Wednesday, July 27, 2022

ከሀገር ውጭ ለሚገኙ መቅደሶቻችን ታቦታትና ንዋያተ ቅድሳት ይዞ ለመሔድ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን የመጀመሪያውም ብቸኛውም አባት አይደሉም
ከዚህ ቀደም ለተባረኩት ቤተ መቅደሶች ኹሉ ታቦታትና ንዋያት የተወሰዱት በዙሁ ተመሳሳይ አሠራርና መጓጓዣ ነው። ለኒህ ኹሉ መቅደሶች ታቦትና ንዋያት ከግብፅ ወይ ከሶርያ አልተላከም፤ ወይም እዚያው አልተባረከም። እንኳንስ የሲኖዶሳችን ሰብሳቢ፣ የጳጳሳቱ አለቃ ፓትርያርክ ይቅርና ተራው ቄስ እንኳ ለመቅደሱ ታቦት ይዞ ሲሔድ ይታወቃል። ጭራሽ ለክርስትና፣ ለተክሊል፣ ለክህነት ማክበሪያ የሚውል ቅብዐ ሜሮን እስከመቀማት መድረስ እውነት ነገሩ አዲስ ኾኖባችሁ ነው? ይኽን ያኽል ጥንቃቄ ቢኖርማ ባሕር ማዶ የግለሰብ ቤቶችንና አብያተ መዘክርን የሞሉት ቅርሶቻንን በአየርና በመሬት እንጂ በሰርጓጅ መርከብ አልሸሹም እኮ! ያኔ ይኽ ክትትል የት ነበራ?! የተጠረጠረ ነገር ካለም በደህንነት ካሜራ የተያዘ ድምፅና ምስል ለሚመለከተው መርማሪ አካል ከማቅረብ በፊት ለበይነ መረብ ቀላጤዎች እንዴት ተሰጠ? ይልቁንም የቤተ ክህነቱን ተቋማዊ ክብርና አሠራር ጠብቆ በቅድሚያ ማሳወቅና መነጋገር ሲገባ ይኽን ያኽል ክብደት ያለው "መረጃ"ለበይነ መረብ ቀላጤዎች (so called activists) እንዴት በየት ተላለፈ?

እነሱስ (ቀላጤዎቹ) ቢኾኑ መደበኛው የቤተ ክህነት አሠራር ምን እንደኾነ ከማጣራት በፊት "መረጃውን" ለሕዝብ ለመርጨት ለምን ተጣደፉ? ብዙ ጥያቄዎችን ማንሣት ግድ ይላል። ቀድሞ ወደ ኅሊናችን የሚመጣው ከግምት ያለፈ እውነታ አንድ ነው። ሤራ!! አዎ በተለይ ሁለቱን ነባር የኢትዮጵያ ሃይማኖቶችን የማዋረድ፣ ተቋማዊ አቅዋማቸውን የማዳከም፣ ውስጣዊ ኅብረትን የማላላት፣ መተማመንን የማሳጣት ወዘተ. ሤራ!! የሰሞኑ የወንድሞቻችንን ክራሞት ልብ ይሏል። ቀደም ብሎም ቤተ ክህነት ውስጥ የጦር መሣሪያ ተገኘ ተብሎ "የተቀናበረውን" አስቂኝ ምስልና ዜና መርሳት አይገባም። አሁን እየተለቀቁ ወደ አገልግሎት ደብራቸው የተመለሱ የትግራይ ተወላጅ ልዑካኖቿ የጅምላ እሥርም አይዘነጋም።

ከኹሉ የገረመኝ ከቀላጤዎቹ አንዱ ያቀረበው "በተአምር ጽላት ከሀገር አይወጣም" ዐይነት ደረቅና ደፋር መከራከሪያ ነው። ደፋር እርግጠኛ አለ ወዳጄ። ሰውየው! እና ዘመዶችኽ የሚያስቀድሱበት መቅደስ ታቦት ከአእስክንድርያ ወይ ከሶርያ የተላከ መስለኽ? ወይስ ከሲና ተራራ የወረደ? በዚሁ አሠራር ተባርኮ የተወሰደ ወይም ቢያንስ በቄስ እጅ የተላከ እንጂ። ጊዜው የግርግር ኾኖባት እንጂ እናንተንስ በስም ማጥፋት ከመፋረድ በላይ ከአባሎቿ ኀረብረትና አንድነት ለይቶ አስከማሰናበት የተገባ ነበር።

ይብስ የሚነደው ደግሞ እውነተኛ ምስክር አገኘሁ ብሎ የሚያጋራውና አስተያየት የሚሰጠው መናጆ ብዛት ነው። በገዛ አባቱና በተቀደሰ ሥርዓቱ ላይ የበይነ መረብ መሐለቅ ለቃሚዎች በመዘባበት ሲፏንኑ ደህና ግጥም እንዳቀበሉት አዝማሪ ተቀብሎ ያጮኻል። ሰምቶ ጯኺ በቀቀን ኹላ! ግራ ቀኝ፥ ፊት ኋላ የማይመለስ፣ ለምን እንዴት ከየት የማይል መናጆ ኹላ! ይኽቺ ጥፋት ትምህርት ትኹንኽና አድብ፣ ተረጋጋ፣ የተመከረብኽን ራስህ በራስ አትፈጽም። እንደ ይሁዳው ንጉሥ ሕዝቅያስ "ዛቲ ተግሣፅ ትኩነኒ እም ዮም እግዚኦ" በል።

ለማንኛውም የጠቅላይ ቤተ ክህነታችን ብፁዕ ሥራ አስኪያጅ ዛሬ በጉዳዩ ላይ ሐሰተኛ ወሬውን ጨምሮ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሏልና እንጠብቃለን። እውነተኛውን መረጃ በፍጥነት በማድረስ ወሬውን በመረጃ ያከሸፋችኹ ወንድሞችን እናመሰግናለን።

ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ጤናዎን ይመለስልን፣ በቸር ያግባልን፣ ሐዘንዎ አይቆጠርብን፣ ግፍዎ አያስፈርድብን። ይፍቱን!!

(ውሎ ባደረ ቁጭት የወጣ የአንድ የቤተ ክርስቲያን ምስኪን አባል ሐዘን)"

እሸቱ ማሩ

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/176302

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...