Friday, December 1, 2023
ቦታ፡ አሜሪካ ፣ ሳንሆዜ ካሊፎርኒያ
ቀን፡ ኖቬምበር 2023
የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን
ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ
በቅድሚያ ከሁሉ አስቀድሜ የአማራ ፋኖ እስክንድር ንጋና መላው ይፋኖ ታጋዮች ለእናንተ የላኩትን የከበረ ሰላምታ ለማቅረብ እወዳለሁ። ጀግናው የነጻነት ታጋይ፣ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ፣ የድሆች ጠበቃ፣ የነጻነት ታጋይ፣ እስክንድር ነጋ በውጪ ሃገር ሆናችሁ በተለያዬ መንገድ የፋኖን ትግል ለምትደግፉ ሁሉ በአማራ ፋኖ ታጋዮች ስም ምስጋናው ብዙ አድናቆቱ እጥፍ ድርብ እንደሆነ ገልጿልና በዚህ አጋጣሚ ይህንን መልዕክት እንድትቀበሉ በአክብሮት እጠይቃለሁ።
ውድ ወገኖቼ
የዛሬውን ንግግሬን በአንድ ገጠመኝ ልጀምርላችሁ:: እኔ ብዙ የኖርኩት አሜሪካ ውስጥ ቦስተን አካባቢ ነው። በዚህ አካባቢ ስኖር በማቹሴትስ ግዛት ስር ያሉ መኪናዎች የመኪና ታርጋ ላይ የተጻፈውን ሳይ “The spirit of America” የሚለውን ሃይለ ቃል አያለሁ:: ይህ ሃይለ ቃል በአማርኛ ሲተረጎም የአሜሪካ መንፈስ እንደማለት ይሆናል። በጎረቤት ስቴት የኒውሃምሸር ግዛት ስር የተመዘገቡ መኪናዎች ታርጋ ላይ የተፃፈው መሪ ቃል ደግሞ “live free or die” ይላል። ነጻ ሆነህ መኖር ካልቻልክ ብትሞት ይሻላል እንደ ማለት ነው። ሁለቱ ቢያያዝ The spirit of America Live free or die ይሆናል:: ነጻ ሆነህ መኖር ካልቻልክ ብትሞት ይሻላል የሚለው የአሜሪካ መንፈስ ነው የሚል ትልቅ ትርጉም የሚሰጥ ነገር ሆኖ አየሁት።
እዚያ አካባቢ በተንቀሳቀስኩ ቁጥር ይህንን መርህ ስመለከት ለአማራ ወገናችን ለኢትዮጵያ አገራችን ፋኖ የገባውን ቃለ ምህላ ዘወትር የምናስታውስበት የምናድስበት እንዲሆን እውቀትና ንቃት እንዲስጠን እፀልያለሁ:: The Spirit of Amhara The Spirit of Ethiopia : Live Free or Die ወይም የአማራነት መንፈሥ ከኢትዮጵያ መንፈስ አይለይም እላለሁ፣ ነጻ ሆነን ለመኖር እስከ ሞት መስዋዕትነትን እንከፍላለን። እንግዲህ ለነጻነት የሚታገለውን ፋኖን እግዚአብሄር ያጠናክርልን:: መስዋእትነቱን ቀንሶ ህዝባችን በነፃነት የሚኖርበትን ጊዜ ያቅርብልን እላልሁ::
ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ
እውነት ነው። የሰው ልጅ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ ጉዳይ ህይወቱ ነጻ ይሆን ዘንድ አጥብቆ ይሻል። ይህ ነጻነቱ ሲገሰስ ሙሉነት አይሰማውም። የነጻነት እጦቱ ለከት የሌለው ሲሆን ደግሞ ለነጻነት ትግል እስከ ሞት ይታገላል። live free or die ወይም በነጻነት ኑር አለያ ብትሞት ይሻላል ብሎ ታጥቆ በነጻነት አውድማ ላይ ህይወቱን እንኳን ሲሰጥ ከቶውንም ትንሽ አይሰስትም።
በሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ጊዜ ብሄር ሳይለይ በጅምላ፣ ሌላ ጊዜ ብሄር እየነጠለና እየለዬ በሚወረወር ጦር ሲጠቃ የቆየው ህዝብ የበደሉና የግፉ መጠን ልኬት ከማጣቱ የተነሳና የግፉ ጽዋ ሞልቶ መፍሰስ በመጀመሩ ዛሬ አማራ በአጭር ታጥቆ ለትግል ወጥቶአል::
አማሮች በተለይ ባላፉት ዓመታት በዴሞክራሲና በመልካም አስተዳደር እጦት እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ እየተሰቃዩ መኖራቸው ሳያንስ በማንነታቸው ላይ ያነጣጠረ ሌላ ጥቃት ሰለባ ሆኑ። አማሮች ብዙ ዋጋ በከፈሉላት ሃገራቸው፣ በሞቱላት ኢትዮጵያ ውስጥ ጎጆ ቀልሰው ለመኖር ያልቻሉበት ሁኔታ በምድሪቱ ተፈጠረ። ከጉራ ፋርዳ የጀመረው ብሄር ተኮር ጥቃት በተለይ በአብይ አህመድ ዘመን የደረሰውን የአማሮች ስደት፣ ግድያና የንብረት ዝርፊያ ከቶ ምን ሃይለ ቃል፣ ከቶ ምን አንደበት ይገልጸዋል?። አማራ ምን ያልሆነው ነገር አለ?
እኔ በአፍሪካ በጦርነትና በግጭት ላይ በነበሩ ሀገራት ሁሉ፣ ከሩዋንዳ ጀምሮ ሁሉም ቦታ ሰርቻለሁ:: ይሁን እንጂ በአማራ ላይ የደረሰውን ዓይነት ግፍ የትም አላየሁም ብዬ እመሰክራለሁ:: ይህ ወንጀል በዓይነቱ የተለዬ ነው፣ የትም አላየሁም:: እውነት ነው በተናጠል በየመንደሩ ብዙ ዓይነት ግፎች ሲፈፅሙ ያየን ቢሆን በአንድ ዝብ ላይ መንግስት ተብየው እያወቀ ያለህፍረትና ያለ ፍርሃት ይህንን ግፍና ጭካኔ ሲፈጽም አላየንም:: እልመስከርንም:: በወለጋ፣ በቤንሻንጉል፣ በመተከል፣ በአጣዬ፣ በሻሸመኔ በጋምቤላ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ ሳይቀር በአማሮች ላይ የደረሰውን እልቂትና ሰቆቃ፣ ስደትና መፈናቀል ከቶ ምን ሃይለ ቃል፣ ከቶ ምን አንደበት ይገልጸዋል? አማራ በአደባባይ ተስቀለ፣ ተቃጠለ፣ ተፈናቀለ፣ እልቆ መሳፍርት የሌለው መከራ አየ። እኛም ዝም እልን ዓለምም ዝም አለ:: ዓለም የኛን ስቆቃ ሊያዳምጠን አልፈቀደም:: ዩክሬን ውስጥ እንድ ህፃን ስትሞት በየሚዴያው ርእስ ይሆናል::: ዩክሬን ጦርነቱ በጀመረ በሳምንቱ 100 የዩክሬን ሰዎች በራሽያ ወታደሮች መገደላቸውን ተከትሎ የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ጠበቃ ከሄግ በሮ ሄደ ምርመራ ለመክፈት ሞከረ:: በአማራ ላይ የደረሰውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ከነማስረጃዎቹ በዓለም ለታወቁ ጠበቃዎች እቅርበን የሀያላን መንግስታት ድጋፍና ግፊት አላገኘም። ይሁን እንጂ ትግላችን ይቀጥላል። አማራ ድምፅ እስኪኖረው ትግላችን ይቀጥላል። በአለንበት ዓለም መብት በልመና እይገኝም:: ኢንትርናሽናል ህጎችና መለኪያዎች ለድሀና ለደካማ እገርና ህዝብ ዓይሰራም:: መቼም የትም እይሰራም:: እስሪኤልን
ብቻ መመልከት ብዙ ያስተምረናል:: ስንደራጅ ነፍጥ ስንይዝ አንድ ስንሆን: የኛን መብት መንካት የነሱንም ጥቅም መንካት መሆኑን ሲረዱና በእነሱ መንገድ ሳይሆን በእኛ መንግድ ካልሄዱ የራሳችንን እድል ራሳችን መወስን እንደምንችል ስናሳይ ብቻ ነው የምንመኘውን የሚገባንን ማግኘት የምንችለው::
ዛሬ የፋኖ መነሳት የሃይል ሚዛኑን ለውጦታል:: ፋኖና አማራ መነጋገሪያ ሆነዋል:: ዛሬ እኛ ጠይቀን ብቻ ሳይሆን ሃያላንና የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ ድርጅጅቶች የአማራን የፋኖን ትግል ትኩረት ስጥተውታል:: ፋኖ ትግሉን ወደ አዲስ ምእራፍ እያሽጋገረው ነው:: አሁን ትልቁ መሰናክል እኛው አማሪዎች እንዳንሆን እስጋለሁ:: ወገኖቼ ድል ጫፍ ላይ ነን:: ደርሰናል:: ጠላታችንን እናውቃለን:: የማናውቃቸው እኛን መስለው ከውስጣችን የሚቦረብሩንን ነው::
እንግዲህ መቼም፣ አንድ ህዝብ ግፍን ተሸክሞ የሚኖርበት የሆነ ልክ ይኖረዋል አይደለም? የአማራ ልጆች እጅግ የሚሳሱላት ሃገራችው ኢትዮጵያ በህገ መንግስት ፈራሽ ናት ተብላ የተፈረደባት ሀገር ስለሆነች አገሪቱ በቋፍ ሆናለችና እኛን አማሮችን ነጥሎ የሚያጠቃን ስርዓት ቢኖርም፣ ግፍ ቢበዛም፣ በአማራ ስም አንደራጅም፣ የከፈልነውን ዋጋ ከፍለን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ሆነን ትግላችንን መቀጠል አለብን በሚል በየእለቱና በየወሩ፣ በማንነቱ ለሚጠቃው አማራ ተገቢ መከታና ጋሻ ሳይሆኑለት ቆዩ። አማሮች በብሄራቸው፣ በማንነታቸው መደራጀታቸው ለሃገራዊ አንድነት አይጠቅምም፣ እስቲ ጊዜ ያልፍ ይሆናል እያሉ ቢጠብቁም በአማሮች ላይ የሚደርሰው የማንነት ተኮር የጥቃት ጦር ከቶውንም አልበርድም አለ። ይባስ ብሎ ማንነት ተኮር ጥቃቱ እየተሻለ ሳይሆን እያደር እየከፋ.... እየከፋ.... እየከፋ መጣ። አሁን አማሮች ማንነት ተኮር የሆነውን ጥቃት ለመመከት በማንነት ከመደራጀት ውጪ ሌላ አማራጭ የጠፋበት ደረጃ ላይ ደረሱ። እነሆ ተደራጁ፣ ከእንግዲህ ምንም ዓለማዊ ሀይል ይሁንን ትግል ወደ ኋላ አይመልሰውም::
እስከ ዛሬ ድረስ በአንድ በኩል ከክልሉ ውጪ የሚሆነው አማራ በማንነቱ ሲፈናቀል፣ ሲገደልና ሲዘረፍ በሌላ በኩል በክልሉ ውስጥ የሚኖረው አማራ ደግሞ በመልካም አስተዳደርና በድህነት የሚቀጣው ክፉ አስተዳደር እንደ መዥገር በላዩ ላይ ተጣብቆበት ቆይቷል። አማራ በክልሉ ውስጥም ከክልሉ ውጪም ሳይመቸው ኖረ። ይህ ህዝብ ህወሃት የተከለው ደካማ አስተዳደር ከዛሬ ነገ ይሻል ይሆናል ብሎ በጀርባው አዝሎ ቢቆይም ይህ አስተዳደር ለአማሮችም ሆነ ለኢትዮጵያ ተስፋ የማይሆን እንደሆነ በተግባር ታዬ። ስለሆነም አማሮች ይህንን አስተዳደር በቃኝ አንተን የማዝልበት ማንገቻዬ ተበጥሷል ብለው እነሆ ዛሬ ከባድ ትግል ላይ ናቸው። በቅርቡ እንደምታስታውሱት የአማራ ህዝብ ሆ ብሎ ወጥቶ በይልቃል ከፋለ ይመራ የነበረውን የብልጽግና ካቢኔ አፍርሶ እንደነበር ታውቃላችሁ። ይሁን እንጂ ትንሽ ትምህርት የማይወስደው የአብይ አህመድ አስተዳደር ከይልቃል ከፋለ ካቢኔ የባሰ ሌላ የብልጽግና ካቢኔ አቋቁሜ አማሮችን አስተዳድራለሁ ብሎ ተነሳ። የአብይ መንግስት ይህንን በማሰቡ በአማሮች ዘንድ የተደረገውን ትግል መናቅ በመሆኑ የአማራ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መራራ ትግል ላይ ይገኛል።
ዛሬ የአማሮች ትግል ህዝባዊነቱ አድጎ ባህላዊ የአማሮች የክተት ጥሪ ታውጆ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ሸዋ፣ ወሎ ድረስ ያስተጋባ መለከት ተነፍቷል። የአራቱም ክፍሎች የፋኖ መሪዎች አጠቃላይ እዝ እየመሰረቱ ናቸው:: የአማራን ማንነት በተግባር እያሳዩ ነው:: አማራ ማለት ትርጓሜው ነጻ ህዝብ ማለት ነውና በሃገራችን በነጻነት መኖር ካልቻልን ለነጻነት እየታገልን ልንሞት መርጠናል ብለው የአማራ ልጆች በአጭር ታጥቀው እየታገሉ ነው። live free or die ብለው ፋኖዎች በነጻነት፣ የመኖር መብታቸውን ለማስከበር ለእኩልነትና ለፍትህ ቤዛ ለመሆን በተዋጊነት ስልት ተደራጅተውና በአጭር ታጥቀው እነሆ የአብይ አህመድን አገዛዝ እያርገበገቡት ይገኛሉ። በክልሉ ውስጥ ከፋኖ የቅርብ ርቀት ቁጥጥር ውጭ የሆነ ከተማም ሆነ ገጠር የለም። ፋኖ በየትኛውም ጊዜ የትኞቹንም ቦታዎች ተቆጣጥሮ እያሰላ ወደፊት እየተራመደ ነው።
ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ
ከፍ ሲል እንደገለጽኩት ኢትዮጵያ ውስጥ ብሄር ተኮር ፖለቲካ ሲመጣ አማሮች ይህንን አደረጃጀት ሲነቅፉ ቆይተው ዛሬ ለህልውናቸው መራራ ትግል ውስጥ ሲገቡ አንዳንድ ወገኖች የአማራን የፋኖ ትግል በኢትዮጵያ ላይ ተስፋ የቆረጠ የብሄርተኝነት ትግል አድርገው የሚያቀርቡ አሉ። አንዳንዶች ደግሞ ፋኖነት የብሄርተኝነት (ethnonationalism) ስሜት በአማሮች መካከል እያበበ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ይላሉ። አንዳንዶች በአማሮች ውስጥ የነበረው የኢትዮጵያዊነት ስሜት እየተነነ መጥቶ የብሄር ሽታ በአማሮቹ መንደር በርትቷል ይላሉ። እነዚህ ትንታኔዎች ሁሉ የአማራን ህዝብ ትግል ፈጽሞ ያልተረዱ ናቸው። አማራ እንደ ህዝብ፣ እንደ ሌሎች ወገኖቹ ሁሉ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ነው። የአማራ ህዝብ ኢትዮጵያዊነትን አኮስሶ አማራነትን ሊያገዝፍ ከማይችልባቸው ምክንያቶች መካከል ጥቂት ዋቢዎችን ላሳያችሁ።
- ሀይማኖት
እንደምታውቁት የአማራ ህዝብ በዋናነት ወይ የክርስትና ወይ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ህዝብ ነው። ክርስቲያኑ በቤተክህነቱ ላይ ጠንካራ እምነት አለው። ኦርቶዶክሱ አንዲት ቤተክርስቲያን አንዲት ቤተክህነት ብሎ የሚያምን ህዝብ ነው። አማራ ውስጥ አማራነትን ከኢትዮጵያ ማንነት ገንጥሎ ለብቻው ብሄርተኛ እንዲሆን የሚጥር ቡድን ቢነሳ መጀመሪያ ከቤተክህነት ጋር፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ጋር ይጋጫል። አማራ እንደ ህዝብ ይህንን የሃይማኖት አጸዱን የሚያናጋ ማንኛውም ሃይል ሲመጣ የሚታገለው ጉዳይ ነው። ለኢትዮጵያና ለቤተክህነት ስጋት የሆነ ማንኛውም እንቅስቃሴ በአማሮች መንደር ህልውና አይኖረውም። የብሄርተኝነት አስተምህሮና ጸረ ኢትዮጵያ አስተምህሮ በአማራ ህዝብ ዘንድ በጣም ጽዩፍ የሆነ ተግባር
የሆነው አንድም ይህ መከፋፈል የሃይማኖቱን አጸዶች የሚያፈርስ ስለሆነ ነው።
ሙስሊም አማሮች ደግሞ ልክ እንደ ክርስቲያኑ የሃይማኖት ተቋማቸው በብሄር እንዲከፋፋል አይሹም። ሙስሉሙ አማራ በምንም ዓይነት የተከፋፈለች ኢትዮጵያን ማየት አይሻም። መጅሊሱን የሚከፋፍል አስተሳሰብ በሙስሊም አማሮች ዘንድ የማይታሰብ ነው። ስለሆንም ጸረ ኢትዮጵያ አጀንዳ ያለው ሃይል አማራ ውስጥ ቢነሳ ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋርም ይጋጫል ማለት ነው። በአጠቃላይ ክርስቲያኑም ሆነ ሙስሊሙ በሃይማኖቱ መጽሃፎች ላይ የተጠቀሰችውን ኢትዮጵያን ህልውናዋን ጠብቆ ለትውልድ ማሳለፍ የሃይማኖት ግዴታው አድርጎም ያስባል። ስለሆነም ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ እንቅስቃሴ በአማራ ክልል ሊጠነሰስ፣ ተጠንስሶ ሊያድግ የማይችለው አንድም በዚህ ሃይማኖታዊ ምክንያት ነው።
- ታሪክናእሴት
አማሮች የስነ መንግስት ታሪካቸውም ሆነ ባህላቸው ከኢትዮጵያ ጋር እጅግ የተቆራኘ ነው። ቋንቋቸው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚናገረው ነው። ኢትዮጵያን ለብዙ ሽህ አመታት ያቆዩት የሶሎሞንና የዛግዌ ስርወ መንግስታት አንዱ ዋና መሰረት አማራ ነው። ታሪኩ ገድሎቹ ሁሉ የሚናገሩት ኢትዮጵያንና ስለ ኢትዮጵያ ነው። ይህ ህዝብ ዛሬ የብሄር ፌደራሊዝም አስተምህሮ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰፈነበት ዘመን ያንን አባቶቻችን ሲዋደቁ ይዘውት የነበረውን ባንዲራ ይዞ ነው የሚታየው። ብአዴን የሰጠውን ባንዲራ አይቀበልም። አማሮች በአድዋ ጦርነት ጊዜ አብረውት የዘመቱት የኦሮሞ ጀግኖች፣ የትግራይ ጀግኖች፣ የከምባታ ጀግኖች፣ የጉራጌ ጀግኖች፣ ወዘተ. በአድዋ ጦርነት ጊዜ አንግበውት የሄዱትን ባንዲራ ዛሬም ከፍ አድርጎ ይዞት ይኖራል። በምስራቁ የሃገራችን ክፍል በቅርብ አመታት ገጥሞን የነበረውን የህልውና ጦርነት በድል ካጠናቀቁ በኋላ ጀግኖች ትግሪዎች፣ ጀግኖች ኦሮሞዎች፣ ጀግኖች ደቡቦች፣ ጀግኖች ጋምቤላዎች ወዘተ. ካራ ማራ ላይ የተከሉትን ያንን ባንዲራ ዛሬም አማሮች ከፍ አድርገው ይኖራሉ። ያንን ባንዲራ አማሮች ዛሬም ልጃቸውን ሲድሩ የሚያጌጡበት፣ ሃይማኖታዊ በዓላቸውን ሲያከብሩ ከፍ የሚያደርጉት፣ በተቃውሞ ሰልፎቻቸው ላይ የሚይዙት ያው የኢትዮጵያ ባንዲራ መሆኑ የሚያሳየው
አማራና ኢትዮጵያዊነት የማይፋቱ ጉዳዮች መሆናቸውን ነው። ዛሬ በአማሮች አካባቢ ብዙ እንስቶች ለአንገታቸው ድሪር የሚያደርጉት ይህንን ባንዲራ ነው፣ የነጠላና የቀሚሶቻቸው ጌጥ ይሄው ባንዲራችን ነው። የብዙ ወገኖች ቤት በዚህ ባንዲራ ያጌጣል። ይህ የሚያሳየው በዚህ ክፉ ጊዜም አማሮች ኢትዮጵያን በልቦናቸው ጽላት ውስጥ ምን ያህል ጠብቀው እንደሚያኖሩ ነው። በዚህ ህዝብ መሃል ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ የብሄርተኝነት ንቅናቄ ከቶውንም አይበቅልም።
- ዲሞግራፊውወይም የህዝቡ አሰፋፈሩ
ሌላው አማራን ከኢትዮጵያዊነት ለመነጠል የማያስችለው ጉዳይ የአማራ ህዝብ አሰፋፈር ጉዳይ ነው። አማሮች ከሌሎቹ ወንድም እህቶቹ ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን ለማቅናትና የተጠናከረ ማዕከላዊ መንግስት እንዲኖር ብዙ ደፋ ቀና ያለ ህዝብ ነው። በሃገሪቱ በየትኛውም ክፍል ተዘዋውሮ መኖር መብቱ በመሆኑ ተሰባጥሮ የሚኖር ህዝብ ነው። በኦሮምያ፣ በደቡብ፣ በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ ወዘተ ተሰባጥሮ ይኖራል። ይህ አሰፋፈሩና ይህ ተክለ ሰውነቱ ለብሄር ፖለቲካ የሚመጥን አይደለም። አማራ ከኦሮሞው ከትግሬው ከጉራጌው ተዋዶ ተጋብቶ የሚኖር ህዝብ ነውና ለዚህ ህዝብ የብሄር ፖለቲካ ጥብቆ ልኩ አይሆንም። አማራን የሚመጥነው ትግል በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ እኩልነት እንዲመጣ መታግልን እንጂ ብሄርተኝነት በምድሪቱ እንዲያብብ አይደለም። ስለዚህ አማራ ውስጥ የብሄርተኝነት አስተምህሮ አንድም ማደሪያ የማይኖረው በዚህ ምክንያት ነው።
- የዘርፖለቲካ ለሃገራችን መጻኢ እድል አዋጭ እንዳልሆነ አማሮች መረዳታቸው
የብሄርና የዘር ፖለቲካ ለሃገራችን ኢትዮጵያ መጻኢ እድል አደጋ እንዳለው አማሮች በጥብቅ ያምናሉ። አማሮች መዋቅራዊ ለውጥ ይምጣ ሲሉ ሃገራችንን ከተጣባት የዘር ፖለቲካና ፌደራኪዝም እናላቃት ማለታቸው ነው። የእኔ.......የእኔ....የእኔ.... ከሚል ፖለቲካ ወጥተን ወደ እኛ..እኛ... እኛ .... ወደሚል ማህበረ ፖለቲካ እንደግ ማለታቸው ነው። የአማራ ህዝብ እንደ ህዝብ ያለው ስነ ኑባሬ (ontology) የብሄር ፖለቲካን አያስተናግድም። አማሮች እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ወገናቸው በባህላቸውም በሃይማኖታቸውም አብሮነትን የሚያበረታቱ በመሆናቸው በዚህ ህዝብ መሃል አክራሪ ብሄርተኝነት ተዘርቶ ሊበቅል የሚያስችል የፖለቲካ እርሻ ሊኖር አይችልም።
- አማራንከኢትዮጵያ ገንጥሎ አገር መመስረት የማይታሰብ መሆኑ
አንዳንድ ብሄርተኝነት የተጠናወታቸው ወገኖች የዩጎዝላቪያን መገነጣጠል እያነሱ ኢትዮጵያም እንደ ዩጎዝላቪያ መሆን ብትችል ምንድን ነው ክፋቱ ይላሉ። ይህ ግምትና ንጽጽር የተሳሳተ ነው። የዮጎዝላቪያን ታሪክ ስናይ ለምሳሌ Croatia, Montengro, Serbia, Slovenia, Bosnia, Herzegovina, Macedonia የየራሳቸው ታሪክ፣ የየራሳቸው መንግስት፣ የየራሳቸው አገር የነበራቸው ሃገሮች ነበሩ። እነዚህ ሃገራት ለተወሰነ ጊዜ ተሰባስበው ቢቆዩም ህብረቱ ስላልጸና የለም ወደ ነበርንበት እንመለስ ብለው ህብረቱን ለማፍረስ ተስማምተው ተገነጣጥለዋል። እነዚህ ሃገራት ህብረታቸውን ሲያፈርሱ በሰላም ነበር የጨረሱት። ቀድሞ የነበራቸውን ሃገራዊ ቅርጽ እየያዙ በሰላም ተገነጣጥለዋል። የኢትዮጵያ ሁኔታ ከዚህ ፍጹም የተለየ ነው። አማራም፣ ትግሬም፣ ኦሮሞም ሆኑ ሌሎች ብሄሮች ዓለም የሚያውቀው ሃገራት ሆነው አያውቁም። ስለሆነም ዛሬ የመገንጠል ጥያቄ ቢነሳ ኢትዮጵያን እርስ በእርስ የሚያጠፋፋ ጉዳይ ይሆናል። ከሁሉም በላይ የሃገራችን ህዝብ የፈጠረው ሶሻል ፋብሪክና መዋለድ ኢትዮጵያን እስካ ሃቹ የማትከፋፈል ሃገር አድርጓታል። ኢትዮጵያ ውስጥ አማራው፣ ትግሬው፣ ኦሮሞው ወዘተ ከአብሮነት(coexistence)ውጭ አማራጭ የለውም። ኢትዮጵያውያን ተጋጭተን የየራሳችንን ሃገር ልንመሰርት ብንነሳ መቼስ አንድ ህዝብ ዙሪያውን ጠላት አፍርቶ ሃገረ መንግስት መመስረት አይችልም። ሰላምና መረጋጋት አይኖረንም። ይህ የኢትዮጵያ የውስጥ አለመረጋጋት ደግሞ የአፍሪካን ቀንድ ሊያፈርሰው ይችላል። ይህንን ችግር አማሮች አብጠርጥረው ያውቃሉና አማራን ከኢትዮጵያ የመነጠል የብሄርተኝነት እሳቤ በአማሮች መንደር አይሰራም ብቻ ሳይሆን አማሮች አጥብቀው የሚታገሉት ጉዳይ ነው። የአማሮች ትግል ሁላችንንም አቻችሎ የሚያኖር አዲስ የፖለቲካ ስርዓት ዘርግተን ተቻችለን የምንኖርበትን ምዕራፍ መክፈት ነው።
በአጠቃላይ በአማሮች መንደር ጸረ ኢትዮጵያ ይዘት ያለው የፖለቲካ ንቅናቄ ተዘርቶ የማያድግ ብቻ ሳይሆን አማሮች ህይወታቸውን ገብረው የሚዋጉበት ዋና ጉዳይ እንደሆነ መታወቅ አለበት። አማሮች ዛሬም፣ ነገም፣ ሁል ጊዜም አንድ ሃገር ነው ያላቸው። እሷም ኢትዮጵያ ናት ። ይህቺ ሃገር የኢትዮጵያውያን ሁሉ እናት እንደሆነች አማሮች የሃይማኖት ያህል የያዙት ጽኑ እምነት ነው።
እዚህ ላይ የሚነሳ ጥያቄ ይኖራል። ታዲያ አማራነትና ኢትዮጵያዊነት እንዲህ የተሳሰሩ ከሆኑ የአማራ ፋኖ ትግል ምንድን ነው? የአማራ ጥያቄስ ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ። ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠትና የአማራን ትግል ዓላማ በሚገባ ማጥራት ተገቢ ነው። አማሮች ከፍ ሲል እንደገለጽነው የብሄርተኝነት ትግል ላይ አይደሉም። ብሄርተኝነት (ethnonationalism) የሚባለው አስተሳሰብ ፖለቲካው ሁሉ በብሄር ይሁን፣ እኔም አንድ የአማራ ፖለቲካ ፓርቲ ይኑረኝ፣ የፌደራል ስርዓቱ በብሄር ላይ ተከልሎ ይቆይ፣ በእኔ ክልል መስተዳደር ውስጥ ከአማራ ሌላ የሌላ ብሄር ሰው አይሾምብኝ፣ ወዘተ አይደለም። አማሮች ለመዋቅራዊ ለውጥ እንታገላለን ሲሉ አንዱ የሚታገሉት ነገር ይህንን ለእኔ ለእኔ የሚባል የስስት ፖለቲካ ነው።
ታዲያ በዚህ ወቅት አማሮችን ያደራጃቸውና መራራ ትግል ውስጥ የከተታቸው ምንድን ነው? ብለን ከጠየቅን የአማሮች ጥያቄዎችና በአማራነት ተደራጅተው የሚታገሉላቸው አንኳር ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው።
- በሃገራችንመኖር አልቻልንም
ከፍ ሲል እንደተናገርኩት በተለይም ያለፉት አምስት አመታት የመርዶና የሃዘን አመታት ናቸው። አማሮች በሃገራቸው መኖር አልቻሉም። መፈናቀልና ሞት፣ ዝርፊያና እንግልቱ ለከት የለውም። ይህ ጥቃት በኢትዮጵያ ውስጥ በሌሎች ብሄሮች ላይም አልፎ አልፎ የሚታይ ቢሆንም ማንነት ተኮር በሆነ መፈናቀል፣ ስደትና ሞት የአማራን ያህል የተጎዳ የለም። ስለዚህ አንዱ የአማራ ትግል የብሄርተኝነት ትግል ሳይሆን አማሮች፣ ብሎም መላው ኢትዮጵያውያን በመረጡት የሃገሪቱ ክፍል ጎጆ ቀልሰው መኖር የሚችሉበትን ስርዓት ለመፍጠር የሚደረግ ትግል ነው። አንዱ የአማራ ፋኖነት ትግል መነሻ ይሄ ነው። አማሮች በሃሰተኛ ትርክት የጥላቻ ሰለባ እንዲሆኑ ተደርጎ እጅግ ብዙ አማሮች ለጥቃት ሰለባ ከመሆናቸውም በላይ በነሱ ላይ የሚፈጸመው ይህ ወንጀል አሁን ድረስ ቀጣይ ነውና አማሮች ለህልውና ትግል ትጥቅ ትግልን ያስመረጣቸውና ጠመንጃ ያስነሳቸው አንዱና ዋናው ጉዳይ ይሄ ነው። በሃገራችን ሰላም አጣን፣ መኖር አልቻልንም የሚል የህልውና ጥያቄ ነው የአማራን ገበሬ ቤልጅጉንና ምንሽሩን መውዜሩን እንዲያነሳ ያደረገው።
- ብልጽግናንያዘልኩበት ማንገቻ ተበጥሷል
የመልካም አስተዳደር ችግር የመላው ኢትዮጵያውያን ችግር እንደሆነ አማሮች በሚገባ ይረዳሉ። አማሮች የወገኖቻቸው ብሶት ሁሉ ብሶታቸው ነው። ከዚህ በፊት በህወሃት ጊዜ የመንግስት ወታደር ኦሮሞ ወገኖቻችን ሲገደሉ የጎንደር ህዝብ የኦሮሞ ደም ደሜ ነው በማለት የወገኑ ጥቃት የእርሱን ጥቃት እንደሆነ አሳይቷል። ዛሬም ነገርም ቢሆን ይህ የአማራ ህዝብ አቋም አንድ ነው።
አማሮች በአንድ በኩል በተዋረድ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር ለጋራ ትህል ወደ ጎን እጆቹን እየዘረጋ በሌላ በኩል በክልሉ ውስጥ ያለውን ደካማ አስተዳደር ለመለወጥ ይታገላል። እንደሚታወቀው ህወሃት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ጉዳይ አስፈጻሚዎቹን በየደረጃው ሾሞ ይህ ህዝብ በመልካም አስተዳደር እጦት፣ በድህነት ሲገረፍ ቆይቷል። ህወሃት/ ኢህአዴግ የህዝብ ትግል ሲበረታበት ጊዜ አሁን ተለውጫለሁ፣ ሪፎርም አደርጋለሁ በማለት እነ አብይ አህመድን አምጥቶ ብልጽግና የተባለ የዳቦ ስም አውጥቶ ተከሰተ። ይሁን እንጂ ይህ ስሙን እየቀያየረ የሚመጣው ብአዴን በበደል ላይ ሌላ በደልን ከመጨመር ባለፈ በአማሮች ላይም ሆነ በሃገሪቱ ላይ ምንም አይነት ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም። አማሮች ለረጅም ጊዜ ጀርባቸው እስኪላጥ አዝለውት የቆዩት ብአዴን የሚባል ድርጅት የዚያ ህዝብ መከራ ሆኖ ቆየ። ሰርቶ የማያሰራ፣ የገበሬውን ችግር የማይፈታ፣ ፍትህ ርቱዕ ለማውረድ አቅም የሌለው ከመሆኑም ባሻገር በሙስና የተዘፈቀ፣ የዴሞክራሲ ጸር የሆነ ፓርቲ ነው። የአማሮች ጥቃት ጥቃቱ ያልሆነ፣ ከአማሮች አብራክ ያልወጣ ፓርቲ ነው። ስለሆነም የአማራ ህዝብ አንዱ ትግል ይህንን አስተዳደር ማፍረስና አዲስ የሽግግር ምዕራፍ መክፈት ነው። ይህ ፓርቲ በምርጫ እያጭበረበረ ከህዝብ ትከሻ የማይነሳ ስለሆነ በህዝባዊ ክንድ ይወገድ ዘንድ ስለሚገባው አማሮች የሚመጥናቸውን አስተዳደር ለመዘርጋት በአጭር ታጥቀው የሚታገሉበት አንዱ አጀንዳ ይሄ ነው።
- “አዲስ አበባ የእኔ ብቻ ናት” የሚለው ትርክትና“አማሮች ወደ አዲስ አበባ አትገቡም” የሚለው ተደጋጋሚ ክልከላ እንዲሁም ከአዲስ አበባ አካባቢ የሚፈናቀለው አማራ ጉዳይ
አዲስ አበባ የሁላችን የጋራ ቤታችን ናት ። አማሮች ይህቺን ከተማ እዚህ ለማድረስ ሰፊ አስተዋጾ አድርገዋል። ይሁን እንጂ በዚህ አስተዋጾዎቻቸው ልክ ልዩ ጥቅም አይጠይቁም። ተገቢም አይደለም። አማሮች አዲስ አበባ የሁላችን ናት ብለው ያምናሉ። ታዲያ ይህቺ የጋራ ቤታችን የሆነች ከተማ ዛሬ ዛሬ በተለይ ወቅት እየጠበቁ አማሮች ወደ አዲስ አበባ አትገቡም እየተባሉ ነው። በዚህ ሳቢያ መጉላላትና ወደመጡበት መመለስ ተደጋጋሚ ክስተት መሆኑን መቼስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ታዝቧል። ይሄ ጉዳይ ታዲያ በአማሮች ዘንድ በቀላል አልታዬም። የብዙ አማሮችን ስነ ልቡና የጎዳ፣ ስሜታቸውን የጎዳ ጉዳይ ነው። የቡድን ኩራታቸውን (collective pride) የነካ ክብረ ነክ ተግባር አድርገው አይተውታል። አማሮች ላይ ያነጣጠረው ይህ እቀባ በተወሰኑ ጽንፈኞች የሚደረግ ደባ ሳይሆን ከፍተኛ መዋቅራዊ ይዘቶች እንዳሉት አማሮች በሚገባ አጥንተዋል። ስለዚህም ይህ ግፍ ይቀጥል ዘንድ አማሮቹ አይፈቅዱም። እኩልነት እንዲመጣ ይህንን አሳፋሪ ድርጊት የሚፈጽሙ ሃይሎችን በህግ ፊት አቅርቦ ለማስተንፈስ ዛሬ አማሮች ታጥቀው የሚታገሉለት አንዱ ጉዳይ ይሄ ነው። አዲስ አበባ የእኔ ብቻ ናት የሚለው ሃይል ከዚህ ድርጊቱ ተቆጥቦ አዲስ አበባ የሁላችን ትሆን ዘንድ አማሮች የበኩላቸውን ለመታገል ወስነው ለትግል ሜዳ ወጥተዋል። አክራሪው የአብይ አህመድ መንግስት በአዲስ አበባ ዙሪያ ሌላ ከተማ ልገነባ ነው በሚል ሰበብ በተለይ አማሮች ላይ ያነጣጠረ ማፈናቀል ታይቷል። ይህ ሊቀጥል አይችልም። ስለዚህ አማሮች ተደራጅተው ታጥቀው እየታገሉ ነው። አዲስ አበባ የሁላችን ከተማ መሆኗን ለማረጋገጥ ትግላችን ይቀጥላል።
- ትጥቅአንፈታም
አማሮች ትጥቅ ባህላቸው ነው። ለለቅሶ፣ ለሰርግ፣ ለባህላዊ ክንዋኔዎች ሁሉ መሳሪያ አንግቶ መሄድ ባህል ነው። ይህ ህዝብ የታጠቀ በመሆኑ ለሃገር ስጋት ሆኖ አያውቅም። ከሁሉም በላይ መንግስት በዛሬው ጊዜ ጸጥታ ማስከበር ተስኖት ባለበት በዚህ ወቅት ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም በማይገቡበት ምድር ውስጥ ገበሬው ራሱን እንዳይከላከልበት ትጥቅ አውርድ መባሉ በአማሮች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። ከሁሉም በላይ የአማራን ፋኖ ለመበተንና ማንነት ተኮር ጥቃት ለሚዘንብበት ለዚህ ህዝብ መከታ እንዳይኖረው የሚደረገውን ሴራ አማራ ሁሉ በንቃት አይቶታል። ስለሆነም አማሮች ትጥቅ አንፈታም ብለው ለትግል የወጡት አንድም በዚህ ምክንያት መሆኑ ይታወቃል።
- የአብይአህመድ ሽግግር ክሽፈት
አማሮች ሃገራችን ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንድትገባና በልማት፣ በቴክኖሎጂ እንድትራመድ ከሌሎች ወገኖቻቸው ጋር ታግለዋል። ባለፉት በህወሃት ኢህዓዴግ ዘመናት ሀገራችን በዘር ፖለቲካ ውስጥ ገብታ ስትታመስ አማሮች አምርረው ታግለዋል። ሃገራችን ሃቀኛ ሽግግር ታይ ዘንድ ከኦሮሞ ቄሮ ወንድሞች ጋር በመተባበር ፋኖ ታግሏል። ኢህዓዴግ በህዝብ ትግል ከተፈረከሰ በኋላ ከውስጤ የለውጥ ሃይል አምጥቻለሁ፣ ሪፎርም አደርጋለሁ ብሎ አብይ አህመድን ሊቀመንበር አድርጎ ሲቀጥል የአማራ ህዝብ ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ደምና አጥንት ሳይቆጥር ደግፏል። ይሁን እንጂ የአብይ አህመድ መንግስት ሃገሪቱ የምትጠብቀውን መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ቀርቶበት ዛሬ ስለ ሃገራችን ህልውና ከፍተኛ ስጋት ላይ እስክንወድቅ ድረስ ቁልቁል ወስዶናል። በኢትዮጵያውያን ዘንድ የነበረው የወንድማማችነት ስሜት በዚህ ሰው አስተዳደር ተሸርሽሯል። አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ መፈናቀልና ግጭት ያልሰማንባቸው ሳምንታት ከቶ የትኞቹ ናቸው? በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሰምተነው የማናውቀው ጭካኔና ወሮበላነት የሚታይበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። በኢኮኖሚው መስክ የዋጋ ግሽበቱ የማይለበልበው ኢትዮጵያዊ የለም። በትምህርት ቁልቁል፣ በዴሞክራሲ ቁልቁል ነው የሄድነው። አማሮች ብዙ የህይወት ጎናቸው ተጎድቶ ችለው እየኖሩ ሳለ የሃይማኖት አጸዶቻቸውን ሳይቀር ይህ መንግስት በአንድም በሌላም መንገድ ሰርጎ እየገባ ጎድቶባቸዋል። የኦርቶዶክስ ሲኖዶስ ችግር፣ የመጂሊሱ ችግር ሁሉ ፖለቲካዊ እንደሆነ አማሮች አጥንተውታል። የአብይ አህመድ አስተዳደር ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በስጋም፣ በነፍስም፣ በመንፈስም ያማረረበት
የጨለማ ዘመን እንደሆነ አይተዋል አማሮች። ይህ የአብይ አህመድ መንግስት ወንድም በሆነው በኦሮሞ ህዝብ ስም ሊነግድ እንድሚሞክር አውቋል አማራ። የኦሮሞ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለከፋ ረሃብና ቸነፈር እንደተዳረገ አማሮች ተረድተዋል። በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረውን ችግር ፖለቲካዊ በሆነ መንገድ መፍታት ሲገባ የከፋ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ገብተን ቁጥራቸው አያሌ የሆኑ የትግራይ ወገኖች አልቀዋል። አብይ አህመድ ፖለቲካዊ መግባባት ማምጣት ባለመቻሉ የሀገራችን ፖለቲካ ክፍፍል በጣም ሰፍቶ ይታያል። ዘረፋና ሙስና ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍቷል። ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ህዝብ ተፈናቅሎ ይገኛል። በዚህም የአለም አንደኛ ሆነናል። ድንበራችን ተደፍሮ አይተንም ሰምተንም የማናውቅ ህዝቦች ዛሬ የሃገራችን ድንበር ክፍቱን ነው። በቀረጥ ያቋቋምነው መከላከያ ሰራዊት በአንዳንድ ጥቅመኛ ጀነራሎች አማካኝነት የአብይ አህመድ ጠባቂ ሆኗል። ሃገራችን በታሪኳ አይታው የማታውቀው ችግር ውስጥ ገብታለች ። የውጪ ኢንቨስተርስ መጥተው ሃገራችን ወደ እድገት እንዳትራመድ መንግስት የተረጋጋ ሃገር መፍጠር ባለመቻሉ ኢንቨስተርስ ድርጅቶቻቸውን እየዘጉ እየወጡ ነው። አዲስ የሚመጡትም ኢትዮጵያን እንደ ስጋት እያዩ ነው። ይህ ሁሉ የሚያሳየው የሃገራችን የለውጥ ሽግግር መክሸፉን ነው። አብይ አህመድና ግብረ አበሮቹ ይህንን የሽግግር ምዕራፍ አክሽፈዋል።
ታዲያ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጣችን ከሸፈ ማለት የሃገራችን የሽግግር ተስፋ ከሸፈ ማለት አይደለም። እየወደቅን ተነስተን እኛ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እውን እናደርጋለን። በመሆኑም ፋኖ የእኔ የትግሌ መነሻው አማራ መዳረሻዬ ኢትዮጵያ ናት ሲል በክልሉ ያሉ አካባቢያዊ የአስተዳደር ሰንኮፎቼን አጽድቼ ደግሞ ለጋራው ቤታችን ለሽግግራችን የሚገባኝን ትግል አደርጋለሁ ማለቱ ነው። መዳረሻዬ ኢትዮጵያ ናት ሲል ኢትዮጵያ ሃገራችን ሃቀኛ ሽግግር እንድታይ የበኩሌን ትግል አደርጋለሁ ማለቱ ነው።
ውድ ወገኖቼ
እነዚህ ከፍ ሲል ያነሳኋቸው ጉዳዮች የአማሮች መራራ ጥያቄዎችና የሚታገሉላቸው ጉዳዮች ናቸው። ከፍ ሲል እንደገለጽኩት የአማራ ትግል መዳረሻው ኢትዮጵያ ናት ። ኢትዮጵያ ደግሞ የአማሮች ብቻ አይደለችም። የሁላችን እናት ናት። ኢትዮጵያ የጋሞዎች፣ የጉራጌዎች፣ የአኙዋኮች፣
የአፋሮች፣ የኮንሶዎች የሁላችን ቤት ናት ። ይህቺ ዋናዋ ቤታችን ኢትዮጵያ በጎ ስትሆን አማሮች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጎነትን ያያል። ዋናው ቤታችን ካዘመመና የረጋ ሃገረ መንግስት ካላቆምን በተናጠል የተሻለ ህይወት የምናይበት ሁኔታ የለም። ታላቁ መጽሃፍ “ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ መልኩን ይቀይር ዘንድ ይቻለዋልን?” ይላል። እውነት ነው የኢትዮጵያ መልክ ዥንጉርጉር ነው። የተለያዬ ባህል፣ የተለያዬ ቋንቋ፣ የተለያዬ ሃይማኖት ባለቤት ናት ሀገራችን። ይህ የኢትዮጵያ መልክ ሲሆን ውበቷም ነው። ይህንን መልክ ሊቀይር የሚችል ሃይል የለም። ስለሆነም ማንኛውም በዚህች ምድር ውስጥ የሚካሄድ ፖለቲካና የመንግስት ቅርጽ ይህንን የሃገሪቱን ብዝሃነት ያገናዘበ መሆን እንዳለበት የአማሮች ዋና ትግል ነው። አንዳንዶች የፋኖ ትግል አንድ ሃይማኖት አንድ ባህል ለመጫን ነው ይላሉ። ይሄ ትክክል አይደለም። በመሰረቱ አማራ ራሱ ብዝሃ ነው። አማራ በሃይማኖት ብዝሃ ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን ዘርን የፖለቲካ መጫወቻ ሳናደርገው የግለሰብና የቡድን መብት የተከበረበትን ስርዓተ መንግስት መቅረጽ እንችላለን። ብሄራዊ ወይም ኢትዮጵያዊ ማንነታችንና ሌሎች ማንነቶቻችን እርስ በርስ ሳይጋጩ የምንኖርበትን ስርዓት መገንባት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የህልውናችን ትግል ነው። ፋኖ በዚህ ረገድ የሃገራችን ሽግግር ምን መምስል አለበት? በሚለው ላይ ጥናቶችን አጥንቷል። ይህ ጥናት ከሁሉም ወገኖቻችን ጋር ተመክሮበት የሽግግራችን ሮድ ማፕ ሆኖ ያገለግላል። ሃገራችን የቡድንና የግለሰብን መብቶች አቻችላ የምትኖርበትን አማራጭ ቅርጸ መንግስት ለውይይት ተዘጋጅቷል። ፋኖ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር ሆኖ ሃገራዊ ሽግግር ሲተከል የሽግግሩ ኮንቬንሽን ምን መምሰል እንዳለበት የፋኖ የፖለቲካ ዘርፍ ዶክመንቶችን አዘጋጅቷል። በወቅቱና በጊዜው ለውይይት ይቀርባል። በዚህ ወቅት ኢትዮጵያውያን በተናጠል ሳይሆን በጋራ ተደራድረን የተሻለ ሽግግር የምናመጣበት ሁኔታ ይፈጠር ዘንድ ሁላችንም መታገል አለብን።
ውድ ወገኖቼ
ፋኖ በአማራ ክልል ውስጥ እስካሁን ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረገ ሲሆን ይህ ጦርነት በምንም መልኩ ረጅም ጊዜ ሊቆይ አይገባም። በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ኢትዮጵያ ሃገራችን የተውጣጣ የሽግግር መንግስት አቋቁማ መዋቅራዊ ለውጦችን ማምጣት አለባት። የአማራንም ሆነ አጠቃላይ የኢትዮጵያውያንን አበሳ ለማሳጠር የአማሮች ትግል ክልሉን ተሻግሮ ሌሎች ወገኖቹን አቅፎ ወደ ፊት የሚገፋበት ምዕራፍ ላይ ደርሰናል። ጦርነቱ አንድ አካባቢ ብቻ የሚቆይ ከሆነ ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራዎቹ አያሌ ከመሆናቸውም በላይ በሚፈለገው ፍጥነት ትግሉ አይራመድም። ስለዚህ መላው ኢትዮጵያውያን ፋኖነትን እንዲደግፉ ጥሪ እናደርጋለን። ፋኖነት ኢትዮጵያዊ አርበኝነት ነው። በአድዋ ጦርነት ላይ የተሳተፉ ኦሮሞዎች፣ ወላይታዎች፣ ጉራጌዎች፣ ወዘተ ፋኖዎች ነበሩ። ስለዚህ መላው ኢትዮጵያውያን የፋኖን ንቅናቄ በመደገፍ ትግሎቻችንን ወደፊት እናራምድ።
ኢትዮጵያውያን ሁላችን ተባብረን ይህንን ስርዓት መለወጥ ግዴታችን ሆኗል። አሁን የኢትዮጵያውያን ትግል ትግል የህልውና ትግል ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሄሮች እንደ ብሄር፣ ኢትዮጵያም እንደ ሃገር ከመቼውም ጊዜ በላይ የህልውና አደጋ ላይ ናቸው። ከዘር ፖለቲካ የተነሳ የእርስ በርስ ግጭት የሞት ጥላ በሃገራችን ላይ አጥልቷል። ከሰላም እጦት የተነሳና ከልማት መስተጓጎል የተነሳ የረሃብና የችጋር ጥላ በሃገራችን ላይ አጥልቷል። ስለዚህ ኢትዮጵያውያን በዚህ ጊዜ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ወላይታ፣ ሲዳማ ወዘተ ብለን ሳንከፋፍል ሁላችንም ተባብረን የተሻለ የሽግግር ስርዓት ለመፍጠር የህልውና ትግል የምናደርግበት ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል። ስለዚህ ፋኖ ዛሬ የትብብር ጥያቄን ለመላው ኢትዮጵያውያን ያቀርባል። ፋኖ የሚታገለው በኢትዮጵያ ውስጥ ብዝሃነት እንዲከበር፣ እኩልነት እንዲሰፍን ነውና ኑና በሃገራችን ውስጥ ዴሞክራሲያዊና ሁሉን አቀፍ ሽግግር ለምማምጣት በአጭር ታጥቀን እንታገል። live free or die! እንደተባለው ለነጻነታችን የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ከፍለን የኢትዮጵያን ሽግግር እውን እናድርግ። ኑ እና ብዝሃነትን ያከበረች የተባበረች ኢትዮጵያን እንደገና እንገንባ!
መነሻችን የአማራ ህልውና መድረሻችን የኢትዮጵያ አንድነት !
አመሰግናለሁ
https://amharic-zehabesha.com/archives/187465
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment