Monday, January 8, 2024

የፋኖ እስረኛ አያያዝና አወዛጋቢ ውሳኔዎች፤ከተሞችን በመስዋዕት ይዞ በማግስቱ በነጻ መልቀቅ፤ ለምን???
አንዳንድ ማብራርያ የሚያስፈልጋቸው ነገሮች አሉ፡፡ የሚድያ አካላት የፋኖ መሪዎችን ሲያገኙ መጠየቅ አለባቸው፡፡ እኒህ አንገብጋቢ ነገሮች ለህዝብ መብራራት አለባቸው ያለበለዝያ ዋጋ እያስከፈሉ ትግሉን ወደ ኋላ ሊያስቀሩት ይችላሉ፡፡ ህዝብ በፋኖ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበት እያደረጉ ነው፡፡ የፋኖ ዓላማ ከተማ ይዞ በማግስቱ መልሶ ለብልጽግና አመራር መልቀቅ ሳይሆን ከተሞችን በቁጥጥሩ ስር አውሎ የብልጽግናን መዋቅር በሙሉ መደምሰስና በምትኩ በፋኖ የሚመራ የህዝብ አስተዳደር ማቋቋ፤ መሆን አለበት፡፡ ከተማ ይዞ፤ከተማ መልቀቅ እቃቃ ጨዋታ ሆኗል፡፡ ህዝብ ማብራርያ ይፈልጋል፡፡ ፋኖ ከተማ ለመያዝ የሚከፍለው መስዋዕትነት ከባድ ነው፤ታድያ በከባድ መስዋዕትነት የተያዘው ከተማ በማግስቱ ተመልሶ ለብልጽግና አመራር ይለቀቃል፤ለምን?

ባለፉት ስምንት ወራት በተደረገው የፋኖ ትግል ብዙ አያሌ ድሎችን አስመዝግቧል፡፡ አብዛኛው የአማራ ክልል በፋኖ እጅ ሆኗል ነገር ግን ከተሞችን ለረጅም ግዜ ፋኖ ይዞ መቆየት አልቻለም፡፡ ላሊበላን ጨምሮ አያሌ ከተሞች በፋኖ ተደጋግመው ቢያዙም ብዙ ሳይቆዩ ፋኖ ለቅቋቸው ወጥቷል፡፡ ከተሞች በፋኖ ተይዘው ያልቆዩበት ምክንያት አይታወቅም፡፡ የማንም አገር የፖለቲካ ሚዛን ከተሞች ውስጥ ነው፡፡ በከተሞች የአገልግሎት ተቋማትና የህዝብ ክምችት ስለሚገኝ ፖለቲካዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡ ፋኖ አብዛኛውን የገጠር አካባቢ ለረጅም ወራት መያዝ ቢችልም የዞን ከተሞችን ይዞ መቆየት አልቻለም፡፡ የፋኖ መሪዎች እንደሚናገሩት ከሆነ ከተሞችን ለረጅም ግዜ ይዘው ከቆዩ ብልጽግና በከባድ መሳርያና በድሮን ከተሞችን ስለሚያወድም እየለቀቅን ለመውጣት ተገዳናል ይላሉ፡፡ ይህ አባባል እውነት ከሆነ ታድያ ፋኖ ከተሞችን መያዝ አይችልም ማለት ነው? ፋኖ ከተሞችን ይዞ የሚያስተዳደረው መቼ ነው ታድያ?

ሌላው የፋኖ አወዛጋቢ ውሳኔ የምርኮኛ አያያዝን በተመለከተ ነው፡፡ የብልጽግና ጦር እስከ ደም ጠብታ ሲዋጋ ከርሞ መጨረሻ በፋኖ ሲሸነፍ ይማረካል፡፡ ይህ ምርኮኛ የብልጽግና ወታደር ቄስ ሲያርድ የነበረ፤ እናቶችን የደፈረ፤ ገዳማትን ያቃጠለ፤ ተቋማትን ያወደመ፤ንጹሃንን በጅምላ በአስፓልት የረሸነ፤የአርሶ አደሩን የእርሻ በሬ ቀምቶ አርዶ የበላ ቀማኛ ወንጀለኛ ነው፡፡ ይህ ምርኮኛ ለአገዛዙ ታማኝ ሆኖ ለወራት ሲዋጋ፤ ብዙ ፋኖዎችንም የገደለ ደመኛ ጠላት ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ወንጀለኛ፤ደመኛ የአማራ ጠላት ምርኮኛ ሲሆን በዓለም ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ እርህራሄ ይሰጠውና፤ መጫሚያው ተቀይሮለት፤ ልብስ ተሰጥቶት፤የላመ የጣመ ቀለብ ተሰጥቶት፤ መታወቂያ ወጥቶለት፤ የትራንስፖርት ገንዘብ ተሰጥቶት ምንም እንዳልተከሰተ፤የሰራው ወንጀል ሳይጣራና ፍትህ ሳይሰጥ በሰላም ወደ ቤቱ ይላካል፡፡ ፋኖ ሙሉ ወጪውን ሸፍኖ ይልከዋል፡፡ በዚህ መልኩ የተሸኑት ምርኮኞች ተመልሰው ለብልጽግና ሲዋጉ በድጋሚ ተማርከዋል፡፡ የሚላኩት ምርኮኞች አማራ የሆኑት ጭምር ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በነጻ የተላኩት አማራ ምርኮኞች ተመልሰው ለብልጽግና በመግባት የሚሊሻና አድማ ብተና ስልጠና እየሰጡ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በነጻ የተላኩት የኦሮሞ ምርኮኞች ተመልሰው ለመከላከያ ሲዋጉ የተማረኩ አሉ፡፡

ይህ የሚያሳየው የፋኖ የምርኮኛ አያያዝ በስህተት የተሞላ መሆኑን ነው፡፡ ብልጽግናን ማርኮ በነጻ የሚለቅ ብልጽግና እንጅ ፋኖ ሊሆን አይችልም፡፡ብልጽግናን ማርኮ በነጻ የሚሸኝ ፋኖ የህዝብ ትግል መሪ መሆን አይገባውም፡፡ እንዲህ አይነቱ ፋኖ የአማራ ትግልን ያዳክማልና ከአመራርነት መወገድ አለበት፡፡ በነጻነት ትግል ውስጥ ጽድቅና ኩነኔ የሉም፡፡ ባህታዊነት በፋኖ አርበኝነት ማዕረግ ቦታ የላቸውም፡፡ መጽደቅ የፈለገ ሱባኤ ይግባ እንጅ የህዝብ ትግል በመጥለፍ ሩህሩህ በመምሰል መንግስተ ሰማያትን መውረስ አይቻልም፡፡

ፋኖ እራሱን መገምገም አለበት፡፡ ፋኖ የአቅም ችግር ካለበት ሳይውል ሳያድር እራሱን ማነጽ አለበት፡፡ ፋኖ መዋቅሩን ማሳደግ አለበት፡፡ ፋኖ በውስጡ የደህንነትና የፍትህ ስርዓትን ገንብቶ የስለላና ዳኝነት ተግባር ስራ ላይ ቢያውል ኖሮ ተመልሰው ለብልጽግና የገቡት ምርኮኞች በማጣራት ሂደቱ ታውቀው በፋኖ እስር ቤት መቆየት ነበረባቸው፡፡ ፋኖ የብልጽግና ታማኞችን ተንከባክቦ ስለሚልክ ተመልሰው እየወጉት ነው፡፡ ይሄ አሳሳቢ ነገር ነው፡፡ ፋኖ ህዝብ እያስተዳደረ ስለሆነ የደህንነትና የፍትህ ስራንም አብሮ መዘርጋት አለበት፡፡ ፋኖ የተማረ ኃይል ችግር የለበትም፡፡ የፋኖ የስለላ መዋቅርም በሳይንሳዊ ዘዴ መደገፍ አለበት፡፡

ባጠቃላይ ፋኖ ከተሞችን መስዋዕት ከፍሎ ከያዘ በኋላ በነጻ መልቀቅ ትርጉም የለውም፡፡ ፋኖ የተማረኩትን ሳያጣራና ፍትህ ሳይሰጥ በጅምላ ስለሚለቅ፤መልቀቅ ብቻ ሳይሆን አሞላቅቆ ልብስና ገንዘብ እየሰጠ ስለሚልክ አላግባብ ከልክ ያለፈ እርህራኈ በማድረጉ የራሱን ትግል እየጎዳ ነው፡፡ ይሄ መታረም አለበት፡፡ የፋኖ ምርኮኛ የህዝብ ጠላት ነው፡፡ ይሄ ምርኮኛ ዘር ማጽዳት የፈጸመ የኢትዮጵያ ጠላት ነው፡፡ ይሄ ጠላት ተጣርቶ ፍርድ ሳይሰጠው በነጻ መለቀቅ የለበትም፡፡ ፋኖ ወንጀለኛን በነጻ የሚለቅ ከሆነ ከህዝብ ያጣላዋል፡፡ ምርኮኛ ይለቀቅ ከተባለ ቢያንስ በምትኩ የፋኖ መሪዎችን ማስለቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በእስራኤልና በፍልስጤም ምርኮኞች መካከል የሆነው ይህው ነው፡፡ እስራኤል ባትፈልግም አፍጫዋን ተይዛ የሃማስ መሪዎችን ለቅቃለች፤ በምትኩ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸውን ጨምሮ የተያዙ ሰላማዊ ዜጎችን ሃማስ ለቅቋል፡፡ በዪክሬይንና በሩስያ መካከልም እየሆነ ያለው ይህው ነው፡፡ ትናንትና ብቻ ከመቶ በላይ የሩስያ ወታደሮች ከዩክሬይን ተለቀዋል፡፡

የፋኖ የተለየ ሊሆን አይችልም፤ምርኮኛ ለምን በነጻ ይለቀቃል፤ለምን? ፋኖ ምርኮኞችን ለምን በነጻ ይለቃል? ለምን? እነ መስከረም፤ሲሳይ አውግቸው፤ወንደወሰን፤ክርስትያን ታደለ፤ዮሃንስ ቧያለውና የመሳሰሉት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ መሪዎችና ጋዜጠኞች በአዋሽ አርባ በኮንቴይነር እስር ቤት በበረሃ እሳት እየተሰቃዩ የብልጽግና ገዳይ አዋጊዎች፤ ካድሬዎችና አመራሮች በነጻ ይለቀቃሉ፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም፤ መታረም አለበት፡፡ ፋኖ ብዙ የወረዳ እና የዞን አመራሮችን ማርኮ በነጻ ሲለቅ ቢያንስ የፋኖ መሪዎችን ማስለቀቅ ነበረበት፡፡ ሚሊሻና አድማ በተናም ከተማረከ በኋላ በነጻ መለቀቅ የለበትም፡፡ ቢያንስ ለፋኖ ቀለብ የሚሆን የእርሻ ስራ በመስራት ዋጋ መክፈል አለበት፡፡ ሂሳብ መወራረድ አለበት፡፡ ፋኖ በዳንግላ እስር ቤት የነበሩ 18 የትግሬ ተዋጊዎችን በነጻ ሲለቅ ህወሃት አያሌ የሚታወቁና የማይታወቁ አማራ እስረኞችን እስካሁን አስሮ እያሰቃየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከወልቃይት ታፍነው ተሰውረው ዳናቸው ጠፍቶ የቀረ ሺዎች አሉ፡፡ ፋኖ መስዋዕት ከፍሎ የትግራይ ተዋጊዎችን ነጻ ሲያወጣና ሲልካቸው በምትኩ ህወሃትን መጠየቅ ነበረበት፡፡ ምርኮኛን በነጻ መልቀቅ መልሶ እራስን ይጎዳልና ይታሰብበት!!

ለክርስትያን አንባቢዎቼና የዓለም መድኃኒት (በግዕዝ መድሃኒዓለም) ከድንግል ማርያም በማህጸን ተወስኖ መወለድ ለምታምኑ፤ መልካም የገና በዓል ይሁንላችሁ!!

ድል ለፋኖ፤ሞትና ስደት ለብልጽግና!!

እንስማው ሃረጉ
https://amharic-zehabesha.com/archives/188090

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...