Sunday, June 4, 2023

ሕዝብ ሆይ! - በላይነህ አባተ
#image_title

ሕዝብ ሆይ!

ጅቡ ሲመጣ አፍጦ በአውሬ ባህሪው ሊገምጥህ፣

እንደ አምናው ተዛሬ ነገ ሰውን ይሆናል ብለህ ተጠበክ፣

እንደ ታች አምናው ዘንድሮም ዳግም ቂል ተሆንክ፣

የራስህ አጥፊው ጅብ ሳይሆን አንተው ራስህ ሕዝብ ነህ!

ሕዝብ ሆይ!

ከተቀደሰው ቤተክርስትያን ከምትሰግድበት መስጊድህ፣

እርኩስ ጅብ ገብቶ እየጎመደ ሲበላህ ሲያረክስህ፣

ያላዬ መስለህ ተተኛህ እጅህን አጣጥፈህ ቁጭ ታልክ፣

እንኳንስ ይህ ከንቱ ምድር እግዜር ያለበት ሰማይም አይረዳህ፡፡

ሕዝብ ሆይ!

እርዳኝ እረድሃለሁ ያለውን ትእዛዙን ሕጎቹን ቦጫጭቀህ፣

ጅብ ተቤተ መቅደስ ደም ሲያፈስና ሲጠጣ ዝም ታልክ፣

በአምሳሌ ሰርቸዋለሁ ያለውን ፍጥረቱን መቼ ሆንክ?

ሕዝብ ሆይ!

አሞት አልቦ ጅብ ግራ እግር ጎርሶ ሲውጥህ እያየህ፣

“ቀኜን እንዳይደግም ዝም በል” የሚል ጡርቂ አመል ታሳየህ፣

ልብ አድርግ ለቀብር የሚሆን እራፊ ገላም አይተርፍህ፡፡

ሕዝብ ሆይ!

ጅብና ውሻ ፈሪ እንደማይለቅ እያወክ፣

ወግድ ክላልኝ የሚልን እንደማይነካ ዘንግተህ፣

ፊትለፊት እንደመጋጠም ለመሸሽ ከተፈተለክ፣

እንኳንስ የአንተ የልጅ ልጅህም ታፋው አይተርፍህ፡፡

ሕዝብ ሆይ!

ጅብ ተጠራርቶ ሊጎርስህ በሁሉ አቅጣጫ ሲከብህ፣

አካሎችህን አንድ አርገህ በጥኑ ወኔ መፋለም ሲገባህ፣

የግራ የቀኝ እጅህን አጋጭተህ ክንድ ማስለሉን ተቀጠልክ፣

እንኳን ቀን የሰጠው ጅብ ጆፌ አሞራውም አይምርህ፡፡

ሕዝብ ሆይ!

እንደ ቅደም አያቶችህ አንድ ላይ ሆነህ መፋለም ሲገባህ፣

በጎጥ በመንደር እየጮህክ እርስ በራስህ መናከስ ተጀመርክ፣

ማለቅህን እወቅ በጅቦች የከረፋ አፍ ተራ በተራ ተውጠህ፡፡

ሕዝብ ሆይ!

የቀን ጅብ ተዱሩ ወጥቶ ሊውጥህ አምቧትሮ ሳለ፣

ቀኝ እግርህ ግራውን በተንኮል ጠልፎ ተጣለ፣

ለራስህ የከፋ ጠላት ያለ አንተው ሌላ ማን አለ?

ሕዝብ ሆይ!

ቀኑ የጅቦች መሆኑን በእዝነ ልቡናህ አጥንተህ፣

ቀኝ ክንድን በጡንቻህ ተግራው ጋራ አጣምረህ፣

ግራ እግርን ተቀኙ እንደ ብረት ከንች አምቧትረህ፣

ህልውናህን አረጋግጥ እንደ ታሪክህ በትግልህ፡፡

ሕዝብ ሆይ!

ዘመኑ የጅቦች መሆኑን በአይምሮ ልብህ አጢነህ፣

የአያትን ክብሮች አስጠብቅ ክንድ መንፈስክን አንድ አርገህ፡፡

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

ግንቦት ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ.ም.

 

What does the demonstration tell you ? People and power , where people have the right to select their leader , honesty is the best political policy.. #JusticeForEthiopia pic.twitter.com/DS3N9SvrTd

— @ዥትዊተር @Ramsey 🇪🇹 (@1juxa) June 3, 2023

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/183165

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...