Tuesday, August 16, 2022

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ባለፈው ሣምንት ከፕሬዝደንትነታቸው የለቀቁት አቶ እስክንድር ነጋ የት እንዳሉ እንደማያውቅ ገለጸ
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ባለፈው ሣምንት ከፕሬዝደንትነታቸው የለቀቁት አቶ እስክንድር ነጋ አሁንም የት እንዳሉ እንደማያውቅ ገለጸ። የፓርቲው ኃላፊዎች ዛሬ ሰኞ በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ከሐምሌ 16 ቀን 2014 ጀምሮ አቶ እስክንድር ከባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጽህፈት ቤት እና ከሥራ አስፈጻሚው ጋር ያላቸው ግንኙነት ሙሉ በሙሉ መቋረጡን ገልጸዋል።

የፓርቲው ምክትል ፕሬዝደንት አቶ አምኃ ዳኘው በንባብ ባሰሙት መግለጫ አቶ እስክንድር "ምንም የነገረን ነገር ባለመኖሩ፤ የት እንደሔደ እና በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ባልታወቀበት ሁኔታ አድማጭን የሚያረካ መልስ መስጠት የሚቻልበት ሁኔታ አልነበረም" ብለዋል።

በአሜሪካ ሀገር የሚገኙት የአቶ እስክንድር ባለቤት እንዳልደነገጡ እና ከፓርቲውም ሆነ በውጭ አገር ከሚገኘው የድጋፍ ኮሚቴ ማብራሪያ እንዳልጠየቁ የጠቀሱት ምክትል ፕሬዝደንቱ በዚህ ምክንያት "የመታፈን አደጋ እንዳልደረሰበት ገመትን" ሲሉ ተናግረዋል። ፓርቲው አቶ እስክንድር ያሉበትን ሁኔታ ያሳውቁናል ብሎ በመጠባበቅ ላይ ሳለ በአሜሪካ ከሚገኘው የድጋፍ ኮሚቴ በኩል የመልቀቂያ ደብዳቤው ይፋ እንደሆነ አስረድተዋል።

አቶ እስክንድር የኢትዮጵያ መንግሥት "በባልደራስም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ በፈጠረው የለየለት አምባገነናዊ ጫና ሳቢያ በአባልነትም ሆነ በአመራርነት መሥራት የማልችልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ" ሲሉ ሐምሌ 16 ቀን ተጽፎ ነሐሴ 5 ቀን 2014 በፓርቲው የተረጋገጠ የፌስቡክ ገጽ ላይ በተለጠፈ ደብዳቤ ገልጸው ነበር።

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ የሆኑት ወይዘሮ ቀለብ ሥዩም ከሐምሌ 16 ቀን 2014 ወዲህ አቶ እስክንድርን "በስልክም ይሁን በአካል አግኝተናቸው አናውቅም" ሲሉ ተደምጠዋል። መንግሥት አቶ እስክንድርን "እንዳላፈናቸው እና እንዳላሰራቸው" ፓርቲው እንደሚያምን የገለጹት ወይዘሮ ቀለብ ከቤተሰቦቻቸው "ደህና" መሆናቸው እንደተገለጸላቸው በዛሬው ዕለት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስረድተዋል። ይሁንና አቶ እስክንድር ከአሜሪካ ከተመለሱ በኋላ "የተለያዩ የደህንነት መኪናዎች እና የተለያዩ ሰዎች" ይከታተሏቸው እንደነበር የገለጹት ወይዘሮ ቀለብ "ውጥረት እና ከፍተኛ ጭንቀት" ውስጥ ለመሆናቸው "ምልክቶች እንደነበሩ እናውቃለን" ብለዋል።

DW
https://amharic-zehabesha.com/archives/176617

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...