Thursday, May 11, 2023

የጠቅላይ ሚንስትሩ የቤተመንግስት ፕሮጀክት ለሶስት ተቋራጮች ተሰጠ (ዋዜማ)

የጠቅላይ ሚንስትሩ የቤተመንግስት ፕሮጀክት ለሶስት ተቋራጮች ተሰጠ (ዋዜማ)
የ”ጫካ” ፕሮጀክት የሚል ስያሜ ላለው እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርበት ለሚከታተሉት የአዲስ ቤተ መንግስት ግንባታ ተጨማሪ ሶስት ተቋራጮች መቀጠራቸውን ዋዜማ ከሁነኛ ምንጮቿ ሰምታለች።

ከቤተ መንግስት በተጨማሪ ፣ የቅንጡ መኖርያ እና መዝናኛ መንደርን የሚያካትተው ይህ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካ ክፍለ ከተማ ፣ የካ ተራራን ታኮ የሚሰራው ፕሮጀክት እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በግዙፍነቱ የሚመዘገብ መሆኑ ሲነገርለት የቆየ ነው።

503 ሄክታር መሬት ላይ በሚያርፈው በዚህ ፕሮክጀክት እስካሁን ድረስ በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የ29 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ እየተሰራ ሲሆን አብዛኛው የመንገድ ስራ ወደ መጠናቀቁ ተቃርቧል።

የ”ጫካ” የሚል ስያሜ ባለው ፕሮጀክት ውስጥ ሶስት ሰው ሰራሽ ሀይቆች የሚኖሩ ሲሆን ፣ እነዚህ ሰው ሰራሽ ሀይቆች ኢ ቶሎ በተባለ ተቋራጭ እየተሰሩ መሆናቸውን መረዳት ችለናል። ከሶስቱ ሀይቆች ውስጥም የአንዱ ሀይቅ የመሰረት ስራ መጠናቀቁን ከምንጮቻችን አረጋግጠናል።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ደግሞ በዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት ውስጥ የሚሳተፉ ተጨማሪ ሶስት ተቋራጮች መቀጠራቸውን ዋዜማ ሰምታለች።

መንግስታዊው የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን(ኢኮስኮ) የዋናውን ቤተ መንግስት ግንባታ እንዲያከናውን ውል ተሰጥቶታል። የቻይናው መንግስታዊ የኮንስትራክሽን ኩባንያ ሲሲሲሲ ደግሞ በፕሮጀክቱ የሚካተተውን የቅንጡ ሆቴል ግንባታን ያከናውናል። ሆቴሉም “ስካይ ቪው” የሚል ስያሜ እንደሚኖረው ተነግሯል። የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ደግሞ ከቤተ መንግስቱ እስከ የካ አባዶ የሚገነባውን መንገድ በተቋራጭነት ይሰራል።

ይህ ግዙፍ ግንባታ በቀጣይ ተጨማሪ ተቋራጮች ይሳተፉበት እንደሁ ማረጋገጥ አልቻልንም።

የ”ጫካ” ፕሮጀክት ወጪ በትክክል ባይታወቅም ፣ 49 ቢሊየን ብር እንደሚያወጣ በስፋት ሲነገር ነበር። ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከወራት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ፕሮጀክቱ እንደሚባለው የ49 ቢሊየን ብር ብቻ ሳይሆን ከ300 እስከ 400 ቢሊየን ብር የሚያወጣ የ”ስማርት ሲቲ” ልማት አንዱ አካል ነው ሲሉ ማብራሪያ መስጠ ታቸው ይታወሳል።

የምዕራቡ ዓለም የዲፕሎማቲክ ምንጮች በበኩላቸው የጫካ ፕሮጀክት አሁን ባለው የምንዛሪ ተመን ከ850 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጣ መሆኑን እየተናገሩ ነው።

የገንዘቡን ምንጭ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍንጭ አልሰጡም ። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርብ ክትትል የሚሰራው ይህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር የቅደም ተከተል ጥያቄ በተደጋጋሚ ሲነሳበት ቆይቷል።

ለግንባታው በአቅራቢያው የነበሩ ነዋሪዎች እንዲነሱ የተደረጉ ሲሆን ፣ በስፍራው መንግስት የሚያስቀምጠውን የቅንጡ መኖርያዎች ዲዛይንን አሟልተው ግንባታ ማከናወን የሚችሉ ግለሰቦች ብቻ መኖርያ ቤት መስራት እንደሚችሉ ተገልጿል።

የጫካው ፕሮጀከት ከዚህም ሲያልፍ በሚሰራበት የየካ ተራራ አካባቢ በአቅራቢያ ካለችው እንቁ ልደታ ቤተ ክርስቲያን ጋር የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ክርክር ውስጥ ገብቶ ፍርድ ቤት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ፈርዷል።
https://amharic-zehabesha.com/archives/182412

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...