Monday, October 3, 2022

እዌጥና ለዛቲ ጦማር በስመ ሥሉስ ቅዱስ - ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ
ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ/ም

“ሰው መላክ አይሆንም”

“ሰው መላክ አይሆንም” ያለቸው ኑሮዋን በዘመዶቿ ይሁንታና ምርቃት ላይ ለመመሥረት ተመኝታ ምኞቷ ያልተሳካላት አንዲት ኢትዮጵያዊት ወጣት ናት፡፡ ወጣቷ ካፈቀረችው ጋራ የትዳር ሕይወት ለመመስረት ወሰነች፡፡ ብትወስንም በባህሏ ያለወላጆች ምርቃት ትዳር አይመሠረትምና የወላጆቿን ፈቃድ ለማግኘት ፍቅረኛዋን ወደወላጆቿ ቄስ እንዲልክ መከረችው፡፡

ወላጆቿ ራሳቸውን ካካባቢው ሕዝብ አልቀው የሚመለከቱ ትቢተኞች ነበሩና የሕይወቷ ተካፋይ እንዲሆን የመረጠችውን አልተቀበሉላትም፡፡ ቄሱ በእውቀታቸው ከወላጆቿ የተሻሉና የላቁ ናቸውና ራሳቸውን አብልጠው በማየት ሌላውን የሚንቁትን ወላጆቿን በተልእኳቸው መክረው አስተምረው የትዳር ሕይወቷን መሰረት ያሲዙልኛል ብላ ጠብቃ ነበር፡፡ እንደጠበቀችው አልፈጸሙላትም፡፡ ቄሱ እምነትም ትምህርትም ብቃትም እንደሌላቸው ተረድታ የነበራትን እምነትና ተስፋ በራስ ብርታት ብቻ ላይ እንዳለ ተገነዘበችና፦

“በርታ እንግዲህ ጓዴ ቢሆንም ባይሆንም ሰው ቢማር ቄስ እንጅ፤ ሰው መላክ አይሆንም” ብላ በኅብር ቅኔዋ ፍቅረኛዋን መከረችው፡፡ ይህም ማለት በቄሱ ላይ የነበራትን እምነትና ተስፋ ከቄሱ ላይ አንስታ የሕይወቷ ተካፋይ እንዲሆን ወደ መረጠችው ሰው ህሊና አሻገረችው፡፡ ሰሞኑን በሰፊው ሲወራ የሰማሁት የፋኖ ዘመነ ካሴ መታሰር በዚህች ልጅ ቅኔ ውስጥ ተሰበሰቦ የታሸገውን እምቅ ምሥጢር እንድከፍተው አስገደደኝ፡፡ ፋኖ ዘመነ ካሴ ከምንግሥት ጋራ እንዲታረቅ በቄሶችና በአገር ሽማግሎች ተይዞ በውይይት ላይ ሳለ መንግሥት ቄሶችን ተጥቅሞ አሰረው እየተባለ በሰፊው ይነገራል፡፡ በተቃራኒው ሊዝናና ወደ ባህር ዳር መጥቶ ሲዝናና ሲያድነው የነበረው መንግሥት በጠቋሚ አግኝቶ አስረው የሚል ወሬም ይሰማል፡፡

እንደምንሰማውና እንደምንረዳው ያለንበት ዘመን እውነት ፍትሕ ርትዕ የተደመሰሱበት ሰባዊ ሕሊና የተሰረዘበት የመገናኛ አውታሮችና ሕዝባውያን አምራሮች ዝቅተኛ ሞራል ባለቸው ሰዎች እጅ የወደቁበት ነው፡፡ ለገንዘብ የሰከሩ ሰወች ለገንዘብ ሲሉ ብቻ የሞተውን ሬሳ ሳይቀር የጠሉትን ሲወጉበት፤ የወደዱትን መደገፊያ ሲያደርጉ እየታየ ነው፡፡ ከሟቹ ቤተሰብ ይልቅ እጅግ የተጎዱና በሀዘኑ እንደተጠቁ ለመምሰል ራሳቸውን ሲብለጨልጩበት እየታዩ ናቸው፡፡

 

“ጅብን ሲወጉ ባህያ ይጠጉ” እንደሚባለው የጠሉትን በማይወደደው በጅብ እየመሰሉ ብንግግራቸው ለመውጋት፡ ድንገተኛና አስደንጋጭ ነገር የተከሰተብን እየተጠጉ የመውጊያቸው መሸፈኛ በማድረጋቸው እየተተቹ ናቸው ፡፡

የፋኖ ዘመነ ካሴ ጉዳይም በዚህ ጥልፍልፍ ውስጥ ገብቶ መካሰሻና መወቃቀሻ ሆኗል፡፡ ምክንያቱ በመንግሥትና ባሸማጋዮች ደባ ወይስ በራሱ ስሕተት በየትኛው እንደሆነ ስለማላውቅ ማንንም ከመውቀስ ተቆጥቤ ከሁለት ታላላቅ መምህራን ከሲራክና ከጳውሎስ ምክር ሳልርቅ ክስተቱን ብቻ ለመግለጽ እሞክራለሁ፡፡ አሳልፎ መሰጠቱ ዛሬ በዘመነ ካሴ ባይፈጸምም ከዚህ ቀደም በቄስና ባሸማጋይ ተላልፎ መሰጠቱ ተደጋግሞ የተነገረ ስለሆነ በዘመነ ካሴ ላይ ተፈጸመ ተብሎ ቢነገርም የዘመኑን ውድቀት ስለሚገልጽ የሚያስገርም አይሆንም፡፡

ሲራክ ”ኢትሒስ ዘእንበለ ትህትት ጠይቅ ቅድመ ወድህረ ገስጽ“( 11፡6 ) መጀመሪያ እውነቱን ለማግኘት ጠይቅ ከመረዳትህ በፊት አትተች አትንቀፍ የሚለውን መመሪያ መከተል ተገቢ ነው፡፡ ሌላው ሐዋርያው ቅዱስ ጵውሎስ “ትጋታችሁ በእግዝዚአብሄር እንዲገለጥ እንጅ ስለ በዳዩና ተበዳዩ አልጻፍኩም”(2 ቆሮ 7፡12) እንዳለው፦ ተወቃሹና ተከሳሹ ማን እንደሆነ ስላልተገለጸ ክስተቱን ብቻ ግለጥ እንጅ ስለበዳይና ስለተበዳይ ከመግለጽ ተቆጠብ፡፡

በዚህ መርሆ የልጅቷ ቅኔ ከራሴ ጀምሮ በዚህ ዘመን ያለነውን ቄሶች ነን፡፡ ምሁራን ነን፡፡ ልሂቃን ነን፡፡ የምንለውን ሁሉ ያጋለጠ መሆኑን ለመግለጽ እሞክራለሁ፡፡ ባለ ቅኔዋ በባህላችን ቄሶች የተማሩ የሞራል ሰወች ይልቁንም ለእግዚአብሔር ቀራቢወች የማይዋሹ ናቸው ብሎ ከሚያምነው ሕዝብ ጉያ የፈለቀች ናት፡፡ በቄስ ባገር ሽማግሌ የተያዘ ጉዳይ በፍትህ በርትዕ በሰላም በምህረት ያልቃል ተብሎ ይታመናል፡፡ ይህ ክቡር የሆነ ታላቅ ቅርስ ኢትዮጵያ የተዋቀረችበት መሠረቷ እንደሆነ ስለ ኢትዮጵያ በተነገረበት አደባባይ ሁሉ ተነግሯል፡፡ ታሪኳ በተጻፈበት ሁሉ ተጽፏል፡፡

ይህን ቅርስ ወያኔወችና ከወያኔ የተወለዱት ድርጅቶች ቢክዱትም፤ ኢትዮጵያውያን ሁሉም የሚጋሩት ነው፡፡ ይበልጡን የሞራል የባህልና የስነ ጽሑፍ ምንጭ ናት ተብሎ በሚነገርላት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ደጀ ሰላም ያደገ የእኔ ቢጤ የሚገጥመኝን ሁሉ የምለካውና የምተረጉመው እሷ በቀረጸችው ጻሬሕሊና ነው፡፡ የልጅትንም ቅኔ የተረዳሁትና የተረጎምኩት በዚያው ንጻሬዬ ነው፡፡ አይሰለችህም ብትሉኝም በግፍ የተገደለ ሰው ስናይ በግፍ የገደለውን ቃኤልን ማንሳት ሰለችን እንደማይባል በወገን ላይ የተፈጸመውን ግፍ ባነሳንበት ሁሉ፡ ኦርቶዶክሱንና አማራውን ሰበርናቸው ያሉትን አቶ ስብሐት ነጋንና ገብረ ኪዳን ደስታን ማንሳት አይሰለችኝምና አሁንም አነሳቸዋለሁ፡፡

አቶ ስብሐት ነጋና ገብረ ኪዳን ደስታ ለብዙ አመታት በአማራው ኅብረተ ሰብ ላይ ማስጨፍጨፍ ከፈጸሙ በኋል፤ በ 2005 ዓ/ም ለሲኖዶስ እርቅ ከአሜሪካ በተላኩት ላይ አቶ ስብሀት ነጋ “እርቅ የሚሉ ሁሉ ይገደሉ” ብለው ያውጁትን ለመርሳት የሚያስረሳው ብሽታ አላጠቃኝም፡፡ ጀዋር አማራው መታረድ አለበት ብሎ ለኦነግ ሸኔወች ያቀረበውን ገጀራ በይደው ሞርደውና ስለው ለኦነግ ሸኔወች ያቀረቡላቸው እነ አቶ ስብሀት ነጋ ዓለም እስካትልፍ ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡ ባለቅኔዋ ተስፋዋን የገለጸችበትን የሕብረተሰቡን ትሥስር በጣጥሶ እንዳልነበረ ያደረግው በነሱ ተባርኮ ለኦነግሸኔወች የተሰጠው ገጀራ ነው፡፡

ባለ ቅኔዋ በዘመኗ የተከሰተውን የተመለከተችበት መነጽር ከኔ መነጽር ጋራ የሚመሳሰል ነው፡፡ ዓለምን የምተርጉመበት የኔ መነጽር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቀርጻ በህሊናየ የሰካቸው እየተማርኩ ያደኩባቸው የነብያት የሐዋርያትና የቀኖናው ስልት ናት፡፡

ለፍቅረኛዋ የሰጠችው ምክር ነቢዩ ኢሳይያስ “የደከሙትን እጆች አበርቱ የላሉትንም ጉልበቶች አጽኑ ፈሪ ልብ ላላቸው እነሆ አምላክችሁ በበቀል በእግዚ ብድራት ይመጣልና መጥቶም ያድናችኋልና በርቱ አትፍሩ በሏቸው”(ኢሳ 35፡4) ብሎ ለተጎዱትና ለተጠቁት የሰጠው ምክር ነው፡፡ ፍቅረኛዋ ለቤተ ሰቦቿ ትቢትና ትምክህት እንዳይንበረከክ “የትቢተኞችን ኃይል አውቃለሁ ቃላቸውን አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ነው እንጅ በቃል ብቻ አይደለም፡፡ ምን ትፈልጋላችሁ በብትር ወይስ በፍቅር ልምጣ”(1ኛ ቆሮ 4፡) ብሎ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለትቢተኞ ያቀረበላቸውን ምርጫ ነገረችው፡፡

አማላጅ ሆነው የተላኩት ቄሱ የመላኩን የቅዱስ ገብርኤልን ምሳሌ መከተል ይገባቸው ነበር፡፡ መላኩ ምክሩን ያልተቀበለውን ዘካርያስን ዲዳ እንዳደረገው ቄሱም የንስሀ ልጆቻቸውን ምክረው ገስጸው የንቀትና የትቢት ትጥቃቸውን ማስፈታት በተጋባቸው ነበር፡፡ ከግዚአብሔር የራቁ በመሆናቸው ተልእኳቸው ከሸፈባቸው፡፡ ራሳቸው የማይናገሩ ዲዳ በመሆናቸው መላኩ የሰራውን መስራት ስለተሳናቸው “ሰው መላክ አይሆንም” እንድትል አስገደዳት ፡፡ በዘመኗ ብዙ ምሁራን ነን ልሂቃ ነን የሚሉ እንደነበሩና፡ ቢኖሩም ከዘመኑ ቄስነት ተሽለው አለመገኘታቸውን ገለጸችው፡፡

እኔም በዘመኔ ሊቀ ሊቃውንት ነኝ፤ መላከ እገሌ ነኝ ፤ዶክተር እገሌ ነኝ፤ እያለ በህዝብ ፊት በተለይ በአውደ ምህርት ላይ የሚቆመውን እሷ በመዘነችባቸው ሚዛን ከመመዘን ባለማምለጤ ልቀበላቸው አልቻኩም፡፡ ይልቁንም “ቁራሽ እንጀራ እበላ ዘንድ ብር ለማግኘት ይረዳኛ ዘንድ መተዳደሪያ ይሆነኝ ዘንድ ካህን አርገኝ” (2ሳሙ፡36) ያለውን የገለጸ የብሉይ መምህር በጠፋበት ዘመን ይህን ቅኔ መቀኝቷ እጅግ ይገርመኛል፡፡

በዘመናችንስ ጵጵስናውን በገንዘብ የገዛ፡ በዝሙት የተከሰስና እነ ዮሐንስ አፈውርቅን እየዘለፈ መጽሐፋቸውን የክህደት መጽሐፍ ነው ብሎ ያውገዘበትን መጽሐፍ አሳትሞ ሸጦ የበላ፡ እንደገና ያንኑ ያወገዘውን ቅዳሴ በመጠቀም እየቀደሰ ገንዘብ የሚሰበስብ የበረከተበት ዘመን እንደሆነ በዓይናችን አይተናል፡፡ በግሌ የተቃውምኩበት ወቅት ነበር፡፡ አንዳን ጊዜ ሲነገር የሰማሁትንና እኔ ራሴ አይቼ የተቃውምኩት ስህተት ሰው ሁሉ ተቀብሎት ያላንዳች ሀፍረት ቀጥሎ ሳየው፡ ሁሉም ተስማምቶበት እንደመመሪያ አድርጎ ተቀብሎታል ማለት ነው? እኔ ብቻ ነኝ መቀበል የተሳነኝ? ብየ ከራሴ ጋራ እሟገታለሁ፡፡ ከሕሊናየ ክስ ነጻ መሆኔን ከሕሊናየ በቀር ምስክር ስለማልፈልግ አልጨነቅምና ከሕሊናየ ጋራ ብቻ እየተሟገትኩ እቀጥላለሁ፡፡

መጽሐፈ ቀኖናችን “እመ ቦ ዘየተሉ ኖላዌ እኩየ ሞቱ ክሱት በቅድሜሁ” (ፍ አእ 5፡139) እንዳለው ማለትም፦ “እየተነገረው እያወቀ ጠማማ መሪ የሚከተል ሕብረተሰብ ሞት ከፊቱ ቆሟል” ይላል፡፡ የራሱን ብርታት እምነትና ሞራል መጠቀሙን ትቶ የኔ ቢጤወችን ቄሶች የሚከተል ከሆነ ለደብዳቢ ላሳሪ ተላልፎ መሰጠት ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ ለነፍሰ ገዳዮችም ቢዳርጉት ሊደንቀን አይገባም፡፡

ለህዝብ ተላልፈው ለመሞት ለተዘጋጁት መንፈሳውያን ካህናት “ኦ አበዊነ ንቡራነ እድ ሥዩማን እለ መትለወ ሐዋርያት እስመ ነሣእናክሙ አስተብቋዕያነ ለነ ለኀበ እግዚአብሔር ውነሣዕናሆሙ በመዋዕሊነ ለነ ለኀበ እግዚአብሔር”(ቅ ማ ገጽ 164፡ 10) እንድንል በቀኖናችን ታዝዘናል፡፡ ማለትም ብቅርብም በሩቅም የተሰየማችሁ አበው ወደ እግዚአብሔር እንድትማልዱልን ተቀብለናችኋል” ይህን እንድንልላቸው የታዘዝነው የነቅዱስ ጳውሎስን ፈለግ ለሚከተሉት ለታማኞች አባቶች ቄሶች ነው፡፡

“የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እነሱ ናቸውና እግዚአብሄር ለረጅም ወራት ይስጠን ዘንድ” (ሥ ቅ ገ 41፡ቁ74)፡፡ የሚለውን ክፍል በሕዝቡ ፊት ቆመን የምናውጀውና ሕዝቡን አሜን እንዲል የምናደርገው በዚህ ዘመን ላለን እኔን ለመሳሰሉ አስደብዳቢወች አይደለም፡፡ ይህ ማለት እኮ ግፈኞች አርመኔወች በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጽሙት አፈና እስራት ግድያ ይቀጥሉበት የሚተባበሩት ቄሶችም ግፈኛውን በመደገፋቸው እንዲቀጥሉበት ለዘላለም ይኑሩልን ማለት ነው፡፡

ይህም ማለት የምናነበውን አልተረዳነውም ማለት ነው፡፡ ከተረዳነው እንዴት በህዝብ ፊት ቆመን እናነበዋለን? ወጣቷ በዘመኗ ካሉት ሁሉ ባህሏን ያከበረች ሁሉንም ተረድታ የታዘበች ከወላጆቿም ከቄሱም ከምሁራኑም የተሻለች ሆነች፡፡ ትዕማር በጥበቧ ከሱ ተሽላና ልቃ በማየቱ ይሁዳ “ትዕማር ከኔ ይልቅ እውነተኛ ሆነች” (ዘፍ 38፡24_26) እንዳለው እኔም ባለ ቅኔዋን ልጅ ከኛ ሁሉ ተሻለች ብል ማን ይፈርድብኛል? የወጣቷ ቅኔ የተሰወረበትና የመረዳት አቅሙ የተወሰደበት ካልሆነ በቀር ይህችን ጦማር ያነበበ ባለ ቅኔዋን ወጣት ከኔ ትሻላለች የማይል ይኖራል ብየ ማመን ይከብደኛል፡ ይህች ወጣት፦

 

“በርታ እንግዲህ ጓዴ ቢሆንም ባይሆንም

“ሰው ቢማር ቄስ እንጅ፤ ሰው መላክ አይሆንም” ብላ በራስ ብርታትና ጥንካሬ ላይ ትኩርት ከማደረግ የተሻለ ምርጫ እንደሌለ ለሕይወቷ ተካፋይ ለፍቅረኛዋ ያቀረበችው ምክር ከነብያት ከሐዋርያትና ከሊቃውንት ጋራ የተወሀደ ነው፡፡ እኛ የዘመኑ ቀሳውስት ምሁራን ልሂቃን እንደቀደሙ አባቶች መስለነው በመዘናጋት ከመጠቃት ይልቅ የራሱን ብርታትና ጥንካሬ ከእግዚአብሔር ረድኤት ጋራ በማዋሀድ ትኩረቱን በራሱ ላይ እንዲያደርግ ይህች ወጣት ዛሬም በቅኔዋ መልእክቷን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በማስተላለፍ ላይ ናት፡፡

በተረፈ እግዚአብሔር የዚህችን ወጣት ጥበብ በሕሊናችን እንዲያሰርጽብን እመኛለሁ፡፡ ይቆየን

 

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/177313

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...