Monday, May 22, 2023

ቀጥ ብሎ ለመቆም የለገማችሁ የዘመኑ ካህናት ሆይ! ሰማእታት አባቶቻችን ከሰማይ ቤት እያዘኑ ነው!
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

የአቡነ ጴጥሮስን፣ የአቡነ ሚካኤልን፣ የአባ ገብረየሱስን፣ የአቡነ ቴዎፍሎስን፣ የመላከ ብርሃን አድማሱንና የሌሎችንም ሰማእታት.መስቀል ጨብጣችሁ በቤተክርስቲያኗ ቁማር በመጫወት ላይ ታሉት ወሮበሎች ትእዛዝ ስትቀበሉ ትንሽ እንኳ እግዚአብሔርን አትፈሩም ወይ?

የዘመኑ ካህናት ሆይ! እንደምታውቁት ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ከቱርክ፣ ከመጀመርያውም ሆነ ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ዘመን የከፋ ነው፡፡ በአምስት ሺ ዘመኗ ኢትዮጵያ ወራሪውን ሁሉ ያንበረከከችው በካህናት ተጋድሎና ሕዝብ አንቂነት ነው፡፡ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል እንኳን ሕዝባቸው የአገሪቱ ሜዳ፣ ተራራ፣ ሸለቆው ለወራሪ እንዳይገዛ ገዝተው እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ተወግረው መስዋእት የሆኑት የጨበጡት መስቀልና የደፉት ቆብ ስለሚያዝዝ ነው፡፡

ፋሽሽት የደብረ ሊባኖስን መነኩሳት ሲጨፈጭፍ እነ አባ ገብረየሱስ ታጥቀው መፋለም የጀመሩት መስቀላቸውና ቆባቸው ሳጥናኤልን ወይም ዲያብሎስን መፋለም እንዳለባቸው ስለሚያዝዝ ነው፡፡ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ በአምስቱ ዘመን ተጋድሎ ተቆላ እስከ ደጋ በሌጣ እግራቸው እየተንከራተቱ ሕዝብን ያነቁትና እንደ አንበሳ ያገሱ የነበሩ የጎበዝ አልቆችን እያስተባበሩና የተጣሉትን እያስታረቁ ለአምስት አመታት የታገሉትን አገርን ሊወስድ፣ ሃይማኖትንና ባህልን ሊያጠፋ የመጣን ፋሽሽት መፋለም ቅድስና መሆኑን የጨበጡት መስቀል ስለነገራቸው ነው፡፡ ከሃምሳ አመታት በፊትም አቡነ ቴዎፍሎስ በኮሚኒስት ካድሬዎች ታንቀው ሰማእት የሆኑት ቤተክርስትያኗን አሳልፈው እንዳይሰጡ የጨበጡት መስቀለና የደፉት ቆብ ስላስገደዳቸው ነው፡፡

እናንተ የእነሱን መስቀል የጨበጣችሁትና በእነሱ መንበር የተቀመጣችሁት ካህናት ከጣሊያን እንኳ በከፋ መንገድ በጭራቆች ምእመናን እየታረዱ ሲጎተቱ፣ ከአምልኮ ቦታ በእሳት ሲቃጠሉ፣ ቤተክርስትያኖች ሲቃጠሉ፣ ቀሳውስት እየተወገሩ ሲገደሉ፣ ሰዎች ዘራቸው እየተመረጠ አገር አልባ ሲሆኑ ምን እየሰራችሁ ነው? ቤተክርስቲያኗን ሊያጠፉ የተነሱ ይሁዳዎች የቤተክርስትያኗን ዶግማና ቀኖና እያፈረሳችሁ በአመንዝራዎችና በነፈስ ገዳዮች እንድትሞሏት ሲያስገድዷችሁ ምን እየመለሳችሁ ነው?

መጽሐፉ እስተንፋስ ያለው ሁሉ እንዲተነፍስ ያዝዛል፡፡ ዳሩ ግን እናንተ ይህንን የመጽሐፍ ቃል በመሻር ደመወዝ ከፋዮቻችሁ ምዕመናን ዘራቸው እየተመረጠ ሲታረዱና አገር አልባ ሲሆኑ ያላዬ ያልሰማ መስላችሁ ባቄላ እንደ ዋጠ አውራ ዶሮ ጪጪ ብላችኋል፡፡ ልብ በሉ ምዕመናን ተጨፍጭፈውና ተሰደው ታለቁ ደመውዝ የሚቆርጥ አስራት ከፋይም ይጠፋል፡፡

 

ለክርስትናና ለፍትህ ሲሉ  ተዘቅዝቀው የታረዱትንና የተሰቃዩትን ሐዋርያት ስም ጴጥሮስን፣ ጳውሎስን፣ ማርቆስን፣ ሉቃስን፣ ዮሐንስን፣ ማትያስን፣ ገብርዔልን፣ ቀውስጦስን፣ ገሪማን ወዘተርፈ ወርሳችሁ እናንተ እነሱን ታሰቃዩአቸውና ታረዷቸው ጪራቆች ጋር ቆማችሁ ስትታዘዟቸው ይታያል፡፡ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካዔል የጨበጡትን መቋሚያ እየጎተታችሁ ተሞሶሎኒን የአላማ ዲቃላዎች ቢሮ ስትንከረፈፉ ይታያል፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ አቡነ ጎርጎሪዎስና መላከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ የጣፏችውን መጽሐፍት እያገላበጣችሁና በቆሙበት መንበር ተገትራችሁ በጨበጣችሁት መስቀል የተሰቀለውን የክርስቶስ ሳይሆን የከሀዲ ገዥዎችን ቀጭን ትእዛዝ ስትፈጥሙ ይስተዋላል፡፡

 

ኦርቶዶክስ ማለት ቀጥ ያለ ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ጨብጣችሁ፣ መንኩሰ ሞት የሚለውን ቆብ ደፍታችሁ፣ ምዕመናን በነቂስ ወጥቶ አየደገፋችሁና ሞት መቼም እንደማይቀር እያወቃቸው ቀጥ ብሎ መቆም ምነው ተሳናችሁ? ተመቃብር እንደ በቀለ ውልክፋ ምነው ልፍስፍስ አላችሁ?

 

በስግብግብነት፣ በራስ ወዳድነት፣ በሆዳምነትና በፍርሃት ባህር ውስጥ ተውጣችሁ የሚቀልቧችሁን በጎቻችሁን ለቀበሮ  ገብራችሁ በቁንጣን፣ በልብ፣ በኩላሊት፣ በጉበትና በሌሎችም  በሽታዎች ወደ እማይቀረው ዓለም ስትሄዱ የሰማዩን ዳኛ ምን ሰርተን መጣን ትሉት ይሆን?

 

“ቤተክርስትያን እየተቀጣለ ምእመናን ሲደደዱና በገጀራ ሲቀሉ እናንተ እነሱን ለማዳን እንደ ጳውሎስና ጴጥሮስ መስዋእት እንድትሆኑ ቤተክርስትያን አደራ ስትጥልባችሁ ድምጣችሁን አጥፍታችሁ ክትፏችሁንና ቁርጣችሁን ትዝቁ ነበር” ብሎ መለኮት ሲያፋጥጣችሁ ምን ልትመልሱ ይሆን?

 

“ልጃገረዶች ከትምህርት ቤት ተጠልፈው ሲሰቃዩና ወላጆቻቸውም የምድር ሲዖል ሲኖሩ እናንተ እነሱ ለታቦት ያስገቡትን አስራት እየዋጣችሁ በምቾት ኑሯችሁን ትቀጩ ነበር” ብሎ ተሚዛን ሲያስቀምጣችሁ ምን ይውጣችሁ ይሆን?

 

ሥራ የሌለው እምነት የሞተ ነው የሚለውን ጠቅሶ “የጨበጣችሁትን መስቀል፣ የደፋችሁትን ቆብ፣ የደረባችሁት ካባና የተሸከማችሁትን የሐዋርያትና የቅዱሳን ስም በምን ሥራ ተረጎማችሁት” ብሎ ቢጠይቃችሁ በምን ግብር ተረጎምነው ልትሉት ይሆን?

 

ታሪክስ “በእናንተ ዘመን ቤተክርስትያን ስትከፋፈል፣ ምእመናን እንደ በግ በካራ ሲታረዱ፣ የክርስቶስ ማደሪያ ቤተክርስትያኖች ባለቤት እንዳጣ ጫካ በአሪዎሶች ሲቃጠሉ እናንተ ፓትሪያሪኮችና  ጳጳሳት ምንም ሳታደርጉ ጪጪ ብላችሁ ሆዳቸውን እየሞላችሁ በምእመናን አስራት በተገነባ የአማረ ህንፃ ውስጥ ትንቡክ በሚል አልጋ ስትንፈላሰሱ ታድሩ ነበር” እያለ በብዕር ጦር እየወጋችሁ ሲኖር ህመሙን እንዴት ትችሉት ይሆን?

 

የዘመኑ ካህናት ሆይ! የአቡነ ጴጥሮስን፣ የአቡነ ሚካኤልን፣ የአባ ገብረየሱስን፣ የአቡነ ቴዎፍሎስን፣ የመላከ ብርሃን አድማሱንና የሌሎችንም ሰማእታት.መስቀል ጨበጣችሁ በቤተክርስቲያኗ ቁማር በመጫወት ላይ ካሉት ወሮበሎች ትእዛዝ ስትቀበሉ ትንሽ እንኳ እግዚአብሔርን አትፈሩም ወይ? ህሊናችሁን ትንሽም አይቆጠቁጠው ወይ? መስቀል ጨብጣችሁና ቆብ ደፍታችሁ ምዕመናን ፊት ስትቀርቡስ ትንሽ አታፍሩም ወይ? እግዚኦ!

 

ግንቦት ሁለት ሺ አስራ አምስት ዓ.ም.

 

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/182797

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...