Wednesday, June 7, 2023

አማን ነወይ ቅየው! - በላይነህ አባተ
አማን ነውይ አገር፣ ቅዬውና አድባሩ፤

አማን ነወይ ሕዝቡ፣ ጎልማሳው ወጣቱ፣

ለአገር ስል ልገፋ ብሎ በማሰቡ፣

ግፍ እንደ ዶፍ ዝናብ የሚወርድበቱ፣

በአጥንቱ ካስማነት ባቆማት አገሩ!

አማን ነወይ ሎሌው ባንዳስ አማን ነወይ፣

ንስሃ ውስጥ ገብቶ ልብን አልገዛም ወይ፣

ምሳር ዛቢያ ሆኖ ወገንን ማስጨፍጨፍ አልሰለቸውም ወይ፣

አማን ነወይ ናዝሬት፣ አሰላ አማን ነወይ፤

አማን ነወይ ጅማስ፣ ሚዛን አማን ነወይ፤

አማን ነወይ ድሬ፣ ሀረር አማን ነወይ፤

አማን ናት ወይ ሻሹ፣ ጎባስ አማን ነወይ፤

አሩሲ ነገሌ፣ ዝዋይ አማን ነወይ፤

ግፍን መታገሱ አልሰለቸውም ወይ?

አማን ነወይ ህዝቡ፣ አማን ነወይ አገር፤

ስንት ሌሊት ያንጋ፣ ይሄ ችሎ ማደር?

አማን ነወይ ደሴ፣ አማን ነወይ ምንጃር፤

አማን ነወይ ማርቆስ፣ አማን ነወይ ጎንደር፤

አማን ነውይ ታቦር፣ ወልድያ ባህርዳር፤

ምናለ ሲታረድ፣ ወገኑ ተዳር ዳር?

አርማጮ አማን ነወይ፣ ጃናሞራ ሰሜን፤

ሸበል አማን ነወይ፣ ጉባያና ለምጨን፤

ወልድያ አማን ነወይ፣ ቦረና ሳይንትን፤

መራኛ አማን ነውይ፣ አንኮበር ጥግ ጥጉን፤

ወዴት ልንደርስ ነው፣ ተገፍተን ተገፍተን?

ጠለምት አማን ነወይ፣ ራያ ወልቃይት፤

ደራስ አማን ነወይ፣ ከሚሴ መተከል፤

ዘር የሚዘሩበት፣ ነቅለው የኛን ተክል!

ደንበያ አማን ነወይ፣ አማን ነወይ ዳሞት፡

ሰቆጣ አማን ነወይ፣ አማን ነወይ ጋይንት፤

ብቸና አማን ነወይ፣ አማን ነወይ ሰቀልት፤

ባቲስ አማን ነወይ፣ አማን ነወይ ተጉለት፤

ታልጋው አስወርደው፣ ወለል ቁጪ በል ያሉት?

አማን ነወይ ዳባት፣ ጃግኒስ አማን ነወይ፤

አማን ነወይ መቄት፣ ሸንኮራ አማን ነወይ፤

አማን ነወይ ሞጣ፣ እስቴስ አማን ነወይ፤

አቸፈር ወንድዬ፣ ማጄቴ አማን ነወይ፤

ልቻል ብሎ ማደር፣ ጤና ላይሆን ነወይ?

አማን ነወይ ግሼ፣ ሰቆጣ አማን ነወይ፤

አማን ነወይ ፋርጣ፣ ዳንግላ አማን ነወይ፤

እነሴ እነብሴ፣ በለሳ አማን ነወይ፤

አማን ነወይ ዋድላ፣ ጭልጋስ አማን ነወይ፤

በደል ቁና ሞልቶ፣ ተርፎ አልፈሰሰም ወይ?

አማን ነወይ ዳሽን፣ ጮጬስ አማን ነወይ፤

በላያ ተራራ፣ የጎፍ አማን ነወይ፤

ቆሞ መመልከቱ፣ አልሰለቸውም ወይ?

አማን ነወይ ዓባይ፣ ግዮን መቀነቱ፤

ተከዜ አማን ነወይ፣ ስንቱን ያየው ባይኑ፤

አማን ነወይ ጀማ፣ መሀሉ ዳርዳሩ፤

አማን ነወይ በሽሎ፣ ድንብልዙና ስርጡ፤

አልሰለቸውም ወይ፣ ዝምብሎ መፍሰሱ?

አማን ነወይ ፋኖ አርበኛ አማን ነወይ፣

የጎብዝ አለቃ ሶታው አማን ነወይ፣

አንበሳና ነብሩ ጎሹስ አማን ነወይ፣

ተገፍቶ ተገፍቶ ጫፍ አልደረሰም ወይ፣

የአምስቱ ዘመን ድል አልሸተተውም ወይ፣

ሞረሽ ተጠራርቶ በአንድነት መክሯል ወይ?

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

መጀመርያ ጥቅምት ሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓ.ም.

እንደገና ሰኔ ሁለት ሺ አስራ አምስት ዓ.ም.

 

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/183218

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...