Wednesday, June 21, 2023
ክፍል ፩
ማክሰኞ፣ ሰኔ ፲፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ. ም. (6/20/23)
በአገራችን በኢትዮጵያ ያሳለፍነውን የሃምሳ ዓመታት የፖለቲካ ሂደት ዞረን ብንመለከት፤ ተጨባጩ እውነታ ብዙ የተመሰቃቀሉ ለውጦች እንደተስተዋሉበት እንረዳለን። የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ኑሮ አንገፈገፈኝ ብሎ ከተነሳበት ከየካቲት አስራ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ስድስት ዓመተ ምህረት ጀምሮ፤ የተለያዩ የነፃ አውጪ ግንባሮች በየቦታው ተፈጥረዋል። መሪ ልሁን ባዮች በብዛት የፖለቲካ መድረኩን አጥለቅልቀውታል። ረሃብ የአገሪቱን አንዳንድ ክፍሎች እስካሁንም ወጥሮ ይዟል። እጅግ ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ለስደት ተዳረገዋል። በጎረቤት አገራትና በሩቅም ተበትነዋል። ከገጠር ወደ ከተማ ብዙ ሰው ጎርፏል። የሕዝቡ ቁጥር በሚያስገርም ሁኔታ አድጓል። ብዙ ትምህርት ቤቶች የተከፈቱ ቢሆኑም፤ የትምህርቱ ጥራት ከመውደቁ ሌላ፤ ለተመራቂዎች ሥራ አልተፈጠረላቸውም። ከመቼውም ጊዜ በላይ የቴሌቪዝን፣ የሬዲዮ እና የስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር አይሏል። እጅግ በጣም ጥቂት የሆኑ ሰዎች በልፅገው፤ የነሱ ሀብት እጅግ እየበዛ ሲሄድ፤ በአንጻሩ የድሃው ቁጥር እየጨመረና ድህነቱ እየከፋ ሄዷል። የአብዛኛው ሰው ኑሮ፤ ከእጅ ወደ አፍ፤ አለያም ጦም ማደር ሆኗል። በተመፅዋችነት የሚተዳደረው የወገናችን ቁጥር ወደላይ ጉኗል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የዘይት ዋጋ መናር፤ በሸቀጣ ሸቀጥና ዝውውሩ ላይ የዋጋ ክምር በማስከተሉ፤ የሕዝቡ የኑሮ ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት እየከፋ ሄዷል። የውጪ መንግሥታትና የውጪ ኃይሎች በአገራችን የፖለቲካ ሂደት፤ የጣልቃ ገብነት ድርሻቸው እያየለ ሄዷል። ይህ በድምሩ፤ በሕዝቡ ግንዛቤና የኑሮ ሀቅ ላይ ያስከተለው ብዙ ለውጥ አለ። ይሄ ሁሉ ሲሆን፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እየተፈራረቁ ያስተዳደሩትና አሁን በፌዴራል የተዋቀረው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ በምን መርኅ ነበር አገሪቱን የሚያስተዳድሯት? በዚህ ሁሉ ሂደትስ የመንግሥት ሚናው ምንድን ነበር? እንዴት ነበር አገሪቱን ሲያስተዳድሩ የቆዩት? በዚህ ጊዜ ምንድን ይሠሩ ነበር? አሁን ላለንበት ተጨባጭ ሀቅ ምን ያህል ባለቤትነት አላቸው። የመንግሥቱና የሕዝቡስ ግንኙነት ምን ይመስል ነበር? በዚህ ጽሑፍ ይሄን ትኩረት ሠጥተን እንመለከታለን።
የመንግሥት ምንነትና ተግባር የሚገለጠው፤ በአገሪቱ በተቀመጠው ሕገ-መንግሥት፣ ይህ አካል በሚያራምደው የአስተዳደር መመሪያ፣ በተግባር በሚያውለው ሕግና ደንብን የማስከበር ድርጊቱ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሕገ-መንግሥት፤ በመጀመሪያ፤ አረመኔው የደርግ ወታደራዊ አምባገነን፤ በራሱ ፍላጎት ዙሪያ የስቀመጠውና ከአገራችን ጊዜያዊ ሀቅ ጋር ያልተዛመደ ስርዓትን ያወጀ ነበር። የደርግ መንግሥት በወደቀበት ጊዜ፤ ለወቅቱ የፖለቲካ ግኝት፤ በወቅቱ በትውልድ ማንነት (በጎሣ) ፖለቲካ ተደራጅቶ ሥልጣን የወሰደው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር፤ ለራሱ የሚፈልገውን ግብ ያስገኝልኛል ብሎ ባስበው መሠረት የጻፈው ነው። ይህ ሕገ-መንግሥት አገራዊ ሳይሆን፤ የገዢውን ጠባብ ወገን በሚጠቅም ሁኔታ የተሰናዳና፤ በዝግጅቱ ወቅት፤ የአማራውን ወገን ለውክልና እንኳን ያልጋበዘ ነበር። በወፍ በረር የዚህን የትውልድ ማንነት ፖለቲካ መሠረት ያደረገ ሕገ-መንግሥት እንመርምር። መሠረቱ፤ አገሪቱ የኢትዮጵያዊያን ሳትሆን፤ በትውልድ ማንነት ላይ ተመርኩዘው የተደራጁ ክፍሎች ባለቤትነት ያላቸው ስብስቦች፤ ንብረት ናት! ይላል። ለሁሉም የአገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች፤ ተጠያቂው አማራ ነው ይላል። በቀጥታ ለመጥቀስ፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር መርኀ-ግብር መግቢያ፤ “ . . . የአማራን የበላይነት በመገርሰስ” ይልና፤ “በአማራው መቃብር ላይ . . . ” ይላል። እንግዲህ በሥልጣን ላይ የወጣው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ በኢትዮጵያ የገዢ መደብ ሳይሆን፤ “አማራዎች በአንድነት የበላይ ሆነው ሌሎች ኢትዮጵያዊያንን ሲገዙ የነበረበት ሀቅ ነግሦ ነበር!” ብሎ አሰራጭቷል። ይህ ደግሞ፤ ደርግን የሚመለከትና፤ ደርግና የአማራ ነው ብሎ የፈረጀ ነው። ተከታዩ በሙሉ የዚህ ትርክት ውልድ ነው። እናም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ፤ የትውልድ ማንነትን የፖለቲካ ማንነት ይዘት ሠጥቶ ቀጠለ።
በኢትዮጵያ፤ የትውልድ ማንነት ፖለቲካ፤ አንኳር የሆኑ የመብት ጥሰቶችን አካሂዷል። በኢትዮጵያ፤ ግለሰብ ኢትዮጵያዊያን የሉም። እንግዲህ በዚህ ከሄድን፤ እያንዳንዱን ዜጋ፤ ቁጥርና ድምር ተደርጎ ስለተቀመጠ፤ የግለሰቦች መብት ተሽሯል። ግለሰቦች ቁጥር ናቸው። በአገር ደረጃ፤ የቁጥር ሂሳብ መቀመሪያ ሆነው፤ የፖለቲካ ክንውኑን በመወሰን በኩል፤ መሳሪያ ተደርገው ተቀምጠዋል። ይህ እንግዲህ ግለሰቦች፤ በግል አመለካከታቸውና በግል ፍላጎታቸው ሳይሆን፤ በትውልድ ማንነታቸው፤ የፖለቲካ አመለካከታቸውና ተሳትፏቸው ተወሰነ ማለት ነው። ይህ የትውልድ ማንነት ፖለቲካ፤ ግለሰቦችን ሲወለዱ ጀምሮ እንደ እጅና እግር ሊለውጡት የማይችሉት ዕሴት ሠጥቶ፤ ሰዎችን ተገዢ እንጂ ባለቤትነት የሌላቸው አደረጋቸው። እናም የየክልሉ ልሂቃንና ሥልጣን ጥመኞች፤ ዕቃ አደረጋቸው። አንድ ግለሰብ የኦሮሞ ተወላጅ፤ ኦሮሞ ክልል ብቻና፤ በኦሮምኛ ብቻ የፖለቲካ ተሳትፎ ሲያደርግ፤ ትግሬውም እንዲሁ፤ በትግራይና በትግርኛ ብቻ ተሳትፎውን አደረገ። እዚህ ላይ የዴሞክራሲ አሰራር ቦታው ተሻረ። ግለሰብ፤ የሚያስብ፣ ምኞት ያለው፣ ሃሳቡን በፈለገው ጊዜ ሊቀይር የሚችል አካል ሳይሆን፣ ግዑዝ እንደ
ዕቃ ተቆጣሪ ሆነ። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሳይሆን፤ በትውልዱ ፖለቲካ ብቻ እንዲሳተፍ ተደረገ። በፌዴራል ደረጃ ለሚደረገው ክንውን፤ የትውልድ ማንነቱን ተሸክመው የሄዱት ወከሉት። ቀጥሎ ደግሞ፤ በአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ፤ የ“እኛና” የ“እነሱ” ክፍፍልን ፈጠረ። ይህ የአገር አንድነቱን ከመሸርሸሩ በላይ፤ ወደ የማይመለሱበት የልዩነት መንገድ እንዲያመራቸው ገፋቸው። እናም ይሄ አገር አፍራሽ እርምጃው፤ አሁን ላለንበት እውነታ ዳረገን። አሁን ያለንበት እውነታ፤ ከኔ አካባቢ አትኖርም እየተባለ፤ በተለይ አማራው፤ የሚባረርበት፣ ንብረቱ የሚዘረፍበትና፣ ሕይወቱ በኢሰብዓዊ መንገድ የሚቀጠፍበት ነው። እንዴት ለዚህ በቃን? በሕዝቡ ፍላጎት ነው ወይንስ በፖለቲካ ባለሥልጣኖች የሰላ ጥረት?
ክፍል ፪
ሐሙስ፣ ሰኔ ፲፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ. ም. (6/22/23)
(በክፍል አንድ መነሻ የሆነውን የርዕሱን መንደርደሪያ አስቀምጬ፤ በኢትዮጵያ ያለውን ሕገ-መንግሥትና የአስተዳደሩን ሂደት አስፍሬያለሁ። ይህ ከዚያ በቀጥታ የሚቀጥል ነው።)
የማንነት መሠረቱ የግለሰቡ ሕይወት ነው። የግለሰቡ ሕይወት ለግለሰብ ማንነቱ ማጠንጠኛ ነው። ከዚያ ቀጥሎ፤ ከሌሎች ጋር የሚኖረው ግንኙነት፤ ለሌሎች ተከታታይ ማንነቶቹ መንገድ ይከፍታል። በርግጥ ከትውልድ ያገኘው ማንነት፤ የሰውነትን ቅርጽ፣ የቆዳን ቀለም፣ የፀጉርን ጥንካሬ ይገልጽ እንደሆነ እንጂ፤ የትኛውን የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዲይዝ ወይንም የትኛውን የፖለቲካ ፓርቲ እንዲቀላቀል፣ ምን እንደሚያስብ፣ ምን እንደሚጠላ፣ ምን የሙያ መስክ እንደሚከተል ወሳኝ አይደለም። ያ በዕድገታችን የምንገነባው የየራሳችን የግል ጉዳይ ነው። በርግጥ ዝንባሌን የሚገፉ አስተዋፅዖ ሊያደርጉ የሚችሉበት መንገድ ይኖራል፤ ወሳኝነት ግን የላቸውም። አባትየው አጥባቂ ወገኛ ሆኖ፤ ልጅየው ነውጠኛ ሊሆን ይችላል። የፖለቲካ አመለካከት ከናት ወደልጅ በእትብት አይተላለፍም። የአንዲት ግለሰብ ተመክሮ፤ ግለሰቧ ለምትከተለው የግለሰብ የፖለቲካ አመለካከት አስተዋፅዖ ያደርጋል። ይህ ግን የግለሰቧ ጉዳይ ነው። ግለሰቧ በፈለገችው ጊዜ ልትለውጠው የምትችለው ጉዳይ ነው። ማንም ሊሠጥና ሊነጥቅ የሚችለው የፖለቲካ ማንነት አይደለም። ኢትዮጵያዊት የትም ትኑር የት፤ ኢትዮጵያዊት ነች። በኢትዮጵያዊነቷ፤ በአገሯም ሆነ በውጪ አገር መብቷ የተከበረ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ፤ የላንዳች ጥያቄ ካንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ የመዘዋወር መብቷ የተጠበቀ ነው። በፈቃዷ ይሄን ትታ የሌላ ዜጋ ልትወስድ ትችላለች። ያ የርሷ ምርጫ ነው።
አዎን፤ የትውልድ ማንነት የአንድ ግለሰብ መገለጫ ነው። ነገር ግን እያንዳንዱ መገለጫ ለግለሰቡ የፖለቲካ ማንነት ሆኖ አያገለግልም። ፖለቲካ የተፈጥሮ ጉዳይ አይደለም። ፖለቲካ ከተወለዱ በኋላ የሚሳተፉበት የኅብረተሰብ ክንውን ነው። ሃይማኖትም፣ ሙያም ሌሎችም እንዲሁ። በሙያ መስክ፤ ሐኪም፣ መሐንዲስ፣ ወታደር፣ ነገዴ ሆኖ መኖር ይቻላል። በሃይማኖት በኩል የክርስትና ወይንም የእስልምና ተከታይ መሆን ይቻላል። ሃይማኖት አያስፈልገኝም ብሎ መኖርም ይቻላል። እኒህ ሁሉ ግን፤ በአገር ውስጥ ለሚደረግ የፖለቲካ ተሳትፎ፤ መመዘኛ አይሆኑም። የአገሩ ተወላጅ መሆንና ፈቃደኛ ሆኖ በፖለቲካ መድረኩ መርጦ መሳተፍ ነው የፖለቲካ ማንነትን የሚያስይዘው። የመኖሪያ ቦታም፤ የፖለቲካ ማንነት አይሆንም። የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ እንግሊዝ አገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ፤ ለንደን በመኖሩ፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካ እንጂ፤ በለንደን ፖለቲካ ይሳተፋል ማለት አይደለም። እናም ይሄን ሀቅ የትውልድ ማንነት ፖለቲካ ይስታል። የፖለቲካ ማንነት በፈቃደኝነት የሚወሰድ እንጂ፤ በትውልድ ወይንም እንደሽልማት የሚሠጥና የሚነጠቅ ማንነት አይደለም። የአንድ ፓርቲ አባል ለመሆን፤ ያ ፓርቲ ያስቀመጠውን መስፈርት አሟልቶ መገኘት ብቻ ነው የሚያስፈልገው። ያ መስፈርት፤ በአንድ አገር ላለ ማንኛውም ዜጋ ክፍት ሆኖ፤ ማንንም በትውልዱ ወይንም በሌላ ምክንያት የማያገልል መሆን አለበት። አለበለዚያ፤ ያ ፓርቲ በዚያች አገር የፖለቲካ ሂደት ተካፋይ ሊሆን አይገባውም። ምክንያቱም ዜጎችን አግላይ በመሆኑ። በርግጥ ይሄ በትክክለኛው የዴሞክራሲያዊ አሰራር የሄድን እንደሆነ ነው። እንግዲህ መነሻችን ይሄ ሆኖ፤ ሕገ-መንግሥቱ በዚያ መንገድ አገራችንን የኢትዮጵያዊያን ሳይሆን፤ በትውልድ ማንነት የተደረገ የፖለቲካ ስብስብ ናት ብሎ ካስቀመጠ፣ ይሄን እንዲተገብር መንግሥትን ኃላፊነት ከሠጠ፣ ለዚህ እንዲረዳ ክልሎችን ካዋቀረ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና የመንግሥቱ ግንኙነት ምን ሊሆን ይችላል? እንመርምር፤
የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር አዲስ አበባ ሲገባ፤ የፖለቲካ መሠረት የሚሆነው ሕዝብ፣ ወይንም አገር አቀፍ ድርጅታዊ ጥንካሬ አልነበረውም። እናም አገሪቱን በመከፋፈልና ሊቀናቀኑት የሚችሉትን በማዳከም ብቻ፤ ሊገዛ እንደሚችል ተረዳ። ለዚህ ሊረዳው የሚችለው፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፋፍሎና ለያይቶ ማደራጀት ነበር። በርግጥ ከመሠረቱም የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ነውና፤ አንድም ትግራይን ከኢትዮጵያ መገንጠል፤ አለያም ደካማ ኢትዮጵያን ፈጥሮ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር የበላይ የሆነበትን አስተዳደር በአገሪቱ መጫን ነበር። ያደረገውም ይሄንኑ የኋለኛውን ነበር። ሁላችን እንደምናውቀው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር ኢትዮጵያን የገዛው፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ሆኖ ነው። ትግራይን ከማን ነው ነፃ የሚያወጣ? ከኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ የትግራይ ጠላት ናት ብሎ፤ ኢትዮጵያን ለማጥቃት የተመሠረተ ድርጅት ነው! ስለዚህ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር የኢትዮጵያ ጠላት ነው! ይህ አያጠያይቅም። ማንም ነፃ አውጪ ድርጅት፤ የሕልውናው ትርጉም፤ የኢትዮጵያ ጠላትነት ነው። በኋላም እንዳየነው፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ካዲስ አበባ ሸሽቶ መቀለ ገብቶ፤ ያንኑ የመገንጠልና የራሱን መንግሥት በትግራይ መመሥረቱ ላይ ነበር የተሰማራው። በተገንጣይነቱ ቆሞ፤ የበላይ ሆኖ መግዛቱን እንዲያስተካክልለት፤ “ኢትዮጵያ፤ የኢትዮጵያዊያን ሳትሆን፤ በትውልድ ማንነት ፖለቲካ የተደራጁ ስብስቦች ባለቤት የሆኑባት ናት!” የሚል ሕገ-መንግሥት ጻፈ። ይሄ ሕገ-መንግሥት፤ በፈለጉ ጊዜ ኢትዮጵያን ጥለ የሚሄዱበትና
የራሳቸውን መንግሥት የሚመሠርቱበት ክልልን ፈጠረላቸው። ክልሎቹ የአስተዳደር ክፍፍሎች ብቻ ሳይሆኑ፤ የትውልድ ማንነት ፖለቲካ ማቅኛ፤ ለም መሬቶችም ሆኑ። እኒህ ለም መሬቶች የየራሳቸው ቋንቋ፣ ኢኮኖሚ፣ ባህል፣ የትምህርትና ሕክምና ዘርፍ ያላቸው አስተዳደሮች ሆኑ። አልፎ ተርፎም የየራሳቸው ልዩ ኃይሎች እንዲኖራቸው ተደረገ። ይህ ሁሉ ሌሎችን እንዳሻቸው እንዲሠሩ ሲፈቅድ፤ አማራው በዚህ እንዲሠራ አልተፈቀደለትም። ይልቁንም አማራውን እንዲቆጣጠሩ ከገዢዎቹ ትራፊ ተወርውሮላቸው የተመደቡት የአማራው ገዢዎች፤ ለክልሉ የተመደበውን ገንዘብ፤ ክልሉን ሳያለሙ መልሰው ለጌቶቻቸው መሥጠት፣ አማራውን ማሸማቀቅና ወንጀለኛ ነው የሚለውን ትርክት ማስተማር ያዙ። ይሄ ግን ለትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባርም ሆነ ለኦሮሞ ነፃነት ግንባር በቂ አልሆነላቸውም። የአማራ ክልል መሪዎችን እንደፈለግን እናነሳለን እንጥላለን በማለት፤ እነ አምባቸውን፣ ምግባሩን፣ አሳምነውን ገድለው፤ ሌሎችን ተኩ። ይሄ ሁሉ በፌዴራል ብልፅግና ስም ይደረግ እንጂ፤ በአብይ አሕመድና ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ብልፅግና ነው የተከናወነው። የአማራ ብልፅግና አገልጋይ መሳሪያ ነው።
ክፍል ፫
አንዱ ዓለም ተፈራ
ሐሙስ፣ ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፲፭ ዓ. ም. (6/24/23)
(በክፍል አንድና ሁለት፤ መነሻ የሆነውን የርዕሱን መንደርደሪያ አስቀምጬ፤ በኢትዮጵያ ያለውን ሕገ-መንግሥትና የአስተዳደሩን ሂደት አስፍሬያለሁ። ቀጥዬ ይሄ ሕገ-መንግሥትና የአስተዳደር ሂደት ምን እንደሆነ ዘርዝሬያለሁ። ይህ ከነዚያ በቀጥታ የሚቀጥል ነው።)
ሕገ-መንግሥቱ ከታወጀና የክልል አስተዳደሮች ከተመሠረቱ በኋላ፤ የትውልድ ማንነት ፖለቲካ በአገራችን የፖለቲካ ማኅደር እግሩን አፈራግጦ ተቀመጠ። እንግዲህ ከዚያ ለተከተለው የፖለቲካ ሂደት ወሳኝነት ቦታ ይዞ የሄደው ይሄ የትውልድ ማንነት ፖለቲካ፤ የአሰተዳደር መመሪያ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ በአገራችን ላለው ማንኛውም የፖለቲካ ሂደት የበላይ ተርጓሚ ሆነ። እናም አሽከርካሪውና ቅኝቱን አዘጋጅ በመሆን፤ አሁን ላለንበት እውነታ፤ ባለቤቱ ይሄው የትውልድ ማንነት ፖለቲካ ሆነ። ግለሰቦች በግድ፤ የቡድን የትውልድ ፖለቲካ ማንነትን ጋቢ ተጎናነቡ። አንድ ግለሰብ በፖለቲካ አመለካከቱ በአገሪቱ ባለው የፖለቲካ መድረክ መሳተፍ እንዳይችል ተደረገ። በርግጥ በአንድ ጉዳይ ላይ፤ ዕርዳታዎችን አስተባብሮ አንድ ተልዕኮ ለማከናወን፣ ተቃውሞን ለማሰማት፣ ወይንም አንድ የሚፈልጉት ግብ ላይ ለመድረስ ሰዎች ሊቧደኑ ይችላሉ። በአገር ደረጃ ላለ የፖለቲካ ተሳትፎ፤ ግለሰቦች ሁሉን አቀፍ የአገር አመለካከታቸው ነው በግለሰብ ደረጃ እንዲሳተፉ የሚያደርጋቸው።
የትውልድ ማንነት ፓለቲካ፤ ተመክሮን፣ ባህልን፣ ቋንቋን፣ ታሪክን ሁሉ አቅፎ ስለሚይዝ፤ ተወደደም ተጠላም ወደ ጠነከረና የተለያዬ አቅጣጫ መሄጃ የልዩነት መስመር ይወስዳል። የዚህ የትውልድ ማንነት ፖለቲካ መዳረሻ፤ በየክልሉ የየራሱ አምባገነኖች መረገጥ ነው። ከአስራ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ስድስት ዓመተ ምህረት (፲፱፷፮ዓመተ ምህረት) በፊት በነበረው ስርዓት፤ ለኦሮሞውም ሆነ ለትግሬው፣ ለአፋሩም ሆነ ለሶማሊው፣ ለአኙዋኩም ሆነ ለሲዳማው፣ ለወላይታውም ሆነ ለኩናማው፤ ለአማራውም ሆነ ለአዲስ አበቤው፤ ከማዕከላዊ መንግሥቱ ጋር የነበረው ግጭት፤ የጨቋኝ ገዥዎችና የተጨቋኝ ሕዝቡ ግጭት ነበር። የኦሮሞውና የአማራው፣ የትግሬውና የአማራው፣ የአፋሩና የአማራው፣ የሶማሊውና የአማራው፣ የአኙዋኩና የአማራው፣ የሲዳማውና የአማራው፣ የወላይታውና የአማራው፣ የኩናማውና የአማራው አልነበረም። ይሄ መስመር ያለበት ዋና ጉዳይ ነው። አመጹና ትግሉ፤ በአገዛዙ መሪዎችና በቀሪው የአገሪቱ ሕዝብ መካከል ነበር። የተጠለፈው፤ ሥልጣን ፈላጊ ጠባብ አጀንዳ አራማጆች፤ የመደብ ትግሉን የብሔር ትግል ያደረጉት ጊዜ ነው። በትውልድ ማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ትግል መጨረሻ መዳረሻው፤ “በራሴ የትውልድ አባል ገዢ የበለጠ ልረገጥ!” ነው። በንጉሠ ነገሥቱ ጊዜ፤ በደል ከግለሰብ ጀመሮ እስከ መላ የአገራችን ሕዝብ ድረስ ነበር። ለዚህም ነበር የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት፤ የካቲት ፲፱፷፮ዓመተ ምህረት የተነሳውና፤ የነበረው መንግሥት “መውረድ አለበት!” በማለት የተነሱት። አማራ ይጥፋ ብለው አልተነሱም። ይልቁንም የነበረውን የመደብ ጭቆና አምርረው በመቃወም፤ የብዙዎቹ ሰልፎች መሪና ተሳታፊ አማራዎች ነበሩ። በመደብ ይዞታ፣ በትውልድ ማንነት፣ በባህል፣ በግለሰብ ተበዳይነት፣ የተመረኮዙ ተቃውሞዎች፤ መነሻና መድረሻ አላቸው። ምንጩ አንድ ነው። ምንጩን በማድረቅ ሁሉም መልስ ያገኛል። ከዚያ ካለፈና ከተገፋ፤ ሌላ አጀንዳ ያዘሉ ባለጉዳዮች የሚያሽከረክሩት ይሆናል። ያም ነው ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነው። በውጪ አገር ያለው ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይልና መንግሥታትም ያራመዱት ይሄኑ ነው። አማራዎችም ሆኑ ቀሪዎቹ ኢትዮጵያዊያን፤ በየካቲት ፷፮ቱ አመጹ ስንሳተፍ፤ ከኢትዮጵያ ነፃ እንውጣ ብለን ሳይሆን፤ የነበረው ገዢ ይውረድ ብለን ነበር። ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊያን ሁላችን እንጂ፤ የገዢዎቹ ብቻ አይደለችም ብለን ነበር።
በምዕራባዊያን የጥቅም ማሳደድ ጣልቃ ገብነት፤ ዓለም አቀፉ የፖለቲካ ነፋስ የገረፈው የኢትዮጵያዊያን አንድ ሆነው በዜግነት የተመሠረተ አገርነት ሳይጠናቀቅ፤ በጥቂት ሥልጣን ፈላጊ፣ የትንሽነት ስሜት ያጠናወዛቸው ልሂቃን የታሪክ ሂደቱ ወደኋላ ተጠምዝዞ፤ ለትውልድ ማንነት ፖለቲካ አራማጅ ነፃ አውጪ ድርጅቶች መፈልፈል፤ መንገዱን ከፈተ። ይህ አባዜ ነው ከኢትዮጵያ ነፃ እንወጣለን በሚል እንዲደራጁ ያደረጋቸው። እንግዲህ፤ ከኢትዮጵያ ነፃ እንወጣለን ሲሉ፤ ፀረ-ኢትዮጵያ ትግል አድርገን እናፈርሳትና የራሳችንን አገር እንገነባለን የሚል ትርክት ይዘው ነው። ከነዚህ ኢትዮጵያን ወይንም ኢትዮጵያዊነትን እንዲያጎለብቱ ማሰብ፤ ከእባብ እንቁላል የእርግብ ጫጩት መጠበቅ ይሆናል። በምንም ሰዓት ሆነ በምንም መልኩ፤ እኒህ ነፃ አውጪ ግንባሮች ኢትዮጵያዊነትን አይቀበሉም። ኢትዮጵያንም እንደ ጠላት ከመቁጠር ዝንፍ አይሉም። የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር፤ ምን ጊዜም የኢትዮጵያ ጠላት እንጂ ኢትዮጵያዊ አይሆንም።
ይሄ የትውልድ ማንነት ፖለቲካ፤ በየክልሉ ለታጎሩት የዚያ ተወላጆች፤ አጠቃላይ ብልፅግናን ወይንም ትርፍን አያስገኝም። ይልቁንም በራሳቸው ገዢዎች መተዳደር፤ በጠባብ ቦታ የበለጠ ጭቆናን እንዲያስተናግዱና፣ የራሳቸው በመሆኑ ዝም እንዲሉ
የሚያደርግ ነው። በግልጥ ሲቀመጥ፤ የትውልዱ ጥቂት የፖለቲካ ሥልጣን ፈላጊዎች፤ ሥልጣን ላይ ለመውጣት አቋራጭ መንገድ ዝየዳ ነው። አዲስ የፖለቲካ ሂደት አይደለም። ከላይ እንደተቀመጠው ባለፈው ምዕተ ዓመት አጋማሽ ላይ የነፃ አውጪ ግንባር የፈሉት ለዚሁ ሲባል ነበር። ይሄ የግዳጅ የቡድን የትውልድ ማንነት ፖለቲካ፤ ምን ያህል የተሳታፊዎችን አእምሮ ይበርዛል? በምን መንገድስ የሚያደርጉትን አስተዋፅዖ ይወስናል? በርግጥ በኛ አገር የፖለቲካ ሂደት፤ ለኒህ ጥያቄዎች መልስ መሥጠቱ ሰፊ ጥናት ይጠይቃል። ሆኖም ግን እስካሁን ባየነው እውነታ፤ በቂ ግንዛቤ ሊያስይዘን የሚያስችል መረጃዎች አሉን። በጭፍን ከመከተል አልፈው፤ አረመኔ ተብሎ እንኳን ሊገለጥ በማይችል ጭካኔ፤ ወጣት የዚህ ጠባብ የትውልድ ማንነት ፖለቲካ ልፈፋ ተከታዮች፤ አማራዎችን ከመግደል አልፈው ሬሳቸውን ያደረጉትን መመልከቱ በቂ ነው።
ክፍል ፬
አንዱ ዓለም ተፈራ
ሰኞ፣ ሰኔ ፲፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ. ም. (6/26/23)
(በክፍል አንድ፣ ሁለትና ሶስት፤ መነሻ የሆነውን የርዕሱን መንደርደሪያ አስቀምጬ፤ በኢትዮጵያ ያለውን ሕገ-መንግሥትና የአስተዳደሩን ሂደት አስፍሬ፣ ይሄ ሕገ-መንግሥትና የአስተዳደድር ሂደት ምንን እንደሆነ ዘርዝሬያለሁ። ከዚያም ይህ ሲተገበር የፈጠረውን አቅርቤያለሁ። ይህ ከነዚያ በቀጥታ የሚቀጥል ነው።)
በዚህ መንገድ እየተተገበረ ያለው በትውልድ ማንነት ላይ የተመረኮዘ ጥላቻና ተፈጻሚነት፤ በጊዜ አለመፈታቱ ያስከተለው ክረት፤ መንግሥቱ በአገር ላሉ መላ ኢትዮጵያዊያን ሳይሆን የአንድ ክልል አገልጋይና ባለቤትነት ያለው ሆኖ፤ አገሪቱን ወደ የማትመለስበት አዘቅት እያንደረደራት ነው። የዚህ ከፋፋይ ስርዓት መሰንበት፤ የአገሪቱን ሰላምና የሕዝቡን አስተሳሰብ ምን ያህል ጫና እንዳደረሰበት መገመቱ አስቸጋሪ አይደለም። እያየነው ነውና! ችግሮቹ ደግሞ፤ አንደ ችግር ራሳቸው ከመከሰታቸው በላይ፤ የተወሳሰቡ መሆናቸው የበለጠ የከፉ አጥፊ አድርጓቸዋል።
አሁን የተያዘውን በአማራ ላይ ዘመቻ እንመለከት። አማራው፤ በትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ከፖለቲካ ተሳትፎ መገለሉ ከላይ ተቀምጧል። መነሻው የአማራውን መሬቱን እንጂ ሕዝቡን አንፈልገውምና፤ እናጥፋው ነው። እንግዲህ ከዚህ የተነሳው የፖለቲካ ሂደት፤ በስፊው ታስቦበትና ተጠንቶበት የተካሄደ ነው። ምን ማለት ነው? መልካም። ባለፉት ሃምሳ ዓመታት፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በሚደረገው ሂደት፤ የሥልጣን ባለቤትነቱ፤ ከኢትዮጵያዊነት ወደ የትውልድ ማንነት ፖለቲካ አንጋቾች ተዛውሯል። ከዚያ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ዕሴቶችን ማጥፋት ተከትሏል። ያ በዘገምታ እየተከናወነ ነው። አሁን የምናየው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን አማኞችና ተቋማት እየደረሰ ያለው ጥፋት፣ በእስልምና ተከታዮችና በእምነት ተቋማቸው እየደረሰ ያለው ጥፋት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የተደረገው ክህደትና አዲስ ትርክት፣ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ምልክቶችን በማጥፋት የተደረገው ዘመቻ፣ በድምሩ ፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻውን በግልጥ ያሳያል። በአማራው ላይ ለምን ዘመቻው ጠነከረ? የአማራ ክርስትያን ዒላማ ሆኗል። የአማራ እስልምና ተከታይ ዒላማ ሆኗል። የአማራ ባለሀብት ዒላማ ሆኗል። ወለጋ ያለ አማራ ዒላማ ሆኗል። አርሲ ያለ አማራ ዒላማ ሆኗል። የአማራ ምሁራን ዒላማ ሆነዋል። የአማራ ጋዜጠኞች ዒላማ ሆነዋል። የአማራ ባለሙያዎች ዒላማ ሆነዋል። የአማራ ሴቶች ዒላማ ሆነዋል። የሁሉም ጥፋታቸው አንድና አንድ ብቻ ነው። አማራ ሆነው ተወልደው፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለታቸው! ዋና ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው፤ “ኢትዮጵያዊ ነኝ!” ማለታቸው ነው። በኢትዮጵያዊነታቸው ነው በየትኛውም የአገራቸው ክፍል እንኖራለን ብለው የተበተኑት። በተበተኑበት አካባቢ ካሉት ተዋልደውና ሀብት አፍርተው ኖረዋል። ይሄ ኢትዮጵያዊነታቸው ወንጀል ሆኗል። አሁን ያለንበት የፖለቲካ ቀውስ፤ ተከትለውት ለመጡት ቀውሶችና ለአገራችን ሰላም ማጣትና ድህነት ባለቤት ነው። ግለሰቦች በመላ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያዊነታቸው በነፃ መንቀሳቀስ አለመቻላቸው በአገሪቱ ሰላምና ኢኮኖሚ ላይ ያስከተለው ቀውስ፤ መጠኑን መገመት አስቸጋሪ ነው።
አማራው አሁን የያዘው ትግል፤ የሕልውና ትግል ነው። አማራው የማንንም ቦታ ልንጠቅ ብሎ አልተነሳም። የማንንም ንብረት አልነጠቀም። የራሴ ክልል ብሎ መልክዐ ምድር አስቀምጦ ከኢትዮጵያ ልገንጠል አላለም። አማራው የሚያደርገው የሕልውና ትግል፤ ራሴን አተርፋለሁ፤ በዚህም ኢትዮጵያን አድናለሁ! ብሎ ነው። እናም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ፤ የዕለቱ የኢትዮጵያ ጥሪ፤ ከአማራው ጋር ተሰባስቦ ኢትዮጵያን ማዳን ነው። አማራው ቀድሞ ለኢትዮጵያ የቆመበትና አሁን ለሕልውናው በሚያደርገው ትግል ግንባር ቀደም መሆኑ፤ የአማራ ወይም የኢትዮጵያ ብሎ የሚለየው ስለሌለው ነው። ከአምስት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ በአመጽ ተነስቶ ያስከተለው ለውጥ ዋጋ ቢስ ሆኖ፤ የነበረው ስርዓት በአስከፊ ሁኔታ ቀጥሏል። አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ የፖለቲካ እውነታ፤ የአማራ የሕልውና ትግል የኢትዮጵያ የሕልውና ትግል ነው። አማራ በእናቱና በአባቱ አማራ የሆነ ብሎ አጥር አላበጀም። አማራ በተናጠል በአማራነቱ ሲዘመትበት፤ ራሱን የመከለከል የተፈጥሮ ግዴታው ሆኖ፤ አማራ ነኝ ብሎ አስነሳው። እናም ኢትዮጵያዊ በያለበት፤ አማራው መጠቃት የለበትም! ብሎ እንዲነሳ የሚያስገድደው፤ የየራሱ ኢትዮጵያዊነትና የነገ ሕልውና ነው። አማራ ይሄ የአማራ፤ ያ የኢትዮጵያ የሚለው ጉዳይ የለም። ትግሉ የኢትዮጵያ ሕልውና ትግል ነው። አሁን የተያዘው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ዘመቻ ሳይገታ ከቀጠለ፤ ነገ የሚከተለውን መገመት አያዳግትም።
ተመልከቱ፤ አማራው የሚታገለው፤ በመላ ኢትዮጵያ እያንዳንዳችን መዘዋወር፣ መኖር፣ ሀብት ማፍራት፣ በኅብረተሰቡ ክንውን መሳተፍ አለብን! ብሎ ነው። ይህ የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጥያቄ ነው። አማራው የሚታገለው፤ አማራነቴ ወንጀል አይደለም! እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ! ብሎ ነው። ይህ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጉዳይ ነው! አማራው የሚታገለው፤ ክርስትናን ወይንም እስልምናን መከተል፤ የራሴ የግሌ መብቴ ነው! ብሎ ነው። ይህ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጉዳይ ነው። እናም የአማራው ትግል
የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ትግል ነው። አሁን ባለው ሀቅ፤ በኢትዮጵያ ብዙኀኑ ተፈናቃይ፤ አማራ ነው። ይሄ ማለት ሌሎች አልተፈናቀሉም ማለት አይደለም። ሶማሊው ተፈናቅሏል። አፋሩ ተፈናቅሏል። አዲስ አበቤው ተፈናቅሏል፤ ወዘተ። አማራው ግን፤ በሌሎች ክልሎች ብቻ ሳይሆን፤ ለራሱ በተከለለለትም ቦታ ተፈናቃይ ሆኗል። ከሌሎች ቦታዎች፤ አማራ ተፈናቃዮች፤ ባዶ እጆቻቸውን ነፍስ አውጪኝ ብለው ነው አምልጠው የሸሹት። ልጆቻቸው ከትምህርት ገበታ ከራቁ ዓመታትን አስቆጥረዋል። ትምህርት ቀርቶ የሚበሉትና የሚጠጡትም ያለው፤ በሰው እጅ ነው። አሁን እነሱ ላሉበት ሁኔታ ተጠያቂው፤ ኢትዮጵያን የሚገዙት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር መሪዎች አብይ አሕመድና ሽመልስ አብዲሳ ናቸው።
በአገራችን አሁን ያለው የፖለቲካ እውነታ ቀጣይነት የለውም። አንድም ነገ ኢትዮጵያ ፈራርሳ የተበጣጠሱ ትንንሽ ደካማና ደሃ እርስ በርሳቸው የዋጉ አገራት ይኖራሉ። አለያም ሕግና ስርዓት የሌለባት የዘራፊና ተዘራፊዎች መንግሥት የጠፋበት አገር ትሆናለች። ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የኦነግ ብልፅግና ነው። ባገራችን አምስት ሚሊዮን ስደተኛ ሲገኝ፤ ሃያ ሚሊዮን ደግሞ በመፅዋዕት ተቀባይነት ይተዳደራል። አትጠይቁኝ የሚል የኦነግ መሪ ለራሱ ቤተመንግሥት ለመሥራት በትሪሊየን የሚቆጠር ያገሪቱን ገንዘብ መድቧል። ያገሪቱ የገንዘብ አቅምና ያለበት ዕዳ ምን ያህል እንደሆነ ጥቂቶች ነው የሚያውቁት። ትንሹ መሪ ደግሞ ያራሱ ከተማና ቤተመንግሥት ሊሠራ ተነስቷል። እንግዲህ ይህ ነው የአሁኑ እውነታችን። ይህ ተጠያቂው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር መንግሥት መሪ አብይ አሕመድ የሥልጣን ዕድሜውን ባረዘመ ቁጥር፤ የአገራችን እንደ አገር መቀጠል አስተማማኝነቱ እየመነመነ ነው። ይህ መንግሥት መወገድ አለበት። ማስወገዱ ደግሞ የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ነው። አገራችን ኢትዮጵያ ከሁሉ በላይ ናት። ለነገዎቹ ማትረፍ ሳይሆን ለራሳችን አገር እንደይኖረን እያደረገ ያለውን ይሄን መንግሥት አብረን እናስወግደው።
https://amharic-zehabesha.com/archives/183724
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment