Monday, January 22, 2024
January 22, 2024
TG
2004 Timkat in Gondar `
የሰው ልጅ በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረበትን መሠረታዊ ዓላማ ማለትም ከሌሎች ፍጡራን ተለይቶ የተሰጠውን ረቂቅ እምሮውንና ብቁ የማከናወኛ አካሉን ተጠቅሞ በሚያደርገው የማያቋርጥ የአስተሳሰብና የተግባር መስተጋብር አማካኝነት በሰላም፣ በፍቅር፣ በእኩልነት ፣በነፃነት፣ በመከባበር፣ በመተባበር፣ እና የእነዚሁ ድንቅ እሴቶች ውጤት የሆኑት ሥልጣኔ፣ እደገት እና ልማት (ብልፅግና) የሚያስገኙለትን እርካታና ደስታ እያጣጣመና ፈጣሪውን እያመሰገነ የመኖርን ሃላፊነት ዘንግቶ ወደ ደመ ነፍስ እንስሳት የሚያስጠጋውን ተግባር በማድረጉ ነበር አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት ሥጋ ለብሶ የተወለደው፣ ያስተማረው፣ በጥምቀት ራሱን የገለጠው ፣ የመጣበትን ድንቅ ተልእኮና ዓላማ ባልወደዱለት የዘመኑ ገዥዎች የስቃላት ሞት ተፈፃሚ የሆነበት እና በመጨረሻ ግን ሞትን አሸንፎ የተነሳው።
እናም ስለ እውነት በእውነት ከተነጋገርን ሃይማኖታዊ እምነት ከገሃዱ ዓለም የሰው ልጆች የህይወት ሂደትና መስተጋብር የጤናማነት ወይም የመታወክ ጥያቄ ተለይቶ በአየር ላይ የሚንሳፈፍ አንዳች አይነት መንፈስ አይደለምና ከምር ልብ ልንለው ይገባል ብሎ መከረከር የፅድቅ እንጅ የኩነኔ መንገድ አይደለም። እንኳንስ ሃይማኖታዊ የትኛውንም በጎ ህዝባዊ / ማህበረሰባዊ በዓል ስናከብር ይህንኑ እውነታ ባገናዘበና በሚያንፀባርቅ ሁኔታ ካልሆነ ነገረ ሥራችን ሁሉ የዘልማድ ነው የሚሆነው። በሌላ አገላለፅ የሃይማኖታዊ በዓላትን እሴትነት ከመልካም (ከትክክለኛ) አማኝነት ፣ ከዜግነት መብትና ክብር (ከእውነተኛ የአገር ባለቤትነት) ፣ ከነፃነትና ከፍትህ መስፈን ፣ ከእውነተኛ የሰላምና የፍቅር ምንነትና እንዴትነት ፣ ወደ እውንነት መተርጎም ከሚችል ተስፋ/ምኞት ፣ ወዘተ ጋር በጥብቅ አቆራኝተን ለማየትና ለማሳየት ካልቻልን የምንሸነግለው ራሳችንን ብቻ ሳይሆን እውነተኛውን አምላክ ጭምር ነውና አደብ እየገዛን እንራመድ ብሎ ለማስገንዘብ የሰበብ ድሪቶ እየደረትን መሽኮርመም በፍፁም አይኖርብንም።
በስሜት የመነዳቱን አባዜ በመቆጣጠር ከቅርፅ (ከሰው ሠራሽ አንፀባራቂነት) ይልቅ ለይዘት (መሆንና መደረግ ላለበት ጉዳይ) ይበልጥ አትኩሮት የሚሰጥ የዝክረ በዓላት አውድ ካልፈጠርን በስተቀር በፖለቲካ ወለድ የመከራ፣ የዋይታ/የእግዚኦታ እና የውርደት ደመና ሥር እየተርመጠመጥን/እየተደናበርን “እፁብ ድንቅ የሆ ኑ፣ ዓለምን ያስደመሙ ፣ ህዝብ ክርስቲያን ግልብጥ ብሎ የወጡላቸው ፣እልልታውና ሆታው የተስተጋባላቸው፣ ቅኔውና ዝማሬው እንደ ጉድ የወረደላቸው፣ሰላምና ፍቅር የተትረፈረፈባቸው ፣ የክቡራንና ክቡራት የብልፅግና ባለሥልጣናት/ከፍተኛ ካድሬዎች ቡራኬ የተቸራቸው ፣ ወዘተ በዓላት ባለቤቶች ነን” ማለት ለግልብ ስሜታችን እንጅ በእውነት ሆነንና አድርገን ማስመስከር ስለሚኖርብን ምንነታችንና እንዴትነታችን የሚያደርገው አስተዋፅኦ በፍፁም የለም።
እውነተኛው ክርስቶስ (አምላክ) ዝክረ በዓሉን ሲባርክ የሰነበተው እንኳንስ ለገዛ ወገን ለማነኛውም ጤናማ ህሊና ላለው ሰው ለማሰብ በሚከብድ ሁኔታ ጥንብ በሆነው የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የመቃብር ራት ከሆኑት፣ በመፈናቀልና በርሃብ ጠኔ የቁም ስቃይ ሰለባ ከሆኑት ፣ ከመቃብር ሙትነት ተርፈው የአካልና የአእምሮ መዛባት ሰለባ ከሆኑት፣ በየማጎሪያና ማሰቃያ ማእከላት የሰቆቃ ሰለባ በመሆን ላይ ከሚገኙት፣ እና ይህ ሁሉ የመከራና የውርደት ዶፍ ፍፃሜ አግኝቶ ለሁሉም የምትሆን የነፃነትና የፍትህ አገር እውን ትሆን ዘንድ እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ ከሚያደርጉ አርበኞች ፣ ወዘተ ጋር እንጅ ከባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች ቤተ መንግሥት ጋር በአሳፋሪ ሁኔታ እየተሻሹና የሚሰጣቸውን መመሪያ/ትእዛዝ እየተቀበሉ የሃይማኖትን ምንነትና ለምንነት ምስቅልቅሉን ካወጡት የሃይማኖት መሪዎችና ሰባኪዎች ጋር አይደለም።
ይህንን ግልፅና ቀጥተኛ አስተያየቴን መሪዎችን ከመዳፈር አልፎ የጥምቀቱን ድምቀት የሚጣጣል እንደሆነ በመቁጠር የእርግማንና የውግዘት ናዳ ለማውረድ የሚሞክሩ ወገኖች ቁጥር ቀላል እንደማይሆን በሚገባ እረዳለሁ።
ለዚህ ያለኝ መልስ ፦
ሀ) ለመግለፅ በእጅጉ ከሚከብደው ዘመን ጠገብ ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ሰብረን መውጣት እንችል ዘንድ መሬት ላይ ተዘርግቶ እየሰማንና እያየን ያለነውን መሪር ሃቅ በደፋርነትና በቅንነት ለመጋፈጥ ያለመቻላችንን መሪር እውነት ተረድተንና ተቀብለን ተገቢውን ማድረግ ካልቻልን ከቶ የትም እንደማንደርስ ከምር መታወቅ ይኖርበታል፤
ለ) ተስፋ እውን መሆን የሚችለው ጠንካራ በሆነ ፍኖተ ተግባር ላይ መቆም ሲችል ስለሆነ ይህ የሚጎድለው ተስፈኝነት ከንቱ /ትርጉመ ቢስ ምኞት ወይም ቅዠት መሆኑን ተገንዝበን ዛሬውኑ የማስተካከያ እርምጃ ካልወሰድን የተሸናፊነት ሰለባዎች ሆነን የመቀጠላችን መሪር እውነት አይቀሬ ሆኖ እንደሚቀጥል ለመረዳት የተለየ እውቀትን አይጠይቅም፤
ሐ) ከገዛ ራሳችን የዘመናት መከራና ውርደት ሰብረን ለመውጣት እንዳንችል ካደረጉንና እያደረጉን ካሉት እጅግ የተዛቡ/የተንሸዋረሩ አስተሳሰቦቻችን መካከል አንዱ ሃይማኖታዊ እምነትን ጨምረን የድርጊት አልባ ተስፈኝነታችን መሠረት አድርገን የማየታችን ጉዳይ መሆኑን አምነን በመቀበል ተገቢና ገንቢ ወደ ሆነ ፍኖተ ለውጥ መሰባሰብ ይኖርብናል፤
መ) ገድለው፣ አስገድለውና አገዳድለው ሃዘናችን ላይ አብረውን በሚቀመጡ፣ በርሃብ አለንጋ ገርፈውና አስገርፈው ምፅዋእት በሚያስለምኑን፣ አደንቁረውና አደናቁረው በዕውቀትና በጥበብ እንዳንበሸበሹን በሚሳለቁብን ፣ ምድረ ሲኦል ያደርጎትን አገር አገረ ገነት እንዳደረጓት ሊያሳምኑን ሲሞክሩ ጨርሶ ህሊናቸውን በማይኮሰኩሳቸው እኩያን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ዘዋሪዎች (ገዥ ቡድኖች) ሥርዓት ሥር እየጓጎጥን ሃይማኖታዊ “በዓሎቻችን በአስደናቂ ሰላምና ፀጥታ ተከበሩ” የሚለው ትርክታችን እጅግ አሳሳች መሆኑን ተገንዝበንና ተቀብለን ወደ ትክክለኛው ፍኖተ መልእክት መመለስ ይኖርብናል።
ሠ) ይበጃል የሚሉትን ሂሳዊ ትችት ይጠቅማል ከሚሉት የመፍትሄ ሃሳብ ጋር የሚያቀርቡትን ወገኖች ሃይማኖትንና የሃይማኖት መሪዎችን እንደተዳፈሩ በመቁጠር (በመተርጎም) ያዙኝና ልቀቁኝ የማለት ነገር የውድቀት ውድቀት ነውና ከምር ልናጤነው ይገባል የሚሉ ሃሳቦችን የያዘ ነው።
ማመን ፈለግንም አለፈለግንም ወይም ወደድነውም ጠላነውም ለዘመናት የመጣንበትና ከአምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በእጅጉ የተዘፈቅንበት ግዙፍና መሪር እውነት ይኸው ነውና የሚሻለው የዘልማድ አይነት አስተሳሰባችንና አካሄዳችን በቅጡ መርምረን/ፈትሸን የሚበጀንን ማስተካከያ/እርምት ማድረግ ነው እንጅ ትእይንተ ትውፊት በሚመስል የሃይማኖት በዓል አከባበር ራስን መሸንገል (ማታለል) ከቶ የትም አያደርስም።
አዎ! ለዘመናት ከመጣንበትና ከአምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለማሰብም የሚከብድ የመከራና የውርደት ዶፍ እያወረደ ከቀጠለው የባለጌዎችና የጨካኞች የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ለመገላገል ካልቻልንባቸው ምክንያቶች አንዱ የራሳቸውን ተገቢ ሃላፊነትና ድርሻ ከመወጣት ይልቅ በቤተ እምነት ጽህፈት ቤት እና የሸፍጠኞችና የሴረኞች ከፍተኛ ምሽግ በሆነው ቤተ መንገሥት መካከል እየተመላለሱና እየተሻሹ ስለ የእምነት ፅዕናት፣ስለ ሰላምና ፍቅር አስፈላጊነት፣ ስለ ትዕግሥት ወርቃማነት፣ ስለ ሃይማኖታዊ በዓላት የግድ ባይነት፣ ስለ ሃይማኖታዊ ሰማእትነት፣ ወዘተ የሚሰብኩን የሃይማኖት መሪዎች መሪር ውድቀት ነው።
“ከሐርያት የተቀበልነው ሥርዓተ ቀኖና ሲጣስ ቆመን ከማየት ሞትን በፀጋ እንቀበላለን” እያሉ ለአያሌ ዘመናትና በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲሰብኩን ኖረው በእኩያን ፖለቲከኞች ትእዛዝ እና በእነርሱ በራሳቸው ልክ የሌለው የአድርባይነት ልክፍት ምክንያት ሽረው/አፍርሰው ለምን? ሲባሉ “ለሰላም ስንል ሻርነው” በሚል እንደማነኛውም መርዶ ያረዱበት (የተናገሩበት) አንደበታቸው ገና በቅጡ ሳይረጋጋ ጥምቀቱን አስመልክተው ከዋዜማው ጥቂት ቀናት ቀደም ሲል ደግሞ እውነተኛ የሃይማኖት አርበኛ በሚመስል አቀራረብ ብቅ ብለው “ጣልቃ አትግቡብን” በሚል ኮስተር ያለ መግለጫ (ዲስኩር) ካስደመጡን በኋላ በበዓሉ ዋዜማ ደግሞ ከቤተ መንግሥትና ከቤተ ከንቲባዋ (አ.