Thursday, August 10, 2023

ዳንዔል ክብረት የሚታወቅበትን ተረት ተረት ትቶ ፉከራ ላይ ተጠምዷል - መሳይ መኮነን
አንዴ ከሳትክ፡ ጨርቅህን ጥለህ ካበድክ መመለሻም የለህ። የአብይ አህመድ ራፖር ጸሀፊ፡ ቃለጉባዔ ያዥ፡ ሶፍትና መሀረብ አቀባይ፡ እራቱን ሲበላ ሻማ ያዥ፡ የፈለገውን የመሆን መብቱ የተጠበቀ ነው። የ100ሺህ የአዲስ አበባ ህዝብ ድምጽ ይዞ የአቢይ እግር ስር መርመጥመጡን በተመለከተ ግን ድምጽ የሰጠው የአዲስ አበባ ነዋሪ ሊያስብበት ይገባል። የጎባጣ አሽከር ለምን አጎንብሰህ ትሄዳለህ ቢሉት ጌታዬን ለመምሰል እንዳለው፡ ዳንዔል በፖለቲካ ክስረት ለጎበጠው አብይ ጎብጦለት ቀርቷል። ታማኝነቱ እስከቀራኒዮ ነው። የምን ክርስቶስ?! የምን ሃይማኖት?! አብይ ሁለቱንም ተክቶለታል። ጋሽ ስብሃት ገብረእግዚያብሄር 'እኔ በአይኔ ያየሁት ኢየሱስ ክርስቶስ ቼጉቬራን ነው' እንዳለው ዳንዔልም ክርስቶስን በአይኑ አይቶታል - 'አብይን'። እንደሌላው ክርስቲያን ህዝብ የክርስቶስን ዳግም መምጣት አይናፍቅም። ክርስቶስ መጥቶለታል። አግኝቶታል። ለዳንዔል ከዚህ በላይ ምን ዓለም አለለት?!

ከዚያች ከቤተመንግስት ነጯ ቢሮ ቁጭ ይልና 'ጃውሳ' እያለ ሲፎክርና ሲሸልል ይውላል። በደህና ጊዜ ብልጽግና የሚሉት ሸለፈት ፓርቲ የማያላምጥ፡ ዝም ብሎ የሚውጥ ግሪሳ ሰብስቦለታል። የወፍ ጫጩት አፏን ከፍታ የእናቷን ጥሬ እንደምትጠብቀው ዳንዔልም ለግሪሳው ቀለብ የምትሆን ወሬ ጣል ለማድረግ ከነጯ ቢሮ ነጭ በርጩማ ላይ ቁጢጥ ይላል። 'ጃውሳ' ብሎ ይጀምራል። ግሪሳው ጠብ ሲል ጠብቆ ላፍ ያደርጋል። የሚገርመኝ የዳንዔልን ቤተመንግስት ገብቶ ከአብይ እግር ስር መውደቅ ሲረግሙና ሲያጣጥሉ የሰነበቱት የኦሮሞ ብሄርተኞች ሰሞኑን ፕሮፋይል ፎቶአቸውን በዳንዔል ፎቶ ቀይረው 'ጀባዱ ሌንጫ አባ ቢያ' እያሉለት ነው። የፖለቲካ ውስልትናና አንሶላ መጋፈፍ ብልጽግና መንደር የወርቅ ዋንጫ የሚያሸልም ሆኗል። ዳንዔል ብዙ ዋንጫ እያገኘ ነው።

ዳንዔል ቀረርቶውን ቀንሶ ቅኔውን ቢጨምርበት የሚል ጭላንጭል ተስፋ ይዤ ነበር። ህዝብን ጨፍጭፎ፡ ህጻናትን ረፍርፎ፡ ህንጻና ቅርስ አውድሞ ከተማ የገባን የአብይ ሰራዊት ጭካኔ እንደ ድል ቆጥሮ 'ከጃውሳ ጋር ድርድር የለም' እያለ ይፎክራል። ቆይ ትንሽ ታገስ ቢባል ጆሮዬን የዝሆን ያድርገው እያለ ነው። የአብይ አፍ ሆኖ ይሸልላል። የብልጽግና ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት መሪነትን ቦታ ይዞ 'እስቲ ወንድ የሆነ ይሞክረን' አይነት ፉከራ ጀምሯል። የለገሰ ቱሉን ስራ ነጥቆታል። 'ከዳመና በላይ' እንደንስር የሚለው የለገሰ ቱሉ ቅዠት ሳይሻል አይቀርም። ለገሰ እንደአሽሙረኛ ነገረኛ ባልቴት አንገቱን እየነቀነቀ 'ጉም ውስጥ ከሚበረው፡ ሰማየ ሰማያትን ከሚቀዝፈው ብልጽግና ጋር ወደፊት' ሲል ይደንቀኝ ነበር። ዳንዔል መጣና በአስር ክንድ ገፈተረው። የለገሰን የእንጀራ ገመድ እንዳይበጥስበት ያሰጋል። ዳንዔል ቁልቁለቱን ተያይዞታል። መጨረሻዬን ያሳምረው' ማለትም አንድ ነገር ነው። ለንሰሀ መብቃትም እኮ መታደል ነው። እንደሰው ኖሮ እንደእንስሳ ከመሞት ይሰውረን። ዳንዔል ስለራሱ በመጻፉ ግን ልናደንቀው ይገባል።
https://amharic-zehabesha.com/archives/184907

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...