Tuesday, March 26, 2024

ለአቶ ኤፍሬም ማዴቦ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ዋናው ችግር ምንድነው? ብሎ ለጠየቀውና “መልስም ለመስጠት ለመኮረው” የተሰጠ ትችታዊና ሳይንሳዊ ሀተታ መልስ!! ቁጥር ፪
የዛሬዋ ኢትዮጵያ ትልቁ ችግር ሳይንሳዊ ዕውቀት ጋር አለመተዋወቅ፣ የንቃተ-ህሊና አለመኖር ወይም አለመዳበር፣ ጥያቄ ለመጠየቅ ያለመቻል ችግር ነው! ለአቶ ኤፍሬም  ማዴቦ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ዋናው ችግር ምንድነው? ብሎ ለጠየቀውና “መልስም ለመስጠት ለመኮረው” የተሰጠ ትችታዊና ሳይንሳዊ ሀተታ መልስ!! ቁጥር ፪     

      Sometime people don`t want to hear the truth because they don`t want their illusion       

      destroyed. (Friedrich Nietzsche)

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

         መጋቢት 17፣ 2016(March 26,  2024)

 

መግቢያ

ኤፍሬም ማዴቦ “የዛሬዋ ኢትዮጵያ ዋናው ችግር ምንድነው? ብሎ ላቀረበው ጥያቄና መልስም ለመስጠት ለሞከረው፣ የሱን ጽሁፍ ተመርኩዤ ደረጃ በደረጃ ሰፋ ያለ ሂሳዊ ሀተታ ሰጥቼበታለሁ። ኤፍሬም ማዴቦም ሆነ አንዳንድ ጽሁፌን ያነበቡ ግለሰቦች የጽሁፌን መሰረተ-ሃሳብና የተመረኮዝኩበትን ሳይንሳዊ መሰረት ሳይረዱ ከጽሁፌ ጋር የማይጣጣም ወይም ጽሁፉን የማይመለከት ትችት ለማቅረብ ሞክረዋል።

በመጀመሪያ ደረጃ እንዲታወቅልኝ የምፈልገው በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታና ከዓለም ፖለቲካ ጋር የተያያዙ ሳይንሳዊ ሀተታዎችን በእንግሊዘኛ፣ በጀርመንኛም ሆነ በአማርኛ ቋንቋዎች በመጻፍ ለንባብ አቅርቤአለሁ። እነዚህም ጽሁፎች ደረጃ በደረጃ በድረ-ገጼ ላይ ተቀምጠው ይገኛሉ። የተለያዩ ጽሁፎቼን ያነበበ ሰው ሊገነዘበው የሚችለው  ነገር አንዳችም ቦታ ላይ  ከተጨባጭ ሁኔታዎችና ከሰዎች ድርጊቶች፣ በተለይም የፖለቲካ ተዋናይ ነን ከሚሉትና፣ በተለይም ደግሞ በፖሊሲ ደረጃ ረቅቀው ተግባራዊ ከሁኑ ነገሮችና አሉታዊ ውጤታቸው ውጭ የጻፍኩበት ጊዜ የለም። ጽሁፎቼ ከኢትዮጵያ ውጭ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥም በመነበብ የድጋፍ መልዕክቶችና ያልገባቸው ነገሮች ካሉ በጥያቄ መልክም ደርሰውኛል። ኤፍሬም ማዴቦ ያቀረበውን ”የዛሬዋ ኢትዮጵያ ዋናው ችግር ምንድነው?” የሚለውን ጽሁፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው ያነበቡ ሰዎች ከጽሁፉ ብዙ ቁም ነገሮችን እንደተማሩ በኋትስ አፕ መልዕክት አስተላልፈውልኛል። እስካሁን እንድተከታተልኩት ከሆነ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ዘንድ አንዳንድ የማቀርባቸውን ክሪቲካል የሆኑ ጽሁፎቼን አስመልክቶ በሚገባ የማንበብና የመረዳት ችግር ያለባቸው ይመስለኛል። በአንዳንዶች ዘንድ  የሚታየው ይህ ዐይነቱ ችግር ደግሞ በተለያዩ መንገዶች ዕውቀት በተስፋፋበትና፣ የተለያዩ የሳይንስና የፍልስፍና መጽሀፎች እንደልብ በሚገኝባቸው በአሁኑ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ነው። መጽሀፍ ለመግዛት ቢከብድም እንኳ ካለምንም ወጭ ከመጻህፍት ቤቶች መጻፎችን በመዋስ በጣም ጠቃሚና ለጭንቅላት ገንቢ የሆኑ ዕውቀቶችን መቅሰም ይቻላል። በአሁኑ በኢንተርኔት ዓለምም አንዳንድ መጽሀፎችን ገንዘብ ሳይከፍሉ ማውረድና ማንበብ ይቻላል። ባጭሩ አንድ ሰው ከተለያዩ ዕውቀቶች ጋር የሚተዋወቅ ከሆነ በቀላሉ ግራ ሊጋባ አይችልም። እንዲያም ሲል ሳይንስ እያልክ ግራ አታጋባን ብሎ ሊጽፍ አይችልም። በሌላ ወገን ግን ማንኛውም ጽሁፍ ትችታዊ በሆነ መልክ መገምገምና ተገቢው ሂስ መቅረብ አለበት። ተተቸሁ ብሎ ቡራ ከረዩ የሚል ሰው ከሌሎችም ለመማር የማይፈልግ ሰው ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ነገር አውቃለሁ የሚል ነው። እንደሚታወቀው ማንኛውም ነገር በሂደት ላይ ያለ ነው። በየጊዜውም አዳዲስ ግኙቶችና ዕውቀቶች ይፈልቃሉ። በአንድ ዘመን ተቀባይነት ያላቸው ተሽረው በአዲስ ዕውቀቶች ይተካሉ። ይሁንና ግን ዘመን የማይሽራቸው ዘለዓለማዊ ዕውቀቶች አሉ። እነዚህም በሶክራተስ፣ በፕላቶንና፣ በአጠቃላይ ሲታይ በግሪክ ፈላስፎች የተፈጠሩ ፍልስፍናዎች፣ የተፈጥሮ ሳይንስና የማቲማቲክስ ዕውቀቶች ናቸው። እነዚህ ዕውቀቶች ደግሞ የኋላ ኋላ ላይ ከ15ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በአንዳንድ የአውሮፓ ፈላስፋዎች በመዳበርና ጥልቀትን በማግኘት ለተፈጥሮ ሳይንስ መሰረት ሊጥሉ ችለዋል። በአጭሩ ዘመን የማይሽራቸው ለሰው ልጅ የማቴሪያልም ሆነ የመንፈስ ዕድገት በጣም ጠቃሚ የሆኑ  ዕውቀቶች አሉ ማለት ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ የሚመለከተው ሰው ኤፍሬም ማዴቦ የጽሁፉን ይዘት በሚገባ ሳይረዳ  በቅድሚያ  ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ መታገል ያስፈልጋል ብዬ እንደጻፍኩ አድርጎ  በማስመሰል የጽሁፉን አቀራረብ፣ የቲዎሪ መሰረትና የሀተታ ዘዴውን ሳይረዳ  የተሳሳተ ግምገማና ትችት ለመስጠት ሞክሯል። አንድነት ሰመረ የሚባል ግለሰብም እንደዚሁ የጽሁፌንና የአሰራር ስልትና የአተናተን ዘዴዬንና ሳይንሳዊ መሰረቱን ሳይረዳ ልክ ኤፍሬም ማዴቦ የጻፈውን በማስተጋባት ለመተቸት ሞክሯል። አልፎም በመሄድ “የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ስለማትረዳና የግራ አመለካከት ስላለህ ነው እንደዚህ ዐይነት ጽሁፍ የጻፍከው” በማለት ተራ ውንጀላ መሰል ነገር ለመሰንዘር ሞክሯል። ይሁንና ግን ራሱ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታና ታሪካዊ ሂደቱን በምን መልክ እንደሚረዳ ለማስረዳት አልሞከረም። ይህ ብቻ ሳይሆን “የግራ አስተሳሰብ ስላለህ ነው እንደዚህ ብለህ የምትጽፈው ሲል” የግራ አስተሳሰብ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ለማድረግ አልሞከረም። ይሁንና አንድነት ሰመረ ጽሁፌን በደንብ አንብቦ ከሆነ በአብዮቱ ወቅት የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታና የህብረተሰብ አወቃቀር፣ እንዲሁም በጊዜው  ተፍ ተፍ በማለት አብዮቱን እናራምዳለን ወይም ለውጥ መምጣት አለበት ብለው ይታገሉ የነበሩ የተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎች ሁኔታውን በቲዎሪም ሆነ በኢምፔሪካል ደረጃ ስላላጠኑ ብዙ ስህተቶች ሊሰሩ እንደቻሉ ለማብራራት ሞክሬአለሁ። ይህ ብቻ ሳይሆን የራስን ኢጎ በማስቀደም የተወሰዱ አመጻዊ እርምጃዎች በማንኛውም የማርክሲስት መጽሀፎች ውስጥ እንዳልተጻፉና፣ ይህም አመጻዊ ድርጊት ሊፈጸም የቻለው ከጭንቅላት ብስለት ጉድለትና የፖለቲካን ትርጉም ለመረዳት ካለመቻል የተነሳ እንደሆነ ለማተት ሞክሬአለሁ። ወደ መሬት ለአራሹና የቤቶችን ወረሳ ጋ ስንመጣ በሚገባ ሳይጠኑ ተግባራዊ እንዲሆኑ በመደረጋቸው በተለይም ጥሮ ግሮ ሀብት ያፈራውን ዝም ብሎ ፊዩዳል እያሉ በመወንጀል ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀል ሊፈጠር እንደቻለ ለማሳየት ሞክሬአለሁ። እንደነዚህ ዐይነት ስህተቶችም ሊሰሩ የቻሉት የተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎችና ደርግም ራሱ ከተለያዩ ዕውቀቶች ጋር ለመተዋወቅ ባለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን በንፅፅር ጥናት(Comparative Studies) በቻይናም ሆነ በሶቭየት ህብረት በአብዮት ስም በጅምላ ተግባራዊ እንዲሆኑ የተደረጉ ዕርምጃዎች በሙሉ ምን ዐይነት ጉዳት  እንዳስከተሉ ጠጋ ብሎ ለማጥናት ባለመቻሉ እነዚህን የመሳሰሉ ስህተቶች ሊሰሩ እንደቻሉ ግልጽ ነው። ሌላው አብዮተኛ ነን በሚሉ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች የሚሰራው ትልቁ ወንጀል የታሪክን ሂደትና ውጣ ውረድነትን፣ በተለይም ደግሞ የንቃተ-ህሊናን ጉዳይ ግንዛቤ ውስጥ ሳያስገቡ የሚወሰዱ እርምጃዎችና የሚስተጋቡ መፈክሮች ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉ ጥሩ እሴቶችንና ባህሎችን እንደሚያናጉና ህብረተሰብአዊ  መመሰቃቀልን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አለመረዳት ነው። ከዚህ ሁሉ ውስጥ አደገኛውና ለምሁራዊ እንቅስቃሴም እንቅፋት የሚሆነው በአገራችን ምድር የተሰሩትን ስህተቶችና ወንጀሎች በሙሉ በሶሻሊዝም ወይም በግራ አስተሳሰብ ላይ ማላከኩ ነው። በህብረተሰብ ግንባታ ሂደት ውስጥ ወርቃማ መንገድ የለም። የሰው የማሰብ ኃይል እስኪዳብርና ረጋ እስኪል ድረስ ብዙ ዓመታትን ስለሚፈጅ እንደነዚህ ዐይነት ስህተቶች መሰራታቸው የታሪክ ግዴታ ነው።

ለምሳሌ የካፒታሊዝምን ዕድገት ስንመለትና በሶቭየት ህብረትም ሆነ በቻይና ውስጥ በአብዮቱ ዘመን ከተሰሩት ስህተቶች ወይም ወንጀሎች ጋር ስናወዳድረው በካፒታሊዝም የዕድገት የታሪክ ሂደት ውስጥ የተሰሩት ወንጀሎች በብዙ እጅ እንደሚበልጡ መታወቅ አለበት። በምዕራብ አውሮፓ አገሮች ውስጥ ብዙ ጦርነቶች ተካሂደዋል። ገበሬው በከፍተኛ ደረጃ ይበዘበዝና እንደ ግል ሀብትም ይቆጠር ነበር። ከባላባቱ ፈቃድ የሚያርስበትን መሬትና የሚኖርበትን ጓሮ ጥሎ የመሄድ መብት አልነበረውም። ገበሬው ለማግባት ከፈለገ ባላባቱን ፈቃድ መጠየቅ ነበረበት። ይህንን ዐይነቱን ጭቆናዊ ድርጊት በመቃውም በፊዩዳሉና በገበሬው መሀከል ብዙ ጦርነቶች ተካሂደዋል። በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን የሰፈነውን ጭቆናዊ አገዛዝና ጭፍን የሆነውን የካቶሊክ ርዕዮተ-ዓለም የተቃወሙና ትክክለኛውን ሳይንሳዊ መንገድ ለማሳየት የሞከሩና ያረጋገጡም ከነነፍሳቸው እንዳሉ ተቃጥለዋል። ብዙ ምሁራንም አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ለመደርግ በቅተዋል። ካፒታሊዝምም በአሸናፊነት ከወጣ በኋላ የባርያ ንግድና ቅኝ-ግዛት ተስፋፍተዋል። በእነዚህ መሰረቶች ላይ በመመርኮዝ ነው ካፒታሊዝም ከፍተኛ የሀብት ክምችት ማዳበር የቻለው። አሜሪካ የተቆረቆረቺው 17 ሚሊዮን የሚያህሉ ኢንዲያኖችን በማረድና ታሪካቸውንና ስልጣኔያቸውን በማውደም ነው። የኋላም ኋላም የአንደኛውና የሁለተኛው ዓለም ጦርነቶች ሰለጠንኩ በሚለው በካፒታሊስቱ ዓለም የተቀሰቀሱና ለብዙ ሚሊዮኖች ሰዎች ህይወት መቀሰፍ ምክንያት የሆኑ ናቸው። ባጭሩ ለማለት የምፈልገው የግራ አመለካከትን ወይም የሶሻሊስት አስተሳሰብን የሚቃወም ወይም ይህን አስተሳሰብ ያራምዳሉ የሚላቸውን የሚወነጅል ሰው ወይም ቡድን በካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ግንባታ ታሪክ ውስጥ የተፈጸሙትን ወንጀሎች ሁሉ ማወቅም አለበት። ይህ ብቻ ሳይሆን መጻፍና ማብራራትም አለበት።  በሌላ ወገን ግን አንድነት ሰመረ ያልተረዳው ነገር እሱ እኔን “የግራ አመለካከት ያለህ ነው” ብሎ ሲወነጅለኝ ራሱ የቀኝ ወይም ፋሺሽታዊ አመለካከት ያለው ለመሆኑ ያለመረዳቱ ነው። በመሰረቱ በሳይንስ ዓለም ውስጥ የግራና የቀኝ አስተሳሰብ የሚል አቀራረብ የለም። ሳይንስ ሳይንስ ስለሆነ ማንኛውም የተፈጥሮንም ሆነ የህብረተሰብን አወቃቀር በሚመለከት አንድ ሰው ጽሁፎችን መጻፍ ያለበት ሳይንሳዊ መሰረትን ምርኩዝ በማድረግ ብቻ ነው። ይህም ማለት የህብረተሰብን አወቃቀር ሁለንተናዊ በሆነ መልክ ከቲዎሪም ሆነ ከኢምፔሪካል አንፃር በመመርመር ብቻ ነው።

ይሁንና በህብረተሰብ የግንባታ ታሪክ ውስጥ በአገሮች ውስጥ የፖለቲካ መዛባት፣ እንዲያም ሲል የጭቆናና የሀብት ክፍፍልና የድህነት ጥያቄዎች፣ ማለትም የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጥያቄዎች አፍጠው አግጠው የነበሩ ጉዳዮች ስለሆኑና፣ በተለይም ስልጣንን የጨበጡና ተጠቃሚ ኃይሎች ሀብትን በተስተካከለ መልክ ለማከፋል ስለማይፈልጉና የማህበራዊ ችግሮችም እየጎሉ ስለመጡ ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ወደ ህብረተሰብአዊ ግጭት እንዳይሸጋገር የግዴታ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፍትሃዊነት መስፈን እንዳለበት አንዳንድ የተገለጸላቸው ምሁራን በተለይም ተጨቆነ፣ ወይም ተበደለ ከሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ጎን በመቆም ለፍትሃዊነት ታግለዋል። አንዳንዶችም ቀደም ብለው በመሄድና ሳይንሳዊ ሀተታ በመሰጠት ለመሰረታዊ ለውጥ ታግለዋል። እነዚህ ዐይነቱ የተገለጸላቸው ምሁራን ለመሰረታዊ ለውጥ ሲታገሉ በ19ኛው ክፍለ-ዘመንና በ20ኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ላይ  የነበረውን የድህነት መስፋፋት፣ የከተማዎች መቆሸሽና፣ በተለይም በየፋብሪካዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችን የስራ ሁኔታና በሰውነታቸው ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ በሚገባ ከተመለከቱና፣ የፋብሪካም ስራ በዚህ መልክ መዋቀር የለብትም ብለው ሰፋ ያለ ሀተታ መስጠት ከጀመሩ በኋላ ነው። በተለይም የኢንዱስትሪ አብዮት ሲካሄድ ተፈጥሮንና የሰውን ልጅ በከፍተኝ ደረጃ የሚጎዱ ነገሮች ስለተከሰቱና ህብረተሰቡም በከፍተኛ ደረጃ መመሰቃቀል ስለጀመረ የግራ ወይም የማርክሲዝም አስተሳሰብ ከመስፋፋቱ በፊት የሰብአዊነት ባህርይ ያላቸውና ጠለቅ ብለው የሚያስቡ ምሁራን በአንድ አገር ውስጥ ለውጥ በዚህ መልክ መካሄድ የለበትም በማለት ይታገሉ ነበር። ይህም የሚያመለክተው እንደኛ አገር ሳይሆን በአውሮፓ የምሁራን እንቅስቃሴ ታሪክ ውስጥ የነገሮችን ሂደት ትችታዊ በሆነ መልክ የመመልከትና ሀተታ የመስጠት ልምድ ስላለ  እንደኛ አገር ዝም ብሎ የሚታለፍ ነገር የለም።  አብዛኛዎችም ሀተታዎች በአቦሰጡኝ ሳይሆን የሚጻፉት በስልትና ሳይንሳዊ መሰረተ-ሃሳብን በማስደገፍ ብቻ ነው። በጭፍን መጓዝ የተለመደ ነገር አይደለም ማለት ነው። በሌላ ወገን ያለው ሁኔታ መለወጥ ወይም መሻሻል የለበትም ብለው የሚታገሉና ሳይሰሩና ሳይንቀሳቀሱ ሌላው በሰራው ተንደላቀው ለመኖር የሚፈልጉ ሰዎች ነበሩ። እነዚህም ቀኝ የሚባል ስም ተስጥቶአቸዋል። አንዳንዶችም ከዚህ ገፍተው በመሄድ ወዝአደሩንና መሪዎችን፣ ወይም የእሱን ጥቅም ያራምዳሉ የሚባሉ ምሁራንን እንደዋና ጠላት በማየት ያሳድዱና ይገድሉ እንደነበረ ይታወቃል። እነዚህ ኃይሎች የኋላ ኋላ አደገኛ አዝማሚያ በመውሰድ ከሌሎች ሁኔታዎች ጋር በመዳበል ለፋሺዝም እንቅስቃሴ መነሳት እንደዋና ምክንያት ለመሆን በቅተዋል።

ከዚህ አጭር ሀተታ ስንነሳ የህዝብ ኑሮ መሻሻል አለበት፣ የኢኮኖሚው እንስቃሴና ዕድገት ሰፋና በጠነከረ መሰረት ላይ መገንባት አለበት ብሎ መታገል የግራ አመለካከት ተብሎ ሊወነጀል የሚገባው ጉዳይ አይደለም። ለውጥ ወይም መሻሻል አያስፈልገንም የሚል ሰው ካለ የግዴታ እዚህ አገር የቀኝ ወይም የፋሺሽት ኃይሎች ከብዙ አስርት ዓመታት ጀምሮ እንደሚታገሉት የራስን አቋም ግልጽ በማድረግ መታገል የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ካለበለዚያ የሰውን አስተሳሰብ የግራ አስተሳሰብ እያሉ ማስፈራራት ኃይልን መበታተንና ብዙ ነገሮች ተድበስብሰው እንዲቀሩ ማድረግ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በምንም ዐይነት ለውጥ አያስፈልግም ማለት ነው። ስለሆነም የእኔ አቀራረብ የአገራችንን ሁኔታ በሚገባ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ በሆነ መልክ መነበብና መጠናት ስላልተቻለና ልምድም ስለሌለን ነው እንደዚህ ዐይነቱ መወናበድና ዕልቂት ለመድረስ የቻለው ስል  ትግላችን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ብቻ ያትኩር ማለቴ ሳይሆን በጭንቅላት ዙሪያና መንፈስን በማጎልበስ መሰራት የነበረባቸው ነገሮች ስላልተሰሩ አብዮተኛ ነኝ ይል የነበረው ታጋይና መሪዎቻቸው ከመደማመጥ ይልቅ እንደ ጠላት በመተያየት ወደ መሳሪያ ትግል አመሩ ለማለት ፈልጌ ነው። የመሳሪያን ትግል የሚያስቀድምና ወደ አመጽም የሚያደላ ግለሰብም ሆነ ቡድን ጭንቅላቱ በሚገባ ያልተኮተኮተ ስለሆነ በመሰረቱ ሰፋ ያለና ለጭንቅላት መዳበር፣ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ የሚያመቸውን በሁሉም መልክ የሚገለጸውን ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዲዳፈን ያደርጋል። በተግባርም ያየነው ይህንን ሀቅ ነው። በትግራይ ክልልና በኤርትራ ውስጥ ያሉት ሁኔታዎች ይህንን ነው የሚያረጋግጡት። በአገራችንም ምድር የሚታየው ሁኔታ ከምሁራዊ እንቅስቃሴ የራቀና በአመጽ ላይ የተመሰረተ አገዛዝ ነው። ፖለቲካን ወደ ማወናበድ፣ ወደ ተራ ተንኮልና ወደ ሽብርተኝነት የለወጠ አገዛዝ ካለፉት ስድስት ዓመታት ጀምሮ በአገራችን ምድር የፖለቲካውን መድረክ በመቆጣጠርና የመጨቆኛ መሳሪያውን ተገን በማድረግ አገራችንን በሁሉም መልክ በማዘበራረቅ ለዲሞክራሲና ለነፃነት የሚደረገውን ትግል ፈሩን እንዲስት አድርጎታል።

ኤፍሬም ማዴቦ የኢኮኖሚ ችግር አለ፣ ደርግም የተከተለው የማይገባውን የሶሻሊስት ኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ሲል፣ ይህ ትክክል አለመሆኑና ደርግ ስልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት የነበረውን የአገራችንን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታ በማሳየት፣ ከአፄ ኃይለስላሴ አገዛዝ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተሳሳተ መሰረት ላይ ለመመርኮዝ በመቻሉ ይህ ሁኔታ ለኢኮኖሚ ዝቅጠትና ለማህበራዊ ሁኔታ መዳከም እንደዳረገን ለማሳየት ነው የሞከርኩት። አንድነት አስመረ ጽሁፌን መስመር በመስመር በሚገባ ቢያነብ ኖሮና ቀድም ብዬ ካወጣኋቸው አያሌ የኢኮኖሚ ጽሁፎቼ ጋር ቢያወዳድር ኖሮ ተራና ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ ውንጀላ ውስጥ ባልገባ ነበር። የኤፍሬም ማዴቦንም ጽሁፍ በሚገባ ካነበብኩ በኋላ ነው መሰረታዊ ትችት ለመስጥት የሞከርኩት እንጂ ሙሉ የምትባል ሌላዋ ተቺ እንደምትለው ግራ ለማጋባት የጻፍኩት ነገር አይደለም። ሁልግዜ ግራ የሚጋባ ሰው መሰረታዊ ዕውቀት የሌለውና መጽሀፎችንም የማንበብ ልምድ የሌለው  ሰው ብቻ ነው። ይህንን ካልኩኝ በኋላ ኤፍሬም ማዴቦ ባነሳው ጥያቄና በእኔ ግምት ግልጽ ያላደረጓቸው ነገሮች አሉ በምላቸው ነገሮች ላይ አንዳንድ ማብራሪያዎችን እንደገና ለመስጠት እሞክራለሁ። እንደገና ስል ቀደም ብዬ ባወጣኋቸው አንዳንድ ጽሁፎቼ ላይ ብዙ ነገሮችን ለማብራራት የሞከርኩ ስለነበር በዚኸኛው ጽሁፌ ላይ እንደገና ለመመለስ ስላልፈለጉ ዝምብዬ ስላለፍኩ አንባብያን ግራ ተጋብተው ይሆናል በሚል አስተባብ ብቻ  ነው።

 

እረ ለመሆኑ ሳይንሳዊ ዕውቀት ሲባል ምን ማለት ነው?

“የዛሬዋ ኢትዮጵያ ዋናው ችግር ከሳንይሳዊ ዕውቀት ጋር አለመተዋወቅ ነው” ስል በመጀመሪያ ደረጃ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ መታገል ማለቴ ሳይሆን፣ ተፈጥሮንም ሆነ የአንድን ህብረተሰብ አወቃቀር ጠጋ ብሎ በማየት(Observe) ከላይ ከሚታዩት ነገሮች በማለፍ ተፈጥሮንንም ሆነ ህብረተሰብን ምን ምን ነገሮች እንደሚያያዛቸውና፣ እንዴትስ አንደኛው ነገር በሌላኛው ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ለመረዳት መሞከር ማለት ነው። የተፈጥሮን ነገር ትተን ወደ ህብረተሰብ ጋ ስንመጣ፣ ከመንግስት አወቃቀር አንስቶ ሰለፖለቲካ አወቃቀርና፣ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ያሉትን ነገሮች ደረጃ በደረጃ ማጥናት ያስፈልጋል። የእነዚህ ነገሮች ደግሞ በስርዓትና በጥናት ወይም ደግሞ ያለስርዓትና ካለጥናት መዋቀር በጠቅላላው ህብረተሰብ ላይ ሊኖረው የሚችለውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንድንገነዘበው ይረዳናል። ለዚህ ደግሞ ሳይቻኮሉ ጊዜ በመውሰድ ጥናትና ምርምር በማድረግ ብቻ ነው መገንዘብ የሚቻለው። በጥናትና በምርምር መልክ የሚታገዝ ግምገማ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ለዕድገት፣ ለስልጣኔ፣ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ምጥቀት እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን እንድናውቅና ቀስ በቀስም ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ እርምጃዎችን ደረጃ በደረጃ እንዲወሰዱ ግፊት ለማድረግ ያስችላል። ይህ ብቻ ሳይሆን በጥናትና በምርምር ላይ የሚደገፍ ህብረተሰብአዊ ሀተታ ለተከታታዩ ትውልድም እንደመነሻ በመውሰድ በዚያው እንዲቀጥል ይገፋበታል፤ የማሻሽልና የማስፋፋት ዕድልም ያገኛል።

የአንድ ህብረተሰብ ዕድገት ስልጣንን በተቆናጠጡ ወይም በመንግስት ብቻ የሚሳበብ አይደለም። አንድን ህብረተሰብ የሚያያዙ ልዩ ልዩ ባህሎችና እሴቶች፣ እንዲሁም የፈጠራ ስራዎች በሙሉ ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በግለሰቦች ወይም በቡድን የሚፈጠሩና የሚተገበሩ ናቸው። የሃይማኖትን ጉዳይ ወደ ጎን በመተው ለምሳሌ የእርሻ ስራንና በኢትዮጵያ ምድር የተገኙትን ሰብሎችና መራባት ስንመለከት ገበሬው በማየት፣ በሙከራና በልምድ ያስፋፏቸው ናቸው። ለምሳሌ ጤፍ በየትኛው ክፍለ-ዘመን እንደተገኘና ገበሬውም ለምን ጤፍን እንደ እህል በመቁጠር በመዝራትና ለምግብ እንዲውል ማድረጉ የሚታወቅ ነገር የለም። ይሁንና ይህ ዐይነቱ የአስተራረስ ባህልና እንደጤፍ የመሳሰሉትን ለምግብ እንዲሆኑ ማድረግ ራሱን የቻለ የፈጠራ ችሎታ ብቻ ሳይሆን፣ አንደኛው የዕድገት መገለጫና ህብርተሰብአችንንም ለማያያዝ የቻለ ነው ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በዚህ ረገድ ገበሬው በረቀቀ መልክ በማሰብና ልዩ ልዩ ሰብሎችንና ለዘይት የሚሆኑ እንደተልባና ሰሊጥ፣ እንዲሁም ኑግ የመሳሰሉትን በመዝራትና በማስተዋወቅ በአገራችን ምድር የምግብ አብዮት እንዲካሄድ ለማድረግ በቅቷል። እናቶቻችንም ይህንን ዕድል በመጠቀም እንጀራና ዳቦ በመጋገር ለአገራችን የባህል ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለማበርከት ችለዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን እንደ ጠላ፣ ጠጅና ካቲካላ የመሳሰሉትን እዚያው አገር ውስጥ በመፍጠርና በመጥመቅ የባህል መጠጦች እንዲሆኑ ለማድረግ በቅተዋል። የእነዚህን መጠጦች አጠማመቅ ስንመለከት ደግሞ ሳይንሳዊ ናቸው። ለምሳሌ የካቲካላን አጠማመቅ ስንመለከት ለካቲካላ የሚሆን የእህል ዐይነት ዳጉሳ ብቻ ነው። ይህ እህል በመጀመሪያ ደረጃ በውሃ እንዲበቅል ከተደረገ በኋላ ከጌሾ ጋር በመዋሃድ በመቆምጠጥ በስሎ ድፍድፉ በጋን ውስጥ ተቀምጦ በትንሽ እሳት እንዲበስል ይደረጋል። የተወሰነ የቴምፕሬቸር መጠን ላይ ከደረሰ በኋላ እንፋሎቱ በቀርቀሃ ጠብ ጠብ  በማለት ካቲካላ ይወጣዋል። የካቲካላ አጠማመቅም ሂደት ኬሚካላዊና ፊዚክስ ነው። መኮምጠጡ የኬሚካል ሂደት ሲሆን፣ ሲቀቀልና ወደ እንፋሎት ተለውጦ ካቲካላ ሲሆን ደግሞ ፊዚክስ ነው። ባጭሩ እናቶቻችን በኢንቲዩሽን  ደረጃ ሳይንቲስቶች ናቸው ማለት ይቻላል። ይህ ዐይነቱ የካቲካላና የጠላ አጠማመቅ በማዕከለኛው ዘመን በምዕራብ አውሮፓ የተለመደና ቀስ በቀስም ወደ ኢንዱስትሪ ምርትነት የተለወጠ ነው። ጌሾም በአውሮፓ ምድር የተስፋፋና ለቢራ ጠመቃና ለልዩ ልዩ የአልክሆል መጠጦች መጥመቂያ የሚያገለግል ነው። ይህንን ሁኔታ ስንመለከት በጥንት ዘመን አንደኛው አገር ከሌላው ሳይኮርጅ በማየት፣ በሙክራና በልምድ ብዙ ነገሮችን እንዳገኘና እንደፈጠረ ለመገንዘብ እንችላለን።

ወደ አባባሌ ስመጣ ከሳይንሳዊ ዕውቀት ጋር ስላልተዋወቅ ነው እንደዚህ ዐይነቱ ወንጀል ለመሰራት የተቻለው ስል ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ማለት የአንድን ህብረተሰብ ምንነት፣ የተጓዘበትንና በሂደት ውስጥ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተፈጠሩ፣ ይሁንና ደግሞ ለህዝብ ጠቀሚታ ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ለመጠናት ባለመቻላቸውና በቁንጽል አስተሳሰብ ላይ ብቻ መረባረብ ስለተጀመረ የማያስፈልግ ግብግብ ውስጥ ለመግባት ቻልን ማለቴ ነው። እንደዚህ ስል ግን የመሬት ላራሹ የመሳሰሉት ነገሮች በተጠናና ፊዩዳል የሚባለውንም የህብረተሰብ ክፍል በማይጎዳ መልክ መታወጅና መተግበር የለባቸውም ማለቴ አይደለም። በማንኛውም አገር፣ በተለይም ደግሞ በካፒታሊስት አገሮች ውስጥም የጥገና ለውጦችና እንዲያም ሲል ገበሬውን ከቀየው ሳያፈናቅሉ የኢንዱስትሪ አብዮት የመሳሰሉትና በአጠቃላይ ሲታይ ኢኮኖሚያዊና ህብረተሰብአዊ ዕድገት ለመምጣት ባልቻለ ነበር። በሌላ ወገን ግን የሚነሳው ጥያቄ ጥገናዊ ለውጥም ሆነ የኢንዱስትሪ አብዮትን ለማካሄድ የግዴታ ገበሬው ከመሬቱ መፈናቀል አለበት ወይ? የሚለው ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። በጊዜው የነበረው አስተሳሰብ ፊዩዳላዊ ስለነበረና ፖለቲካ የሚባለው አስተሳሰብ ስር የሰደደ ስላልነበረና የኃይል አሰላለፉም ለከበርቴው መደብ የሚያደላ ስለነበር ገበሬው ዝም ብሎ ከማየት በስተቀር ሌላ አማራጭ አልነበረውም።  ይሁንና ግን በአጠቃላይ ሲታይ በማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ በተጠና መልክና በዕቅድ አንድን ህብረተሰብ የሚጠቅሙና እንደማህበረሰብም የሚያያዙት ነገሮች ቀሰ በቀስ ተግባራዊ መሆን አለባቸው። ካለጥገናዊ ለውጥ መሻሻልና ዕድገት በፍጹም ሊታዩና ሊመጡ አይችሉም።

በአጠቃላይ ሲታይ የህብረተሰብአዊ ለውጥን ሂደት ስንመለከት ስልጣኔ ሊመጣ የቻለው ጥቂት ምሁራን የማሰብ ኃይልን ከፍተኛ ቦታ በመስጠት ነው። ምክንያቱም የማሰብ ኃይሉን ለመጠቀም የማይችል ሰው ወይም የህብረተሰብ አካል ኃይልን ስለሚያስቀድም የግዴታ በቀላሉ እልባት ሊያገኝ የማይችል ህብረተሰብአዊ ውዝግብ ውስጥ ይገባል። ህብረተሰብአዊ  ውዝግብ ባለበታገር ውስጥ ደግሞ አንደኛው የህብረተሰብ ክፍል በታጠቀው መሳሪያ በመተማመን ረብሻ የሚፈጥር ከሆነ የሰው ልጅ የመፍጠር ኃይል እንዲታፈን ያደርጋል። የእያንዳንዱም ግለሰብ አስተሳስብ በማያስፈልጉና ለራስም ሆነ ለህብረተሰብ በማይጠቅሙ ነገሮች ላይ እንዲጠመድ ያደርጋል። በግሪክ ምድር በጊዜው የነበረውን በተለይም በፈረጠሙ ኃይሎች ይደረግ የነበረውን የእርስ በርስ ሽኩቻ ምክንያቱን ለማወቅ የግሪክ ፈላስፋዎች መነሻ ያደረጉት የጭንቅላትን ሁኔታ በመመራመር ነበር። ፕሌቶ የሚባለው ታላቅ ፈላስፋ በጊዜው የነበረውን ሁኔታ በደንብ ካጠና በኋላ የደረሰበት ድምደማ “የሰው ልጅ ችግር የማሰብ ችግር ነው”( Problem of Thought) በማለት በትክክል ያስቀምጣል። ፕሌቶ ይህንን ምርኩዝ በማድረግ በዕውነተኛ ዕውቀትና በተሳሳተ ዕውቀት መሀከል ያለውን ልዩነት ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጣል። በፕሌቶ ዕምነት ትክክለኛ ዕውቀት ከጭንቅላት ውስጥ በማሰብ ወይም በመመራመር ኃይል የሚገኝ ነው። ትክክለኛ ያለሆነ ዕውቀት ግን በምናያቸውና ይህንን ያህልም በጥልቀት ለማስበ በማንችልባቸው(Sense Preception) ነገሮች ላይ የሚመረኮዝ ሲሆን፣ የዚህ ዐይነት ዕውቀት በማሽተት፣ በማየት፣ በመነካካት ባጭሩ በአምስቱ የሴንስ ኦርጋኖች ላይ በመመርኮዝ የሚገኝ ዕውቀት ነው። ይህ ዐይነቱ ዕውቀት በነገሮች መሀከል መተሳሰብ እንዳለ፣ አንደኛው በሌላኛው ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችልና፣ በተለይም ደግሞ የታሪክን ሂደትና የሰውም ልጅ በሂደት ውስጥ ያካበታቸውን ነገሮች ከቁጥር ወይም ከግምት ውስጥ የማያስገባ ነው። ባጭሩ ይህ ዐይነቱ ዕውቀት በውጫዊው ዓለም ላይና በዛሬው ላይ ብቻ የሚያተኩር ነው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ የተሳሳተ ዕውቀት ሰለተፈጥሮም ሆነ ስለህብረተሰብ አገነባብ ዕውነተኛ ግንዛቤ ሊሰጠን አይችልም። በዚህ ዐይነት አስተሳስብ መንፈሱ የተቀረፀ ሰው ነገሮችን ከሁለመንታዊ አንፃር ጠጋ ብሎ የመመራመር ኃይል በፍጹም የለውም። ስለሆነም በቁንጽል አስተሳሰብ በመጠመድ ጠቅላላው ህብረተሰብ እንዲናጋ ያደርጋል። በተለይም በዛሬው ወቅት በአገራችንም ሆነ በተቀረው ዓለም የምንመለከተው መወናበድና በየአገሮች ውስጥ ውዝግብ መፈጠር ዋናው ምክንያት በተለይም የኤሊቱ አስተሳሰብ በዚህ ዐይነቱ ቁንጽል አስተሳሰብ ስለተጠመደ ነው።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በታሪክ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ በአንድ አገር ውስጥ ጦርነት፣ ኢ-ፍትሃዊነትና በአጠቃላይ ሲታይ ማህበራዊ ውዝግቦች የሚፈጠሩት ሳይንሳዊ ዕውቀት ባልተስፋፋበትና፣ በተለይም ደግሞ መንግስት የሚባለው አካል ራሱን ከማደለብ ባሻገር ህብረተሰብን በስርዓትና ምርታማ እንዲሆን ለማደራጀት ብቃትነት ወይም አስፈላጊው ዕውቀት የሌለው ከሆነ ብቻ ነው። ስለዚህ ነው ከጥንት ግዜያት ጀምሮ ሰለመንግስት ፍትሃዊ በሆነ መልከ መዋቀር ጉዳይ፣ የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠሩ ሰዎች ደግሞ አይ ፈላስፋዎች መሆን እንዳለባቸው አሊያም ደግሞ በፈላስፋዎች የሚመከሩና ሁለ-ገብ ፖሊሲ በማውጣት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው መሰበክ ወይም ማስተማር የተጀመረው። ይህ ዐይነቱ ያልተቋረጠ ትግልና ምሁራን ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ ስልጣንን ለመያዝ ሳይሆን የበለጠ መመራመር ያስፈልጋል ብለው በማትኮር ለተለያዩ ለሰው ልጅ የሚጠቅሙ ዕውቀቶችን በማፍለቅና ከአገሮቻቸው አልፈው ዓለም አቀፋዊ ማድረግ የጀመሩት። ስለዚህም ነው በግለሰቦች ጥረትና ምርምር የተነሳ ማቲማቲክስ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ ማለትም እንደ ፊዚክስ፣ ባይሎጂና ኬሚስትሪ የመሳሰሉት ዕውቀቶች በሙሉ በመፈጠር ተፈጥሮን የበለጠ በመቃኘትና በመመራመር እንዲሁም ምስጢሩንም በመረዳት በተፈጥሮ ውስጥ የሚገኙ ነገሮችን አውጥቶ ወደ መሳሪያነት በመለወጥ ልዩ ልዩ ነገሮችን መፍጠርና ማመረት የተቻለው። ቀደም ብለው በተለያዩ አገሮች የተፈጠሩት ዕውቀቶች፣ የከተማ አገነባቦች የኋላ ኋላ ለአውሮፓው ስልጣኔና ለካፒታሊዝም ዕድገት መሰረት መጣል እንደቻሉ የሚታወቅ ጉዳይ ነው።

ወደ አገራችን ስንመጣ ግን ከመንግስት አወቃቀር አንስቶ፣ እስከ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች፣ እንዲሁም ስለከተማ ግንባታዎችና መንደሮች አወቃቀር ሁኔታዎችን ስንምረመር የምናገኘው ሀቅ አብዛኛው ነገሮች በአቦሰጡኝ  የተሰሩ እንጂ በከፍተኛ ምርምርና ጥናት እንዳልሆኑ መገንዘብ እንችላለን። ይህንን ለማወቅ ደግሞ የተወለድንባቸውንና ያደግንባቸውን መንደሮችና የገጠሩን ሁኔታ ወደ ኋላ መለስ ብለን ለማየትና ለመመራመር መቻል አለብን። ለምሳሌ በተወለድንበት መንደር ወይም ገጠር ውስጥ በስርዓት ወይም ጥበባዊ በሆነ መልክ የተገነቡ መኖሪያ ቤቶች አሉ ወይ? የትምህርትቤቶችስ አገነባብና ሁኔታ ምን ይመስላል? ቤተመጻህፍቶችስ አሉ ወይ? በተወለድንበትና ባደግንበት መንደር ውስጥ ከትምህርትቤት ውጭ ለመንፈሳችን መዳበር የሚያስፈልጉ ሁኔታዎች ተዘጋጅተዋል ወይ? እያልን ጥያቄ ለማቅረብ ብንሞክር አብዛኛዎች ነገሮች ካለማሰብ ወይም ከምርምርና ከጥናት ውጭ እንደተሰሩ በቀላሉ ለመገንዘብ እንችላለን። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ የግዴታ በአስተሳሰባችንና በአዕምሮአችን ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ  ለማሳደር እንደቻለ ካለብዙ ጭንቀት መገንዘብ ይቻላል።

ይህንን ትተን ወደ ምንማረው ትምህርት ጋ ስንመጣ ትምህርቱ በዚያ መልክ ለምን እንደተዘጋጀና ለምንስ ዓላማ እንደተዋቀረ ሊነግረን የሚችል ሰው የለም። ይሁንና ግን ካለበቂ ጥናትና ካስፈላጊው ሁኔታዎች ውጭ መሰረተ-ትምህርትቤቶችም ሆነ የመለስተኛና የከፍተኛ ትምህርት መስጫ ትምህርትቤቶች እዚህና እዚያ ተቋቁመዋል። ይህ ዐይነቱ ካለብዙ ምርምርና ጥናት እንዲሁም ጭንቅላትን በሁሉም አቅጣጫ እንዲያዳብር ሆኖ ያልተዘጋጀው የትምህርት አሰጣጥና የአስተማሪዎችም ሁኔታ የግዴታ ለጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት መሰረት ሊሆን ችሏል። በዚህ መልቅ የተዋቀረው ጭንቅላታችን የኋላ ኋላ በቁንጸል መልክ ተግባራዊ ከሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር በመዳበል ሳንወድ በግድ አመጸኛ ሊያደርገን በቅቷል። እንዲያም ሲል ለመደማመጥ የማይችልና ነገሮችን ከሁሉም አቅጣጫ ለማየትና ለማንበብ የማይችል ትውልድ በመፈጠሩ ሁሉም ባይሆን የተወሰነው ጥራዝ-ነጠቅ በመሆን አገራችንን ወደ ማይሆን አቅጣጫ ሊመራት ችሏል ማለት ይቻላል። በሌላ አነጋገር፣ የነገሮችን ሂደት፣ በጊዜው የነበረውን የመንግስት መኪና አወቃቀር፣ በአጠቃላይ ሲታይ ፖለቲካ ብለን የምንጠራው፣ ይሁንና ደግሞ ፊዩዳላዊ አስተሳሰብ የሰፈነበት፣ ወይም ፖለቲካ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግንዛቤ ያለነበረበት ሁኔታና፣ ሁሉም ነገሮች በግብታዊ መልክ ይካሄዱ ስለነበር የኋላ ኋላ አመጸኛ ሊያደርገን በቅቷል ማለት ይቻላል። እነዚህ ነገሮች ደረጃ በደረጃ ሳይጠኑና፣ በተለይም ደግሞ የመንግስትን ምንነትና ሚና ሳይረዱ በአቦ ሰጡኝ የሚወሰዱ ፖሊሲ ነክ እርምጃዎች መንፈሱን ለመሰብሰብና በቅጡ ለማሰብ የማይችል የህብረተሰብ ኃይል እንዲፈጠር ለማድረግ በቅቷል። ይህ ሁኔታ የግዴታ ጥራዝ ነጠቅነትን ከማስፋፋት አልፎ፣ የነገሮችን አመጣጥና ሂደት በጥናት ላይ በመመርኮዝ ሀተታ ከመስጠት ይልቅ ወደ ተሳሳተ ትረካ ላይ ለመድረስ ተችሏል። ለዚህም ነው በጊዜው የመደብ ትግልና የብሄረሰብ ጥያቄ ወይም የጭቆና ጉዳዮች ሊነሱ የቻሉት። እነዚህ ነገሮች በመነሳታቸው፣ እንደፋሽን በመወሰዳቸውና ጭንቅላታችንን በመያዛቸው ነው ለአንድ አገርና ህብረተሰብ ጠቃሚ የሆኑት እንደ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ ማቲማቲክስ፣ የከተማ አገነባብ፣ የሶስዮሎጂና የኢኮኖሚ፣ እንዲሁም የስነ-ልቦና ዕውቀቶች አትኩሮ ሊሰጣቸው ያልተቻለው። አሁንም ቢሆን በእነዚህ ዙሪያ ጥናት የሚያካሂድና ሀተታ በማቅረብ ታዳጊውን ትውልድ የሚያስተምር የለም። አብዛኛው የተረት ተረት በማውራት ጊዜውን እንዲያሳልፍና ህዝብን እንዲያደናግር ዕድል ለማግኘት ችሏል።

ከላይ እንዳልኩት እነፕሌቶ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ያለን ችግር ለማጥናት የሞከሩት ትክክለኛ ዕውቀት በሌለበትና የማሰብ ኅይል ባልዳበረበት፣ በተለይም ደግሞ የገዢው መደብ ፍልስፍናዊ ዕውቀት ከሌለው፣ ወይም በፈላስፋዎች የማይመከርና የማይመራ ከሆነ የግዴታ ኢ-ፍትሃዊነትና ያልተሰተካከለ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ነው። ይህም ማለት የገዢው መደብ የተሳሳተና ኢ-ፍትሃዊነት ያለው ፖለቲካ የሚከተለው ወይም አመጽን የሚያስቀድመው ጭንቅላቱ በትክክለኛ ዕውቀት ያልታነፀ ከሆነ ብቻ ነው። ስለሆነም የማህበራዊ ውዝግቦች ዋናው መነሻ በቁንጽል አስተሳሰብ በመመራት ኃይልን ማስቀደም ነው። በሌላ አነጋገር፣ ጭንቅላት ወይም የማሰብ ኃይል ባልዳበረበት አገር ውስጥ ተግባራዊ የሚሆኑ ነገሮችና አንድን ህብረተሰብ ፈሩን እንዲለቅ የሚያደርጉት ነገሮች ታስቦበት(Intentionally) የሚካሄዱ ሳይሆን ካርቆ ማሰብ ጉድለት የሚተገበሩ ስለሚሆኑ ብቻ ነው።

ወደ አገራችን ሁኔታ ስንመጣ በጊዜው የነበሩትን የብሄረሰብን ሁኔታና ሌሎች ኢ-ፍትሃዊ ነገሮችንና፣ በአጠቃላይ ሲታይ ድህነትን ፈልፋይ የሆኑ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን መተግበር ጉዳይ ለመረዳት የተቻለው በቀላሉ ህብረተሰባችን በመደብ ስለተከፋፈልና የመድብ ትግል ስላለና የብሄረሰብ ጭቆና ስለሰፈነ ነው የሚል ነው። ይህ ዐይነቱ ግንዛቤ የአገራችንን አጠቃላይ ሁኔታ ከዕውቀት ማነስ ጋር ለማያያዝ ካለመሞከርና፣ በተለይም ደግሞ በቲዎሪ ደረጃ እንደ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎችና የሶስይሎጂ ምርምሮች ባልተስፋፉበት አገር ውስጥ ሊከሰቱ እንደሚችሉ ግንዛቤ ውስጥ አለማስገባት ነው። በተለይም የብሄረሰብ ጥያቄ አነሳስ በሚገባ ሳይጠና የተነሳና ማለቂያ ወደሌለው ውዝግብ ውስጥ ወይም ደግሞ ከዚህም ከዚያም ለፈለቁ የዚኸኛው ወይም የዚያኛው ብሄረሰብ መሬ ነኝ ለሚሉ፣ በመሰረቱ ዕውቀት ለሌላቸውና አመጽን ለሚያስቀድሙ መፈንጫ መድረክ የከፈተ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ነገሩን የበለጠ ለመረዳት በአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን ተግባራዊ የሆኑት የኢኮኖሚና የትምህርት ፖሊሲዎች በሙሉ አንድን ብሄረሰብ ብቻ ለመጥቀም ተግባራዊ የሆኑ አልነበሩም። ኢ-ሳይንሳዊ የሆነውና ለጥቅላላው ህዝብ ብሄራዊ ሀብት ለማዳበር የማይችለውና ለፈጠራና ለተከታታይ ምርምር መሰረት ሊሆን የማይችለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በመሆኑ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ወይም አብዛኛው  ብሄረሰብ በድህነትና በኢ-ፍትሃዊነት የሚማቅበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። ለዚህ ደግሞ የግዴታ ብዙ መማር አያስፈልግም። በቀላል ዕይታና ጥናት የነበረውን ሁኔታ መረዳት ይቻላል። ለማንኛውም ሳይንሳዊ በሆነ መልክ ለማሰብ ባለመቻሉ ወይም ከሳይንሳዊ ዕውቀት ጋር ልምምድ ስለሌለንና የነገሮችን አነሳስና ሂደት ጠጋ ብሎ መመልከት ስለማንፈልግ በተሳሳተ ትረካ ላይ ብቻ በመመርኮዝ ማለቂያ ወደሌለው ግብግብ ውስጥ ለመግባትና አገርን ለማፈራረስ በቅተናል። ባጭሩ የኤፍሬም ማዴቦ ጥያቄ አነሳስና መልስም ለመስጠት ያለመቻል በዚህ መልክ ነው ግልጽ መሆን ያለበት። ስለሆነም የአገራችንንም የተወሳሰቡ ´ችግሮች መፍታት የምንችለው በሳይንሳዊ ዕውቀት እንጂ እዚህና እዚህ ውርውር በማለትና ሰፊውን ህዝብም በማሳሳት አይደለም።

የንቃተ-ህሊና ያለመዳበር ጉዳይ የሚያስከትለው ችግር!

በፈላስፋዎች፣ ንቃተ-ህሊና(Consciousness) ራስን ማወቅ(Self Consciousness) የሚሏቸው ነገሮች አሉ።  አንድን  ነገር በማየት ይህ ነገር እንደዚህ ነው ብለን መናገር እንችላለን። በሌላው ወገን ግን በህብረተሰብ ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ወይም በተጨባጭ የሚታዩ ነገሮችን ለመረዳት በቀጥታ ለማየት ከምንችለው የሚያልፍና ቶሎ ብለን ለመገንዘብ የማንችለው ነገር ነው። ለምን አንድ ህብረተሰብ በዚህ መልክ መዋቀር አለበት? ብሎ የሚጠይቅ አንድም ግለሰብ የለም። ሁላቸንም ስንወለድ ቀድሞውኑ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በተዋቀረ ሁኔታ ውስጥ ስለምንወረወርና ስለምናድግ ያደግንበትን፣ ያየነውንና የምንኖርበትን ሁኔታ ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን በጥያቄ ውስጥ ሳናስገባ ዝም ብለን ብቻ በመቀበል ከመንፈሳችን ጋር በማዋሃድ በዚያው እንገፋባታለን። የተወለድንበትንና ያደግንበትን ሁኔታ በስርዓት መዋቀሩና ያለመዋቀሩን ቀስ በቀስ በመጠየቅና በመመራመር ወይም ደግሞ ውጭ አገር ለብዙ ዓመታት ስንኖር ጥያቄ ስናነሳና በማነፃፀር ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘት የምንችለው። ውጭ አገር የምንኖርበትን ከተማ አገራችን ውስጥ ከተወለድንበት መንደር ወይም ከተማ ጋር ለማወዳደር ደግሞ ያኔውኑ በቀጥታ የሚደረስበት ጉዳይ ሳይሆን ብዙ ዓመታት ካሳለፍን በኋላ ብቻ ነው። ይህንንም ለማድረግ የምንችለው ወይም ጥያቄ የምናነሳ ሁላችንም አይደለንም። አሜሪካም ሆነ አውሮፓ ከሰላሳና ከአርባ ዓመታት በላይ ኖረን በአስተሳሰባችን የማንለወጥ ጥቂቶች አይደለንም። በምዕራብ አውሮፓም ሆነ በአሜሪካን  ለብዙ አስርት ዓመታት ኖረን ንቃተ-ህሊናችንን ለማዳበር የማንችልና ጥያቄም ለመጠየቅ የማንችል ብዙዎች ነን።

የንቃተ-ህሊናችን መዳበርም ሆነ ያለመዳበር ጉዳይ በልጅነታችን ወቅት በዕድገት ላይ የሚወሰን ጉዳይ ነው። በተለይም በልጅነታችን ወቅት  በነቃና የህብረተሰብን ምንነት በተገነዘበ ቤተሰብ ውስጥ የተወለድንና ያደግን ከሆነ ንቃተ-ህሊናችምም የመዳበርና አስተሳሰባችንም ጥሩ የመሆን ዕድል ያገጋጥማቸዋል። በተጨማሪም የአካባቢው ሁኔታ ለንቃተ-ህሊና በጥሩ መልክ መዳብርም ሆነ አለመዳበር  ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ ምን ዐይነት ቤተሰብ ውስጥ እንደተወለድን፣ ምን ዐይነት አስተዳደግ እንደነበረን፣ ጭንቅላታችንን ለማጎልመስ የሚያስችል ዕውቀት ቀስመን ወይም አልቀሰምን እንደሆን፣ በልጅነታችን ብዙ የምንቀሳቀስና ጂምናስትክም የምንሰራ ከሆነ ወይም የማንሰራ ከሆነ፣ በተለይም ደግሞ ከልዩ ልዩ የሙዚቃ መሳሪያዎች ጋር ትውውቅ ካለንና ወይም ከሌለን፣ ...ወዘተ. ወዘተ.
https://amharic.zehabesha.com/archives/189518

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...