አ) የተሰጣቸውን ዝርዝር መመሪያና ማስጠንቀቂያ የብልፅግና ካድሬዎችን በሚያስከነዳ (በሚበልጥ) አቀራረብና አንደበት ያለምንም ሃፍረት ሲነግሩን/ ሲያስተላልፉልን መስማት የእውነተኛ አማኝንና የሁሉም አይነት ነፃነቶች መከበር ግድ የሚለውን የአገሬ ሰው ቢያንስ ምነው ምን ነካን? ሳያስብለው የሚቀር አይመስለኝም።
ስለ እውነት በእውነት የሁሉም አይነት ነፃነትና ፍትህ የሚሰፍንባት ኢትዮጵያን የምንፈልግ ከሆን ለብዙ ዘመናት የመጣንበትንና በአሁኑ ወቅት ደግሞ አስከፊና አስፈሪ በሆነ ሁኔታ ተዘፍቀን የምንገኝበትን ግዙፍና መሪር ደጋግሞ የመውደቅ አዙሪት/አባዜ ግልፅና ዴሞክራሲያዊ በሆነ አርበኝነት መጋፈጥን ግድ ከሚል ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ነው የምንገኘው።
ይህንን ሆነንና አድርገን ለመገኘት ደግሞ ትውፊታዊ/ባህላዊ ትእይንተ ህዝብ ከሚመስል የሃይማኖት የአደባባይ በዓላት አከባበር አልፈን በይዘቱ ( ምድራዊ ህይወታችን የሰማያዊ ተስፋችንን ከምር በሚገልፅ አኳኋን) ለመረዳትና ለማክበር የሚያስችል ሥርዓተ ማህበረሰብ እውን ለማድረግ ምን እና እንዴትስ ማድረግ አለብን? የሚለውን ግዙፍና አንገብጋቢ ጥያቄ አግባብነት ባለውና ጊዜን ግምት ውስጥ ባስገባ አኳኋን እስካልመለስን ድረስ በሚቀጥለው ዓመትም ሆነ ከዚያም በኋላ ራሳችንን በተመሳሳይ ብቻ ሳይሆን ይበልጥ በከፋ ሁኔታ ውስጥ ልናገኘው እንደምንችል ለመገመት ሚዛናዊና ቅን ግንዛቤን እንጅ ልዩ እውቀትን ወይም የቲዎሎጅ ሊቀ ሊቃጥንትነትን ወይም ሰፊ የፖለቲካ ትንታኔን አይጠይቅም ።
ይህንን እጅግ አስከፊና አስፈሪ ሁኔታ ወደ መልካም የለውጥ ሂደትና ግብ ለመለወጥ ወይም ለመተርጎም ከተሳነን የአደባባይ ሃይማኖታዊ በዓሎቻችን ለታይታ እና ከቱሪስት ሊገኝ የሚችል ሳንቲም መሰብሰቢያ (መልቀሚያ) ከመሆን አያልፉም። ለምን? ቢባል በባለጌና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴዎች ፍፁማዊ መመሪያና ትእዛዝ ሰጭነት እና በአድርባይ የሃይማኖት መሪዎች መልእክተኛነትና አስፈፃሚነት በሚካሄዱ የዝክረ ሃይማኖት በዓላት ላይ የሚገለጥ እውነተኛ አምላክ አይኖርምና ነው።
ለመሆኑ ለብዙ ዘመናት ያከበርናቸው የሃይማኖት በዓላት ከመከራና ውርደት እንወጣ ዘንድ ለምንና እንዴት አልረዱንም? እውን ፈጣሪ የመከራችንና የውርደታችን መንስኤና መፍትሄ ምን እንደሆነ አያውቅም? ታዲያ ለም? ብለን ራሳችንን ጠይቀን እናውቃለን?
ሌላውን ሰው ወይም ቡድን የመጠየቅ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ራስን ከምር መጠየቅና መመርመር የእውነተኛ አማኝነትና ከስህተት የመማር አዋቂነት እንጅ የደካማነት ወይም ፈጣሪን የማስቀየም ህፀፅ አይደለምና ዛሬም እንጠይቅና ቢያንስ ለከርሞ (ለሚቀጥለው ዓመት) የሃይማኖት ነፃነትን ጨምሮ ለሁለንተናዊ ነፃነቶቻችን የሚበጅ ሥርዓተ ፖለቲካ እውን ለማድረግ ከምር የሆነ የጋራ ጥረት እናድርግ ።
ዋነኛ ተጠያቂዎች እኩያን ገዥ ቡድኖች መሆናቸው እንደ ተጠበቀ ሆኖ እንደ አማኝና አገር እንዳለው ማህበረሰብ ነፃነታችን የነፈገንን እና የጋራ አገር እያሳጣን ያለውን ፖለቲካ ወለድ ወረርሽኝ በዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ወኔ በመጋፈጥ የነፃነትና የፍትህ ሥርዓትን እውን ለማድረግ አለመቻላችንን ባለመታደል ወይም የፈጣሪ ፈቃድ ስላልሆነ በሚል ሰንካላ ሰበብ ፈፅሞ ልናልፈው አይገባም።
እናም የውድቀታችን እና የፈጣሪም ዝም ማለት ምክንያቶቹ እኛው ራሳችን ነን። ፈጣሪ በሰጠን አእምሮና አካል እየተጠቀምንና የፈጣሪን እርዳታ እየጠየቅን ለሰማያዊውም ሆነ ለምድራዊው ህይወታችን የሚበጅ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ ሳናደርግ “እግዚኦ ካልወረድክና ካልፈረድክ” እያልን ብንማፀን በተግባር አልባ አውዳችን ላይ የሚገኝ ፈጣሪ የለም ። በአገራችን ለዘመናት የሆነውና እየሆነ ያለውም ይኸው ነው።
አዎ! አለመታደል ወይም የፈጣሪ ቁጣ ሆኖብን ሳይሆን በራሱ አምሳል ከማሰቢያ አእምሮና ከማከናወኛ አካል ጋር የመፈጠራችንን ሚስጥር በአግባቡና ከምር በመረዳት መሆን ያለብንን ሆነንና ማድረግ ያለብንን አድርገን ባለመገኘታችን ይኸውና ዘመን አልፎ ዘመን በተተካ ቁጥር ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላትን በተሻለ የነፃነትና የፍትህ እኛነት አስበንና አክብረ ን ለመዋል አልቻልንም። ወደድንም ጠላን መሪሩ ሃቅ ይኸው ነው።ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት መሪዎች ውድቀት እና የሃይማኖት መሪዎችንን በአግባቡና በአክብሮት ተሳስታችኋል ማለት ሃጢአት ተደርጎ የተነገረውን ተቀብሎ አሜን አሜን የሚለው አማኝ (በተለይ ፊደል የቆጠረው) ተጠያቂ ነው።
ባለጌ፣ ሸፍጠኛ፣ ሴረኛና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴዎች የሚሰጧቸውን (የሚግቷቸውን) ጥብቅ የቅድመ ሁኔታ እና የዮላችሁ ማስጠንቀቂያ በአጀንዳቸው (በማስታወሻ ደብተራቸው) ላይ እያሰፈሩ ከካድሬዎች በተሻለ አቀራረብና አገላለፅ ሲያስተላልፉ ለምንና እንዴት? ተብለው ሲጠየቁ እጅግ ጥልቅ ትርጉም ያለውን ሰላምን እጅግ ደምሳሳ በሆነና በተሳሳተ ትርጉም እየተረጎሙ መከረኛውን ህዝብ ግራ የሚያጋቡ የሃይማኖት መሪዎችንና ሰባኪዎችን ለአደብ ግዙማለት ይገባል። ይህ የሚጠቅመው ለራሱ ለሃይማኖቱም ነውና ከምር ሊያሳስበን ይገባል።
ለዘመናት የዘለቀውንና ከአምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በእጅጉ እየከፋ የቀጠለውን ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ከፈጣሪ እገዛ ጋር ለመቀልበስ የጋራ ጥረት ሳናደርግ “በእጅጉ የደመቀ፣ ዓለምን ያስደመመ፣ ተአምር የታየበት፣ ታላላቅ መሪዎች ድንቅ ዲስኩር/ ንግግር ያደረጉበት፣ ህዝብ ክርስቲያኑ ግልብጥ ብሎ የወጣበት፣ ቅኔው እንደ ጉድ የወረደበት፣ ከበሮውና ፀናፅሉ ያስተጋቡበት፣ ድንቅ መልእክት የተነገረበት፣ ወዘተ በዓል አከብርን ማለት ከጊዚያዊና ግልብ ከሆነ ስሜት አያልፍም። ተነጣጥለው መታየት የሌለባቸውን የመንፈሳዊና የዓለማዊ ህይወቶቻችን በእኩያን ገዥ ቡድኖች በእጅጉ በተመሰቃቀሉበት እጅግ አስቀያሚ ሁኔታ ውስጥ እየጓጎጥን እፁብ ድንቅ በዓል አከበርን በሚል አገር ምድሩ በሰላምና መረጋጋት የተንበሸበሸ ማስመሰል ከራስ አልፎ ፈጣሪነም መሸንገል ነው።
ከዘመን ጠገቡ የባለጌዎች፣ የሸፍጠኞች፣ የሴረኞች እና የጨካኞች የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ክፉ ቀንበር ለመላቀቅና ለሁሉም የሚበጅ ሥርዓተ ማህበረሰብ እውን ማድረግ ያለመቻላችን መሪር እውነት የማያሰማንና የማያሳየን ነገር የለም። የአገሬ ህዝብ በመንበረ ሥልጣን ላይ እየተፈራረቁ መከራና ውርደትን እንዲለማመድ ያደረጉትን እኩያን ገዥዎች አምርሮ በሚታገልበት በዚህ እጅግ ወሳኝ ወቅት ከሃይማኖት ተቋሞቻችን መሪዎችና ሰባኪዎች እያየን፣ እየሰማን እና እየታዘብን ያለነው ነገር ባይገርምም ቅንና ሚዛናዊ ህሊና ያለውን የአገሬ ሰው በእጅጉ ይፈታተናል።
በመንበረ ሥልጣን ላይ እየተፈራረቁ በነፃነት ተዘዋውሮና ሠርቶ ይኖርባት ዘንድ ከፈጣሪ የተሰጠችውን ውብ አገር ምድረ ሲኦል ካደረጉበትና እያደረጉበት ከሚገኙት የእኩይ ሥርዓት አራማጅ ገዥ ቡድኖች ጋር እየተሻሹ እና ማስጠንቀቂያ እየተቀበሉ “የሃይማኖት በዓላትን በደስታ፣ በሰላም ፣በእልልታ፣ በሽብሸባ፣ በልዩ ዝማሬ፣ በግሩም ቅኔ፣ እና በአጠቃላይ እኩያን የጎሳ አጥንት ስሌት ገዥዎች የሚጠሉትን በመጥላት እና የሚፈቅዱትንና የሚወዱትን በመውደድ አክብሩ ፤ ይህን ሁናችሁና አድርጋችሁ ካልተገኛችሁ ግን ፈጣሪን መጋፋት ስለሚሆን ሃላፊነቱ የእናንተ ነው” የሚል እጅግ የወረደና አዋራጅ ትእዛዝ የሚያውጁ የሃይማኖት መሪዎች በሚታደሙበት አውድ ላይ የሚገኝ እውነተኛ አምላክ የለም።
እናም ከዘመን ጠገቡ ፖለቲካ ወለድ አጠቃላይ መከራና ውርደት እና በተለይ ደግሞ ሃይማኖታዊ በዓላትን በዚሁ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል አራማጅ ገዥ ቡድኖች ፍፁም ፈቃድና ትእዛዝ ከማክበር (ከማዋረድ ማለት ይሻላል) እጅግ አሳፋሪ እውነታ ሰብሮ ለመውጣት ብቸኛው መንገድ የፋኖን ተጋድሎ በአገራዊ የትግል ሰንሰለት እያቆራኙ እና ዘመኑን በሚመጥን የፖለቲካ አደረጃጀትና ሁለገብ በሆነ የትግል ስልት እያጠናከሩ በአይበገሬነት ወደ ፊት መገስገስ ነው። ይህንን ሆነንና አድርገን ከተገኘን ብቻ ነው የሃይማኖት ነፃነትን ጨምሮ ሁሉም መሠርታዊ የነፃነት ፣ የመብትና የፍትህ ጥያቄዎች የሚመለሱበትን እና የሚረጋገጡበትን ሥርዓት እውን ማድረግ ምንችለው።
ለዚህ ተግባራዊነት ደግሞ ከአድርባይነት ልክፍት ነፃ የሆኑና ፖለቲካ ወለድ በሆነ መከራና ውርደት የሚማቅቁውን ህዝብ የተሸከሙትን ሥልጣንና ሃላፊነት በሚመጥን ደረጃ ለመታደግ ፈቃደኞችና ዝግጁዎች የሆኑ የሃይማኖት መሪዎች ሚና በእጅጉ የጎላ ነው።
https://amharic.zehabesha.com/archives/188259
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment