Monday, October 24, 2022

የክፉዎች ፍልሰት ይሁን (Let Exodus of Evil be) - ሰማነህ ታ. ጀመረ-ዖታዋ፤ ካናዳ፤
ጥቅምት 14, 2015

በሰባዎቹ የጀመረው የፈላሻ ሙራ ወደ እስራኤል ፍልሰት እስካሁን አልተጠናቀቀም። ፍልሰቱ የተከናወነበት መርሃ ግብር ‘ዘመቻ ሙሴ’ (Operation Moses) ተብሎ ነበር። መንፈሳዊ ፍልሰት ስለነበር ሁሉም ተቀብሎታል።

እነዚህ ወገኖቻችን በሃይማኖት ምክንያት ይውጡ እንጂ ኢትዮጵያዊነታቸውን አዝለው ይዞራሉ። ኢትዮጵያ ስትነካ ይቆጣሉ፤ ስትደሰት ይደሰታሉ፤ ስታዝን ያዝናሉ፤ ስትጠቃ በቁጭት ዘብ ይቆማሉ። በትግራይ በተነሳው ጦርነት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ቆመው ለመዋጋት የኢስራኤልን መንግስት ፈቃድ እስከመጠየቅ ደርሰዋል። የቁርጥ ቀን ወገኖች ናቸው።

በአንፃሩ ከኢትዮጵያ ከአብራኳ የፈለቁ፤ በሃብቷ የተማሩና የበለፀጉ፤ ልጆቸ እያለች ያንቆለጳጰሰቻቸው ወያኔ የተባሉ የትግራይ ልጆች በዓለም አደባባይ ውድቀቷንና ስቃይዋን አብዝተውባት አይተናል። እዚህ ላይ ወያኔ፤ ትህነግ፤ ሕወሃት በሚል መጠሪያ ብዙ ሰው ይጨነቃል። ለዚህ ፀሐፊ ግን ሁሉም የአንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታዎች እንደሆኑ ስለሚአምን ብዙ አያስጨንቀውም። አሳማን ምንም ዓይነት የከንፈር ቀለም ቀብተን ለማቆነጀት ብንሞክር ያው አሳማነቱን አይቀይረውም።

ወያኔም ሆነ ሕወሃት የውጭ ጠላት ሊአደርገው የማይችለውን ደባና ተንኮል በኢትዮጵያ ላይ ፈፅሟል። ለሃምሳ ዓመታት ኢትዮጵያን አድምቷል። ንብረቷን ያለገደብ ዘርፏል። ሕፃናትንና አዛውንቶችን በውጊያ አስጨርሷል። ዘግናኝ የሆነ የዘር ፍጅት ፈጽሟል። የሰባ ዓመት መነኩሲትና ለአቅመ ፍሬ ያልደርሱ እህቶችንና እናቶችን ደፍሯል። የጤና፣ የመብራት፤ የስልክ፤ የትምህርት፤ የመንገድ፤ የፋብሪካ የማህበራዊና የኢኮኖሚ አውታሮችን በግፍ ዘርፏል። መሸከም ያልቻለውን አውድሟል። ፋሽስት ኢጣልያ ያላደረገውን ወያኔ ፈጽሟል። የፈፀሙትን ግፍ ከመዘርዘር ያልፈፀሙትን መጥቀስ ይቀል ይሆናል።

ሌላው ቢቀር ጣሊያን መንገድና ድልድይ ሰራ እንጂ አላፈረሰመ፤ መነኩሲት አልደፈረም፤ የማረከውን አልጨፈጨፈም። ይህን የፈፀመው ይሉኝታቢሱ ወያኔ ነው። ከኢትዮጵያ የቀረውና የሚቀርበት ነገር የለም። ኢትዮጵያዊነቱን አሟጦ ጉድጓድ ከቷል። ይባስ ብሎ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር የለችም፤ ካለችም መውደም አለባት ሲል ዘምቷል። ከ110 ሚሊዮን  በላይ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አሳዷል። ኢትዮጵያን በማዋረድ፤ በማውደም የእፉኝት በሐሪውን ስላሳየ የኢትዮጵያዊነት ስብዕናን አያሟላም።

ለትግራይ ነፃነትና ለትግራይ ሕዝብ ሕልውና እታገላለሁ እያለ የራሱን ሕዝብ በመንደርና በቀየ ሸንሽኖ ቁምስቅሉን አሳጥቷል። ለሰላሳ ዓመታት ሴፍቲኔት የተባለ መርሃ ግብር ዘርግቶ ሕዝቡን ሴፍቲውን አሳጥቶ ገዝቷል። የእርዳታ እህል ተቀባይ አርጎ በድህነት ሲአሰቃየው ኖሯዋል። በአንፃሩ ቡድኑ ከኢትዮጵያና ከትግራይ ሕዝብ በዘረፈው ሃብት እራሱን፤ ቤተሰቡን፤ ዘመዱን፤ በዓዳን ጓዶቹንና ጠበቆቹን በገንዘብ አንበሽብሿል።

በዘረፈው ሃብት በአሜሪካ ‘ተጋሩ ኢንቨስትመንት ቡድን’ (Tegaru Investment Group)  ብሎ ባቋቋመው ድርጅቱ አማካይነት የተንደላቀቀ ኑሮውን እያጧጧፈ እንደሆነ ያለሃፍረት  በቅርቡ አስመርቋል። ለዚህም በታሕሳስ 2014 መጨረሻ በካሊፎርኒያ፤ ሎሳን ጀለስ ከተማ የመሰረተውን የተጋሩ መንደር በሚል የገዛውን ሕንፃና መሬት ለደጋፊዎቹ አስጎብኝቷል። የትግራይ ሕዝብ ግን የሚጠጣው ውሃና የሚበላው አጥቶ በለስ እየተመገበ ይኖራል።

ወያኔዎች ከድሃው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉሮሮ እየነጠቁ በሃብታም ሃገር የራሳቸውን ከተማ እና መኖሪያ እየገነቡ ከሆነ በግልጽ ኢትዮጵያዊነታቸውን አራግፈው ጨርሰዋል ማለት ነው። እነዚህ ክፉና የጊንጥ በሐሪ የተላበሱ ናቸው። ለኢትዮጵያም፤ ለትግራይም ለዓለምም የሚጠቅሙ አይደሉም። ስለሆነም ‘የክፉዎች ፍልሰት’ የሚል  መርሃ ግብር ቀርፀን ከኢትዮጵያ ወደ ሎሳንጀለስ ልናስተላልፋቸው ግድ ይላል። ወያኔ ከኢትዮጵያ ጋር የሚአመሳስለውን ስነምግባር፤ በሐሪና ስብዕና አሟጦ ጨርሷል። የኢትዮጵያ እዳነት እንጅ ኢትዮጵያዊ ወገንተኝነት የለውም።

ይህ የአሸባሪ ቡድን (ሕዝብ አላልሁም) ከሃገራችን ይውጣ። ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ዝንተ ዓለሙን ሲአልቀስ ይኖራል እንዲሉ፤ ወያኔ የሚባል አጋም ኢትዮጵያን በበቂ አስለቅሷል። ኢትዮጵያ ከዚህ ቡድን ጋር ሕጋዊ ፍች በማድረግ ስርዬትን ታግኝ። ምስኪኑ የትግራይና የኢትዮጵያ ሕዝብም ሸክሙ ይቅለለው። ከተሸከሙት የዓለም ባንክ (WB) እና የዓለም ገንዘብ ተቋም(IMF) እዳ  ሸከም  በላይ የመሸከም አቅም የላቸውም። ወያኔ የሕዝብና የአገር ጀርባን በበቂ አጉብጧል። ከዚህ ዕዳና ፍዳ የሚገላገሉበት መፍትሔ አንድ ነው። ይህም ኢትዮጵያዊ አይደለንም የሚሉትን የትግራይ አሸባሪዎች ወደ አዘጋጁት የሎሳንጀለስ ቀያቸው እንዲፈልሱ እንፍቀድላቸው።

አሜሪካም በገቢር፤ በበሃሪ ትህነግን ስለሚመስሉና በአምሳላቸው የፈጠሯቸውም ስለሆነ አንቀበልም አይሉም። እነርሱስ ቢሆን ከእንግሊዝና ከአውሮፓ ፈልሰውና የሰው ሃገር ወረው ሰው ሆነው አይደል ዓለምን ዓለማችንን የሚአባሉት። አሸባሪው መለስ “መንገዱን ጨርቅ ያርግላችሁ” እንዳለው ወደ ሎሳንጀለስ የሚአደርጉትን ፍልሰት ‘የክፉዎች ፍልሰት’ በሚል መርሃ ግብር  ፍልሰታቸው ይመቻችላቸው። ከዚህ የተሻለ ሰላማዊ ፍችና ግልግል አይኖርምና ይፍለሱ። ኢትዮጵያም ከአመርቃዡ የመከራ ምጧ ትገላገል።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን  ይባርክ፤

ሰማነህ ታ. ጀመረ-ዖታዋ፤ ካናዳ፤

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/177506

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...