Wednesday, January 31, 2024
ባይሳ ዋቅ-ወያ
መግቢያ
ሰሞኑን፣ መንግሥት ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉትን ዜጎች ወደ ቄዬያቸው ለመመለስ ዝግጅት ላይ ነው ተብሎ የተሰማውን ወሬ አስመልክቶ ጉዳዩ ያሳሰባቸው ዜጎች ከተለያየ አቅጣጫ የተቃውሞ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ይስተዋላል። ተፈናቃዮቹን ያለ አንዳች ዋስትና ወደ ቀድሞ ቤታቸው መመለስ ከበፊቱ ለባስ አደጋ ስለሚያጋልጣቸው፣ በመንግሥት ታቅዷል የተባለውን የመመለስ መርኃ ግብሩን ተፈናቃዮቹ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ዜጎች እንዲቃወሙት ከያቅጣጫው ጥሪ እየተደረገ ነው። በአገራችን ሁሉም ነገር በምሥጢር የሚካሄድና ግልጽነት ውድ ሽቀጥ ስለ ሆነ፣ በግሌ መንግሥት ስላቀደው መርኃ ግብር በየሚዲያው ከሚወራው ውጭ አንዳችም መረጃ የለኝም። ወሬው እውነት ይሁን ውሸት እንዳለ ሆኖ፣ በቀድሞ ሙያዬ ምክንያት የተፈናቃዮችን እና የስደተኞችን ወደ ቄዬያቸውና እናት አገራቸው የሚመለሱበትን ዓለም አቀፋዊ መሪህና ለመመለሳቸው መሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ጠንቅቄ ስለማውቅ፣ ከፖሊቲካ ነጻ በሆነ መንገድ፣ ዛሬ ከአማራ ክልል ወደ ወለጋ ሊመለሱ ነው ስለ ተባሉት ተፈናቃዮች የሚለተለውን ግላዊ ሃሳቤን ለማጋራት እወዳለሁ።
ከወለጋ ስለ ተፈናቀሉት ወገኖቻችን በየሚዲያው ተቋማት የሚወራውና በተጨባጭ መሬት ላይ ያለው ዕውነታ እጅግ በጣም የተለያየ ሆኖ ስላገኘሁት፣ ትንሽ በተጨባጭ ማስረጃ የተደገፈ መረጃ በዚህ ጽሁፍ ባካትት፣ ለበሽታው እየቀመምን ያለው መድኃኒት ፍቱን ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለኝ። በግል ተነሳሽነት በምሥራቅና በምዕራብ ወለጋ ተዟዙሬ እንዳሁት ከሆነ ስለ ወለጋ መፈናቀል እየተወራ ያለው ግማሽ ዕውነት ብቻ ሆኖ አግኝቻለሁ። በርግጠኝነት ያየሁት ነገር ቢኖር፣ በቁጥር ይለያይ እንደው እንጂ፣ ወለጋና ጎጃም ድንበር አካባቢ ጊዳ ኪራሙ ከሚባለው ሰፈር በታጣቂ ኃይላት የተፈነቃቀሉት ሁለቱም ሕዝቦች ናቸው። ከቄዬው ተፈናቅሎ ወደ ጎጃም የሄደውን የአማራን ሕዝብ ቁጥር በትክክል አላውቅም እንጂ፣ በቦታው ተገኝቼ በዓይኔ ያየሁትን በከተማው አስተዳደር በተሠጠኝ ማስረጃ መሠረት በነቀምቴ ከተማ ውስጥ ብቻ 28 ሺህ ከጊዳ ኪራሙና አካባቢው የተፈናቀሉ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች እንዳሉ የከተማው የመንግሥት ባለ ሥልጣናት አርተጋጠውልኛል። እኔም ከብዙ ተፈናቃይ ቤተሰቦች ጋር የግል ቃል መጠይቅ አድርጌያለሁ። ሌላው ተንሸዋርሮ ለሕዝብ በተከታታይ የሚቀርበው ዜና ደግሞ፣ እንደው በጅምላው “ከወለጋ” የተፈናቀሉ የአማራ ሕዝቦች የሚለው አሳሳችና አደገኛ ወሬ ነው። ወለጋ ትልቅ አገር ነው። በውስጡ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች በተጨማሪ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ለብዙ ዘመናት የሚኖሩበት ሲሆን፣ በተጨማሪ ደግሞ በሰሜኑ የአገራችን ግዛቶች በተከሰተው ረኃብ ምክንያት ወደ ሚሊዮን የሚጠጉ የአማራና የትግራይ ብሔር ተወላጆች በደርግ መንግሥት የሰፈራ ፕሮግራም መጥተው ከወለጋ ኦሮሞ ጎረቤቶቻቸው ጋር ተዋድደውና ተጋብተው ዛሬም ድረስ በሰላም የሚኖሩበት አገር ነው።
ከአምስት ዓመት ወዲህ ግን በተለያዩ ምክንያቶች፣ በወለጋ ክፍለ ሃገር ውስጥ ስለ ተከሰተው የእርስ በእርስ መፈነቃቀል የተካሄደው በጠቅላላው ወለጋ ውስጥ ሳይሆን ጊዳ ኪራሙ በተባለው፣ ከሻምቡ ከተማ 50 ኪሜ ርቀት ላይ ወለጋና ጎጃም ድንበር ላይ በምትገኘው የሠፈራ ጣቢያና አጎራባች ቀበሌዎች በአማርኛ ተናጋሪ ሰፋሪዎችና በአካባቢው በሚኖሩት የኦሮሞ ማኅበረ ሰብ አባላት መካከል በውጭ ኃይል ጣልቃ ገብነት በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ነው። ምዕራብ ኦሮሚያ ላለፉት አምስት ዓመታት ያለማቋረጥ በአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ (ኮማንድ ፖስት) ሥር ስለምትገኝ፣ የግጭቱን ምክንያት በቦታው ተገኝቶ መረጃና ማስረጃን አመላክቶ አሳማኝ የሆነ ዘገባ ያቀረበ መንግሥታዊም ሆነ የግል ሚዲያ ጋዜጤኛ ባይኖርም፣ አንባቢ መረዳት ያለበት አንድ ትልቅ ቁም ነገር፣ ከጊዳ ኪራሙና ከአሙሩ ወረዳ ውጪ፣ ለምሳሌ በሻምቡ፣ በባኮ፣ ሲሬ፣ ጉደያ ቢላ፣ ጀሬ፣ ነቀምቴ፣ ግምቢ፣ አርጆ፣ ነጆ፣ መንዲ፣ ቤጊ፣ ጊዳሚ፣ ቄለም ደምቢ ዶሎ፣ እና ሌሎችም የወለጋ ወረዳዎችና አውራጃዎች ወደ ሚሊዮን የሚጠጉ አማርኛ ተናጋሪዎች ዛሬም ያላንዳች ችግር ከጎረቤቶቻቸው የኦሮሞ ሕዝቦች ጋር በሰላም እየኖሩ መሆኑን ነው።
ጊዳ ኪራሙ አካባቢ ለዚህ መጠነ ሰፊ ለሆነ የሕዝቦች መፈነቃቀል ያደረሰው ምክንያት ምን እንደሆነ በትክክል ባይታወቅም፣ ባለኝ መረጃ መሠረት፣ ለግጭቱ መንስዔው፣ የጊዳ ኪራሙ ሰፈራ ጣቢያ በዘጠናዎቹ መጀመርያ ላይ ሲቋቋም፣ ሰፋሪዎቹ ከአካባቢው የኦሮሞ ማኅበረ ሰብ ጋር በምንም መልኩ እንዳይገናኙና በሂደትም ተዋህደው አንድ ማኅበር ሰብ ፈጥረው በሰላምና በፍቅር አብረው እንዳይኖሩ ተደርጎ የተሠራ “ራሱን የቻለ የሠፈራ ጣቢያ” ስለሆነ ነው የሚል ግምት አለኝ። ከላይ በዘረዘርኳቸው ወረዳዎችና አውራጃዎች ባሉት የሁለቱ ማኅበረ ሰብ አባላት መካከል አንዳችም ችግር ሳይፈጠር ለምን ጊዳ ኪራሙና አካባቢው ላይ ብቻ ይህን መሰል ችግር ተፈጠረ ለሚለው ጥያቄዬ መልስ ለማግኘት ስለ ሰፈራው ፕሮግራም የአፈጻጸም ሂደት የተወሰነ ምርምር አድርጌ የሚከተለውን አግኝቻለሁ። ሌሎችም ተመሳሳይ ምርምር ቢያደርጉ፣ የመፈናቀሉን እውነተኛ ምክንያት ለማግኘት ይረዳል ባይ ነኝ።
አስተማማኝ ማስረጃ በእጄ ላይ ባይኖርም፣ ባለኝ መረጃ መሠረት፣ በዘጠናዎቹ መጀመርያ አካባቢ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ “በአዲሱ አስተዳደር (ሕወሓት መራሹ መንግሥት) ውስጥ ቦታ የማይገኝላቸው ወይም የሚመጥን ዕውቀት የሌላቸው ወይም ደግሞ ጤና ጉድለት ያለባቸው የሕወሃት አባላት በመንግሥት ድጋፍ ወደ ሁመራና ወልቃይት ጠገዴ ተወስደው እንዲሠፍሩ ሲደረግ በዚያው ዓመት፣ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ከወሎ ክፍለ ሀገር ልዩ ስሙ አማራ ሳይንት ከሚባል ቦታ ብዙ የአማራ ማኅበረ ሰብ ተወላጆች ያለ ፍላጎታቸው ከቤታቸው ተፈናቅለው ለነሱ ብቻ ተብሎ አስቀድሞ በአካባቢው ሕዝብ በተሠራላቸው የጊዳ ኪራሙ የሠፈራ ጣቢያ እንዲሰፍሩ ተደረገ። የሰፈራ ጣቢያው፣ ለሻምቡ ከተማ በጣም ቅርብ ቢሆንም፣ ሰፋሪዎቹ፣ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ከአካባቢው የኦሮሞ ማኅበረ ሰብ ጋር አንዳችም የሚያገናኛቸው ማኅበረ ሰባዊ፣ አስተዳደራዊም ሆነ ፖሊቲካዊ ግንኙነት እንዲፈጥሩ አልተደረገም። በአንጻሩ ግን፣ የጊዳ ኪራሙ የአማራ ማኅበረ ሰብ አባላት፣ ልክ በሁመራና በወልቃይት ጠገዴ እንደ ሰፈሩ የትግራይ ተወላጆች፣ መንግሥት፣ ትራክተርና ሌሎች የማምረቻ መሳርያዎች፣ እንዲሁም ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ስላደረገላቸው፣ ከአካባቢው የኦሮሞ ማኅበረ ሰብ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል። የሰፋሪዎቹ ኅበረ ሰብ፣ ከእርሻ በተጨማሪ ከብቶችን፣ ፍየሎችንና በጎችን በማርባት ዘርፍ በጣም ከመታወቁ የተነሳ የአካባቢው የኦሮሞ ሕዝብ ዓመት በዓል ወይም ድግስ በመጣ ቁጥር የሚያስፈልገውን የሥጋ ምርት የሚሸምተው ከነዚህ የጊዳ ኪራሙ አማርኛ ተናጋሪ ሰፋሪዎች ነበር። ሁለቱን ማኅበረ ሰብ የሚያገናኛቸው አንድ ነገር ቢኖር ይህ የገበያ ጉዳይ ብቻ ነበር ማለት ይቻላል። በተረፈ፣ የጊዳ ኪራሙ ነዋሪዎች፣ ራሱን ችሎ በሆነ ግዛት እንደሚተዳደር የአማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ እንጂ፣ አንድም ጊዜ ራሳቸውን በኦሮሚያ ክልል እንደሚኖሩ አድርገው አይቆጥሩም ነበር። ይህ እንግዲህ፣ በነቀምቴ ከተማ ከመንግሥት ባለ ድርሻ አካላትና ከተፈናቃትዮቹ ራሳቸው ባገኘሁት መረጃ ላይ የተመሠረተ ግርድፍ እውነት እንጂ መቶ በመቶ ትክክለኛ ነው ብዬ ለመሞገት አልደፍርም። በቦታው ተገኝቼ ሁኔታዎችን ለመገምገም ዕድል አልነበረኝምና!
የግጭቱ መንስዔ ምን ነበር? ሁለቱ ማኅበረ ሰቦች ለሰላሳ ዓመት ሙሉ ጎን ለጎን እየኖሩ እንዴት ለመዋሃድ ወይም ቢያንስ ቢያንስ እንደ መልካም ጎረቤት አብረው ለመኖር ለምን አልቻሉም? በሌሎች የወለጋ ግዛቶች የሚኖሩ ወደ ሚሊዮን የሚጠጉ አማርኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን ከኦሮሞ ማኅበረ ሰብ አባላት ጋር ተስማማተው በሰላም አብረው መኖር ሲችሉ፣ የጊዳ ኪራሙና አካባቢው የአማርኛ ተናጋሪዎች በአካባቢው ከሚገኙ የኦሮሞ ማኅበረ ሰብ አባላት ጋር ለምን በሰላም አብሮ መኖር አቃታቸው ለሚለው ጥያቄ፣ በግሌ አንድ የደረሰኩበት ትክክለኛ ድምዳሜ ቢኖር፣ “የሰፈራው ፕሮግራም፣ የአማራ ሳይንቱ ማኅበረ ሰብ ከአካባቢው የኦሮሞ ማኅበረ ሰብ ተወላጆች ጋር በመልካም ጉርብትና መንፈስ አብሮ እንዳይኖር ከመጀመርያው የታሰበበትና፣ ዓለም ዓቀፋዊውን የሕዝቦች የሰፈራ ፕሮግራም መርህ ያልተከተለ” መሆኑን ነው። ባለኝ መረጃ መሠረት፣ እውነተኛውን ምክንያት በውል የሚያውቁና ሁለቱን ሕዝቦች ለዚህ መፈነቃቀል ያደረሰውን የተሳሳተ የሕዝቦች የሰፈራ ፕሮግራም ከመጀመርያው ጀምሮ ቀርጸውና በተግባር የተረጎሙት የያኔው ከፍተኛ የኢሕአዴግ መንግሥት ባለ ሥልጣን ዛሬም በአሜሪካ አገር በሕይወት ስላሉ፣ ታሪካዊ ኃላፊነታቸውንና ተጠያቂነታቸውን ተረድተው እውነቱን ለሕዝቡ ቢገልጹ እኔ ካቀረብኩት የተሻለ መረጃ ሊሆን ይችላልና ያስቡበት እላለሁ።
ሕዝቦችን ከሚያፈናቅሏቸው ምክንያቶች ዋና ዋናዎቹ፣
ሰላማዊ ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች ከቄያቸው ሊፈናቀሉ ይችላሉ። አንዳንዶቹ ምክንያቶች ሰው ሰራሽ ሲሆኑ የዚያኑ ያሕል ደግሞ ተፈጥሮያዊ ምክንያቶች አሉ። ጥቂቶቹን ብቻ ለመጥቀስ ያህል፣
ሀ) ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ማሕበራዊ ቀውስ፣ ለምሳሌም ሕግ የበላይነት መጥፋት፣ መንግሥት የሕዝቦችን ሰብዓዊና ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን ለማስከበር ሳይችል ወይም ሳይፈልግ ሲቀር፣ በጽንፈኞች ውትወታና በተለያዩ ምክንያቶች በሕዝቦች መከከል በሚከሰት የጎንዮሽ (የእርስ በርስ) ግጭቶች ምክንያት፣
ለ) ከሰው ልጆች ቁጥጥር በላይ የሆኑ ተፈጥሮያዊ አደጋዎች ምክንያት (ጎርፍ፣ መሬት መንቀጥቀጥ፣ እሳት አደጋ፣ ድርቅ፣ ወዘተ፣ የሚሉ ናቸው።
እነዚህ ሕዝብን የማፈናቀያ ምክንያቶች በቅርጽና በይዘት የመለያየታቸውን ያሕል፣ ተፈናቃዮችንና ስደተኞችን ወደ ቀድሞ ቤታቸው የመመለስ ቅድመ ሁኔታዎችም ያኑን ያህል የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ። ሁለቱንም የሚያመሳስላቸውና የሚለያያቸውን ምክንያቶች በአጭሩ ስንመረምር ደግሞ፣ የሚከተሉትን እናገኛለን።
ተፈናቃዮችና ስደተኞች፣ የሚመሳሰሉበትና የሚለያዩበት ሁኔታ፣
“ተፈናቃዮች” እና “ስደተኞች” በስሕተት እንደ ተመሳሳይ ክስተት ተደርገው ትንተና ሲደረግባቸው ይስተዋላል። ምንም እንኳ የሚፈናቀሉበትና የሚሰደዱበት ምክንያቶች ከሞላ ጎደል ቢመሳሰሉም፣ የሁለቱን መብትና ግዴታ፣ እንዲሁም ወደ ቀድሞ ሰፈራቸው የመመለስ ሂደትን በተመለክተ ግን ትልቅ ልዩነት አለ።
ስደተኞች የአገራቸውን ድንበር ተሻግረው በሌላ አገር ጥገኝነት (asylum) ጠይቀው የሚኖሩ ሲሆን ለመብታቸው ጥበቃ የሚውለው የዓለም ዓቀፍ የስደተኞች ጥበቃ ሕግ (international protection of refugees - 1951 Geneva Convention etc.) ስለሆነ፣ የዜግነት አገራቸው ሕግ በምንም መልኩ እነሱን ለመጥቀምም ሆነ ለመጉዳት ሊተገበር አይችልም። ተፈናቃዮች ግን በተቃራኒው፣ ያለፍላጎታቸው ከቄያቸው ቢፈናቀሉም ድንበር ስለማይሻገሩ፣ ለነሱ ጥበቃ ዋቢ አድርገን የምንወስደው ብሔራዊ ሕግንና መንግሥቱ የፈረማቸው ዓለም ዓቀፋዊ ውሎችን ነው። ለመፈናቀላቸው ምክንያት ግን ከላይ የጠቀስኳቸው ምክንያቶች ለነሱም እኩል ይሠራሉ። ለዝርዝሩ፣ በ 2 February 1995 ዓ/ም የተላለፈውን የተመድ ውሳኔ E/CN.4/1995/50 ይመልከቱ።
ለስደተኞች ወደ አገራቸው ለመመለስ (Repatriation) ወይም ለተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው ለመመለስ (Return) ግልጽ የሆኑ መሟላት ያሉባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። ቅድመ ሁኔታዎቹ በይዘት ቢለያዩም በቅርጽ ተመሳሳይ ናቸው። ለምሳሌ፣ ለስደተኞች መመለስ የሚያስፈልገው ሂደት፣ መጀመርያ፣ የዜግነት አገር መንግሥትና የስደት አገር መንግሥት በተመድ የስደተኞች ኮሚሽን (UNHCR) ድጋፍና ሰብሳቢነት የሶስትዮሽ (Tripartite) ስብሰባ ተደርጎ፣ የዜግነት አገሩ መንግሥት ዜጎቹን መልሶ ለመረከብ ቃል ይገባል። ይህ የዜግነት አገር መንግሥት ዜጎቹን ከስደት አገር መልሶ ለመውሰድ መስማማት የንግግሩ ቁልፍ ጥያቄ የሚሆነውን ያሕል፣ ስደተኞች ደግሞ ለመመለስ ሙሉ በሙሉ ፈቃደኛ መሆናቸው (voluntary repatriation) እኩል ወሳኝነት ያለው ቅድመ ሁኔታ ነው።
የተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ ቄያቸው መመለስን በተመለከተ ግን፣ የሶስትዮሽ ንግግር ባያስፈልግም፣ በቂ ዕርዳታና እንክብካቤ እንዲያደርጉ ከማለት አብዛኛውን ጊዜ የዓለም አቀፍ ማኅበረ ሰቡ በተለይም ተመድ አስፈላጊውን ተሳትፎ ያደርጋል። መመለሱ ግን፣ ልክ እንደ ስደተኞቹ፣ የተፈናቃዮቹን ሙሉ በሙሉ ፈቃደኝነት (voluntary return) ይጠይቃል። በሌላ አነጋገር፣ ስደተኞችንም ሆነ ተፈናቃዮችን ያለ ፍላጎታቸው ወደ አገራቸው ወይም ወደ ቀድሞ ሰፈራቸው መመለስ አይቻልም ማለት ነው። (ተፈናቃዮችም ዝም ብለው “መመለስ አንፈልግም” የማለት መብት አላቸው ለማለት ሳይሆን፣ መመለስ የማይፈልጉበት ተጨባጭ ምክንያት ካለ መንግሥት አስገድዶ ሊመልሳቸው አይችልም ማለት ነው። ለምሳሌ well-founded fear of persecution (ተጨባጭ የሆነ የኅልውና ሥጋት) የሚባለው ግላዊ የፍርሃት ስሜት ለተፈናቃዮች ላለመመለስ በመጀመርያ ደረጃ ከሚመደቡት ተጨባጭ ምክንያቶች አንዱ ነው)።
የስደተኞቹን ሁኔታ ለጊዜው ወደ ጎን ብንተውና፣ ከወለጋ ስለተፈናቀሉ የአማራ ብሔር ተወላጆችንና የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ ሰፈራቸው ለመመለስ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን ላይ ብናተኩር፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረ ሰብ በተለያዩ አገራት የሚጠቀምባቸውን ሕጎችና ልምዶችን ተግባራዊ ማድረግ ግድ ይላል።
ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ ቤታቸው ለመመለስ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች
ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ ሰፈራቸው ለመመለስ ከመወሰን በፊት መሟላት ካለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸው።
ሀ) ተፈናቃዮች ወደ ቄዬያቸው ከመመለሳቸው በፊት ያፈናቀላቸው ምክንያት በዘላቂነት መወገድ አለበት። ይህም ማለት ተፈጥሮያዊም ሆነ ሰው ሠራሽ ምክንያቶቹ አስተማማኝ በሆነ መንገድ ተወግደው፣ ተፋናቃዮቹ ወደ ቄያቸው ሲመለሱ፣ ከመፈናቀላቸው በፊት የነበራቸውን ሰላማዊ ሕይወት ለመምራት መቻላቸውን በሕግ ወይም በደንብ ብቻ ሳይሆን በተግባር ማስወገድና ተመላሾቹ በሰላም እንዲኖሩ መንግሥት ተጨባጭ የሆነ ዋስትና መስጠት አለበት። (የመፈናቀሉ መንስዔ የሕዝቦች የእርስ በእርስ ግጭት ከሆነ፣ ሁለቱን ሕዝቦች ከልብ አስታርቆና የግጭቶቹን መንስዔ አስወግዶ ወደ ቀድሞ ሁኔታ ለመመለስ ጊዜ ስለሚጠይቅ፣ ቅጽበታዊ ስኬትን መጠበቅ አይቻልም)።
ለ) ለተመላሾች ሰላምና መረጋጋት በሰፈነበት አካባቢ የመኖር ድባቡን ለመፍጠር አቅምም ሆነ ግዴታው ያለበት በዋናነት መንግሥት ሲሆን፣ ዓማጽያንም በሚቆጣጠሯቸው ሥፍራዎች ያንኑ ያሕል ኃላፊነት አለባቸው። የማኅበረ ሰቡም አባላት፣ በተለይም የኃይማኖት ተቋማት ለሰላምና መረጋጋት የበኩላቸውን ለማዋጣት ዝግጁ መሆን አለባቸው። ይህም ማለት፣ ለምሳሌ ከጊዳ ኪራሙና አካባቢው የተፈናቀሉትን ወገኖቻችንን ወደ ሰፈራቸው ከመመለሳቸው በፊት፣ ለሁለቱም ማኅበረ ሰብ አባላት ማለትም ለአማራውና ለኦሮሞ ተፈናቃዮች ወገንተኛ ያልሆነ ጥበቃ ሊያደርጉ የሚችሉ የጸጥታ አስከባሪ ኃይላትን መንግሥት ማሠማራት አለበት።
ሐ) በቀድሞ ቄያቸው ሰላምና መረጋጋት መስፈኑን ብቻ ሳይሆን፣ የሁለቱም ማኅበረ ሰብ አባላት አብረው በሰላም ለመኖር የሚያስችል ሰላማዊ ድባብ መፈጠሩን ለማረጋገጥ በዓለም ዓቀፉ ማኅበረ ሰብ ቋንቋ “ሂዶ መጎብኘት” (Go and See Visit) በሚባለው ፕሮግራም መሠረት፣ የሁለቱም ወገን ተፈናቃዮች ተወካዮች ወደ ቀድሞ ሰፈራቸው ተመልሰው አጭር ጉብኝት በማድረግ ሁኔታውን በገዛ ዓይናቸው ተመልክተው ወደ ቀድሞ ሰፈራቸው ተመልሰው በሰላም ለመኖር አመቺ ሁኔታ መኖሩን ራሳቸው አመነውበት ማኅበረ ሰቦቻቸውንም እንዲያሳምኑ ለማድረግ መንግሥት የጉብኝቱንና ተያያዥ የሆኑ የሎጂስቲክና የጸጥታ ሁኔታዎችን በተመለከተ ትልቅ ኃላፊነት መውሰድ አለበት። (በጉብኝቱ ወቅት፣ የሁለቱም ማኅበረ ሰብ ተወካዮች በአካል ተገናኝተው ስለ ግጭቱ መንስዔዎች በግልጽ ተነጋጋረው ይቅርታ መጠያየቅም ካስፈለገ ተጠያይቀው፣ ካሁን በኋላ ግን፣ አብረው በሰላም ለመኖርና የግጭት መንስዔዎቹን በጋራ ለማስወገድ ቅን የሆነ ውይይት ማካሄድ ይችላሉ)።
መደምደምያ
በተለያዩ አገሮች በሠራሁባቸው ዘመናት ከቀሰምኳቸው ልምዶች ያስተዋልኩት አንድ ነገር ቢኖር፣ በተለምዶ፣ ተፈናቃዮች አብዛኛውን ጊዜ አርሶ አደርና ኑሮአቸው ከመሬት (ከእርሻ) ጋር የሚገናኝ ስለሆነ፣ በተቻለ መጠን በአስቸኳይ ወደ ቀድሞ ቄያቸው ተመልሰው በዚህ ምድር ላይ ካላቸው ብቸኛ ሃብታቸው ጋር ማለትም ከመሬታቸው ጋር ተገናኝተው አንድ የሚያውቁትን ሙያቸውን ማረስን ለመጀመር ከማለት፣ በመንግሥት ባለ ድርሻ አካላትና በዓለም ዓቀፉ ማኅበረ ሰብ ላይ ጫና ማሳደራቸውን ነው። ከትውልድ ሰፈራቸው ውጭ ስለ ዓለም ያላቸው ዕውቀት እምብዛም ስላይደለ፣ ወደ ሌላ አገር የመሄድ ዕቅድ አይኖራቸውም። ከመሬታቸው ተለያይተው በመኖራቸው፣ ሌላ አካል ወይም ቡድን መጥቶ መሬታቸውን እንዳይወስድባቸው፣ በተቻለ መጠን በአስቸኳይ ወደ ቀድሞ ቤታቸ ለመመለስ ይፈልጋሉ። (አንዳንድ የፖሊቲካ ዓላማ ያላቸው ድርጅቶችና ከተፈናቃዮቹ ጋር በመሥራት ብቻ ዳጎስ ያለ ገቢ የሚያገኙት አገር በቀልና ዓለም ዓቀፍ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ግን፣ የመመለስ ቅድመ ሁኔታዎች እንኳ ቢሟሉ፣ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀድሞ ቄያቸው እንዲመለሱ አይፈልጉም)።
ሳይወዱ በግድ የቀድሞ ሰፈርንና አካባቢን ጥሎ መሄድ በጣም አሳዛኝ ነገር ነው። በተለየዩ ጊዜያትና ምክንያቶች ብዙዎቻችን ዛሬ በውጭ አገር የምንገኝ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያለፍንበት ስለሆነ፣ ያደጉበትን ሰፈር፣ ቤተሰብ፣ ዘምድና አካባቢን ጥሎ መሰደድ፣ ለማንም የማንመኘው አስከፊ ጉዞ ነው። መሰደድ፣ ከአርሶ አደሩ ሕዝብ በተለየ መልኩ ለተማረው ዜጋ ግን በአንጻሩ ቀላል ነው። የተማረ ሰው ራቅ ብሎ ቢሰደድም ሠርቶ ራሱንና ቤተሰቡን የመርዳት ዕድሉ ከፍ ያለ ሲሆን፣ ለአርሶ አደሩ ተፈናቃይ ወይም ስደተኛ ግን፣ ከቄዬው ራቅ ብሎ መሄድ በጣም ይከብዳል። ለአርሶ አደሩ ወይም ነጋዴው ተፈናቃይና ስደተኛ፣ ዋነኛ ሕልማቸው፣ የመፈናቀላቸው ወይም የመሰደዳቸው ምክንያት በቶሎ ተወግዶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ቄያቸው ተመልሰው ወደ እርሻቸው ወይም ንግድ ሥራቸው መመለስ ነው። ስለዚህ ከጊዳ ኪራሙና አካባቢው የተፈናቀሉት ወገኖቻችን ወደ ቄያቸው የመመለስ ፍላጎታቸው ከዚህ አንጻር ነው መታየት ያለበት።
ወደ ቀድሞ ሰፈር መመለስ ለተፈናቃዮች መብት ሲሆን ለመንግሥት ደግሞ ግዴታ ነው። ይህ ማለት ግን፣ የተፈናቃዮች የመመለስ መብት ገደብ የለሽ ነው ወይም የመንግሥትም ግዴታ በአንዳችም ቅድመ ሁኔታ አይወሰንም ማለት አይደለም። ተፈናቃዮች፣ ሁኔታዎች ሳይመቻቹና ተመልሰው በሰላም ለመኖራቸው ዘላቂነት ያለው ዋስትና ሳይኖር ዝም ብሎ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ መመለስ አለብን የማለት ገደብ የለሽ መብት የላቸውም። መንግሥትም ሁኔታዎች ሳይመቻቹ ተፈናቃዮቹን አስገደዶ የመመለስ መብት የሌለውን ያህል፣ ሁኔታዎች ተመቻችተው እያለ ግን፣ ዝም ብሎ ተፈናቃዮችን ከመመለስ ሊያግድ አይችልም። እንግዲህ ስለ ተፈናቃዮች የመመለስን ሁኔታ በተመለከተ በሚዲያም ሆነ በተለያዩ መድረኮች ላይ ስንሰብክ እነዚህን ተጓዳኝ ክስተቶችን ግምት ውስጥ መክተት አለብን ማለት ነው።
በተረፈ ግን፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት፣ በአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ ምክንያት በቦታው ተገኝቶ እውነተኛ መረጃና ማስረጃ ሊያጋራን የቻለ አንድም ግለ ሰብ ወይም የመግሥት አካል ስላልነበር፣ እንደው ዝም ብሎ “ወለጋ ውስጥ በአማራ ሕዝብ ላይ ጄኖሳይድ እየተፈጸመ ነው” “ኦሮሞዎች አማሮችን አፈናቀሉ” ወዘተ እያልን፣ ግፋ ብሎም በሌላ አገር የተፈጸመን ጥቃት በአገራችን እንደተፈጸመ አስመስሎ የውሸት ቪዲዮ እያሠራጨን፣ በሕዝቦች መካከል ጥላቻንና ቂም በቀልን ከመዝራት፣ የመፈናቀሉን መንሥዔ በበቂ አጥንተን ሁለቱ ሕዝቦች በሰላም አብረው በዘላቂነት የሚኖሩበትን መፍትሄ ፍለጋ ላይ ብናተኩር ለሁሉም ይበጃል ባይ ነኝ። አለበለዚያ፣ ላለፉት አምስት ዓመታት በአገራችን ታሪክ ውስጥ ተድርጎ የማይታወቅ በወለጋ ላይ ብቻ የታወጀ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ (ኮማንድ ፖስት) ዛሬም በተግባር እያለና፣ በጊዳ ኪራሙና በአካባቢው በአካል ተገኝቶ እውነተኛውን የግጭቱን መንሥዔና ያስከተለውን ሰዋዊና ቋሳዊ ውድመትን የሚዘግብ የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያ በሌለበት ወቅት፣ ዝም ብሎ በግምት ከተለያዩ አቅጣጫ ከምናገኛቸው ተጨባጭ ያልሆኑ መረጃዎችን ይዘን፣ ስለ ጉዳዩ አንዳችም ግንዛቤ የሌላቸውን ሰላማዊውን የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦችን ለሌላ ዙር ግጭት ባናነሳሳ የተሻለ ነው ባይ ነኝ።
በኔ ግምት፣ ተፈናቃዮቹ ይመለሱ አይመለሱ ብለን በጭፍን ከመስበክ ተቆጥበን፣ ገለልተኛ ባለ ድርሻ አካላት፣ የግልና መንግሥታዊ የሚዲያ ተቋማት በቦታው ተገኝተው ወገንተኛ ያልሆነ ዘገባ እንዲያቀርቡልን እና በዘገባው መሠረት በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲመሠረት ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለበትን መንግሥት ላይ ጫና ማሳደሩ ላይ መረባረብ አለብን። አሁንም መሸ እንጂ አልጨለመም። ስለዚህ ሰከን ብለን፣ በእውነት ስለ እውነት የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ሥቃይና እንግልት ከልባችን የሚቆረቁረን ከሆን፣ ጽንፈኞች በቀደዱልን የተሳሳተ የትርክት ቦይ እየፈሰስን ሕዝባችንን ለመፈነቃቀሉ እንደ ዳረግናቸው ተገንዝበንና፣ ሰፊው ሕዝብ ደግሞ ምን ጊዜም በርስ በርስ ላይ ተነስቶ እንደማያውቅ በመረዳት፣ ግጭትን ከማባባስ ብንቆጠብና አብሮነትን በሚያለመልሙ እንቅስቃሴዎች ላይ ብናተኩር የተሻለ ነው ባይ ነኝ።
ፈጣሪ አስተውሎትን ያብዛልን።
*****
ጄኔቫ፣ ዴሴምቤር 2023 ዓ/ም
wakwoya2016@gmail.com
https://amharic.zehabesha.com/archives/188475
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment