Tuesday, August 30, 2022

የወልዲያ ከተማ ወቅታዊ ሁኔታ
ከወልዲያ ከተማ ሸሽተው መርሳ ከተማ ከደረሱ በርካታ ነዋሪዎች ወደ ከተማዪቱ የሚመለሱም እንዳሉ ለዶይቸ ቬለ (DW) የዐይን እማኞች ተናገሩ። ከተማዋን ለቅቀው ከወጡት መካከል አንዳንዶች ዛሬ ከሰአት በኋላ ወደ ወልደያ በመመለስ ላይ ነበሩ ሲሉም አክለዋል። ከቀኑ ዐሥር ሰአት አካባቢ ዶይቸ ቬለ በስልክ ያነጋገራቸው አንድ የወልዲያ ነዋሪ «የባጃጅ እና የሰዎች እንቅስቃሴ» መኖሩን ተናግረዋል። መብራትም፣ ኔትወርክም እንዳለ እኚሁ ነዋሪ አክለዋል። በብዛት ሰዉ ከከተማዪቱ ወጥቶ የነበረው ትናንት ማታ እና ዛሬ ጠዋት እንደነበር፤ በአሁኑ ወቅት ግን ወደ ከተማዪቱ የሚገባም የሚወጣም እንዳለ የዐይን እማኙ ተናግረዋል።

መርሳ ከተማ እንደደረሱ የተናገሩ አንድ ግለሰብ ደግሞ ከራያ ቆቦ ተፈናቅለው በወልደያ በኩል መርሳ ከተማ መግባታቸውን ገልጠዋል። ከቅዳሜ አንስቶ ቀኑን ሙሉ በእግር እንደተጓዙ የተናገሩት እኚሁ ተፈናቃይ፦ ወልዲያ የገባሁት እሁድ ጠዋት ነው ብለዋል። እስከ ትናንት ድረስ በርቀት ተኩስ ይሰሙ አንደነበረም ነዋሪው አክለዋል።

ሌላኛው የወልዲያ ከተማ ነዋሪ መሆናቸውን ለዶይቸ ቬለ የተናገሩ ግለሰብ፦ ሰዎች «ተራ ወሬ ሰምተው ነው የኼዱት» እንጂ ከተማው ውስጥ ምንም የለም ብለዋል። ሆኖም «ከተማ ውስጥ ያለውን ነዋሪ በድምፅ ማጉያ እየዞረ የሚያረጋጋ የለም» ሲሉም አክለዋል።

ደሴ ከተማ እንደገቡ ለዶይቸ ቬለ የተናገሩ አንዲት ነዋሪ በበኩላቸው፦ «እስከ ሦስት ሺህ ብር ድረስ ከፍለው የመጡም አሉ» ብለዋል። «የራሳችን መኪና ስለነበረን ቀጥታ ነው የመጣነው» ሲሉ እንዴት ደሴ ከተማ እንደደረሱ አብራርተዋል። ደሴ ከተማ ተፈናቃዮችን ለማስተናገድ ከአቅሟ በላይ ነችም ብለዋል።

የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዲያቆን ተስፋሁን ባታብልን ጠቅሶ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገፁ ባሰራጨው ዘገባ «ወልድያ በጠላት እንደተያዘች የሚሰራጨው መረጃ ሐሰት መኾኑን ዞኑ አረጋግጧል» ብሏል።

DW
https://amharic-zehabesha.com/archives/176756

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...