Thursday, June 15, 2023
አገራችን በውጥንቅጥ ባለችበት በዚህ ወቅት ከፋፋይ አሳብ መሰንዘር ተገቢም የማይመከርም ቢሆን፣ ግን ስለዚህ ሲባል ዝምታን መምረጥ ሐቅን ለሐሰት ከመሠዋት አያንስም። ውሸት ቢደጋገም እየዋለ እያደር የሐቅነትን ዳባ ለብሶ፣ እሳት ጐርሶ፣ ራሱን በእውነትነት ከመተካት ወደኋላ አይልም። ይሁንና ቅዠት አለ ተብሎ ሳይተኛ እንደማይታደር ሁሉ፣ የከፋ ችግር እንዳይመጣ ሲባልም፣ እውነትን መድፈን ተገቢ አይደለም ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው። ሐቅ የጊዜ ገደብ የለውምና፣ አሁን ጊዜው አይደለም ብሎ መተቸት አያዋጣም። ትክክል ያልሆነ ነገር ከታየ፣ ጊዜው አይደለም ብሎ ዝምታን መምረጥ፣ የድርጊቱ ተባባሪ ከመሆን ባሻገር ያስወቅሳልም።
ብዙዎቻችን እንደምናውቀው የብሔር ብሔረሰብና የመደብ ጭቈና ታሪክ፣ ትርፍ ጊዜውን እንዴት እንደሚያጠፋ ያጣ፣ የሺዘጠኝ መቶ ስድሳዎቹ የቦዘኔው ተማሪ የበሬ ወለደ፣ የ ሐሰት ብቻ ሳይሆን የምናባቸውም ትርክት ውጤት እንደሆነ አይካድም። ተማሪው በአገራችን ተከሥቶ የማይታወቀውን፣ በምንም መልክ የሌለውን፣ በምዕራባውያን የታሪክ መጻሕፍት ሳያገናዝብ ያነበነበውን የመደብና የብሔር ጭቈና አላንዳች ተጨባጭ ማስረጃ ድርቅ ብሎ በኢትዮጵያም አለ ሲል በመስበክና በመንዛት ሌላው ቀርቶ የበቃሁና የነቃሁ ነኝ ባዩንም ክፍል እስከማሳመን ደርሷል። በርካቶች የኋላኋላ የትም የማያደርስ፣ የተማሪው የእምቦቃቅላነት ዕድሜ ጥንስስ ነው ብለው ቢያምኑም፣ ሐቁ ግን እነሱ እንደገመቱት ሳይሆን፣ አቀንቃኞቹ በትረመንግሥት ለመጨበጥ በቅተው፣ ራእያቸውን እግብር ለመተርጐም ሲሉ አሁን አገራችን ላለችበት ትርምስና ቀውስ እንዲፈጠር ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክተዋል። እውነት እያደር ይጠራል እንደሚሉ፣ የተማሪዎቹም ሐሰት ለብዙዎቹ እየተገለጸ ያለው አሁን ገና ነው። ይሁንና ያስከተለው መዘዝ በቀላሉ የሚቀለበስ ባለመሆኑ አገር በሞትና በሕይወት መኻል እየጣረች ትገኛለች።
በዓለም፣ በተለይም በአፍሪቃ ውስጥ ካለው ማንኛውም ሕዝብ፣ ከእንጅላትና ከቅድመአያት ጀምሮ ሲወርድ ሲወራረድ በጋብቻና በደም የተዋሀደ፣ ባህሉ የተሳሰረ፣ እምነቱ የተወራረሰና የተከለሰ እንደኢትዮጵያ ያለ አገር የለም ማለት ይቻላል። ተማሪዎቹ በተግባር ያልታየውን ብቻ ሳይሆን፣ ሊኖር እንኳን የማይታሰበውን የብሔር ብሔረሰቦችና የመደብ ጭቈና ትርክት ነፍስ ዘርተውበት አሁን ላለው ሥርዐት መሠረት ስለጣሉለት ሕያው ሁኖ እያገለገለ ይገኛል። ዛሬም አንድ በድግግሞሽ እየተነገረ ያለው የሐሰት ትርክት ቢኖር፣ በቅርቡ በብልፅግና ጉጅሌ (ፓርቲ) ተካሄደ የሚባለውን ብሔራዊ ምርጫን ይመለከታል። ይኸም ትርክት ነፍስ ዘርቶ፣ እውነት ተላብሶ በመነዛት ተረካቢውን ትውልድ እንዳያሳስት፣ በእማኝነት ለታሪክ ማስቀመጥ ይገባል ባይ ነኝ፤ የነፃነት መስፈርቷም መርህዋም እውነት ናትና።
በሥልጣን ላይ ያለው የብልፅግና መንግሥት ራሱን በሰፊው ሕዝብ እንደተመረጠ አድርጎ የማቅረብና ምርጫውንም አስቀድመውት ከተካሄዱት ሁሉ መስፈርቱን በማሟላት ታሪካዊ ብሎ ወሬ እስከማናፈስ ደርሷል። በኔ ዕይታ ስለዚህ ምርጫ ሁለት አነታራኪ ነገሮች እየተነገሩን ናቸው። አንደኛው፣ ብሔራዊ ምርጫ በወያኔ የተጀመረ በማስመሰል፣ በቊጥር ተራ ደርድሮ "ስድስተኛው" ብሎ የመጥራት አባዜ አለ። ወያኔዎች ሁሉም ነገር በነሱ ዘመን እንደተፈጠረ አድርገው በማቅረብ ምሁር ነኝ ባዩን እንኳን ስላወናበዱ፣ በርካታው እነሱ የነዙትን ሐሰት ሳያጣራ እየደገመው፣ በየጊዜው አላንዳች ኀፍረት ሲያስተጋባ ይታያል።ይኸ አብዛኞቻችን መወቀስ ያለንበት ጉዳይ መሰለኝ። ብዙዎች አዲስ መንግሥት በመጣ ቊጥር የሚሰብክላቸውን ከእውነት የራቀ ወሬ ብዙም ሳያገናዝቡ ተቀብለው እንደገደል ማሚቶ ማስተጋባትን እንደሙያ አድርገው ከያዙ ቈይቷልና። ወያኔ ሌላው ቀርቶ እውነተኛዋ ኢትዮጵያና መንግሥቷም ራሱ በሱ ዘመን የተፈጠሩ እንደሆኑ አድርጎ የማቅረብና የማሳመን ዝንባሌም አሳይቷል። ባንድ ቃል፣ የሁሉም ፈርቀዳጅና ጀማሪ እሱ እንደሆነ ከመስበክ ታክቶ አያውቅም ማለት ይቻላል።
በግሌ ዕይታ፣ ሕዝባዊ ምርጫ በወያኔ ዘመን ከፋ እንጂ አልተጀመረም። ዕድሜ ተለግሦልኝ ሦስት የተለያዩ የአስተዳደር ሥርዓታት በሕይወቴ ዐይቻለሁ። ሦስቱም ሕዝባዊ ምርጫ አካሂደዋል። ደርግ በእምነቱ መሠረት አቋሙን የሚያንፀባርቅ ሕዝባዊ ምርጫ አድርጓል። ግን በልጅነቴ በንጉሠነገሥታችን ዘመን ካየኋቸው ሕዝባዊ ምርጫዎች የተሻለ እስካሁን ድረስ አንድም አልታየም ለማለት በግልጽ እደፍራለሁ። የዚህ ምርጫ ሥርዐትና ሂደት እጅግ በጣም እየተሻሻለ በመጣበት ወቅት ደርግ አጨናገፈው እንጂ። ይኸ በ"ዘውዳዊ"ሥርዐት ዘመን የሆነ በመባል የሚንኳሰስና የሚንቋሸሽ ምርጫ በብዙ ረገድ መደነቅ ያለበት ነው ባይ ነኝ። ዋነኛው ምክንያት በአገራችን የምርጫን መሠረት የጣለ ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቷን ነባር ሁናቴ ያገናዘበና የመጀመርያ በመሆኑ። እስኪ በዚህ ጥቂት ላክልበት።
በአገራችን አቈጣጠር በሺዘጠኝ መቶ ኻያሦስት ዓ.ም. የተደረገው የመጀመርያው ምርጫ ሰፊው ሕዝብ ባይሳተፍበትም፣ ሕገመንግሥቱም ሥልጣኑን በመሳፍንት፣ በመኳንንትና በባላባቶች እጅ ቢተወውም፣ "ወደፊት ሕዝቡ ራሱ መብቱንና ግዴታውን ዐውቆ ራሱ በቀጥታ እንደራሴውን ለመምረጥ ከሚችልበት ደረጃ እስኪደርስ ድረስ" በማለት የማታ ማታ መራጩና ተመራጩ ማን መሆኑን በግልጥ ይነግረናል። ሥልጣን ይዘው እወንበሩ ላይ ተቀምጠው ያሉት መኳንንትና መሳፍንት፣ እንዲሁም የየአገሩ ሽማግሌዎች ሥፍራውን የያዙት በሞግዚትነት እንጂ በይገባኛል እንዳልሆነ በይፋ ያስታውቃል። ይሁንና ምርጫው በሸንጎው ውስጥ በማዕርግ እጅግ በተራራቁ መሳፍንት፣ መኳንንትና ባላባቶች መካከል እኩልነትን እንዳነገሠ አይካድም። መጻፍና ማንበብ የሚችል በጣት የሚቈጠር በነበረበት ወቅት፣ የሕዝቡም ቊጥር ስንት መሆኑ በማይታወቅበት አገር፣ ከዚህ የተሻለ ምርጫ የሚጠብቅ ሰውም ሆነ ድርጅት ደግሞ በሕልም ዓለም የሚኖር ብቻ ነው ብል የተሳሳትሁ አይመስለኝም። በወቅቱ የነቃው ክፍል የመሳፍንቱ፣ የመኳንንቱና የባላባቶቹ ነበርና። አሁን በሠለጠነው የምዕራብ ዓለምም እንኳን ቢሆን፣ በመጀመርያዎቹ ምርጫዎች ዕጩዎቹ መሳፍንቱ፣ መኳንንቱና ባላባቶቹ ሲሆኑ፣ እነሱም ራሳቸውን ያስመርጡ የነበሩት በመግለጫና በልምምጫ ብቻ ሳይሆን ይልቅስ ይበልጥ በርግጫና በግልምጫ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል።
ዘውዳዊ ሥርዐትን ለሚያጥላላ ወይንም ለሚጠላ ካልሆነ በስተቀር፣ንጉሠ ንጉሠነገሥቱ ከሥልጣናቸው ከመውረዳቸው በፊት የተደረገው የመጨረሻው ምርጫ፣ ያንዳንድ የሠለጠነውንም ዓለም ሳያስንቅ አይቀርም ነበር ማለት ይቻላል። ተመራጮቹ የተለያየ አመለካከትና አስተሳሰብ ባላቸው በጐባን ጉጅሌዎች (ፓርቲ) ባይከፋፈሉም፣ በመካከላቸው የነበረው ውድድርና ፉክክር፣ ለመራጩ ሕዝብ ይገቡ የነበሩት የተለያየ ቃልኪዳን (ተስፋ)፣ የመልእክታቸው ርጥበት፣ ከዚያ ወዲህ በአገሩ ውስጥ በተካሄዱት በማንኛቸውም ምርጫዎች አልታዩም። በደርጉም ሆነ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ማለትም በወያኔ ዘመን የተካሄዱት በምንም መልኩ ልነጻጸሩት አይችሉም። እጅግ አሳፋሪ ስለሆኑ። ይኸ በሺዘጠኝ መቶ ዐምሳ ሦስት ዓመተምሕረት ላይ የተደረገው ምርጫ እጅግ በጣም በትምህርት የመጠቁ፣ በአስተሳሰብ የነቁ፣ በቃላቸው የጸኑ ዕጩዎችን ያካተተ ነበርና። በተግባሩም ሆነ በባሕርዩ የያኔ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደወራሾቹ የደርጉና የወያኔው እንዲሁም የተተኪው ብልፅግና ዐይነቶች፣ የምንደኞችና የጐጠኞች ክብረቢስ ስብስብ ሳይሆን፣ እንደቃሉ በሐቅ የአገርና የሕዝብ እንደራሴ ሸንጎ ነበር ማለት ይቻላል። ይኸም ማለት እንደኋለኞቹ ተተኪዎች፣ ‘እንደራሴዎቹ’ በሥልጣን ላይ የነበረው የመንግሥት አካልም ሆነ፣ የሹማምንቱ ምክር ቤት ደንገጡሮች አልነበሩም። ይልቅስ ምክርቤቱ ከገዢው አካል የቀረበውን ሕግ ሲሽር፣ ሲያሻሽል፣ ሚኒስቴሮችን ጠርቶ ሲፈትሽ፣ የቀረበለትን ወጪና ገቢ በማጽደቅና ውድቅ በማድረግ ጠንካራ ክንድ እንዳለው በተደጋጋሚ አሳይቷል። ምክር ቤቱ የሞላው፣ እንደደርጉም ሆነ፣ እንደወያኔ እንዲሁም እንደብልፅግና፣ በመንደር ጐልማሶችና በሆዳቸው ላደሩ ምንደኞች ሳይሆን ምራቃቸውን በዋጡ፣ በቀዬአቸዋም ሆኑ በአገር ደረጃ፣ ከዚያም ባሻገር በባሕርማዶ ሳይቀር የተከበሩ፣ ይሉኝታ ያላቸው፣ በአገራቸውና በሕዝባቸው ጉዳይ የማይደራደሩና፣ እንደገደል ቀጥ ብለው የቆሙ ባለግርማ ግለሰቦች እንደነበሩ የሚካድ አይመስለኝም። ይኸንን ለመረዳት አመራረጡን ወይንም የምርጫውን ሥነሥርዐት ማየቱ ይበቃል። መራጩ ከተመራጩም ሆነ ከገዢው ክፍል አንዳችም ግልጥ ተፅዒኖ አልነበረውም ማለት ይቻላል። እንደደርጉ ዘመን በአብዮት ጠባቂዎችና ዘበኞች እየተጐሰጐሰ ወጥቶ በጠበንጃ አፈሙዝ እንደከብት እየተነዳ ወደምርጫ ጣቢያ አይሄድም። ወይንም እንደወያኔዎቹ በደላሎችና በጀሌዎች እየተወተወተ በመሰለፍ አይደለም። መራጩ፣ በገዛ ፈቃዱ በፈለገበት ወቅት በቀጥታ ወደምርጫ ጣቢያ ይሄዳል። የሚመርጠውም በሕዝብና በመንግሥት መካከል ሁኖ አገር ለማገልግል ይበቃል ብሎ ያሰበውን ተወዳዳሪ እንጂ በኢሕአዴግ መሪዎች ወይንም በጀሌዎቻቸው ተመልምለውና ተመርጠው ድምፁን እንዲሰጥላቸው የተመደበላቸውን አይደለም።
በተመራጮቹም ቢሆን ልዩነቱ የጐላ ነበር። ለዕጩነት በአካባቢው ለተወሰነ ጊዜ መኖርንና ሳያንስ ሳይበልጥ የዐምሳ ሰው ድጋፍ እንጂ እንደወያኔ የአንድሺና የሁለትሺ ሰው ፊርማ መሰብሰብ ወይንም የአካባቢው ብሔረሰብ አባል መሆን አይጠበቅበትም። ወይንም እንደደርጉ መንግሥት የሰው ድጋፍ ቀርቶ ራሱን እንኳን ለመራጭ ሳያስታውቅና እምርጫው ጣቢያ ሳይሄድ የአሸናፊነት ምስክር ወረቀት በመታደል አልነበረም።
እስኪ የደርግንና የወያኔን ወደጐን አድርገን እንለፈውና፣ ይኸንን አብዛኛው ሕዝብ የተሳተፈበትና ታሪካዊ ነው ከሚባለው ‘ከስድስተኛ’ው የብልፅግና ጉጅሌ ምርጫ ጋር እናወዳድረው። ምርጫ ቢያንስ፣ ማለትም ከልክ በላይ ዝቅ ተብሎ ቢታሰብ፣ ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን ያካትታል፤ ተወዳዳሪ ግለሰብ፣ ወይንም ጉጅሌና የሚያረጥብ መርሕ። “በኛ አስተዳደር ዘመን ኢትዮጵያ ትበለፅጋለች” ብሎ ከመስበክ ውጭ ብልፅግና ሌላ ያስተላለፈው መልእክት፣ ወይንም ርጥበት አልነበረም። ድህነትና ችጋር ለጠበሰው ሆድ፣ ዕውቀት ላላዳበረ አንጐል፣ ንግግሩ ርጥበት ሊኖረው ይችላል። በቀላሉ ስለሚታለል። ግን እንዴትና በምን ይኸ ሊሆን ይችላል ብሎ በቅጡ ለሚጠይቅ አጥጋቢ መልስ ነው ብሎ ማመን ያስቸግራል። አሁን ባለው ሥርዐት ላይ ተንተርሶና ጥገኛ ሁኖ ከሆነማ የኋላ ኋላ የሚጠበቀው ብልፅግና ሳይሆን ጒስቁልና፣ አለበለዚያም ቀጠናና ዲና መሆኑ የሚያጠራጥር አይመስለኝም። ፍሬውን በገዛ ዐይናችን አሁን ላይ እያየን ስለሆነ። በብልፅግና ዘመን ለተረኛ ነኝ ባዩ፣ ፓለቲካ ቁማር እንደሆነ መረሳት የለበትም። ብልፅግና የሚለው ቃል ራሱ ትርጒም የለሽ የባለቁማሩ የቃላት ጨዋታና ጋጋታ ሲሆን፣ አሁን ነግሦ ባለው ሥርዐት ከተኼደ ደግሞ መጨረሻው ያንድ ብሔር ጭቈና የማይሆንበት ምክንያት የለም። ስለዚህ ብልፅግና እንደመፈክር በተወናበደና በድኅነትና በችጋር ለተጠበሰ ሕዝብ ዘንድ ርጥበት ቢኖረውም፣ በግብር ደረጃ ግልጥ የሆነ ምንም የተባለ ነገር ስለሌለ ተፎካካሪ መርህ አለ ለማለት ያስቸግራል።
ተወዳዳሪ ግለሰብ ወይንም ጉጅሌ ካየን ደግሞ፣ ምርጫ ነበር ከተባለ በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ ካልሆነ በስተቀር እሌላ ጋ ነበር ለማለት በጣም ያዳግታል። በቀረው በአብዛኛው አካባቢ ቅርጫ እንጂ ምርጫ አልነበረምና። ዕጩዎቹ በየጉጅሌአቸው መሪዎች ተመልምለውና ተመርጠው የሚቀርቡት ለውድድር ሳይሆን ቅርጫቸውን ለመረከብ ነው ማለት ሐቀኛ መግለጫው ነው። ስለዚህ ተመራጮቹ ለሐሰት ድል የበቁት በውድድር ሳይሆን የምርጫውን ቦታ እንደቅርጫ ሥጋ በመከፋፈል ነው። ኦቦ ሺመልስ አብዲሳ፣ ወይንም ያ "ዶክተር"ሳይሆን ተሳዳቢና ቅሌታም የሚል ስያሜ የሚገባው ጣፍወርዴ ጐልማሳ ወደሸንጎ ሊገቡ የቻሉት በተሰገሰጉበት የጐሣ ድርሻ፣ በተደበቁበት የጐጥ ዋሻ እንጂ በሕዝብ ምርጫ አይደለም። አቶ ዐቢይ አሕመድስ ቢሆን። እርሱ ምርጫው “ታሪካዊ” ነው ሲል ቢያክላላም፣ እውነቱ ግን በተመረጠበት አካባቢ ጉጅሌውም ሆነ ራሱ ከሌላ ጋር ተፎካክሮ ነበር ወይ ብሎ መጠየቅ የግድ ይላል። መልሱ ግልጥ ነው። ከማንም ጋር አልተወዳደረም ብቻ ሳይሆን፣ ለጉጅሌው ሊቀመንበርነትም ሆነ፣ ከዚያም ዐልፎ ለጠቅላይ ሚኒስቴርነት የበቃው ራሱን በራሱ በመሾም ወይንም በሽንገላ በመጫን ነው። ስለዚህ በምንም መልክ የኢትዮጵያን ሕዝብ አይወክልም ማለቱ እንደጠራራ ፀሓይ ግልጽ የሆነ የማይካድ ሐቅ ነው።
ይኸ የኔ የግሌ ግንዛቤ ብቻ ሳይሆን፣ ስለምርጫው አስተያየት የሰጡት ሁሉ የሚስማሙበት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ሁለቱን ብቻ እንጥቀስ። ሌላው አካባቢ ቀርቶ ተፎካካሪነት በመጠኑ የሰፈነበት ነው በተባለው በአማራ ክልል እንኳን፣ ምርጫውን ያሸነፈው የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባል አቶ ደሳለኝ ጫኔ ለአሶሼትድ ፕሬስ እንደተናገረው ምርጫ ቦርድ በጥቅሉ ጥሩ ቢሠራም፣ “ዋና ግዴታው በሆነው ማለትም በገለልተኝነትና ለቅሬታዎች ፍትሃዊ ፍርድ በመስጠት ረገድ በደምብ አልተወጣም። የሰፈሩ ምርጫ አስፈፃሚዎች፣ የታጠቁ ሰዎችና ጀሌዎቹ የምርጫ ታዛቢዎችን አርማ እየነጠቁ ይደበድቧቸው ነበር" ይለናል። የአሜሪቃ መንግሥት በበኩሉ ምርጫው ከፍተኛ ጉድለት ያለበት ነው ሲል ፈርጆታል።
የምርጫውን ጊዜ አለሕግ በማራዘም፣ የሚያሠጉትን ተፎካካሪ ጉጅሌዎችን መሪዎች በተለያየ ሰበብ በእስርቤት በማጐር፣ የምርጫው ሜዳ በደምብ ለብልፅግና ጉጅሌ ተስተካክሎ እንደተዘጋጀለት አይካድም። በተጨማሪ፣ የብልፅግና ጉጅሌ ሕዝባዊ መገናኛውን ብቻ ሳይሆን፣ የየቀበሌውን ሕዝብ የየዕለቱን እንደጨው፣ ዘይትና ሌላውንም መሠረታዊ የኑሮ ፍላጎቶቹን ቊጥጥር ሙሉ በሙሉ እሥሩ በማድረግ፣ የያንዳንዱን ቤት እያንኳኳ እንዲመዘገቡ በማስገደድና ለብልፅግና ድምፅ እንዲሰጡ በማዘዝ የምርጫው ውጤት ምን እንደሆነና ልምምዱም የውሸትና የይስሙላ መሆኑን ገና ከመነሻው አረጋግጧል። በዚህ የምርጫ ቦርዱ በተለይም ወይዜሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ሜዳውን ለብልፅግና በማመቻቸት የተጫወተችው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ አይካድም። እንደአንድ ጸሓፊ አባባል የቦርዱ ሊቀመንበር፣ የሿሚዋ የዐቢይ ብልፅግናና፣ በቅንጅት ዘመን የትግል ጓደኛዋ የነበረው የብርሃኑ ነጋ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ፣ ጥገኛና ወገንተኛ ከመሆን ዐልፋ፣ ከፓርቲ ምዝገባ እስከመሰረዝ እንዲሁም የቅሬታ አያያዝ የመሳሰሉትን መሠረታዊ የሆኑ የምርጫ ሕግ በመጣስ፣ በአ.አ. በሁለትሺ ዐምስት ዓ.ም. ምርጫ ስትቃወም የነበረችውን ተግባር ሁሉ አስገራሚና አሳፋሪ በሆነ መልክ በዚህ ምርጫ ፈጽማለች በማለት ሲዘልፋት፣ ከላይ የጠቀስሁትን የአቶ ደሳለኝ ጫኔን ምስክርነት ያጠናክራል።
ይኸ ሁሉ እንዳለ ሁኖ፣ በእውነትም ምርጫው የሚደነቅበት አንድ ገጽ አለው። በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ማዶ የነበረው ተመልካች ብዙ ብጥብጥና ውጥንቅጥ እንዲሁም ደም መፋሰስ የመላበት እንደሚሆን ሲጠባበቅ፣ በተቃራኒው የብዙውን አገር (አንዳንድ የሠለጠንን እኛ ነን ባዮችንም ሳይቀር) የሚያስንቅ ሰላምና ርጋታ የሰፈነበት ምርጫ መሆኑ አይካድም። ከዚያ ውጭ የመጀመርያው ሐቀኛ ምርጫ ነው ማለት ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ከመሆን አያልፍም። ስድስተኛም ነው ማለት ትክክል እንዳልሆነ ሁሉ፣ ምርጫም ነው ብሎ መጥራቱ እውነቱን አያንፀባርቅም። ኢትዮጵያ በወያኔ እንዳልተፈጠረች ሁሉ፣ ምርጫም የዚሁ ‘ሽብርተኛ’ በመባል የሚታወቀው ድርጅት ልጅ አይደለም። የጀመረውም ሆነ በአገባቡ እየተካሄደ የነበረው፣ ኢትዮጵያን ለክብርና ለታላቅነት ባበቋት ነገሥታት ሥር እንጂ፣ ዛሬ ያንን ሁሉ ረስተው በሚያብጠለጥሏቸውና ፓለቲካን እንደነሱ ለመልካም አስተዳደር አስፈላጊ ጥበብ ሳይሆን የቁማር ጨዋታ እንደሆነ በሚሰብኩልን የመንደር ጐልማሶች ዘመን አይደለም። ባይሆን ሌላው ቢቀር ተገቢው ዕውቅና ለሚገባው ይሰጥ፤ መሸፋፈን ቀርቶ እውነት ሳይሟጠጥ ይገለጥ።
ቸር ይግጠመን።
https://amharic-zehabesha.com/archives/183397
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment