Monday, June 19, 2023

ምዥለጋ ወይም ቶርቸር በራስ ካልደረሰ በስተቀር ሥቃዩ አይሰማም !!
" ብቻውን የሚቆጣ እብድ ተብሎ ተቆንጥጦ ይሞታል ። "

ባለቅኔ ፀሐፊ ተውኔት ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን

.........................................................

#image_title

በዓለም ላይ ፣ በሰላማዊ ትግል ና ተቃውሞ  ፤ ብዙሃኑ ከሚያውቃቸው ፣ በታሪክ ድርሳናት ከተፃፉ ግለሰቦች ባሻገር ፣ ከጥቂቶች በስተቀር ዓለም የማያቃቸው  ፣ ለሰው ነፃነት ለፍትህ ፣ ለእኩልነት ፣ለሰብዓዊ መብት ፣ ለእኩል ተጠቃሚነት  ፣ ለፆታ እኩልነት ... ብቻቸውን በብዕርና በአንደበት ብቻ  ጨቋኝና አምባገነን ሥርዓቶችን በየአገሩ የታገሉ ዜጎች ፣ በገዢዎች ተመዥልገው ሞተዋል ።

በእኛም አገር ከንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን አንስቶ ምዥለጋ በጥቂቱና በብዛት እየተከናወነ ለዘመነ “ ብልፅግና “ ደርሷል ።

ባለፉት ዘመናት ሁሉ እና አሁንም   በነፃነት የመናገር እና የመፃፍ መብት በግልፅና በሥውር ክልከላ ተጥሎበት ዜጎች አፋቸውን እንዲቆልፉ በነጭ ለባሾች ፣ ዛሬ ደግሞ በካድሬዎች ና በጠመንጃ አፋኝ ነፃ አውጪዎች ተገደዋል ። በጉማ የሽልማት ሥነ- ሥርዓት ጀግናችን ያሳየችን ሃቅ ይህንኑ ነው ። “ ዝም ካለላልክ  ባግባርህ ፣ በግምባርሽ ጥይት ይቀረቀራል ። “ ነው ። መልዕክቱ ። ኢትዮጵያ ዛሬ በጥቂት ስግብግቦች ( ትላንት ወያኔ ስግብግብ ነበር ብለው ይሳደቡ ነበር ። ዛሬ ከወያኔ የባሰ ስግብግብ ሆነው ተገኝተዋል ። ) አፏ ተፍኗል ።

ሳንሱርድ ወይም አፈና ዛሬም አለ ። ያውም በፖሊስና በአቃቢ ህግ የሚመራ ። በተፈጥሯዊ መብትህ በመጠቀምህ ሌላ ታርጋ ለጥፎ ያስርሃል ። ይከስሃል ።

ይኽንን እውነት ደራሲ እንዳለ ጌታ ከበደ ሥለ ሣንሱር በፃፈው ፅሑፍ ፣ እንዲህ ሲል ያብራራል ። ለዛሬም ይሰራል ።

" በደርግ ዘመን የጠጡት ና ያሰከራቸው የፍርሃት  አልኮሆል _ሀንግኦቨር ( የዞረ ድምር ) እስካሁን ሳይለቃቸው ቀርቶ ነው እንበል ? እባብን ያየ በልጥ በረየ እንዲሉ ።ወይስ የማናውቀው ስውር የመንግሥት መዳፍ ባለማተሚያ ቤቶችን በጥፊ እያጮላቸው ? - አናውቅም  ! እነሱ ግን አናውቅም አይሉንም ፤ ' እናውቃለን ፤  ብንናገር እናልቃለን ባዮች ናቸው ። ( የሥፖርት ጋዜጣ ብቻ ሥንት ነበር ? ሌሎችን ሁሉን አቀፍ መፅሔቶችን ሳንቆጥር ኪነት ነክ መፅሔቶች ሥንት ነበሪ ? በዘመነ ወያኔ / ኢህአዴግ ። ዛሬ እንዲህ የሚነበብ ጋዜጣም ሆነ መፅሔት ለአይን ብርቅ ሆኖ ሲታይ ያስገርማል ።)

' ሟቷል ' ከተባልኩ በኋላ ፣ መሞቴን ላልሰሙ እንዲያሰማ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ጡርንባ ነፊ ሆኖ አዋጁን እንዲናገር በመንግስት ከታዘዘ በኋላ  ፤ አዋጅ ለፋፊዎችን  ውሸታም '  አስብዬ አላውቅም ?

ገጣሚው

“ ...መቃብር ፈንቅሎ - እንደ ክርስቶስ

ትንሳኤ    ጀመረ - የሳንሱር መቀስ ..."

ብሎ የገጠመው ለምን ይመስላችኋል ? ሞቼ ስነሳ ስላየኝ ነው ፤ የእባብን ባህሪ ተውሼ ፤ ከተቀጠቀጥኩ በኋላ አፈር ልሼ ነፍስ ስዘራ ስላየኝ ነው ። አውቃለሁ አምባገነኖች  ያለ እኔ አይሆንላቸውም ። ፤ ያለ እኔ አይናቸው ተገልጦ አያይም ። ሕይወት ምቹ ፍራሽ በመሆን ፈንታ የምታረገርግ አልጋ እንደምትሆንባቸው ያውቃሉ -እኔ ሳንሱር ነኝ የሕይወታቸው ዘብ - የበትረ መንግስታቸው - ጠባቂ - ርዕዮተ ዓለማቸውን አስፈጻሚ  ! ... "

እንዳለጌታ ከበደ  " ማዕቀብ "   ገፅ 90 እና 91 ።

በዚህ መፅሐፍ ክፍል አንድ ላይ " ድርሳነ ሳንሱር " በሚል ርዕስ የኢ- ልቦለዱ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ፣ በሳንሱር የተነሳ ፣ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ፣ በመንግሥት ደህንነት ና ሹማምት የተሰቃዩ ፣  የተጋዙ ፣ በሴራ ህይወታቸው እንዲያልፍ የተደረገ የብዕርና የኪነት ሰዎች እንዳሉ ይተርካል ። የሰው ምሥክርም ያቀርባል ።

እኛም ለታሪክ የጎለተን ፣ በዘመነ ህውሃት / ኢህአዴግ የሥልጣን ጅማሮ እስከ 1997 ዓ/ም የነበረው ነፃ ፕሬስ እጅግ የሚደነቅ እንደነበር እናውቃለን ።በዚህ ረገድ ፣ በወቅቱ  የአገሪቱ ጠ/ሚ የነበሩት አቶ መለሥ ዜናዊ ከሚገባው በላይ ታጋሽነትን ያሳዩ እንደነበር መካድ አይቻልም ። ለዚህም  የጦቢያ መፅሔት ምሥክር ናት ። በ13 ዓመቷ ምርጫ 97 ን ታዝባ ከመሞቷ በፊት ፣ በመፅሔቷ የሽፋን ስእል ሣይቀር የአቶ መለሥን አሥተዳደር ክፉኛ ትተች ነበር ። አቶ መለሥ ዛሬ በህይወት ቢኖሩ ኖሮ ፣ ከመፅሔቷ አምደኞች አያሌ ቁም ነገር እንደገበዩ ይመሰክሩ ነበር ።

ዛሬ ድረስ ያለችው የሪፓርተር ጋዜጣ ባለቤት ጋዜጠኛ አማረ አረጋዊም በፕሬስ ነፃነት ተማምኖ በጋዜጣው ባወጣው ፅሑፍ ሰበብ የክልል ባለሥልጣናት ሳይቀሩ እንዳገላቱት ታሪክ መዝግቦታል ።

ዛሬስ ? ዛሬ እንኳን ህሊናችንን ለመመገብ ይቅርና ሰውነታችን ቆሞ እንዲሄድ የሚረዳው ምግብ መግዣ ቸግሮናል ። ጋዜጦች ፣ መፅሔቶች እና መፅሐፍቶች የህሊና ምግቦች መሆናቸው ቀርቶ   የቅንጦት እቃዎች ሆነውብናል ። ከዚህ ነባራዊ እውነት የተነሳ ድንቁርና በዚች አገር እየተስፋፋ እንደሆነ ግን ሊሰመርበት ይገባል  ።

ወዳጄ ፤ ወስፋቱ እየጮኸ ሬዲዮ ና ቴሌቪዥን  የሚከታተል ፤ የሚያዳምጥና የሚመለከት ሰው ከቶም አታገኝም ።

"እኔ መንግስት ስለሆንኩ ያዳምጠኛል ። " ብለህ የምታስብ ከሆነ ፍፁም ተሳስተሃል ። እዬዬም የሚያምረው  የጠገበ ላይ ብቻ ነው ። በችጋር የተጠበሰ አንጀት ለመጮኽ  የሚችል አንጀት ከቶም የለውምና ።

ዛሬ በመንግሥት እየተያዙ ወደ እስርቤት የገቡት ግለሰቦች ፣  የህዝብን በጠኔ ውስጥ እና በተዛባ የሀብት ክፍፍል ውስጥ መኖርን  የተገነዘቡና ያስቆጫቸው ናቸው ። የህዝቡን  አሁናዊ ችግሩን በመገንዘብ  መንግሥት “የለውጥ  አራማጅ ነኝ ። አሻጋሪያችሁ እኔው ነኝ ። “ በማለቱ መንግሥት  የሥርዓት ለውጥ እንዲያመጣ በብርቱ ይመክሩ የነበሩ ናቸው ። አንዳንዶቹ ጋዜጠኛ በመሆናቸው ከንባብ ክምችታቸው ውስጥ ከአንጎላቸው እያወጡ ህዝብን ያሳወቁ ናቸው ። ከታሪክ አንፃር በግለሰቦች የሚጠነጠኑትን የወገኑ አፈታሪኮች የኮነኑ ናቸው ።  ህገ መንግሥቱ በቋንቋ መደራጀትን በመፈቀዱ በአማራነት ያለመደራጀታችን አሥጠቅቶናል ። ብለው እንደ ኦሮሞ ና ትግሬ የአማራን ህዝብ ለማደራጀት በግልፅ በአደባባይ የተናገሩትን ነው መንግስት አሸባሪ በማለት ፈርጆ ወደእስር ቤት የወረወራቸው ።

ይኽ መንግሥት  የሚያራምደው የውርስ ፓለቲካ ለአጠቃላይ ህዝቡ   እንደማይጠቅም  ካለማየቱ የተነሳ ወይም ከእውነት ጋር መፋጠጥና እውነት አርነት እንድታወጣው ካለመሻቱ የተነሳ ፣  ጠብመንጃ ሳይዙ በሃሳብ እየታገሉ  ያሉ ዜጎችን ፣ ( ጋዜጠኞችን ፣ ምሁራንን ፣ የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች ...) እስር ቤት አጉሯል ። ( የፍትህ ጥያቄ የህግ የበላይነት ጉዳይ ነው ቢባል እንኳ በመንግሥት ላይ ሸፍተው ጫካ ያልገቡትን እና ጫካ የደበቁት ጦር የሌላቸውን ምሥኪን ዜጎች በየጊዜው ቀጠሮ እየሰጡ የዋሥ መብታቸውን መከልከል ፤ ከሃሳባቸው ጋር የወገነን ዜጋ ብቻ ሣይሆን ፈጣሪንም የሚያስከፋ ነው ። )

ደሞም ይኽ የመንግስት ድርጊት በራሱ የመንግሥትን  በራስ ያለመተማመን ወይም ፍርሃት የሚያሳብቅ ነው ። “ አምባገነኖች  ፈሪዎች ናቸው ። “ ያለው ማነው ? እውነት ነው ። ቦካሳም ሆነ ኢዲያሚን ፣  ጋዳፊም ቢሆን ፖልፖት ፤ ወዘተ ። በፍርሃት ብዙ ንፁሐንን ገድለዋል ።  በሃሳብ ልዩነት ብቻ በማሰር ና በመግደል  ብሎም በመመዥለግና  በማሰቃየት ሠላምን አገኛለሁ ማለት ግን ዘበት ነው ።

ሠላም የሚገኘው ፤ ከእውነት ጋር ታርቆ ፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ በመወያየት  ብቻ ነው ። “ ይቅር ለእግዛብሔር ... “ በመባባል ። ይኽንንም  እውነት ከትግራይ ክልል ጋር በተደረገው ጦርነት እና ባልተጠበቀው “ የፕሪቶሪያ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት  ፍፃሚው “ መንግሥት የተማረ መስሎኝ ነበር ።

የትግራይ ጦርነት ፍፃሜ በጠረጴዛ ዙሪያ ድርድር የተገኘ ነው ። ከዚህ ድርድርና ሠላም መውረድ የኢትዮጵያ ህዝብ ትምህርት አግኝቷል ። የኢትዮጵያ መንግሥት ከዛ አውዳሚ ፣ በጣም ዘግናኝና  አሥፈሪ እንዲሁም በእጅጉ አሳፋሪ የእርስ በእርስ ጦርነት ካልተማረ ግን “ መንግስት በተባለው ግዙፍ  መዋቅር ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ከሣይንሳዊ ፓለቲካ ይልቅ በሴራ ፓለቲካ በእጅጉ ያምናሉ  ። “ ብሎ መደምደም ይቻላል ።

ጭራቅ እና የልጆች ማስፈራሪያ መሆን አለባቸው ከተባሉ " የወያኔ " ቁንጮ መሪዎች  ጋር መንግሥት ቁጭ ብሎ በመነጋገር ጠመንጃቸውን እንዲያስቀምጡ ማድረጉን እና ጭራቅነታቸውን መሰረዙን ( ጭራቅ የማድረግና የመሠረዝ የሰው መብት ባይሆንም ) የሰማነው በጠረጴዛ ዙሪያ ነው ።

ዛሬ ወያኔ / ኢህአዴግ የፓርቲውን ስያሜ እንኳን አልቀይርም ብሎ ( ዳሩ ደሃውን የበለጠ ደሃ ከማድረግ አልፎ ሀብታሙንም ደሃ እያደረገ ያለ ፓርቲ መሆኑ ይታወቃል ። ) ዛሬም መሐት አካለ ግዶሎ ሰው ለማምረት የጦርነት ነጋሪት ውስጥ ውስጡን ይመታል ።

በእውነቱ ፣ የጠረጴዛ ዙሪያ ድርድሩን ለሌላ ጦርነት መንደርደሪያ ለማድረግ የትግራይ ጊዜያዊ አሥተዳደርም ካሰብ   ዛሬም ለህዝብ ሞት ፤ ለአካሉ  ጉዳት ፤  መፈናቀል ፣ መራብ ና መጠማቱ ፤ ወዘተ ። ደንታ እንደሌለው ነው ፣ የሚያሳብቀው ።

በነገራችን ላይ ፣ ሰው ጭራቅ ከሆነ ሁላችንም ጭራቆች ነን ። ብዬ ለመደምደም እገደዳለሁ ። ወያኔ የሰው ስብስብ እንደመሆኑ ዓባላቱን በሙሉ በጭራቅነት መፈረጅ ድንቁርና ነው ። ሰው በአንድ ፋብሪካ የተመረተ ጠርሙስ ወይም ቆርቆሮ አይደለም ። ከአንድ መሐፀን በአንድ ጊዜ የተወለዱ መንትዮች እንኳን ፍፁም የሆነ ተመሳሳይነት አይኖራቸውም ። በድምፃቸው ወይም በአንዱ የአካል ክፍላቸው ሊለያዩ ይችላሉና !

ያም ሆነ ይህ ፣ ያን ሰሞን ሁላችንም በስሜት እንነዳ ነበር ። በነገር አሳማሪነቱ ለታወቀ ሁሉ እናጨበጭብ ነበር ። ከተረታው ህዝብ እስከ ከፍተኛ የመንግሥት  ባለሥልጣን  አጨብጫቢነት ነግሶ ነበር ።

ዛሬስ ? ሰከን ብለናል ወይ ? በበኩሌ አይመስለኝም ። " በለው ! ፍለጠው ! ቁረጠው !  "ብቻ ሳይሆን በየከተማው ረብጣ ብር እየመነዘርን  ሰማይን በእርግጫ እየመታን  ፤ በየመድረኩ ፣ ስለልማት ፣ ስለድህነት ቅነሳ ፣ ስለዳቦ መወደድ ፣ ህዝቡ ላይ ሥለተጫነው የኑሮ ውድነት ፣ ... መደስኮር በእውነቱ ፊዝ ነው ።

እውን ህዝቡ ሥለ ራሱ የወስፋት ጩኸት አያውቅምና ነው ፤ በመንግሥት ካድሬ በድግግሞሽ  የሚነገረው ? የመንግሥት ዋና ተግባርስ በመንግሥታዊ ግዛቱ ውስጥ ሠላምና ፀጥታ እንዲሰፍን ያላሰለሰ ስራ የሚሰራ ጠንካራ ማዋቅር መዘርጋት አይደለምን ?  መሰረተ ልማቶችን በመዘርጋት ወይም  ህዝብ ፣ ውሃ ፣ መብራት ና መንገድ  እንዲኖረው ዜጎችን አስተባብሮ በተግባር መንቀሳቀስ አይደለምን ? የሥራ ዕድል መፍጠርስ በከፊል የመንግሥት ድርሻ አይደለም እንዴ ?  የውጭ ግንኙነትን ለአገር ጠቃሚ ማድረግስ  ? የማን ሥራ ነው ? ህዝብ ዳቦ ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲንም እንዲመገብ በዚች አገር ሰፊ ምህዳር መክፈት የለበትምን ?

ሰፊ የፓለቲካ ምህዳር ባለመፈጠሩ እኮ ነው ፤ ዛሬም ግለሰቦች በሃሳባቸው ልዩነት ብቻ እስር ቤት እየታጎሩ ያሉት ። እነዚህ የፓለቲካም ሆነ የነፃ ሃሳብ እሥረኞች  እኮ ፤  መንግሥትና በግራና በቀኝ የተሰለፈው  የኢትዮጵያ ህዝብ በሥሜት ተነሳስቶ  ከሰራው ጥፋት የበለጠ ጥፋት አላጠፉም ። መሳደብ ፣ ማንጓጠጥ ፣ ማጥላላት ፣ መዛት ና መፎከርን ሁላችንም በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ፈፅመናል ። ጥቂት የማይባሉ ዜጎችም ከግራና ከቀኙ ተሰውቷል ። አካሉን አጥቷል ። ...

በዛን ጊዜ  በስመ ወያኔ ፍፁም የማያኗኑር " ሰው ጠልነትን "   በሰላማዊ ሰልፍ ሳይቀር አንፀባርቀናል ። በሰሜኑ ያለው ወንድምና እህታችን በመሪዎቹ ተነጂ እንደነበረ  ሁሉ በተቃራኒነት የተሰለፍንም ተነጂ ነበርን ።

ከተነጂነታችን አንፃር የፈፀምናቸውን ጥፋቶች ዛሬ ስናስተውል ፍፁም እናፍራለን ።... ከተተብተብንበት አዚም የተነሳ ...ሰውን በሰውነቱ ማየት እኮ አቁመን ነበር ። ዛሬም ከዛ አዚም የተላቀቅን አይመስልም ።

አንዳንድ የመንግስት ባለሥልጣናትም ከአዚሙ የተላቀቁ ያለመሆናቸው ድርጊታቸው ያሳብቃል ። ከአዚሙ  ቢወጡ  ኖሮ ፤ በተጨባጭ የሚታየውን የሥግብግብነት ተግባር እና ህገመንግስታዊ ችግር   እና መፍትሄ   በኃይለ ቃል  ወይም በአንክሮ  የሚነግራቸውን ሰው ይወዱትና ያከብሩት ነበር  ። እብድ በማለት በመመዥለግ ለመግደል ወደ እስር ቤት አይወረውሩትም ነበር  !
https://amharic-zehabesha.com/archives/183687

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...