥቂት ወታደሮች ፣ ፖሊሶች ና ልዩ ኃይሎች ሥለደላቸው ህልውናህን የሚያሥጠብቁልህ ከመሰለህ ተሣሥተሃል ። የራሳቸው አእምሮ የሌላቸው እንደ ታገሠ ጫፎ አይነቶቹም ከነፍሰ ገዳዮች ጋራ ተቃቅፈው ሥለተሞዳሞዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ለነፍሰ ገዳዮች ይቅርታ የሚያደርግ ከመሠለህ ተሣሥተሃል ። ወታደሩ ፣ ፖሊሱ፣ ልዩ ኃይሉ የተሰዋውና እግርና እጁን ያጣው እንዲሁም በብዙ ሺ የሚቆጠር የቆሰለው ፣ በዜሮ ዓላማ እና ግብ ከመሬት ተነስተው በሰሜኑ መከላከያ ሠራዊታችን ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ እንዲፈፀም ትዕዛዝ በሰጡት በነ ደብረፅዮን አማካኝነት ነው ። ይኽንን እውነት የምንረሳ እኛ ሰው እንጂ የምንሰረዝ ( ዲሌት ) የምንደረግ ማሽን አይደለንም ። በዚህ የመጀመሪያ ወንጀላቸው ብቻ የሞት ፍርድ ሊበየንባቸው ይገባ ነበር ። "
እንዴ ! እኛ የኢትዮጵያ ዜጎች እኮ ፤ ትውስታችን አጭር አይደለም ። የደበዘዘ የማሥታዋስ ችሎታ የለንም ። የጥቅምት 24/2013 ዓ/ም ዘግናኝ የወያኔ ጭራቃዊ ድርጊት ከቶም አይረሳንም ። በዛን ወቅት በላያቸው መኪና የተነዳባቸው እኮ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሳይሆኑ ኢትዮጵያ ናት ። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ላይ ነው እኮ መኪና በላዩ ላይ የትህነግ ባለሥልጣናት የነዱት ። ህመሙ ዛሬም ድረስ ይሰማናል ። ፈፅሞ ፣ ፈፅሞ አይረሳንም ።
እኛ ኢትዮጵያውያን ነን ። በኢማጅኔሽን የምንኖር ህዝቦችም አይደለንም ። በብልጭልጭ ነገሮችም እንደህፃን አንደለልም ። መራባችንን የወሥፋታችን ጩኸት ሁሌም እየነገረን እንሆ በኢትዮጵያዊነታችን እንደኮራን አለን ።
ለመሆኑ ሣንቲም ሳይኖረን የዳቦ ፋብሪካ ምን ይጠቅመናል ? በነፃ ዳቦ ማነው የሚሰጠን ? በገንዘብማ አያሌ ዳቦ ቤቶች ግለሰቦች አቋቁመውልናል ። ሺሌም ፣ ድንች ና ንፍሮም በየሜዳኽ ሞልቷል ። አብይ ሆይ የተረት አባት አትሁንብን ፤ በዚህ በዳቦ ፋብሪካ ትርክት ፣ እባክህ ለራሥህ ተጃጃል ። እውነታው በእያንዳንዳችን ጓዳ እና በህሊናችን ውሥጥ ነው ያለው። ድህነታችንም ምሥጢር አይደለም ።
አብይ ፣ ሽመልሥ ፣ ታገሠ ፣ ይልቃል ፣ ደመቀ ፣ ሬድ ዋን ፣ አገኘሁ ፣ ለጌ ( ሥራው መለጋት ፣ መጠለዝ ይመሥላል ። ከተራ አድናቂ አዝማሪ ያልተሻለ ባህሪ ነው ያለው ። ሥንት እና ሥንት አማሮች ለዚች አገር እንደተሰው አገር እያወቆች አማራን እንደአልቃሻ መቁጠሩ እጅግ ያሥገርማል ። ያሳዝናልም ። ) ዛሬ ደሞ ደብረፅዮን ፣ ታደሠ ፣ ጌቾ ምላሱ ፣ ጮማ ሥለቆረጡ እኛ የምናገሣ ከመሰላቸሁ ተሳስታችኋል ። ለራሳችን ጎመን አሮብናል ።
ይህንን ሁሉ እንድፅፍ ያነሳሱኝ ፣ ጀግኖቹ የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው ። ከዚህ ቀደም የፃፍኩት ፅሑፍም እውነት እንደሆነ ዛሬ ግልፅ እየሆነ መጥቷል ። ኢትዮጵያን በሃቅ እና በእውነት ለማገልገል ብቃቱ እና ፍላጎቱ ያላቸው በጠብ መንጃ ዞር ተደርገው የቀን ጅቦች አገርን እየመሯት ነው ። ሠርክ ለራሳቸው እና ለቤተሰቦቻቸው የሚያስቡ በሚሊዮን የሚገመት ዶላር ዛሬም በአውሮፖ አሽሽተው ሥለሌብነት የሚያወሩን የዓለም ቁጥር አንድ ውሸታሞች ናቸው ዛሬ ይህቺን አገር እየመሩ ያሉት ።
ይህንን በማሥተዋል መሠለኝ ጀግናው ኢትዮጵያዊው ዜጋ ፤ አቡሽዬ እሱንም ጨምሮ መላው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሰው እንጂ ቋንቋና ነገድ እንዳልሆነ ባስመሠከረበት “ ነጠላ ዜማው “ ወይም የኪነት ቱሩፋቱ ፣ ከዚህ በታች የተቀኘልን ።
ሰላም ይንገሥ " እርፎ መረባ " በማለት ። በአገርኛ ምርቃት ። በመጀመር " ዘረኝነት ይውደም ! ኢትዮጵያ ትቅደም ! " ያለን በገደምዳሜ ።
......
ሰላ በይ ! ሰላ በይ ! አንቺ የማር ጣዝማ
ውድድ አደረኩሽ ምሥለኔውን ሳልሰማ ! ( ወይ አክስሙት ! ወይ አክሙት ! )
ስንቴ ዘላበዱ ስንቴ ታዘብናቸው
ከሳሽም ፈራጅም ሆነው እያየናቸው (...)
አያቁት እንዳንል ከአይናቸው መች ርቆ
የሚያገዛግዙን ልክ እንደማሥንቆ (...)
የእግዜር ቃል አይደለ አልወረደ ከላይ
ያጣነው እልፍ ነው ከፊደሉ በላይ ። (...)
ስልቻም ቀልቀሎ ቀልቀሎም ሥልቻ
አብረን ነው የምደምቀው አይሆንም ለብቻ ። ( ወይ አክሥሙት
ወይ አክሙት ከእያንዳንዱ ሥንኝ በኋላ አጃቢዎቹ ይጫወቱታል ። )
ካለፈው እንማር ከመጣንበቱ
እየተጠላለፍን አንቁም ከዳገቱ (...)
ሰማያዊ ልባሥ በውሥጡ መርዝ ይዞ
ሥንቱ መንገድ ሣተ ያቺን አንቀፅ መዞ (...)
.....
ያተረፍነው የለም ያጎደልነው እንጂ
የሚያገዝፈንን ጥለን ለሰፈር ሥንዋጅ (...)
አንዱ አንዱን ለማጥፋት የሚደክመውን ያህል
እርፍ ጨብጦ ቢያርስ ከየት በደረስን (...)
ፀጋውን ሣይነሣን በችግር ጎበጥን
በእናንተው እንቶፈንቶ ነፍስ እየገበርን (...)
የካቻምናው እንቅፋት ዘንድሮም ከመታን
የታለ እውቀታችሁ ያለንን ካሳጣን ። (...)
አውጡት ከፖርላማው ያንን የሞት መዝገብ
የጨው ዘር እንዳንሆን እንድንሰባሰብ (...)
ለሰው ቦታ የለው ዜጋ አያውቅ ዘውግ እንጂ
ሥንት ዓመት አየነው ለማንም አይበጅ (...)
አትማሉ በእርሱ እጃችሁን ጭናችሁ
በየአንጎው ከፋፍሎ መደገም ካላሻችሁ (...)
አዲስ ሃሳብ አምጡ ለትውልድ የሚጠቅም
ሰው የፃፈው ነገር ፍፁም ሆኖ አያውቅም (...)
እኔም እላለሁ
“ የፈጣሪያችን ትዕግሥት የተሟጠጠ ይመሥለኛል ። “
https://amharic-zehabesha.com/archives/178514
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment