Thursday, September 7, 2023

የመከራና የውርደት አዙሪቱን ሰብሮ ለመዉጣት የተሳነው እኛነታችንና እንዴትነታችን
September 2, 2023

T.G   

በቅድሚያ የሁልጊዜም እምነቴ የሆነውን ሃሳቤን ግልፅ ላድርግ።  በሂሳዊ አስተያየቴ ላይ ጥንቃቄ የማደርገው  ስለ ሰዎች የግል ሰብእና፣ አመለካከት ፣ እምነት፣ ህይወት ላይ ያነጣጠረ  እንዳይሆን ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ግን እንኳንስ አገራዊ በሆኑ ግዙፍ ጉዳዮች በማናቸውም የጋራ ትኩረት በሚሹ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚነሳ ሃሳብንና አካሄድን በተመለከተ ስንነጋገር አካፋን አካፋ ማለት በሚያስችል አቋምና ቁመና ደረጃ መሆን አለበት ።  ከዚህ ውጭ ያለው ወይም ሊኖር የሚችለው አስተሳሰብና አካሄድ ፈፅሞ የትም አያደርሰንም። ስለ ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊነት እውን መሆን የምንመኘው ምኞትም ከባዶ ምኞትነት ፈፅሞ አያልፍም። ይህንን የመሠረታዊ እሳቤ እጥረት ከምር ተረድቶ የጎደለውን ለማሟላት የማይተጋ የመንፈሳዊም ሆነ ዓለማዊ የትምህርት ደረጃ፣ የእድሜ ባለፀጋነት፣ የሃይማኖታዊውም ሆነ የዓለማዊው የሥልጣን ደረጃ ፣ የዚህና የዚያ ሙያ ባለሙያነት ፣ ወዘተ ፈፅሞ እውነተኛ ትርጉም የለውም።  አዎ! የአስተሳሰባችንና የአካሄዳችን መለኪያ (መመዘኛ)  በገሃዱ ዓለም እየሆነ ወይም እየተደረገ ያለው መሪር እውነታ እና ይህንኑ በአግባቡ ተረድተን ወደ ተግባራዊ ሃይል  ለመተርጎም  በምናቀርበው የመፍትሄ ሃሳብ መሠረት ካልሆነ ስለ እውነተኛ የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት ያለን ግንዛቤና እምነት በግልብ ስሜትና ምኞት ላይ የተንጠለጠለ ነው የሚሆነው።

 ይህ አይነት የኮሰመነ አስተሳሰብና አካሄድ ደግሞ ከእኩያን ገዥዎችና ግብረ በላዎቻቸው አልፎ የሃይማኖታዊ እምነት መሪዎችና አስተማሪዎች ልክፍት ሲሆን የሚያደርሰው አሉታዊ ተፅዕኖ በእጅጉ አስቀያሚ ነው።

አዎ! ፆምና ፀሎት የምድራዊውና ተስፋ የምናደርገው ሰማያዊ ህይወት በተቻለ መጠን የሰመረ ግንኙነት ይኖራቸው ዘንድ የሰራነውን ስህተት የምናርምበት ፣ መወጣት ያለብንን ሃላፊነት ሁሉ ለመወጣት ቃል የምንገባት እና ይህንንም  ፈጣሪ እንዲባርክልን (የተቃና እንዲያደርግልን) የምንማፀንበት እንጅ ፈጣሪ የሰጠንን ረቂቅ የማሰቢያ አእምሮና ብቁ የማከናወኛ አካል አቅመ ቢስ (ሰነፍ) እያደረግን እግዚኦ የማለት ጉዳይ አይደለም።

አዎ! በእውነት ከተነጋገርን የገዛ ራሳችንን መሪር እውነታ ከመጋፈጥና ወደ ትክክለኛው ፍኖተ ጉዞ (ፍኖተ ህይወት) ከመመለስ ይልቅ የሰበብ ድሪቶ በመደረት ባለንበት መርገጥ ብቻ ሳይሆን በአስደንጋጭ ሁኔታ ወደ ኋላ እየወደቅን የቀጠልንበት መሪር ምክንያት ይኸው ነው።

