Thursday, May 25, 2023

አዲስ አበባ፡ እህት ዋና ከተማ ያሻት ይሆን? (ዳንኤል ካሣሁን)
አዲስ አበባ ከፌደራል ዋና ከተማነት ባሻገር ከኒዮርክና ጄኔቫ ቀጥሎ ሶስተኛዋ ትልቋ የዲፕሎማቲክ ዋና ከተማ ናት ይባላል። በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት፣ በርካታ የተባበሩት መንግስታት ቅርንጫፍ ተቋማት፣ ኤምባሲዎች፣ ቆንሲላዎች የሚገኙባት እንዲሁም አሕጉራዊና ቀጣናዊ ጉባኤዎች የሚስተናገዱባት ከተማ ናት። ስለዚህም በአፍሪካም ሆነ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ አዲስ አበባ “ከባድ ሚዛን” የተጎናፀፈች ከተማ ናት ቢባል ማጋነን አይሆንም። ዘርፈ ብዙ ሚና እና ኃላፊነትን የተሸከመች ከተማ አቅሟ የፈረጠመ ቢሆንም ፈተናዋም በዚያው ልክ ወደር የለውም። ይህ የተወሳሰበ ህልውናዋ እክል ቢገጥመው ዳፋው የትየለሌ ነው፤ too big to fail እንዲሉ።

 

አዲስ አበባ በተስፋ ወይንስ በሥጋት ጎዳና?

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ አበባ ፈጣንና ዘርፈ ብዙ የመሠረተ ልማት እድገትን እሳይታለች፤ በፖለቲካው አውድ ደግሞ ጫፍ የረገጡ አጀንዳዎችን እያስተናገደች ናት። በከተማው እየተፈጠረ ያለው ቅጥ አልባ የኢኮኖሚ ሃብት ክምችት የበርካታ የፖለቲካ ቡድኖችን ቀልብና ትኩረት ስቧል። የያዙትን አመራር ላለማጣት ወይንም መሪውን ለመቀበል የሚያስችል መላም እየሻቱ ነው። ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ ሲናገሩ “ቅጥ አልባ የሥልጣን ሽሚያ የፖለቲከኞቹን አስቀያሚ ድብቅ ገመና ያወጣል፣ ቀድሞ ተላብሰው የነበረውን ሥነ ምግባርና መርህ በማክሰም ወደ አክራሪነት ያወርዳቸዋል”። ይጠቅመናል የሚሉትን የህዝብ ብዛትን፣ ታሪክን፣ የጂኦግራፊያዊ ቀረቤታን፣ ሕገ መንግስታዊ አንቀጽን፣ ወዘተ እየጠቀሱ የባለቤትነት ሽሚያ ፉክክሩን አክርረውታል። በውጤቱም የሥጋት ደመና ያጠላው በከተማዋ የፖለቲካ አየር ላይ ብቻ ሳይሆን በመኖር ዋስትና ላይ ጭምር መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ጫፍና ጫፍ ላይ የሚገኙት የአዲስ አበባ ፖለቲካ ተዋናዮች መፈክሮቻቸውን በሚከተለው መልኩ እያስተጋቡ ይገኛሉ። 

 

አዲስ አበባ ....የፌደራል መንግሥቱና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከተማ ናት፤ ... የአዲስ አበቤ ከተማ ናት፤ ... በረራ የምትባል ንጉስ ዳዊት የቆረቆራት የአማራ ከተማ ናት፤ ... በኦሮሞ መሬት ላይ የተቆረቆረች የፊንፊኔ ከተማ ናት፤ ... የባልደራስ ፓርቲ ሊያስተዳድራት የሚገባት ከተማ ናት፤ ... የኦሮሚያ ቤተ መንግሥት መቀመጫ ከተማ ናት፤... ወዘተ። 

 

የፖለቲካ ተዋናዮቹ ውጥረትን ተከትሎ በርካታ ክሶችና ስሞታዎች ይደመጣሉ። ተቀናቃኞች “የከተማው አመራሮች የአዲስ አበባን ዲሞግራፊ ለመቀየር እየተንቀሳቀሱ ናቸው” ብለው ሲከሱ፤ በየከተማው ባለሥልጣናት ደግሞ “ከሌሎች ክልሎች ያልተፈቀደላቸው ሰዎች የአደባባይ በዓላትን እየተንተራሱ ወደ አዲስ አበባ በመጉረፍ ሥልጣን በኃይል ለመቆጣጠር እየሞከሩ ነው” ሲሉ በግላጭ ይወነጅላሉ። ጉዳዩ ከሚዲያ አጀንዳነት ያለፈ ነው። የአደባባይ ክብረ በዓል በመጣ ቁጥር ወደ አዲስ አበባ ከተማ “አትገቡም” ተብለው ወደመጡበት ስለሚመለሱም ሆነ ለቀናት መንገድ ላይ ስለሚጉላሉ ዜጎች በተደጋጋሚ ተዘግቧል። ጉዳዩ ፍጥነትና ትኩረት አግኝቶ መላ ካልተበጀለት ውሎ አድሮ የተወሳሰበ ችግር ለመፍጠሩ አሌ አይባልም። የዚህ አጭር ጽሁፍ ዓላማ የችግሩን ሥረመሰረት በመቃኘት ለምሁራዊ ውይይት ግብአት የሚሆን መነሻ ሃሳብን ለማቅረብ ነው። 

 

ተደናቂ ወይንስ ተነቃፊ አድራሻ?

እንደ ጥንታዊው ፕሌቶም ሆነ ዘመናዊዎቹ ፈላስፎች አገላለፅ የአንድ ሀገር ዋና ከተማን ፍጹም ተመራጭ (ideal location) የሚያደርገው በሃገሪቱ ዕምብርት (geographic center) ላይ ሲቆረቆር ነው። ለምን ቢሉ ዋና ከተማው ከሁሉም የሃገሪቱ ጫፍ በእኩል ርቀት ተደራሽና ለሁሉም ስፍራ የፍትሃዊነት ተምሳሌት ተደርጎ ስለሚወሰድ። በዚህ ረገድ አዲስ አበባ ተመራጭ ከሚባሉ የዓለማችን ጥቂት ሃገራት ተርታ ትሰለፋለች። የአዲስ አበባ የሰፈረችበት ከፍታ መጠን (2,355 ሜትር) ከአፍሪካ ዋና ከተሞች አንደኛ፣ ከዓለም ደግሞ በቦሊቪያ (ላ ፓዝ)፣ በኢኳዶር (ኹዊቶ)፣ እና በኮሎምቢያ (ቦጎታ) ብቻ ተበልጣ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ያደርጋታል። በጥቅሉ የኢትዮጵያ ምድረገጽ (physiography) መሃሉ ከፍታማ፣ ጥሩ ዝናብ ያለው፣ የአየሩ ሙቀት የተመጣጠነና ለኑሮ አመቺ ሲሆን ወደ በሁሉም አቅጣጫ ያለው ዳርቻ መሬት ደግሞ ከፍታው እያዘቀዘቀ፣ ዝናቡ እያጠረ፣ እና የአየር ሙቀቱ ከፍ ያለ የሚሄድ ነው። የአገሪቱ አግሮ ኤኮሎጂ ሥርጭትም ከከፍታ ሥርጭቱ ጋር የተጋመደ በመሆኑ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ አግሮ ኤኮሎጂያዊ አካፋይ ማማ (agroecological divide) ላይ የተቆናጠጠች ልዩ ከተማ ያደርጋታል።

 

በ1879 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ላይ እንዲቆረቆር ካስቻሉት መግፍዔዎች አንዱ ከሰሜናዊው የአክሱም ዋና ከተማ ዘመን ጀምሮ በጊዜ ሂደት የአገሪቱ ግዛት ዳር ድንበር በስተደቡብ አቅጣጫ የስፋት አድማሱን በመጨመሩ ነው። በሳይንሳዊ ቀመር የተመራ በሚመስል መልኩ የዋና ከተሞች አድራሻ በየወቅቱ የሚፈጠረውን የአገሪቱን ጂኦግራፊያዊ ማዕከላዊነት እያስጠበቁ ዘልቀዋል። ሥልታዊ በሆነው ደቡባዊ ሽግሽግ ሳቢያ አዲስ አበባ በዋና ከተማነት መቆርቆሩ ከፍተኛ አድናቆት ሊቸረው ይገባል። አንዳንድ አገራት ዋና ከተማቸው ጂኦግራፊያዊ መዛባት እንዳለበት ከረፈደ ተገንዝበው ነው ወደ ሌላ ማዕከላዊ ዋና ከተማ የተጓጓዙት። ለምሳሌ ናይጄሪያ (ከሌጎስ ወደ አቡጃ)፣ ብራዚል (ከ ሪዮ ዲ ጄኔሮ ወደ ብራሲሊያ)፤ ማይናማር (ከያንጉን ወደ ናይፒዳው)፣ ወዘተ መጥቀስ ይቻላል።

 

ሆኖም ላለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመታት የኢትዮጵያን ፖለቲካ ማዕበል ከዘወሩ ድርጅቶች ቀዳሚ የሆነው ህወሓት ሲመሰረት በማዕከላዊ (ገዢ) መንግሥት ላይ ያነሳው አንዱ ክስ እኛ የኢትዮጵያ ታሪክ የሥልጣኔ ምንጭና የመንግሥት የስበት ማዕከል የነበርን ሆኖ ሳለ (የአክሱምን ሥልጣኔ መሆኑ ነው) በተለይም ከአፄ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ በሸዋ ነገስታት ሴራ የሀገሪቱ የሥልጣን ዕምብርት ከመዳፋችን ተፈልቅቆ ወደ ዳር ተገፋን... የሚል ነው። ይህን ቅያሜና ቁጭት በመሰነቅ አስራ ሰባት ዓመታትን የፈጀ የትጥቅ ትግል አካሂዶ በውጤቱ ህወሓት ለሃያ ሰባት ዓመታት በአውራነት አዲስ አበባ ላይ ተቀምጦ ኢትዮጵያን መርቷል። በ2010 ዓ.ም በተፈጠረው አስገዳጅ የአመራር ለውጥ ሳቢያ ከሥልጣን ገሸሽ ሲደረግ “ወደ ዳር የመገፋቱ” (ማርጂናላይዝድ የመደረጉ) ቁጭት ነፍስ ዘርቶና በድጋሚ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ውሎ በቅርቡ ለተካሄደው የህወሓት ጦርነት የራሱን አስተዋፅዖ አበርክቷል። አዲስ አበባ የተቆረቆረበት ጂኦግራፊያዊ ኮኦርዲኔት አጠቃላይ የሃገሪቱን የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ሥርጭትን ያማከለ መሆኑን ማጠየቅ ልክ የተፈጥሮ ስበትን ሕግ አንደመቃረን ቢቆጠርም የአዲስ አበባ ዋና ከተማነት ዛሬም ጥያቄ ውስጥ እንዳለ ልብ ይሏል።

 

እድገቱ የጤና ነው?

አዲስ አበባ ከሁሉም የሃገሪቱ ክፍል በሚፈልቅ የባሕል፣ የቋንቋ፤ የሃይማኖት፤ የብሄር፤ የእድገት ደረጃ፣ ወዘተ የተዋቀረችና ህዝቡም ተከባብሮ “የጋራ ቤቴ” ብሎ የሚኖርባት ከተማ ናት። ከተማዋ የተላበሰችው ባሕላዊ ህብረቀለምን (cultural mosaic) ብቻ ሳይሆን ላቅ ያለውን ባሕላዊ ውህደትም (melting pot) ጭምር ነው። ማኅበራዊ-ባሕላዊ ብዝሃነትን ያበለጸጉ ከተሞች የሥራ ፈጠራን፣ የኢኮኖሚ እድገትን እና አገራዊ ትስስርን ያቀላጥፋሉ ይባላል። በዚህ ረገድ አዲስ አበባ ቀዳሚ ተጠቃሽ ናት።

 

ጠለቅ ብሎ ላስተዋለው ከበርካታ ኢትዮጵያ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው የህዝብና የካፒታል ፍልሰት መጠን ጤናማነት አይታይበትም። በፕሪሜት ሲቲ ሕግ መሰረት (The Law of the Primate City)  ታዳጊ አገራት ከሚገለጹባቸው ባህሪያት አንዱ የዋና ከተሞቻቸው ህዝብ ብዛት ከመጠን በላይ የገዘፈ ሆኖ የሌሎች አነስተኛ ከተሞችን ኗሪና ጥሪት ምጥጥ አድርጎ መና የሚያስቀር ነው። ይህ የሚሆነው የግዙፉ ከተማቸው የህዝብ ብዛት መጠን በሁለተኛ ደረጃ ከሚገኝ ከተማቸው ሲነፃፃር ከእጥፍ በላይ ሲሆን ነው። ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት ሀገር ብትሆንም አዲስ አበባ በአፍሪካ ግዙፍ ከሚባሉት የግብጹ ካይሮ እና የናይጂሪያው ሌጎስ ከተሞች የህዝብ ብዛት መጠን እጅግ ያነሰ ህዝብ ነው ያላትያላት። ሆኖም ግን የናይጄሪያው ሌጎስ ከተማ ከተከታዩ የካኖ ከተማ በ3.7 እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን የካይሮ ከተማ ህዝብ ደግሞ ከተከታዩ የጊዛ ከተማ ህዝብ በሁለት እጥፍ ይልቃል። የአዲስ አበባ ጉዳይ አጀብ ነው። ከተከታይዋ ድሬዳዋ ከተማ ኗሪ ከ13 እጥፍ በላይ መላቋ የሚያበስረው አዲስ አበባችን ጤናማ ያልሆነ የስበት ሀይል (center of gravity) የሚስተናገድባት ከተማ መሆኗን ነው። በሌላ አባባል አዲስ አበባ አምባገነንነትን ፀንሳ ለመውለድ አመቺ ትሆናለች ማለት ነው። የበርማዋ የነጻነት ተምሳሌቷን ኦን ሳን ሱ ቺ እንደምትለው “በዋና ከተማ ኃይል ሲከማች ለአምባገነነት ንጋት፤ ለዲሞክራሲያዊ መርሆ ደግሞ ምሽት ይሆናል”።

 

ሰው ካልቸገረው አገሩን አይለቅም።

ለገበሬ መሬቱ ሁለ ነገሩ ነው። መሬቱን ጥሎ ወደ ከተማ ከተሰደደ ችግሩ ከፍቷል ማለት ነው። 

 

- በህልውና ዋስትና እጦት፡ አዲስ አበባ የበርካታ ችግሮች ቋት ብትሆንም በአንፃራዊነት ከሌሎች የሃገሪቱ ከተሞች “የተሻለ” የኑሮ ዋስትና አላት ተብሎ ይታመናል። ከተማይቱ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የዲፕሎማቲክ መናኸሪያ በመሆኗ እና ኗሪዎቿ ከበርካታ ብሄር ብሄረሰብ የተውጣጡ በመሆኑ የተሻለ የኑሮ ዋስትና ትላበሳለች ተብሎ ስለሚታመን ይሆናል። ከአዲስ አበባ ርቀው ሲጓዙ የህግ የበላይነትና ሰብአዊ መብቶች እየሳሱ፤ በምትኩ ደግሞ የባለሥልጣናቱ አይነኬነት ይገዝፋል። የግለሰብ ይዞታን መንጠቅና ከቆዬ ማፈናቀል እንደ ቁብ አይቆጠርም። “ያልተገላበጠ ያራል” ይባላል እና ተጣጥሮ ሃብትን ማፍራት የቻለ ግለሰብ ሃብት ባካበተበት ሥፍራ ኢንቨስት አድርጎ አካባቢውን ከማልማትና የሥራ ዕድል ከመፍጠር ይልቅ ገንዘቡን ቋጥሮ “ቢያንስ መንግሥት አለባት” ወደሚባልላት አዲስ አበባ ከተማ ይመጣል፣ አሊያም ለልጆቹ የወደፊት መኖሪያ ቤት ያዘጋጅባታል። ሌላው ይቅርና የዳያስፖራው ማኅበረሰብ እንኳ ከተለያየ ሃገራት ይዞ የሚመለሰውን ጥሪት በገፍ የሚያፈሰው ባብዛኛው በአዲስ አበባ ለመሆኑ ነጋሪ አያሻም። 

 

- በምግብ ዋስትና እጦት፡ በተለይም በደጋው ክፍል ከትውልድ ትውልድ በውርስ የሚገኘው የእርሻ መሬት መጠን እየተበጣጠሰ እና እየጠበበ መጥቶ በርካታ ገበሬዎች ቤተሰባቸውን መመገብ እያዳገታቸው የሴፍቲ ኔት ተደጓሚ ሆነዋል። መሬት አልባ የሆኑ ቤተሰቦች ቁጥር ሁሌም እያደገ ነው። በሃገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ አንዳንድ አካባቢዎች ግለሰቦች የሚያርሷቸው ማሳዎች 'ነፍስን ከስጋ ለማቆየት ያህል የሚታረሱ ትንንሽ ማሳዎች ሲሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ የኢትዮጵያ የግብርና ሥርዐት ከአነስተኛ ይዞታ ወደ ደቂቅ ይዞታነት ተለውጧል ብሎ ተመራማሪው ደሳለኝ ራህመቶ በ1994 (እ.ኤ.አ.) ከመሰከረ እንኳ ወደ ሶስት አስርት ዓመታት ተቆጥሯል። ባንዳንድ ስፍራዎች የመሬቱ ስፋት በቂ ቢሆን እንኳ ያላንዳች እፎይታ ከዓመት ዓመት ስለሚታረስ ለምነቱ የተሟጠጠ ነው። የማዳበሪያ ግብአቱ ኢምንት መሆኑ ሳያንስ በአየር ንብረት መዛባት ሳቢያ ለተደጋጋሚ ድርቅና ረሃብ ስለሚጋለጥ ወደ ከተሞች ለመሰደድ ይገደዳል፤ አዲስ አበባ ደግሞ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል።

 

- በነፃነት የመዘዋወር እጦት፡ ቀደም ባሉ መንግሥታት በድርቅ፤ በምርታማነት እጥረት፣ በመሬት ጥበት እና በምግብ ዋስትና እጦት ሳቢያ ገበሬዎች ከአዲስ አበባ ይልቅ ወደ ተለያዮ የሃገሪቱ ለም አካባቢዎች ሄደው የግብርና ሕይወታቸውን “ሀ” ብለው ይጀምሩ ነበር። በራስ አነሳሽነትም ሆነ በመንግሥት አነሳሽነት (በውዴታ ወይንም በግዴታ) የህዝብ ጫና ወደሌለባቸው በአገሪቱ ምዕራባዊ አካባቢዎች ይሰፍሩ ነበር። የመሬት ጥበት ያለባቸው የደቡብ መሃል ኢትዮጵያ ገበሬዎች ይከተሉት የነበረው ዘይቤ ደግሞ ይለያል። ለምሳሌ ከከምባታ እና ሃዲያ አካባቢ ያሉ ገበሬዎች ቀያቸውን ሳይለቁ በተመላላሽነት (seasonal migration) በመንግሥት እርሻዎች (ለምሳሌ በወንጂ እና በመተሃራ ስኳር ፋብሪካዎች) ተቀጥረው እየሰሩ ወደ ቀያቸው ተመልሰው የቤተሰቦቻቸውን ምግብ ዋስትና ያስጠብቁ ነበር። አሁን ዘይቤው ተቀይሯል። ወጣት ገበሬዎች ከቀያቸው ሲፈናቀሉ መዳረሻቸውን የሚያደርጉት ከፊሉ ወደ አዲስ አበባ ነው። ቀሪው ወጣት በርካታ ድንበሮችን እያቆራረጠ ወደ ደቡብ አፍሪካ መጓዝ ከጀመረ አሥርት ዓመታት ተቆጥረዋል። ዜጎች ለሕይወት አስጊ በሆነ አስቸጋሪ ባህርና በረሃን አቋርጠው ወደ ሌሎች ሃገራት ለመድረስ የሚጓዙበት አንዱ ምክንያት በሀገር ውስጥ በነፃነት ተዘዋውሮ ሃብት ማፍራት ባለመቻላቸው ነው ብሎ ለመገመት አልበርት አንስታይንን መሆን አያሻም። 

 

ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ መሥራት ለእድገት ፈር ቀዳጅ ነው። ግለሰቦች ከተወለዱበት ሥፍራ ርቀው ወደ አዲስ ስፍራ ሄደው ስራ ሲጀምሩ ከነባሩ ኗሪ ይልቅ ሥራ የመፍጠር (entrepreneurship) እና በፍጥነት የማደግ ብቃታቸው እጅግ ይልቃል። በውጤቱም አካባቢያቸውንና ሀገርን ያሳድጋሉ። ዛሬ ዛሬ ዜጎች በነጻነት ከትውልድ ሥፍራቸው ርቀው ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው በነፃነት የመኖርም ሆነ ሃብት የማካበት ዕድላቸው የሚያወላዳ አይደለም። 

 

የአካባቢ ቀውሱ።

አዲስ አበባ ወደ ውጪም ሆነ ወደ ውስጥ በመስፋፋቷ መተናፈስ እየከበዳት ነው። የትራፊክ መጨናነቁ የለት ተለት ፈተና ነው። ተሽከርካሪዎች ቆም-ሄድ እያሉ እያዘገሙ እንዲጓዙ ስለሚገደዱ ወደ ከባቢ አየር የሚለቁት የብክለት የዜጎች እና የአካባቢና ጤንነትን አደጋ ላይ ጥለውታል። የአየር ብክለት “ድምፅ አልባው ገዳይ” ይባል የለ? ከፍተኛ የህዝብ መጨናነቅ በአዕምሮ ላይ የሚያስከትለው ቀውስም መጠኑ አይታውቅ እንጂ አስከፊነቱ እሙን ነው። 

 

በሌላ በኩል በፍጥነት እየተመነደገ ያለውን የህዝብን ፍላጎት ለማሟላት ሲባል በአካባቢው ከርሰ ምድር ውሃ ሃብት ላይ የሚፈጥረው ጫና ከፍተኛ ነው። አዲስ አበባ ስትስፋፋ ምርታማ የሆኑ አጎራባች የእርሻ መሬቶች ለቤት መስሪያ እና ለግንባታ የሚውል ድንጋይና አሸዋ ማምረቻነት ይውላሉ። ይህ ብቻ አይደለም። ከበርካታ ህዝብ እና ከኢንዱስትሪ የሚመነጨው ፍሳሽና ብካይ ኬሚካል እየጎዳ ያለው ከተሜውን ብቻ አይደለም። የአካባቢውን ማኅበረሰብ ጭምር ይጎዳል። ለምሳሌ በመርዛማ ዝቃጭ ሳቢያ የአቃቂ ወንዝና ገባሮቹ እንዲሁም የቆቃ ሃይቅ በወንዙ የታችኛው ክፍል የሚገኙ ኅብረተሰቦችን እና እንስሶችን ጤና አቃውሶ ነበር። የእርሻ መሬቶችም ተመርዘው እንደነበርም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። የከተማ እድገት ዋጋው የሚተመነው በአየር እና በውሃ ብክለት ሰለባ በሆነው የከተማው ዙሪያ ማኅበረሰብ ብዛት መጠን ነው ይባላል።

 

አዲስ አበባን ሲያስነጥሳት የክልል ከተሞች በሳምባ ምች ይጠቃሉ። 

ተገፍቶም (push factor) ይሁን ተስቦ (pull factor) ወደ አዲስ አበባ የሚነጉደው ዜጋ በመሬት፤ በመኖሪያ ቤትና በንግድ ቤት ግዢ ላይ ይጫረታል። በውጤቱም ከተማይቱን ለማያባራ የዋጋ ግሽበት ይዳርጋታል። በቤት ገበያ ሳቢያ የሚከሰት የግሽበት ትኩሳት ደግሞ በቀላሉ አይበርድም። multiplier effect አለው። በ2008 (እ.ኤ.አ) የዓለም ፋይናንሻል ገበያ ቀውስ ከመኖሪያ ቤት ዋጋ ግሽበት ሳቢያ የተከሰተ እንደነበር ማስታወስ ይቻላል። የአዲስ አበባው የቤት ገበያ ግሽበትም ወደ ምግብ ነክ ሸቀጦች እና የኢንዱስትሪ ምርትና የአገልግሎት ዘርፍ ተዛምቷል። እንደ ሰደድ እሳት በመላው አገሪቱ ተቀጣጥሏል። ቅጥ አምባሩ ለጠፋው ግሽበት አስረጅ የሚሆነው በተለምዶ “የረከቦት” ቡናን ዋጋ በመቃኘት ነው። የአንድ ሲኒ ቡና ዋጋ በአዲስ አበባ፤ በአርባ ምንጭ፤ በኮንሶ፤ በጂንካ ጎዳኖች መሃል ምንም የዋጋ ለውጥ ልዩነት የላቸውም። በአዲስ አበባ የሚፈጠር ጉድፍ በአዲስ አበባ ተወስኖ የሚቀር አይደለምና።

 

ሁሉም መንገዶች ወደ አዲስ አበባ ያመራሉ።

ወንዞች መዳረሻቸውን ከውቅያኖስ እንደሚያደርጉ ሁሉ መንገዶችም መዳረሻቸውን ከዋና ከተማ ያደርጋሉ ይባላል። እንዲሁም ዋና ከተማ ልክ እንደ ልብ ህይወትን ለመላ የአገር ክፍል በደምስር የሚረጭ ነው ይባላል። ከተሞች ደሴት አይደሉም። ከከባቢያቸው ጋር ነፃ የሆነ መስተጋብር (open system) አላቸው። ከውጭ ወደ ውስጥ የሚገባ (input) አለ፤ ከውስጥ ወደ ውጪ የሚወጣ (output) አለ። መስተጋብሩ እንዲዘልቅ ገቢና ወጪው ሊመጣጠን ግድ ይላል። አሁን ባለው ሁኔታ በርካታ ዜጋ ከሁሉም አቅጣጫ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ይገባል እንጂ በኑሮ ውድነቱ፣ በትራፊክ መጨናነቁ፣ በመኖሪያ ቤት እጥረቱ ወዘተ ሳቢያ ተማርሮ ወይንም ተገፍቶ አዲስ አበባን ለቆ ሲወጣ እምብዛም አይታይም፡ መግቢያ እንጂ የመውጫ መንገድ የሌለው one way street ይመስል። ይባስ ብሎ ተጨማሪ ዜጋ ወደ ከተማዋ በገፍ ይፈሳል። “የበላችው ያቅራታል፣ በላይ በላይ ያጎርሳታል” እንዲሉ። ባጭሩ የአዲስ አበባ ከተማ ሥርዓት ሚዛን የተዛባ ነው። 

 

እንደ ወትሮው ቢሆን በርካታ የአዲስ አበባ ወጣት ከሁለተኛ ደረጃም ሲያጠናቅቅም ሆነ ከዩኒቨርሲቲ ሲመረቅ በመረጠውና እጣ በደረሰው ክፍለ ሃገር ነበር ህይወቱን የሚመሰርተው። በንጉሱ ዘመን ሰፊ የሥራ ዕድል በምስራቅ ኢትዮጵያ ተፈጥሮ በርካታ ወጣቶች ወደ ድሬዳዋ እና ሐረር ከተሞች ተጉዘው ኖሮ “እልም አለ ባቡሩ፣ ወጣት ይዞ በሙሉ” ተብሎ ተዘፍኖላቸው ነበር ይባላል። እያደገ የሚመጣውን የኗሪ ክምችት ለማስተናገድ አዲስ አበባ ራሷን እንደ ላስቲክ እየለጠጠች ለተወሰኑ ጊዜያት ልትዘልቅ ትችል ይሆናል። ችግሩ ግን ተለጣጭ ነገር ሁሌም ገደብ አለው፣ elastic limit እንደሚባለው። የጊዜ ጉዳይ እንጂ አዲስ አበባ ወደ ውስጥም (implosion) ወደ ውጪም (explosion) የመፈንዳት አደጋ ተጋርጦባታል ቢባል ጨለምተኝነት አያሰኝም። 

 

እነሆ ጥቆማ።

ከተሞች በተፈጥሯቸው በውስብስብ ችግሮች የተተበተቡ ናቸው። በታዳጊ አገራት የከተሞች ችግር መጠን የባሰ ቢሆንም የአዲስ አበባ ከተማ ችግር ግን የትየለሌ ነው። የማይታወቀው መልስ “መቼ” ለሚባል ጥያቄ እንጂ በሆነ ሰዓት የመፈንዳቱ ጉዳይ አይቀሬ ነው። በርካቶች የሚስማሙበት መፍትሄ፡ በነጻነት ተዘዋውሮ የመሥራት ዋስትና፣ የዜጎች ደህንነት ዋስትና፤ እርሻ ምርታማነት ማዘመን፣ ወዘተ ሳይዘነጋ በአዲስ አበባ ላይ እያገጠጠ ለመጣው ችግር ተጨማሪ የማስተንፈሻ ቫልቭ ማስፈለጉ አሌ አይባልም። አንድ አይን ያለው በእሳት አይጫወትም። ችግሩ እሳቱ የፖለቲካ ስለሆነ  ልራቅህ ቢሉት የሚከስም አይደለም። ስለዚህ ሌላ መላ መሻት ግድ ይላል። 

 

አሁን በኢትዮጵያ ባለው አካባቢያዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ታሪካዊ ሁኔታ አንድ ዋና ከተማ ብቻ ሁሉን ጠቅሎ መያዙ ችግሩን እያባባሰው ይሄዳል። እንደውም ጦሱ ለመላ አገሪቱ ይተርፋል። ይህ ጽሑፍ በነኚህ ሥጋት ላይ ተመርኩዞ የሁለት ዋና ከተሞች አስፈላጊነትን እንደመፍትሄ ይጠቁማል። ሃሳቡ አዲስ አይደለም። በተለያዩ አገራት ተተግብሯል፡ ደቡብ አፍሪካ (ፕሪቶሪያ እና ኬፕታውን)፣ ቦሊቪያ (ሱክሬ እና ላፓዝ)፣ ኔዘርላንድስ (አምስተርዳም እና ዘ ሄግ) መጥቀስ ይቻላል። ከተጠቀሱት ሃገራት መማር የሚቻለው ሁለተኛ ዋና ከተማን ከነባር ከተሞች መሃል አወዳድሮ ማጨት ወጪውንና የሚፈጀውን ጊዜ እጅግ እንደሚቀንሰው ነው። ግብፅም ዋና ከተማዋ ካይሮ ዕጅግ በመጨናነቁ ሳቢያ ብዙም ሳይርቅ (ወደ 45 ኪሜ ገደማ) በስተምዕራብ በኩል ገና ኦፊሴላዊ ስም ያልወጣለት (“ግብፅ” ተብሎ ሊጠራ እንደሚችል ጭምጭምታ አለ) አዲስ ዋና ከተማ መገንባት ከጀመረች ወደ ስምንት ዓመታት ተቆጥሯል። አርባ ቢሊዮን ዶላር የፈጃል የተባለለት አዲስ የዋና ከተማ ግንባታ ፕሮጀችት በኮቪድ ምክንያት ቢጓተትም እስካሁን አስራ አራት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቿ ወደ አዲሱ ከተማ ተጠናቀው ገብተዋል።  

 

እርግጥ ነው አዲስ ዋና ከተማን መመስረት ከፍተኛ ጉልበት፣ የሀገር ሃብት፣ እና የፖለቲካ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል። ሆኖም ግን አሁን ካንዣበበውና  አደጋ አንፃር መንትያ ዋና ከተማ በኢትዮጵያ ቢመሰረት በርካታ ትሩፋቶችን መቋደስ ይቻላል።

 

አዲስ አበባ ላይ የተከማቸውን ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ሃይልን ለማመጣጠን ይረዳል። በተለይም “አዲስ አበባን በባለቤትነት መያዝ ባቋራጭ መላው ሃገሪቱን ጠቅሎ መያዝ ያስችላል” ብለው ለሚያስቡ የፖለቲካ ቡድኖች ልጓም ያበጃል።

በአዲስ አበባ ላይ ተከማችቶ ለመተናፈስ የተቸገረውን ኤኮኖሚ በሁለተኛው ዋና ከተማ አማካይነት መተንፈሻ ቀዳዳ ይፈጥርለታል። ያልተማከለ የኢኮኖሚ ክምችት ደግሞ እድገትን ያሳልጣል። 

ከአዲስ አበባ ከተማ በተጨማሪ ሌላ ባሕላዊ ብዝሃነትን የተገናጸፈ ትልቅ የፌደራል ከተማ ስለሚፈጠር የህዝብ ለህዝብ ቁርኝትና አንድነት መሰረቱ ይጎለብታል፤ ውጥረቱ ረገብ እንዲል አስተዋፅዖ ያበረክታል። 

አዲስ አበባ ላይ በቅጥ አልባነት የተከማቸው የመሰረተ ልማትና ተሽከርካሪ ወደ ሁለት ዋና ከተሞች ይሸጋሸግና ፍትሃዊ ሥርጭትን ያላብሳል የትራፊክ መጨናነቅን ያስወግዳል።

ከፍተኛ የተፈጥሮ አደጋ ቢከሰት እንኳ (አዲስ አበባ ከምስራቅ አፍሪካ ሰምጥ ሸለቆ በቅርብ ርቀት በመገኘቷ ሳቢያ ለመሬት መንቀጥቀጥ ያለውን ተጋላጭነት ልብ ይሏል) መንግሥት በመንትያው ዋና ከተማ አመራሩን ሊያስቀጥል ይችላል። 

 

Email፡ daniel.kassahun@gmail.com

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/182921

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...