Wednesday, January 10, 2024
እ.ኤ.አ. ግንቦት 20፣2018 ዓ.ም. ወይንም በኛ አቆጣጠር ግንቦት 12፣ 2010 ዓ.ም. ጠ/ሚ አብይ ወደ ስልጣን በመጡበት ሰሞን አንድ ጽሑፍ "እውነት አንደ ሳንቲም ሁለት ገጽታ አላትን?" በሚል ርዕስ በእንግሊዘኛ ጽፌ ፌስ ቡኬ ላይ ለጠፍኩ፡፡ በዚያን ሰሞን ስለ አዲሱ ጠ/ሚ ብዙ ይወራላቸው ነበር፡፡ ነገሩን ውስጤ ጠረጠረ መሰል ጠ/ሚ ላይ ሶስት ቢሆኖች(Scenarios)፣ አባባል ዘይቤዎችንና የአባቶች ወግን በመጠቀም አቀረብኩ፡፡
ቢሆን I (Scenario I)
አንድ ሁለት ሚስቶች የነበሩት ሰው ነበር፡፡ አንድ ምሽት አንዷን በቀኝ በኩል ሌላዋን በግራ በኩል አስተኝቶ አለሙን ከቀጨ በኃላ ሁለቱም ድንገት ተነስተው አንድ አይነት ጥያቄ ጠየቁት "ከእኔና ከእሷ ማንን ትወዳለህ?" ሰውዬው ይኽን ግዜ ሁለት እጆቹን ወደ ጎን ግራና ቀኝ በመላክ ጣራ፣ ጣራ እያየ ሁለቱንም በመቆንጠጥ "አንቺን!" አለ፡፡ ለዚያን ምሽት ብቻ ሁለቱም ሴቶች እኔን ነው፣ እኔን ነው ያለው በማለት በእቅፉ ውስጥ ሰላም ሰጥተዉት አደሩ፡፡
ቢሆን II (Scenario II)
በጥንት ግዜ ነው አሉ፣ በሰማይ አእዋፋትና በምድር በሚመላለሱ እንስሳት መካከል ጦርነት ተነሳ፡፡ ታዲያ የለሊት ወፍ ወደ ላይ ወደ ሰማይ ወጥታ ለአእዋፍቱ "እኔ ወፍ ነኝ!" አለቻቸው፡፡ "አይ አንቺ ሲያዩሽ ታስታውቂያለሽ አይጥ ነሽ፡፡" አሏት፡፡ እዩት ክንፌን ብላ ክንፏን አሳየቻቸው፡፡
ወደ ምድር ደግሞ ወርዳ ለመሬት እንስሳት ፊቷን እያዟዟረች አሳይታ "አይጥ ነኝ!" አለች፡፡ እነሱም ክንፏን እያዩ "አይ አንቺ ወፍ ነሽ!" አሏት፡፡ እሷም መልሳ "እዩት ጥርሴን!" ብላ አረፈችው፡፡ ጦርነቱ እየበረታ ሲሄድ እሷ መሃል ላይ ተገኘችና፣ የሰማይ ወፎች ክንፏን ይዘው የምድሮቹ ደግሞ እግሯን ይዘው የኛ ነች፣ የኛ ነች እያሉ ሲጎትቷት ተገነጣጥላ ሞተች፡፡
ቢሆን III (Scenario III)
አንድ ግዜ የእስራኤል ንጉስ፣ ንጉስ ሰለሞን በእግዝአብሔር ህቡዕ ስም ያሰረውን የአጋንንት አለቃ አሽሞዳያን ይጠራና ጥያቄ ይጠይቀዋል፡፡ "እናንት አንዳንድ ግዜ ከመለአክት የበለጠ ኃያል የሚኖራችው ምስጢር ምንድን ነው?" አሽሞዳይም መለሰ "የእግዚአብሔር ህቡዕ ስም የተፃፈበት ይህ አንገቴ ላይ ያደረግክብኝን ስነሰለት ብትፈታልኝና የእግዚአብሔር ህቡዕ ስም የተቀረጸበት ቀለበትክን ከጣትህ ላይ ብታወልቅ ምስጢሩን እነግርሃለው፡፡" አለው፡፡
ንጉስ ሰለሞንም ተስማምቶ ስንሰለቱን ፈታለት፣ የጣቱንም ቀለበት አወጣው፡፡ ይህን ግዜ አሸሞዳያ የንጉስ ሰለሞን የጣት ቀለበትን ከሰለሞን ነጥቆ አርቆ ወደ ባህር ወረወረው፡፡ንጉስ ሰለሞንንም ከእየሩሳሌም ከ600 ኪ.ሜ. በላይ በንፋስ አውታር ጭኖ ውስዶ እሜዳ ላይ ጣለው፡፡
ንጉስ ሰለሞን ከስልጣን ተወግዶ ለሶስት አመት ያህል በልመና ኖረ፡፡ መንገድ ላይ ላገኛቸው ሰዎች ሁሉ እኔ የእየሩሳሌም ንጉስ ሰለሞን ነኝ እያለ ቢናገርም እንደ እብድ ተቆጥሮ ኖረ፡፡ ልብሱ በላዩ ላይ አልቆ ትቢያ ለበሰ፡፡ ህጻናትም በየመንገዱ ሲያገኙት እያባረሩ በድንጋይ ይወግሩተረ ጀመር፡፡
አሽሞዳይ ግን የዶሮ(ፒኮክ) የመሰለውን እግሩን ደብቆ መልኩን እንደሰለሞን ቀይሮ፣ ድምጹ እንኮን ሳይቀር የንጉስ ሰለሞንን አስመስሎ(Imposter) በእየሩሳሌም በንጉስ ሰለሞን ዙፋን ላይ ለሶስት አመታት ነገሰ፡፡ በአገዛዝ ዘመኑም የአጋንንትነት ስራውን እየሰራ ቆየ፡፡ንጉስ ሰለሞን የጠፋበትን ቀለበት ከአሳ ሆድ ውስጥ አግኝቶ በተአምር ወደ እየሩሳሌም ቢመለስ አሸሞዳይ ተጋለጠ፡፡ እሱም ወደ ሰማይ በኖ ጠፋ፡፡
እነዚህን ቢሆኖች እንደ ቫሪያብል ግብአት ወስደን ቀመሩን(Equation) ስንሰራ እንደ ምንጭ አሰጣጤ የማይቀረውን የአሰመሳዩን(Imposter) አሽሞዳይ የመጨረሻ የእንጦሮጦስ ጉዞ(Dead end) አመላካች ነበር፡፡
እነዚህን ቢሆኖች የጻፍኩት የጠ/ሚ ማንነት በማጥናትና የሚነገርላቸውን በመስማት ነበር፡፡ ጠ/ሚ በኃላ እንደተናገሩት በኢህአዲግ የስልጣን ዘመናቸው ለግንቦት ሰባትና ለኦነግ ይሰልሉ እንደነበር አሳውቀውናል፡፡ አረ ምን ይኼ ብቻ ለሲ.አይ. ኤ ሰርቸለሁ ብለዋል፡፡ እንግዲህ ደብል ኤጀንት ሰላይ መሆናቸውን ከእሳቸው አረጋግጠናል፣ የደህንነት ሰዎች ሌላ ቃል እንዳላቸው አላውቅም ግን ትሪፕል ኤጀንትም ይመስላሉ፡፡ እውነት ነው ሃገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ነገር ነው፣ መሃል ተኝተው በግራና ቀኝ እጃቸው እየቆነጠጡ ያንቺ ነኝ፣ ያንቺ ነኝ ማለትን በስልጣናቸው መጀመሪያ ሰሞን ተጠቅመውበታል፡፡
ከሃጫሉ ግድያ በኃላ በአማራና የአማራ ተዛማቾች ባሏቸው ሰዎች ሃብት፣ ንብረትና የሰው ህይወት ላይ በሻሸመኔ፣ዝዋይ፣ሐረር…ያ ሁሉ ጥፋት ከደረሰ በኃላ ደግሞ ጠ/ሚሩ የሌሊት ወፍ ሆኑ፡፡ አንተን ነኝ አንተን ነኝ ጨዋታ ውስጥ ገቡ፡፡ ለትንሽ ግዜ ኦሮሞው በአንድ ወገን ሌላው በዚያኛው ወገን ሆኖ የኔ ነው፣ የኔ ነው እያለ ጎተታቸው፡፡ ከዚያም ሁሉም ጉተታውን አቁመው ፍጥረታቸውን ይመረምሩ ጀመር፡፡ የሆኑ አይጥና ወፍ!
አሁን ያሉበት የስልጣናቸው የመጨረሻ ዘመን አሽሞዳይን አስመስሏቸዋል፡፡ ለአምስት አመታት በቤተ መንግስት ንጉስ ሆነው ተሰይመዋል፡፡ ያውም የንጉስ ሰለሞን ልጅ፣ ቀዳማዊ ምኒሊክ በመሰረተው ዙፋን ላይ፡፡እራሳቸውን ነጉስ ነኝ ብለው ስለጠሩ ነው እንዲህ ያልኩት፡፡ የንጉስ ሰለሞን የጣት ቀለበት ደግሞ በቀዳማዊ ምንሊክ ጣት ላይ ነበረችና፡፡
ሲያሰኛቸው እሳቸውና መንግስታቸው ሸኔን እየሆኑ ኖረዋል(የሻሸመኔው ከንቲባ እንደነገረን) ፡፡ ሚሊዮኖች አማራዎች ከገዛ ሃገራቸው ሲፈናቀሉ፣ ለሚሞቱት ዛፍ ተክዬ ጥላ እሰራላቸዋለው ብለውም ነግረውናል፤ ወቼ ጉድ ለአፈር ጥላ መስራት ምን የሚሉት ፍልስፍና ነው? ትግራይ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሁሉም ወገን አልቀዋል፡፡ አሁን ደግሞ አማራ ክልል ውስጥ በሚደረገው ጦርነት ብዙ ሰው እያለቀ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ውስጥም ብዙ ህዘብ ለሞት፣እስራትና እነግልት ተዳርጓል፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ የሚሆነው በእሳቸው የአገዛዝ ዘመን ነው፡፡
በተረኘነት መንፈስ በተለያየ ቡድን የተቧደኑ ኦሮሞዎች እጅ ውስጥ ስልጣን ገብቶ ነበር፡፡ ሁሉም ገዳይ ሆኑ፡፡ ኦሮሞውንም በ"ልዋጥህ ተድበልበል" መርሆቸው ዙሪያው ገባውን ከሁሉም ቤሔረሰቦች ጋር አናጩት፡፡ በኦሮሚያ ህገ ወጥነትን ህጋዊ አደረጉ፡፡ ትርጉሙ ለራሳቸው ባለገባቸው "አሳምን ወይም አደናግር" ፖለቲካዊ ስልት ጠ/ሚሩ እሰከ ጀሌዎቻቸው፣ በአፍሪካና በአለም ደረጀ ተቀባይነታቸው ዜሮ ሆነ፡፡ ዲፐሎማሲያቸውም በሕጻን ልጅ አይ.ኪው. ደረጃ አስለኩ፡፡
እንደ ግዜው ሆኖ ስልጣን በኦሮሞ እጅ ሲገባ፣ ኦሮሞና ኢትዮጵያ ጽዋ ተጣጡና፣ነገሩ የፕ/ር ደበበ ሰይፉን በተረት ላሰላስል ሆነ፡፡
እና!...
መሬትና ጥንቸል መኋበር ገቡና ጽዋ ተጣጡና
መሬት የበኩሏን ስትከፍል በጽሞና
እብስ አለች፣ ጥንቸል መክፈል ጠላችና…
ግና ምን ይሆናል?
ብትሮጠው ብትሮጠው፣ ጋራውን ተሸግራ፣
ሜዳውን አቋርጣ
አልቻለችም ከቶ፣ ከእዳዋ ልትድን፣
ከመሬት አምልጣ፡፡
እንዲህም ሆኖ ወደ ሐይማኖት ስንመጣ ደግሞ ጠ/ሚሩ እራሳቸውን በክርስቶስ ትረክት ውስጥ ተክተው ሲናገሩ ደጋግመን ሰምተናል፡፡ አሁን ደግሞ የክርስቶስ በልተጠበቀ ቦታ መወለድ ከሳቸው የፖለቲካ አካሄድ ጋር አያይዘው ለገና ተረኩልን፡፡ ይገርማል! የነገሩ ውስጠዘ ግን በሻሻን አመላካች ነው ባይ ነኝ፡፡ ቴውድሮስ ንጉስ ከምስራቅ ይመጣል ተብሎ አይደል የሚጠበቀው? እሳቸው ሶማሌ ላንድ ሄደው የዲፐሎማሲ ውድቀት የሆነውን ቀይ ባህርን ከኤደን ባህረ ሰላጤ ያለዩበትን ንግግር አደረጉና በሻሻን ምስራቃዊ አደረጓት፡፡ ትግሬ ሲተርት "ዘይገርም ድሙ ገበረማርያም ሽሙ" ይላል፡፡
ኢትዮጵያዊቷ ሚኒስተር ጠይባ ሃሰን፣ ስለ እየሱስ ክርስቶስ ተናግራ ጠ/ሚሩን የምስራቅ አፍሪካ መሲህ አድርጋ ገለጸቻቸው፡፡ በምን እይነት ቻርጀር ይህን እንዳለች አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ጠ/ሚሩ ግን በእዚህ ደስተኛ ናቸው፡፡
እንግዲህ እርስዎ የክርስቶስ እየሱስ ትይዩ መሲህ ከሆኑ፣ አሁን ዘመኑ ሰልጥኗልና አለም እያየዎት ይሙቱና ከሶስት ቀን በኋል ትንሳኤ ሙታን ያድርጉ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፣ ሁላችንም እያየንዎት ክርስቶስ እንዳደረገው ወደ ሰማይ ያርጉ፡፡ ከዚያ በኋላ መሳሳታችንን እንጠረጥራለን፡፡
እንግዲህ መጪው አመት በዓል ጥምቀት ነው፡፡ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ ውሃው ወደ ወይን ጠጅ እንደቀየረ መጽሐፉ አስነብቦናል፡፡ መቼም አዋሽ ወይን ጠጅ፣ ጉደር…ይክሰሩ አልልም፡፡ ውሃውን ወደ ወይን ጠጅ አይቀይሩ ግን እሰቲ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈሰውን ደም ወደ ውሃነት ይቀይሩልን፡፡በ
ቱሪ ናፋ!
አስቻለው ከበደ አበበ
ሜትሮ ቫንኩቨር፣ካናዳ
https://amharic-zehabesha.com/archives/188110
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment