Tuesday, December 26, 2023

ፋኖ 2020! - አስቻለው ከበደ አበበ
 

ሰውዬው ሸበታሙ የጎፈረ ጺማቸውን እያሻሹ ሰቱዲዎው ውስጥ ጠረጴዛውን በእጃቸው ተደግፈው ተቀምጠዋል፡፡ ቃለ መጠይቅ ሊደርግላቸው የጋበዛቸው የካም ሚዲያ ጋዜጠኛ፣ቃለ መጠይቁን ሊጀምር ካለ በኋላ የሆነ የረሳው ነገርን ለማምጣት ብሎ ወደ ሌላ ክፍል ትቷቸው ወጣ፡፡

ስቱዲዮው መጠነኛ ቢሆንም ዘመናዊ ነው፡፡ ሰውዬው ዞር ዞር ብለው ድምጽ አያስተጋቤ የሆነውን የግድግዳ ልብጥ ዙሪያ ገባውን በቀኝ አይናቸው ተመለከቱ፡፡ የግራ አይናቸው ሽፋሽፍት ላይ ግማሽ ጨረቃ ምስል የሰራ ጠባሳ አለ፡፡  አይናቸው ደግም የተሰበረ ግን ያልረገፈ መስታወት ይመስል ስንጥቅጥቅ በዝቶበትና ከቀኝ አይናቸው አንሶ ይታያል፡፡

መቅረፀ ድምጹን እየነካኩ ጠረጴዛው ላይ ጋዜጠኛው አዝረክርኮ የሄደውን ወረቀቶች ተመለከቱ፡፡ ትኩረታቸውን የሳበው እሳቸው የሚሰሩበት የፋኖ ድርጅት አርማ ነበር፡፡ በስተግራውና ቀኙ በግማሽ ጨረቃ አምሳል የገበብስ ዘለላና የማሺን ጥርስ አሉት፡፡ መሃል ላይ አንድ ወደ ቀኝ የዞረ የማረሻ ምልክትና የክላሽንኮቭ መሳሪያ ስዕል ኤክስ ምልክት ሰርተው ተመሳቅለው አሉ፡፡ ከበላዩ ደግሞ የቄስ ይሁን የሼክ ያለየለት ጥምጣም ይታያል፡፡

ድንገት በራፉን ከፍቶ የገባው ጋዜጠኛ ተስተካክሎ እየተቀመጠ "ቀን ሚያዚያ 7፣ 2020ዓ.ም." አለና  እራሱን አስተዋውቆ እራሳቸው እንዲያስተዋውቁ እድል ሰጣቸው፡፡

ሰውዬው "ስሜ መኮንን ቢሰጥ እባላለሁ፡፡ የአማራ ፋኖ ትግል እሰከተጋጋመበት 2015 ዓ.ም. አጋማሽ  ድረስ በእንጂባራ ዩንቨርስቲ መምህር ነበርኩ፡፡" ይሄን ግዜ ጋዜጠኛው አቋርጧቸው፣

"የአገው ተወላጅ የነበሩና ወዶ ገብ አማራ እንደሆኑ ሰምተናል፡፡ በዚህ ሶስት አመት ውስጥ ወደ አራት መጽሐፍ ጽፈዋል፡፡" ከሌላ ቢሮ ይዞ የመጣውን አራት መጽሓፎች እያገላበጠ የመጽሐፍቶቹን ርእስ  አነበባቸው የአባቴ ጅራፍ፣ የሽቅርቅሯ ፒኮክ መጨረሻ፣ የዳንግላ መሐተምና ፋኖ 2025!፡፡ መጽሐፎቹን ወደ ጎን አስቀምጦ "አሰኪ ስለመጽሐፎቹ ጥቂት ይበሉን አላቸው"

"ያው ሁሉም በፋኖ ትግል ውስጥ ካሳለፍኩት ህይወት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ የአባቴ ጅራፍ የሚለው ፣ ክርስቶስ የአይሁድ ቤተ መቅደስን የንግድ ስፍራ አድርገው የነበሩትን ሰዎች በጅራፍ ገርፎ እንዳባረራቸው የፋኖ ትግል በተናቀው የጎጃም ገበሬ ጅራፍ ማጮህ ተጀምሮ የደረሰበትን ውጣ ውረድና ድል ያሳያል፡፡ በሁለቱ ክረምቶች መሃል የሚለውን ጽሑፍ መጽሐፉ ውስጥ አንብበሃል?" በፊቱ ላይ ካዩት ሁኔታ እንዳላነበበው ስለተረዱ ቀጠሉ፡፡

" ፋኖ 2025! ደግሞ ፋኖ አሊ እንዱስትሪያል ግሩፕ የሚያመርታቸውን ለአካባቢ ተሰማሚ የግብርና ግብአት እቀዎች ከአምስት አመት በኋላ በ2025 ዓ.ም. ለአፍረካ ገብያ ማቅረብን ይመለከታል፡፡ አሁን እያመረትናቸው ያሉት እቃዎች ላለፉት ሁለት አመታት በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ተቀባይነት ስለገኙ በአፍሪካ ደረጃ ረዕይ ስለሰነቅንበት ጉዞችን ነው መጽሐፉ የሚያትተው ፡፡"

ጋዜጠኛው " እርሰዎ አገው ነዎት ነገርግን ወዶ ገብ አማራ እንደሆ ነው መጽሐፍቶችዎ የሚነግሩን፡፡ ያረጀውን የሰለሞንና ንግስት ሳባ ትርክትንም አቀንቃኝ ነዎት፡፡ አሊ የሚለው ድርጅታችሁም የአላሙዲን ቤተሰብን ሃብት ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡"

ይሄኔ ሰውየው በትዝታ ወደኃላ ሄዱ፡፡ እስራኤል ሀገር ስለ አገውና አማራ ህዝብ ግነኙነት ያቀረቡት ጽሑፍ ትዝ አላቸው፡፡ አገው፣አማራና ትግሬ በዘረመል(ዲ.ኤን.ኤ) አንድ ናቸው፡፡ የሚለያዩት በቋንቋ ብቻ ነው፡፡ የሚጋሩት የጋራ ባህል፣ሐይማኖትና ትርክት አላቸው፡፡ቅይጥ ቅይጥይጥ ህዝብ ናቸው፡፡

እሳቸው የተወለዱባት ዳንግላ በእብራይስጥኛ ዳን- ጊላ የእግዚአብሄር ፍርድ ደስታ ማለት ነው፡፡ ያስተምሩበት የነበረው የተሰየመበት ዩንቨርስቲ ኢንጂባራ ማለት ደግሞ ኢንጂ-ባራ፣ ኢንጂ በአረብኛ እንቁ ማለት ሲሆን ባራ ደግሞ በእብራይስጥ የእግዚአብሔርን አፈጣጠር የሚያሳይ ቃል ነው፡፡ ያ ደግሞ ከእግዚአብሔር ጥበብ ቶፓዚዮን ጋር የሚገናኝ ነው፡፡

የዳንግላ መሐተም የሚለውን መጽሐፋቸውን አጠር አድርገው ለጋዜጠኛው ከነገሩት በኋላ እንዲያነበው ጋብዘውት ስለ አሊ እንዱስተሪል ግሩፕና ስለእራሳቸው ማብራራት ቀጠሉ፡፡

" እኔ ወዶ ገብ አማራ አይደለሁም፡፡ አባቴ ጎንደር ውስጥ ነው የተወለደው እናቴ ደግሞ ዳንግላ ዙርያ የተወለደች አገውኛ ተናጋሪ ነበረች፡፡ አማርኛ አገው ቤተመንግስት ውስጥ ነው የተፈጠረው(ያደገው) ካልን የአገውኛና አማርኛ ግንኙነታቸው የዶሮዋና የእንቁላሉ ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው፡፡ መጀመሪያ እንቁላሉ ነው ወይስ ዶሮው ነው የነበረው ለሚለው ጥያቄ መልሱ የለንም፡፡ እንቁላሉን ዶሮዋ ጥላው ሊሆን ይችላል፣ ወይንም ዶሮዋ ከእንቁላሉ ተፈልፍላ ሊሆን ይችላል፡፡

"ሌላው እንደሚባለው አሊ የሚለው የድርጅታችን መጠሪያ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ውስጥ የተጠቀሰው ስም አይደለም፡፡ አሊ ምህጻረ ቃል ሲሆን የሁለት ስም መነሻ ፊደሎችን የያዘ ነው፡፡ አመዴ ሊበን የሚባል የተሰዋ ፋኖን የሚዘክር ነው፡፡ ይህ እንዱስትሪ የተከፈተው ደግሞ ዲያሰፖራው ባዋጣው ገንዘብ፣ከቦንድ ግዢና ከአለም አቀፍ እርዳታ ሰጨዎች ከተገኘ አስራ አምስት ቢሊዮን ብር ነው፡፡"

ግራ አይናቸውን ቆረቆራቸው፡፡ በሞርታር ፍንጣሪ የተመቱ ግዜ የተሰማቸው ስሜት ተሰማቸው፡፡ ህዳር መጀመሪያ ላይ የጎጃም ፋኖዎች በደረጉት ጦርነት ነበር የቆሰሉት፡፡ አይናቸው ባይፈስም ጠፍቷል፡፡ ከዚያ በላይ ግን ህይወታቸውን ሙሉ የመይረሱትን ጓዳቸውን ያጡበት ግዜ ነበር፡፡

አመዴ ሊበን በወለጋ ተወልዶ ያደገ የሰላሳ አምስት አመት ወጣት ነበር፡፡ የተሳካለት ነጋዴና ሃብቱን ለሁሉ ያበላ የነበረ ለጋስ ወጣት ነበር፡፡ወለጋ በተደረገው የወሎ ሰፋሪዎች ጭፍጨፋ ወቅት ሁለት ልጆቹን ጨምሮ ዘጠኝ ቤተሰቡን በሞት አጥቷል፡፡ አንድ የደረሰች ሴት ልጅ እነደበረችው ለሰውዬው አጫውቷቸዋል፡፡ ሸኔዎቹ የነ አመዴን ቤት ሲያቀጥሉ ሮጣ ወደ ጫካ ገብታ ጠፋች፡፡ አውሬ ይብላት፣ ሸኔ ጠልፎ ይውሰዳት አመዴ የሚያውቀው ነገር የለም ፡፡ከተለያዩ ግዜ ጀምሮ የዘወትር ፀፀቱ እንደሆነች ነው ላገኘው ሰው ሁሉ የሚናገረው፡፡ አመዴ ከወለጋ ከተፈናቀለ በኋላ  ምንም የሌለው ጎዳና ላይ የወደቀ ተፈናቃይ ሆነ፡፡ቦኃላም የባህረርዳር ፋኖን ተቀላቅሎ እንደንግዱ ተዋጊነቱንም በአልሞ ተኳሸነት ተያያዘው፡፡

ምንያደርጋል፣ ከስምንት ወር ትንቅንቅ በኃላ የእሰቸውን አይን ያጠፋው የሞርታር ፍንጣሪ እሱን አንገቱ ላይ መቶት ለሞት አበቃው፡፡ በአልሞ ተኳሸነቱ በጎጃም ፋኖዎች ዘንድ ታዋቂ ስለነበርና የወለጋ ቤተ አማራ ፋኖዎችን ጭፍጨፋ ለመዘከር ሲሉ ከድል በኋላ ለገጠሩ ህዝብ ተሰማሚ ቴክኖሎጂ ማሸጋገሪያ እንዱሰትሪ ሲቋቋም በሰሙ ተሰየመለት፡፡

ጋዜጠኛው ሰውየው በትዝታ ፈረስ መንጎዳቸውን አይቶ "እሺ አመዴ ሊበን…" አለ ንግራቸውን እንዲቀጥሉ ምልክት እየሰጣቸው፡፡ እሳቸውም ስለጀግንነቱና ስለህልሙ አንድም ሳይቀር ከነገሩት በኋላ ጠረጴዛው ላይ የተቀመጠውን የእነዱስተሪውን ሎጎ አንሰተው እየተመለከቱ፣

"አመዴ ሊበን የስዕል ተሰጦ የነበረው ልጅ ነበር፡፡ በጣም አርቆ አሳቢና ይህ የምታየውን አርማ ዘወትር ከእጁ ከማትለየው ማስታወሻ ደብተሩ ላይ ደጋግሞ ይሰለው ነበር፡፡"

ከኪሳቸው ትንሽ ማሰታወሻ መያዣ ደብተረ አውጥተው ለጋዜጠኛው አቀበሉት፡፡ ማሰታወሻ ደብተሩ ላይ፣ ማረሻ ተስሎ ከጎኖ አራሽ የሚል ጽሑፍ ይነበባል፡፡ ከክላሽነኮብ ጎን ደግሞ ተኳሸ የሚል ጽሑፍ አለ፡፡ ከጥምጥሙ አጠገብ ደግሞ ቀዳሽ ወይም ቀሪ የሚል ጽሑፍ ይገኛል፡፡

"አመዴ ሲሰዋ አጠገቡ ነበረኩ፡፡ እንደምንም ብሎ ይህቺን ማሰታወሻ ደብተር ከኪሶ አውጥቶ ሰጥቶኝ ነበር እጄ ላይ ያረፈው፡፡" ሰውዬው ስቅስቅ ብለው አለቀሱ፡፡ ድንገት ስልካቸው በጎጃም እንጉረጉሮ ዋሽንት ደጋግሞ ጠራ፡፡

ይህን የስልክ ጥሪ ለአንድ ሰው ስልክ ብቻ ነው የሚጠቀሙበት፡፡ ያ ሰው ድግሞ የአመዴን ልጅ ፍለጋ ጉዳይ የያዘው ሰው ነው፡፡ ስልኩን አነሱት፡፡ በወደዲያኛው ጫፍ ያለው ሰው "እንኳ ደስ ያለህ መኴ፣ ልጅቷ ተገኝታለች፡፡ እኔ እራሴ በስልክ አውርቻታለሁ፡፡ ከአባቷ ከተለየች በኃላ ሶስት ቀን ጫካ አድራ ከተፈናቃዬች ጋር ወደ አዲስአበባ መጥታ ነበር፡፡ ታሪኩ ውስብስብ ነው፡፡ መጀመሪያ ወደ ሱዳን ሄደች  ሱዳን የርስበርሱ ጦርነት ሲነሳ ደግሞ ወደ ቻድ ሄደች፣ ከዚያም ሊቢያ፡፡ አውሮፓ ለመሄድ ብላ ሞክራ ሞክራ ሰይሆንላት ሲቀር ቱርክ ገብታ ከተመች፡፡ ብዙ የመከራ ግዜን አሳልፋለች፣ ክብሩ ይስፋው አሁን ጠሩ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ነግራኛለች፡፡"

"ስልኳን ቴክስት አድርግልኝ፡፡" የሚል ትእዛዝ ሰጥተው ስልኩን ዘጉት፡፡  ወደጋዜጠኛው ዞረው እንግዲህ ጨርሰናል በሚል አተያይ ተመለከቱት፡፡ ወዲያው ወደ ስልካቸው መልእክት ገባ፡፡ ግዜ ሳያጠፉ የመጣላቸው የስልክ ቁጥር  በቀጥታ ደወሉ፡፡

ስልኩ ደጋግሞ ጠራ ግን አይነሳም፡፡ ከዚህ ድምጽ በኋላ መልክት ይተዉ ከሚለው መልክት መተውያ ድምጽ እንደተሰማ ጣፋጭ በሆነ የወለዬ አማርኛ አነጋገር ዘዬ የሚያምር ልጅ ድምጽ" ናፍቆት አህመዴ ሊበን" ሲል ተሰማ ያንን ተከትሎም ሌላ የህጻን ልጅ ድምጽ"ወላሂ፣ ወላሂ አማራ ነኝ! ወላሂ፣ ወላሂ አማራ ነኝ" ሲል ተስተጋባ፡፡ ይህን ግዜ ሰውዬው ስልካቸውን እንደያዙ በረዥሙ ተንፍሰው ወንበሩ ላይ ተንሰራፍተው ተቀመጡና ጮክ ብለው "ሰላም- ሻሎም" አሉ፡፡

 

አስቻለው ከበደ አበበ

ሜትሮ ቫንኩቨር፣ ካናዳ

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/187880

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...