Thursday, December 8, 2022

በሴቶች ላይ የሚደርስ የኃይል ጥቃት በአስቸኳይ ይቁም - ከአኒሳ አብዱላሂ
በአለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ግምባር ቀደምትነት አዘጋጅነትና ጉዳዩ በጥብቅ በሚያሳስባቸው በሰላም ወዳድ ኃይሎች በመደገፍ የብርቱካናማ ቀለም ቀን ተብሎ በተባበሩት አለም አቀፍ መንግስታት ድርጅት የተሰየመውንና ከ 1999 አ.ም ጀምሮ በየአመቱ እንደሚዘከርና እንደሚከበር ሁሉ በያዝነው አመትም ከኖቬምበር 25 ጀምሮ የሰብአዊ መብት ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ እስከሚከበርበት እስከ ዲሴምበር 10 ቀን 2022 ዓ.ም. ለ 16 ቀናት፣ በተለያዩ መሪሃ መፈክር በማጀብ ግን በዋነኝነት በሴቶችና ሴት ሕፃናት ላይ እየደረሰ ያለውን የኃይል ጥቃት ሰለባ መሆናቸው ለአንዴም ለመጨረሻም ለመግታት የሚያስችል ፖሊሲ ለመቀየስ ይቻል ዘንዳ የተለያዩ አውደ ትርኢቶችንና ጥናታዊ የፅሁፍ መልዕክቶችን በማቅረብ ውይይቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ። በተለይም ስለ ሁናቴው በሕብረተሰቡ አባላት ሊኖራቸው የሚገባውን ንቃተ ሕሊና ለማስረፅና ብሎም ለማሳደግ የሚረዳና የሚያግዝ ፖሊሲ ለመቀየስ ትኩረት የሚያደርግ እንደሆነም አፅንዖት ተሰጦበት የታለመና የሚሳካ እንደሚሆን አዘጋጆቹ ይፋ የሰጥቷቸው መግለጫዎቻቸው የሚያመላክቱት ናቸው። “ነፃነት አንስታይነት ነው” ተብሎ በአፅንዖት የሚገለፀው ተራ አነጋገር ሳይሆን በተለያዩ አካባቢዎች በበርካታ የሴቶች ትግል ተመክሯዊ አስተዋፅዖ ያበረከቱና ለትግል አርአያነት የበቁትን ለመዘከርና ለማስታወስ ዋነኛ እሴት መሆኑን ለማመላከት እንጂ ለሌላ አይደለም።

ለምንድን ነው ለመሆኑ በኖቬምበር 25 ቀን በየከተሞቹ በበርካታ ቦታዎች በብርቱካናማ ቀለም እንዲያሸበርቅ ተደርጎ በየአመቱ በአለም አቀፍ ደረጃ የተግባር ቀን ተበሎ እየተከበረ የሚገኘው? መሰረቱስ ምንድን ነው? የሚሉት መሰረታዊ ጥያቄዎች መነሳታቸው ስለማይቀር ታሪኩን በአጭሩ ማቅረብ አግባብነት ያለውና አጠር ባለ መልኩ መዳሰሱ መልካም ነው። በተለያዩ ታሪካዊ ድርሳናት ውስጥ እንደሚገለፀው አፅኖዖት ተሰጥቶበት በዋቢነት የሚጠቀሰው በላቲን አሜሪካ በምትገኛዋ የዶሚኒካን ርፑብሊክ ወታደራዊና ፋሺስታዊ አገዛዝ በሰፈነበት በ1960 ዓ.ም. ወቅት የትሩጂሎ አምባገነን አገዛዝን ይቃወሙ ከነበሩት የቤተክርስቲያን ምዕመናን ሚኔቫ፣ ፓትሪያና ማሪያ ቴሬዛ ሚራባል ስም ይጠሩ የነበሩ ሴት አገልጋዮችን ምንም እንኳ ከእስር ለጊዜው ቢፈቱም የታሰሩትን የቅርብ ዘመዶችና የትግል አጋሮቻቸውን ለመጎብኘት ወደ እስር ቤቱ በሄዱበት ወቅት በማን አህሎኝነት መልሶ በማሰር፣ በእጅጉ ለኃይል ጥቃት ዳርጎና በስተመጨረሻም በኖቬምበር 25 ቀን እጅግ አሰቃቂና ዘግናኝ የሞት ግድያ ተፈፀመባቸው። ይህንን የግፍና የበደል በደል የሆነ ድርጊት የአንደኛዋ እህት እስከ እለተሞቷ 2014 ዓ. ም ተረስተው አንዳይቀሩና የገድል ታሪካቸው የሚታወስበት አንድ ትንሽ ቤተ መዘክር በማዘጋጀት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም የስብአዊ መብት ጥያቄ የሚያንገበግበው ሁሉ መንፈሳዊ ፅናት የሚያገኙብት፣ እቅፍ አበባ የሚያስቀምጡበት፣ መሰል ታሪክ ካላቸው ጋር አብረው በጋራ ተመክሮ የሚለዋወጡበት፣ ደብዛቸው የጠፋን የሚያስታውሱበት፣ ቀሪ ዘመድ የሚጽናናበት የተቀደሰ ቦታ እንዲሆን የታቀደ ሂደት ብቻ ሳይሆን በተጓዳኝም በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ማናቸውንም የኃይል ጥቃቶች ለመቃወምና ብሎም ለማስወገጃ በአንቂንት መገልገያ እንዲሆን ታስቦ በመወሰኑ ነው። የነዚህ ሶስት ንቁ የመብት ተማጋቾችና የበርካታ የአገዛዙ ተቃዋሚዎች ሰቆቃ፣ የተከሰከሰው አጥንታቸውና የፈሰሰው ደማቸውም ከንቱ ሆኖ ግን አልቀረም። ለ 30 አመታት የዘለቀውና ከ 30 000 በላይ ዜጎችን ለእልቂት የዳረገው የአምባገገን አገዛዙ መሪ የነበረው ትሩጂሎ ቀኑን ጠብቆ በመኖሪያው አካባቢ በሜይ 1961 ዓ.ም በጥይት ተኩስ ተደብድቦ ሕይወቱ እንድትጠፋ መደረጉ የታሪክ ዘገባዎች የሚገልፁት ናቸው።

 

በሴቶች ላይ እየተደረገ የሚገኝ የኃይል ጥቃት በብዛት የሚደረጉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲሆኑ መሰረታቸውም በፆታዎቹ ማለትም በወንድና ሴት መካከል የመብት መዛባት በመኖሩ ምክንያት የሚከሰቱ ናቸው። የሴቶችን አካላዊና ማህበራዊ ጤንነት የሚጎዳ ውጤቱም በልጆቻቸው ላይ ሳይቀር የሚከሰት፣ በሕብረተሰቡ ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባውን ማህበራዊ ተሳትፎና የኑሮ እድላቸውን የሚገድብና የሚያኮላሽ ነው። በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚካሄድ የኃይል ጥቃት በመላው አለም የተስፋፋና በማናቸውም ማህበራዊ ክፍሎች የሚታይ ነው። በመሆኑም በቸልታ የምንመለከተው ጉዳይ ሊሆን አይችልም።

 

ማህሳ አሚን የቀብር ስርአት በትውልድ አካባቢዋ

ሌላው ከፍተኛ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ በዚህ ፅሁፍ አቅራቢ እምነት ከላይ ከተገለፀው ጋር ተመሳሳይነት ያለው ከሴፕቴምበር 19 ቀን 2022 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ በኢራናዊያን ሴቶች ግንባር ቀደምትነት ያለማቋረጥና መጠነ ሰፊ የሕይወት መስዋዕት እየከፈሉ “አገዛዙ ይውደም” “አንስታይነት፣ ሕይወትና ነፃነት“ የተሰኘ መርሃ መፈክራቸውን አንግበው በአገዛዙ ላይ ያላቸውን ፍፁም ጥላቻ በማሰማት እያደረጉ ያሉት የተቃውሞ እንቅስቅሴ በአለም አቀፍ ደረጃ በደማቅ ሁናቴ እየተስተጋባ ይገኛል። በቅርቡ ካታር በተዘጋጀው የአለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድር ወቅት በዲያስፖራ የሚኖሩ ኢራናዊያን በካታር ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የአውሮፓና የአሜሪካ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ ለሰላም ወዳድ ኃይል “ለትግላችን ድምፅ ሁኑልን” እያሉ የሚያስተጋቡት የጥሪ መልዕክት በወቅቱ በሀገራቸው ያለውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ስፋትና ጥልቀት ለማፈን አገዛዙ እየወስዳቸው ያሉ እጅግ የጭካኔ ድርጊቶቹ የራሱን አረመኔነት ብቻ ሳይሆን የጥሪያቸው አግባብነትን የሚያመላከት በመሆኑ ልዩ ዋቢ መጥራት የሚያሻው አይሆንም።

 

የወቅቱ የተቃውሞ ግለትና ስፋት ከላይ እንደተገለፀው አይነት መሆኑን የሚያመላክተው ደግሞ የ 22 አመት እድሜ የነበራት ጂና ማህሳ አሚኒ (Jina Mahsa Amini) የፀጉር መሸፈኛ ፎጣ (ሂጃብሺን) በአግባቡ አልተጠቀምሺም በሚል ተልካሻ ምክንያት በአገዛዙ የግብረገብ ደህንነት ጠባቂ አባላት ተይዛ ለእስር ከዳረጓት ከሶስት ቀናት በኋላ ሕይወቷ በማለፉ እንደሆነ በተለያዩ የዜና አውታሮች መገለፁ ይታወሳል። ሆኖም የግብረገቡ ድህንነት ተቋምም ሆነ አገዛዙ በማህሳ አማኒ ላይ ምንም አይነት ሕገወጥ ጥቃት አልፈፀምንም ብለው በደም የተጨማለቀ እጃቸውን ለማጠብና ስቃይ ከተሞላበት አሰቃቂ ድርጊቶቻቸው ራሳቸውን ነፃ ለማድረግ ቢጥሩም ከቅርብ ዘመዶቿም ሆኑ ከጤና ሕክምና አባላት የተገኘው መረጃ ሌላ ሆነ በመገኘቱ እስካሁን በሴቶች ግንባር ቀደምትነት እየተካሄደ ለሚገኘው የተቃውሞ እንቅስቃሴ በክብሪት ጫሪነትና የትግሉን ችቦ አብሪ ሆና መሰያሟ ብቻ ሳይሆን ላለፉት 40 አመታት ውስጥ ውስጡን ሲቀጣጠል የነበረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ግፍን የሚፈራ ሳይሆን የሚጠየፍ፣ ፍርሃትን ያሸነፈና ድፍረትን የተላበሰ፣ ነፃነትን ያልተላበሰ ሕይወትን የናቀና የሞትን ፅዋ በፀጋ በጀግንነት ለመቀበል የቆረጠ አዲስ ትውልድ በመፈጠሩ የአገዛዙ መረን የለቀቀ አፈና፣ እስራትና ግድያ

 

ሳያስበረግጋቸው እንቅስቃሴያቸው “ስር ነቀል አብዮት” የሚል ሥምን ተከናንቦ ይኸው ይህ መጣጥፍ እስከተዘጋጀበት እስከዛሬ ድረስ አገዘዙን እያናወጠ ይገኛል። በተወሰኑ የአገዛዙ ንቁ የተቃውሞ ተሳታፊ በሆኑት ላይ የሞት ቅጣት አስወስኖ ተግባራዊ ማድረጉና ለአቅመአዳም ያልደረሱ ወጣቶችን የበርካታ አመታት የእስር ፍርድ አገዛዙ ቢያስወስንባቸውም በትግላቸው ወደፊት ከመጓዝ እንዳላገዳቸው በቅርቡ የወሰኑትና ተግባራዊ እያደረጉት ያሉት የሶስት ቀን የሥራ ማቆም እርምጃ ይህንኑ ፅናታቸውን የሚያረጋግጥ እንደሆነ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች የሚጋሩት ነው። በአጠቃላይ የስራ ማቆም አድማ በርካታ የንግድ ተቋማት ሱቆቻቸውንና መደብሮቻቸውን በመዝጋት የአድማው ተካፋይነታቸውን እያረጋገጥ ይገኛሉ። በኢራናዊያን አገላለጽ ሥር ነቀል አብዮታዊ ትግላቸው እስካሁን ድረስ በተደረገው የተቃውሞ እንስቃሴ ከ470 በላይ የሚሆን የሰው ሕይወት መቀጠፉ ይነገራል። የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ይህንን አጋጣሚ በምክንያትነት በመውሰድ ለኢትዮጵያ የተማሪዎች የትግል እንቅስቃሴ ደጋፊና ተባባሪያችን የነበሩትንና በአገዛዙ የተገደሉትን ወጣት ኢራናዊያንን እያስታወሰና እየዘከረ የቀረበውን ጥሪ “ማህሳ አሚኒን ልጄ፣ እህቴ፣ እናቴ” ብሎ በመጥራት የትግል አጋርነቱን ለኢራን ታጋይ ሴቶች ያደርሳል። በርቱ ተበራቱም እያለ መልካም ምኞቱን ይገልፃል።

 

ውደተነሳሁበት የወቅቱ ርዕስ ሳተኩር ብርቱካናማ ቀለም የሚያመለክተው ሴቶችና ሕፃናት የኑሮ ሕይወታቸውን የትኛውም የኃይል ጥቃት ሳይደርስባቸው የወደፊቱን ብሩህ ተስፋቸውን የሚያበስሩበት፣ የህብረተሰቡ አባላት የርስ በርስ ግንኙነታቸው በመከባበርና ስለ ሰው ፍጡር ስላላቸውና ለሚኖራቸው እሴታዊ ማንነት በማወቅና በመከባበር ላይ የተመሰረተና እንዲሁም በህብረተሰቡ ውስጥ በሴቶች ላይ ሰፍኖ የሚገኘውን ማናቸውንም የፆታ ጥቃት ትኩረት አግኝቶ መፍትሄ እንዲሰጠው ለቅስቀሳ፣ ለማስገንዘቢያና ለማነቃቂያ እንዲያገለግል ታስቦ የተወሰነ ለመሆኑ በርካታ ጥናቶች ይገልፃሉ። ከ 2008 ዓ.ም ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፅህፈት ቤት አቀናባሪነትና በሴቶች ግንባር ቀደምትነት “በሴቶች ላይ የሚደረግ የኃይል ጥቃት እንዲቆም በጋራ እንነሳ” UNITE to End Violence against Women“ በሚል በሴቶች ግምባር ቀደምትነት የተለያዩ “አለምን ብርቱካናማ እናደርግ“ „Orange The World“ በሚል መሪሃ መፈክር በተደረጉ ቅስቀሳዎች ሳቢያ ዳብሮ ለመውጣት የቻለ ሃሳብ እንደሆነም የሚገልፁ አልታጡም።

 

ለማንኛውም በሴቶችና በሕፃናት ላይ እየደረሰ የሚገኘውን የኃይል ጥቃት በመቃወም የሚንቀሳቀሱ በርካታ ለስብአዊ መብት መጠበቅ ተከራካሪና ታጋይ የሆኑ ሕዝባዊ ድርጅቶች ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ ቀኑን ለመዘከር በርካታ እንቅስቃሲዎች ማደረጋቸው የሚታወቅ ነው። ከ 1991 ዓ.ም. በአለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ አካባቢዎች የሴቶች ጥያቄ የሰብአዊ መብት እምብርት መሆኑ ታውቆ በተግባር ሊተረጎም ይገባዋል ብለው በሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ሕዝባዊ ድርጅቶች ቀኑን የሚያስታውሱትና የሚያከብሩት በመሆኑ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢም የነፃነት መብታችንን ለመጎናፀፍ የምናደርገው እልህ አስጨራሽ ትግል ያለ ሴቶች ትግል ተሳትፎ የናደርገው ገድል የተሟላ አይሆንም የሚል ፅኑ እምነት ያለው በመሆኑ የቀኑን ተገቢነትና ወሳኝነትን በርካታ ዜጎቻችን ይህንን አውቀውና ተገንዝበው በሴቶችና ሕፃናት ላይ እየተደረገ የሚገኘውን የኃይል ጥቃት በፅኑ በመቃወም ድጋፋችንን አብረን በጋራ ሳናለሰልስ እንድንገልፅ፣ እንድናበረታታ የከበረ ጥሪውን ያቀርባል።

 

የተግባራችን፣ የእንቅስቃሴያችን ከፍታ ትርጉምና ዋጋ ሊኖረው የሚችለው የፆታ፣ የብሄር፣ የኃይማኖት፣ የምንከተለው ርዕዮተ አለም፣ የእድሜም ሆነ የፍተወተ ሥጋ ዝንባሌያችን ሳይለያየን ወይንም ደግሞ የማህበራዊ መሰረታችን(ሃብት፣ ዘር) ከግምት ሳይገባና ምንም አይነት ልዩነት ሳይደረግ በብዙሃንነታችን ላይ የሚመሰረት የራሳችንን የወደፊት እጣ በራሳችን ለመወሰን የሚያስችለን ከበባዊ ለመመስረት ተደራጅቶ ከመታገል ውጪ ሌላ አማራጭ የሌለው መሆኑ ለሕዝብ ቀናኢና ሀገር ወዳድ የሆኑ ማንኛቸውም ኢትዮጵያዊ ኃይላት በሙሉ ተገንዝበው በአፅንዖት ትግሉን በመቀላቀል ከግብ እንዲደርስ ያለመታከት አስተዋፅዖ ስናበረከት ብቻ ነው። ሰላምም ሆነ እኩልነት፣ ነፃነት ከተላበሰ የመብት መከበር ውጭ የሚገኙ አይደሉም። ሰላምም ሆነ ነፃነት በልመናና በፀሎት ወይንም ደግሞ በስጦታ ከአምባገነን አገዛዞች የሚቸሩ ሳይሆኑ ተጨምድደው ከተያዙበት እጄታ በግዴታ ተፈልቅቀው የሚነጠቁና ከተፈጥሮ ባለቤቱ ከብዙሃኑ መዳፍ ውስጥ በመልካም እሴትነታቸው እየተከበሩና እንክብካቤ የሚቸራቸው ናቸው። መሰረታዊ ለሆኑ የሕዝብ ጥያቄዎች ምክንያት የሆነ አገዛዝ ከስረ መሰረቱ ሳይወገድ፣ ሕዝብ የሚተዳደርበት ሕገ መንግሥት ለራሱ በራሱ ባልመሰረተበት፣ የአማራ ሕዝብ ተለይቶ በጠላት የተፈረጀበት የፖለቲካ አምድ ባልተወገደበት ጨርሶውኑ ለሌላው የመኖር ዋስትና ተደረጎ የሚወሰድበት ፖለቲካ ስፍኖ በሚገኝበት፣ የሕብረተሰቡ ግማሽ አካል የሆኑት ሴቶች መብታቸው ያለገደብ ባልተከበረበት፣ የተረጋጋና ለማህበራዊ እድገት መሰረት የሚሆን ከበባዊ ባልተጣለበት ሰላም ይገኛል፣ ይገነባል ብሎ ማለም ራስን በማታለል ሌላውን ለማወናበድና ለአምባገነን አገዛዝ በረግረግነት ለማዘጋጀት ያለመ አሳሳች የሆነ ትርጉም የለሽ ቅዠት እንጂ ሌላ አይሆንም። ሰዉ በማንነቱ በጅምላ ተገድሎ፤ በየጥሻው የሚቀበርበት፣ በተለያዩ የወንጀል ተግባር አቀንቃኞችና ፈፃሚዎች ለፍርድ ሊቀርቡ በማይቻልበት፣ ፍትህ ደብዛዋ ጠፍቶ አድሎአዊነት በነገሰበት፣ ፍርሃትና ጭንቀት በሰፈነበት ከባቢ ምን አይነት ሰላም እንደሚረጋገጥ የሚያውቁት በሹመኛው የበላይነት ባለው አገዛዙና የሱ አፈቀላጤዎች ብቻ ናቸው።

 

ፆታን የተመረኮዘ የኃይል ጥቃትን ለማስወገድ ዜጎች የተለያዩ የጥቃትን አይነቶችንና መሰረታቸውን እንዲሁም የተቃውሞና የመፍትሄ ስልቶችንም ጨምሮ በቅጡ ማወቅና መገንዘብ የሚጠበቅ ነው። በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚደርግ የኃይል ጥቃት “የሴቶች ችግር” ሳይሆን የሁሉም የፆታ ጥያቄ ነው። “ነፃነት አንስታዊነትን የተላበሰ ነው” ተብሎ የሚገለፀው አለምክንያት አይደለም። ወንዶች ሴቶች ለነፃነታቸው መከበር በሚያደርጉት እልህ አስጨራሽ ትግል ከጎናቸው ሊቆሙና ትግላቸውን በሁለመና መልኩ ሊተባበሯቸውና ሊያግዟቸው የሚገባ መሆኑን አፅንዖት ለመስጠት እንጂ ለሌላ አይደለም።

 

ተደጋግሞ በበርካታ ጥናታዊ ፁሁፎች እንደተገለፀው የኃይል ጥቃት ሲባል በሴቶችና ሴት ሕፃናት ልጃገረዶች ላይ የሚሰነዘር የአካልና የመንፈስ፣ የስነልቦና ጉዳት አስከታይ ድርጊት ብቻ ሳይሆን በፆታ እኩልነት መብት ባለመኖር ላይ የሚመሰረት የበደል ክስተት ነፀብራቆችን ጭምር የሚያጠቃልል ነው። ተፈፅሞ የሚገኘውም የጊዜ ገደብ ሳይኖረው በማንኛውም ማህበራዊ ግንኙነቶች እየተስተናገዱ በሚገኙበት አደባባዮች፣ በመኖሪያ ቤትና፣ በሥራ ቦታ የሚስተዋሉ ናቸው። ጥቃቶቹ በሰውነት አካልና መንፈስ ላይ ሲከሰቱ የሚጀመር ሳይሆን በማስፈራራት፣ አንገትን የሚያስደፋ አስፀያፊ ተግባራት በመከወን ስድብን በማሽጎድጎድ፣ በተለያዩ ደረጃዎች ነፃነታቸውን በመጋፋት በቁጥጥር ሥር ማዋል፣ ለሴተኛ አዳሪነት መገደድ፣ ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ ሕፃናትን ለጋብቻ መዳረግ፣ የኑሮ እድገትን ማሰናከል፣ ለዘመናዊ ባርነት መመልመል፣ ግፊትና ጫና ማሳደር፣ በኃይል አስፈራርቶ ማገትና ለክፉ ድርጊት መዳረግ፣ ጨለማን ተገን አድርግ ጠልፎ መያዝና መሰወር፣ ማታለል፣ ማጭበርበር፣ በደካማዎች በተለይም በአካለ ስንክሎች ላይ ኃይልን ባልተገባ ሁናቴ መጠቀም፣ ለተዛባ የሥራ ግንኙነት መዳረግም ለወንጀል ተግባር ማስገደድ፣ ግላዊ ነፃነት በስውር መገደብ፣ የቤተሰቤ ክብር ተነካ፣ ተደፈረ በሚል ሳቢያ ህይወትን እስከ ማጥፋት የሚደርስ ድርጊቶች እንዲፈፅሙ ጫናና ግፊት ማድረግ፣ እነዚህ ሁሉ የኃይል ጥቃት ነፀብራቆች ናቸው። ወላጅ እናቶች በልጆቻቸው ፊት የአካልና የመንፈስ ስብራት የሚያደርስ ጥቃት ሲደርስባቸው ለመመልከት የተገደዱ ልጆቻቸውም በእድገታቸው ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የተረጋጋ ሕይወት ለመምራት እንኳ ጋሬጣ እንደሚሆንባቸው በመስኩ መጠነ ሰፊ ምርምርና ጥናት ያደረጉ ሊቃውንቶች በየጊዜው የሚያረጋግጡት ናቸው። በመሆኑም በሴቶችና ሕፃናት ላይ እየተደረጉ ያሉት ማናቸውም አይነቶች የኃይል ጥቃቶች ምንም አይነት የተገቢነት መሰረት የሌላቸው፣ አሰቃቂነት የተጠናወታቸው ድርጊቶች በመሆናቸው ሊወገዙና ሊወገዱ የሚገባቸው ናቸው።

 

ለዚህም ነው ብርቱካናማ ቀን ሲታሰብ የኃይል ጥቃት “አሁኑኑ በአስቸኳይ ይቁም” በሚል መርሃ ግብር እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች ለሴቶች የመብት ትግል ድጋፍ የሚሰጥበትና ለዚህ ስኬታማነት የራሳቸውን አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ የታለሙና አፅንዖት የተላበሱ ጥሪዎች እየተደረጉ የሚገኙት። ማንኛውም ሕብረተሰብ የሚመዘነው ለራሱ በሚሰጠው ግምት ሳይሆን ለዜጎቹ በተለይም ግማሽ አካላቱ ለሆኑት ሴቶች መብታቸውን ለማስጠበቅና ለማስከበር በሚያደርገው መጠነ ሰፊ ጥረት እንዲሁም የነፃነት መብታቸውን ያለምንም ገደብ ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ወርዱንና ስፋቱን በተለይም ጥልቀቱን አስመልክቶ የሚወስዳቸው በተለያዩ ተግባራቱ የሚመዘን እንደሆነ በመስኩ በርካታ ጥናታዊ ምርምር ባደረጉ ምሁራኖች ተበክሮ የሚገለፅ ነውና ይህንን ጥሪ በየትኛውም ባለንበት ቦታ በግለሰብም ይሁን በቡድን በማስተጋባት ለሴቶች ትግል ፍፁም የሆነ ድጋፋችንን በማንኛውም መልኩ እንግለፅ በማለት አበቃለሁ። ከአለም አቀፉ መድረክ ወጥተን ትኩረታችንን በወቅታዊ የሀገራችን ሁናቴ ላይ በማድረግ ሴት ጀግኖቻችንና የተመክሮ አርአያ ሆነው የተለዩንን ሴት ንቁ ታጋዮችን የምንዘክርበትና የምናስታውስበት ቀን “የ 16 ቀናቱ የተግባር እንቅስቃሴ” ማሳረጊያ የሆነው ዲሴምበር 10 አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ቀን ከጥቂት ቀናት በኋላ ስለሚከበር ልዩ ትኩረት በሴቶች ጥያቄ ላይ በመስጠት “የት ነበርን፣ የት ደርሰናል፣ ወደፊትስ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል” የሀገራችን የወቅቱን ሁናቴ በስፋት ለመዳሰስ እስከምንገናኝ ድረስ መልካም ንባብ ለአንባቢያን እመኛለሁ።

 

ያለ ሴቶች መጠነ ሰፊ ተሳትፎ ትግላችን ግቡን አይመታም!!

የኢትዮጵያ ሴቶች የትግላችን ምሶሶ ናቸው!!

ትግላቸው መከበሪያችን፣ የጀግንነት መሰረታችን ነው!!

በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደረግ የኃይል ጥቃት ይወገድ!!

 

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/178078

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...