Tuesday, August 1, 2023
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ነሐሴ 1፤ 2023
Yonas
Allow me to disagree on the impact of Western intervention. I believe it was “nefarious”. The West first hoped that the TPLF would emerge victorious. When the expectation crashed, it reverted to all kinds of pressure to rescue the TPLF. Because of this, we have the major problem of Welkait and other claimed territories.
Hi Messay,
Thank you. The role the international community plays is positive there is no nefarious intention behind it. However, the US system is such that both local and international policies are influenced by lobbyists. Our hermitized and quite frankly stupefied intellectual class failed to play by the rules of international engagement.
እናንተ ሁለት ምሁራን፣ ፕሮፈሰር መሳይ ከበደና ዶ/ር ዮናስ ብሩ ብዙ ወጣቶችን እያሳሳታችሁ ነው። ካፒታሊዝምና በተለይም ኢምፔሪያሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰለሚጫወቱት አሊታዊ ሚና፣ ወይም ደግሞ እያንዳንዱ አገር ትንሽም ሆነ ትልቅ ራሱን እንዳይችል በተለያየ መልክ የሚሰራውን ሴራ አይ በፍጹም አልገባችሁም፣ አሊያም ደግሞ አውቃችሁ እያሳሳታችሁ ነው። በዚህ አካሄዳችሁ እንደ ኢትዮጵያ የመሰለችን አገር ወደ ውስጥ ነፃ የሆነ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተና፣ ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅም ኢኮኖሚ እንዳይገነባ ነው የምትታገሉት። ከአራት ዓመት በፊት ባወጣሁት ጽሁፌ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ጠንካራ ኢኮኖሚ የሌላት አገር በራሱ የሚተማመንና ፈጣሪ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል ለመፍጠር እንደማትችል ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አንድ አገር በማኑፋክቸሪንግ ወይም በመሺን ኢንዱስትሪ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ከሌላት ከፖለቲካ አንፃር እየተወዛገበች እንደምትኖር ነው። ምክንያቱም አንድን ህዝብ የሚያስተሳስረው በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረተ ውሰጠ-ኃይሉ ጠንካራ የሆነ ኢኮኖሚ ሲኖር ብቻ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በአንድ አገር ውስጥ በስፋት የተዘረጋ ተቋማት(Institution) ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። በሰለጠነ የሰው ኃይል በሚመራና ሰፋ ብሎ በተዘረጋ ተቋማት አማካይነት ብቻ ነው በአንድ አገር ውስጥ ያሉ የጥሬ-ሀብቶችና የሰው ጉልበት በስራ ላይ በመሰማራት አገርን በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት የሚቻለው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ከሌሎች ነገሮች ጋር በመዳመር ነው ለካፒሊዝም ዕድገት አመቺ ሁኔታን ሊፈጥር የቻለው። በአጭሩ፣ መንደሮችና ከተማዎች ስርዓት ባለው መልክ ሳይገነቡ፣ እነዚህ ደግሞ በተለያዩ የመመላለሻ ዘዴዎችና መንገዶች ካልተገናኙ፣ ተቋማት በየቦታው ካልተገነቡ፣ ለሰፊው ህዝብ የትምህርት መስጫ መስኮች ካልተዘረጉና፣ በየጊዜው ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅሱና በሁለ-ገብ የአገር ግንባታ ውስጥ ሊሳተፉ የሚችሉ ኃይሎችን እያሰለጠኑ ማቅረብ ካልተቻለ ስለካፒታሊዝም ሆነ ስለ አንዳች ዐይነት የኢኮኖሚ ዕድገት በፍጹም ማውራት አይቻልም።
ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ ግሎባል ካፒታሊዝም ወይም ኢምፔሪያሊዝም በሁሉም አገሮች ውስጥ ጠንካራ ኢኮኖሚና የሰለጠነ ተቋማት እንዲዘረጋ በፍጹም አይፈልጉም። ምክንያቱም አንድ አገር በተሟላ መልክ ካደገች ተወዳዳሪ ለመሆን ትችላለች ብለው ስለሚያስቡና፣ ከዚህም በላይ በተከታታይ የጥሬ-ሀብት ሳይፈበረክ ለማግኘት ስለማይችሉ በተቻለ መጠን እንደ ኢትዮጵያ ባለው አገር ውስጥ አይ የማያቋርጥ ውዝግብ እንዲኖር የተቻላቸውን ያደርጋሉ፤ አሊያም ደግሞ ለነሱ አጎብዳጅ የሆነ አገዛዝ ስልጣን ላይ በማስቀመጥ ጠቅላላውን ህዝብ ሞራሉን በማደሸቅ እጁን አንስቶ አገሩን ለውጭ ኃይል እንዲሸጥ ያደርጋሉ። በተለይም በነፃ ገበያ ስም የሚካሄደው አሻጥር አንድን አገር በዕዳ ከመተብተብና፣ ያልተሰተካክለ የንግድ ሚዛን እንዲፈጠር ከማድረግ ባሻገር፣ የብልግና ኢንዱስትሪ በማስፋፋት የሰፊውን ህዝብ ሞራል በማድቀቅ አቅጣጫውን እንዲስት ማድረግ ነው። በዚህም ምክንያት ነው ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ የብልግና ኢንዱስትሪ የተስፋፋውና፣ የግብረ-ሰዶማዊነት ባህል በአገዛዝ ደረጃ ዕውቅና የተሰጠው። ሰሞኑን አምስተርዳም ከተማ ውስጥ ተቀማጭነታቸው በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች በሆኑ ኢትዮጵያውያን በተዘጋጀ የኳስ ዝግጅት ላይ ተገኝቼ ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከሲያትል/ አሜሪካ የመጡ የበሰለ አስተሳሰብ ካላቸው ሁለት ኢትዮጵያውያን ጋር ተገናኝቼ ነበር። ሰለ አሜሪካን ፖለቲካ ጠይቄያቸው የሰጡኝ መልስ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው። በተለይም ዲሞክራቶች የሚሰሩት ስራ በጣም የሚያሳዝን ነው ብለው ነው የነገሩኝ። ይኸውም፣ በየትምህርትቤቱ በወንድና በሴቶች መሀከል ስላለው ግኑኝነት፣ ስለ ግብረ-ሰዶማዊነትና፣ እንዲሁም ስለ ትራንስ-ጀንደር ለህፃናት በትምህርት መልክ እንደሚሰጥ ነው። ይህም እንዳስፈራቸውና ምን እንደሚያደርጉ ግራ እንደገባቸው ነግረውኛል። እንደሚታወቀው አሜሪካ ሁለት የፓርቲ ሲስተም ብቻ ነው ያለው። ዲሞክራቲክና ሪፓብሊካን ፓርቲ ብቻ ነው። እንደነገሩኝ ከሆነ በሚቀጥለው ምርጫ ትረምፕ የመወዳደር ዕድል ካለው እሱንና ፓርቲውን እንደሚመርጡ ነው የነገሩኝ። ቀድሞ በባራክ ኦባማ፣ አሁን ደግሞ በባይደን አስተዳደር የሚመራው አገዛዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በተለይም በአፍሪካ ምድር ውስጥ ግብረ-ሰዶማዊነት እንዲስፋፋ ከፍተኛ ግፊት እያደረጉ ነው። የዩጋንዳው አገዛዝ ይህንን እንደማይቀበል በህግ መልክ አረጋግጧል።
ወደ አገራችን የተመሰቃቀለው ሁኔታ እንምጣ። በተለይም ዮናስ ብሩ እንደሚለንና ሊያሳምነን እንደሚሞክረው በኢትዮጵያ የምዕራቡ ካፒታሊዝም ጣልቃ-ገብነት ከበስተጀርባው ምንም ተንኮል የለውም በማለት ከሳይንስ ውጭ የሆነ አስተሳሰቡን እንድንቀበለው ለማድረግ እየሞከረ ነው። ሳይንሳዊ ዘዴ አንድን ተጨባጭ ሁኔታን፣ የህብረተሰብ አወቃቀርን፣ የፖለቲካ ሁኔታን፣ የኢኮኖሚ ሁኔታን፣ የስነ-ልቦና ሁኔታን...ወዘተ. በማየትና በመመርመር ሰፋ ያለ ትንተና የምንሰጥበት ዘዴ ነው። በሳይንሳዊ ዘዴም ብቻ ነው በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ በተለያየ መልክ የሚገለጹ የተበላሹ ሁኔታዎችን ማንበብና ምክንያቶቻቸውን ለመናገር የሚቻለው። ምክንያቶቻቸው በደንብ የሚታወቁ ከሆነ ደግሞ አነሰም በዛም መፍትሄ ለመስጠት ይቻላል። በሌላ ወገን ደግሞ ሳይንሳዊ አቀራረብ የሚመስል በመሰረቱ ከፕሌቶን ጀምሮ፣ እስከ ላይብኒዝ፣ ሄገልና ካንት፣ እንዲሁም ሌሎች ታላላቅ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች የተቀበሉትና ትክክልም የሆነውን የሚቃወም ፖዘቲቭ ሳይንስ ወይም ኤምሪሲዝም የሚባል አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን ያገኘ አሳሳች አካሄድ አለ። በዚህ ዐይነቱ የተጣመመ ወይም ኢ-ሳይንሳዊ አስተሳሰብ በነገሮች መሀከል መተሳሰር የለም፤ ወይም አንደኛው ነገር በሌላኛው ላይ ተፅዕኖ አይኖረውም የሚል ነው። ለምሳሌ በፖለቲካ ሁኔታ፣ በመንግስታዊ አወቃቀርና በሰለጠነ የሰው ኃይልና፣ በሌላ ወገን ደግሞ በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና ዕድገት መሀከል ምንም ግኑኝነት የለም። ሁሉም ነገር እንደተሰጠ(as given) ነው መወሰድ የለበት። በተለይም የፖለቲካ፣ የመንግስት የጥገና ለውጥና የተቋማት ግንባታ አያስፈልግም ነው የሚለን; ይህንን ኢ-ሳይንሳዊ ፀረ-ሁለገብ ዘዴ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ የሚያራምዱት አሣሰብ ነው። አንድ አገር የራሷን መንገድ ከመረጠችና ሰፊውን ህዝብ በማንቀሳቀስ አገር ለመገንባት ደፋ ቀና በምትልበት ጊዜ ቀጥተኛ ጦርነት ይታወጅባታል።
ወደ ተጨባጩ የአገራችን ሁኔታዎች ስንመጣ አፄ ኃይለስላሴ ከስደት ሲመለሱ ዋናው ወዳጃቸው አድርገው የመረጡት የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊዝም ነው። ለዚህም አንድ ጋሻ መሬት ያህል ተሰጥቶት ኤምባሲውን እንዲገነባና ሰላይ ኃይሎችን ለማሰልጠን የቻለው። ጠቅላላው የቢሮክራሲው መዋቅርና ቢሮክራሲውን የሚቆጣጠሩት፣ ከሲቪሉ እስከ ፀጥታውና እስከ ወታደሩ ድረስ የተገነቡት በአሜሪካን “የአሰራር”አስተሳሰብ ነው። ለዚህም ነው ወደ ውስጥ ራሱን የቻለና በንቃት የሚያስብ የህብረተሰብ ክፍል ሊዳብር ያልቻለው። ሰለሆነም ስንኩል በሆነ መልክ የሰለጠነው ቢሮክራሲያዊ አወቃቀርና አገዛዙ ቢያንስ ለካፒታሊዝም ዕድገት የሚያመች ሁለ-ገብ መሰረት ለመጣል አልቻሉም። በዚህም ምክንያት ነው የየካቱቱ አብዮት ለመፈንዳት የቻለው። አፄ ኃይለስላሴ ከስልጣን ላይ እስከተወገዱበት ጊዜ ድረስ በአገሪቱ ውስጥ ያልተስተካከለ ዕድገት በሁሉም አቅጣጫ ይታይ ነበር። በተለይም በአዲስ አበባና በተቀሩት ክፍለ-ሀገራት ከተሞች መሀከል ከፍተኛ ልዩነት ይታይ ነበር፤ አሁንም ይታያል። እንደዚሁም በገጠሩ ነዋሪ ህዝብና በከተማው ነዋሪ ህዝብ መሀክል ከፍተኛ ልዩነት ይታይ ነበር። ይህንን ሁኔታ በአብዮቱ ወቅት በጥገናዊ ለውጥ ለማስተካከል ቢሞከርም፣ በአንድ በኩል የተለያዩ ቡድኖች ከፖለቲካ አንፃር የበሰለ አስተሳሰባ ስላልነበራቸው ያመሩት ወደ ርስ በርስ መጋጨት ላይ ነው። በተለይም በአሜሪካ የስለላ ጉያ ስር የወደቀው የተወሰነው የግራ ኃይል ነኝ ባዩ፣ የሲቪልና የሚሊታሪ እንዲሁም የፀጥታው ቢሮክራሲው ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር በማበር አጠቃላይ ጦርነት ነው በህዝባችንና በአገራችን ላይ ያወጁት። በጊዜው በቀይና በነጭ ሽብር ተሳቦ የተካሄደው የርስ በርስ መተላለቅ የአሜሪካኑ የስለላ ድርጅት እጅ እንደነበረበት የሚታወቅ ጉዳይ ነው። አሜሪካ በዚህ ብቻ ሳታበቃ ሶማሊያን በማስታጠቅና ሻቢያን በመደገፍ በደርግ አገዛዝ ላይ ጦርነት እንዲቀሰቅሱ አደረገ። ወያኔንም በመደገፍ ለዛሪዩት የተመሰቃቀለና ለፋሺሽታዊ አገዛዝ አመቺ ሁኔታ ፈጠረ። በሌላ አነጋገር፣ አፄ ኃይለስላሴ ስልጣን ላይ እንደገና ከወጡ ጀምሮ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ለተወሰነ ጊዜ ካልሆነ በስተቀር የኢትዮጵያ ሁኔታ ወይም የፖለቲካው፣ የኢኮኖሚው፣ የማህበራዊው፣ የባህሉና የስነ-ልቦናው ሁኔታ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር በጥብቅ የተቆላለፈ ነው ማለት ይቻላል። በተለይም የላይኛው የህብረተሰብ ክፍልና የንዑስ ከበርቴው መደብ ዕድላቸውንና ዕጣቸውን ከአሜሪካን ኢምፔርያሊዝም ጋር ነው ያቆላለፉት።
ይህ የውስጥና የውጭ ኃይሎች መቆላለፍና በጥቅም መተሳሰር የመጨረሻ መጨረሻ የአገራችንን ውድቀት አፋጥኖታል ማለት ይቻላል። ከ90% በመቶ በላይ የሚሆነው የብሮክራሲውና የቴክኖክራቱ ኃይል ንቃተ-ህሊናው ከዜሮ በታች በመሆኑ በምሁራዊ ኃይል ሁኔታዎችን፣ በተለይም የአሜሪካንንና የግብረ-አበሮቹን አሻጥር የማንበብ ችሎታ አልነበረውም፤ አሁንም የለውም። ዋናው ነገር በተጣመረ መልክ አስፈሪውን ጉግ ማንጉግን ወም ክሙኒስታዊ ስርዓትን መዋጋትና፣ ለጠንካራ ኢኮኖሚና ለብሄራዊ ነፃነት የሚታገሉ ኃይሎችን ማሳደድና መግደል ነው። አሜሪካን በስለላ ድርጅቱ አማካይነት የኢትዮጵያን የስለላ ድርጅት ካፈራረሰው በኋላ ወታደሩ ከወያኔና ከሻቢያ የሚመጣበትን ግፊት ለመቋቋም ያልቻለውም በዚህ ምክንያት ነው። በርዕዮተ-ዓለም ወይም በአንዳች ፍልስፍና መሰረትና ውስጣዊ ጥንካሬ ያልተገነባው የደርግ አገዛዝ መፈረካከስ ጀመረ። በአጭሩ ደርግ ከአፄው የወረሰው ቢሮክራሲያዊው አስተዳደር የአገራችንን ልዑላዊነት ለማስጠበቅ ተሳነው። በአብዮቱ ወቅት አሜሪካኖች ለኢትዮጵያ ቢሮክራቶች “ቃል-ኪዳን የገቡላቸው” የነበረው “ደርግን ጣሉልንና ኢትዮጵያን እንደ ደቡብ ኮሪያ እናደርግላችኋለን “ በማለት ነበር የሚያታልሏቸው። በመሰረቱ ግን እንደዚህ ሲሉ ደርግ ከወደቀ በኋላ ኢትዮጵያን እናፈረካክሳታለን ማለታቸው ነው፤ አዲስና ሁኔታዎችን በሚገባ ማየት የማይችል ኃይል በመፍጠር ኢትዮጵያችሁን እንደፈለግን እናሽከረክራታለን ማለታቸው ነበር። የኋላ ኋላም ይህንን ዐይነቱን ወርቃማ ዕድል ነው አሜሪካ ለማግኘት የቻለችው።
ወያኔንና ሻቢያን ስልጣን ላይ ሲያወጡ የጎሳ ፌደራሊዝም ተግባራዊ እንዲሆን በማስገደድና የኒዎ-ሊበራሊዝም የኢኮኖሚ “ፖሊሲን” ተግባራዊ እንዲሆን ጫና በማድረግ ነው። የጎሳ ፌዴራሊዝምም ጉዳይ በለንደኑ ስብሰባ ኸርማን ኮኸን በተገኘበት የተመከረበትና በወያኔም ተቀባይነት እንዲኖረው የተደረገበት ጉዳይ ነው። ይህም ማለት ለግለሰባዊ መብት፣ ለሊበራሊዝም አስተሳሰብና ለነፃ ገበያ እታገላለሁ የሚለው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረ-አበሮች በአገራችን ምድር የታሪክን ሂደት በማጣመም ነው የጎሳ ፌዴራሊዝም ተቀባይነት እንዲኖረውና እንዲተገበርም ለማድረግ የበቁት። ይህ ዐይነቱ አካሄድ በአገራችን ምድር ከረጅም ጊዜ አንፃር ሲታይ ህብረተሰባዊ ውዝግብን እንደሚያስተክል የታወቀ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ በየክልሉ የዎር-ሎርድ ሜንታሊቲ በመዳበር ውስጣዊ ወይም አገራዊ ጥንካሬ እንዳይኖር የሚያደርግ ነው። ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለተቋማት ግንባታም የሚያመች ሁኔታ አይደለም። ይህንን ዐይነቱን አወቃቀር በመጠቀም ነው ወያኔ ከአላሙዲንና በመዋዕለ-ነዋይ ስም ከሚመጡ የውጭ ከበርቴዎች ጋር በመመሳጠር ነው የአገሪቱን ሀብት መዝረፍ የተቻለው። በማኑፋክቸሪንግ ላይ ከመሰማራት ይልቅ የአበባ ተከላና የሆቴል ቤቶችን መስራት ነው እንደፈሊጥ የተያዘው። አንድ በሳይንሳዊ ኢኮኖሚ የሰለጠነ ሰው የሚገነዘበው ነገር የአንድ አገር ኢኮኖሚ አበባን በመትከልና ሆቴል ቤቶችን በመስራት ለሰፊው ህዝብ የስራ መስክ መክፈት እንደማይቻል ነው። ከዚህም ባሻገር አነስተኛና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች በማቋቋም ርስ በርሱ የተያያዘ ኢኮኖሚ መገንባት በፍጹም እንደማይቻል ሳይንሳዊና ታሪካዊ ኢኮኖሚ ያስገነዝቡናል። የዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ፣ ሌሎች የውጭ ኢክስፐርቶች ነን የሚሉት ሁሉ ወያኔና አገዛዙን፤ እንዲሁም በቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ውስጥ ያሉትን የንዑስ ከበርቴ ኃይሎች በተሳሳተ መልክ በማማከር ነው ሰፊውን ህዝባችንን ወደ ድህነት ዓለም እንዲገፈተር ያደረጉት። በካፒታሊዝም ዕድገት ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ በተደጋጋሚ የገንዘብ ቅነሳ(Devaluation) እንዲደረግ በማድረግ ነው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እንዲፈጠር ለማድረግ የበቁት። የአንድ አገር ገንዘብ አርቲፊሻል በሆነ መልክ እንዲቀንስ ከተደረገ የግዴታ ገንዘቡ የመግዛት ኃይል ይቀንሳል። በተለይም ከውጭ የመለዋወጫ ዕቃዎችንና የጥሬ.-ሀብቶችን የሚያስመጡ የአገር ውስጥ አምራቾች በዶላር ስለሚገዙ አንድ ዶላር ለመግዛት በደርግ ጊዜ ከነበረው ምንዛሪ ሁኔታ በወያኔና አሁንም በአቢይ የአገዛዝ ዘመን በብዙ እጥፍ የሚቆጠር የኢትዮጵያን ብር ማቅረብ ስላለባቸው ይህ ዐይነቱ የገንዘበ ልውውጥ የግዴታ በምርት ዋጋ ላይ (Production Cost) ከፍተኛ ጭማሪ ይኖረዋል። ይህም ማለት፣ አንድ ምርት ተመርቶ ገበያ ላይ ወጥቶ በሚሸጥበት ጊዜ የግዴታ የዋጋ ግሽበትን ያስከትላል። ከዚህ ባሻገር ከአገሪቱ የኢኮኖሚ መሰረት ጋር የማይመጣጠኑ ባለ አምስትና ባለ ሰባት ኮከብ ሆቴል ቤቶች በሚሰሩበት ጊዜ ሆቴል ቤቶቹ ለሰፊው ህዝብ የሚቀርቡ ሪሶርሶችን፣ ማለትም እንደ በርበሬ፣ ሚጥሚጣ፣ ዘይትና ቅቤ፣ ስጋና ሌሎች የእህል ዐይነቶችን ስለሚጋሩ በገበያው ላይ ክፈተኛ የዋጋ ግሽበት እንዲፈጠር ምክንያት ለመሆን በቅተዋል። በተለይም በአዲስ አበባ ውስጥ በየጊዜው የሚከሰተው የመብራት መቋረጥና የንፁህ ውሃ እጥረት ዋናው ምክንያት ትላልቅ ሆቴልቤቶችና ሌሎች ህንፃዎች ሲሰሩ ከእነሱ ጋር የሚመጣጠን፣ በተለይም ለሰፊው ህዝብ ሊዳረስ የሚችል ሰፋ ያለ የውሃ ገንዳና የመብራት ስርጭት ኃይል ለመዘርጋት አለመቻሉ ነው። ለማለት የምፈልገው፣ በአጠቃላይ ሲታይ ወያኔ ከዕውቀት ማነስ የተነሳ ተገዶ ተግባራዊ ያደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ራሱን ቢጠቅመውምና ሀብትም ለመዝረፍ አመቺ ሁኔታን ቢያገኝም፣ አገሪቱንና ህዝባችንን መቀመቅ ውስጥ ነው የከተታቸው። ይህ ዐይነቱ የምዕራቡ ካፒታሊስት አገሮች ጣልቃ-ገብነትና ወያኔን አስገድዶ ይህ ዐይነቱ ከሳይንስ ውጭ የሆነ፣ ወይም በካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ግንባታ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በአገራችን ምድር ተግባራዊ እንዲሆን ማስገደድ ዋናው ምክንያትና ዓላማው አገራችንና ህዝባችን ጠንካራ አገርና ባህል እንዳይገነቡ ለማድረግ ታስቦ ነው። ከዚህ ውጭ ማሰብ ኃጢአት ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ወንጀልም እንደመስራት የሚቆጥር ነው።
ወደ ጦርነቱ ስንመጣ፣ በመሰረቱ ወያኔም ሆነ አሁን ደግሞ የአቢይ አገዛዝ በህዝባችን፣ በተለይም በአማራው ላይ የሚያካሂዱት ጦርነት የአሜሪካንን አገርን የሚያፈራርስ ወይም የሚበታትን ጦርነት ነው። በሌላ አነጋገር፣ የውክልና ጦርነት ነው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳና፣ በተለይም የኢምፔሪያሊዝምን አገሮችን የማፈራረስ፣ ታሪካቸውንና ባህላቸውን የማውደም ታሪካዊ ሂደት ስንመለከት ፕሮፌሰር መሳይ ከበደና ዶ/ር ዮናስ ብሩ እንደሚሉን የምዕራቡ ካፒታሊስት አገሮች፣ በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በአገራችን ምድር ጣልቃ መግባታቸው ከበስተጀርባው ምንም ዐይነት ተንኮል የለበትም የሚለው አባባላቸው ከታሪክም ሆነ ከሳይንስ አንፃር ተቀባይነት የሌለው በጣም አሳሳችና በከፍተኛ ደረጃ መወገዝ ያለበት አደገኛ አካሄድ ነው። በተለይም ዮናስ ብሩ በተደጋጋሚ ኢ-ሳይንሳዊ በሆነው ጽሁፉ ሊያሳምነን የሚሞክረው የኢትዮጵያ ህዝብና ምሁሩ በሙሉ ዝም ብላችሁ የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊዝም ወይም የነጩን ኦሊጋርኪ የበላይነት ተቀበሉ፤ ተገዙ፣ ተበዝበዙ፤ ጥቁር ህዝቦች ስለሆናቸሁና የተረገማችሁም በመሆናችሁ ምርጫችሁ አንድ ብቻ ነው፤ አፍን ዘግቶ እሺ እያሉ በነጩ ኦሊጋርኪ የበላይነት በመታዘዝና በመነዳት ታሪክን አለመስራት ነው የሚለን። በሌላ አነጋገር፣ በተለይም ዮናስ ብሩ ጥብቅናው ለኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ነው። ጭንቅላቱና መንፈሱ በዚህ የታነፁ በመሆናቸው ኢትዮጵያ የምትባል አገር በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ቁጥጥር ስር መሆን አለባት ነው የሚለን;፡ ይህንን ሃሳቡን የሚጋሩ ምሁራን ነን የሚሉና፣ የድሮ ሻለቃዎችና ኮለኔሎች፣ እንዲሁም ከመሳፍንቱ ዘር የተወለድን ነን የሚሉና ዕጣቸውን ከነጩ የኦሊጋርኪ ማህበረሰብ ጋር ያደረጉም ይገኙበታል። ይህ ዐይነቱ አካሂድ በነቁ የነጭ ምህራንም የሚወገዝ ነው። የአሜሪካን ኢምፔርያሊያዝምና የግብረአበሮቹ አካሄድና የዓለምን ማህበረሰብ በአንድ ወጥ አስተሳሰብ የመቅረጹን ጉዳይ ራሳቸው የተማሩና በተወሳሰበ መልክ የሚያስቡ በጣም የነቁ የነጭ ምሁራን የሚቃወሙት ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ይህ ዐይነቱ አካሄድ የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ ስለሚጻረርና የዓለምን ማህበረሰብ ዘለዓለማዊ ውዝግብ ውስጥ የሚከተው መሆኑን በማወቃቸው ነው።
ወደ እኛ አገር ምሁራን፣ በተለይም የዮናስ ብሩን አስተሳሰብ ወደ ሚጋሩት ጋር ስንመጣ አስተሳሰባቸውና አካሄዳቸው በሙሉ የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ የሚፃረር ነው። ሳይንሳዊ መሰረት የሌለውና እያንዳንዱ አገር ከትውልድ ወደ ትውልድ ያስተላለፈውን ባህል በመንከባከብና በማሻሻል አዲስና የሰለጠነ ማህበረሰብ እንዳይገነባ የሚያደርግ ነው። እያንዳንዱ ግለሰብ በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረ ነው፤ ስለሆነም አንዱ ሌላውን ከማክበር በስተቀር፣ አንዱ የሌላው ታዛዥ መሆን አይገባውም የሚለውን አስተሳሰብ የሚፃረር አስተሳሰብ ነው። ለግለሰባዊ ነፃነትና ለሁለ-ገብ ዕድገት የተደረገውን ከግሪኩ ስልጣኔ፣ እስከሬናሳንስና ሬፎርሜሽን ድረስና እስከ ኢንላይተንሜንት ድረስ ያለውን የመንፈስ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ስንመለከት በፍልስፍናና በቴኦሎጂ መሀከል ይህንንም ያህል የአስተሳሰብ ልዩነት የለም። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የምዕራቡ ካፒታሊዝም፤ በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የመንፈስ ተሃድሶን የሚያስቀድመውንና ለተሟላ ዕድገት በጣም አስፈላጊ የሆነውን ሁለ-ገብ የሆነን ምህራዊ እንቅስቃሴ ይቃወማል። በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አስተሳሰብ ያለው አማራጭ አንድና አንድ ብቻ ነው። ይኸውም በእሱ የተደነገገውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ የነፃ ገበያ ርዕዮተ-ዓለም መቀበል፤ አልቀበለም ያለ አገር ቀጥተኛ ጦረነት ይታወጅበታል።
ያም ተባለ ይህ በተለይም ዮናስ ብሩ በየጊዜው የኢትዮጵያን ምሁራን ኋላ የቀራችሁ ናችሁ እያለ የሚወነጅለውና የኢንላይተንሜንት አስተሳሰብን እቀበላለሁ የሚለው እዚያው በዚያው በተግባር የኢንላይተንሜንትን አስተሳሰብን ይቃወማል። የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ አራማጅና ለብዙ ዐመታትም ለዓለም ባንክ የሰራ በመሆኑ በተጨባጭ ሲታይ ያደረገውና የሚያካሂደው ተግባሩ የኢንላይተንሜትን አስተሳሰብ የሚፃረር ነው። የሳይንስንና የቴክኖሎጂን ዕድገት አጥብቆ ይቃወማል። ከዚህም ባሻገር ግለሰባዊ ነፃነትንና ግለሰባዊ ድርጊትን ይጻረራል። አንድ ሰው በነፃ ማሰብና መፍጠርም የለበትም ነው የሚለን። ኢንላይተንሜት የሚለው በአስራስድስተኛው፣ በአስራሰባተኛውና በአስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን በአውሮፓ ምድር ውስጥ የተንሰራፋውን ዲስፖታዊ አገዛዝን በመቃውም የተነሳ ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ነው። ከህግ የበላይነት ባሻገር በፍልስፍናና በተፈጥሮ ሳይንስ ላይ በመረባረብ አዲስ ማህበረሰብ እንዲመሰረት መሰረት የጣለ ከፍተኛ የሆነ የጭንቅላት እንቅስቃሴና ምርምር ነው። ከዚያ በኋላ ነው የተፈጥሮ ሳይንስ፣ ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ባይሎጂና ማቲማቲክስ ለሳይንሳዊና ለቴክኖሎጂ ዕድገት አስፈላጊ መሆናቸው ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ የተቻለው። በዚም መሰረት ነው የኋላ ኋላ የኢኮኖሚ ሳይንስና ሶስይሎጂ፤ እንዲሁም ልዩ ልዩ ዕውቀቶች ሊዳብሩ የቻሉት። በተለይም በእንግሊዝ ምሁራንና በጀርመን ምሁራን መሀከል ፍልስፍናንና ሳንይሳዊ ምርምርን በሚመለከት የአስተሳሰብ ልዩነት ቢኖርም፣ ሁለትም ለግለሰብአዊ ነፃነትና ለህግ የበላይነት የቆሙ ናቸው። የሲቪል ማህበረሰብ አስፈላጊ እንደሆነም ይናገራሉ። በሌላ አነጋገር፣ በአንድ አገር ውስጥ ሰፋ ያለ በሁሉም መልክ የሚገለጽ እንቅስቃሴ ሲኖር ብቻ ነው ዲስፖታዊ አገዛዝ፣ በዛሬው ወቅት ደግሞ አምባገነናዊ አገዛዝ ላይኖር የሚችለው፣ ወይም መሰረት እንዳይኖረው ለማድረግ የሚቻለው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የግብረ-አበሮች በተለይም ያለፈው የሰባ ዓመት ታሪካቸው፣ ማለትም ከ1945 ዓ.ም እስካሁን ድረስ ያለውን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያካሂዱትን የፖለቲካ ውንብድና ስንመለከት ዋና ዓላማቸው ለህዝብ ጠበቃ የሚሆን፣ አገሩን የሚንከባከብና ለተከታታዩ ትውልድ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ምሁራዊ ኃይልና የሳይንስ ኩሙኒቲ በየአገሮች ውስጥ እንዳይፈጠር ማድረግ ነው። ከዚህ ውጭ ማሰብ ፀረ-ህዝብና ፀረ-ነፃነት ነው። በተጨማሪም በየአገሮች ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚደገፍና፣ ስፋ ባለ የስራ-ክፍፍል የሚገለጽ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ ማድረግ ነው። የዮናስ ብሩና የመሳይ ከበደ አካሄድም ከዚህ ውጭ አይደለም። በአማረ እንግሊዘኛ እየጻፉ ብዙ ታዳጊ ኢትዮጵያውያንን እያሳሳቱ ናቸው። እንደነዚህ ዐይነት ምሁራን አዕምሮአቸው በተሳሳተ አስተሳሰብ የተቀረፀና ከደማቸው ጋር የተዋሃደ በመሆኑ በፍጹም ማስተካከል አይቻልም። ያለው አማራጭ ኢ-ሳይንሳዊና ኢ-ፍልስፍናዊ አስተሳሰባችውንና አካሄዳቸውን በሳይንሳዊና በፍልስፍናዊ መንገድ መዋጋት ብቻ ነው። አስተሳሰባቸው በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን የነበረውን በካቶሊክ ርዕዮተ-ዓለም የሚሰበከውንና የሚገዛውን፣ እንዲሁም ተቀባይነትን ያገኘውን የተሳሳተ የቀኖና ዘመን ያስታውሰኛል። በጊዜው ምድር የማትንቀሳቀስ ወይም የቆመች ነገር ነች፤ ፀህይና ሌሎችም ፕላኔቶች በሙሉ በምድር ዙሪያ የሚሽከረከሩ ናቸው በማለት የካቶሊክ ቀሳውስት ይሰብኩና ተቀባይነትም እንዲያገኝ ያደረጉ ናቸው። ይህንን ኢ-ሳይንሳዊ አስተሳሰባቸውን የሚቃወም በሙሉ አይ ወደ እስር ቤት ውስጥ ይወረወራል፣ አሊያም እስከነነፍሱ ይቃጠል ነበር። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረ-አበሮቻቸውም ይህንን የካቶሊክ ቀኖናዊ አስተሳሰብ መሰረት በማድረግ ነው የእነሱን የበላይነት አልቀበልም የሚለውን አገር በሙሉ ጦርነት የሚያውጁበት፤ የግብረ-ሰዶማዊነት ባህል እንዲስፋፋ በማድረግ አገሮችን ውልቅልቃቸውን የሚያወጡት። ስለሆነም መሳይ ከበደና ዮናስ ብሩ ይህንን ሁሉ ሳያገናዝቡና በተወሳሰበ መልክ ሳያስቡ ነው ነገሮችን አደባብሰው የሚጽፉት። ይህ ዐይነቱ አካሄድና አስተሳሰብ በሳይንሱ ፖዘቲቭ ሳይንስ ወይም ኤምሪሲዝም በመባል ይታወቃል። መልካም ግንዛቤ!!
fekadubekele@gmx.de
www.fekadubekele.com
https://amharic-zehabesha.com/archives/184609
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment