Monday, April 1, 2024

የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴና የ1966ቱ ሕዝባዊ አብዮት ዋዜማ - ፫ በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)
(ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደጻፈው)

- የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ እ.ኤ.አ. ከ 1950-1975

1967-74: Ethiopia's Student Movement

‹‹… ጭንቅ ብሎኛል ኢትዮጵያዊ ማን ነው?

ወጣት ሽማግሌው አገር ሲጠየቅ፤

አንዱ ጐጃም ነኝ ሲል ሌላው በጌምድር፤

አንዱ ኤርትራ ሲል ሌላው ተጉለት፤

አንዱ መንዝ ነኝ ሲል ሌላው ጋሙ ጐፋ፤

ኢትዮጵያዊ ነኝ ባይ ብፈልገው ጠፋ፤

እስቲ አዋቂዎች እናንተ ንገሩኝ፤

እኔን ያስጨነቀው ኢትዮጵያዊው ማን ነው…?!››

 

(በ1950ዎቹ በዛን ጊዜው ቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፤ የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረው ኢብሳ ጉተማ፤ ‹‹ኢትዮጵዊ ማነው?!›› ከሚለው ግጥሙ ተቀንጭቦ የተወሰደ)

በአፍሪካና በመላው ጥቁር ዓለም የናኘውና ከፍ ብሎ ከተሰማው የዐድዋው ድል ለሀገራችን ፖለቲካዊ እንጂ የሚጠበቀውን ያህል ኢኮኖሚያዊ ድል እንዳላጎናጸፈን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ጣሊያን ለዐርባ ዓመት ዝግጅት አድርጎ፣ አቅሙን አጠናክሮና በሰለጠነ የሚሊተሪ ኃይል፣ በተራቀቀ ወታደራዊ መሳሪያ፣ ዘመናዊ ተዋጊ ጀት ጭምር ታጥቆ ነበር ፋሽስት የሮማን የቀደመ ክብር አስመልሳለሁ በሚል ቁጭት ወደ ኢትዮጵያ የዘመተው፡፡

‹‹… የዛን ጊዜዋ ኢትዮጵያ ግን በወታደራዊ ኃይልም ሆነ በኢኮኖሚ አቅም ረገድ ከዐድዋው ጊዜ እምብዛም የተሻለ አቋም ላይ አልነበረችም፤›› ይላሉ የታሪክ ምሁሩ ባሕሩ ዘውዴ (ፕ/ር) ኢትዮጵያና ኢጣሊያ ከአርባ ዓመት በኋላ በሁሉም ረገድ የነበራቸውን ልዩነት ሲቃኝ፡፡

የፋሽስት ጦር የኢትዮጵያን ጦር በአጭር ጊዜ ውስጥ አዳክሞ መዲናዋን አዲስ አበባን ሲቆጣጠር በእውነትም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የኃይል ሚዛን ጎልቶ ታየ፡፡ ከጣሊያን ወረራ በኋላ ራሳቸው ንጉሠ ነገሥቱ ኃይለ ሥላሴም እንዳመኑት ከዐድዋው ድል ዐርባ ዓመታት በኋላ በፋሽስቱ ኢጣሊያ ፊት የነበረችው ኢትዮጵያ ይህን ነው ሊባል በሚችል ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊና ማኅበራዊ ለውጥን አላሳየችም ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በቀላሉና ለጊዜውም ቢሆን በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች እግር ስር እንድትወድቅ እንዳደረጋት የታመነ ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡ እናም ዐፄ ኃይለሥላሴና መንግሥታቸው አገሪቱ በለውጥና በዕድገት ጎዳና ላይ እንደትጓዝ ለማድረግ ፈጣንና በቀላሉ ሊገታ ማይችል ሁለተናዊ ዘመቻ ነበር የከፈቱት፡፡

የዚህ ዘመቻ ዋንኛው ቁልፍ ጉዳይ ትምህርት መሆኑ የገባቸው ዐፄ ኃይለሥላሴ ሳይውሉ ሳያድሩ ነበር በርካታ ትምህርት ቤቶችን የከፈቱት፡፡ ከዛም ባሻገር ከአገሪቱ የተለያዩ ጠቅላይ ግዛቶች ታዳጊ ልጆችን በራሳቸው ወጪ እያመጡ እንዲማሩ አድርገው ነበር፡፡ በተጨማሪም በርካታ ተማሪዎችን ወደ አሜሪካና አውሮፓ በመሔድ እንዲማሩ ሰፊ የሆነ ዕድልም ተመቻችቶላቸው ነበር፡፡ እነዚህ በውጭ አገር የተማሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም ወደ አገራቸው በተመለሡበት ወቅትም፣ አገራቸው ያለችበት ድህነት፣ ኋላ ቀርነትና ጭቆና በእጅጉ ያንገበግባቸው ጀመር፡፡

ከዓመት ወደ ዓመት ከውጭው ዓለም ጋር ግንኙነት የነበራቸው ኢትዮጵያውያን ሌሎች ዜጎችን በተገናኙና ስለሌሎች አገሮች የዕድገት ደረጃ ባነበቡ ቁጥር፣ የሀገራቸው መሪነት ሣይሆን ጭራነቷ ወደ እውነታ የሚጠጋ ሐቅ እንደሆነ እየተገነዘቡ መጡ፡፡ በሚያስደንቅም ሁኔታ ነገሮች ለውጥ ማሳየት የጀመሩት ወጣቱ ትውልድ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሪነት በመንግሥት ላይ የፖለቲካ ተበቃይ ኃይል ሆኖ ብቅ ባለባቸው በ1950ዎቹ መጨረሻ ዓመታት ውስጥ ነበር፡፡

ለተማሪዎቹ አየል ብሎ መውጣት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል የ1953ቱ የከሸፈው የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ አንዱ መሆኑን የታሪክ ምሁራንና የፖለቲካ ተንታኖች በአንድ ድምፅ ይስማሙበታል፡፡

ቀደም ሲል በ1953 ዓ.ም. ትምህርቱን በአሜሪካ አገር በተከታተለው በግርማሜ ንዋይ በወንድማቸው በጄ/ል መንግሥቱ ንዋይ የተሞከረው የመፈንቅለ መንግሥት የንጉሡን የ‹‹ሥዩመ እግዚአብሔር›› ካባ በመግፈፉ፣ ሥልጣናቸው ተበጋሪ የሆነ ግለሰብ እንደሆኑ አሳየ፡፡ ከዚህ አልፎ ሙከራው በኅብረተሰቡ ውስጥ የነበሩትን ኢኮኖሚያዊና ማኅበረሰባዊ መበላለጦች ቁልጭ አድርጎ አሳየ፡፡ በከሸፈው በሁለቱ ወንድማማቾች የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራም የዛን ጊዜዎቹ የቀ.ኃ.ሥ ተማሪዎች ሙሉ ድጋፋቸውን ሰጥተውት እንደነበር በጊዜው ወጥተው የነበሩት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

እንደውም ጄ/ል መንግሥቱ ንዋይ በመፈንቅለ መንግሥቱ ዋዜማ ለቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ባደረጉት ንግግራቸው እንዲህ ብለው መናገራቸው ይጠቅስላቸዋል፤

‹‹እናንተ የነገይቱ ኢትዮጵያ ተስፋዎች የኾናችሁ ተማሪዎች እኛ የለውጥ መስኮቱን ከፍተናል፣ ታላቁን የለውጥ በር የምትከፍቱት ግን እናንተ ናችሁ፤›› በእርግጥም ይሄ ትንቢታዊ ሊባል የሚችል የወቅቱ የጄ/ል መንግሥቱ ንዋይ ንግግር ከዐሥር ዓመት በኋላ አገሪቱን ከዳር እስከ ዳር ለለውጥ በእንዴት ያለ ኅብረትና አንድነት፣ በእንዴት ያለ ቁጣና እልክ ሁሉንም እንዳንቀሳቀሰው እውነታው በተግባር ታይቷል፡፡

የዚህ መፈንቅለ መንግሥት መንሥኤው አገሪቱ የነበረችበት ድህነትና የሕዝቡም መከራና ጉስቁልና ነበር፡፡ ምንም እንኳን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ብርቱ ፍላጎትና ጥረት የተጀመረው የኢትዮጵያ ሥልጣኔና የዕድገት ሂደት ስር ነቀል ለውጥ ያመጣል ተብሎ ቢታሰብም የኋላ ኋላ በራስ ወዳድነትና ስግብግብነት ምክንያት የተጓጓለትንና ተጠበቀውን ያህል የረባ ዕድገትና ለውጥ ማሳየት ሲሳነው ማስተዋል ለሕሊና የሚቆጠቁጥ ሐቅ ሆነ፡፡ በመሆኑም በፊውዳሊዝም ቅሪቶች ላይ ለሚካሄደው ዘመቻ በንጉሡ ይተማመን የነበረው የብዙዎች ምኞት ቀስ በቀስ እንደ ጉም መተነን ጀመረ፡፡

እንደውም የገዥው መደብ አምርሮ በሚቃወማቸው የመሬት ስሪት ለውጥን በመሳሰሉ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ዐፄ ኃይለ ስላሴ ለውጥ ለማካሄድ ፍላጎት ወይም ችሎታው እንዳልነበራቸው ግልጽ እየሆነ መጣ፡፡ ቀስ በቀስም በንጉሠ ነገሥቱ የሚመራው መንግሥት ራሱ ለአገሪቱ ዕድገት ዋንኛው እንቅፋት ስለሆነ መነሳት አለበት የሚለው ግንዛቤ መልክ እየያዘና እየተጠናከረ መጣ፡፡ በቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርስቲ የሚገኙ ተማሪዎችና አንዳንድ ምሁራንም አገሪቱ ለውጥ እንደሚያስፈልጋት በማመን ሌሎችንም ለማሳመን ጥረት በማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ፡፡

ተማሪዎቹ በየዓመቱ በግቢያቸው በሚያቀርቡት የግጥም ውድድርም የዘውዱን ሥርዓት የሚሞግቱና አገሪቱ ያለችበትን አስከፊ የሆነ ኋላ ቀርነት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም የሚገኝበትን አሰቃቂ ድህነትና ጭቆና የሚየጋልጡ ግጥሞችን ማቅረብ ጀመሩ፡፡ እነዚህ ንጉሠ ነገሥቱና ባለሟሎቻቸው ሳይቀር በሚገኙበት መድረክ የሚቀርቡ ግጥሞች ንጉሡንና ተከታዮቻቸውን ማስኮረፍ ብቻ ሳይሆን በሂደትም ግጭት ውስጥ አስገባቸው፡፡ በ1954 ዓ.ም. ለዩኒቨርሲቲው ቀን/በኮሌጆች ቀን የሚቀርቡት ግጥሞች በተቀዳሚ ለሳንሱር እንዲሰጡ ተጠየቀ፡፡ ተማሪዎቹም እምቢኝ ጽሑፎቻችንን አንሰጥም አሉ፡፡

ንጉሡም በዚሁ ተቀይመው በበዓሉ ላይ ሳይገኙ ቀሩ፡፡ በዓሉ ተከበረ፣ ግጥሞቹም ተነበቡ፡፡ አሸናፊ የሆኑት ግጥሞችም በፀረ-መንግሥትነት ተከሰሱ፡፡ ሦስት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር መሪዎችም ከትምህርት ገበታቸው ተባረሩ፡፡ በየጊዜው በሚከበረው የዩኒቨርሲቲ ቀን ከቀረቡት ዝነኛ ግጥሞች መካከልም፣ ‹‹ምላሴን ተውልኝ!›› በአበበ ወርቄ፣ ‹‹በረከተ መርገም!›› በኃይሉ ገ/ዮሐነስ/ገሞራው፣ ‹‹የገደል ስር አጥንት›› በዮሐንስ አድማሱ፣ ‹‹ኢትዮጵያዊ ማነው?!›› በኢብሳ ጉተማ፣ ‹‹ልረሳሽ እሻለሁ!›› በዋለልኝ መኮንን ይገኙበታል፡፡

በዚህ የተሟሟቀ የለውጥ ሂደትም የተማሪዎቹ እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ እየተደራጀና ሌላ መልክ እያዘ በመምጣቱ በመንግሥት ዘንድ እምብዛም አልተወደደለትም ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ የተማሪውና የመንግሥት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ በሚሄድበት ወቅት ቆራጥ የተማሪ መሪዎችን የሚያሰባስብ የድርጅት አስኳል በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ተጣለ፡፡

በ1956 ዓ.ም. ቀደም ሲል የተፈጠረው ስብስብ/ማኅበር ተጠናክሮ አዞዎቹ (Crocodiles) የተባለ ጠንካራ የሆነ ስብስብ ሊፈጥር ቻለ፡፡ በዚሁ ዓመትም ብሔራዊ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበርን የሚያቋቁመው ስብሰባ በይፋ ተደረገ፡፡

በዚህ ጉባኤም ማሳረጊያ አስራ ሁለት ገጾች የአቋም መግለጫዎችና ውሳኔዎች ተላለፉ፡፡ የመንግሥትን ቅጣትና ተፅዕኖ ሳይፈራ በኢትዮጵያ የተንሰራፋውን ችግርና አሰከፊ ድህነት ለመታገል ወደኋላ እንደማይል ማኅበሩ አስገነዘበ፡፡ የዐፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ማሻሸያ እርምጃዎችን ይወስድ ዘንድም ጠየቀ፡፡

ተማሪዎቹ በዚህ ጥያቄቸውም በአርሶ አደሩ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል በጢሰኛውና በባለመሬቱ መሀል ያለው ግንኙነት ሕጋዊ እንዲሆን ጠይቀው ነበር፡፡ በዚህ ስብሳባ ላይ በተካሄደው ምርጫም ብርሃነ መስቀል ረዳ የብሔራዊው ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር የመጀመሪያው ዋና ጸሐፊ ሆኖ ሲመረጥ፣ ባሮ ቱምሳ ደግሞ የዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ማኅበር ፕሬዝዳንት ሆኖ ተመረጠ፡፡

 

- የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴና የመሬት ላራሹ ጥያቄ፤

‹‹መሬት ላራሹን የምትሹ፤

ተዋጉለት አትሽሹ፡፡››

በ1957 ዓ.ም. ብሔራዊ ማኅበሩ ለኃይለ ሥላሴ ፓርላማ አንድ ወሳኝ የሆነ ጥያቄ ይዞ መጣ፡፡ ይኸውም፤ ‹‹የሰባ አምስት በመቶ የአርሶ አደሩን ምርት ባለ መሬቱ እንዲወስድ የሚደነግገው የፍትሐ ብሔር ሕግ ወደ ሰላሳ በመቶ እንዲወርድ፤›› የሚጠይቅ ነበር፡፡

‹‹መሬት ላራሹን›› በፊታውራሪነት ይዞ የተነሣው ተማሪዎቹ እንቅስቃሴ በተመሳሳይም አይነኬ የሚባሉ ሌሎች ጥያቄዎችን ይዞ ወደ አደባባይ ወጣ፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ታሪክ ከ1950ዎቹ አጋማሽ በኋላ ‹‹መሬት ላራሹ›› በሚለው መፍክር ስም የዘመኑ ተማሪዎች ያደርጉት ነበረውን ተከታታይ የተቃውሞ የአደባባይ ሰልፍና በተለይም ደግሞ በ1961 ኅዳር ወር መግቢያ ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ልደት አዳራሽ የተካሔደው የተማሪዎቹ ስብሰባ የተማሪዎቹን እንቅስቃሴም ሆነ የአገሪቱን ፖለቲካ መሠረታዊ በሆነ መንገድ እንደቀየረው የታሪክ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡

በተጠቀሱት ሁለት ዘመናት መኻል የተማሪውን እንቅስቃሴ ርዕዮተ ዓለምን የአሳብ መደላድል ለመስጠት በማሰብ ራሳቸውን ‹‹ኮሮኮዳይል›› በሚል ስም የጠሩ ጥቂት ተማሪዎች የግራ-ዘመም አሳቦችን የሚያብራሩ ሥራዎችን በማንበብና በአሳቡም ላይ መወያየት ጀመሩ፡፡

የኢትዮጵያን ተማሪዎች እንቅስቃሴ በማጥናት ቀዳሚ የሆኑት አውሮፓዊው ራንዲ ቫልሲቪክ፤ ‹‹Haile Selassie Students the Intellectual and Social Background to Revolution›› በሚለው ሥራቸው እንዳስነበቡት፣ ይሄ ኃይለኛ ምሥጢረኝነት፣ አይገመቴነትና በሌሎች ተማሪዎች ዘንድ አይነኬ የነበረው ከ10-15 ተማሪዎችን የሚይዘው የጥናት ቡድን አባል የነበረው የ27 ዓመቱ ወጣት የቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ ዋለልኝ መኮንን፤ ‹‹On the Question of Nationalities in Ethiopia›› በሚል ርእስ የጻፈውን ባለ አራት ገጽ ጽሑፍ በዩኒቨርሲቲው አዳራሽ በይፋ አቀረበ፡፡

- የብሔር ብሔረሰቦች መብት ጥያቄ በኢትዮጵያ

ይህ በዋለልኝ መኮንን የቀረበው ዝነኛ ጽሑፍ፤ ‹‹ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት/ማጎሪያ ናት፤ ኢትዮጵያዊነትም በአማራነት እንዲያም ሲል በትግሬነት ወይም ደግሞ በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ባህልና ማንነት፣ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት የተቀነበበ ማንነት ነው፤›› ሲል ወቀሰ፡፡ ይህ ባለ 5 ገጽ ጽሑፍም በተለይም ከኦሮሚያና ከደቡብ የአገራችን ክፍል ለመጡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ትልቅ ደውልና ማንቂያ ሆኖ ነበር፡፡

‹‹የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል›› የሚለው የእስታሊን መርህም ለመጀመሪያ ጊዜ ለብዙዎች ተማሪዎች ጆሮ ደረሰው የዛን ጊዜ ነበር፡፡ የለውጡ እንቅስቃሴ በጣሙን እየተጋጋለና እየደመቀ፣ ተማሪዎቹም እንደ ‹ታገል›፣ ‹ቻሌንጅ› ባሉ ጋዜጦቻቸው አሳባቸውን እያስፋፉ ትግሉን አፋፋሙት፡፡

ይህ የለውጥ እንቅስቃሴም አውሮፕላን እስከ መጥለፍና በሰሜናዊ አፍሪካና በመካለኛው እስያ ካሉ እንደ ፍልስጤም ነጻ አውጭ ድርጅት ጋር በጋራ ሥልጠና እስከመውሰድ የዘለቀ ግንኙነትን መፍጠር ችሎ ነበር፡፡ የኤርትራና የኦሮሞ ሕዝብ ነጻነት ጥያቄም ከዚሁ ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል›› ጥያቄ ጋር ተሰናስሎ ነበር በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ ልደቱን አግኝቶ፣ ወደ በረሃ የተመመው፡፡

የሕወሓት ታጋዮችም፤ ‹‹ፍትሕን ተነፍገናል፣ የጭቁን ሕዝባችንም መብቱ ተረግጧል እናም ሁሉም በአገሪቱ ያሉ ብሔረ ብሔረሰቦችና ነጻ ሊወጡ ይገባቸዋል!›› የሚል መርሕን አንግበው ነበር የዩኒቨርስቲና የኮሌጅ ትምህርታቸውን አቋርጠው፣ ‹‹እምቢ ለሕዝባችን፤ እምቢ ለነጻነታችን!›› በማለት ወደ ደደቢት በረሃ ያቀኑት፡፡

እዚህ ጋር ‹‹ከብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ›› ጋር በተያያዘ አንድ ማጥራት ያለብን እውነታ ያለ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ብሔረሰብ መብት ጥያቄ አሁንም ድረስ ተጋግሎ ያለ ጥያቄ ሲሆን፤ ‹‹ለኢትዮጵያ የመበታተን አደጋን የጋረጠ፤ የዛ ትውልድ ክፉ ዘር›› በሚል የዋለልኝን ጽሑፍ የሚረግሙና የሚተቹ በርካታዎች ናቸው፡፡ እውነታው ግን በሀገራችን የብሔር ብሔረሰቦች መብት ጉዳይ ሲነሳ እንኳን የተማሪ ጥያቄ ቀርቶ የዛን ጊዜው የቀኃሥ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም አልተመሠረተም ነበር፡፡

የታሪክ ድርሳናት እንደሚጠቁመትም፤ የብሔር ጥያቄ ቀድሞ የተጀመረ ትግል ነው፡፡ ኤርትራ ውስጥ የትጥቅ ትግል የተጀመረው ለምሳሌ ከአብዮቱ ብዙ ዓመታት በፊት ፌዴሬሽኑ እንደፈረሰ ነበር፡፡ ከትጥቅ ትግሉ በፊት ደግሞ የፖለቲካ ትግሉ እንግሊዞቹ ሳሉ ጀምሮ ለአሥር ዓመታት ተካሂዷል፡፡ ትግራይ የመጀመሪያው የወያኔ አመፅ የተነሳው ዩኒቨርሲቲው ከመመሥረቱ በፊት ነው፡፡ በኦጋዴን የነበረው ችግርም ቀድሞ ነው የተፈጠረው፡፡

ለአብነትም፤ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በጻፉት ‹‹የለውጥ ያለህ›› ተማጽኖና የማስጠንቀቂያ ደብዳቤያቸው፤ ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች መብት ጥያቄ›› በጊዜ መፍትሔ ካልተሰጠው ውሎ አድሮ የአገሪቱ አደጋ፣ ቀውስ መሆኑ የማይቀር ሐቅ መሆኑን እንደሚከተለው ገልጸውላቸው ነበር፤

‹‹… ከሁሉ በላይ ግርማዊነትዎ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለው እንቅስቃሴ በተለይ የብሔሮች ጥያቄ አንድ ወቅት ፈንድቶ አደጋ እንደሚያመጣ እንዲገነዘቡት እፈልጋለሁ፡፡ ግርማዊነትዎ አቤቱታዬ እንደ ፊተኞቹ ደብዳቤዎቼ ያነጣጠረው የኢትዮጵያን ሕዝብ ለሥቃይና ለእንግልት የዳረጉትን ጭቆናዎችና ስሕተቶች እንዲያስተካክሉና አሁንም ቢሆን ጊዜው እንዳልመሸ ለማሳሰብ ጭምር ነው፤››

እንግዲህ ልብ ልንለው የሚገባው ጉዳይ ዩኒቨርሲቲ ሳይኖርና ተማሪው ትግል ሳይጀምር በፊት ነበር በሀገራችን ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች መብት›› ጥያቄ ይነሳ የነበረው፡፡

- የዘውዱ መንግሥት የቁጣ በትር በተማሪዎች ላይ  

የዘውዱን ሥርዓት ዙፋን ያነቃነቁ ጥያቄዎችን ይዞ የተነሣው የተማሪዎች የለውጥ እንቅስቃሴ በሥርዓቱ ላይ በፈጠረው ጫና የተነሣ መንግሥት ቀስ እያለ በተማሪዎቹ መሪዎችና አመራሮች ላይ የአፈና፣ የግዞትና የግድያ ርምጃዎችን እንዲወስድ ገፋፋው፡፡ በዚህ ሁኔታም በ1964 የተማሪዎች እንቅስቃሴ ዋና መሪ የነበረው ጥላሁን ግዛው ተገደለ፡፡ ይህ የመንግሥት ዕርምጃ ክፉኛ ያስቆጣቸው ተማሪዎችም፤

ጥላሁን ለምን ለምን ሞተ?

ዋለልኝ ለምን ለምን ሞተ?

ማርታ ለምን ለምን ሞተች?

በኃይል በትግል ነው፣

ነጻነት የሚገኘው፡፡

በሚል መፈክር የለውጥ እንቅስቃሴያቸውን ወደ ሌላ ወሳኝ ምዕራፍ እንዲሻገር አደረጉት፡፡ በነገራችን ላይ ጥላሁን ግዛው ከንጉሣውያኑ ቤተሰብ የተገኘ ቢሆንም ያን በተረት ተረትና በግብዝነት ላይ የተመሠረተ ማንነት አሽቀንጥሮ ጥሎ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ራሱን የጭቁኑ ኢትዮጵያውያን ወገን አድርጎ ነበር ሲቆጥር የነበረው፡፡

በአውሮፕላን ጠለፋ ሙከራ ወቅት የተገደሉት ዝነኛው የተማሪዎቹ እንቅስቃሴ መሪና ፖለቲከኛ ዋለልኝ መኮንንም በተመሳሳይ ሁኔታ ራሱን ከጭቁኑ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚመድብ ነበር፡፡ የጥቁር አንበሳ የህክምና ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበረችውና በአይሮፕላን ጠለፋው ወቅት በጥይት ተደብድባ የሞተችው ማርታ መብራቱም፣ አባቷ ጄ/ል መብራህቱ ፍስሐ የጃንሆይ ከፍተኛ መኮንንና ባለ ሥልጣን ነበሩ፡፡

እንደ እነ ጥላሁን ግዛው፣ ዋለልኝ መኮንን፣ ማርታ መብራህቱ የመሳሰሉ ኮከብ የሆኑ የትግል አጋሮቻቸውን በእስራት፣ በግዞትና በሞት የተነጠቁ ተማሪዎቹ ትግላቸው መሥዋዕትነትን የሚጠይቅ መሆኑን አስተማሩበት፣ ቀሰቀሱበት፡፡ ዐድዋና የአምስት ዓመቱ የፋሽስት የኢጣልያን ወረራ ድል የመቶ ሺህዎች ደምና አጥንት ውጤት መሆኑን ተገንዝቦ፤

ፋኖ ተሰማራ፣ ፋኖ ተሰማራ፣

እንደ ሆችሚኒ፣ እንደ ቼጉቬራ፣

በዱር በገደሉ፣ ትግሉን እንድትመራ፡፡

የሚሉት የቆዩ ወኔ ቀስቃሽ ዝማሬዎች የሰልፉና የተቃውሞው ማድመቂያና መቀስቀሻ ሆኑ፡፡ ማንነቱን ለሕዝብ መብትና ነጻነት አሳልፎ ሊሰጥ የተዘጋጀ በነፍሱ የቆረጠ ትውልድ በኢትዮጵያ ምድር ድምፁ እንደ ብዙ ውኆች ድምፅ ከፍ ብሎ ተሰማ፡፡ ቅድሚያ ጩኸቱ ለሀገርና ለሕዝብ ያደረገ ትውልድ፣ ያ ሩቅ አላሚ ቅርብ አዳሪ የሆነ ትውልድ!

ተው ስማኝ አገሬ፣ እረ ስማኝ አገሬ፣

ተው ስማኝ አገሬ፣ ሲከፋኝ ነው መኖሬ፡፡

ስማኝ ያገሬ ሰው፣ በአንድ ላይ ተነሳ፣

ድር ከተባበረ፣ ይጥላል አንበሳ፡፡ በማለት የዘመናት ብሶት እንጉርጉሮውን አሰማ፡፡

- ለውጥ ፈላጊ የዛን ጊዜው ተማሪዎች/ያ ትውልድ፤

‹‹ድሃ፣ ድሃ ምን ታየበት፤

እንዳይማር የሆነበት፤››

ብሎ ትምህርት ለሁሉም ብሎ የጮኸ ትውልድ ነው፡፡ ማንም የማንንም መብት ሰጪና ከልካይ አይደለም ብሎ፣ ‹‹የዲሞክራሲ መብት ያለገደብ ለሁሉም›› በሚል ደሙን አፍሶበታል፡፡ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጣ ‹‹ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት አሁኑኑ›› መፈክሩ በሥልጣን ጥመኞች ጥይት ሕይወቱን ገብሮበታል፡፡ ‹‹የሴቶች መብት ይረጋገጥ›› መፈክሩ ጀግና ሴቶችን ወደ ትግሉ አደባባይ አሰልፏል፡፡ ሕይወታቸውን እስከ ጽንሳቸው የከፈሉ ታሪክ መዘገባቸው የትግል እመቤቶችን አፍርቶበታል፡፡

‹‹የሃይማኖት እኩልነት መረጋገጥ›› መፈክሩ እስላምና ክርስቲያኑ በአንድ ዓላማ አሰልፎ፣ አስተቃቅፎ አታግሏል፡፡ ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች መብት ያለገደብ›› ጩኸቱ ኦሮሞው፣ አማራው፣ ትግሬው፣ ጉራጌው፣ ወላይታው፣ አደሬው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በጋራ እንዲሰለፍ አድርጎታል፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ የተጠራቀመ የዘመናት ብሶት ወለደው የተማሪዎቹ እንቅስቃሴ በጊዜ ሂደት የ1966ቱን የየካቲት ሕዝባዊ አብዮትን የወለደው፡፡

ይቀጥላል . . .

(ይህ ጽሑፍ ማስታወሻነቱ፤ በቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን መስሪያ ቤት የማይዳሰሱ ቅርሶች /Intangible Heritage/ ከፍተኛ ኤክስፐርት፤ የኢትዮጵያና አፍሪካ ታሪክ ተመራማሪ፣ ተቆርቋሪ ለነበረው ለወዳጄ፤ ለነፍሰ ኄር አቶ ኃ/መለኮት አግዘው እና በቅርቡ በሞት ለተለየን፤ ‹ለታሪክ አዋቂውና ለታሪክ ነጋሪው› ለነፍሰ ኄር፣ ገነነ መኩሪያ/ሊብሮ ይሁንልኝ)፡፡

 

 

 

 

 
https://amharic.zehabesha.com/archives/189590

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...