Friday, December 1, 2023
ፋኖስ Fanos ፋኖስ ቁጥር 4
ህዳር19ቀን 2016 ዓም(29-11-2023)
የዛሬው የውይይታችን እርዕስ የምንታገለው ለምንና ለምን አይነት ሥርዓት ነው?የአማራ ፋኖስ ለምንፈልገው የሥርዓት ለውጥ ያበቃናል ወይ? በሚለው እርእስ ዙሪያ የደረስንበትን የጋራ አቋም የሚያንጸባርቅ ይሆናል።
ህብረተሰብ ባለፈባቸው የታሪክ እርከኖች ጊዜው በዳረገው የንቃት ደረጃ ለኑሮ የሚደረገው ትግል ለተለያዩ ስርዓቶች መምጣት ምክንያት ሆኖ አሁን ላለንበት ዘመን አብቅቶናል።ባለፉት ዘመናት በተከታታይ የሰፈኑት ስርዓቶች ሙሉ ለሙሉ የጥፋት መንገድ ቀይሰዋል ብሎ መኮነን ተገቢ አለመሆኑን የተረዳንበት ውይይት ሲሆን በፊደላት ቀረጻ፣ ታሪካዊ ቦታዎችን ማለትም የእምነት ቦታዎችን በመገንባት፣ የራሳችንን የቀንና የዓመት አቆጣጠር በማስላትና በመቀመር፣ብሔራዊ ስሜትን በማጠናከር፣ከውጭ ወራሪዎች የጸዳች አገር ማስረከባቸውን፣በሙዚቃ ፣በአመጋገብ፣በአለባበስ የምንለይበትን ባህል በማዳበራቸው ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ በአጽንኦት መርምረናል።ጥያቄው ግን ማደግ የሚገባቸው ተግባራትና መሻሻልና መከበር የሚኖርባቸው መብቶችና የመንግሥትና የሕዝብ ግንኙነቶች አለመታዬታቸው ነው። በነዚህም ምክንያቶች ያለፉት ስርዓቶች የሕዝቡን ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ ለማሟላት የቻሉ ሳይሆኑ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ የጠቀሙ ሌላውን ለጉዳትና ለመከራ የዳረጉ ነበሩ ማለት ነው።ያም ብቻ አይደለም በጉልበት አንዱ ሌላውን እያንበረከከ ሥልጣኑን በመቆጣጠር ያሻውን ሲያደርግ የነበረ፣የሕዝብን ያገር ባለቤትነት የካደ።የጥቂቶች ንብረት አድርጎ ያሻውን ሲያደርግ የነበረበት ሥርዓት መሆኑ ላለፉትና አሁንም ላለው ሥርዓት የጋራ መገለጫዎቹ ናቸው። ሥልጣኑን የተቆጣጠረ የኤኮኖሚውን መስክ በመቆጣጠሩ ጥቂት ሃብታምና ብዙ ደሃ የሆነ ማህበረሰብ ሊፈጠር ችሏል። ለዚያም ነው የመደብ አሰላለፍ ተከስቶ የደላውና ያልደላው፣የአገርን ሃብትና ንብረት በመዳፉ ስር ያደረገ የገዥ መደብና ያጣ የነጣ የተገዥ መደብ ተብሎ ሊመደብ የቻለው።
በዚህ የመደብ ሰልፍ ውስጥ ጥቂቶቹ ብዙሃኑን እንዳሻቸው የሚያደርጉበት፣የጉልበቱንና የላቡን ፍሬ መበዝበዝ ብቻ ሳይሆን ሰብአዊ ክብሩን የሚገፍ፣ሲፈልጉ የሚሸጡት የሚለውጡት፣ሲያሻቸው የሚነቅሉት የሚተክሉት ከዕቃ በታች ሆኖ እንዲኖር የሚያደርጉ በተለያዩ ጊዜያቶች በይዘት ሳይሆን በስም ብቻ የተለያዩ ስርዓቶች የሰፈኑባት ዓለም እንደነበረችና አሁንም እንደሆነች ታሪክ ይመሰክራል።የአገራት መወረርና በቅኝ ግዛት ስር መውደቅ የዚያ ውጤት እንደሆነ እኛም ባለንበት ዘመን ደርሰን ያዬነውና የምናውቀው ነው።
ያንን የተዛባና ኢሰብአዊ የሆነ አድራጎት በመቃወም የስርዓቱ ሰለባ የሆነው ሕዝብ በዬጊዜው በሚችለው መንገድ እምቢተኛነቱን አሳይቷል።የውጭ ወራሪዎችንም ታግሎ ሌላው ቢቀር የአገሩን ዳር ድንበር አስከብሮ ባንዲራ ሰቅሎ ለመዘመር በቅቷል።ምንም ያህል ትግል ቢያደርግም ግን የሚፈልገውንና የተሟላ ነጻነቱን ተቀዳጅቷል ማለት አይደለም።ስርዓት ሄዶ ስርዓት በመጣ ቁጥር የታሰረበት የብረት ሰንሰለት በመዳብ ሰንሰለት ከመለወጥ በቀር ያገኘው ለውጥ የለም።ቢለወጥ ያው ሰንሰለቱ ነው።ታሳሪውን ለተሻለ የኑሮ ደረጃ አያበቃውም።በተመሳሳይም አንዱ አይን ያወጣ ግፈኛ ስርዓት ወይም ፣የቅኝ አገዛዝ ስርዓት ተወግዶ በተዘዋዋሪ መንገድ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ከቀጠለ በብረትና በመዳብ ሰንሰለት የመታሰር ያህል እንጂ ሙሉ ለሙሉ ነጻ መሆን አይደለም።አገራችንና ህዝባችንም ያሉበት ሁኔታ ከግፈኞች ሰንሰለት ወደ ለዬለት ብሎም አጭበርባሪ ስርዓት የወደቀችበት ዘመን ነው።የውጭ የዘረኞች ወራሪ ስርዓትን ያሶገድን ኢትዮጵያውያን ለባዕዳን መሣሪያ በሆኑ በአገር ተወላጅ ዘረኞች የሚዘወር ስርዓት ስር ወድቀን መከራ የምናይበት ወቅት ላይ ነው ያለነው።
በታሪካችንም ሆነ በሌሎች አገሮች ታሪክ እንዳዬነው የውጭ ወራሪን ሃይል የተወራሪው አገር ሕዝብ ጎሳ እምነትና የመደብ ልዩነት ሳይለዬው በአንድ ላይ ታግሎ አገሩን ነጻ ለማድረግ ችሏል ፤ያ ማለት ግን ለዘለቄታውና አስተማማኝ ለሆነ ብሔራዊ ነጻነት አብቅቷል ማለት አይደለም፤፤ያ የጋራ ጠላት ሲወገድ በቦታው ላይ የአገር ተወላጁ ጨካኝ የሥልጣኑ ባለቤት ሆኖ በመከራ ጊዜ አብሮ የተሰለፈውንና ህይወቱን የገበረውን ሕዝብ መልሶ የሚግጥና የሚበዘብዝ ስርዓት እንዲፈጠር አድርጓል።ያም ግንኙነት በመደብ ትግሉ ላይ የማንነት ትግል ጨምሮበት የተለዬ መልክ እንዲይዝ ሆኗል።
የአማራ ፋኖ መነሳት ዋና ምክንያት የሆነው በሁለተኛው ምክንያት ማለትም በማንነት ጥያቄ ዙሪያ የተመለከተው ነው።ዘረኞች ሊያጠፉት ሲነሱ ላለመጥፋት ሲል የጀመረው የሞት የሽረት ትግል ነው።ለዚያም ብቻ ሳይሆን የጎሳ ማንነቱን ከዜግነት ማንነቱ ጋር አስተሳስሮ የተነሳ በመሆኑ መጀመሪያ እራሱን አድኖ የጋራ ማንነቱን ማለትም ኢትዮጵያዊነቱንና ኢትዮጵያን ለማዳን የሚያደርገው ትግል ነው።ሁለቱም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች ናቸው።
ይህንን ትግሉን በድል ከቋጨ በዃላ ሙሉ ለሙሉ ፍትህና እኩልነት ዴሞክራሲና አንድነት መጣ ማለት አይደለም።ለከፍተኛውና አስተማማኝ ለሆነው ሰላምና እድገትን ለሚያበስረው፣ብዝበዛና ጭቆናን ለሚያሶግደው የመደብ ትግል ይሰማራል ማለት ነው።ለዚያም አስተማማኝ የሆነ በፍልስፍና የታገዘ ሕዝባዊ ድርጅት መፍጠር የግድ ይሆናል። በህብረተሰብ እድገት ላይ የተመሰረተ በሳይንሳዊ ፍልስፍና የተመራ የፖለቲካ ትግል አካሂዶ አሸናፊ የሆነው ሕዝባዊው ሃይል አገሩንና ሕዝቡን ለአስተማማኝ እድገት፣ለጋራ ጥቅም ያበቃዋል፣ከድህነትና ከዃላ ቀር አስተሳሰብ መንጥቆ ያወጣዋል።በዚህ አቅጣጫ ተጉዘው ከሞላ ጎደል የተሳካላቸው አገሮች እንዳሉ አይካድም።ይህ ማለት ግን መቶ በመቶ የሕዝቡ ኑሮና ፍላጎት ተሟልቷል ማለት አይደለም።ህብረተሰብ እስካለ ድረስ ጊዜው የሚወልዳቸውን ፍላጎቶችና ፈተናዎች ለማሟላት በማያቋርጥ ትግል ውስጥ ይኖራል ።ከእርስ በርስ መተላለቅና ከወራሪዎች በኩል የሚደርስበትን ጥቃት ለመከላከል የሚያደርገው ትግል ይቀጥላል ማለት ነው።ትግል አቆመ ማለት ህይወት የሌለው በድን ሆኗል ማለት ነው።ህይወት ያለው ሁሉ ከውጫዊና ውስጣዊ አካላት ጋር በትግል እንቅስቃሴ ውስጥ የመኖሩ ነገር የተፈጥሮ ግዴታው ነው።
ወደ አገራችን ስንመለስ አሁን ያለንበት የታሪክ ወቅት ካለፉት ዘመናት የታሪክ ወቅቶች አይለይም።ቢለይ በስምና በዘመኑ አቆጣጠር ብቻ ነው።የገዥና የተገዢው፣የበዝባዥና የተበዝባዥ መደብ አለ።የአገሪቱን ሃብትና ንብረት የሕዝቡን ኑሮ የሚወስንበት በጎሳ ተዋረድ የተደራጀ ሥልጣኑን በጉልበቱ የተቆጣጠረ የገዥ መደብ አለ። ይህ ጎሰኝነትን ከለላ አድርጎ ላለፉት 33 ዓመታት የቆዬ ቡድን ከለላና መጠቀሚያ ላደረገውም ጎሳ ተወላጅ የረባ ነገር አልሰራለትም።በስሙ በመዝረፍ የእራሱን ሃብት አካበተ እንጂ ለደሃው የተሻለ ኑሮ አላመጣለትም።ከርሃብና ከድህነት ከበሽታም አላዳነውም፣የተረፈው ቢኖር በሚቀሰቅሰው የሥልጣን ግጭት በጦር ሜዳ እዬተሰለፈ ማለቅ ብቻ ነው።
የሚያሳዝነው ተበዝናዡም እንደበዝባዡ ቡድን በጫጨ የጎሳ የአስተሳሰብ ደረጃ ላይ የወደቀበትና እርስ በርሱ የሚባላበት የከፋ የጎሳ ህሳቤ ከነገሰበት ዘመን ላይ ደርሰናል።በዬአቅጣጫው የኔ ጎሳ ከዚያኛው ጎሳ ይበልጣል የሚለው ፉክክር ተባብሷል።የሰው ልጅ ፣ኢትዮጵያዊው ዜጋ በጎሳ ማንነቱ የሚጠቃ፣የሚጨፈጨፍበት፣የሚፈናቀልበት ግፍ የሚፈጸምበት ሥርዓት ሰፍኗል።ተጠቂውም ሲመረውና ሲበዛበት በቃኝ ብሎ አመጹን በአመጽ ለመመለስ ቆርጦ ተነስቶ በመፋለም ላይ ነው።ይህንን ሕዝባዊ ትግል ግን ጠልፎ መጠቀሚያ ለማድረግ የሚሞክሩ ግለሰቦችና ቡድኖች እንዲሁም የውጭ ሃይሎች መኖራቸውን ልብ ልንለው ይገባል።ለብሔራዊ ክብር፣ነጻነትና አንድነት፣ ለእውነተኛ ለውጥና ለሰብአዊ መብት መከበር ለፍትህና ለዴሞክራሲ መስፈን ለሚያበቃው የስርዓት ለውጥ ያላሰለሰ ትግል ማድረግ ይገባል።አሁን በሚታዬውና ሜዳውንና አዬሩን በሸፈነው የጎሳ አሰላለፍ ከተቀጠለበት ለባሰ ውድመት ይዳርገናል።አገራችንን ከጎሳ ስርዓት ቀለበት ሳትወጣ ከድጡ ወደማጡ መነከር ይሆናል።አንዱ ጎሳ በሌላው ጎሳ ቢሸነፍ አርፎ አይቀመጥም።ይህም ለቀጣይ የጎሳ ንትርክና ጦርነት ይዳርገናል ማለት ነው። ያው የብረቱና የመዳቡ ሰንሰለት አይነት ማለት ነው።
ስለሆነም የጎሳን አስተሳሰብ፣ዘረፋና ጭቆናን ብሎም የውጭ አገር ጣልቃ ገብነትን ለመከላከል በሚረዳው በሳይንሳዊ ፍልስፍና የታገዘ የህብረተሰብን አጠቃላይ ችግር የሚፈታ የፓለቲካ አስተሳሰብ መከተል የግድ ይላል።የዓለም ፖለቲካ በከበርቴውና በሶሻሊስቶች ሁለት ጎራዎች የተከፈለ ነው። ያንን ተረድተን ብሔራዊ ክብራችንንና ጥቅማችንን ይበልጥ በሚያስከብረው ጎራ ውስጥ መሰለፍ የማናሶግደው ምርጫ ነው።ሌላውም ከሁለቱም ጎራዎች ሳይሆን በመሃል ሰፋሪነት የሚዘወር( የሊበራል ወይም ለዘብተኛ) የፖለቲካ አስተሳሰብ መኖሩ አይካድም።ግን የራሱ የሆነ ፍልስፍና የሌለው ከሁለቱም መካከል የተንሳፈፈmb,መሆኑ የማታ ማታ ከሁለቱ ወደ አንደኛው ማዘንበሉ አይቀሬ ነው። እዚህ ላይ ሊበራል ሲባል ኒዎ ሊበራሊዝም(Neoliberalisim) የሚለውን የዘመኑን የስውር ቅኝ አገዛዝ ስልት ማለታችን እንዳልሆነ ለመግለጽ እንወዳለን።
አሁን በመካሄድ ላይ ያለው የአማራው ፋኖ ትግል በመሰረቱ ብሔራዊ ክብርን ለማስጠበቅ፣የዜጋን የእኩልነት መብት ለማረጋገጥ የሚደረግ መደብ ያለዬ ትግል ነው።ይህ ትግል ዴሞክራሲያዊ ይዘት ስላለውና ሕጋዊ ጥያቄም ስላነገበ ሊደገፍ ይገባዋል።ሆኖም ግን በዚህ ሕዝባዊ የፍትሕ ትግል ጀርባ የጎሳ መተካካት ሆኖ እንዳይቀር፣ ሥልጣኑ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ እጅ እንዳይወጣ፣ገፊና ተገፊም እንዳይኖር ፣እንዲሁም የውጭ ሃይሎች በተለይም ላለፉት ስርዓቶችና ለአሁኑም አገር አጥፊዎች የጀርባ አጥንት የሆኑት አገሮች ጣልቃ እንዳይገቡበትና እንዳይቆጣጠሩት ማድረግ ከሁሉም አገር ወዳድ ይጠበቃል።
የአማራ ፋኖ ትግል ለአማራው ህልውና ከመሆን ባለፈ ለሥልጣን የሚደረግ ትግል አድርጎ ማቅረብ ሌላውን ጎሳ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ ከአጋርነትና ከባለቤትነት ድርሻ ሊያገል ብሎም በጸረ አማራነት ለማስነሳት የሚያስችል ስጋት ሊፈጥር ስለሚችልና ለአገዛዙ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ስለሚረዳ ለስርዓት ለውጥም ስለማያበቃ መስተካከል አለበት።በተጨማሪም በፋኖ ትግል ውስጥ የአንድ አስተሳሰብና ፍልስፍና ተከታዮች ሳይሆኑ በተለያዩ አስተሳሰቦችና የመደብ ጥቅሞች የተሰለፉ ብሶት ያገናኛቸው ግለሰቦችና ቡድኖች የተሳተፉበት በመሆኑ እነሱን የስልጣን ባለቤት ማድረጉ ለጥቅማቸው የሚነታረኩበት ቀውሰኛ ስርዓት መፍጠር ማለት ነው።የፖለቲካችን ማጠንጠኛ እንዝርቱ ኢትዮጵያዊነት ሲሆን ከዃላቀር የጎሳ አስተሳሰብና ንትርክ ተላቀን ለተሻለ ነጻና ብሔራዊ የኤኮኖሚ እድገትና የጋራ ጥቅም ከሚያበቃን ምዕራፍ ላይ ለመድረስ በሚያስችለን የፖለቲካ አሰላለፍ ውስጥ መታገል ተገቢ ነው።
በእዚህ ላይ ሶሻሊስቶች ድምጻቸውን አጥፍተው መቀመጥ ሳይሆን ካለፈው ስህተታቸው ተምረው በድፍረት የዓለም አቀፉን የፖለቲካ አሰላለፍ በዋጀ መልኩ ለአገራቸው እድገትና ለሕዝብ ጥቅም የሚረዳውን በፖለቲካ ፍልስፍና የታገዘ ራዕይ ነድፈው መስራት ይጠበቅባቸዋል።በአላዋቂዎችና በቀኝ ፖለቲካ አቀንቃኞች በሚነፍሰው የስም ማጥፋትና የጸረ ግራ ፖለቲካ ትርክት ተንበርክከው የትግል ቦታውን ሊለቁ አይገባም።ሶሻሊዝምን ከአምባገነኖች፣ ከወራሪዎቹና ከዘራፊዎቹ ጋር እያቆራኙ ሕዝቡን ማሳሳት የምዕራቡ ስልት እንደሆነ መታወቅ አለበት።ሶሻሊስት ሲባል በሩስያና በቻይና ዓይን ብቻ መታዬት የሌለበት ሳይንሳዊ ፍልስፍና ነው።ሶሻሊስት አስተሳሰብ ማለት ሕዝባዊነት ማለት ነው። ያንን በመጥለፍ ሥልጣን ላይ ወጥተው አገራቸውንና ሕዝባቸውን ሳይቀር በጎዱ አምባገነኖች ዓይን መታዬት የለበትም።የሶሻሊስት እምነትና መመሪያ ጸረ አምባገነንነት፣ጸረ ዘራፊና ወራሪ መሆን ማለት ነው። ሶሻሊስቶች ባይኖሩ ኖሮ የዓለም ሃገራት በተለይም አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት መዳፍ ባልወጡ ነበር።አሁንም በያገሩ የስደተኛው መብት የሚከበረው ሶሻሊስቶቹ በሚያደርጉት ትግልና ጥረት ነው።በተለይም በአሁኑ ጊዜ ዘረኝነት የሚያስተናግዱ የቀኝ ፖለቲካ ፓርቲዎች እያደጉ መምጣት ለሁሉም የሰው ልጆች አደገኛ ክስተት ነው።ለዚያም ነው የግራው ፖለቲካ መጠናከር አስፈላጊነቱ። በዴሞክራሲ ሕግ መሰረት የቀኙ የፖለቲካ አቀንቃኝ መብት መከበር እንዳለበት ሁሉ የግራውም የፖለቲካ ፍልስፍና ተከታይ መከበር ይገባዋል። ስርዓትን በተከተለ መልኩ የሁለቱ የሃሳብ መፋጨት ለተሻለ ስርዓት ያበቃል።መራጩና ወሳኙ ሕዝቡ ነው።ለመምረጥ ደግሞ የተሟላ እውቀትና ግንዛቤ ሊኖር ይገባል።ለዚያ አይነቱ ዘመናው የፖለቲካ ባሕል መስፈን ሁላችንም እንታገል።
አገራችንን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች እናድን!ለዘላቂ አገራዊና ሕዝባዊ ችግሮች መፍትሔ ወደመሻቱ እናተኩር! ከጎሳ ማንነት በላይ ኢትዮጵያዊና ሰብአዊ ማንነትን እናስቀድም!!!
https://amharic-zehabesha.com/archives/187462
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment