Tuesday, November 21, 2023
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ዛምበራ አፉን እንደተቆጣ አንበሳ በከፈተው የዓባይ ሸለቆ እንደ ምላስ የተዘረጋ ቆላማ ሥፍራ ነው፡፡ ዛምበራ ሽፍቶች በልጅግ፣ ምኒሽር፣ ዲሞትፌር፣ ራስማስር፣ ጓንዴና እናት አልቢን እያቀማጠሉ እንደ አንበሳ የሚጎማለሉበት አገር ነው፡፡ ዛምበራን ከሸበል፣ ከጉባያና ከደራ አፋፍ ቁልቁል ሲያዩት ሜዳ ከሱሃና ከአባይ ሽቅብ ሲመለከቱት ግን ተራራ ይመስላል፡፡ ዛምበራን የከደነው ሰማይ አድማሱን ከሸበል፣ ከየጉባያ፣ ከደራ፣ ከደጀንና ከጎሐጽዮን ዳገት ስለዘረጋ ከዛምብራ ወጥቶ ለማያውቅ የዓለም መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ የዓባይ ሸለቆ ይመስለዋል፡፡ የዛምበራን ሰማይ እንደ ግርግዳ ቀጥ አርገው የያዙት የዓባይ ጋራዎች ከጫካውና ከገመገሙ ተዳብለው ዛምበራን ግርማና ሞገስ እንደ ብልኮ አልብሰውታል፡፡ ግርማና ሞገስን የለበሰው ዛምበራ እንደ ጦቦያ ገዳማት የሚያስፈራ ክብርን ተጎናጽፏል፡፡ አስፈሪ ክብር የተጎናጸፈው ዛምበራ ያምስቱን ዘመን ፋኖዎችና ኢፍትሐዊነትን የታገሉ የሸበል፣ የበረንታ፣ የጉባያ፣ የጫቃታና የደራ ሽፍቶች በክብር ሲያስተናግድ ኖሯዋል፡፡
ለጀግኖች ምሽግና ለባህታውያን መጠለያ ጉድጓድ የሚቆፍሩት ቀበሮዎች የዛምበራን ታሪካዊነት ግምት ውስጥ በማስገባትና አለክላኪው ውሻም እንደ ዛምበራ ካለ ቆላ ሊያጠቃቸው እንደማይችል በመገንዘብ አመታዊ ስብሰባቸውን በዛምበራ ለማድረግ ከሞያሌ እስከ ቀይ ባህር፣ ከኦጋዴን እስከ አሶሳ፣ ከሁመራ እስከ ባሌ፣ ከአሰብ እስከ ጋምቤላ ተጠራርተው የበጋው ሙቀት የሚያከትምበትንና ወንዞች የማይሞሉበትን ወራት መርጠው ግንቦት አስራ አምስት ቀን ሁለት ሺህ ሰባት ዓመተ ምህረት ከተው ገብተዋል፡፡
የሁለት ሺ ሰባቱ ስብሰባ ያተኮረው በውሻና ውሻን መሳይ ሰዎች በሚፈጽሙት የቀበሮን ዘር የማጥፋት ዘመቻ ላይ ነበር፡፡ የቀበሮን ዘር ለማጥፋት ስለሚፈጸመው ዘመቻ ትምህርት ከሰጡት አያሌ የቀበሮ ምሁራን፣ የሃይማኖት መሪዎችና የጦር መኮንኖች መካከል የተከበሩ መጋቢ ብሉይ ዓይነኩሉና ክቡር ጄኔራል መከተ ደመላሽ ይገኙበታል፡፡ እንደሌሎች የስብሰባ ቀኖች ሁሉ ትምህርቱ ከመጀመሩ በፊት በውሾች የሰላ ጥርስ በመዘንቸር፣ በውሻ መሳይ ሰዎች በተተኮሰ ባሩድ በመቆላት፣ በእስር በመንገላታት፣ የሚያመክን መድኃኒት በመዋጥ፣ በቅያቸው በመፈናቀል፣ ለስደት በመዳረግ፣ ለርሃብ በመጋለጥና በበሽታ በመነደፍ ላለቁት ቀበሮች የሚደረገውን የመክፈቻ ጸሎት ለመምራት ቄስ ወልደ አማኑኤልና ሼህ ሙዴሲር ወደ መንበሩ ወጡ፡፡ እነዚህ የሃይማኖት አባቶችም "ይህንን የተባረከ ስብሰባ በጸሎት መክፈት የነበረባቸው የቀበሮ ሲኖድና መጅሊስ አባላት ነበሩ፡፡ ዳሩ ግን ለጊዜያዊ ምድራዊ ቅንጦት ሳስተው ዘላለማዊውን እግዚአብሔርን፣ እውነትን፣ ፍትህንና ሰፊውን ቀበሮ ከድተው ከውሾችና ውሻ መሳይ ሰዎች ጋር ተሰልፈዋል፡፡ ይህንን ክህደት አጢነው የሚፈርዱ አምላክና ታሪክ ስላሉ ፍርዱን ለነሱ እንተዋለን!" ብለው ስብሰባውን በጸሎት ከከፈቱ በኋላ መንበሩን ለመጋቢ ብሉይ ለቀቁ፡፡
መጋቢ ብሉይ ከአንገት እስከ እግር አንጓቸው የሚሸፍን ከጥቁር ለምድ የተሰራ በርኖስ ለብሰዋል፡፡ በትምህርት ያሳለፉትን ዘመንና የእውቀታቸውን ጥልቀት የሚያመለክት ሻሽ አውሎ ነፋስ አስመስለው ጠምጥመዋል፡፡ መጋቢ ብሉይ ማእረጋቸውን ያገኙት በካድሬ ደፍተራነት እንዲያገለግሉ ከካንቦ ተመልምለው ከድንጋይ ማምረቻው መንፈሳዊ ኮሌጅ ሰልጥነው አይደለም፡፡ መጋቢ ብሉይ ዓይነኩሉ የመጋቢ ብሉይ ማእረግ የተሰጣቸው ለማእረጋቸው የሚመጥን እውቀት ያካበቱና ሃይማኖታዊ ሥርዓትንም የጠበቁ አባት ስለሆኑ ነው፡፡ መጋቢ ብሉይ ቅኔ እንደ ዶፍ ከሚወርድባቸው ዋሸራ፣ ዲማ፣ ደብረ ወርቅ፣ ጎንጅ፣ የገወራ፣ ዋድላና ድለንታ፤ ዜማ እንደ አባይ ወንዝ ከሚፈስባቸው የጎንደር አድባራት የሃይማኖት ትምህርትና ፍልስፍናን ቀስመዋል፡፡ አእምሯቸውን በቅኔና በዜማ አስልተው የብራና መጻሕፍት ፈትሸዋል፡፡ ደብረሊባኖስ ገዳም ዘልቀውም እንደ ቀሲስ አስተርአየ አንድምታውንና መጽሔፈ ትርጓሜውን እንደ ሸንኮራ አገዳ እምሽክ አርገው በልተዋል፤ በብሉይ ኪዳንም ምርምር አድርገዋል፡፡ መጋቢ ብሉይ በመስቀላቸው ሶስት ጊዜ አማትበው "ምንትስ ምንትስ" ብለው በግዕዝ ተናገሩና መልሰው ባማርኛ "በመልካም እንዳስጀመረ በመልካም ያስጨርሰን፤ ያዝ ተሚል ሆዳም ሰውና ያዝ ሲሉት ተሚናከስ ውሻ ይጠብቀን" ብለው ማስተማሩን ጀመሩ፡፡
"የጀመርያው ፊደል ማን ይባላል?" ብለው ጠየቁ "ሀ" አለ ተሳታፊው፡፡ "የመጨረሻውስ?" ብለው ሲጠይቁ "ዜድ" አለ አንድ ከቱሪስት በርገር ሲቀበል የኖረ የባሌ ቀበሮ፡፡ "ምርቱን ተግርድ አትቀላቅል" ብለው መጋቢ ብሉይ እንደ ማንኛውም ካህን በኃይለ-ቃል ሲገስጹ ተሰብሳቢው "የእኛ ካህኖች ነገር!" አለና አፉን ይዞ መሳቅ ጀመረ፡፡ "ፐ" አለች አንድ የት እንደተቀመጠች የማትታወቅ ቀበሮ፡፡ "አዎ ፐ! የመጀመሪያውን ሳያውቁ የመጨረሻውን ማወቅ ይቻላል?" ብለው ሲጠይቁ ጥቂቱ "አይቻልም!" ሲል አብዛኛው ለምን ይህንን እንደጠየቁ ስላልገባው ማጉረምረም ጀመረ፡፡ "መሰላል ሲወጡ የመጀመሪያውን አግዳሚ ዘለው የመጨረሻውን ሊረግጡ ቢቃጡ ምን ይከተላል?" ብለው ሲጠይቁ "መንጠር!" አለ ተሳታፊው በአንድ ድምጥ፡፡ "እርግጥ ነው የመጀመሪያውን አግዳሚ ሳይረግጥ ተመጨረሻው ሊንጠለጠል እሚሞክር እንደሚነጥረው፣ ራሱን ሳያውቅ ሌላውን ለማወቅ እሚከጅልም እንደ ኳስ ነጥሮ ይንከባለላል፡፡ ስለዚህ ኦሜጋን ተማወቅ በፊት አልፋን፣ ሌላውን ተማወቅ በፊት ራስን ማወቅ ይበጃል!" እያሉ ሲያስተምሩ ብዙው ሚስጢሩ ስላልገባው ላጨበጨቡበት ቤትና ደመወዝ እንደሚሰጣቸው "የጦቢያ እንደራሴዎች" ማንቀላፋት ጀመረ፡፡
"ተገዳማትና ተዋሻዎች የመጣጭሁ እስቲ ይህንን መልሱ! የቅዱሱ መጽሐፍ አልፋ ምን ይባላል?" ብለው ሲጠይቁ እንደ አባ መላኩ ከመማር መጠምጠምን ያስቀደመ ጠብደል የቀበሮ ካህን ከመጽሐፈ-ንዋይ!" አለ "አንተ ተዚያ...ማነው አምጡልኝ.. ጳውሎስና ያኛው በቅርቡ አምጥተው ያለሙያው የጎለቱት ጉልቻ ደሞ ማነው ማ... ማትያስ አህያውንም መጋዣውንም ተከተቱበት ሲኖድ እንጅ ተገዳም የመጣህ አይመስለኝም!" ሲሉ ሆድ ያባውን ብቅል ያዋጣዋል እንደሚባለው ተሳታፊው ሁሉ የታዘበው ጉዳይ ስለነበር "መጽሐፈ-ንዋይ ካሉት ቀበሮ በቀር ሁሉም መፋቂያ ያልነካውን ጥርሱን እያሳዬ ተንተከተከ፡፡ ሳቁ በረድ ሲል "የኔታ ቅዱሱ መጽሐፍ ተዘፍጥረት ይጀምራል!" አለ አንድ ፊቱ በፆምና በጸሎት የተሰረጎደ የላሊበላ ቀበሮ፡፡"ትክክል የመጽሐፍ ቅዱስም የዓለምም አልፋ ዘፍጥረት ነው" ሲሉ አረጋገጡ መጋቢ ብሉይ፡፡ መጋቢ ብሉይ በሶቅራጥስ የማስተማር ዘዴ የሰለጠኑ ይመስል በጥያቄ መልክ ማስተማራቸውን ቀጠሉ፡፡ "በመጀመሪያውና በሁለተኛው ቀን ምን ተፈጠረ?" ብለው ሲጠይቁ " ሰማይና ምድር፣ ብርሃንና ጨለማ " አለ ተሳታፊው፡፡ "በሶስተኛው ቀንስ?" " አትክልት" "በአራተኛው ቀንስ? "ከዋክብት" "በአምስተኛው ቀንስ? "ወፎችና ሌሎችም ፍጥረታት፡፡" አለ ተሳታፊው፡፡ "በስድተኛው ቀንስ?" ብለው ሲጠይቁ "በስድስተኛው ቀን መናጢው ሰው ተፈጠረ!" ብሎ ተሳታፊው ሲመልስ "የእንሽርት ውኃ ሆኖ በቀረ ኖሮ!" ስትል ጮኸች ሁለት ልጆቿን ሰው ያዝ ብሎ በውሻ ያስበላባት ቀበሮ፡፡
"እንግዲህ ቀበሮ የተፈጠረው በስንተኛው ቀን መሆኑ ነው?" ብለው መጋቢ ብሉይ ከፊት ከተቀመጡት አንዱን ሲጠይቁ አእምሮው እንደ ዘመኑ ወመኔና ከሀዲ ገዥዎች አንጎል የሐሳብ -ሰንሰለት (ሎጅክ) እማይቀበል ስለነበር "በስድስተኛው ቀን" ሲል መለሰ፡፡ "በስድስተኛው ቀን መፈጠርህን በሁለት እግርህ ቆመህ ሁለት እጆችና አስር ጣቶችህን አሳዬና!" ብለው መጋቢ ብሉይ ተሳለቁበት፡፡ "ቀበሮ በአምስተኛው ቀን ተፈጠረ!" ሲሉ መለሱ ብዙ ቀበሮዎች ባንድነት፡፡ "አዎን እኛ ቀበሮዎች የተፈጠርነው በአምስተኛው ቀን ነው፡፡ እሚያሳዝነው አለክላኪው ውሻም የተፈጠረው በዚሁ ቀን ነው" አሉና መሬቱን እያዩ በመተከዝ "እንግዲህ ባፈጣጠር ተሰውና ተቀበሮ ማን ይቀድማል?" ሲሉ ጠየቁ፡፡ "ቀበሮ" አለ ተሳታፊው፡፡ "በዚች ምድር ቀድሞ የታዬው ቀበሮ ወይስ ሰው? "ቀበሮ" ብሎ አብዛኛው ተሰብሳቢ ሲመልስ በቱሪስቶች ሲጎበኝ የኖረ የሰሜን ቀበሮ "ተመራማሪዎች ቀበሮም ሰውም ባዝጋሚ ለውጥ ከትላትል ተፈጠሩ ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡" ሲል አስተያየት ሰጠ፡፡ "እና አንተም የትል ልጅ እንደሆንክ ታምናለህ ማለት ነው? እስቲ ትሉን አንተን አርግና አሳዬን! አያችሁ! ራሱን ሳያውቅ ሌላውን ለማወቅ እሚሻ መጨረሻው ውድቀት ነው ያልነው ለዚህ ነው! የራስን ብራና ሳይገልጡ የሌሎቹን ወረቀት ማነብነብ መጨረሻው ውድቀት ነው! ለማንኛውም እኛ በምናምንበት በፈጣኑም ሆነ ሌሎች በሚያምኑበት አዝጋሚ ለውጥ ብታስበው በዚች ምድር ቀበሮ ከሰው በፊት ታይቷል! አራት ነጥብ!፡፡" አሉ መጋቢ ብሉይ ያራት ነጥብ ምልክት አየሩ ላይ እየሳሉ፡፡
"እንግዲህ በፈጣኑም ሆነ በአዝጋሚው መንገድ ሰው ከምድር የደረሰው በመጨረሻ ተሆነ ምድር ለማን ትገባ ነበር? ቀድሞ ወይስ መጨረሻ ለደረሰው?" ብለው ሲጠይቁ ፡፡ "ቀድሞ ለደረሰው" አለ አብዛኛው ቀበሮ፡፡ "አዎን ምድር ቀድሞ ለደረሰ ትገባ ነበር፡፡ ነገር ግን በኋላ የመጣ አይን አወጣ እንደሚባለው ሰው በኋላ መጥቶ እኛንም ሆነ ሌላውን ፍጡር እያጠፋ ምድርን ተቆጣጠረ" እያሉ መጋቢ ብሉይ ሲያስተምሩ አንድ የቀበሮ ካህን ብድግ አለና "ሰው ዓለምን እንዲገዛ ተፈቅዶለታል እኮ" ብሎ ዘሌዋውያን ውስጥ የተጻፈውን እየጠቀሰ ተከራከረ፡፡ "ሰው ዓለምን እንዲገዛ የተፈቀደለት ፈጣሪ ለእውነትና ለፍትህ ይቆማል ብሎ በአምሳሉ በሰራው ጊዜ ነበር፡፡ ሰው ይህንን የተሰጠውን ፀጋ አውልቆ ከሳጥናኤል ጉያ ሲገባ የዓለምን መግዣ ፈቃዱን እንደ ሰካራም መቺና ነጂ ተነጥቋል፡፡ ስለዚህ ሰው እንኳን ዓለምን እንዲገዛ ሊፈቀድለት በጥፋት ውኃና በእሳተ ገሞራ እንዲጠፋ ተደርጓል፡፡ ታጋም የተጠጋ ቁልቋል ሲያለቅስ ይኖራል እንደሚባለውም የጥፋቱ ውኃምና እሳተ ገሞራው ለኛም ደርሷል፡፡" ሲሉ ሌላ የቀበሮ ሊቅ ተከራከሩ፡፡ በክርክሩ የረኩት መጋቢ ብሉይ "ትክክል መልሰሃል!" ብለው ለሁለተኛው ተናጋሪ አጋርነታቸውን ገለጡና "ለመሆኑ ሰው ወደ ምድር እንዴት እንደወረደ እሚያውቅ አለ?" ብለው ሲጠይቁ "ወገቡን ተጠርንፎ በመሰላል!" አለች አንድ የቀበሮ ወይዘሮ እንደ ዘመኑ ቄሶችና መነኩሴዎች መጋቢ ብሉይን ልታሳስት ተውረግራጊ ሽንጧን እያሳየችና እየተሽኮረመመች፡፡ "ጥሩ ጠላ ጠማቂ ሳትሆኝ አትቀሪም፤ እንደ ብቅል በመሰላል ወረደ ማለትሽ ነው?" ብለው ቀለዱና ፈገግ አሉ፡፡ "ጠላዬን ቢቀምሱማ ሥስት ጊዜ አፍርሶ እንደ ቆመሰው ቄስ ታደሰ ሌላም ያምርዎ ነበር" አለች ወይዘሮዋ በልቧ፡፡ "ሰው ወደ ምድር የተላከው ለልማት ነው!" አለ እንደ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በቴክኒክ ምክንያት ተነስቶ መናገር ያቃተው ቀበሮ ባለመነሳቱ ይቅርታ ጠየቀና፡፡ መጋቢ ብሉይም "ምንትስ ምንትስ ብለው ግርማ ወልደ ጊዮርጊስን በሚመስለው ቀበሮ ለተራ ቀበሮ እማይገባ እንደ አዋዜ የታሸ ቅኔ ከተቀኙ በኋላ "ይህ የካድሬዎች ስብሰባ ሳይሆን የምሁራን ስብሰባ መሆኑን አትዘንጉ! ጥርነፋ፣ ልማት ቅብጥሶ ቅብጥሶ የሚሉ የኮር አባል ቃላት እያመጣችሁ ውይይታችንን አታቆርፍዱ" ሲሉ ገሰጹ፡፡
"ጥያቄውን አሁንም እደግመዋለሁ! ሰው ለምን ተገነት ወደ ምድር እንደ ቁልቢጥ ተወረወረ?" ሲሉ ጠየቁ፡፡ "ሰው በእባብ አመካኝቶ ከእግዚአብሔር ሆዱን መርጦ አትብላ የተባለውን ፍሬ ስለበላ በእርግማን እንደ ቁልቢጥ ተወረወረ!" አሉ አንድ ኩርምት ብለው የተቀመጡ ቀበሮ በሰነነ ድምጽ፡፡ መጋቢ ብሉይ "ሆዱን ሳይሆን ጭንቅላቱን ሲመግብ የኖረ እንደዚህ የመጽሐፉን ቃል ይናገራል!" ብለው መላሹን ቀበሮ ሲያደንቁ ተሳታፊው አይኑን ጥያቄውን ከመለሱት ኮስማና ቀበሮ አሳረፈው፡፡ "እኒህ ሊቅ እንዳሉት ሰው ወደ ምድር የተወረወረው በእርግማን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ሰው የተረገመ ፍጡር ነው፡፡ ሌላውን እርኩስ እያለ ይጠራል እንጅ እርኩስ ራሱ ነው፡፡ እርሱ በመረገሙና በመርከሱም ምድር በእሾህና በእንቅፋት ተሞላች፤ በብርድ ተኮማተረች፣ በሐሩርም ነደደች፡፡ ገነት ውስጥ የሰራው ስህተቱ ሳያንሰው ክፋቱን በምድርም ስላበዛው መጀመሪያ በጎርፍ አጠፋው፡፡ የእርሱ ኃጥያት ለእኛም ደርሶ አብረን ጠፋን፡፡ ኖህ በሚባል ብሩክ ሰው ምክንያት ዘራችን ተርፎ እንደገና አቆጠቆጥን፡፡ የሰው ክፋት ግን ከጥፋት ውኃ በኋላም በመቀጠሉ በገሞራና በእሳት አጋዬው፡፡ በገሞራና በእሳት ጋይቶም ስላልተማረ ኑሮን እንዲያስተምር ልጁን የሰው ሥጋ አልብሶ ወደ ምድር ላከው፡፡ አትብላ የተባለውን ፍሬ በልቶ ወደ ምድር የተወረወረው፤ ስካርን፣ ዝሙትን፣ ውሸትን፣ ክህደትን፣ ስግብግብነት በማብዛቱ በጎርፍ የተጠረገው፤ ከዝሙትም አልፎ ግብረ ሰዶም በመፈጠው በገሞራና በእሳት የጋዬው ሰው ይባስ ብሎ የእግዚአብሔርን ልጅ በሐሰት ከሶ፣ በሐሰት መስክሮና በሐሰት ፈርዶ በእሾህ ከጨቀጨቀ በኋላ በምስማር ከርችሞ ሰቅሎ በጦር ወጋው! እንግዲህ ሰውን በአምሳሉ የሰራውን ክርስቶስን አሰቃይቶ የገደለ ሰው ለቀበሮ ያዝናል ተብሎ ይጠበቃል?" "ከጉረሮ እየሞለቀቀ ህጻናትን በርሃብ የሚጨርስ፣ ቀለሙ ያላማረውን ሰው በኮረንንቲ የሚጠብስ፣ በፈላ ውኃ እሚቀቅል ውሻ መሳይ ሰው ውሻን ያዝ እያለ ቀበሮን ከማስፈጀት ይቆጠባል ተብሎ ይጠበቃል? ብለው ሲጠይቁ "አይጠበቅም" አሉ አይኖቻቸው በእንባ የረጠቡ ተሳታፊዎች በጎረነነ ድምጽ፡፡ መጋቢ ብሉይ እየተንጎራደዱ "እንግዲህ መታገል ያለብንን የእርጉሙን ሰው ተፈጥሮ የተገዘባችሁ ይመስለኛል፡፡ የራሱን ሥጋ እየቆረጠ ከመብላት ከማይመለሰው ውሻ መሳይ ሰውና ውሻ ለመዳን ልባዊ ጸሎትንና የመንፈስ ጽናትን ይጠይቃል፡፡ የመንፈስ ጽናቱን ይስጠን፡፡" ብለው ንግግራቸውን ሲጨርሱ እንደ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በቴክኒክ ምክንያት መነሳት ካልቻሉት በስተቀር ሁሉም ቀበሮዎች ከመቀመጫው ተነስተው ከሐዘንና እልህ በመነጨ እንባ ተራጩ፡፡
መጋቢ ብሉይ ማስተማራቸውን እንደጨረሱ ተሰብሳቢዎች ነፋስ ተቀብለውና ከስንቃቸው ተቃምሰው ወደ ስብሰባው ሥፍራ ተመለሱ፡፡ ጀኔራል መከተ ደመላሽ በደረታቸውና በትክሻዎቻቸው ኒሻናቸውን እንደ ግርግዳ ፎቶ ሰድረው እየተጀነኑ ከመድረኩ ሲወጡ ተሰብሳቢው ተነስቶ በተደጋጋሚ "በቃ ተቀመጡ! በቃ! በቃ! ተቀመጡ!" እንስከሚባል ድረስ "ጩዋ..ጩዋ..." እያደረገ ጭብጨባውን አቀለጠው፡፡ ጄኔራል መከተ የቀበሮን ግዛት ለማስከበርና ቀበሮን ለማዳን ብዙ ጀብዱ የሰሩ ሥመጥር ጀኔራል ናቸው፡፡ ጀኔራል መከተ የጀኔራልነት ማእረግ ያገኙት አቶ ኤርሚያስ ፊደል አስቆጥሮ ከአራተኛ ክፍል እንዳስመረቃቸው ተገዳላዮች ያስፈጁትና ያሰቃዩት ሕዝብ ተገምቶ አይደለም፡፡ ጀኔራል መከተ በታወቀ የቀበሮ የጦር አካዳሚ የስድስት ዓመት ትምህርትን በከፍተኛ ማእረግ ያጠናቀቁ፤ በቀበሮ፣ በሰው፣ በውሻ ታሪክና ሥነ-ልቡና በቂ ትምህርት ወስደው ምርምር ያኪያሄዱ፤ በአያሌ የጦር ሜዳዎች የቀበሮ ጠላቶችን ተፋልመው የቀበሮን ግዛት ያስጠበቁ ወታደራዊ መሪ ናቸው፡፡ ጀኔራል መከተ በተለያዬ ጊዜ ቀበሮን ሊያንቁ የመጡ ውሾችን አይኖች በጥፍራቸው አፍሰውና በአቀንጣጤአቸው የደም ሥራቸውን በጥሰው ደማቸውን ያፈሰሱ ታሪክ በብራና የጣፋቸው መኮንን ናቸው፡፡ ጄኔራል መከተ ውሻን አስከትለው ሊያጠቁ የመጡ ሰዎችን ባቀንጣጤ ወግተው ሬቢስ በሚባለው የጀርም መሳሪያ የረፈረፉ ጀግና ናቸው፡፡ በዚህ አስደናቂ ታሪካቸው የተደመመው የስብሰባ ተሳታፊ ጀኔራሉ የሚናገሩትን ለመስማት እንኳን ጆሮውን አፉን፣ አፍንጫውንና አይኑንም ከፍቶ የመርፌ ኮሽታ በሚሰማበት ጸጥታ ጠበቃቸው፡፡
ጀኔራል መከተ እንደ አንበሳ ትክሻቸውን ከምረውና ደረታቸውን እንደ ጋሻ ለጥጠው የቀኝ የፊት እግራቸውን ወደ ቀኙ የራስ ቅላቸው ወስደው ወታደራዊ ሰላምታ ለተሰብሳቢው አቀረቡ፡፡ ጄኔራል እንደ ታምራት በነፍጠኛ ወቢ እማይተፉ እንደ ስዬም ጦርነት ፈጣሪ ብለው እማይደነፉ የበሰሉ ጀግና ናቸው፡፡ በዚህ የበሰለና የሰከነ አንደበታቸውም መጋቢ ብሉይ ያሉትን ጠቅሰው ንግግራቸውን ጀመሩ፡፡ "አባታችን መጋቢ ብሉይ ሥለ ሰው፣ ሥለ እኛና ሌሎችም ፍጡራና አፈጣጠር ሲያስተምሩ መሰላል ሲወጡ የመጀመሪያውን አግዳሚ መርገጥ እንደሚያስፈልግ መክረው ነበር፡፡ የአባታችንን ምክር በመከተል ሌሎች ቦታዎችን ከመርገጣችን በፊት በዚቺ ሰዓት የቆምንባትን ዛምበራን እንቃኛለን፡፡ ከገዥዎች ጋዜጣ ወሬ እየለቀሙ ታሪክ ጻፍን እሚሉ 'ታሪክ ጸሐፊዎች' ችላ ቢሉትም ዛምበራ ታሪካዊ ቦታ ነው፡፡ ለመሆኑ ዛምበራ ለምን ታሪካዊ እንደሆነ እሚያውቅ አለ?" ብለው ሲጠይቁ አንድ ወጠጤ ቀበሮ ዛምበራን ደራ ከሚለው ስም አምታቶ "ሰዎች የሚዳሩበት ቦታ ስለሆነ?" ብሎ ሲመልስ እንኳን ጥርስ ያለው የሌለውም ተሰብሳቢ የተጋጠ ቆረቆንዳ የመሰለ ድዱን እያሳዬ ከዳር እስከ ዳር ሳቀ፡፡ ከዚያም አንድ በመልሱ ያልተደሰቱ ተሰብሳቢ "የነቀዘ ትውልድ! አንተ ያልከውን ለማድረግ የክትፎ መጎስጎሻና የመሸታ መጨለጫ ካሞቦውን ትቶ እዚህ ለምን ይመጣል?" የሚል አስተያዬት ሰጥተው ሳይጨርሱ አንድ ዛምበራ ያደገ ቀበሮ ዛምበራን የመዳሪያ ቦታ ባለው ወጠጤ አይኑን አጉረጥርጦ "ልክስክስ! አንተ እንዳልከው ሳይሆን ዛምበራ የአምስቱ ዘመን ፋኖዎችንና ሽፍቶችን በመጠለል ቅኝ አገዛዝና ኢፍትሐዊትነት ድባቅ ለመምታት በተደረገው የሞት የሽረት ፍልሚያ ትልቅ አስተዋፅዖ ያደረገ የአገር ደጀን ነው" አለ፡፡ "ትክክል የዛምበራ ታሪክ ይህ ጎበዝ እንዳለው ነው! በአምስቱ ዘመን የጎጃም፣ የሸዋ፣ የወሎና የጎንደር ጀግኖች ጣሊያንን ያርበደበዱት በዛንበራ በኩል ያባይን በረሃ እያቋረጡ መረጃ በመቀባበል ነበር፡፡ ጣሊያን ከላይ በመነጥር እያዬ በቦንብ ሲያጋያቸው እሚያመልጡት እንደ ዛምብራ ባሉ የተፈጥሮ ጸጋዎችና የእኛ ቅድመ አያቶች በቆፈሯቸው ጉድጓዶች በመመሸግ ነበር፡፡ ይህም ማለት እኛ ቀበሮዎችም እንደ ዛምበራ ቅኝ አገዛዝንና ኢፍትሐዊነትን ለመታገል ትልቅ አስተዋጽዖ አድርገናል ማለት ነው! አይደለም እንዴ?" እያሉ ጀኔራል የጀግንነት ታሪክ ሲያስተምሩ ተሳታፊው "ትክክል!" እያለ ጭብጨባውን አቀለጠው፡፡
የጋለው ጭብጨባ እየቀነሰ ሄዶ ሲቆምም "እርግጥ ነው እኛ ከጀግና ሰዎች የትግል አጋሮች ነን፡፡ ለፋኖዎችና ለሽፍቶች እንደዚሁም ለባህታውያን ጉድጓዶቻችን ለምሽግነትና ለመጠለያ ስናበርክት ኖረናል፡፡ ሽፍቶችም ስለቀበሮ ጉድጓድ አንጎራጉረዋል፡፡ ከጀግና ሰዎች ጋር የነበረን የትግል አጋርነት እስራኤላዊያንን ከፈርኦን መንጋጋ ካላቀቀው ሙሴና ኢትዮጵያን ከጣሊያን ወረራ ካዳኗት ያምስቱ ዘመን ተናዳፊ ጀግኖች ጋር ባሳዬነው ትብብር ተረጋግጧል፡፡" ሲሉ "ትክክለኛ ታሪክ ነው!" አለ የስብሰባው ተሳታፊ፡፡ "ልብ በሉ! ጀግና ሰዎች ጥቂት እንደሆኑት ሁሉ ጀግና ቀበሮዎችም ጥቂት ናቸው፡፡ ባምስቱ ዘመን የሰውም ሆነ የቀበሮ ጀግኖች ጥቂቶች ነበሩ፡፡ ብዙው ወገኑን ክዶ ለጣሊያን እንቁላል ሲገዛና መንገድ ሲያያሳይ ይውል አለዚያም ጎመን በጤናን እየተረተ በላይም በታችም እያገሳ ተኝቶ ያድር ነበር" ብለው ጀኔራሉ ሳይጨርሱ " ባንዳውና ሰላቶው ዛሬ ብሷል ጀኔራል!" አለ ተሰብሳቢው፡፡ "አዎ! ዛሬ ብሷል! አብዛኛው በሆዱ እየተገዛ ነፍሰ ገዳዮችን እያገለገለ አለዚያም ጎመን በጤናን እየተረተ የውርደት ሞቱን ይጠብቃል፡፡ ሆዳም እንኳን ጎረቢትና ጓደኛውን ልጁንና ወላጁንም ይሸጣል" አሉ ጀኔራል የተኮሳተረው ግንባራቸው ለከሀዲ ያላቸውን ጥላቻ እያሳዬ፡፡ "ስለዚህ የእኛ ችግር ከጀግኖች ጋር ሳይሆን ከውሻና ከውሻ መሳይ ሆዳምች ጋር ነው!" ሲሉ ከውሻ አምልጠው የተረፉት ተነስተው ጭብጨባውን አቀለጡት፡፡ "አዎ ዛሬም በውሻ መሳይ ሆዳሞች ቀበሮና ሰው አንድ ላምስት ተጠርንፈው እርስ በርስ እንዲበላሉ እየተደረገ ነው፡፡ መጋቢ ብሉይ እንዳሉት ይህ እርስ በርሱ እሚበላላ ሰው በእኛ ውሻ ከመልቀቅ ይቆጠባል ብሎ የሚያስብ አለ?" ብለው ጀኔራል ሲጠይቁ "ማንም የለም! ሰውም እንደ ውሻ ጠላታችን ነው!" አለ ተሳታፊው በአንድነት፡፡
በቀረበላቸው ውኃ ጉረሯቸውን አረጠቡና ጀኔራል አሁንም ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡ "ቀደም ሲል እንደተወያየነው የፋኖ ምሽጉ የቀበሮ ጉድጓድ ነው፡፡ ምግቡም ድኩላ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን ሆዳም ሰው መኝታው የጥጥ ፍራሽ ምግቡም በሬና በግ ነው፡፡ ልብ በሉ! ጀግና ድኩላን አድኖ ሲበላ ሆዳም በግን ከእነአጥንቱ እየቆረጠመ ቀበሮን ያባርራል፡፡ "መጋቢ ብሉይ እንዳስተማሩት ቀበሮና በግ የሚተዋወቁት ሰው ከመፈጠሩ በፊት ነበር፡፡ ይህ የሚያረጋግጠውም በግ ለቀበሮ ምግብነት የተፈቀደው ለሰው ከመፈቀዱ በፊት መሆኑን ነው፡፡ አይደለም እንዴ?" ብለው ሲጠይቁ "ይበል ብለናል ጀኔራል!!" አሉ መጋቢ ብሉይ፡፡ አንዳንዶቻችሁ "ቀበሮስ ለምን በግን ይበላል ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል፡፡ ቀበሮ በግን እንዲበላ የሚያስገድደው ተፈጥሮው ነው፡፡ የሥነ-ህይወት ጠበብቶች በሙያችን ገባህ አይበሉኝ እንጅ የቀበሮ ጥርስ የተሰራው ሥጋን ለመብላት ብቻ ነው" ብለው አቀንጣጢአቸውን ለማስረጃነት አሳዩ፡፡ "በሥነ-ህይወት ጠበብቶች ፊት ስለ አካል ክፍሎች ማውራት እንደሚከብደው መጋቢ ብሉይ ባሉበት ስለብሉይ ኪዳን መናገር ይከብዳል እንጅ ሰው ደም ያለው ፍጡር እንዳይበላ በዘሌዋውያን ሕግ ተከልክሎ ነበር፡፡ ሰው ግን እንኳን አምላክ የደነገገውን ራሱ የሞነጫጨረውን ሕግም እንደማያከብር በወመኔው አገዛዝ እያየነው ነው፡፡ ሕግ አፍራሹ ሰው ሕግን ጥሶ እንኳን በግን አህያውንና አይጡንም እየበላ ነው፡፡ አህያውና አይጡ ሲነጥፍ እኛንም መብላቱ እማይቀር ነው፡፡ ቢጫ አይነ-ገናዎች ወመኔዎችን እያጎረሱ ኢትዮጵያን ከወረሩበት ጊዜ ጀምሮ ያህያና የአይጥ ቁጥር መቀነሱ እሙን ነው፡፡ ቢጫዎችንና ነጮቹን መምሰል መሰልጠን እሚመስላቸው አሻንጉሊት አበሾችም አህያና አይጥ መብላት እንደሚጀምሩ አትጠራጠሩ፡፡ አህያውና አይጡ ሲጠፋም እነዚህ አሻንጉሊቶች ወደ እኛ እንደሚዞሩ አትዘንጉ!" ሲሉ ሴት ቀበሮች ሆድ ባሳቸውና አፋቸውንና አፍንጫቸውን በጥፍሮቻቸው ይዘው ሰቅስቅ ብለው አለቀሱ፡፡ "በምናወጣው ወታደራዊ ስልት ሽንጥን ገትሮ መፋለም እንጅ ማልቀስ መፍትሔ አይሆንም! ቀይ ቀበሮ፣ የሰሜን ቀበሮ፣ የባሌ ቀበሮ ጂኒ ጃንካ የሚባሉትን ክልሎች ደርምሰን ቀበሮ በሚል ጃንጥላ ተሰባስበን በጥፍር፣ በጥርስና በድድ መፋለም ይኖርብናል" ሲሉ ታሳታፊው ምክራቸውን መቀበሉን በደማቅ ጭብጨባ አረጋገጠ፡፡
"ሰው በሆዱ ብቻ ሳይሆን በክህደቱም ውሻን ይመስላል፡፡ መጋቢ ብሉይ እንዳሉት ውሻ በአካሉም ሆነ በአፈጣጠር ዘመኑ እሚመደበው ከኛ ጋር ነው፡፡ ዳሩ ግን በአራት እግሩ እየሄደ በሁለት እግሩ ከሚሄደው መናጢ ሰው ወግኖ እኛን እየፈጀ ነው፡፡ ከሀዲውን ውሻም መናጢው ሰው በአገልጋይነቱ የመጀመሪያው ለማዳ፣ ታማኝ ጓደኛ፣ የተደበቀን ፈላጊ፣ ቅብጥሶ ቅብጥሶ እያለ ያሞካሸዋል፡፡ ይህ ሙከሻም ምእራባውያን እንደ ባርያ የሚያገለግሏቸውን ወመኔ ገዥዎች ዲሞክራቶችና ምጣኔ ሐብት አሳዳጊዎች እንደሚሉት ማታለያ ነው፡፡ ወመኔዎች ለሚያሞካሿቸው ምእራባውያን አቤት ወዴት እያሉ እንደ አሽከር በላኳቸው ግዛት ሁሉ እንደሚዘምቱት ውሾችም ጅራታቸውን እየቆሉ ሰው ያዝ ብሎ በላካቸው የቀበሮ ግዛት ሁሉ እየዘመቱ ነው" እያሉ ጀኔራል ሲያስተምሩ አንድ በጀኔራሉ ቁመና፣ ጀግንነትና ምሁርነት የተማረከች ቆንጆ ቀበሮ በደንብ እንድትታይ በኋላ እግር ጥፍሮቿ ቆማ መቃ አንገቷን እየሰበቀችና ችቦ ወገቧን እንደ እዝርት አሹራ ዳሌዋን እያሳዬች "የሁለት ሺ ስድስቱ ቆጠራ እንደሚያመለክተው የቀበሮ ቁጥር እጅግ ቀንሷል፡፡ እንዲያውም ሴቶች በርትተው እያከታተሉ ወልደው ባያሳድጉ እንደ ወንዶቹ ጡርቂነትማ ጨርሰን እንጠፋ ነበር" ብላ ለወንዶች ያላትን ንቀትና ለሴቶች ያላትን አድናቆት ገልፃ ሳትጨርስ ከግዕዝና ከቅኔ መምህሯ ከእማሆይ ገላነሽ ሰፈር የመጣች አንድ ወጣት ቀበሮ "ምንት ምንትስ.." ብላ በግእዝ ተቀኝታ ለቆንጆዋ ቀበሮ መልስ ስትሰጥ ቅኔው የገባቸው ጥቂቶች ሽንታቸው እስኪመጣ ሲስቁ ሌሎችም ካልገረማቸው አልሳቁም በሚል ተራ በተራ ፈገግ ማለት ጀመሩ፡፡ "ጨለማን ተገን አድርገው ወንዶች በርትተው ጉድጓድ ባይቆፍሩ ልጆች ከየት ይመጡ የትስ ያድጉ ነበር! ይላል ቅኔው ሲተረጎም" ይበል ብለናል! አሉ አንድ የግዕዝ ሊቅ፡፡ ሞኝ ሁለት ጊዜ ይስቃል መጀመሪያ ሌሎች ሲስቁ ዳግመኛም ነገሩ ሲገባው እንደሚባለው ጠቅላላ ተስብሳቢው በሐይል ሲስቅ የገደል ማሚቶው ድፍን ዛምበራን አናጋው፡፡
ተሳታፊዎች ሊቋ በተቀኙት ቅኔ እየተንፈራፈሩ ሲስቁ ከቀበሮዎች ኪስ የሾለኩ ሁለት የእጅ ስልኮች ከመሬት ተገኙ፡፡ ጸጥታ አስከባሪ ኮማንዶዎች ስልኮቹን አንስተው ሲፈትሹ ሰርገው የገቡ ሰላዮች ስብሰባውን እየቀዱ መሆኑን ተረዱ፡፡ ስብሰባውን ሊቀዱ የገቡትን ሰላይዎች ኮማንዶዎች አንቀው ሲያወጧቸው ግርግር ተፈጠረ፡፡ ሰላይ መሆናቸውን የተረዳው ተሰብሳቢ እየተረባረበ ሲረግጣቸውና በጥፍር ሲሞነጭራቸው ከሰላዮቹ አንዱ የቀበሮ ለምድ የለበሰ ውሻ ሆኖ ተገኘ፡፡ ይህንን ውሻ ያዬ ሁሉ አፉን እንደ ዓባይ ሸለቆ ከፍቶና አይኑን እንደ ልቅ አንጎልጉሎ እንደ ስልክ እንጨት ደርቆ ቀረ፡፡ ተሰብሳቢው ከድንጋጤና ከግርምት አለም ሲመለስ "አሁኑኑ እርምጃ ይወሰድባቸው!!" ሲል ጀኔራል መከተን ጠየቀ፡፡ ጄኔራል መከተም "ክቡራትና ክቡራን ቀበሮዎች ሆይ! አንዴ! አንዴ! አዳምጡኝ! እንደማመጥ! እንደማመጥ!" ብለው ሲጠይቁ ጀኔራሉ የሚሉትን ለመስማት ሁሉም እረጭ አለ፡፡ "ከስሜታዊነትና ግብታዊነት እንላቀቅ፡፡ እኛ ቀበሮች እንደ ወመኔ ገዥዎች ከእጃችን የገባን እስረኛ የምናሰቃይና የምንገድል እርጉሞች አይደለንም፡፡ እንደምታዩት በባንዳ ቀበሮዎች እርዳታ የእኛን መልክ ለብሶ የመጣውን ውሻ በቁጥጥር ሥር አውለናል፡፡ ነገር ግን ሌሎችም ሰላዮች ሊኖሩ ስለሚችሉ ስብሰባውን እዚህ ላይ እናቆምና ጸጥታ ማስከበሩ ላይ እናተኩራለን፡፡ ከጸጥታ አስከባሪዎች በስተቀር ሁላችሁም ከተመደበላችሁ ጉድጓድ እንድትገቡ እንጠይቃለን፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድ ነገ ከጧቱ በሁለት ሰዓት እዚሁ ቦታ እንገኛለን" ብለው ስብሰባውን በተኑ፡፡
ጀኔራልና ኮማንደሮቻቸው እንደ ወመኔ ገዥዎች እየገረፉና ጥፍር እያወለቁ ሳይሆን እያበሉና እያጠጡ እጅ ከፈንጅ ከተያዙት ሰላዮች መረጃ ሲሰበስቡ አደሩ፡፡ ከተያዙት በስተቀር ሌላ ሰላይ እንደሌለና አደጋም እንደማይፈጠር ካረጋገጡ በኋላ ሰብሰባውን በሁለት ሰዓት ጀመሩ፡፡ ተሰብሳቢው ቦታ ቦታውን ከያዘ በኋላ ኮማንደሮቹ ሰላዮቹን እግር ለእግር አስተሳስረው ከተሰብሳቢው ፊት አቀረቡ፡፡ አንደኛው ኮማንደርም ሰላዮቹ ለጀኔራልና ለኮማንደሮች የተናዘዙትን በራሳቸው አንደበት ለሰፊው ቀበሮ እንዲናዘዙ አዘዟቸው፡፡ የቀበሮ ለምድ ለብሶ የገባው ሰላይ ውሻ ጆሮውንና ጅራቱን ወትፎ "በመጀመሪያ ከሰው ልጅ ያላየሁትን ርህራሄ ከቀበሮ በተለይም ከእኒህ ጀኔራል በማግኜቴ ለመላው ቀበሮዎች ምስጋናዬንና አድናቆቴን አቀርባለሁ፡፡" ብሎ ጭብጨባ ከተሰብሳቢው ለመለመን ቀና አለ፡፡ ተሰብሳቢው ግን ጥርሱን ነክሶ "የምታታልለውን አታል!" በሚል ስሜት አፈጠጠበት፡፡ ምህረት የተነፈገ የመሰለው ሰላዩ ውሻ በፍርሃት ተውጦ ኑዛዜውን እንዲህ ሲል ቀጠለ፡፡ "እንደምታዩኝ ውሻ ነኝ፡፡ ነገር ግን ቀበሮ በማባረር የምኖር ውሻ አይደለሁም፡፡ እውነቱን ለመናገር ከትናንትናው በቀር ቀበሮን አስደንግጬ አላውቅም፡፡ ከአካሌ መረዳት እንደምትችሉትም ክልስ ነኝ፡፡ እናቴ አበሻ ብትሆንም አባቴ ጣሊያናዊ ውሻ ስለሆነ ያደኩት ሮም ከተማ የተቀመመ ምግብ እየበላሁ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የመጣሁትም በሁለቱ የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነቶች አበሻ ቀበሮዎች ምሽግ እየቆፈሩ ፋኖዎችን ስለረዱ ቀበሮዎችን በቀለም፣ በዘር፣ በክልልና በሃይማኖት ከፋፍሎ እርስ በርሳቸው እንዲፋጁ የሚያደርገውን የቆዬ ያውሮጳ እቅድ ለማስፈጸም ነው፡፡ ይህንን ተልኮዬን ለማሳካትም እዚህ አብረውኝ እንደቆሙት ያሉትን ቀበሮች በጥቅማጥቅም ደልያለሁ፡፡ በስህተቴ ተጸጽቼ ከእግራችሁ ተንበርክኬ ይቅርታ እጠይቃለሁ" ብሎ ባፍንጫው ተደፉ፡፡ ባንዳዎቹ ቀበሮዎችም በሐፍረትና በፍርሃት ተሸማቀው መሬት መሬቱን እያዩ በተወካያቸው አማካኝነት ኑዛዜአቸውን እንደሚያቀርቡ ገለጡ፡፡ የተወከለው ባንዳ አይኑን ከመሬት ተክሎ "እኛን ያሳሳተን ይህ ክልሱ ውሻ ነው፡፡ ሰው ያዝ ሲለው ውሻ እያባረረ ከሚደፋችሁ ሮም ወስጄ የተቀመመ ምግብ እየበላችሁ ከአልጋ እንድትተኙ እድሉን አመቻችላችኋለሁ ብሎ አታለለን" ብሎ ሳይጨርስ አንድ ጎረምሳ ቀበሮ እንደ ምኒሊክ ብምርህ ማሪያም አትማረኝ በሚል መንፈስ ቡጢ ሊያቀምሰው ሲቃጣ ኮማንደሮቹ አዳኑት፡፡ ኑዛዜአቸውን ሲጨርሱ ከፊሉ "ይቅርታ ይደረግላቸው' ሲል የቀረው "እንዴት ለሰይጣን ይቅርታ ይደረጋል?" ሲል ተቃወመ፡፡
በዚህ ግርግር መካከል አንድ አዛውንት ቀበሮ ብድግ አሉና እንደ ቄስ አማረ አንገታችውን አንዴ ወደ ግራ ሌላ ጊዜ ወደቀኝ እያቅለሰለሱ "አያችሁ ይሉኝታ ቢሱ ሰው የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ ቀበሮዎች ተጠንቀቁ እያለ ይተርታል፡፡ የቀበሮ ለምድ ለብሰው ከሚመጡ ውሾች ወይም ውሻን የበግ ለድ አልብሰው ያዝ ከሚሉ ሰዎች ተጠንቀቁ ብሎ ሲተርት ግን ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ ፈቃዳችሁ ተሆነ በአይናችሁ ያያችሁትን የቀበሮ ለምድ የለበሰ ውሻ ልዝለልና ሰው የበግ ለምድ አልብሶ ወደ ቀበሮ ስለላከው ውሻ ላውጋችሁ፡፡ መቼም የቀበሮ ጆሮ ቀጥ ስላለና ደፍቶ ስለሚያይ እንደ ተንኮለኛ ይቆጠራል እንጅ እንደ ቀበሮ ደግና ታማኝ ፍጡር የለም፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ቀበሮ የበግ መንጋን ሲጠብቅ፤ ለአገልግሎቱም አንድ ጠቦት ሊያገኝ ከሰው ጋር ተዋዋለ፡፡ እንደምታውቁት ቃል በቀበሮ ዘንድ እንደዚያ... አምጡልኝ ለሕዝብ ሲል ራሱን እንደ ክርስቶስ አሳልፎ እንደሰጠው ..." ብለው ሳይጨርሱ አብዛኛው ተሰብሳቢ በአንድነት "እስክንድር ነጋ!" አለ፡፡ አዛውንቱ ቀበሮም " እስክ ጥንቱ የጦቢያ ግዛት እስተ እስክንድርያ ይንጋላችሁ" ብለው መርቀው ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡ " አዎ ቀበሮ እንደ ብሩኩ እስክንደር ነጋ እምነት ጥኑና ቃል አክባሪ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ቀበሮ በቃል-ኪዳኑ ጠንቶ አንዲት ግልገል ሳያጎል የበጎችን መንጋ ለሰውየው አስረከበ፡፡ ሰውየውም ቀበሮን በምስጋና ሸንግሎ ጦቦቱን እስታመጣልህ እዚህ ጠብቀኝ አለው፡፡ ቃል አክባሪው ቀበሮ አሁንም የገባውን ቃል አክብሮ ጠበቀው፡፡ ይህ ቃሉን እንደቀበኛ የበላ ሰው ግን የበግ ለምድ አልብሶ ውሻውን አመጣና ያዝ ብሎ ወደ ቀበሮው ለቀቀው፡፡ ቀበሮውም ለሰው ሞት አነሰውን ተርቶ ውሻውን አመለጠው፡፡ ለሰው ሞት አነሰው እሚለው ዜማ የቀበሮ ብሔራዊ መዝሙር የሆነው ተያን ጊዜ ጀምሮ ነው" ብለው ሲተርኩ አንድ ካዲሳባ የመጣ ቀበሮ "ይህ ታሪክ በደንብ እማውቀውን ቃል በላ አስታወሰኝ" አለና "የቀበኛው የልጅነት ስም አብዮት ነበር? ብሎ አዛውንቱን ጠየቀና ተሰብሳቢውን አውካካው፡፡
ሁካታው በረድ ሲል ጀኔራል ተነሱና " ለዚህ አቢይ የቀበሮ ታሪክ አባታችንን እናመሰግናለን፡፡ ይህ አባታችን የነገሩን ታሪክ የተፈጸመውና ብሔራዊ መዝሙር መዘመር የጀመርነው ከሀዲዎች እንደሚሉት ከመቶ አመት ወዲህ ሳይሆን ከአራት ሺህ ዓመታት በፊት ነበር፡፡ እንደምታውቁት ውሾችና ውሻ መሳይ ሰዎች ታሪክ እንዲወራ አይወዱም፤ ከታሪካቸውም መማር አይፈልጉም፡፡ እነዚህ እፊታችሁ የቆሙት ሰላዮችም የሚማሩና የሚታረሙ አይመስለኝም፡፡ ይህንን ስል እንደነሱ ክፉ ሆነን እናሰቃያቸው ወይም እንግደላቸው ማለቴ አይደለም፡፡ በሽተኛ በእግዚአብሔር እጅ እንደሆነው ሁሉ እጅና እግሩ የታሰር እስረኛም በእግዚአብሐር እጅ ነው፡፡ ስለዚህ እስረኛን ማሰቃዬት በእግዚአብሔር ሕግ ያስጠይቃል፤ ምድራዊ ሕግ ባለበት አገር በምድራዊ ሕግም ያስጠይቃል፡፡ ስለዚህ ለእስረኛ እሚደረገው እንክብካቤ እየተደረገላቸው በሕግ ውሳኔ እስከሚያገኙ ማረሚያ ቤት ይቆያሉ፡፡ ውሾችና ውሻ መሳይ ሰዎች በሆዳቸው እየተገዙ በዶላር፣ በዩሮና በፓውንድ ከጠነቡ የቀበሮ መንግስታት ጋር የሚሸርቡትን ሸር ማጣራቱን እንቀጥላለን፡፡ ሆዳምና ውሻ መቼውንም ስለማይጠፋ ከመጥፋት የሚያድነን የራሳችን ጥንካሬ ነው፡፡ ሆዳምንና ውሻን አንድ ሆነን በስልት መዋጋት አለብን!" ሲሉ አንድ ሰበብ የሚያበዛ ቀበሮ ብድግ አለና "ሰው ብዙ መሳሪያ አለው፤ ውሻም በተኩስ ሰልጥኗል ይባላል፡፡ እኛ እጅ እንኳን የለንም፤ በምን ልንዋጋ እንችላለን?" ብሎ ሲጠይቅ አንድ ቆፍጣና ኮማንደር ተቆጣና "ያምስቱ ዘመን ጀግኖች እስታፍንጫው ታጥቆና መርዝ በአውሮፕላን ጭኖ የመጣውን ጣሊያን ያሸነፉት በጦርና በጎራዴ ነው፡፡ አሸናፊው መሳሪያ ሳይሆን ልብ ነው፡፡ ልብ ሲኖር ሜዳው ገደል ነው! ልብ ሲኖር ከተማው ጫካ ነው! ልብ ታለህ እጅ ባይኖርህም በጥርስህ ንከስ፣ መሳሪያ ባይኖርህ በጥፍርህ ቧጭር! አዎ እንደ ክቡር ጄኔራል በጥፍርህ ቧጭረህ አይን አፍስስ፣ በጥርስህ ነክሰህ በበሽታ ረፍርፍ! ቀበሮ በበላበት በሚለምድ ሆዳም ውሻና ተኋላው በመጣ ውሻ መሳይ ሰው ርስቱን ተንጥቆ እየተባረ በጭራሽ አይኖርም! የቀበሮ ፋኖ ወደፊት ይገሰግሳል! ተወደቀም ፎክሮ ይነሳል! የቀበሮ ፋኖ ክብሩን እርስቱን ጥሎ ተመኖር መሞትን ይመርጣል፡፡ ታጠቅ! ተነስ! አለዚያ ፈሪ ለናቱ ያገለግላል፤ ምጣዱ ሲጣድ ሙግድ ያቀብላል እንደሚባለው ከቤትህ ዋልና ለሚስትህ ሙግድ አቀብል! ሰበበኛ!" ሲል አንዳንድ የሚልመጠመጡ ባሎች ያሏቸው ሴቶች ሙግድ አቀባይ ባሎቻቸውን እያዩ በሳቅ ፈነዱ፡፡ ጀግና ቀበሮዎች በጀኔራሉ ፊት ፎከሩ፡፡ ሙግድ አቀባይ ባሎችም በምንተ እፍረት ከጀግናዎች ጀርባ ቆመው ዘራፍ ማለት ጀመሩ፡፡
ፉከራውና ሽለላው ሲያበቃም ጄኔራል መከተ የኮማንደሩን ቆምጫጫ አስተያየትና የፎከሩትን አድንቀው "ወንድማችን እንዳለው አሸናፊው ልብ ነው፡፡ ቀበሮ ከመጥፋት እሚድነው ክብሩን፣ ታሪክና ባህሉን በልቡና በቃል ኪዳኑ ሲጠብቅ ብቻ ነው፡፡ አለዚያማ ክብሩን የተገፈፈ ቀበሮ ቅርቀብ ተጭኖ በዱላ ከሚነረት አህያ በምን ይሻላል? እንደ አህያና እንደ ውሻ ሆድን እየቆዘሩ ክብርን ተራቁቶ ከመኖር በርሃብ ሞቶ በክብር ተከፍኖና በማእረግ ተገንዞ መቀበር ይሻላል፡፡ ስለዚህ ነፃነት ወይም ሞት ብለናል! ከዛሬ ጀምሮ ሜዳው፣ ተራራው፣ ሸንተረሩ፣ ሐይቁ፣ ወንዙና ጅረቱ በዋሽንት፣ በመሰንቆ፣ በክራር፣ በበገናና በእምቢልታ ወኔያማ ዜማዎች ያሸብርቅ፡፡ ጋራው፣ ሸለቆውና ጫካውም ቀረርቶና ፉከራን ያስተጋባ፡፡ የዋሽንት፣ የመሰንቆ፣ የክራርና የበገና እንጉርጉሮዎች፣ የወይዛዝርት ዘፈኖች፣ የካህናት ወረቦችና ቅኔዎች፣ የጎበዝ ቀረርቶዎችና ፉከራዎች የጀግና መብቀያ ለም መሬቶች ናቸው፡፡ እነዚህን የጀግና መብቀያ ለም መሬቶች ሱሪና ቀሚስ በሚያስወልቁ ምዕራባውያን የሚዚቃና የዳንስ አረሞች መበከል የሚያበቅለው ቀበቶውን ከቂጡ ታጥቆ መዥገር እንደያዛት የድርቅ ላም እሚሽመደመድ ትውልድ ነው፡፡ ስለዚህ ስልጡን ለመምሰልና ገንዘብ ለማካበት በማንነቱ አፍሮ ቆዳውን የለወጠውን ማይክልንና የጳውሎስን ወዳጅ ቦያንሲን እየኮረጀ ጀግና እሚያበቅለውን ባህላችንን እሚያጠፋም ከባንዳ እሚመደብ ነው፡፡ ባንዳ እግራችንን እየነከሰን ብዙ መራመድም ስለማንችል በላይ ዘለቀ፣ አበበ አረጋይና ሌሎችም ጀግኖች እንዳደረጉት የመጀመሪያው እርምጃችን ባንዳን ማጽዳት ይሆናል፡፡ ባንዳን አጽድተን በአንድ አላማና በአንድ ባንዲራ ከተሰለፍን የመሳሪያ ጋጋታም ሆነ የውሻ መሰልጠን ከድል አይገታንም፡፡ ውሻንና ውሻን መሳይ ሰው ድል እንደምንነሳ ቅንጣት አልጠራጠርም፡፡" ብለው ኳስ በሚያህለው ቡጢያቸው ጠረጴዛውን ሲያቦኑት ተሳታፊው እየዘለለ ጭብጨባውን ለሁለት ደቂቃ አቀለጠው፡፡ ጭብጨባው በረድ ሲልም ጀኔራል "በምስጢር የምናስተላልፋቸውን ወታደራዊ የትግል ስልቶች እየተከተላችሁ ቀበሮን ከመጥፋት ለማዳን በሚደረገው መራር ትግል በንቃት ተሳተፉ፡፡ አመስግናለሁ፡፡" ብለው ስብሰባውን በጸሎት እንዲዘጉ ቄስ ወልደ አማኑኤልንና ሼህ ሙዴስርን ጋበዙ፡፡
ቄስ ወልደ አማኑኤልና ሼህ ሙዴስር በስብሰባው መደሰታቸውን ከገለጡ በኋላ እውነትና ፍትህ የእግዚአብሔር ባህርያት እንደሆኑ አስረድተው፤ ለእውነትና ለፍትህ የሚደረግ ትግልም ለእግዚአብሔር የሚደረግ ትግል መሆኑን አስተምረው፤ ለእግዚአብሔር ለሚደረገው ትግልም የቤተ-ክርስቲያንና የመስጊድ አገልጋዮች ከፊት እንዲሰለፉ በአፅንኦት ጠይቀው የመዝጊያውን ጸሎት አደረሱ፡፡ ከጾለቱ በኋላ "ለሰው ሞት አነሰው" እሚለው የቀበሮ ብሔራዊ መዝሙር ተዘምሮ ተሳታፊዎች "ፋኖ ተሰማራ" እሚለውን የነፃነት ተጋድሎ ዜማ እያዜሙ ወደ እያገራቸው ተመልሰው የህልውና ፍልሚያውን ቀጠሉ፡፡
መጀመርያ ህዳር ሁለት ሺ ስምንት ዓ..ም.
እንደገና ህዳር ሁለት ሺ አስራ ስድስት ዓ.ም.
https://amharic-zehabesha.com/archives/187228
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment