Saturday, October 28, 2023

ሽብርተኛው የኦህዴድ መንግሥት ፋኖን “ሽብርተኛ” ብሎ ሲከስ መላው ዓለም ታዝቦታል፤ንቆታል
አክሎግ ኢራራ (ዶር)

ቅዳሜ October 21, 2023, Tri-State የተባለው ቡድን ባካሄደው ውይይት ተጋብዠ ለብዙ ዓመታት የማውቀው ወዳጀ፤ አገር ወዳዱ ኢትዮጵያዊ እንጂኔር ግደይ ዘራጽዮን ያቀረበውን ማራኪ ትንተናና ምክረ ሃሳብ አዳምጨ ነበር። እንጂኔር ግደይ ከተነተናቸው አርእስቶች መካከል “የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት፤ የፋኖ የህልውና ትግል፤ የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና አስጊ ሁኔታ፤ በተለይ እየሻከረ የሄደው የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግሥታት ግንኙነት፤ የትግራይ ክልል ወቅታዊ ተግዳሮቶች” ይገኙበታል።

ኢንጅኔር ግደይ ስለ ፋኖ መነሻና መድረሻ ያቀረበው ትንተና ምክንያታዊና በመረጃ የተደገፈ ነበር። የዐብይ መንግሥት እንደሚሰብከው ሳይሆን፤ ፋኖ የቆመው “ለፍትህ፤ ለነጻነት፤ ለዜጎች እኩልነት፤ ለብሄራዊና ግዛታዊ አንድነት፤ ለዲሞክራሲ” መሆኑን አስምሮበታል። እነዚህ የመላው ኢትዮጵያዊያን ምኞቶችና ተስፋዎች ናቸው።

አማራው ፋኖን የሚደግፍበት መሰረታዊ ምክንያት “የፖለቲካና የኢኮኖሚውን የበላይነት መልሶ ለመያዝ ነው” የሚለውን የፈጠራ ትርክት ሲተች እኔም የምጋራውን “ከአሁን በኋላ በምንም መልኩ ኢትዮጵያን አንድ ብሄር/ዘውግ ሊገዛት አይችልም” ወደሚል ድምዳሜ ደርሷል፤ ደርሰናል። በሌላ አነጋገር፤ እብርተኛው ህወሓት ጀምሮ የፈረሰውና አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ አሊ በኦሮሞው ሕዝብ ስም “ከአሁን በኋላ የመግዛትና የመብላት ወቅቱ የኛ (ኼኛ) ነው” የሚለው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ሊያፈርሳት ጫፍ ላይ ደርሷል።  ይህ ግንዛቤ ትክክል ነው። ህብረ-ብሄራዊነት፤ እኩልነት፤ አንድነት፤ ፍትህና ዲሞክራሲ በአንድ በኩል፤ በሌላ በኩል የአንድ ዘውግ የበላይነት (የኦሮሞ ኼኛነት) አብረው ሊሄዱ አይችሉም።

“ኼኛ፤ የኛ” ተራ የሚለው አደገኛ የዘውግ የበላይነት (Absolute Oromo Hegemony) እንቅስቃሴ ሁሉንም ይደፈጥጣል፤ ያመክናል። እንጂኔር ግደይ “እኔም ፋኖ ነኝ” ብሎ ሲናገር ለይስሙላ ወይንም ለመወደድ አይደለም። ምክንያት አለው። ፋኖ የሚታገለውና የአማራው ሕዝብ ከፍተኛ መስዋእት በመክፈል ላይ የሚገኘው፤ መልሶ ሥልጣን ለመያዝ አይደለም።   “መልሶ ሥልጣን ለመያዝ ነው” የሚለው ኦነጋዊያንና ህወሃታዊየን እስከሚሰልች  ድረስ የሚያስተጋቡት የጸረ-አማራው ትርክት አካል ነው። መብቴ ይከበር፤ ፍትህ ይኑር ማለትና “የኔ ዘውግ ብቻ ይግዛ” ማለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። አማራው “የኔ ብቻ ወይንም ኼኛ” ብሎ አያውቅም።  የአማራው ሕዝብ አንዱ የሚለይበት ከሌላው ብሄር፤ እምነት ጋር የመኖር ችሎታው ነው።

የፋኖውና ደጋፊዎቹ ጥሪ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ለእኩልነት፤ ለነጻነት፤ ለፍትህ፤ ለአንድነት፤ ለዲሞክራሲ፤ ለአገራዊ እርጋታ የመቆም ግዴታ አለባቸው የሚል ነው። “እኔም ፋኖ ነኝ” ብየ የምከራከረው እነዚህ መሰረታዊ እሴቶች ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ጽኑ እምነት ስላለኝ ነው። በኢትዮጵያ ዘላቂነት፤ ሉዐላዊነት ኢትዮጵያዊነት የሚያምን ሁሉ ሌላ አማራጭ የለውም። ስድስት ሚልየን የሚገመተው የአዲስ አበባ ሕዝብ ዝም ብሎ በኔ ላይ አይደርስም ከሚል ይልቅ፤ ለፍትህ የሚካሄደውን ትግል መቀላቀል አለበት። “ያልጠረጠረ  ተመነጠረ” እንዲሉ እልቂቱ የአዲስ አበባን ሕዝብም አይምርም።

የፍትህ ትግሉን ስኬታማ ለማድረግ የሚቻለው ግን፤ ሁሉም በዜግነት መብትና ሉዓላዊነት የሚያምኑ፤ ለዘላቂ ሰላምና ፍትህ የቆሙ ፋኖ መሰል እንቅስቃሴዎች ሲጀምሩና በአገር  ደረጃ ለማቀነባበር ሲችሉ ነው። የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ማህበረሰባዊ ስብስቦችም አብረውና ተገናዝበው የሚሰሩበት ወቅት አሁን ነው።

ይህ የፋኖ ብቻ ሃላፊነት አይደለም። በአማራው መስዋእት ብቻ ኢትዮጵያን፤ ፍትህን፤ ሰብአዊ መብትን ለመታደግ አይቻልም።

ህወሓት፤ ኦነግ፤ ኦህዴድ፤ ኦነግ ሸኔ፤ የኦሮሞ ብልጽግናና በዘውግ ፖለቲካ የታነጹ ኃይሎች ሁሉ ከላይ የጠቀስኳቸውን እሴቶት ስኬታማ ለማድረግ ፍላጎትም፤ እምነትም የላቸውም። ቢኖራቸው ኖሮ፤ ባለፉት ሰላሳ ሁለት ዓመታት ብቻ የተከሰተውን አገር አፍራሽ እልቂትና ውድመት ሊያቆሙት ይችሉ ነበር።  የፖለቲካ ፈቃደኛነትና ቅንነት ቢኖራቸው ኖሮ፤ በሰሜኑ ጦርነት ብቻ አንድ ሚልየን የትግራይ ወገኖቻችን አይሞቱም ነበር፤ ከሶስት መቶ እስከ አራት መቶ ሺህ የሚገመት የአፋር፤ የአማራና ሌሎች ዘውግ አባላት አይሞቱም ነበር። ሃያ ስምንት ቢሊየን ዶላር የሚገመት ኢንቨስትመንት አይወድምም ነበር። የኦህዴድ መንግሥት የበላይ ሆኖ አገሪቱን አጣብቂኝ ውስጥ ያስገባው ዐብይ አሕመድና ቡድኑ ከዚህ አስከፊ ጦርነት ይማሩ ነበር።

ጥላቻውን፤ ቂም በቀልነቱን፤ እልቂቱን. ጦርነቱን፤ ውድመቱን ሆነ ብለው የፈጠሩት ራሳቸው የዘውግ ልሂቃን ናቸው። ችግሩን ለመፍታት ፈቃደኛ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ ሞኝነትና አድርባይነት ነው። ምክንያቱም ተጠቃሚዎች ፈልፍለዋል። ከተጠቃሚዎቹ መካከል የብልጽግና ፓርቲ የሾማቸው፤ በሙሰኛነት የተበከሉ፤ ለተራው ወገናቸው ደንታ የሌላቸው ጀኔራሉች አሉ።

የዚህ መንግሥት መለያ የዘውግ ጥላቻን ማጠናከር፤ ከፋፍለህ ግዛውንና ብላውን ተቋማዊ ማድረግ፤ ሥልጣንን በኃይል ስኬታማ ማድረግ ወዘተ ነው። ስንት አገራዊ ወይንም ብሄራዊ ተቋም ነው የዘውግ ስርጭቱ በችሎታ ተሰርቶ ሚዛናዊ እና ኢትዮጵያዊያንን የሚወክል የሆነው? ተተኪነትና የበላይነት የሚጠይቀው የዘውግና የፖለቲካ ተአመኔታን ብቻ ነው (The guiding criteria for assignments is loyalty to tribe; and not competence or dedication to the service of Ethiopia and the Ethiopian people). ይህ ደግሞ የሞራል ልእልናን ይጠይቃል።

ፋኖ በምን ይለያል?

ለማንጻጸር፤ የፋኖ መለያዎች ብዙ ናቸው። ፋኖ ጦርነቱን አልፈጠረውም፤ አልጀመረውም። ፋኖ የኦሮሞን ህጻናት፤ ሴቶች፤ እናቶች አዛውንቶች አልጨፈጨፈም። ፋኖ ማንንም ከቀየው አላባረረም። ፋኖ ባንክ አልዘረፈም። ፋኖ የማረከውን ግዙፍ ብር መልሶ ያስረከበው ለሕዝቡ ነው። ፋኖ ዘውግ ሆነ እምነት ሳይለይ፤ የማረካቸውን ግለሰቦች በጨዋነት በመንከባከብ ላይ ይገኛል። ፋኖ መሰረተ ልማት አያወድምም። ፋኖ ሴቶችን አይደፍርም። ፋኖ አገሩን ኢትዮጵያን፤ በአገር ደረጃ እና የኢትዮጵዊነት መለያውን አልካደም። ፋኖ ሌሎች የታፈኑ፤ የሚሰቃዩ ወገኖቹን “ኑ፤ ተነሱ፤ አብረንና ተባብረን ለፍትህ” እንታገል፤ መድረሻችን ኢትዮጵያ ናት” የሚል የተቀደሰ መርህ ይከተላል። ፋኖ በራሱ ፈቃድ የሚታገለው ለተቀደሰ ዓላማ ነው። ለግል ዝናና ጥቅም አይደለም። ይኼውም አንድ፤ የአማራውን ሕዝብ ከእልቂት ለማዳን፤ ሁለት ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ለመታደግ።

ፋኖን የቀሰቀስው ምንድን ነው?  

- በአማራው ላይ የማያባራ እልቂት መካሄዱና መቀጠሉ፤

 

- በመንግሥት ደረጃ ባለፉት ሰላሳ ሁሉት ዓመታት አማራው ከፖልቲካው፤ ከኢኮኖሚው፤ ከማህበረሰባዊ እድገቱ፤ ከእምነቱ እንዲወገድ፤ ማንነቱና መለያዎቹ ሁሉ እንዲጠፉ መደረጉ፤

 

- በአማራው ሕዝብ ላይ የሚዘገንን የስም፤ የታሪክና የባህል ማጥፋት ዘመቻዎች በህወሃት መራሹና በኦነግ ወይንም በኦሮሞ ብልፅግና አገዛዝ መካሄዱ፤ “ነፍጠኛ፤ ትቢተኛ፤ ጡት ቆራጭ፤ ቅኝ ገዢ” ወዘተ። ይህ የስነ ልቦና ጦርነት አማራውን ጭራቃዊ ሕዝብ አድርጎታል።

 

- በዘመነ ዐብይ መንግሥት፤ ከላይ የጠቀስኳቸው ተባብሰዋል። ረገጣው፤ አፈናው፤ ግድያው፤ ማፈናቀሉና ውድመቱ የሚካሄደው በመንግሥት ደረጃ ነው። ይህ የዐብይን መንግሥት ከሌሎች አምባገነኖች ይለየዋል።

 

- በህወሃት የብሄር ጽንፈኞችና ሽብርተኞች በወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምትና ራያ የተፈጸመው የአማራ ሕዝብ ጭፍጨፋና ከቀየው መባረር በባሰ ደረጃ በወለጋ፤ ኦሮምያ፤ በቤኒ-ሻንግሉ ጉሙዝ፤ በሰሜን ሸውና በአዲስ አበባ ዙሪያ ባለፉት አመስት አመታት ሲካሄድ ቆይቷል፤ አሁንም እየተካሄደ ነው። ከጀርባው ማን አለበት?

 

- የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአማራው ሕዝብ ላይ የሚካሄደውን ጭካኔ የተሞላበት እልቂትና እስራት አላቆመውም፤ ሊያቆመውም አይችልም። ሕገ መንግሥቱ የተመሰረተው ሕዝብን ከሕዝብ በመለያየት ነው።

 

- “አማራው ትግል የጀመረው ግዛትን ለማስፋፋት ነው” የሚለው ፈጠራ አይሰራም። አማራው በሚኖርበት አካባቢ እየተጨፈጨፈ እንዴት በመስፋፋት ይከሰሳል? በአማራው ክልል ላይ የሚዘገንን ጦርነት እየተካሄደና አንጹህ ወገኖቻችን በድሮን፤ በሞርታር፤ በታንክና ሌላ ከባድ መሳሪያ በዐብይ መንግሥት ትእዛዝ እየተጨፈጨፉ አማራው በግዛት መስፋፋት እንዴት ይከሰሳል። የግዛት መስፋፋት ስራን የሚሰራው የኦነባዊያን፤ የኦሮሞ ልዩ ኃይልና የፌደራሉ ባለሥልጣንት መሆናቸው በመሬት ላይ እየታየ ለፍትህ የሚታገለው የአማራ ሕዝብ ለምን ይከሰሳል? አጥፊው ከሳሽ፤ ተበዳዩ ተከሳሽ የሆነባት አገር ኢትዮጵያ ናት።

 

- ባለፉት ሰላሳ ሁለት ዓመታት፤ በትምህርት፤ በጤና አገልግሎት፤ በመሰረተ ልማት፤ በነፍስ ወከፍ ገቢ የአማራው ክልልና ሕዝብ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆናቸውን አልጀዚራ ባቀረበው ዘገባ ላይ ለማየት ይቻላል።

 

- ህወሃት ሥልጣን  ከያዘበት ጀምሮ የአማራው ሕዝብ ቁጥር እየቀነሰ ሂዷል። አማራው እስከ ስድስት ሚልየን የሚገመት ህዝብ አጥቷል። ይህ ሕዝብ የት ሄደ? ማርስ? ብየ የጠየቅሁበት ትንተና ትዝ ይለኛል።

 

- በ2019 ዩኤስ ኤድ (USAID) የአማራው ሕዝብ ቁጥር፤ ባልታወቀ ምክንያት መቀነሱን አረጋግጧል። የቀነሰብት  ምክንያት የጤን አገልግሎት ስለ ተነፈገው ነው? የአማራ ሴቶች እንዳይወልዱ ስለ ተደረገ ነው? በየቦታው በሚካሄደው የአማራ ብሄር ተኮር እልቂ ስለተካሄደ ነው? በኦሮምያ የሚኖሩ ከአስራ አንድ ሚልየን በላይ የሚገመቱ አማራዎች ማንነታቸውን እንዲክዱ ስለተደረገ ነው? ይህ ሰፊ ጥናትና ምርምር ይጠይቃል። አሁንም የሚካሄደው ጦርነት የአማራው ቁጥር ከመቀነስ ጋር የተያያዘ ነው የሚል እምነት አለኝ።

ለፋኖ እንቅስቃሴ መሰረታዊ የሆኑት ምክንያቶች ከላይ የተጠቀሱት ናቸው። ምክንያቶቹ ትግሉ የህልውና ትግል መሆኑን ያረጋግጣሉ። አማራው የሚጠይቀው አስኳል ጉዳይ የሥልጣን ሳይሆን የፍትህ ጥያቄ ሆኖ ሳለ ባለፉት ሰላሳ ሁለት ዓመታት ስላልተፈታና እንዲውም እየተባባሰ ስለሄደ ነው።

አጠናክሬ ለማሳሰብ የምፈልገው፤ ፋኖ የሚከተላቸው እሴቶችና የመጨረሻ ተልእኮው ያለ ከፍተኛ መስዋእት ስኬታማ ሊሆኑ አይችሉም። ፍትህ፤ ነጻነት፤ እኩልነት ዋጋ ሳይከፈል ስኬታማ የሆነበት አገር የለም። ፍትህ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጥያቄ ነው። ያለ ፍትህ “መደመር” እና ልማት አይታሰብም። ያለ አገር ወዳድነትና ፍትህ የአገር ዳር ድንበር አይከበርም። ያለ ፍትህ ሌላው ቀርቶ ከቤት ለስራ ወጥቶ በጤና፤ በሰላም ወደ ቤት ተመልሶ መግባት ብርቅ ሆኗል። የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ህይዎት ማጤን ይጠቅማል። ለዚህ ነው፤ የአዲስ አበባ ሕዝብ “በቃን” የሚልበት ወቅት አሁን ነው የምለው።

እትዮጵያ ወደ የት እያመራች ነው?

ኢትዮጵያ ዛሬ በሁሉም ዘርፎች የተበከለች አገር ናት። አቅጣጫዋ አያምርም። ኢትዮጵያ ወድቃለች ወይንስ አልወደቀችም? በሚል ብዙ ውይይት ይካሄዳል። አንድ አገር ወዳድ ወዳጀ በቅርቡ ያሉትን ምሳሌ ላድርግ። “እኔ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነቴ እንደ አሁኑ አፍሬ አላውቅም።” ያሳፈረን የሚዋዢቀው አመራርና ስርዓቱ ነው። ያሳፈረን የዐብይ ብልጽግና ፓርቲና መንግሥት ነው። ኢትዮጵያ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቷን ለመገምገም፤ በመሬት ላይ ያለው ሃቅ መነገር አለበት።

ዛሬ ኢትዮጵያ የእልቂትና የጦርነት እምብርት ሆናለች። የድህነት እምብርት ሆናለች። ወጣቱ ትውልድ የስራ እድል የለውም። ሰላሳ አንድ ሚልየን ሕዝብ ይራባል። አምስት ሚልየን ሕዝብ ተፈናቅሏል። መካከለኝ መደብ ተብለው የሚጠሩት ኑሯቸውን ለማሟላት አልቻሉም። የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሺፈት አብዛኛውን ሕዝብ በክሎታል። ይህ ብቻ አይደለም።

ከሜያዝያ ወዲህ ብቻ ከመቶ ሽህ በላይ አማራዎች ታስረዋል። ብዙ ሽህ የሚገመት ኦሮሞ ታስሯል። በጦርነቱ በድሮንና ሌላ ከባድ መሳሪያ የተጨፈጨፈው በቅጡ አይታወቅም።   ይባሰውን ብሎ ዐብይ አሕመድና ፊልድ ማርሻል  ብርሃኑ ጁላ ከወዳጅ አገር የኬሚካል መሳሪያ አስገብተዋል የሚል ዘገባ ተሰራጭቱል። ይህ እብድነት ከተካሄደ ዐብይ አሕመድ ሁለተኛው ግራዚያኒ ሆኗል ማለት ነው። ባጠቃላይ ስገመግመው ግን፤ “ኢትዮጵያ የእስር ቤትና የረሃብተኛ ሲዖል አገር ሆናለች” ቢባል ትክክል ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ አሊ የሚመራው የኦነጋዊያን መንግሥት ከአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተጣልቷል ለማለት እደፍራለሁ። ይህ አገዛዝ የሚክደው ሃቅ አንድ ነው። የፈለገውን ያህል የጦር መሳሪያ ቢያከማች፤ የጦር ትርኢት ቢያሳይ፤ ከሕዝብ ጋር የተጣላ መንግሥት ብዙ ዋጋ ማስከፈሉ ባይቀርም ቅሉ፤ ህይዎቱ ግን አጭር መሆኑን ነው። የደርግ መንግሥት ምሳሌ ነው። የወያኔ ማንግሥት ሌላው ምሳሌ ነው። ክፍ አድርጌ ስገመግመው፤ ዓለምን በበላይነት አሸከረክራለሁ ብሎ የሚፎከረው የአሜሪካ መንግሥት ከአፍጋኒስታን ተሸንፎ የወጣው ሌላ ምሳሌ ነው። ሕዝብ የናቀው፤ የማያምነውና የማያከብረው መንግሥት ይወድቃል።

የፕሪቶሪያው ስምምነት ምን አወንታዊ ውጤት አስገኘ?

የአሜሪካ ባለሥልጣናት፤ የዐብይ አሕመድ መንግስትና ህወሃት ለኢትዮጵያና ለመላው ዓለም ሕዝብ የሰጡት ማዘናጊያ መልእክት ህወሃት መሳሪውን ይፈታል የሚል ነበር። ህወሃት ትጥቅ አልፈታም። ህወሃትና የኢትዮጵያ መንግሥት ትጥቅ ለፈቱትና በጦርነቱ ለተጎዱት የአፋር፤ የአማራና የትግራይ ወገኖቻችን የቁሳቁስ ድጋፍ አልሰጡም። እንዲያውም የሰብአዊ እርዳታውን ነጥቀውታል፤ ስርቀውታል፤ ለራሳቸው ቡድኖች አውለውታል።

ህወሃት ትጥቅ ያልፈታበት ዋና ምክንያት ወይንም ምስጥሪ ምንድን ነው?

ዐብይ አሕመድ ከጅምሩም ህወሃት ትጥቅ እንዲፈታ አልፈለገም። ዋናው ትኩረቱ አማራውን በሁሉም ዘርፎች አምክኖ፤ አምበርክኮ፤  ቢቻል ጨፍጭፎ የኦሮሙማን አጀንዳ ስኬታማ ማድረግ ስለሆነ ህወሃትን እንደ ስትራተጂክ አጋር ሲጠቀምበት ይታያል። በተጨማሪ፤  ለህወሃት ምን አይነት የውስጥ ቃል ኪዳን ተነግሮታል? ብለን መጠየቅ አለብን። ታዛቢዎችና የውስጥ አዋቂዎች እንደሚሉትና እኔም እንደ ገመገምኩት፤ የዐብይ መንግሥትና የአማራው ብልጽግና የበላይ ካድሬዎች ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምትንና ራያን በሬፈረንደም አመካኝተው ለህወሃት ለመመለስ ተመሳጥረዋል። ካልተማማሉ ለወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠልመትና ራያ ህዝብ የማንነትና የሰባዊ መብት መከበር ጥያቄ፤ አወንታዊ መልስ ሊሰጡ ይገባል።

ጦርነቱ የተካሄደው ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ናት በሚል እምነት ነው። ዐብይ ለኢትዮጵየ “እቀላለሁ” ሲል ሰምቻለሁ። ይህ ከሆነ ኦነጋዊያን በበላይነት የሚመሩት የኢትዮጵ ፌደራል መንግሥት ሰራዊት ለምን መቀሌ አልገባም? የትግራይ ሕዝብ መብት ተከብሮ  ለምን የራሱን የሺግግር መንግሥት ለመምረጥ እንዲችል አልተደረገም? ዓብይ ሥልጣኑን እንዲያዝ ያመቻቸው ሕዝቡን ሳይሆን ለሱ ሥልጣንና የበላይነት ሊያገለግል ይችላል ብሎ ያመነንበትን አዲስ አገልጋይና ታዝዥ ህወሃትን ነው። ዐብይ ሁልጊዜም የሚኮተኩተውና ሥልጣን እንዲይዝ ጫና የሚያደርገው በታዛዢነቱ፤ በታማኝነቱ፤ በአገልጋይነቱ፤ በሆዳምነቱ የማያሻማውን ክፍል ብቻ ነው። በአማራው ክልል ስንት ፕሬዝደንት ተቀይሯል?” እነ ዶክተር አምባቸው መኮነንና ጀኔራል አሳምነው ጽጌ በምን ምክንያት ሞቱ? ማን ከጀርባ ሆኖ አስገደላቸው ወይንም እርስ በእርሳቸው እንዲገዳደሉ አደረገ? ሃቁ ይፋ የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይመስለኝም።

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከጽንሰ ሃሳቡ የተወላገደና የተጎዱቱን ክፍሎች የማይወክል ነው። አግላይ ነው። እርቅና ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ የአፋር፤ የአማራና የኤርትራ ተወካዮች ተሳታፊ መሆን ነበረባቸው። ቢሳተፉ ኖሮ ስምምነቱን የማስፈጸም ግዴታ ይኖርባቸው ነበር። አለተሳተፉም፤ ግዴታ የለባቸውም ማለት ነው።

በህወሃትና በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ጦር ኃይል መካከል የሚካሄደው ጦርነት መቆሙ ሃቅ ነው። ይህንን በተናጥል ስናየው ስኬት ልንለው እንችላለን። ሆኖም፤ የፕሪቶሪያው ስምምነት ዘላቂ እርቅና ሰላም አስገኝቷል ለማለት አልችልም።

የዐብይ ኦነጋዊያን መንግሥት ዋና ግቡ ኦሮሙማን መምስረት ነው። ኦሮሙማ ግን የእምቧይ ካብ መሆኑ አይቀርም። የአብይን አጀንዳ የሚቃወሙ ኦሮሞች፤ ጋሞዎች፤ ጉራጌዎች፤ ደቡቦች፤ አኟኮች፤ ትግሬዎች ወዘተ አሉ። እነዚህ ወገኖቻችን ቀስ በቀስ ፋኖ መሰል እንቅስቃሴና ሕዝባዊ እምቢተኛነት እንደሚቀሰቅሱ አምናለሁ። ጋሞውና ደቡቡ እኮ ፋኖን እየመረቀ ነው። ይህ የሆነበት ዋና ምክንያት፤ ፋኖ መንፈስ ስለሆነ፤ ፋኖ የነጻነት ተምሳሌት ስለሆነ፤ ፋኖ አገር ወዳድ ስለሆነ፤ ፋኖ የአማራው ሕዝብ የሚፈልገውና የሚታገለው፤ ፍትሃዊ፤ ህብረብሄራዊና ዲሞክራሳዊ የሆነች ኢትዮጵያን ለመመሰረት ስለሆነ ነው።

ፋኖ የሚታገለው ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይና ኦነጋዊያን ኢትዮጵያን በዓለም ደረጃ ስላዋረዷትና ዐብይ ጠቅላይ ሚንስትር ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ በበጎ ነገር ስትጠቀስ የሰማ ሰው ስለሌለ ጭምር ነው።

በህወሓት አመራርና በዐቢይ አህመድ መካከል የተካሄደው የፕሪቶሪያ ስምምነት በሕዝቦች መካከል እርቅና ሰላምን አስገኝቷል ለማለት አይቻልም። የወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠልምትና ራያ የማንነት ጥያቄ አሁንም አልተፈታም። የትግራይ ሕዝብ ሮሮ ድምጽ እላገኘም። በሃላፊነት ለፍርድ የቀረበ የለም። የትግራይ ሕዝብ አሁንም ይታፈኗል፤ ይዘረፋል፤ ይራባል። የትግራይ እናቶች በሃዘን ላይ ናቸው። መዘዙ ለብዙ አስርት ዓመታት የሚቆይ ነው።

አሁንም እኔ የምጠይቀው፤ ጦርነቱ ለምን ተካሄደ? ለምን ብሄራዊ አላማ? ለማን ጥቅም? በጦርነቱ ለረገፉት ወገኖቻችን ተጠያቂው ማነው? የወደመውን ኢኮኖሚ ማን መልሶ እንዲያንሰራራ ያደርገዋል? ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ በማድረግ ፋንታ ለምን ጠቅላይ ሚንስትሩ የቅንጦት ቤተ መንግሥት በ 15 ቢልየን ዶላር ይሰራል? የፓርላማው ሃላፊነት ከምን ላይ ነው?

የዐብይ ስሌት የዜጎች መብት መከበር አይደለም። ስሌቱ አማራውና ትግራዩ እርስ በእርሱ እንዲዋጋና እንዲመክን ማድረግ ነው። ይህ ሲሆን የኦሮሞ ዘውጋዊ የበላይነት ስር ይሰዳል የሚል ስሌት ነው።

ከህወሃት ጋር የተካሄደውን የሚዘገንን የእርስ በእርስ ጦርነት እንደ ምእራፍ አንድ ብናየው፤ ምእራፍ ሁለት ህወሃትን የተካው የዐብይ አህመድ አሊ ብልጽግና በበላይነት የሚያሽከረክረው የኦህዴድ መንግሥት በአማራው ሕዝብ ላይ የሚያካሂደው እልቂት፤ ውድመትና አገር አፍራሺ ዘመቻ ነው።

ይህ ዘመቻ ግን ይከሽፋል። ምክንያቱም፤ ህወሃትም ሆነ ኦነጋዊያን አማራውን ለይተው ማሳደድና መጨፍጨፍ የጀመሩት ባለፉት አስርት ዓመታት ስለሆነ፤ አማራው ከዚህ አማራ ጠል ከሆነ እብሪተኛ፤ ዘረኛና ዘግናኝ ስርዓት ትምህርት ተገኝቷል። አማራው ከአሁን በኋላ እንደ ፈለጋችሁ “ልጀን፤ ሚስቴን፤ እህቴን፤ እናቴን፤ አባቴን፤ ቤቴን፤ መሬቴን፤ ክብሬን፤ ማንነቴን፤ ኃይማኖቴን” ወዘተ ልታመክኑ አልፈቅድም ብሎ ዳር እሰክ ዳር ተነስቷል።

ይህ እብሪተኛነት ይከሽፋል ያልኩበትን ምክንያቶች ላቅርብ፤

- የትግራይ ሕዝብፈቅዶና ተስማምቶ ወደ ሌላ ጦርነት ይሄዳል የሚል እምነት የለኝም። በተለይ፤ እንዳለፈው በፍላጎትና በስሜት ከአፋሩና ከአማራው ሕዝብ ጋር መዋጋት ከጥቅሙ ኪሳራው ያይላል የሚሉት ብዙ ናቸው። ይህ ማለት እብሪተኞችና ጠባብ ብሄርተኞች ለሌላ ጦርነት አልተዘጋጁም ማለት አይደለም። በአማራውና በትግራዩ ሕዝብ መካከል የተከሰተው ችግር በውይይት፤ በድርድር፤ በመቻቻል፤ በጋራ ጥቅም ሊፈታ ይችላልል። አማራጩ ጦርነት ሊሆን አይችልም።

- የአማራው ሕዝብ የሚታገለው ፈልጎና መርጦ አይደለም። በአንድነት ሆኖ በመዋጋት ላይ የሚገኘው በኦህዴድ እብሪተኞችና ተተኪዎች ጸረ-አማራ ጦርነት የህልውና ጉዳይ ስለ ሆነ ነው። ዝንጀሮ መጀመሪያ መቀመጫየን እንዳለችው ሁሉ፤ የመጀመሪይው የአማራው ትኩረት ራሱን ከእልቂት ማዳን ነው። በአንድነት ከመታገል ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም። በውጭ የሚኖረው አማራ በአንድነት፤ ለአንድ ዓላማ ከመስራት ውጭ ሌላ አማራጭ ሊኖረው አይገባም።

- የኢትዮጱያ ዳር ድንበር ፈተና ውስጥ ገብቷል። በጋምቤላና በምእራብ ሰሜን ጎንደር የኢትዮጵያ ድንበር ተጥሷል። የዐብይ ሰራዊት ትኩረት አማራውን ማንበርከክ ስለሆነ ዳር ድንበሩን ለማስከበር ችሎታውም፤ ብቃቱም፤ ፈቃደኛነቱም አይታይም። የመሳሪያ ትርኢት በተደጋጋሚ ማሳየትና የአገርን ዳር ድንበር ማስከበር የተለያዩ ክስተቾች ሆነዋል። ይህ ትርኢት ፋኖውንና የኤርትራን መንግሥት መጣንብህ፤ ወዮልህ፤ ለማለት ሆኖ አየዋለሁ። የኢትዮጵያን ሕዝብ ከጎረቤት አገር ጋር፤ በተለይ ከኤርትራ ጋር ወደ ሌላ ጦርነት እንዲገባ ቀይ ባህርን፤ ወደብን ምክንያት አድርጎ መስበካን ማቅረብ እጂግ የተሳሳተና አደገኛ ሴራ ሆኖ አገኘዋለሁ።

- በወለጋ፤ በቤኒ-ሻኑል ጉሙዝ፤ በሰሜን ሸዋና በአዲስ አበባ ዙሪያ በአማራው ላይ የሚካሄደው እልቂትና መፈናቀል ቀጥሏል። ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት የኦነጋዊዉ የዐብይ መንግሥት፤ የኦሮምያ ክልል ባለሥልጣናት ተባባሪ ስለሆኑ ጭምር ነው። እኔ ኦነግ ሸኔን ከኦነግ ሰራዊት፤ ከፌደራሉ መንግሥት ስራዊት፤ ከኦሮሞ ክልል ሰራዊት ለመለየት አልችልም።

- በዐብይ መንግሥት ደረጃ የተቀነባበረው የኦሮሙማ አጀንዳ አቀንቃኝና ጽንፈኛ ኃይል በመናበብ በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ፤ በተለይ በአማራው ላይ ትኩረት አድርጎ እልቂት (Genocide) እያካሄደ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ሰብአዊ መብት ካውንስል፤ የዋናው ጸሃፊ ልዩ አማካሪ፤ ሌምኪን (Lemkin Institute for the Prevention of Genocide) እልቂቱ እንደ ተፈጸመና የከፋ እልቂት እንደሚከሰት አስጠንቅቀዋል።

- የዐብይ መንግሥት ባለሥልጣናት፤ የአዲስ አበባ ከተማን ከንቲባን ጨሞሮ የአማራ ሕዝብ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ በተደጋጋሚ እገባ አድርገዋል።

- የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት የዜጎችን ደህንነት፤ ነጻነትና መብት በማስከበር ፋንታ፤ ዐብይ አሕመድ አሊ የሚመራው መንግሥት ራሱ ሽብርተኛ መሆኑ በዓለም ደረጃ ያልተከሰተ ሁኔታ ፈጥሯል።

በዚህ ትንተና፤ ሽብርተኛ ምን ማለት እንደሆነ ልጥቀስ። “አንድን የማህበረሰብ ክፍል ለይቶ በዘውግ፤ በዘር፤ በሃይማኖት፤ በፖለቲካ አመለካከትና ተዛማጅ ምክንያቶች ይህንን ሕዝብ እንዲጠቃ ማመቻቸት፤ ያልሰራውን ግፍ ሰርቷል ብሎ ማዋከብ፤ ማሰር፤ ማንገላታት፤ ከቀየውና ከስራው ማባረር፤ ሕግን አስከብራለሁ በሚል ሰበብ በተራው ሕዝብና በመሪዎቹ ላይ እልቂት ማካሄድ፤ መብቱን ሁሉ መግፈፍ፤ ንብረቱን ማውደም፤ ፍትህ ሲጠይቅ የሌለ መረጃና ሃሰተኛ ምስክሮችን እያቀረቡ ክሱ እንዲጸድቅ ጫና ማድረግ” የሚሉትን ይጨምራል። የዐብይ መንንግሥት በአማራው ላይ የሚያካሂደው የሚዘገንን ግፍና በደል ይኼው ነው። ሌላው ቀርቶ በአገሪቱ ሕገ መንግሥትና የፓርላማ መመሪያ መብታቸው መከበር ያለባቸውን አማራዎች አስሯል።

የዐብይ መንግሥት ሽብርተኛ መንግሥት ነው የምለው ለዚህ ነው። መስፈርቱን ያሟላል። ተጠያቂነት የለም።

- በኦሮሞ እሬቻ በዓል ለአማራውና ለአገር ወዳዱ ሌላው ኢትዮጵያዊ የተከለከለው ባንዲራና ሌላ የኢትዮጵያዊነት መለያ ተከልክሎ፤ ለሬቻው ግን አዲስ አበባ በኦሮሞ ባንዲራ እንድታሸበርቅ ተደርጓል። ይህ ፍጹም የሆነ የተተኪነትና የበላይነት ተምሳሌት ነው።

ለዚህ ነው፤ ፋኖ እንቅስቃሴውን በማካሄድ ላይ የሚገኘው። እንጂኔር ግደይ “እኔም ፋኖ ነኝ” በሚል የብዙውን ታዳሚ አድናቆት ያገኘው። “አዲስ አበባ ኼኛ፤ የኦሮሞ ባንዲራ ኼኛ” ወዘተ የሚያሳየው ሃቅ አንድ ነው። ፍጹም የሆነ የአንድ ዘውግ የበላይነት። ይህ የበላይነት ጉዞ ስኬታማ ቢሆን ምን ይከሰታል? ብለን መጠየቅ አለብን። በኔ ግምገማ የኦሮሙ ጽንፈኞች፤ ብሄርተኞችና አሸባሪዎች የበላይነቱን ከያዙ ወላይታው፤ ጋሞው፤ አኟኩ፤ ጉራጌው፤ ሶማሌው፤ አፋሩ፤ ትግራዩ፤  አማራው ወዘተ ይዋጣል፤ ማንንነቱ ሙሉ በሙሉ ይወድማል።

የወደፊቱን በሚመለከት ባጠቃላይ ለማለት የምችለው፤ የዘውግ፤ የቋንቋና የዘር ፖለቲካ እስካልተቀየረ ድረስ እንኳን አገራዊ ልማት ቀርቶ፤ ኢትዮጵያ ሰላምና እርጋት አይኖራትም። ለዚህ ነው፤ የአሁኑ ሕገ መንግሥት፤ የአገዛዝ ስርዓት፤ ተቋማትና መዋቅሮች ሙሉ በሙሉ መፍረስና የዜጎችችን ሉዐላዊነት በሚያንጸባርቅ ስርአትና እውነተኛ የሆነ የፌደራል መንግሥት አወቃቀር መቀየር አለባቸው የምለው።

ፋኖ ትጥቅ እንዲይዝ የተገደደበት መሰረታዊ ምክንያት አማራው የመኖር አለመኖር ወይንም የህልውና አደጋ ስለ ተጋረጠበት ነው። በአንድ በኩል ፋኖን ትጥቅ ማስፈታት፤ በሌላ በኩል የኦሮሞን ልዩ ኃይል ማጠናከርና እስክ አፍንጫው ማስታጠቅ፤ ዝነኛውን የኢትዮጵያን መከላከያ በኦሮሞ ጀኔራሎች የበላይነት ማዋቀር ኢትዮጵያን ከድጡ ወደ ማጡ አሸጋግሯታል።

ሁሉም ለኢትዮጵያ ዘላቂነት፤ ለመላው ሕዝቧ ደህንነት፤ ለፍትህና ለእኩልነት፤ ለዲሞክራሳዊ ስርኣት እታገለለሁ የሚል “ፋኖን መሰል” እንቅስቃሴዎች እንዲያብቡ ድርሻውን ማበርከት አለበት። የኢትዮጵያንና የዓለምን ሕዝብ አድናቆት ያገኘው ፋኖ ሕግን፤ ስርዓትን፤ ጨዋነትን፤ እኩልነትን፤ ሰብአዊነትን፤ ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን ያስተጋባል። በተጻራሪው ግን፤ የኦሮሙማን አጀንዳ የሚያስተጋቡት ጽንፈኞች የሚመሩት ፍጹም በሆነ፤ ጊዜ ባለፈበት፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን በማይመጥንና በማይወክል የፖለቲካ ፍልስፍና ነው።

ለፍትህ ቆመናል ካልን የፋኖን ትግል መደገፍ ብቻ ሳይሆን፤ ፋኖ መሰል እንቅስቃሴዎች በመላው ኢትዮጵያ እንዲያብቡ የማድረግ ግዴታ አለብን። ፋኖ ለምን አላማ ቁሟልና ነው እንደዚህ የምትለው? ለሚለው ጥያቄ የሚከተሉትን አቀርባለሁ

ይህ እንዳለ ሆኖ እኔን እጅግ ያሳሰበኝ ጉዳይ የዐብይ ባለሥልጣናት፤ ኦነጋዊያን፤ የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ ወዘተ በተደጋጋሚ ጦርነቱን በአማራና በኦሮሞ መካክል ነው የሚል ትርክት ማሰራጨታቸው ነው። የአማራ ገበሬ ወደ ኦሮሞያ ክልል ገብቶ ኦሮሞ አልጨፈጨፈም። የኦሮሞ ገበሬ ወደ ጎንደር ሂዶ አማራውን አልጨፈጨፈም። በዘመነ ዐብይ አህመድ አሊ ያለትጎዳ የሕዝብ ክፍል የለም። ለምን ይህንን ሃቅ አይናገሩም? ሕዝብ ለመቀስቀስና ዐብይ ለኦሮሞ ሕዝብ ታጋይ ነው ለማለት ሆኖ አየዋለሁ። የኢትዮጵያ መንግሥት አለ ለማለት የማልችለውም ለዚህ ነው።

ለማጠቃለል፤

- የዐብይ ኦነጋዊያን መንግሥት አሸባሪ መንንግሥት ነው። ይህንን ሃቅ ሳንሰለች ለመላው ዓለም ሕዝብ ማሰራጨትና ማሳመን  አለብን።

 

- በፋኖውና በኦህዴድ ጦር ሰራዊት መካከል የሚካሄደው የሚዘገንን ጦርነት እንዲያከትም ለማመቻቸት ከተፈለገ ሰራዊቱ ሙሉ በሙሉ ከአማራው ክልል መውጣት አለበት። በዐብይ መንግሥት የሚካሄድው ጦረነት ማቆም አለበት።

 

- በአማራው ሕዝብና በኦነጋዊያን መንግሥት መካከል እርቅና ሰላምን ለማመቻቸት ወይንም በሩን ለመክፈት ከተፈለገ ከመቶ ሽህ በላይ የሚገመተው የአማራ ፖለቲካ እስረኛ ሳይውል ሳያድር መፈታት አለበት።

 

- አማራ ያልሆኑ “ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች” ለራሳቸው ደህንነት ሲሉ ፋኖ መሰል ተቋማትን መመስረት አለባቸው።

 

- “ኼኛ፤ የኛ” የሚለው የኦሮሞ ፖለቲካ ልሂቃንና ስብስቦች የበላይነት የጭፍን ጉዞ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን አያዋጣም፤ ቀጠናውን ሙሉ በሙሉ ወደ አላስፈላጊ እልቂ ያመራዋል።

 

- ፋኖ ሁሉን ያማከለ፤ ግልጽነት ያለውና ዲሞክራቲክ የሆነ ተቋምና ፍኖተ ካርታ መመስረት አለበት። ይኼ እኔ ብቻ የምመክረው አይደለም። ፋኖን የሚደግፉ ሁሉ ግለስቦችና ስብስቦች የሚለግሱት አግባብ ያለው ምክረ ሃሳብ ነው።

 

- ፋኖን በረባ ባልረባ ምክንያት፤ በአማራው ስም ሰበብ አድርጎ መከፋፈል መቆም አለበት። ለፋኖ  የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ ሁሉ በአንድ ቋት ገብቶ ፋኖ በአንድነት በሚያምንበት መንገድ መላክ አለበት።

 

- በውጭ አገር የፋኖው አመራር እና ተቋም የሚያምኑበት፤ የሚያምኑባት አንድ ቃል አቀባይ አይስፈልገዋል። ይህ ክፍተት በአስቸኳይ መሰራት አለበት።

 

- የፋኖን ታጋዮች፤ ደጋፊዎችና መሪዎች የምመክራቸው በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ለአንድ ዓላማና ለአንድ ተልእኮ በአንድነት እንዲሰሩ ነው። “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” የሚለው የብልሆች ምክርን መተግበር ወሳኝ ሆኗል።

 

- ለፋኖ ምክር የሚሰጡ በአገር ቤት ሆነ በውጭ የሚኖሩ ምሁራን የፋኖው እንቅስቃሴ የመጨረሻ ግቡ ኢትዮጵያ ስለሆነች፤ ፍኖተ ካርታው ሁሉን አቀፍ እንዲሆን ቀን ከሌት መስራት ይኖርብናል።

 

- ፋኖና ደጋፊዎቹ ጊዚዊ የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት ጥሪ ማድረግ አለባቸው። ይህ ጊዚያዊ መንግሥት ሁሉን ኢትዮጵያዊያን ወይንም ባለድሻዎች የሚውክል መሆን አለበት። ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የማህረሰብ ድርጅቶች፤ አገር ወዳድ ምሁራን በአንድነት ድርሻቸውን እንዲወጡ አደራ እላለሁ።

 

October 27, 2023
https://amharic-zehabesha.com/archives/186793

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...