ባለፈው የፆመ ፍልሰታ ወቅት በየሚዲያው እና በየቤተ እምነቱ ይካሄድ የነበረው የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች ስብከት (ትምህርት) እና ቃለ ምልልስ ወይም የሃሳብ ልውውጥ ለዘመናት ከዘለቀውና ከአምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ እንኳን ለማመን ለማሰብም በሚከብድ አኳኋን ከቀጠለው የእኩያን ገዥዎች የመከራና የውርደት ሥርዓት መሪር እውነታ አንፃር ሲመዘን ምን ያህል ትርጉም  እንደነበረው ወይም እንዳልነበረው በሚገባ የተከታተለ ባለ ሚዛናዊና ባለ ቅን ልቦና የአገሬ ሰው ምነው ምን ነካን? የሚል እጅግ ከባድ ጥያቄ ሳይፈጥርበት የሚቀር አይመስለኝም።

በፈጣሪ አምሳል ተፈጠረ ብለን የምናምንለት የሰው ልጅ (የአገራችን ህዝብ) የገዛ አገሩና ቀየው ምድረ ሲኦል ሲሆኑበት እኩያን ገዥዎችን ለመገሰፅ ወኔ አጥቶ በጅምላ ሰበካና ባዶ በሆነ (ከእውነታው ጋር መዋሃድ ያልቻለ) የሰላምና የፍቅር ስብከት የተጠመደን የሃይማኖት መሪና አስተማሪ ለምንና እንዴት? ብሎ መጠየቅን እንደ ኩነኔ (መርገምት) የሚቆጥር ትውልድ ካለ ስለ ምን አይነት የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት እንደሚናፍቅ ለመረዳት በእጅጉ ይከብዳል።

ስለ ተወለዱበት ፣ ስለ አደጉበትና ለአሁኑ ምንነታቸው ስለ አበቃቸው መከረኛ ህዝብ መከራና ውርደት ቢያንስ ትርጉም ያለው የምሬት ድምፅ (ጩኸት) ለማሰማት የሞራል ወኔው ጨርሶ የከዳቸው የዚህ ትውልድ አባላት በኮሜዲያንነት ወይም በአርቲስትነት ወይም በሃይማኖት ሰባኪነት ወይም በሌላ የሙያና የተሰጥኦ መስክ ታዋቂነትን በሁሉም ነገር ታዋቂና ሁሉን ነገር አዋቂ እንደመሆን በመቁጠር አጉል ቅዠት ውስጥ ሲርመጠመጡ አደብ ግዙ ማለት የግድ ነው።

ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ እንደ ኮሚዲያን እሸቱና ሌሎች  የዚህ ትውልድ አባላት በፆመ ፍልሰታው ወቅትም ስለ መከረኛው ህዝብ መከራና ስቃይ የረባ ድምፅ ሳያሰሙ በየቤተ እምነቱ እየዞሩ የቪዲዮ ምስል እያዘጋጁና እያቀነባበሩ ሰባኪም፣ አስቀዳሽም ፣ ቀዳሽም፣ ሰዓታት ቋሚም፣ ቅኔ አውራጅም ፣ ስለምህረትና አማላጅነት አዋቂዎችም ፣ እግዚኦ በሉ ባዮችም ፣ወዘተ ሆነው የመታየታቸው ተውኔት የሚነግረን  ከሁለንተናዊ የውድቀት አዙሪታችን ሰብሮ ለመውጣት የሚጠብቀን ትግል (ፈተና) በእጅጉ ከባድና ውስብስብ መሆኑን ነው።  ያዩትንና የሰሙትን ሁሉ እየቃረሙ አንዱንም በቅጡ ሳይረዱ ፣ አጥብቀው ሳይዙ እና ለፍሬ ሳያበቁ የመቅረት ክፉ አባዜ! 

ለዘመናት የዘለቀውን የሁለንተናዊ መከራና ውርደት ሥርዓት እንኳንስ ለማመን ለማሰብ በሚያስቸግር ሁኔታ እያስኬዱት ባሉት እጅግ ባለጌ፣ ፈሪና ጨካኝ ኦነጋዊያን/ ኦሮሙማዊያን /ብልፅግናዊያን/ ኢህአዴጋዊያን ምክንያት የመቃብርና የቁም ሞት ሰለባ በሆነው ወገን (ህዝብ) ውስጥ እየኖሩ በሰላም ፣ በፍትህና በነፃነት ፣ በድሎት ፣ ወዘተ ለመኖር በታደለ ማህበረ ውስጥ የሚኖሩ እስኪመስል ድረስ በኮሜዲያንነት እና በሃይማኖታዊ እምነት ስም የማህበራዊ ሚዲያ ንግድ ማጧጧፍ ሌላው ቢቀር የሞራል ኮስማናነት ነው። እንኳንስ እውነተኛውን ፈጣሪ ጤናማ ህሊና ያለውን ሰው ህሊናንም በእጅጉ ይኮሰኩሳል!!!

በህዝብ መከራና ዋይታ መነገድ ምን የሚሉት አዝናኝነት እና ክርስቶሳዊነት እንደሆነ እንኳን ለማመን ለማሰብም ይከብዳል!

እያልኩ ያለሁት ሁሉም ነገር ቆሞ እንላቀስ ሳይሆን በዚህ ለመግለፅ በሚያስቸግር ሁኔታ ውስጥ ከሚኖር ህዝብ ጋር እየኖሩ በተገኘው ጊዜና አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም በእኩያን ገዥዎች ላይ ለመቆጣት እና መከረኛው ህዝብ እንደ ሰው ሰው ሆኖ ይኖር ዘንድ የሚያካሄደውን ተጋድሎ ለማበረታት ቢያንስ የሞራል ወኔ የሌላቸውን የዚህ ትውልድ አባላት አደብ ግዙ ማለት ከትክክል በላይ ትክክል ነውና ይህንኑ ሆነንና አድርገን እንገኘ ነው!

በጣም የሚረብሸው ጉዳይ ደግሞ እነዚህ በግልና በቡድን ጥቅምና ዝና ፍለጋ ናላቸው የዞረ የዚህ ትውልድ አባላት በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በባህር ማዶም በየቤተ እምነቱ እየዞሩ የገዳም መሬት ግዥና ግንባታ የመከረኛውን ህዝብ ህይወት ከመታደግ የበለጠ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሻ ጉዳይ እያስመሰሉ  “ዶላሩን ጣጣል ካላደረጋችሁ የመንግተ ሰማያት በር እላያችሁ ላይ  ይከረቸማል” በሚል እውነተኛውን ፈጣሪ ጨምረው የሃይማኖት ነጋዴነታቸው (merchants of religion) ተባባሪ ማድረጋቸው ነው።

እናም በእንዲህ አይነት እጅግ አሳሳች ዘመቻ ላይ የተጠመዱትን አባላቱን አደብ ይገዙ ዘንድ በግልፅና በቀጥታ “አደብ ግዙ” ለማለት የማይደፍር ትውልድ እንዴትና መቸ ከገባበት የሁለንተናዊ ውድቀት ሊወጣ እንደሚችል ለመገመት ይከብዳል። እናም ልብ ይሰጠን!

ሌላው በእጅጉ ሊያሳስበን የሚገባው ጉዳይ የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎችም የዚሁ እጅግ ቅጡን ያጣ የሚዲያ ላይ ተውኔት ተዋንያን የመሆናቸው መሪር እውነት ነው።

ምን?ለምን? እንዴት? በማንና ለማን? መቸና እስከመቸ? ከየት ወደየት? ወዘተ የሚሉ የአንድን ጉዳይ ወይም ነገር መሠረታዊ እሳቤዎች፣ ባህሪያትና እሴቶች ለመመርመር እና ለዘመናት የመከራ ቀንበር ተሸካሚ ሆኖ የኖረውንና ከምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለማመን ቀርቶ ለማሰብ በሚከብድ መከራና ውርደት ውስጥ የሚገኘውን ወገናቸውን (የአገገራቸውን ህዝብ) ለመታደግ የሚያስችል ተጋድሎ ከማድረግ ይልቅ በሃይማኖት መሪነትና አስተማሪነት ፣ በኮሜዲያንነት ፣ በአክቲቪስትነት፣ በአርቲስትነት ፣ ወዘተ ስም የሚነግዱትን ወገኖች "አደብ ግዙ" ለማለት የሞራል ልዕልና የሚጎድለው  ትውልድ የተሻለ ነገንና ከነገ ወዲያን የመመኘቱ ጉዳይ ከቀን ቅዠትነት አያልፍም!

አዎ! ሃይማኖታዊ እምነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የሰውን ሥሥ ስሜት የሚያሸንፉ (የሚስቡ) ርዕሰ ጉዳዮችን እየመረጡ በማቀናበርና በማቅረብ ልክ የለሽ በሆነ የግልና የቡድን ፍላጎትና ዝና ፍለጋና ማርኪያ ዘመቻ ላይ ለተሰማሩና ለሚሠማሩ ወገኖች በየአደባባዩ፣ በየአዳራሹ፣እና በየማህበራዊ ሚዲያው የሚያጨበጭብንና አቅሉን (ማሰቢያውን) እያጣ ያለን ትውልድ ትክክለኛና አስተማማኝ መዳረሻ ለማወቅ በእጅጉ ያዳግታል!!!

ባዶ ስብከትን (በድርጊት የማይተረጎም የስብከት ጋጋታን) ባርኮ የሚቀበል እውነተኛ ፈጣሪ የለምና በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን እነዚህ ወገኖች ወደ ትክክለኛው ፍኖተ ሃይማኖት እና ሞራላዊ ልዕልና ይመለሱ ዘንድ በግልፅና በቀጥታ መንገርና መነጋገር  የመፍትሄ ፍለጋው አካል ነውና ፈፅሞ ልንሸሸው አይገባም።

እውነተኛው ክርስቶስ ያስተማረው ጎስቋሎች ወደ የሚገኙበት ሥፍራ ሁሉ በመዘዋወር፣ ጨካኝ ገዥዎችን "ህዝቤን ልቀቁ" ብሎ በመገሰፅ፣ የመከረኛውን ህዝብ መከራ በመካፈል፣ እና በመጨረሻም የቁም ስቃይ በመቀበልና በመስቀል ላይ በመሰቀል እውነተኛ ፍቅርና ሰላም ሊያስከፍሉት የሚችሉትን የማይተመን ዋጋ በመክፈል እንጅ እንደ ዛሬዎቹ የእኛ ሰባኪዎች በተመቻቸ ቤተ እምነት ፣ አዳራሽ ፣ አደባባይ፣ መገናኛ ብዙሃን ፣  ወዘተ ላይ ሆኖ አልነበረም!

እያልኩ ያለሁት ዘመኑ ያፈራውንና ያቀረበውን የመገናኛ ዘዴ አንጠቀም ሳይሆን ለእውነተኛና ለትክክለኛ ተልእኮና ዓላማ ሳይሆን በአብዛኛው እጅግ ልክ ለሌለው የግልና የቡድን ፍላጎትና ጥቅም (ንግድ/ቁማር) ነውና ከምር እያሰብንና ንስሃ እየገባን ወደ ትክክለኛው ፍኖተ ለውጥና እድገት እንመለስ ነው።

የገዛ አገሩ፣ ቀየው፣ ቤተ እምነቱ ፣ ወዘተ ወደ ሲኦልነት እንዲለወጡ ስለተደረጉበት መከራኛ ህዝብ ሲሆን በአካል በመገኘት ለማፅናናት ቢያንስ ግን በየአስትምህሮቱና በሌላም አጋጣሚ እኩይ ገዥዎችን ለመገሰፅ እና  የነፃነት ተጋድሎን ለማገዝ  ፈፅሞ ወኔው የከዳው የሃይማኖት መሪነት፣ አስተማሪነት (ሰባኪነት)፣ ሊቅና ሊቃውንትነት፣ ሊቀ ጠበብትነት፣ መጋቢነት ፣ዶክተርነት፣ ፕሮፌሰርነት ፣ ወዘተ እንደማነኛውም የሙያ መስክ ከተቻለ በእጅጉ የተደላደለ ቢያንስ ደግሞ ከመከረኛው ህዝብ በእጅጉ የተሻለ ኑሮ ለመኖር ከማስቻል ያለፈ ዓላማና ግብ የለውም። ።

ለዚህም ነው እንኳን መከራውን ለመካፈል ስለ መከራው ለመናገር እና የመከራው ዋነኛ ምክንያቶች የሆኑትን እኩያን ገዥዎች ለመገሰፅ ወኔው የሚሳነው የሃይማኖት መሪና አስተማሪ   የሚያዥጎደጉደውን ስብከት ፣ ቅኔ፣ ዝማሬ፧ ቅዳሴ፣ ፀሎት፣ ፆም፣ እግዚኦታ ፣ትንቢት እንኳንስ የሚባርክ ለመስማትም  የሚፈልግ እውነተኛ አምላክ የለም ብሎ መናገር የፅድቅ እንጅ የመርገምት መንገድ የማይሆነው ።

ከአብዛኛዎቹ የሃይማኖት መሪዎች ፣ ሰባኪዎች፣ ሊቆች፣ ሊቀ ሊቃውንት፣ ወዘተ እየታዘብነው ያለው እጅግ መሪሩ እውነታ ግን ይኸው ድርጊት አልባ (ባዶ) መነባንብ (ስብከት) መሆኑን ለመረዳት የማይችል ወይም የማይፈልግ በተለይ ፊደል የቆጠረው የማህበረሰብ አካል ቁጥሩ ቀላል አይደለምና ህሊናውን  መመርመር ይኖርበታል!

በእኔ እምነት የምናስበውና የምናከብረው የፆምም ሆነ ሌላ ሃይማኖታዊ ወቅት መከረኛው ህዝብ ከሥርዓት ወለድ የመከራና የውርደት ዶፍ ሰለባነት እንዴትና መቼ መገላገል እንደሚኖርበት በጥሞና  የምናስብበት፣ ለዚሁ ተግባራዊነት ድምፃችንን ከፍ አድርገን የምናሰማበት፣ እኩይ ገዥዎችን የምንገስፅበት ፣ የህዝብን የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ በአግባቡ የምናበረታታበት፣ ካስፈለገም ራሳችንን ለመስዋእትነት አሳልፈን ለመስጠት ቃል የምንገባበት፣ ትክክለኛና ፍትሃዊ በሆነ የጠረጴዛ ዙሪያ ድርድር እውነተኛ ሰላም እውን ይሆን ዘንድ ግፊት የምናደርግበት፣ እና ይህ ሁሉ በጎ እሳቤና ጥረት የፈጣሪ በረከት እንዳይለየው የምንማፀንበት እንጅ ከእህልና ውሃ በመታቀባችን እና ድርጊት አልባ እግዚኦታ በማስተጋባታችን የገነትን ቁልፍ የምንረከብበት አጋጣሚ ፈፅሞ አይደለም ።

መቼም የገዛ ራሳችንን መሪር እውነታ በአርበኝነት መንፈስ ለመጋፈጥ ወኔው እያጠረን በመቸገራችን ነው እንጅ በዚህ ረገድ ያለብን ጎደሎነት በእጅጉ አሳሳቢና አስፈሪ ነው። ባሳለፍነው ፆመ ፍልሰታ የታዘብነውም ይህንኑ መሪር ሃቅ ነው።

በየአብያተ ክርስቲያኑ፣ በየአደባባዩ እና በየሚዲያው በተደረጉ አብዛኛዎቹ ስብከቶች ውስጥ በፖለቲካ ሥርዓት ብልሹነትና ወንጀለኛነት ምክንያት መግለፅ የሚያስቸገር የመከራና የውርደት ዶፍ ሰለባ ስለሆነው መከረኛ ህዝብ ከምር የሆነ ያገባናል ባይነትና ቁጣ ለማግኘት አለመቻልላችን እና ባለጌና ጨካኝ ገዥዎችን በአግባቡ የመገሰፅ የሞራል  ልዕልና ለማየት አለመታደላችን አልበቃ ያለ ይመስል የእኩይ  ገዥዎችን በሸፍጥና በሴራ  የተበከለ “የሰላም ይውረድ” መልእክት ለማስፈፀም የክርስቶስን መስቀል ይዘው  “መኖሪያ ስታሳጡንና ስትገድሉን ቆሞ ማየቱ በቃን” በሚል  ራሱን በመከላከል ላይ ወደሚገኘው መከረኛ ህዝብ ያለሃፍረት የተጎዙ የሃይማኖት ሰዎችንም ታዝበናል።

እናም ከዚህ አይነት እጅግ አስቀያሚና አስከፊ ሁኔታ ትክክለኛው መውጫ መንገድ ለምድሩም ሆነ ተስፋ ለምናደርገው ከሞት በኋላ ህይወት ዋስትና እንዳይኖረን ያደረገን እና በአስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓት እንደ ሥርዓት አስወግደን  በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መተካት ብቻ ነው። እንዲህም ሲሆን ነው የሃይማኖትና የሌላም ሙያ ነጋዴነት ደዌን ከነሰንኮፉ መቀል የሚቻለው ።

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/185647

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...