Friday, September 16, 2022

ቤት እንቦሳ የአማራ ብልፅግና!! - ተዘራ አሰጉ
በመጀመሪያ ለመላው የአማራ ሕዝብ እንኳን ደስ አለን!! “ምን ተእጅ” ብትሉ “ብልጥ ልጅ የተሰጠውን እየበላ ያለቅሳል “ እንዲሉ ትናንት በባህር-ዳር የተፈቱት ፋኖዎች የመፈታታቸው ግብረ መልስ በጥቂትም ቢሆን አስደስቶናል።

ነገር ግን ፋኖዎች በተወሰነ አግባብ መፈታታቸው እንዳለ ሆኖ በሌሎች የአማራ ዞኖች በእስር እየተገላቱና እየተሳደዱ ያሉት ፋኖዎች ሊታሰቡ፣ እርቅ ፣ የጋራ ስምምነት ሊወርድ የግድ የሚል ይሆናል።

ወገኖች መቸም “ቤት እንቦሳ” ለምን እንደሚባል ለእናንተ መናገር “ቀባሪን እንደማርዳት” ነው።

ይህን ርዕስ የመረጥኩት ፋኖ የሃገረ ኢትዮጵያ ብሎም የአማራ ካስማና ማገር በሆነ ፣ ሃገርን ከቅጥረኛ ነፃ ባወጣ ፣በሕውሃት ከጀርባው ግፍ የተሰራበትንና የተመታውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ደም በመለሰ ፣ የአማራን በተለይ የወልቃይትንና የራያን አፅም እርስት ባስጠበቀ ፣ ጀግኖቹ ፋኖዎች ደማቸውን ባፈሰሱ፣ አጥንታቸውን በከሰከሱ ፣ ለሃገረ ጋሻና መከታ በሆኑ ያለአግባብ በስር (በከርቼሌ) መታሰራቸው ግፍ ቢሆንም አማራ ብልፅግና በዘመኑ አነጋገር ቢዘገይም “ነቄ” ብሎ ፣ የሚበጅውንና ሚዛን የሚደፋውን በድርበቡ አጢነህ በግፍ በእስር የነበሩት ጥቂት ፋኖ ወንድሞችህ በመፈታታቸው የፍርድ ውሳኔውን በፀጋ ስለተቀበልክ  ይልመድብህ እንላለን፣ እወቅበት።

በዚህ ከቀጠልክ ሊታደስ የሞከረውን ጓዳህን ፣ ለውጥ ለማሳየት ከሞከረው ልብህ ውስጥ “ ቤት ልንቦሳ “ የምንልበት ጊዜ እሩቅ ላይሆን ይችላል ፣ ፣ ብልፅግና ሆይ አንተም “ እንቦሳ እሰሩ” ለማለት እይገድህም እንላለን ፣ ። አሁን ሃገር በታመሰች ወቅት መከፋፈሉ ለጠላት በር ይከፍታልና።

እንደመሰሎቹ አጋር ፓርቲዎችህ መቸም ታውቀዋለህ “ ሆድ ሲያውቅ ደሮ ማታ” ሁኖብህ ነው እንጂ ፣  በምክንያታዊነት አማራ ብልፅግና ጥርስ ብታወጣ ያዋጣሃል።

አማራ ብልፅግና ልታውቀውና ልትገነዘበው የሚገባው በክፉ ቀን አለሁ የሚልህ ከቅርብ ያለው አማራ ወንድሞችህ ፣ እህቶችህና ዘመድ አዝማዶችህ ናቸው  ሌላውም እስከተመችሃቸው ድረስ ነው “አይሆንንም ትተህ ይሆናልን አስብ” እንዲሉ ካለፉት የአማራ ባለሥልጣናቶች ከደረሰባቸው ፈተናና መበለጥ ተማር።

አሁን በምታደርጋቸው ውሳኔዎችህና እምርታህ ከቀጠልክ ፣ የሚበጅህን ከተረዳህ ፣ ሳይኖረው ፣ ሳይመቸው ፣ እሱ ብጫቂ ልብስ ጣል እያረገና እያደረገች ለከረባት ፣ ለሱፍ ልብስና ለተሽከርካሪ የቢሮ ወንበር ያብቃህን/ችህን ገበሬ ወላጆችህን ፣ መከታና ወንድምህንና እህትህን “አለሁላችሀ” ካልካቸው በተመቻቸ መልክ ማስተዳደር አያስቸግርህም።

እንግዲህ በአዲሱ ዓመት በአዲስ መንፈስ ፣ በታደሰ ልቦና በአስተውሎት ታጅበህ መምራት ከጀመርክ  ኮተት እያልን “ቤት ለእምቦሳ” ልንልህ እንዳዳለን ፣ አንተም አታሳፍረንም “ እምቦሳ እሰሩ” ታለናለህ።

የአገሬ ገበሬ  “እንኳን የሰው ልጅ የታሰረ ጥጃ መጫኛ ገመድ እንዳላላ ይውላል ፣ ያድራል “ ታስሮ መዋል ይሰለቻልና  ፣ ያለወንጀሉ የታሰረ ሰው ደግሞ ብዙ ለሃገሩ አስተዋፅኦ ማድረግ ሲችል በእስር ቤት መማቀቁ ያበሳጨዋል ያውም በዚህ ክፉ ጊዜና “የወገን ያለህ” በሚባልበት ወቅት።

እስኪ እንዲያው በጋራ ሃገረ ኢትዮጵያን ለመምራት ከተዋቀራችሁት ብልፅግና ከተባለው ውህድ ፓርቲ መካከል የኦሮሞ ቄሮ ባንክ ሲገለብጥ ፣ ነፍጥ ይዞ ሲያምስና መሃል አዲስ አበባ ሆኖ ሲፎልል ማን ተናገረው ፣ የደቡብ ሕዝቦች በተለይ የጉራጌ ሕዝብ “የራሴን ዕድል በራሴ ልወስን” ሲል የዞኑ አመራሮች ሳይቀር ደግፈው ተነሱ እንጂ እንዲህ እንደ አማራ ብልፅግና በገፍ ወንጀለኛ የሆነውንም ያልሆነውንም  አላሰሩም ፣ የሶማሌው ክልል እማ “ አትድረሱብኝ ፣ አልደርስባችሁም፣ እናንተም በፀበላችሁ ፣ እኛም በፀበላችን”  ጣልቃ ገብነትን “አይሆንም” ያለ ይመስላል ፣ ትናንት በወሕሃት የተዋቀሩት እነ ጋምቤላና ቤንሻጉል ያፈሯቸው ሽፍቶች ሲያሻቸው ታላቁን የአማራ ሕዝብ ከጠላት ጎን ወግነው ሲያምሱት “ለምን?” ያለ የለም ለምን ቢሉ “ ባለቤቷን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ አሳደረች “ የተማመንቱን ተማምነው ይሆናል ።

ሕወሃት የበደለውን ረስቶ የየዋህውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ ሰጭነት ረግጦ ጦር ሰብቆ ፣ መሳሪያ ታጥቆና ዝናሩን ወድሮ የዘመኑ የፖለቲካ ውጥቅጥ ያመጣው ጣጣ በመንተራስ “ራሴን ችየ መንግስት እሆናለሁ ፣ እገነጠላለሁ፣ ”ኢትዮጵያ “ለኔ ዝርፊያ ካልተመቸችኝና ረግጨ ካልገዛዋት” ብሎ “ዱር ነው ቤቴ ካለ ሰነባብቷል ። ከዚያም አልፎ  “ወልቃይት ፣ ጠገዴንና ራያን በሃይል አበርክኬ ወደ መንግስቴ ስር አስገብቼ ሃገረ ትግራይን  እመሰርታለሁ” ብሎ ፏለለ ፣ ያዙኝ ልቀቁኝ አለ ነገር ግን ዓላማው አጉራ ዘለልነቱ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ስላልተወደደ የዘራውን እያጨደ ነው ፣ በመላ ሕዝቡ ተተፋ ። እንዲህ ዓይነት ፅፈኝነትና ቱሪናፋ ማብዛት ደግሞ ፣ ቅጥ ያጣነው ፣ ሁሉ ሚዛን ጥብቆ ሲሆን መልካም ነው።

የአማራ ብልፅግና ሆይ “ ከስንዴ እንክርዳድ አይጠፋምና” አጥፊን መቆንጠጥ የግድ ነው ነገር ግን በአዋጅ ያውም አዲስ አበባ ከከተመው መንግስት ፋኖ ከጠነከረ መንግስትን ያናጋል በሚል ፍራቻ የወረደን መመሪያ ተቀብሎ ወገንን ማሰቃየት አያዋጣም እንልሃለን።

ይሄው ሰሞኑን የተከሰውን የወያኔ ሶሰተኛ ወረራ ፣”ጀግኖች ፋኖዎች እስር ላይ ናቸው ፣ ተገላተዋል  ፣ እየተሳደዱ ናቸው ፣ ከአማራ ብልፅግና ጋር ተቃቅረዋል ብሎ ጦርነት ሲጭር ፣ በደሉን ፣ ኩርፊያውንና ብሶቱን ወደ ጎን ትቶ “ሆ” እና “ከሁሉ በላይ ሃገር ትበልጥብኛለች” ብሎ ወራሪውን ኃይል ተጣምሮ አፈር ድሜ እያበላ አይደለም እንዴ?።

አማራ ሆደ ሰፊ ፣ አስተዋይ ፣ ሃገር መምራትን ከ3000 ዓመተ ዓለም ጀምሮ የኖረበት ስለሆነ “ከበሮ በሰው እጅ ሲያዮት ያምር ፣ ሲይዙት ግን ያደናግር” እንዲሉ ፣  ሃገረ ገዥነቱን” ያ ውላችሁ ፣ ከቻላችሁ” ብሎ አስተዳድሩ በማለት ለትግሬው ፣ ለኦሮሞው ፣ ለወላይታው  ወዘተ ወንድሞቹ አሳልፎ “እንካችሁ” ካለ ሰነባብቷል ፣ ነገር ግን ሃገር መምራት ተራራ ሆኖባቸው ፣ የሰማይ ያህል እራቃችው ፣ በየትም ዓለም ያልታየ ሃገርና ሕዝብን በአንድነት ከመምራት ይልቅ የመበጣጠስን ገቢር በሕገ- መንግስት አስፈራችሁ  ፣ ሃገርን በብልሃት ከመምራት ይልቅ ጦርነትን የስልጣን ማራዘሚያ እየሆነ እያየን ነው ፣ ሃገረ ኢትዮጵያን የፓለቲካ የቤተ ሙከራና የጦርነት አውድማ ሆነች ። ይህም ሆኖ አማራ አልከፋውም “ሁሉም በጊዜ ሂደት ይስተካከላል” ብሎ በፀሎት ፣ በትዕግስትና በፅሞና ለሃገር መቀጠል ሲል ሁሉን በትዝብት እያየ ነው።

የአማራ ፋኖ በሰላም ጊዜ አራሽና ቀዳሽ ፣ ሃገር ምጥ በያዛትና በጦርነት ከተወጠረች “ ግንባሬን ለጥይት ፣ ስጋየን ለአሞራ “ ብሎ ነፍሱን ሳይሳሳ የሚሰጥ ነው።

ስለዚህ የአማራ ብልፅግና ሆይ የምታስተዳድረው የአማራ ሕዝብ ታላቅ ሕዝብ ነውና ከአብራኩ የወጣህ እንደመሆኑ ከደረጃው ፣  ከከፍታው ዝቅ እንዲል አታድርገው።

ለሕዝብ ጥቅም ፣ ልዕልና ዕድገት እማያባራ ጥረት አድርግ ። የራስ መተማመን መንፈስ የተላበሰ ሕዝብ ስለምትመራ ልበ ሙሉ መሆን የግድ ይላል።

ቢዘገይም ሰሞኑን የተወሰኑ የፋኖ አርበኞችን እንደፈታህ ሁሉ በሌሎችም መስክ ለውጥ ካመጣህ አዲሱን የመለወጥ መንፈስ ጉዞህን ለማበረታታት ላይገደን ይችላል። ካልሆነ ግን ያስተዝባባል ፣ እምቢተኝነት ይነግሳል እንላለን።

 

ተዘራ አሰጉ

ከምድረ እንግሊዝ።

 

 

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/177069

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...