Thursday, December 8, 2022

ገዳይ ወይስ ሸምጋይ !
እኛ ኢትዮጵያዉያን የዋህ አይሉን አስተዋይ በሌላዉ ሞት የምንሰነብት የሚመስለን “ምሽትም ዕድሜ ነዉ ” በማለት በከንቱ ራስ ወዳድነት እና መዘናጋት በሬ ካራጁ በደመ ነፍስ ስንኖር ድፍን ሶስት አሰርተ ዓመታት ባጅተናል፡፡

ዛሬ ላይ ከ፴(ሰላሳ) ዓመት በኋላም ከነበረዉ መከራ አለመማር ምን ያህል አለመኖር መሆኑን መረዳት አለመቻላችን እንደ ሠዉ ተፈጥረን  ሠዉ ሳንሆን ሠዉነት እና ሠባዊነት እየናፈቀን እንገኛለን ፡፡

ለሶስት አሰርተ ዓመታት  ለብሄራዊ አንድነት እና ለኢትዮጵያዉያን ህልዉና አደጋ መግባት ምንጩ ህገ-ኢህአዴግ ፣ በለዉጥ ስም ተባይ እና አድርባይ አለሁ ባይ መገላበጥ ፣ በጦርነት  የፓለቲካ ንግድ ማስረፅ፣ በዜጎች ማንነት ላይ የተካሄደዉ እና እየተካሄደ ላለዉ ሠባዊ እና ተፈጥሯዊ መብት ጥሰት፣ የዘር ፍጂት ፣ ብሄራዊ ክህደት እና ምዝበራ ተካሂዷል ፡፡

ይሁንና ይህን ሆነን ሳለ ስንሞት ገዳይ እንዲደርስልን አቤት ማለታችን ለደንቆሮ ማጨብጨብ ሆኖ የሚጠይቅም ሆነ የሚጠየቅ አካል አለመኖር ነዉ ፡፡

የህግ  እና የመንግስት ድረሱልን ጥያቄ ከድፍን ሶስት አስርተ ዓመታት የነበር እና ግን  የስቃዩ ገፈት ቀማሽ የሆነዉ ኢትዮጵያዉያን በተለይም ብዙኃኑ ዓማራ በህገ-ኢህአዴግ እና በነበረዉ አግላይ የፖለቲካ ስሪት  በጥላቻ እና በስጋት እንዲፈረጁ እና እንዲፈጁ ማድረጉን መርሳት ከስህተትም በላይ በሞት መፅናናት ነዉ ፡፡

በኢትዮጵያ ላይ በዳይ እና አግላይ የህግ እና የፖለቲካ መሠረት መሆኑን ለመገንዘብ ምንም አይነት ማረጋገጫም ሆነ ጠንቋይ መቀለብ የሚጠይቅ ሳይሆን በየትኛዉም ዓለም እና የሰዉ ልጆች ታሪክ አገርን እና አንድን ህዝብ በጠላትነት የመመደብ ሴራ ከ1968 ዓ.ም. የጥፋት ኃይሎች ስምምነት በህግ እና በፖለቲካ ጥላ ሆኖ ዛሬም ለነበረዉ ዘር ፍጂት ፣ ምዝበራ ፣ ብሄራዊ ቁዉስ  እና ሁሉን አቀፍ ዉድመት ሆኖ የጥፋት እና ፍጂት ቀጣይ ሆኗል፡፡

በኢትዮጵያችን ዕዉነተኛ ብሄራዊ አንድነት እና ሉዓላዊ ክብር የሚመጣዉ ዕዉነተኛ እና በፍትህ ላይ የተመሰረተ የህዝብ እና የአገር ጠላቶችን በህግ ስም  በጥላቻ ፖለቲካ ዋሻ ከተዉ የሚገኙትን ከነዋሻቸዉ ማፍረስ ሳንወድ የምንቀበለዉ መሪር ሀቅ ነዉ ፡፡

በኢትዮያ ጥላ ስር ተወሽቆ እና ሸምቆ የሚገኝ ኢትዮጵያ ጠል ተባይ እና አድር ባይ ሆኖ እያለ የዚህችን አገር ምስቅልቅል ከማስቀረት ይልቅ ከምስቅልቅል ወጥመድ ከመግባት አልዳኑም ፤አላዳኑም ፡፡

ኢትዮጵያ እንደ አገር ፤ህዝቧም እንደ ህዝብ ለመኖር አንዱን ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ በማግለል እና በመበደል ሳይሆን ኢትዮጵያን በተለይም ዓማራ መንቃት፣ መደራጀት ፣  ህብረት እና አንድነት መጠናከር ለመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት እና ሉዓላዊነት መቀጠል ወይም መነጠል እንደሆነ ቢመረንም የምንቀበለዉ ነዉ ፡፡

ከዚህ ዉጭ ለሠላሳ ዓመት አግላይ እና ፈንጋይ በሆነ ሴራ እና የክህደት ስራ መሠረት ከሆነ የፖለቲካ እና የህገ-ኢህአዴግ ስርዓት መፍትሄ ወይም ድህነት መሻት ገዳይ ሸምጋይ(ዳኝነት) ከድንቁርና በላይ የሞት  ሞት ነዉ ፡፡

ዛሬ ላይ ሆነን ከሠላሳ ዓመት በፊት የነበረዉን የቁራ ጩኸት የህግ ….የመንግስት ያለህ ማለት  የብድ ገላጋይ እንደመጋበዝ ካልሆነ በቀር እንዴት የሌለ ከሌለ ሊገኝ ወይም ሊመጣ ይችላል ፡፡

ያልነበረ እንደነበር አድርጎ ድረስልን ማለት ዛሬም ከህልም ዓለም አለመዉጣታችንን እና በዕዉን አለመኖራችንን የጨለማ እና የመከራ ጥላ መኖራችንን የሚያሳይ ነዉ ፡፡

“ለነፃነት እና ህልዉና ብቸኛ መሰረት በዕዉቀት  እና አንድነት የሚቆም ኃይል ነዉ ፡፡”

አንድነት ኃይል ነዉ !

Allen Amber!
https://amharic-zehabesha.com/archives/178115

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...